የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ፍንጮች፣ ምስሎች፣ ምሳሌዎች፡ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ማጥኛ መንገድ



2ኛ ሩብ ዓመት 2025


ግንቦት 30 - ሰኔ 6

11ኛ ትምህርት

Jun 7 - 13




ሩት እና አስቴር



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሩት 1:1– 5፣ ሩት 2:5–20፣ ኢዮ. 1:6–11፣ ማቴ. 4:8, 9፣ አስቴ. 3:1–14፣ ራእ. 12:14–17።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ንግሥት አስቴር በአደባባዩ ላይ ቆማ ሲያያት ደስ አለው፤ በእጁ የያዘውን የወርቅ ዘንግ ዘረጋላት፤ አስቴርም ቀረብ ብላ የዘንጉን ጫፍ ነካች።” (አስቴር 5፡2)።

በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የመጨረሻዎቹን ቀናት ክስተቶች የሚገልጡ ታሪኮችን ማሰሳችንን እንቀጥላለን። እግዚአብሔር እውነተኛ የሕይወት ክስተቶችንና ሕዝቦችን እየተጠቀመ ነገሮችን ከእርሱ እይታ አኳያ መመልከት እንድንችል ይረዳናል። እንዲሁም የገዛ እምነታችንን የሚያጠነክሩልንን ኋላ ላይ ፍጻሜ የሚያገኙ ትንቢቶችን እንዴት መፍታት እንደምንችል ማስተዋል ይሰጠናል።

ትኩረታችን በሁለት ወሳኝ እንስቶች ዙሪያ የሚያጠነጥን ሲሆን፣ የእነርሱ ታሪክ ስፍር ቁጥር የሌለውን ትውልድ ልብ ነክቷል—ሩት እና አስቴር። ሩት ከንብረት የተነቀለች ምስኪን መበለት ስትሆን፣ ነገር ግን ደግ ከሆነው ቦዔዝ ጋር ከተገናኘችና እርሱ ከተቤዣት በኋላ ተስፋ የኖራት ሴት ናት። ትዳራቸው ክርስቶስ ለእኛ ያለውን ፍቅር የሚያንጸባርቅ፣ የሚያስቀና እና ትምህርት ሰጭ የፍቅር ታሪክ ነው። ሌላኛዋ ወጣት ልጃገረድ አስቴር—በባዕድ ምድር የምትኖር፣ ሕዝቧን ለማጥፋት የተሸረበን የጠላት ሴራ በንቃት ያስተዋለችና እነዚህን ወገኖቿን ለመታደግ በተለየ አቅጣጫ በድራማው መድረክ ራሷን የምታገኝ ናት።

ሴት በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ዓይነተኛ ምሳሌ መሆኗ እሙን ነው። የሕይወታቸው ወርድና ስፋት በእግዚአብሔር ቃል ሕያው የሆነውን የእነዚህን እንስቶች ማንነት ከመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ እየጨለፍን ከእነርሱ ተሞክሮ የምናገኘውን ትምህርት ለመቅሰም እንሞክር።

ሰኔ 1
Jun 8

ረሃብ “በዳቦ ቤት”


በክርስትና እምነት ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ሰዎች እግዚአብሔር ቢኖር በዚህ መከራ በበዛበት ምድር ላይ እንኖር ነበር—የሚል ጥያቄ አዘል ሂስ ያነሱና፡ (ሀ) እግዚአብሔር የለም (ለ) ክፉ ነገር ሲደርስ ጣልቃ ገብቶ ለመቀልበስ የሚችል አቅም የለውም (ሐ) ጉዳት ሲደርስብን ግድ አይሰጠውም—ብለው ትችታቸውን ለማጠናከር ይሞክራሉ። ይሁን እንጂ አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪኮች ከእነዚህ መላ-ምቶች መካከል አንዳቸውም ትክክል አለመሆናቸውን የሚያረጋግጡ በርካታ ማስረጃዎች ይሰጡናል። ሰብዓዊው ዘር በእግዚአብሔር ላይ ያደረገው የአመጻ ተግባር ያስከተለበትን መዘዝ እያጨደ መሆኑ የአደባባይ ምስጢር ነው። ሆኖም እርሱ የምርጫ ነጻነታችንን ሳይጋፋና ሳይጥስ ሁሌም ከአጠገባችን አለ፣ ሁሌም በሰብዓዊው ዘር ታሪክ ውስጥ እየሠራ፣ ለኃጢአት ችግሮችና ሥቃይ የማያዳግም መፍትሔ ለመስጠት ወደፊት እየመራን ይገኛል። የሩት ታሪክ ለዚህ አንዱና ዓይነተኛው ምሳሌ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሩት 1፡1-5። በኑኃሚንና በሩት ላይ የደረሰው መከራ ምን ነበር? ለምን ተከሰተ? ይህ ሁኔታ ዛሬ መላውን ሰብዓዊ ዘር እያጋጠመ ያለውን ነገር እንዴት ያንጸባርቃል?



