የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ሉቃ. 13፡34፣ ኤር. 32:17– 20፣ ዕብ. 1:3፣ ዘዳ. 6:4, 5፣ ኤፌ. 1:9–11፣ ዮሐንስ 16፡33።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን
ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤
እኔ አለምን አሸንፌዋለሁ” (ዮሐንስ 16፡33)።
የአምላክ ችሮታ (ፍቃድ) በአለም ውስጥ የእግዚአብሔርን ምግባር
ለመግለጽ የሚያገለግል ቃል ነው። ስለ እግዚአብሔር ችሮታ ያለን
አስተሳሰብ፣ ከእግዚአብሔርና ከሌሎች ጋር ባለን ግንኙነት እና ስለ ክፋት
መከሰትና መዘዝ ባለን እይታ ላይ ትልቅ ለውጥ ያመጣል።
ክርስቲያኖች ስለ መለኮታዊው ችሮታ የተለያዩ ግንዛቤዎች አሏቸው።
አንዳንዶች እግዚአብሔር ኃይሉን ሁሉም ክስተቶች ባሉበት እንዲፈጸሙ
በሚወስን መልኩ እንደሚጠቀም ያምናሉ። ማን እንደሚድን እና ማን እንደሚጠፋ
ሳይቀር ይመርጣል! በዚህ አመለካከት ሰዎች እግዚአብሔር ከወሰነው ውጭ
የመምረጥ ነፃነት የላቸውም። እንዲያውም ይህንን የሚያምኑ ሰዎች የሰው ፍላጎት
እንኳን በእግዚአብሔር ይወሰናል ብለው ይከራከራሉ።
በአንጻሩ አሳማኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስረጃዎች እንደሚያሳዩት
እግዚአብሔር የሚሆነውን ነገር ሁሉ አስቀድሞ አይወስንም። ይልቁንም ከእርሱ
ፈቃድ ውጭ ለመኖር እንኳን እስኪመርጡ ድረስ ለሰዎች (ለመላዕክትም ጭምር)
የመምረጥ ነፃነትን ይሰጣል። የውድቀት፣ የኃጢያትና የክፋት ታሪክ ይህንን
የምርጫ ነፃነት ያላግባብ የመጠቀም ውጤት አስደናቂና አሳዛኝ ማሳያ ነው።
የምርጫ ነጻነት፣ ፍቅር እና መለኮታዊው ችሮታ
የደህንነት እቅድ የተዘጋጀው የምርጫ ነፃነትን ያላግባብ መጠቀም ያስከተለውን
አሳዛኝ ሁኔታ ለማስተካከል ነው።
*የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።
አንድ የልጆች ቄስ "እግዚአብሔር ሉዓላዊ ነው" ሲል የመካከለኛ ደረጃ
ተማሪዎቹን ቡድን ያስተምራል። "ይህ ማለት የሚሆነውን ሁሉ እርሱ ይቆጣጠራል
ማለት ነው።" ግራ የተጋባ አንድ የመካከለኛ ደረጃ ተማሪ፡- “ታዲያ ውሻዬ ሲሞት
እግዚአብሔር ይቆጣጠር ነበር? እግዚአብሔር ውሻዬን ለምን ይገድለዋል?
ይህንን ጥያቄ ለመመለስ የልጆቹ ቄስ እንዲህ አለ፡- “ይህ ከባድ ነው።
ነገር ግን አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በአስቸጋሪ ሁኔታዎች እንድናልፍ አድርጎ
ለወደፊት ይበልጥ አስቸጋሪ ለሆኑ ነገሮች ዝግጁ እንድንሆን ያደርገናል። ውሻዬ
ሲሞት ምን ያህል ከባድ እንደነበር አስታውሳለሁ። ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ውስጥ
ማለፌ በኋላ አያቴ በሞተችበት ወቅት የገጠመኝን የባሰ አስቸጋሪ ጊዜ እንድቋቋም
ረድቶኛል። ይህ ትርጉም ይሰጥሃል?”
