የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 6:12–17፣ ማቴ. 24:36–44፣ ዘፍ. 6:1–8፣ 2ጴጥ. 2:4–11፣ ዘፍ. 18:17–32፣ ዳን. 7:9, 10።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ይህ ሁሉ ምሳሌ ይሆን ዘንድ በእነርሱ
ላይ ደረሰ፤ የዘመናት ፍጻሜ የደረሰብንን እኛን ለማስጠንቀቅም
ተጻፈ። ስለዚህ ተደላድዬ ቆሜአለሁ የሚል ቢኖር እንዳይወድቅ
ይጠንቀቅ።” (1ቆሮ. 10፡11-12)።
መጽሐፍ ቅዱስ ወደፊት ስለሚፈጸሙ ክንውኖች በሚነግሩንና አሁን
ያለውን “ወቅታዊ እውነት” እንድናተውል በሚረዱን ቁልፍ
የእግዚአብሔር ሕዝብ ታሪኮች የተሞላ ነው። እንዲያውም አንዳንዶቹ
ዘገባዎች የዳንኤልንና የራእይን ትንቢቶች በግልጽ ለመረዳት የሚያስችል ሰፊ
መሠረት በመጣል፣ በአስገራሚ ዝርዝር መግለጫዎች የመጨረሻውን ዘመን
ክስተቶች በግልጽ ያሳያሉ።
እግዚአብሔር ግለሰባዊውን የሕሊና ነፃነትን ሳይጥስ፣ ነቢያት በመጨረሻዎቹ
ቀናት እንደሚፈጸሙ ከተነበዩት ጋር ፍጹም ሆኖ በሚስማማ መልኩ ሁኔታዎችን
መምራት ችሏል። ከነዚህ ወሳኝ ታሪኮች መካከል አንዳንዶቹ ግልጽ ሆነው ቀርበዋል።
ምክንያቱም አዲስ ኪዳን በተለይ የመጨረሻዎቹን ዘመናት ክስተቶች ለማሳየት
እንደ፡ ሰዶምና ጎሞራ፣ የጥፋት ውሃ ወዘተ የመሳሰሉትን በገሃድ ይጠቅሳቸዋል።
በአምላካዊው ቃል ውስጥ የተሰጡንን ሌሎቹን እውነቶች ምሰን ለማውጣት ደግሞ
በጥንቃቄ ማሰስ፣ ማሰብና ማጤን ከእኛ ይፈለጋል።
በሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት እንደ ዳግም ምጽአት፣ የፍርድ ምርመራ፣
የመጨረሻው ቀውስ፣ እና ሌሎች ክስተቶች ምን ማለት እንደሚጠበቅባቸው
ለመመልከት በበርካታ ቁልፍ ታሪኮች ዙሪያ ቅኝት እናደርጋለን። ክርስቶስ የትንቢቶች
ሁሉ መሰረት ብሎም የመላው ትንቢታዊ መልእክት የመጨረሻ ግብ እንደመሆኑ፣
በዚያ ረጅም ሂደት እርሱን የሁሉም አስኳል ሆኖ እናገኘዋለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6፡12-17። የመጨረሻውን ዘመን ክስተቶች በድንገት ገቢራዊ መሆንን ተከትሎ የሚስተዋለውን የእነዚህን ሰዎች ምላሽ ዝርዝር ሀሳብ ለማጤን ይሞክሩ። ስለ ምላሻቸው ምን አስተዋሉ?