በዚህ ታሪክ መግቢያ ላይ አንድ ምጸታዊ ይዘት የተላበሰ መግለጫ የምናገኝ ሲሆን ይኸውም “የዳቦ ቤት” የሚል ስያሜ በያዘችው ቤተልሔም ረሃብ የመግባቱ ጉዳይ ነበር። የሚበላ ሞልቶ በተትረፈረፈበት የኤደን አትክልት ስፍራ ይኖር የነበረውን አዳም በአንድ ወቅት እግዚአብሔር እንዲህ ብሎት ነበር “ ‘በአትክልት ስፍራው ውስጥ ከሚገኝ ከማንኛውም ዛፍ ፍሬ ትበላለህ” (ዘፍ. 2፡16)።

እንግዲህ የሰው ዘር ሕልውና ሀ—ብሎ የጀመረው ምርጥ የተባለ የምግብ ዓይነት ዙሪያውን ሞልቶ ተትረፍርፎለት እና ለጋስ በሆነው ፈጣሪ አምላክ እንክብካቤ ጥላ ሥር ቢሆንም፣ ነገር ግን ጥንዶቹ የፍጥረት ተንከባካቢነት ሚናቸውን ለኃጢአት ባርነት መለወጣቸውን ተከትሎ እግዚአብሔር አዳምን እንዲህ አለው፡ “ ‘እንጀራህን በፊትህ ላብ ትበላለህ፤ ዐፈር ነህና ወደ ዐፈር ትመለሳለህ።” (ዘፍ. 3፡19)።

እንደ ኑኃሚን ሁሉ እኛም እግዚአብሔር መጀመሪያ ከተከለን ውርስ ላይ መነቀላችንን ተከትሎ ሕይወታችን በምስቅልቅል የተሞላ ሆነ። ኤደን የተሰጠችው በስጦታ ቢሆንም፣ ቅድመ ሁኔታዎች ግን የግድ መሟላት ነበረባቸው። ሰዎች ለማመጽ ነጻነት ነበራቸው። ያ ማለት ግን በገዛ ራሳቸው ደኅንነት ላይ ሊከተል ለሚችል ማንኛውም መዘዝ ኃላፊነቱን መውሰድ የግድ ይሆናል። መጀመሪያ በኃጢአት ያልወደቀው፣ በእግዚአብሔር የበረከት ጥላ ሥር የሚገኝ ዓለም በሙሉ “እንዲገዛልን” ሆነን ብንፈጠርም፤ አሁን ግን ለወደቀው ዓለም የመገዛት አደጋ ላይ ወደቅን። ንፉጎቹ ሰብዓዊ ፍጡራን ሀብት ለማጋበስ የሚያደርጉት ፉክክር መጠነ ሰፊ ለሆነ የልብ ስብራትና ሥቃይ መንስኤ ሆነ።

ይህ አሳዛኝ ክስተት በቃላት ሊነገር አይችልም። ምድር ዛሬም መጠነ ሰፊ ምርት መለገሷ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚያረጋግጥ ጠንካራ ማስረጃ ነው። ይሁን እንጂ ከሰዎች ስግብግብነትና ኃጢአት ካስከተለው ውድመት የተነሣ፣ ምድርን እኛ ከምንገዛት በላይ በእርሷ እየተገዛን ይመስላል። የሆነው ሆኖ፣ አንድ ቀን ይህ ሁሉ ያከትማል። ከስድስት ሺህ ዓመታት ኃጢአትና ሞት በኋላም እንኳ፣ ምድር አስደናቂውን የእግዚአብሔር ፍቅር እና የመፍጠር ኃይል ዛሬም እየገለጸች ያለው እንዴት ነው?