ከረዥም ፀጥታ በኋላ፣ የመካከለኛ ደረጃ ተማሪው እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“ስለዚህ አያቴን ሲገድላት ዝግጁ እንድሆን ነው እግዚአብሔር ውሻዬን የገደለው?”—
ማርክ ኮርቴዝ፣ በጆን ሲ. ፔካም የተጠቀሰ፣ መለኮታዊ ባሕርያት፡- የመጽሐፍ
ቅዱሱን የኪዳን አምላክ ማወቅ (ሚቺጋን፡- ቤከር አካዳሚክ፣ 2021)፣ ገጽ. 141.
ሰዎች አንዳንድ ጊዜ የሚሆነው ነገር ሁሉ የሚሆነው እግዚአብሔር
እንዲሆን በሚፈልገው መልኩ ነው ብለው ያስባሉ። በዓለም ላይ የሚሆነው
ማንኛውም ነገር እግዚአብሔር እንዲሆን ስለፈለገ ነው ይላሉ። ደግሞም
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው። ታዲያ እግዚአብሔር እንዳይሆን የሚፈልገው
ነገር እንዴት ሊሆን ይችላል? ስለዚህ ምንም ያህል መጥፎ ቢሆን፣ የሚሆነው
ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ቢያንስ የዚህ ሥነ-መለኮት አስተምሮ
የሚያስተምረው ይህንን ነው።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
መዝ. 81:11–14ን፣ ኢሳ. 30:15, 18ን፣ ኢሳ. 66:4ንና ሉቃ.
13:34ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች የሚሆነው ሁሉ የእግዚአብሔር
ፈቃድ ነው ወይ ለሚለው ጥያቄ ምን ይላሉ?
ብዙ ሰዎች እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚፈልገውን ያደርጋል ብለው
ቢያምኑም፣ መጽሐፍ ቅዱስ የሚናገረው ግን የተለየ ታሪክ ነው። ቃሉ በተደጋጋሚ
እግዚአብሔር ያልተፈጸሙ ምኞቶች እንዳሉት ይገልፃል። ይህ ማለት ብዙ ጊዜ
የሚሆነው ነገር፣ እግዚአብሔር እንዲሆን ከሚፈልገው ነገር ተቃራኒ ነው። በብዙ
አጋጣሚዎች እግዚአብሔር እየሆነ ያለው ነገር እሱ ከሚፈልገው ተቃራኒ መሆኑን
በግልፅ ይናገራል። እርሱ ለሕዝቡ አንድ ነገር እንዲሆንላቸው ፈለገ፣ እነርሱ ግን
በምትኩ ሌላ መረጡ። እግዚአብሔር ራሱ እንዲህ ሲል አዘነ:- “ሕዝቤ ግን ቃሌን
አልሰሙኝም…። ሕዝቤስ ሰምቶኝ ቢሆን፣ እሥራኤልም በመንገዴ ሄደው ቢሆ፣
ጠላቶቻቸውን ፈጥኜ ባዋረድኋቸው ነበር” (መዝ. 81፡11, 13, 14)።
የሚሆነው ነገር ሁሉ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው የሚለውን ማንኛውንም
የሥነ-መለኮት ትምህርት አንድምታ ያሰላስሉ። እንዲህ ዓይነቱ
አስተምህሮ፣ በተለይም ከክፋት አውድ አንጻር፣ምን አይነት የተወሳሰቡ
ችግሮችን ይፈጥራል?
በቃሉ ውስጥ የእግዚአብሔር አስደናቂ ኃይል ተገልጧል። መጽሐፍ
ቅዱስ ኃይሉን ተጠቅሞ ስለ ሰራቸው እጅግ ብዙ ተአምራቶች ይተርካል። ይህም
ቢሆን እግዚአብሔር እንዲሆኑ የማይፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ይከሰታሉ።
ራዕ. 11:17ን፣ ኤር. 32:17–20ን፣ ሉቃ. 1:37ን እና ማቴ. 19:26
የንብቡ። በተጨማሪም ዕብ. 1:3ን ይመልከቱ። እነዚህ ክፍሎች ስለ
እግዚአብሔር ኃይል ምን ያስተምራሉ?