የሚገርመው ነገር እነዚህ የጠፉ ሰዎች “ይህ ነገር ምንድን ነው?” ወይም
“ከዚህ ጀርባ ያለው ማን ነው?” ብለው ሲጮኹ አይደመጡም። ይልቁንም ምን
እየተከናወነ እንደሆነ የሚያውቁ ይመስላል። የሱስን “በጉ” ብለው የሚጠሩት
ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ስለ ክርስቶስ አንድ የሚያውቁት ነገር እንዳለ ይጠቁማል።
በተጨማሪም “ታላቁ የቁጣው ቀን” መምጣቱን በመገንዘባቸውና ተስፋ አስቆራጭ
ሁናቴ ውስጥ በመውደቃቸው፡ በፊቱ “ማንስ ሊቆም ይችላል?” ሲሉ ይደመጣሉ።
ፍጻሜው ከመምጣቱ አሰቀድሞ ወንጌል ለምድር ሕዝቦች ሁሉ ደርሷል
(ማቴ. 24፡14)፣ የሦስቱ መላእክት መልእክትም ለመላው ዓለም ተሰራጭቷል።
ይሁን እንጂ በመረጃ እጦት ሳይሆን፣ ለማመንና ለመታዘዝ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው
ጠንቅ ይህ ቀን በድንገት የሚደርስባቸው ይኖራሉ። እነዚህ ሰዎች በመጨረሻው ቀን
የሚጠፉበት ምክንያቱ ይኸው ነው።
ጥቅሶቹን ያንበቡ፡ ማቴ. 24፡ 36-44። የሱስ ከኖኅ ታሪክ ምን ዓይነት
ትምህርቶች መውሰድ ይኖርብናል አለ?
የሱስ ዳግም ምጽአቱ ለብዙዎች ሳያስቡት የሚከሰት ዱብ’ዳ እንደሚሆን
ለማስጠንቀቅ ወደ ጥፋት ውሃ ታሪክ ሲያመለክተን ይታያል። የጥፋት ውሃ ያለ
አንዳች መረጃ በዓለም ላይ እንዳልተከሰተ ሁሉ ዳግም ምጽአቱም ተመሳሳይ ገጽታ
ይኖረዋል። ኖኅ ለማመን አሻፈረኝ ላለው ዓለም ለ120 ዓመታት ሰበከ። ሊመጣ
ስላለው ነገር ቢነገራቸውም፣ እነርሱ ግን አላመኑበትም ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በርካቶች—የተባለው ነገር ሳይፈጸም ረጅም ዘመናት
ማስቆጠሩ የትንቢቶቹን ሐሰተኝነት ያመለክታል ሲሉ ራሳቸውን ይሸነግላሉ። ጴጥሮስ
የጥፋት ውሃን ታሪክ የመልእክቱ ዐውድ አድርጎ በመጠቀም እንደሚከተለው
ጽፏል፡ “ከሁሉ አስቀድሞ ይህን ዕወቁ፤ በመጨረሻው ዘመን የራሳቸውን ክፉ
ምኞት የሚከተሉ ዘባቾች እየዘበቱ ይመጣሉ። እነርሱም፣ ‘እመጣለሁ’ ያለው
ታዲያ የት አለ? አባቶች ከሞቱበት ከፍጥረት መጀመሪያ አንሥቶ እስካሁን ድረስ
ሁሉም ነገር እንዳለ ይኖራል’ ይላሉ” (2ጴጥ. 3፡3-4)። እያንዳንዱ ዓመት
ባለፈ ቁጥር፣ ይህ ስሜት እያደገ ሊሄድ ይችላል።
በእያንዳንዱ ሰው የግል ተሞክሮ የየሱስ ዳግም ምጽአት ሰው ከሞተ በኋላ ገቢራዊ
ከሚሆን ቅጽበት የዘለለ አይደለም፤ የሕይወትን በፍጥነት መክነፍ ደግሞ ሁላችንም
በቀላሉ የምንገነዘበው ጉዳይ ነው። ይህ አመለካከት ከብዙዎች ለሚሰማው
“መዘግየት” እንዴት መልስ መሆን ይችላል?