ሰኔ 2
Jun 9

ሩት እና ቦዔዝ


ኑኃሚን በሕይወቷ ላይ የደረሰውን መራራ ገፈት ተከትሎ ስሟ ማራ ተብሎ እንዲጠራ ስለ መጠየቋ እናነባለን (ሩት 1፡20)። ከፈጣሪያችን ጋር የነበረን ግንኙነት በኃጢአት ምክንያት ላይመለስ ተበላሽቷል፤ ይህም መንፈሳዊ ድህነት ውስጥ እንድንወድቅ አስገድዶናል። ተስፋችን በመደብዘዙ ከነዶው መካከል ማግኘት የምንችላትን እየቃረምንና በፈረሰው ዓለም ውስጥ ሊገኝ የሚችለውን የደስታ ሽርፍራፊ እያገኘን ሕይወታችንን እየገፋን እንገኛን። ነገር ግን የአስደናቂው ግኝት ባለቤት በምንሆንበት ቅጽበት እነሆ ሁሉም ነገር ይለወጣል፡ እግዚአብሔር አልረሳንም! ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሩት 2፡5-20። ይህ የታሪኩ ወሳኝ ምዕራፍ የሆነው ለምንድን ነው? ኑኃሚን የሚቤዠውን ሰው ማንነት ማግኘቷ ያን ያህል መልካም ዜና ሆኖ የቀረበው ለምን ይመስሎታል?



ከንብረቷ የተነቀለችው ኑኃሚን ወደ ሞዓብ ከመሄዳቸው በፊት ተመልሳ ወደዚህ ስፍራ የመጣችው ርስቷን ሸጣ ዕዳዋን ለመክፈል ሳይሆን እንደማይቀር ይታሰባል። በተስፋይቱ ምድር እግዚአብሔር ከንብረት የተነቀሉ ዜጎች በውርስ ያገኙትን ርስት መልሰው የሚጠይቁበትን ደንብ አዘጋጅቶ ነበር። በዚህም አንድ የቅርብ ዘመድ ርስቱን ለግለሰቡ መቤዠት ይችል ነበር። ቦዔዝ ደግ ገበሬ ብቻ ሳይሆን፤ ዘመድም ጭምር ነበር። አንድ ሰው ዕዳውን ለመክፈልና በእስራኤል ውርስ ያገኘውን ርስት መጠየቅ የማይችል ከሆነ፣ የቅርብ የሆነ ዘመዱ ይህን ሊያደርግለት (ሊቤዠው) ይችላል። “ ‘ከወገንህ አንዱ ደኽይቶ ርስቱን ቢሸጥ፣ የቅርብ ዘመዱ መጥቶ ወገኑ የሸጠውን ይዋጅለት’ ” (ዘሌዋ. 25፡25)።

የቦዔዝ ደግነትና ለጋስነት ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ዘመድ መሆኑ መታወቁ፣ ከሁሉ የላቀ የምሥራች ነበር። በእነዚህ ሁለት ሴቶች የደረሰው የድኽነት ገፈት በአጭር የሚቀጭ እንጂ አብሯቸው የሚዘልቅ አልነበረም።

ክርስቲያኖች ቦዔዝ የክርስቶስ ምሳሌ እንደሆነ ከረዥም ጊዜ አንስቶ ተረድተዋል። እርሱ ፈጣሪያችን ብቻ ሳይሆን ነገር ግን እውነተኛ ደም እና ሥጋ በመልበስ ሰው ሆኖ ይዛመደን ዘንድ መረጠ። ራሱን “የሰው ልጅ” (ማቴ. 12:8፣ ማር. 8:31፣ ሉቃ. 22:22፣ ዮሐ. 3:14) እያለ በተደጋጋሚ የሚጠራበት ምክንያቱ ይኸው ነው።

በጣም ብዙ ሰዎች እግዚአብሔርን ጨካኝ አድርገው ይስሉታል። ነገር ግን በቦዔዝ የተገለጠው የክርስቶስ ምስል እንደነዚህ ያሉትን አስተሳሰቦች ሙሉ በሙሉ ያስወግዳል። እግዚአብሔር የምንገኝበትን ጥልቅ የመንፈሳዊ ረሃብ ድባብ መገንዘብ ብቻ ሳይሆን ሙሽራው እንድንሆን ይፈልጋል። ፈጣሪ የመፍጠር ሥራው አካል ብቻ ሳይሆን ነገር ግን ለፈጠረው እንደሞተለትም ለማገናዘብ ይሞክሩ። ይህ አስደናቂ እውነት በገዛ ሕልውናችን ዙሪያ ባለን አመለካከት ምን ተጽእኖ ማሳደር ይገባዋል?