የምርጫ ነጻነት፣ ፍቅር እና መለኮታዊው ችሮታ
እነዚህና ሌሎች ጥቅሶች እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ እንደሆነና ዓለምን
በኃይሉ እንደሚደግፍ ያስተምራሉ። በእርግጥም ራዕይ ደጋግሞ እግዚአብሔርን
“ሁሉን ቻይ ጌታ አምላክ” ሲል ይጠቅሰዋል (ለምሳሌ፡- ራዕ. 11:17፤ ከ2ቆሮ.
6:18፣ ራዕ. 1:8፣ ራዕ. 16:14፣ ራዕ. 19:15፣ ራዕ. 21:22 ጋር ያስተያዩ)። “ሁሉን ቻይ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል ፓንቶክርተር ፍቺው “በሁሉም ላይ ሥልጣን
ያለው” ማለት ነው። የእግዚአብሔር ሁሉን ቻይነት በቃላት ብቻ የተረጋገጠ
ሳይሆን፣ እግዚአብሔር ሕዝቡን ነፃ ለማውጣት ወይም በአለም ላይ በተአምር
ጣልቃ ለመግባት ኃይሉን በሚጠቀምበት ብዙ አስደናቂ አጋጣሚዎች ውስጥ
ተገልጧል።
ይሁን እንጂ እግዚአብሔር “ሁሉን ቻይ ነው” ማለት ማንኛውንም ነገር
ያደርጋል ማለት አይደለም። ቃሉ እግዚአብሔር የማያደርጋቸው አንዳንድ ነገሮች
እንዳሉ ያስተምራል፤ ለምሳሌ፡- 2 ጢሞ. 2፡13 እግዚአብሔር “ራሱን ሊክድ
አይችልምና” ይላል።
በዚህ መሠረት፣ አብዛኞቹ ክርስቲያኖች እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ
እንደሆነ ይስማማሉ፣ ይህ ማለት እግዚአብሔር ተቃርኖ የሌለበትን ማንኛውንም
ነገር የማድረግ ኃይል አለው ማለት ነው — ማለትም ምክንያታዊ የሆነና
ከእግዚአብሔር ማንነት ጋር የሚስማማ ማንኛውንም ነገር ያደርጋል። አንዳንድ
ነገሮች ለእግዚአብሔር የማይቻሉት ተቃርኖ የሚያመጡ ሲሆኑ እንደሆነ
በክርስቶስ የጌቴሴማኒ ጸሎት ላይ በግልጽ ይታያል። ክርስቶስ “በእግዚአብሔር
ዘንድ ሁሉ ይቻላል” (ማቴ. 19፡26) ብሎ ቢያረጋግጥም፣ ስቅለቱ ሲቃረብ ደግሞ
ወደ አባቱ እንዲህ ሲል ጸለየ፡- “አባቴ፥ ቢቻልስ፥ ይህች ጽዋ ከእኔ ትለፍ፤ ነገር ግን
አንተ እንደምትወድ ይሁን እንጂ እኔ እንደምወድ አይሁን አለ” (ማቴ. 26፡39)።
እርግጥ ነው፣ አብ ክርስቶስን በመስቀል ላይ እንዳይሰቃይ ለማዳን
ከፍተኛ ኃይል ነበረው፣ ነገር ግን ኃጢአተኞችን ለማዳን ሲል ይህንን ማድረግ
አይችልም ነበር። ሁለቱም ሳይሆኑ፣ አንዱ ወይም ሌላኛው መሆን ነበረበት።
ደግሞም እግዚአብሔር ሁሉን ማዳን እንደሚፈልግ ቃሉ ያስተምራል
(ለምሳሌ፡- 1ጢሞ. 2፡4–6፣ ቲቶ 2፡11፣ 2 ጴጥ. 3፡9፣ ሕዝ. 33፡
11)፤ ነገር ግን ሁሉም አይድኑም። ይህ እውነታ ስለ ምርጫ ነፃነትና
የምርጫ ነፃነት ለተሰጣቸው ፍጡራን የእግዚአብሔር ኃይል ውስንነት
ምን ያስተምራል?