ብዙዎች በጥፋት ውሃ ወቅት የተከሰተውን ነገር “ሆነ ብለው ይክዳሉ”
(2ጴጥ. 3፡5) ስለዚህ ራሳቸውን ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዝግጁ አያደርጉም
ሲል ጴጥሮስ ይነግረናል። ምንም እንኳ ዛሬ ዓለም ስለ ጥፋት ውሃ የተሟላ ትውስታ
ቢኖረውም (ከጥንታውያን ግሪኮች እስከ ማያውያን ድረስ የዘለቁ አስገራሚ ቁጥር
ያላቸው የዓለም ባሕልና ትውፊቶች ስለ አውዳሚው የጥፋት ውሃ ይተርካሉ)፣
ዛሬ በእጅጉ ከሚዘበትባቸው የመጽሐፍ ቅዱስ ዘገባዎች አንዱ የኖኀ ታሪክ ነው።
አስቀድሞ እንደተተነበየው የጥፋት ውሃ ታሪክ በብሉይ ኪዳን የቱንም ያህል ግልጽ
ሆኖ በቁም ነገር ቢቀርብና በአዲስ ኪዳን ውስጥ ተደጋጋሞ ቢጠቀስም፣ ዓለም ሆነ
ብሎ ክስተቱን ከበሬ ወለደ ተረት ሲመድብና ሲክድ ይስተዋላል።
የሱስ የመጨረሻውን ዘመን የዓለም ሁናቴ “ልክ በኖኅ ዘመን እንደሆነው”
(ማቴ. 24፡37-39) ይሆናል ብሎ በንጽጽር አስቀምጧል። ይህን ክፍል
ከዘፍ. 6፡1-8 ጋር ያስተያዩ። ለጥፋት ውሃ የዳረጉ የሥነ ምግባር ጉዳዮች ምን
ነበሩ? እነዚህን ሁለት ዘመናት የሚያመሳስሉ ነገሮች ምንድን ናቸው?
በጥንቃቄ የተሞላ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናትን ተከትሎ ለእግዚአብሔር
የመጨረሻው ዘመን ትሩፋን ሌላ ወሳኝ ትምህርት አለ። ዕብ. 11፡ 7 እንደሚነግረን—
ኖኅ “ቤተ ሰዎቹን ለማዳን መርከብን በእምነት ሠራ፤ በእምነቱ ዓለምን ኰነነ፤
በእምነትም የሚገኘውን ጽድቅ ወራሽ ሆነ።”
ከአንድ መቶ ዓመት በላይ ሲሰበክ—ሰው ሁሉ ለመልእክቱ ጆሮ ዳባ ሲል—
ሰባኪውና ቤተሰቡ ብቻ መርከቧ ውስጥ ሲገቡ—እስቲ ጉዳዩን በዓይነ ሕሊናዎ
ይመልከቱ። ኖኅ የዘመናችን ወንጌላዊ ቢሆን ኖሮ፡ በርካታ አሥርተ ዓመታት የፈጀ፣
ግን ፍሬ ቢስ ስብከት—ብለን እንደ ከሸፈ በቆጠርነው ነበር።
ደግነቱ በዚህ ወቅት፣ በርካታ የዓለም ክፍል ለሦስቱ መላእክት መልእክት
አዎንታዊ ምላሽ እየሰጠ ይገኛል። በዓይነታቸው ልዩ የሆኑትን የመልእክቶቻችንን
ስብከቶች የሚያስተጋቡ የወንጌል ጥረቶች በበርካታ ስፍራዎች አመርቂ ውጤት
እያስመዘገቡ መሆናቸውን ተከትሎ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ወገኖች ጌታን ወደ ማወቅ
በመምጣት ላይ ይገኛሉ። ምንም እንኳ የምህረት ደጅ የሚዘጋበት ወቅት እንደሚመጣ
ቃሉ ቢነግረንም፣ ውጤት የሌለው አገልግሎት ላይ ግን ገና አልደረስንም። “የምሕረት
ጊዜ ያበቃል፤ የምሕረት ደጅም ይዘጋል። እናም ‘ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ
ጋር ወደ ሠርግ ገቡ ደጁም ተዘጋ’ በሚለው አንድ አጭር አረፍተ ነገር ውስጥ
በአዳኙ የመጨረሻ አገልግሎት አማካኝነት፣ ለሰው ልጅ መዳን የተሠራው ታላቅ ሥራ
ወደሚጠናቀቅበት ወደዚያ ጊዜ እንሄዳለን።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡490)