ሰኔ 3
Jun 10

ቦዔዝ—እንደሚቤዥ


ቦዔዝ ሩትን በመውደዱና በእርሷ ላይ ካደረበት ጥልቅ ፍቅር የተነሣ ሊያገባት ቢመኝም፣ ነገር ግን አንድ ብርቱ መሰናክል ከፊቱ ተደቅኖ ነበር። መሰናክሉ በሴቲቱም ሆነ በርስቱ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማቅረብ የሚችል የቅርብ ዘመድ የመኖሩ ጉዳይ ነበር። ቦዔዝን እንደ ክርስቶስ ምሳሌ አድርገን ከተመለከትነው ትዕይንቱ በታላቁ ተጋድሎ ውስጥ ያለውን ቁልፍ ጉዳይ ያሳየናል። ክርስቶስ ይወደናል። ነገር ግን በእኛ ላይ የይገባኛል ጥያቄ ማቅረብ የሚችል “የቅርብ ዘመድ” ደግሞ አለ—ሰይጣን። የሚከተሉት ጥቅሶች ሰይጣን በሰብዓዊው ፍጡር ላይ ስለሚያነሣው የይገባኛል ጥያቄ ገልጠው የሚያሳዩን ነገሮች ምንድን ናቸው? (ኢዮ. 1:6–11፣ ማቴ. 4:8-9፣ ይሁዳ 1:9፣ ሉቃ. 22:31።



ሰይጣን በሰማያዊው ጉባዔ መሃል ተገልጦ ሲያበቃ “ ‘በምድር ሁሉ ዞርሁ፤ ወዲያና ወዲህም ተመላለስሁባት’ ” (ኢዮ. 1፡7) ሲል ለእግዚአብሔር ነገረው። ከዚያም ጌታ ነቀፋ የሌለበትን ጻድቁን ኢዮብ አይቶት እንደሆነ ጠየቀው።

ሰይጣን በኢዮብ ላይ ያለውን የይገባኛል ጥያቄ በማንሣት ልቡ በእርግጥ የእግዚአብሔር ንብረት እንዳልነበረ ተናገረ። ማለትም በእርግጠኝነት እርሱ የሚከተልህ መልካም ስለሆንክለት ብቻ ነው። እስቲ ለእርሱ ያለህን መልካምነት ገታ አድርግና የኢዮብ ታማኝነት ለማን እንደሆነ ተመልከት።

በይሁዳ መጽሐፍ፣ በእስራኤል ገንኖ ይታወቅ ስለ ነበር አንድ ታሪክ አጠር ካለ ማጣቀሻ ጋር እንመለከታለን። ሙሴ ከሞተና በእግዚአብሔር ከተቀበረ በኋላ (ዘዳ. 34፡6)፣ ውሎ አድሮ አርጓል። ምንም እንኳ ዝርዝር ጉዳዮችን ባናውቅም፣ ጥቅሱ ራሱ፣ በሙሴ ሥጋ ላይ ክርክር ስለ መነሣቱ መጥቀሱ፣ ሰይጣን አንዳች የይገባኛል ጥያቄ ማንሣቱን ተከትሎ እንደሆነ እንረዳለን።

“ክርስቶስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሞተው ሰው ሕይወት ሊሰጥ ነው።

የሕይወት ልዑልና አንጸባራቂ መላእክቱ ወደ መቃብሩ ሲቃረቡ፤ ሰይጣን ምድራዊ የበላይነቱ አደጋ ላይ እንደ ወደቀ በመገንዘብ ብርቱ ሃሳብ ገባው። የእኔ በሚለው ግዛቱ ላይ የተደረገበትን ወረራ ለመሟገት ከክፉ መላእክቱ ጋር ቆመ። ሙሴ እንኳ የእግዚአብሔርን ሕግ መጠበቅ እንዳልቻለ፣ ለእግዚአብሔር የሚገባውን ክብር ለራሱ እንደ ወሰደና በዚህም ሰይጣን እራሱ ሰማይ እንዳይገባ የታገደበትን ብቸኛ ኃጢአት እንደሠራ በመግለጽ የእግዚአብሔር አገልጋይ የእርሱ እስረኛ መሆኑን