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ነው ማለት ምክንያታዊ ያልሆነውን ያደርጋል
ማለት አይደለም። በዚህ መሠረት፣ እግዚአብሔር አንድን ሰው በዘፈቀደ በራሱ
ምርጫ እንዲወደው ሊወስን አይችልም። ባጭሩ፣ አስቀድመን እንዳየነውና
በድጋሚ አፅንዖት መስጠት የሚገባን—እግዚአብሔር ማንንም ሰው እንዲወደው
አያስገድድም፤ ግዳጅ ከተጨመረበት፣ ፍቅር ፍቅር ሊሆን አይችልም።
ማቴ. 22:37ንና ዘዳ. 6:4, 5ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለምርጫ
ነፃነት እውነታ ምን ያስተምራሉ?
እግዚአብሔርን ውደድ የሚለው ታላቁ ትእዛዝ፣ እግዚአብሔር
በእርግጥም ሁሉም ሰው እንዲወደው እንደሚፈልግ ያስረዳል። ይሁን እንጂ
ሁሉም ሰው እግዚአብሔርን አይወደውም። ታዲያ ለምንድነው አምላክ ሁሉም
ሰው እንዲወደው የማያደርገው? ምክንያቱም ፍቅር፣ ፍቅር እንዲሆን፣ እንዲሁ
በነፃ መሰጠት ስላለበት ነው።
ዕብ. 6:17, 18ንና ቲቶ 1:2 ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ እግዚአብሔር ምን ያስተምራሉ?
በዘኍ. 23፡19 መሠረት፡- “ሐሰትን ይናገር ዘንድ እግዚአብሔር ሰው
አይደለም” ይላል። እግዚአብሔር ፈጽሞ አይዋሽም (ቲቶ 1: 2)፤ እግዚአብሔር
ሁልጊዜ ቃሉን ይጠብቃል፣ የገባውንም ተስፋ አያጥፍም (ዕብ. 6:17, 18)። ስለዚህ
እግዚአብሔር ተስፋ ከሰጠ ወይም አንድ ነገር ለማድረግ ቃል ከገባ፣ የወደፊት
ድርጊቱ በተስፋው ላይ የተወሰነ ነው።
ይህ ማለት እግዚአብሔር ከሚፈልገውም ውጭ እንዲመርጡ ለፍጡራኑ
የምርጫ ነፃነትን እስከ ሰጠ ድረስ፣ ሰዎች የሚመርጡት የእግዚአብሔር ኃላፊነት
(ጉዳይ) ሊሆን አይችልም። እግዚአብሔር ለፍጡራኑ የምርጫ ነፃነትን ለመስጠት
የምርጫ ነጻነት፣ ፍቅር እና መለኮታዊው ችሮታ
ቃል ከገባ፣ ሰዎች ከአምላክ ምኞት ጋር በሚፃረር መንገድ ነፃነታቸውን የመጠቀም
ችሎታ አላቸው። የሚያሳዝነው፣ ብዙ ሰዎች ነፃነታቸውን በዚህ መንገድ ያላግባብ
ይጠቀማሉ፤ በዚህም መሠረት እግዚአብሔር እንዲሆኑ የማይፈልጋቸው ብዙ
ነገሮች ይፈፀማሉ፣ ነገር ግን ለእነዚህ እግዚአብሔር ተጠያቂ ሊሆን አይችልም፤
ምክንያቱም አይመለከተውምና።
እግዚአብሔር እንዲያደርጉ የማይፈልገውን ምን ነገር አድርገዋል? ይህ
ስለ ምርጫ ነፃነት እውነታና ስለ አስፈሪ ውጤቶቹ ምን ያስተምረናል?
ኤፌ. 1:9–11ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ አስቀድሞ ስለ መወሰን ምን እያለ ነው? አንዳንድ ሰዎች ለመዳን፣ ሌሎች ደግሞ ለመጥፋት አስቀድመው ተወስነዋል?