ያ ጊዜ እስከሚመጣ ድረስ ግን፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን የምንሠራው ሥራ ይኖረናል።
የወንጌል ጥረቶቻችን ለጊዜው ከፍ ያለ ቁጥር ያለው ፍሬ የማያፈሩ መስሎ
የሚታየን ከሆነ፣ ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
ጥረቶቻችንን መቀጠል ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? (ዮሐ. 4፡37)።
ጴጥሮስ የመጨረሻውን ዘመን ክስተቶች ሲገልጽ በቀጥታ የጠቀሰው ሌላ
ቁልፍ የብሉይ ኪዳን ታሪክ አለ፡ የሰዶምና የገሞራ ውድመት። እነዚህ ሜዳማ መልክአ
ምድር የተላበሱ ከተሞች፣ በእርክስናቸው እውቅና ያተረፉ—የመጀመሪያዎቹ
ከሰማይ በወረደ እሳት የወደሙ የሕዝብ መናኸሪያ ምሳሌ ሆነዋል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 2:4–11፣ ይሁዳ 5–8፣ ሕዝ. 16:46–50።
የሁሉንም ዝርዝር ሀሳቦች ልብ ብለው ይመልከቱ። ለእነዚህ ከተሞች ውድመት
መንስኤ የሆኑ የሥነ ምግባር እርክስናዎች ምን ነበሩ? ዛሬስ ከእነዚያ በተመሳሳይ
እየተስተዋሉ ያሉ እርክስናዎች ምድንድን ናቸው?
በሰዶምና ገሞራ ታሪክ በኩል ለዚህች ዓለም የመጨረሻ ዘመን ሕዝቦች
የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ግልጽ ነው። በራእ. 20 በግልጽ እንደተብራራው
ኃጥአንም እንዲሁ በእሳት ይጠፋሉ። ኃጢአት እጅግ አታላይ ከመሆኑ የተነሣ
በሌሎች የሚፈጸሙ እርክስናዎች በጉልህ እንዲታዩን—የገዛ መተላለፋችንን ግን
በግላችን ተቀባይነት ባለው የአቋም ሽፋን በመጋረድ የገዛ ልባችን የሚገኝበትን
ሁኔታ እንኳ ሳይቀር እንዳናይ ያሳውረናል። እግዚአብሔር በሕዝቡ ላይ ፍቅሩን
ምን ያህል እንዳፈሰሰ በተናገረበት በዚያው ምዕራፍ፣ ምንም እንኳ ሕዝቡ
ተመሳሳይ ኃጢአቶች ባይሠራም (ሕዝ. 16፡47) ከሰዶም የባሰ እርክስና ላይ
መውደቃቸውን ግን ማስጠንቀቅ ነበረበት።
እስራኤል በ “ግልሙትና” (ሕዝ፡ 16፡41) ይኸውም በመንፈሳዊ ዝሙት
እርክስና ወድቃ ነበር። የእግዚአብሔር ሕዝቦች በእርክስናቸው ይታወቁ ከነበሩ አረማውያን
ይበልጥ እርኩስ መሆናቸውን ሲሰሙ ያለውን ሁኔታ በዓይነ ሕሊናዎ ይመልከቱ።
ይህ ለጥንቷ እስራኤል ብቻ ሳይሆን ለመላው ሰብዓዊ ዘር አዲስ ነገር
አይደለም። ጳውሎስ በሮሜ 1፡18-32 መልእክቱ ያቀረበው ረጅም ዝርዝር የያዘ
ሰብዓዊ ክፋት፣ የዛሬው ዘመን የማይታበል እውነታ ነው። ጳውሎስ ስለ አሕዛብ
ኃጢአት የሰጠው መግለጫ በአይሁዳውያን ዘንድ የበላይነት ስሜት ለመፍጠር
ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ሕዝቦች የገዛ ኃጢአታቸው ምን ያህል ከባድ እንደሆነ
እንዲገነዘቡ ለማድረግ ነበር። ናታን ዳዊትን ባናገረው ጊዜ የሆነው ይኸው ነበር።