በኩራት ተናገረ። ሰይጣን በመለኮታዊው መንግሥት ላይ ያለውን የቀደመ ክስ ዳግመኛ በማንሳት እግዚአብሔር ለእርሱ ፍትሐዊ አለመሆኑን የሚገልጽ የክርክር ቃል አሰማ።” (የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፡ ቅጽ 2፣ ምዕ. 43 ገጽ ) ክርስቶስ የሰይጣንን የይገባኛል ጥያቄ ውድቅ አድርጎ እነሆ ሙሴን ከሞት አስነሣው (ማቴ. 17፡3)።

በሩት 4፡1-12 ቦዔዝ ወደ ቤተልሔም የከተማዋ በር አደባባይ ሲያመራ የምንመለከት ሲሆን፣ ይህች ከተማ ክርስቶስ የቅርብ ዘመዳችን ሆኖ ይህን ዓለም የተቀላቀለባት ናት። ሽማግሌዎች ተሰበሰቡ፣ እናም በመጨረሻ ጫማ መውለቁ (የመቤዠት ምሳሌ) ያደረጉት ልውውጥ መጽናቱን ያሳያል።

የከተሞች መግቢያ በር ጉዳዮች ውሳኔ የሚያገኙበት—ፍርድ የሚሰጥበት ስፍራ ነው። ይህ ደግሞ በዳን. 7:13-14፣ 22፣ 26-27 የቀረበውን የፍርድ ውሳኔ ያንጸባርቃል። በፍርድ ወቅት “ለቅዱሳን የሚፈረድላቸው”፣ ቦዔዝ ለሙሽራው እንዳደረገው ሁሉ ክርስቶስ እኛን ለመዋጀት ዋጋ በመክፈሉ ብቻ እንደሆነ የሚያሳየውን ይህን ወሳኝ የፍርድ ገጽታ መሳት የለብንም።

ሰኔ 4
Jun 11

ሐማ እና ሰይጣን


በአስቴር ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ የሥልጣንና ከበሬታ ጥማት የነበረውን ሰው—ሃማንን እናገኛለን። ሐማ በግዛቲቱ ከነበሩት መሳፍንት እና መኳንንት ሁሉ የላቀ ሥልጣን ተሰጠው (አስቴር 3፡1)።

ሉሲፈርን አስመልክቶ በሕዝ. 28፡ 11-15 እና ኢሳ. 14፡12- 15 የተጻፉትን ስናነብ፣ ከሐማ ጋር የሚያመሳስሉትን ማለትም ለእግዚአብሔር የበላይነት ለመንበርከክ እምቢተኛነቱንና በእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች ላይ በጠላትነት የተነሣ እኩይ ተቃዋሚነቱን የሚያሳዩ አንዳንድ ባህሪያት እናገኛለን።

የሰይጣን ዋንኛ ዓላማ አጠቃላይ ድምር የተገለጠው ክርስቶስን በፈተነበት ታሪክ ውስጥ ሲሆን፣ ይኸውም ክርስቶስን ከፍ ወዳለ ተራራ አውጥቶ የዓለምን መንግሥታት ከነክብራቸው ባሳየው ወቅት ነበር (ማቴ. 4፡8-11)። ቀደም ብለን እንደተመለከትነው ክርስቶስ የመጣው ዓለምን ሊቤዣትና የይገባኛል ባለመብት መሆኑን ለማሳየት ሲሆን፣ ይህንንም ከእኛ እንደ አንዱ በመሆን ፈጽሞታል። የሱስ የቅርብ ዘመዳችን እነሆ ተቤዢያችን ነው። እርሱ ዓለምን ለመቤዠት የከፈለው ዋጋ ከመጠን በላይ ውድ እና የከበረ ለመሆኑ እሙን ነው።