በዚህ ጥቅስና በሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች “አስቀድሞ መወሰን”
ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል (ፕሮኦሪዞ) አምላክ ታሪክን በምክንያት
ይወስናል ብሎ አያስተምርም። ከዚህ ይልቅ የግሪኩ ቃል “ሳይሆን በፊት መወሰን”
ማለት ነው።
እርግጥ ነው፣ አንድ ሰው በራሱ አንድን ነገር አስቀድሞ ሊወስን ይችላል፣
ወይም የሌሎችን ነፃ ውሳኔ ግምት ውስጥ በማስገባት አንድን ነገር አስቀድሞ
ሊወስን ይችላል። እግዚአብሔር የኋለኛውን አማራጭ ተጠቅሞ እንደሚሰራ
ቃሉ ያስተምራል።
በኤፌ. 1:9–11ና በሌሎች ቦታዎች (ለምሳሌ ሮሜ 8:29, 30) “አስቀድሞ
ወሰነ” ተብሎ የተተረጎመው ቃል እግዚአብሔር አስቀድሞ የሚያውቀውን
የፍጡራኑን ነፃ ውሳኔ ከግምት ውስጥ በማስገባት ወደፊት ያቀደውን ያመለክታል።
ስለዚህ ለእውነተኛ የፍቅር ግንኙነት የሚያስፈልገውን የፍጡራንን ነፃነት
እያከበረ፣ እግዚአብሔር በፈቃዱ ታሪክን ለሁሉም ወደሚመኘው በጎ ዓላማ
መምራት ይችላል።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ኤፌ. 1፡11 እግዚአብሔር “እንደ ፈቃዱ ምክር ሁሉን እንደሚሰራ”
ይናገራል። ይህ ማለት እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደፈለገው እንዲሆን
ይወስናል ማለት ነው? ኤፌ. 1፡9–11 ለብቻው ተነጥሎ ሲነበብ፣ ይህን አመለካከት
የሚደግፍ ሊመስል ይችላል። ሆኖም ይህ አተረጓጎም ሰዎች አንዳንድ ጊዜ
“የእግዚአብሔርን ፈቃድ” እንደማይቀበሉ የሚያሳዩትን ቀደም ሲል ያየናቸውን
ብዙ ጥቅሶች ይቃረናል (ሉቃ. 7፡30፤ ከሉቃ. 13፡34ና መዝ. 81፡11-14 ጋር
ያስተያዩ)። መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን ካልተቃረነ በስተቀር፣ እነዚህን ክፍሎች እርስ
በርሳቸው እንዲስማሙ ሆነው እንዴት ሊስተዋሉ ይችላሉ?
አንድ ሰው በእግዚአብሔር “በጎ ፈቃድ” (ideal will) እና በእግዚአብሔር
“የመፍትሔ ፈቃድ” (remedial will) መካከል ያለውን ልዩነት ከተገነዘበ ይህ
ክፍል ትርጉም ይሰጠዋል። የእግዚአብሔር “በጎ ፈቃድ” እግዚአብሔር እንዲሆን
የሚፈልገው ሲሆን፣ ይህም የሚሆነው እያንዳንዱ ሰው ሁልጊዜ እግዚአብሔር
የሚሻውን በትክክል ካደረገ ነው። በሌላ በኩል የእግዚአብሔር “የመፍትሔ
ፈቃድ” አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር ከሚመርጠው ውጭ የሚሆነውን
የፍጡራንን ነፃ ውሳኔ ጭምር ያገናዘበ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነው። ኤፌ. 1:11
የሚናገረው የአምላክን “የመፍትሔ ፈቃድ” ነው።
እግዚአብሔር ስለ ወደፊቱ ያለው እውቀት አስደናቂ ከመሆኑ የተነሳ፣
ሰዎች የሚያደርጓቸውን ምርጫዎች ሁሉ እያወቀ - መጥፎ ምርጫዎችን
ጨምሮ - "ነገር ሁሉ ለበጎ" እንዲሆን ማድረግ ይችላል (ሮሜ 8:28)።
ከዚህ እውነት ምን ማጽናኛ ማግኘት ይችላሉ?