የአንድን ደኻ ምሰኪን ሰው የበግ ጠቦት ቀምቶ ስለወሰደ ባለጠጋ ሰው ታሪክ
ነገረው። ታሪኩ ዳዊትን “እጅግ አስቆጣው” (2ሳሙ. 12፡5)። ምክንያቱም
የተፈጸመው ግፍ ፍጹም ግልጽ ነበር። ሆኖም ናታን—ዳዊት ራሱን በታሪኩ ውስጥ
እንዲያይ ካደረገ በኋላ እንዲህ አለው፡ “ያ ሰው አንተ ነህ” (2ሳሙ. 12፡7)።
መጽሐፍ ቅዱስ በዋነኝነት የተጻፈው ለውጪው ዓለም ሳይሆን ለራሱ
ለእግዚአብሔር ሕዝቦች መሆኑን ማስታወስ ጠቃሚ ነው። በራእ. 13 እና 17
ባሉት ክፍሎች የተገለጹትን የሌሎችን አስከፊ ኃጢአቶች መመልከታችን፣ እኛም
በተመሳሳይ ወጥመድ ውስጥ ልንወድቅ እንደምንችል የተሰጠን ማስጠንቀቂያ ነው።
ሰዶም ከመጥፋቷ ጥቂት ቀደም ብሎ በመምሬ ሜዳማው መልክአ ምድር ላይ ገቢራዊ የሆነ አንድ አስገራሚ ታሪክ አለ። እግዚአብሔር ከሁለት መልአኮች ጋር በመሆን ለአብርሃም ይገለጥለታል። አብርሃምም እንዳያቸው እነዚህን ሰማያዊ እንግዶች ምግብ ይጋብዛቸዋል። እንግዲህ በዚህ ወቅት ነበር እስከ መሲህ የሚዘልቀውን የዘር ሃረግ ፍሬ አብርሃም እና ሣራ እንደሚያገኙ እግዚአብሔር ለአብርሃም ቃል የገባው። የየሱስ ዝርያ ከአብርሃም የዘር ሃረግ መመዘዙ እሙን ነው (ገላ. 3፡ 16)። ከዚያም ታሪኩ በድንገት ወደ ኃጥአኑ ሜዳማ ከተሞች ያመራል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 18፡17-32። ስለ እግዚአብሔር ባህሪ እና ውሎ አድሮ እርሱ በምድራችን የሰፈነውን ክፋት ለማስወገድ ስላቀደበት መንገድ ከእነዚህ ጥቅሶች ምን እንማራለን?
እግዚአብሔር ለእኛ ማብራሪያ ለመስጠት ግዴታ ባይኖርበትም፣ ነገር
ግን ዓላማውን እና እቅዱን ከሰው ልጅ ባይሸፍን ይመርጣል። “በእውነት
ጌታ እግዚአብሔር ምስጢሩን ለአገልጋዮቹ ለነቢያት ሳይገልጥ፣ ምንም ነገር
አያደርግም።” (አሞጽ 3፡7)።
እግዚአብሔር ሰዶምንና ገሞራን ከማጥፋቱ በፊት ማድረግ የነበረበት
ብቸኛውና ትክክለኛው—ሊሆን ስላለው ነገር ለእርሱ ማሳወቅ እንደሆነ ተናግሯል።
በዚህም አብርሃም በቅርብ በሚሆነው ነገር ምስክር ይሆናል።
ሁለቱ መላእክት ማስጠንቀቂያቸውን ለሚሰሙ ጥሪ ለማቅረብ
ወደዚያች ክፉ ከተማ ሲያመሩ እግዚአብሔር ግን ከአብርሃም ጋር ቆይታ ያደርጋል።
በመጨረሻው ዘመን ተመሳሳይ ተግባር በማከናወን በባቢሎን ውስጥ የሚኖሩ
የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከእርሷ እንዲወጡ ጥሪ የሚያደርጉ መላእክትን ትንቢት
ማሰብ እንችላለን (ራእ. 14:6–12፣ ራእ. 18:1–4)። የመጨረሻው
ማስጠንቀቂያ እየተሰጠ በነበረበት ወቅት፣ እግዚአብሔር ሊሆን ስላለው ነገር
ከአብርሃም ጋር እየተወያየ ነበር። እርሱ—የኃይማኖት አባት የሆነው አብርሃም
ላቀረባቸው ጥያቄዎች ራሱን ግልጽ አድርጎና ፈቃደኛ ሆኖ በፊቱ ቀርቦ ነበር።
“ ‘እንዲህስ አይሁን፤ ጻድቁን ከኀጢአተኛው ጋር እንዴት ትገድለዋለህ?