ሰይጣን ለሥልጣንና አምልኮ ያለው የማያባራ ፍትወት ይህችን ዓለም ወደ መጨረሻው ቀውስ እንደሚያመጣት ከራእይ መጽሐፍ እንመለከታለን። ለእርሱ ለመስገድ ከሚቃወሙ ለየት ያሉ ሕዝቦች በቀር፣ የእርሱ መሸንገያና ማታለያዎች ዓለም በሙሉ “በመደነቅ” አውሬውን እንዲከተለው ያሳምናሉ (ራእ. 13፡ 3-4)። ከእነዚህ ሕዝቦች ጋር ያለውን ጉዳይ በኃይል ለመፍታት ያስባል።

ሐማ ከእግዚአብሔር የተመረጡ ሕዝቦች አንዱ የሆነው መርዶክዮስ ወድቆ እንዳልሰገደለትና ይገባኛል ብሎ ያሰበውን ይህን የ “አምልኮ” ክብር እንዳልሰጠው ሲገነዘብ “እጅግ ተቈጣ” (አስቴር 3፡5-6)። ይህን ተከትሎ የመርዶክዮስን ወገኖች በሙሉ ከምድር ገጽ ለማጥፋት ቆርጦ ተነሣ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ አስቴር 3፡1-14፣ ራእ. 12፡14-17፣ ራእ. 13፡ 15። በእነዚህ ጥቅሶች መካከል የሚያገኙት ተመሳሳይ ሀሳብ ምንድን ነው? ዮሐንስ የእግዚአብሔርን ትሩፋን ቤተ ክርስቲያን የሚገልጽበት መንገድ ሐማ የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ከሚገልጽበት ጋር እንዴት ይመሳሰላል?



ዲያብሎስ በዚህ ዓለም ላይ የይገባኛል ጥያቄ አንስቷል፣ ነገር ግን ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁ ሰዎች መኖራቸው፣ የእርሱን ፍጹም የበላይነት ሐሰት መሆኑን በማስረጃ ይቃወማሉ።

“ሰንበት በመላው የክርስትና ተቋማት ልዩ የውዝግብ መነሾ በሚሆንበት ወቅት፣ ጥቂቶች ለብዙኃኑ ፍላጎት ተገዢ ላለመሆን የሚያደርጉት የማያባራ ተቃውሞ ለዓለማቀፋዊው ውግዘትና እርግማን ይዳርጋቸዋል።”—Ellen G. White, Signs of the Times, February 22, 1910. ዛሬ እምነትዎን እየፈተኑ ስላሉ”ጥቃቅን” ነገሮች አሰብ ያድርጉ። በእነዚህ “ጥቃቅን” ነገሮች ዙሪያ ሰጥቶ የመቀበል ልል አቋም የሚያራምዱ ከሆነ፣ ታላቁ የፈተና ወቅት ሲመጣ ምን ሊያደርጉ ነው?

ሰኔ 5
Jun 12

እንደዚህ ላለው ጊዜ


ጠንከር ባሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ዙሪያ ምልከታ ማድረግ፣ በአንዳንድ ክርስቲያኖች ዘንድ ውስጣዊ ምቾት የማጣት ዝንባሌ ሲፈጥርባቸው ይስተዋልባቸዋል። ከባባድ የፈተና ወቅቶች ከፊታችን እንዳሉ ስንመለከት፣ ትኩረታችንን በታሪኩ ቃል ከተገባው መፍትሔ ይልቅ በመከራው ላይ የምናደርግ ከሆነ፣ የትንቢት ጥናታችን ፍርሐትን መሰረት ያደረገ ሊሆን ይችላል። እግዚአብሔር የወደፊቱን—ላይ ላዩን በስኳር የሚቀባባ አምላክ እንዳልሆነ ሁሉ፣ አሁን እና በታላቁ ተጋድሎ መገባደጃ መካከል የሚከናወኑ ክስተቶችን በሐቅ በመናገር ረገድ ታማኝ ቢሆንም፣ ታሪኩን እስከ መጨረሻው ማንበብ ሁሌም ቢሆን አስፈላጊ ነው፡