ሁሉም ነገር እንደ እግዚአብሔር በጎ ፈቃድ ሆኖ ቢሆን ኖሮ፣ ፍጹም
የሆነ የፍቅርና የስምምነት ደስታ ብቻ እንጂ ክፋት በፍፁም አይኖርም ነበር።
በመጨረሻ አለማት ወደዚህ ፍጹምና በጎ የሆነ የእግዚአብሔር ፈቃድ ይመለሳሉ።
እስከዚያው ድረስ ግን እግዚአብሔር የፍጡራኑን ነፃ ውሳኔ ግምት ውስጥ ባስገባ
መልኩ ፈቃዱን እየፈፀመ ነው።
ሁሉም ተሳታፊዎች የተወሰኑ ንጥረ ነገሮችን እንዲጠቀሙ የሚያስገድድ
የምርጫ ነጻነት፣ ፍቅር እና መለኮታዊው ችሮታ
የኬክ መጋገር ውድድርን ያስቡ፣ ነገር ግን የሚፈልጉትን ኬክ ለመጋገር የፈለጉትን
ሌላ ማንኛውንም ንጥረ ነገር መጨመር ይችላሉ ። ዞሮ ዞሮ ጋጋሪው የሚሠራው
የትኛውም ዓይነት ኬክ፣ በከፊል ጋጋሪው ባልመረጠው አንዳንድ ንጥረ ነገሮች
ይወሰናል።
በተመሳሳይ እግዚአብሔር ለፍቅር አስፈላጊ የሆነውን የፍጡራንን
ነፃነት ስለሚያከብር፣ የዓለምን ታሪክ የሚወስኑት ብዙዎቹ “ንጥረ ነገሮች”
በእግዚአብሔር የተመረጡ ሳይሆኑ፣ እንዲያውም እግዚአብሔር ከሚፈልገው
ተቃራኒዎች ናቸው።
በዚህ አመለካከት፣ እግዚአብሔር የሚሆነውን ሁሉ ብቻውን የሚቆጣጠር
ይመስል፣ መለኮታዊው ችሮታ ዝም ብሎ በአንድ ገፅታ የሚታይ አይደለም።
ይልቁንስ ይህ የእግዚአብሔር ችሮታ ቢያንስ ባለ ሁለት ገፅታ እይታን ይፈልጋል።
በዚህ ዓለም ውስጥ ያሉ አንዳንድ ነገሮች በእግዚአብሔር የሆኑ ናቸው፣ ሌሎች
ክስተቶች ግን የፍጡራን ነፃ ውሳኔ ውጤቶች ናቸው (ሁሉንም ክፋት ጨምሮ)።
እግዚአብሔር እንዲሆኑ የማይፈልጋቸው ብዙ ነገሮች ይከሰታሉ።
ዮሐ. 16:33ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ በመከራም ውስጥ ቢሆን ምን ተስፋ
ይሰጠናል?
ሰዎች በምድር ሲኖሩ እግዚአብሔር ከመከራና ከፈተና ሊያድነን
ይገባል የሚል የተሳሳተ እምነት ስላላቸው፣ በተለይ በመከራ ወይም በፈተና ጊዜ
እምነታቸው ሊናወጥ ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስ ለተከታዮቹ በዚህ ዓለም ፈተናና
መከራ እንደሚደርስባቸው አስጠንቅቋቸዋል፤ ሆኖም ተስፋ አለን፣ ክርስቶስ ዓለምን አሸንፏልና (ዮሐ. 16፡33)።
መከራና ፈተና ገጠመን ማለት ግን አምላክ ለእኛ እንዲሆንልን የሚመኘው
ይህ ነው ማለት አይደለም። ሁልጊዜም የታላቁን ተጋድሎ እውነታ ማስታወስ
አለብን። ሆኖም ግን እርግጠኛ መሆን የምንችለው ነገር፣ ምንም እንኳን ክፋት
እንደ ቅድመ ሁኔታ ለበጎ ነገር አስፈላጊ ባይሆንም፣ እግዚአብሔር ከክፉ ክስተቶች
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ውስጥ እንኳን መልካምን ሊያመጣ ይችላል። በእግዚአብሔር ብንታመን፣
መከራችንንም እንኳን ወደ እርሱ እንድንቀርብና ለሌሎችም እንድንራራላቸውና
እንድንጠነቀቅላቸው ለማድረግ ሊጠቀምበት ይችላል።
የዘመናት ምኞት ከተባለው የኤለን ጂ. ኋይት መጽሐፍ
“እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” የተሰኘውን ርዕስ ከገጽ 19–26 ያንብቡ።
“የእኛ የደህንነት እቅድ ከአዳም ውድቀት በኋላ የተነደፈ አልነበረም።
ይልቅስ ‘ከዘላለም ዘመንም የተሰወረው‘ ምስጢር ተገለጠ (ሮሜ 16፡25)። ከዘመናት በፊት የእግዚአብሔር ዙፋን መሠረት የሆነው መርህ ተዘረጋ። ገና ከጅምሩ እግዚአብሔር እና ክርስቶስ የሰይጣንን ክህደት እና በአታላዩ አማካኝነት የሰው ዘር እንደሚወድቅ ያውቁ ነበር። ኃጢአት እንዲኖር የእግዚአብሔር ፈቃድ አልነበረም፣ ነገር ግን የኃጢአትን መከሰት አስቀድሞ ተመለከተ፣ እናም አስፈሪውን አደጋ ለመቀልበስ ሁኔታዎችን አዘጋጀ። ለዓለማችን የነበረው ፍቅር ታላቅ ስለነበር፣ ‘በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ’ አንድያ ልጁን ለመስጠት ቃል ኪዳን ገባ (ዮሐ. 3፡16)።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 22.
የምርጫ ነጻነት፣ ፍቅር እና መለኮታዊው ችሮታ
1. እግዚአብሔር ሁልጊዜ የሚፈልገውን የማያገኝ ከሆነ፣ ይህ እውነታ
በዓለም ውስጥ ስለሚሆነው ነገር ያለህን አመለካከት እንዴት ይቀይረዋል? እግዚአብሔር ያልተሟሉ ምኞቶች እንዳሉት መረዳት
አንድምታው ምንድን ነው?
2. የሐሙሱን የኬክ ምሳሌ ጥናት ከተመለከትን፣ ምንም እንኳን
"እግዚአብሔርና ክርስቶስ የሰይጣንን ክህደት ያውቁ የነበረ
ቢሆንም"፣ እኛን ለምን እንደፈጠሩን እንረዳለን። ፍቅር
ከሚቀላቀሉት ንጥረ ነገርች ውስጥ መሆን ነበረበት፣ ፍቅርም
ነፃነትን ይሰጣል። እግዚአብሔር እኛን መውደድ እንድንችል
አድርጎ ነው የፈጠረን፣ ነገር ግን ይህ ኢየሱስን ወደ መስቀል
እንደሚመራው እያወቀ ነበር ያደረገው። የፍቅር አካል የሆነውን
ነፃነት ከሚነፍገን ይልቅ ክርስቶስ በመስቀል ላይ መከራን መቀበሉ፣
ፍቅር ለእግዚአብሔር መንግሥት ምን ያህል የተቀደሰና መሠረታዊ
መሆኑን ይህ ምን ይነግረናል?
3. ብዙ ጊዜ በዚህ አለም ውስጥ ስላለው ክፋትና ስቃይ እናዝናለን፣
ነገር ግን እግዚአብሔር ራሱ በመከራና በክፋት እንደሚያዝን
ለማሰላሰል ምን ያህል ጊዜ ይወስዳሉ? እግዚአብሔር ራሱ በክፋት
ምክንያት እንደሚሠቃይ ማወቁ፣ ስለ ክፋትና መከራ ባለዎት
መረዳት ላይ ምን ልዩነት ያመጣል?
4. እግዚአብሔር የማይፈልጋቸው ብዙ ነገሮች በዚህ ዓለም ውስጥ
የመሆናቸው እውነታ፣ በተለይ ትርጉም የማይሰጥና ምንም ዓይነት
መልካም ነገር የማያመጣ የሚመስል ሥቃይ ሲደርስብህ ለመቋቋም
የሚረዳህ እንዴት ነው?