ይህን የመሰለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ፤ የምድር ሁሉ ዳኛ በቅን አይፈርድምን?”
(ዘፍ፡ 18፡25)። አብርሃም የሰዶምን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የእግዚአብሔርንም
ባሕርይ እየመረመረ ነበር። በተመሳሳይ፣ መጨረሻው ከመምጣቱ በፊት
እግዚአብሔር የሰማይ መጻሕፍትን ይከፍታል (ራእ. 20፡4፣ 11–15)፤
በመጨረሻ በምድር ላይ እሳት ከማውረዱ በፊት ማስረጃዎቹን እንድንመረምር
ይፈቅድልናል። በዚህም ዛሬ መልስ ላላገኘንላቸው በርካታ ጥያቄዎች መልስ
የምናገኝባቸው አንድ ሺ ዓመታት ይኖሩናል።
ጌታ በጠፉት ላይ የመጨረሻውን ፍርድ ከመስጠቱ በፊት፣ በማን ላይ እና በምን
ምክንያት ያ እንደ ደረሰ እንረዳ ዘንድ አንድ ሺህ ዓመት ይሰጠናል። ይህ ስለ እርሱ
ባህሪ እና እርሱ በፍጡራኑ ይመረመር ዘንድ ምን ያህል ክፍት እንደሆነ ምን ይነግረናል? (ፍጡራኑ በሕይወት ለመኖር ሙሉ በሙሉ በእርሱ ላይ ጥገኞች
ሆነውና እነዚህን ነገሮች የማወቅ አንዳችም ተፈጥሯዊ መብት ሳይኖራቸው)
በዳንኤል ምዕ. 7 ላይ የሚገኘው የፍርድ መግለጫ ከመጋረጃው
በስተጀርባ ስላለው ነገር ፍንጭ በመስጠት—እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በቃል ኪዳን
ግንኙነት ውስጥ ሊኖሩ የሚሹትን አሁንም እየቤዣቸውና እንዴት የኃጢአትን ችግር
እየፈታ እንደሆነ የምናይበትን አስደናቂ ዕድል ይሰጠናል።
በዳን. 7 ስለ የፍርድ ምርመራ የቀረበውን መግለጫ ይመልከቱ፡ ዳን. 7:9-
10፣ 13-14፣ 22፣ 26-27። የፍርዱ ሂደት ተቀዳሚ ትኩረት ምንድን ነው።
በሂደቱ መጨረሻ ላይ የተሰጠው ብይን ምንድን ነው? ይህ ስለ ደኅንነት እቅድ
ምን ይነግረናል?