እግዚአብሔር በሰብአዊው አመጽ ስለተፈጠረው ውጥንቅጥ እውነቱን የሚገልጥበት አጠቃላይ ንድፍ በትንቢት ውስጥ ያለ ሲሆን፣ በዚህም የሚያስከትላቸውን መዘዞች ያሳየናል። ነገር ግን በዚህ ውስጥ እርሱ ሁልጊዜ ተስፋ ይሰጠናል። አንዳንዶች የመጨረሻውን ቀውስ ማለትም “የያዕቆብን የመከራ ጊዜ” ትንቢት በፍርሃትና በመንቀጥቀጥ ሲመለከቱ ይስተዋላሉ። የምድር ታሪክ የሚቋጭባቸው እነዚያ ወቅቶች ለእግዚአብሔር ሕዝቦች ቀላል አለመሆናቸው እሙን ነው። ነገር ግን የመከራው ዘመን ትንቢት የማይቀለበሰውን ያህል የመዳናችን ተስፋም አስተማማኝ ነው።

በራእ. 12 ዲያብሎስ የክርስቶስን ሙሽራ በጥላቻ ሊበቀላት ቢያሳድዳትም፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ያድናት ዘንድ ጣልቃ ይገባል። የአስቴር ታሪክ በድራማው ውስጥ ወሳኝ ሚና የምትጫወተውን ቆንጆ ንግሥት የያዘ ሲሆን፣ እግዚአብሔርም ሕዝቦቹን ለማዳን እርሷን በኃይል ይጠቀምባታል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ አስቴር 4፡13-14፣ 5፡1-3፣ 9፡20-28። በምድር ታሪክ መደምደሚያ ወቅቶች ላይ ሊደርስብን ስለሚችል መከራ ከእነዚህ መልእክቶች ምን እንማራለን?



እግዚአብሔር በታሪክ የተወሰኑ ዘመናትን ለሚሸፍኑ ጊዜያቶች ትሩፋን ቤተ ክርስቲያኑን አስነሣ። የ1260 ቀናት ትንቢት አካል የሆነው የጨለማው ዘመን መገባደጃ ላይ፣ እግዚአብሔር ሙሽራውን ከተሸሸገችበት (ራእ. 12፡14) ያወጣት ሲሆን፣ ይኸውም የሦስቱ መላእክት መልእክት የሆነውን የመጨረሻውን የምሕረት መልእክት ለዓለም ትሰብክ ዘንድ ነው። እኛ በዚህ ምድር ያለነው “እንደዚህ ላለው ጊዜ” ነው (አስቴር 4፡14/ 1962 ትርጉም/)።

አስቴር ሐማ በሕዝቧ ላይ የከፈተውን ስደት ትጋፈጥ ዘንድ ብቻዋን አለመሆኗን ተገነዘበች። በንጉሡ ፊት ሞገስ ማግኘቷንም ተከትሎ እነሆ በመጨረሻ በሕዝቦቿ ላይ አንዣቦ የነበረው አደጋ ተወገደ። እኛም ወደ ምድር ታሪክ የመጨረሻዎቹ ጊዜያቶች ስንገባ ብቻችንን አንሆንም። ንጉሡ ከጎናችን ስለሚሆን ከዚህ ታሪክ በተመሳሳይ እርሱ ለሕዝቦቹ ጥላ ከለላ በመሆን ይታደጋቸዋል። በዚህ ታሪክ ነገሮች ለእግዚአብሔር ሕዝብ መልካም ገጽታ ይዘው መጠናቀቃቸውን እንመለከታለን። ሆኖም ግን፣ ሁሌም እንዲህ ዓይነቱ ፍጻሜ ይኖራል ማለት እንችላለን? በክርስቶስ ላይ ያለንን ተስፋ ጠብቀን መቆየት እንችል ዘንድ ሁሌም ቢሆን ነገሮችን ረዘም ያለ ጊዜ ሊወስድ ከሚችል ምልከታ አኳያ ማጤን የሚኖርብን ለምንድን ነው?

ሰኔ 6
Jun 13


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት—ከተሰኘው መጽሐፍ—ቅጽ 2 ላይ፡ “የመጀመሪያው የእስራኤል ንጉሥ” የሚለውን ምዕራፍ ያንብቡ።