ሰብዓዊው ፍጡር ከእግዚአብሔር ፍርድ መቀበሉን አስመልክቶ የሚነሱ
ጥያቄዎች አነስተኛ ናቸው። “ማንኛውንም ሥራ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ
ያመጣዋል” ሲል—መክ. 12፡14 ማረጋረጫ ይሰጠናል። ጳውሎስ ደግሞ “ሁላችንም
በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ፊት እንቀርባለን” (ሮሜ 14፡10) ስለዚህ አንዳችን
በሌላው ላይ መፍረድ የለብንም ሲል ያስገነዝበናል። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ እግዚአብሔር
ማን እንደ ዳነ ወይም እንደጠፋ ለማወቅ መዝገብ መያዝ አያስፈልገውም። ነገር ግን
የደኅንነትን እቅድ ከመጀመሪያ አንስቶ ሲመረምሩ የነበሩ መላእክት (1ጰጥ. 1፡
12) እንደ ፍጡርነታቸው የራሳቸው ጥያቄ ሊኖራቸው ይችላል። ለሰይጣን አመጽ
ምስክሮች ስለ ነበሩ ከሰማይ መላእክት ሲሦው ከሰማይ ሲባረሩ ተመልክተዋል
(ራእ. 12፡4)። እነሆ አሁን ደግሞ እግዚአብሔር ወደ እርሱ ሐልዎት እያመጣን
ይገኛል። እግዚአብሔር መጻሕፍትን ከፍቶ ቅዱሳን ሁሉን ነገር እንዲያዩ ይፈቅዳል።
አብርሃም ስለ ሰዶም እና ገሞራ ያቀረበውን ምልጃ አስመልክቶ የሚናገረው
ታሪክ ስለ ፍርድ አንዳንድ ጠቃሚ ግንዛቤዎችን ያስጨብጠናል። የሰዶም ኃጢአቶች
እየተመረመሩ እንደነበር እሙን ነው። በከተማይቱ የተንሰራፋው እርክስና ከእርሷ
የሚደመጠውን ጩኸት እጅግ የበረታ እንዳደረገው እግዚአብሔር ይጠቅሳል (ዘፍ፡
18፡20)። ይሁን እንጂ ከመጥፋታቸው አስቀድሞ ምርመራ የተደረገባቸው
ሰዶም እና ገሞራ ብቻ አልነበሩም። እንዲሁም እግዚአብሔር ኃጢአንን ለማጥፋት
የደረሰበት ውሳኔ ፍትሐዊ መሆን አለመሆኑን አብርሃም ይመረምር ዘንድ በሩን
ከፍቶለት እንደ ነበር ልብ ይሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ በሰማያዊው ፍርድ መሃል የሚገለጠውና በዳን. 7
“የሰው ልጅ” ተብሎ የተጠቀሰው የየሱስ (ዳን. 7፡13፣ ማቴ. 20፡28) በዚያ
ስፍራ መገኘት፣ ይህ ፍርድ “ለልዑሉ ቅዱሳን” እንዲፈረድላቸው (ዳን. 7፡22)
የሚያስችል ብቸኛው መንስዔ ይሆናል። ፍጹም የሆነው የእርሱ ጽድቅ ብቻውን
ሕዝቡ ፍርዱን ያለ ነቀፋ እንዲያልፉ ያስችላቸዋል።
ማንኛውም ምስጢር ብለው የያዙት ነገር በእግዚአብሔር ፊት ወለል ብሎ ተገልጦና
በፍርዱ ፊት ቆመው—እስቲ ራስዎን ለመመልከት ይሞክሩ። በዚያ የፍርድ ወቅት
የሚኖርዎ ብቸኛ ተስፋ ምንድን ነው? (የአርብ ጥናትን ይመልከቱ)።
የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት “የጥፋት ውሃ” ከገጽ
92-108—ይመልከቱ።
“ሊቀ ካህኑ ራሱንም ሆነ ሕዝቡን ከሰይጣን ክስ መከላከል አይችልም።
እስራኤል ከበደል ነጻ አለመሆኗን ያምናል። የሕዝቡን ኃጢአት በምሳሌ በሚገልጹ
የጎደፉ ልብሶች እነርሱን ወክሎ በመልአኩ ፊት ይቆማል። በደላቸውን እየተናዘዙ፣
ንስሐቸውንና ውርደታቸውን ወደ ተሸከመው ወደ እርሱ እያመለከቱ ኃጢአታቸውን
ይቅር በሚለው አዳኝ ምሕረት ላይ ይታመናሉ…
“ሰይጣን ጌታን አጥብቀው በሚሹ ወገኖች ላይ የሚያቀርባቸው ክሶች
በኃጢአታቸው ደስተኛ ካለመሆኑ የመነጨ አይደለም። እርሱ እንከን በማያጣቸው
ባህሪዎቻቸው ይከብራል። ምክንያቱም በእነርሱ ላይ ሥልጣን ማግኘት የሚችለው
የእግዚአብሔርን ሕግ በመተላለፋቸው ብቻ እንደሆነ ያውቃል። የክሱ መነሾ
በክርስቶስ ላይ ያለው ጠላትነት ብቻ ነው። የሱስ በደኅንነት እቅድ አማካይነት
ሰይጣን በሰብዓዊው ቤተሰብ ላይ ያለውን ይዞታ በመሰባበር ነፍሳትን ከመዳፉ
መንጭቆ እያዳነ ይገኛል…
“ሰው በራሱ ኃይል የጠላትን ክስ መቋቋም አይችልም። ኃጢአት የበከለውን
አዳፋ ልብስ ለብሶ፣ በደሉን ለመናዘዝ በእግዚአብሔር ፊት ሲቆም፤ ጠበቃችን የሱስ
በንስሐ እና በእምነት ነፍሳቸውን ለእርሱ በአደራ ለመስጠት ቁርጠኞች ለሆኑ
ሁሉ ሕጋዊና ተፈጻሚነት ያለውን ምልጃ ያቀርባል። ስለ እነርሱ ጉዳይ ይሟገታል፤
እናም በግዙፉ የቀራኒዮ መከራከሪያው ከሳሻቸውን ድል ይነሣል። ለእግዚአብሔር
ሕግ ያለው ፍጹም ታዛዥነት በሰማይና በምድር የኃይል ሁሉ ባለቤት ስላደረገው፣
ለበደለኛው ሰው ከአባቱ ምህረት እና እርቅ ማስገኘት ቻለ።”—Ellen G.
White, Prophets and Kings, pp. 583–586.
1. ደቀ መዛሙርቱ በዓለም እንዳሉ ነገር ግን ከዓለም እንዳልሆኑ የሱስ ነግሯቸዋል
ደቀ መዛሙርቱ በዓለም እንዳሉ ነገር ግን ከዓለም እንዳልሆኑ የሱስ ነግሯቸዋል
(ዮሐ. 15፡19፣ 17፡14-16። ዓለምን የማሸነፍ ኃላፊነታችንን ራሳችንን
“ንጹህና ነውር የሌለበት” አድርገን በመጠበቅ ሚዛናዊ የምናደርገው
እንዴት ነው? (ያዕ. 1፡27)።
2. ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ለሕዝቡ ያቀረበው የተማጽኖ አገልግሎት ስለ
ከጥፋት ውሃ በፊት ኖኅ ለሕዝቡ ያቀረበው የተማጽኖ አገልግሎት ስለ
ታላቁ ተጋድሎ አሠራር ምን ያስተምረናል? እኛ ዛሬ ተመሳሳይ ሚና
የምንጫወትባቸው መንገዶች የተኞቹ ናቸው?
3. ኃጥአን ከሰማይ በሚወርድ እሳት ከመበላታቸው አስቀድሞ (በሰዶም
ኃጥአን ከሰማይ በሚወርድ እሳት ከመበላታቸው አስቀድሞ (በሰዶም
እንደሆነው) እግዚአብሔር ከሞት ያስነሣቸዋል፤ ከዚያም ሰይጣን ለአጭር
ጊዜ ከእነርሱ ጋር እንዲሠራ ይፈቅዳል (ራእ. 20፡7-9)። እግዚአብሔር
ሁሉንም ነገር ከማስተካከሉ በፊት ይህ አስፈላጊ የመጨረሻ እርምጃ
ስለመሆኑ ምን ዓይነት ምክንያቶች በአእምሮዎ ሊመጡ ይችላሉ?
4. በዚህ ሳምንት ያጠናናቸውን ትምህርቶች ሲያጤኑ፣ ለገዛ ሕይወትዎ
በዚህ ሳምንት ያጠናናቸውን ትምህርቶች ሲያጤኑ፣ ለገዛ ሕይወትዎ
የሚበጁ ሆነው የሚያገኟቸው ጥንቃቄዎች ምንድን ናቸው? እነዚህ ታሪኮች
በክርስቶስ ላይ ስላሎት ተስፋ ምን ያስተምሮታል?