“ሰይጣን የብዙኃኑን ልማድና ትውፊት ለመቀበል ፈቃደኛ ባልሆኑ አነስተኛ ቁጥር ባላቸው ወገኖች ላይ ቁጣ ይቀሰቅሳል። ሥልጣንና ዝና ያላቸው ሰዎች በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ለመምከር ከሕገ-ጠሎች እና በእርክስና ከሚመላለሱ ጋር ግንባር ይፈጥራሉ። ሐብት፣ ብልጠትና ትምህርት ተደማምረው የንቀት መሸፋፈኛቸው ይሆናሉ። የቤተ ክርስቲያን የሥራ ኃላፊዎችን፣ አገልጋዮችንና አባላትን ያሳድዳሉ፣ በእነርሱም ላይ ያሴራሉ። በአንደበታቸውና በብዕራቸው፣ በትምክህታቸው፣ በዛቻና ማስፈራሪያቸው እምነታቸውን ገርስሰው ለመጣል ይጥራሉ። በሐሰት ክስ እና በቁጣ በነደደ ስሞታ የሕዝቡን ስሜት ያምሳሉ።

“መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ይላል’ በሚል ማስረጃ መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ሰንበት የሚደግፉ ወገኖችን መሞገት ስለሚሳናቸው ይህን ጉድለታቸውን ለመሙላት ጨቋኝ ሕግጋት ያወጣሉ። ዝናቸውን አስተማማኝ ለማድረግ ብሎም ለሌሎቹ ዝቅ ያለ ግምት ለመስጠት፣ ሕግ አውጪዎች የእሁድ ሕግ ይወጣ ዘንድ ይጠይቃሉ። ነገር ግን እግዚአብሔርን የሚፈሩ ሰዎች የአስርቱን ትእዛዛት መመሪያ የሚጥሰውን ተቋማዊ ውሳኔ መቀበል አይችሉም። በዚህ ዐውደ ውጊያ በእውነት እና በሐሰት መካከል የሚካሄደው የመጨረሻው ታላቁ ተጋድሎ እውን ይሆናል። እናም በጉዳዩ ጥርጣሬ እየገባን እንድንዋልል ሆነን አልተተውንም። ዛሬም እንደ አስቴርና መርዶክዮስ ዘመን ጌታ እውነቱንና ሕዝቡን ነጻ ያወጣል።”—Ellen G. White, Prophets and Kings, pp. 605, 606.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እግዚአብሔር ሕዝቡ በአስቸጋሪና ፈታኝ ወቅቶች ያልፍ ዘንድ ለምን እግዚአብሔር ሕዝቡ በአስቸጋሪና ፈታኝ ወቅቶች ያልፍ ዘንድ ለምን የሚፈቅድ ይመስሎታል? ይህን የመፍቀዱ ፋይዳ ምንድን ነው?

2. አንድ አማኝ ለክርስቶስ ታማኝ ከመሆን ጋር በተያያዘ ሊመጣ ከሚችል አንድ አማኝ ለክርስቶስ ታማኝ ከመሆን ጋር በተያያዘ ሊመጣ ከሚችል ማንኛውም ችግር ራሱን እንዴት ያዘጋጃል? በአስቸጋሪ ሁኔታዎች መሃል ተስፋን ከወዴት ያገኛሉ?

3. በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ትንቢታዊ ጉዳዮች ላይ የማሰላሰል—የምሥራቹን በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ትንቢታዊ ጉዳዮች ላይ የማሰላሰል—የምሥራቹን የሚያቀርበው ትልቁ ምስል ግን እንዲጋረድ የመፍቀድ ዝንባሌ ያለን ለምን ይመስሎታል?

4. አንድ ወዳጅዎ ወደ እርስዎ ቀርቦ የራእይ መጽሐፍን እንዳነበበው ነገር ግን አንድ ወዳጅዎ ወደ እርስዎ ቀርቦ የራእይ መጽሐፍን እንዳነበበው ነገር ግን “አስፈሪ” ሆኖ እንዳገኘው ቢነግሮት፣ መጽሐፉ ይበልጥ ግልጽ ይሆንለትና የአእምሮ ሰላም ያገኝ ዘንድ ምን ዓይነት ዘዴ ይጠቀማሉ?

5. አንድ ሰው “እግዚአብሔር እንደሚወደኝ ወይም እንደሚፈልገኝ እርግጠኛ አንድ ሰው “እግዚአብሔር እንደሚወደኝ ወይም እንደሚፈልገኝ እርግጠኛ አይደለሁም። ለነገሩ፣ ያደረኩትን ብታውቅ ኖሮ ምክንያቱን በተረዳህ ነበር” ሲል ቢያደምጡ፣ ምን ምላሽ ይሰጡታል? የሩት እና የአስቴር ታሪክ ምላሽዎን እንዴት ያጠናክረዋል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL