የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- መዝ. 78፣ ዮና. 4:1–4፣
ማቴ. 10:8፣ ማቴ. 21:12, 13፣ ኤር. 51:24, 25፣ ሮሜ. 12፡17–21።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እርሱ ግን መሓሪ ነው፥ ኃጢአታቸውንም
ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም
ሁሉ አላቃጠለም” (መዝ. 78፡38)።
ብዙ ጊዜ የእግዚአብሔር ርኅራኄ ቢወደስም፣ የቁጣው ነገር ብዙዎችን
ይረብሻቸዋል። እግዚአብሔር ፍቅር ከሆነ፣ ቁጣውን ፈጽሞ መግለጽ
የለበትም ብለው ያስባሉ። ይህ አመለካከት ግን የተሳሳተ ነው።
ቁጣው በቀጥታ የሚመነጨው ከፍቅሩ ነው።
አንዳንዶች የብሉይ ኪዳኑ አምላክ የቁጣ አምላክ እንደሆነ እና የአዲስ
ኪዳኑ አምላክ ደግሞ የፍቅር አምላክ እንደሆነ ይናገራሉ። ነገር ግን አንድ አምላክ
ብቻ ነው ያለው፤ በሁለቱም ኪዳናት ተመሳሳይ እንደሆነ ተገልጿል። ፍቅር
የሆነው እግዚአብሔር በክፋት ላይ ይቆጣል—ምክንያቱ ደግሞ እሱ ፍቅር ስለሆነ
ነው። ኢየሱስ ራሱ በክፋት ላይ ጥልቅ ቁጣውን ገልጿል፤ አዲስ ኪዳንም ጻድቅና
ተገቢ ስለሆነው የእግዚአብሔር ቁጣ ብዙ ጊዜ ያስተምራል።
የእግዚአብሔር ቁጣ ሁልጊዜ በክፋትና በኢ-ፍትሐዊነት ላይ የሚገለጽ
የጽድቅና የፍቅር ምላሽ ነው። መለኮታዊው ቁጣ ከፍፁም መልካምነቱና ፍቅሩ
የተነሳ የሚመጣ የጽድቅ ቁጣ ነው፤ እናም የፍጥረትን ሁሉ ደህንነት ይሻል።
ባጭሩ የእግዚአብሔር ቁጣ የምንለው ለክፋትና ለኢ-ፍትሐዊነት የሚሰጥ ተገቢ
የሆነ የፍቅር ምላሽ ነው። ስለዚህ ክፋት እግዚአብሔርን የተገፉትን ለማዳን እና
በአጥፊዎቹም ለመፍረድ እንዲነሳ ያደርገዋል። እንግዲህ መለኮታዊው ቁጣ
የመለኮታዊ ፍቅር ሌላው ገጽታ ነው ማለት ነው።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
*የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።
የመጽሐፍ ቅዱሱ አምላክ ፍትሕን ይወዳል፣ ክፋትንም ይጠላል። ስለዚህ
ኃጢአትና ክፋት እርሱን ለተጨቆኑና ለተበደሉ በስሜት እንዲነሳ ያደርገዋል -
የአንድ ሰው ክፋት በዋነኝነት ራሱን በሚጎዳበት ጊዜም ማለት ነው። እግዚአብሔር
ክፋትን የሚጠላው ክፋት ሁልጊዜ ፍጡራኑን ስለሚጎዳ ነው - ምንም እንኳን
ጉዳቱን ሰው በራሱ ላይ ቢያመጣውም። በቃሉ እንደተገለጸው፣ በተደጋጋሚ
የተነሳው የአመፅ ዑደት እግዚአብሔርን በቁጣ እንዲነሳ አድርጎታል። ዑደቱም
እንደሚከተለው ነው፡-
ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ በማመፅ ክፉ ይሰራሉ፣ አንዳንዴ
ልጆቻቸውን በመሰዋት እና ሌሎች አጸያፊ ድርጊቶችን በፊቱ በማድረግ አሰቃቂ
ግፍ ይፈጽማሉ።
እግዚአብሔር በእነርሱ ውሳኔ ምክንያት ከእነርሱ ይለያል።
ሕዝቡ በባእድ አገራት ይጨቆናል።
ሕዝቡ እግዚአብሔር እንዲያድናቸው ይጮሃሉ።
እግዚአብሔር በቸርነቱ ሕዝቡን ያድናቸዋል::
ሕዝቡ እንደገና ከፊት ይልቅ በከፋ ሁኔታ በእግዚአብሔር ላይ ያምጻሉ።
በዚህ አስከፊ የክፋት እና የክህደት አዙሪት ውስጥ እንኳን፣ የሰውን
አለመታመን እግዚአብሔር ወሰን በሌለው ታማኝነት፣ በትዕግስት፣ በሚያስደንቅ
ጸጋ እና ጥልቅ ርኅራኄ ደጋግሞ ይገናኘዋል።
መዝ. 78ን ያንብቡ። ለሕዝቡ ተደጋጋሚ አመጽ የእግዚአብሔር ምላሽ
ምን እንደሆነ ይህ ክፍል ምን ይነግረናል?
የመለኮታዊው ፍቅር ቁጣ
በመጽሐፍ ቅዱስ ፍቅርና ፍትሕ እንዳይነጣጠሉ ሆነው የተጋመዱ
ናቸው። መለኮታዊው ቁጣ በክፉ ላይ የሚመጣ ትክክለኛ የፍቅር ምላሽ
ነው፣ ምክንያቱም ክፋት ሁልጊዜ እግዚአብሔር የሚወደውን ሰው ይጎዳል።
በቃሉ ውስጥ እግዚአብሔር በዘፈቀደ ወይም ያለ አግባብ የተቆጣበት ወይም
የተናደደበት ሁኔታ የለም።
ሕዝቡ ደጋግመው እግዚአብሔርን ቢተውትና ቢክዱትም፣
ከምንጠብቀው በላይ እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ በትዕግሥት ራርቶላቸዋል
(ነህ. 9፡7–33)። በዚህም የማይመረመረውን ጥልቅ ትዕግሥት የተሞላውን
ርኅራኄ እና መሐሪ የሆነውን ፍቅሩን አሳይቷል። በእርግጥም እንደ መዝ. 78:
38 እግዚአብሔር “መሓሪ (ሩኅሩኅ) ነው፥ ኃጢአታቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፤ ቍጣውንም መመለስ አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም”።
በእርግጠኝነት በሌሎች ላይ በተፈፀመው ክፋት ተቆጥተው ያውቃሉ።
ታዲያ ይህ ስሜት በክፋት ላይ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቁጣ
በተሻለ ሁኔታ እንዲረዱት የሚረዳዎት እንዴት ነው?
እግዚአብሔር በክፋት ላይ የሚቆጣው ፍቅር ስለሆነ ነው። እግዚአብሔር እጅግ ርህሩህና ቸር ስለለሆነ፣ አንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢይ ከምሕረቱ ብዛት የተነሳ በእግዚአብሔር ላይ አጉረመረመ! የዮናስን ታሪክ ይመልከቱ። በዮና. 4፡1–4 ውስጥ እግዚአብሔር ለነነዌ ሰዎች ላደረገው ርኅራኄ የተሞላ ይቅርታ የዮናስን ምላሽ ያሰላስሉ። ይህ ስለ ዮናስ እና ስለ እግዚአብሔር ምን ይነግረናል? (ማቴ. 10:8ንም ይመልከቱ)
ዮናስ ለእግዚአብሔር ምሕረት የሰጠው ምላሽ በሁለት ዋና ዋና
መንገዶች ይታያል። በመጀመሪያ የዮናስን ልበ ደንዳናነት ያሳያል። አሦራውያን
በእሥራኤላውያን ላይ ስላደረጉት ነገር እጅግ ስለጠላቸው፣ እግዚአብሔር
እንዲምራቸው አልፈለገም።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ለእኛ እንዴት ያለ ትምህርት ነው! ምንም እንኳን ሁኔታው ምክንያታዊ
ቢሆንም፣ ከእንደዚህ አይነት ተመሳሳይ አመለካከት መጠበቅ ይኖርብናል።
ከሌሎች ሁሉ ይልቅ የእግዚአብሔርን ጸጋ የተቀበሉ፣ ጸጋ ምን ያህል የማይገባን
ስጦታ እንደሆነ ተገንዝበው፣ ጸጋን ለሌሎች ለመለገስ ፈቃደኛ መሆን አለባቸው።
በሁለተኛ ደረጃ የዮናስ ምላሽ የእግዚአብሔር ርኅራኄና ጸጋ የባሕርይው
እምብርት መሆናቸውን ያጠናክራል። ዮናስ የእግዚአብሔርን ምሕረት በሚገባ
ስለሚያውቅ፣ እግዚአብሔር “ቸርና ይቅር ባይ” እንዲሁም “ለቁጣ የዘገየ ምሕረቱም
የበዛ“ ስለሆነ፣ ጌታ በነነዌ ላይ ከመፍረድ እንደሚፀፀት ያውቅ ነበር (ዮና. 4፡2)።
እግዚአብሔር ሁሉንም ህዝቦች በፍትሃዊነትና በምሕረት ይዳኛቸዋል።
“ለቁጣ የዘገየ” ወይም “ታጋሽ” ተብሎ የተተረጎመው የዕብራይስጥ ሐረግ
“አፍንጫ ረጅም” ተብሎ ቃል በቃል ሊተረጎም ይችላል። በዕብራይስጥ ፈሊጥ፣
ቁጣ በምሳሌያዊ አነጋገር ከአፍንጫ ጋር ይዛመድ ነበር፣ እናም የአፍንጫ ርዝማኔ
አንድ ሰው ለመናደድ የሚወስድበትን ጊዜ ያሳያል።
አምላክ “አፍንጫ ረጅም” ተብሎ መጠራቱ ለቁጣ የዘገየና ታጋሽ መሆኑን
ያሳያል። ሰዎች ለመናደድ ብዙ ጊዜ ባይወስድባቸውም፣ እግዚአብሔር ግን እጅግ
ታጋሽ እና ጸጋውን በነፃ አብዝቶ የሚሰጥ ነው፤ ነገር ግን ኃጢአትን አያጸድቅም
ወይም ከኢ-ፍትሃዊነት ፊቱን አያዞርም። ይልቁንም እግዚአብሔር ጻድቅ እና
በእርሱ የሚያምኑትን የሚያጸድቅ ስለሆነ ራሱ በመስቀሉ በኩል ኃጢአትንና
ክፋትን ያስተሰርያል (ሮሜ 3፡25፣26)።
ለበደላችሁ ሰው ምሕረትን ወይም ጸጋን ማሳየት አቅቷችሁ ያውቃል?
እግዚአብሔር ላሳየህ የተትረፈረፈ ጸጋ ምላሽ በመስጠት፣ ለሌሎች የበለጠ
ቸር እንድትሆን፣ እግዚአብሔር ያደረገልህን እንዴት በተሻለ ሁኔታ
ልታስታውስ ትችላለህ? ኃጢአትን ሳንፈቅድ ወይም በደልንና ጭቆናን
ሳናበረታታ፣ ለሌሎች ምሕረትን እና ጸጋን እንዴት እናሳያቸዋለን?
ብዙ ተገቢ ያልሆኑ ቁጣዎች ቢኖሩም መጽሐፍ ቅዱስ “የጽድቅ ቁጣ”
እንዳለ ያስተምራል።
የመለኮታዊው ፍቅር ቁጣ
አንዲት እናት የሦስት ዓመት ሴት ልጇን በመጫወቻ ስፍራ ስትጫወት
እየተመለከተች ሳለ፣ በድንገት አንድ ሰው በልጇ ላይ ጥቃት እንዳደረሰባት ያስቡ።
ታዲያ መቆጣት የለባትምን? በደንብ አንጂ። እንደዚህ ባለ ሁኔታ ውስጥ፣ ቁጣ
የፍቅር ተገቢው ምላሽ ነው። ይህ ምሳሌ የአምላክን “የጽድቅ ቁጣ” እንድንገነዘብ
ይረዳናል።
ማቴ. 21:12, 13ን እና ዮሐ. 2:14, 15ን ያንብቡ። ኢየሱስ ቤተ-
መቅደሱን ይገለገሉበት ለነበረው ሁኔታ የሰጠው ምላሽ፣ እግዚአብሔር
በክፉ ላይ እንደሚቆጣ ምን ይነግረናል?
በእነዚህ ሁኔታዎች የአምላክን ቤተ-መቅደስ አርክሰውና “የወንበዴዎች ዋሻ”
አድርገው መበለቶችን፣ ወላጅ አልባ ልጆችን እና ድሆችን በሚበዘብዙት ላይ ኢየሱስ
"አምላካዊ ቅንዓት" የሆነውን የጽድቅ ቁጣ አሳይቷል (ማቴ. 21:13ን ከዮሐ. 2:16 ጋር
ያስተያዩ)። የእግዚአብሔርን ይቅርታና ኃጢአተኞችን ማንጻቱን የሚያመለክቱት
ቤተ-መቅደሱና አገልግሎቶቹ፣ በምትካቸው ምስኪኖችን ለማጭበርበር እና
ለመጨቆን ይውሉ ነበር። ኢየሱስ በዚህ ርኩሰት መቆጣት አልነበረበትምን?
ማር. 10:13, 14 እና ማር. 3:4, 5 የጽድቅ ቁጣውን የሚያሳዩ ተጨማሪ
ምሳሌዎችን ይሰጡናል። ሰዎች ሕፃናትን ወደ ኢየሱስ ሲያመጡና “ደቀ መዛሙርቱ
ያመጡአቸውን ሲገሥጿቸው”፣ ኢየሱስ “በጭራሽ አልተደሰተም” - “ተቈጣ”
እንጂ። እርሱም፡- “ሕፃናትን ወደ እኔ ይምጡ ዘንድ ተው አትከልክሉአቸው”
አላቸው (ማር. 10:13, 14)።
በሌላ ቦታ፣ ፈሪሳውያን ኢየሱስን በሰንበት በመፈወሱ ሕግን እንደ ጣሰ
ለመክሰስ ሲጠባበቁ፣ ኢየሱስ “በሰንበት በጎ ማድረግ ተፈቅዶአልን? ወይስ ክፉ?
ነፍስ ማዳን ወይስ መግደል?” ሲል ጠየቃቸው (ማር. 3፡4)። “ስለ ልባቸውም
ድንዛዜ አዝኖ ዙሪያውን እየተመለከተ በቍጣ አያቸውና” ሰውየውን ፈወሰው
(ማር. 3፡5)። የክርስቶስ ቁጣ እዚህ ላይ በደንዳናነታቸው ማዘኑን ያሳያል።
በብሉይ ኪዳን እንደተገለጸው፣ ይህ ከፍቅር የሚመነጭ የጽድቅ ቁጣ ነው።
በተለይ ክፋት የፍቅሩን ኢላማዎች ሲጎዳ፣ ፍቅር በክፋት ላይ እንዴት አይቆጣም?
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ራስ ወዳድ የሆነን ቁጣ “የጽድቅ ቁጣ” ነው ብለን እንዳናስብ መጠንቀቅ
ያለብን እንዴት ነው? ይህን ማድረግ ቀላል የሚሆነው ለምንድን ነው? ራሳችንንስ
ከዚህ ስውር ግን ተጨባጭ ወጥመድ እንዴት መጠበቅ እንችላለን?
በመላው መጽሐፍ ቅዱስ፣ እግዚአብሔር ለተገፉና ለተጨቆኑ
እንደሚያዝንላቸው እና የጽድቅ ቁጣውን ደግሞ በአስጨናቂዎቻቸውና
በጨቋኞቻቸው ላይ እንደሚያመጣ እየደጋገመ ያሳያል። ክፋት ባይኖር
እግዚአብሔር አይቆጣም ነበር። ቁጣው ሁልጊዜ ፍጥረቱን በሚጎዳው ነገር ላይ
ብቻ ነው።
እንደ ሰቆ. ኤር. 3:32, 33 እግዚአብሔር ሆን ብሎ “ከልቡ” አያስጨንቅም።
በክፉ አድራጊዎች ላይ መፍርድ አይፈልግም፣ ነገር ግን ፍቅር በመጨረሻ ፍትሕን
ይሻል።
ይህ እውነት እግዚአብሔር ሕዝቡን ለረጅም ጊዜ ይቅር በማለቱ እና
ንስሐ እንዲገቡና ከእሱ ጋር እንዲታረቁ እድሎችን ደጋግሞ በመስጠቱ ታይቷል።
በተደጋጋሚ እግዚአብሔር ሕዝቡን በነቢያቱ አማካኝነት ጠርቷቸዋል፣ ነገር ግን
እነርሱ ለማድመጥ ፈቃደኛ አልነበሩም (ኤር. 35፡14–17ን፣ መዝ. 81፡11–14ን
ይመልከቱ)።
ዕዝ. 5:12ን አንብበው ከኤር. 51:24, 25, 44 ጋር ያስተያዩ። ይህ
በባቢሎናውያን በኩል በኢየሩሳሌም ላይ ስለመጣው ፍርድ ምን
ይገልጻል? ( 2 ዜና 36:16ንም ይመልከቱ)
ዕዝ. 5 እንደሚለው ሕዝቡ በእምቢተኝነትና ያለማቋረጥ እግዚአብሔርን
ካስቆጡ በኋላ፣ እርሱ በመጨረሻ ተዋቸውና ሕዝቡን “በባቢሎን ንጉሥ
በናቡከደነፆር እጅ አሳልፎ ሰጣቸው” (ዕዝ. 5፡12)። ይሁን እንጂ አምላክ ይህን
ያደረገው “መድኃኒት ስላላገኘላቸው” ብቻ ነው (2 ዜና. 36:16)። የኋላ ኋላ ግን
የመለኮታዊው ፍቅር ቁጣ
አምላክ ባቢሎንን በይሁዳ ላይ ባደረሰችው ከመጠን ያለፈ ውድመት ፈርዶባታል
(ኤር. 51:24, 25, 44 ፤ ከዘካ. 1:15 ጋር ያስተያዩ)።
ቃሉ እግዚአብሔር እንዳመጣባቸው የሚገልጻቸው ሌሎች በርካታ
ፍርዶች፣ ሕዝቡ ጌታን በመተው የአሕዛብን “አማልክት” ለማገልገል ስለወሰኑ
(መሳ. 10፡6–16፣ ዘዳ. 29፡24–26)፣ አምላክ ሕዝቡን ለጠላቶቻቸው አሳልፎ
መስጠቱን የሚያሳይ ነው (መሳ. 2:13, 14፣ መዝ. 106:41, 42)። እግዚአብሔር
በክፋት ላይ ያለው ቁጣ የሚመነጨው ለሁሉ ካለው ፍቅርና ለዓለማት ካለው
የደህንነት ፍላጎት ነው። ዓለማት ስለ ኃጢአት፣ አመፅና ክፋት ጥያቄ ውስጥ
ናቸው። በመጨረሻም ክፋትን ሁሉ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ያጠፋዋል።
አምላክ በማንም ላይ ፍርድ ለማምጣት የማይፈልግ የመሆኑ እውነታ፣
ስለ መለኮታዊው ቁጣ ያለህን ግንዛቤ የሚቀይረው እንዴት ነው?
አምላክ ለቁጣ የዘገየ ከሆነ፣ በዙሪያችን ላሉ ሰዎች የበለጠ ታጋሽ መሆን
አይገባንምን? በደል የደረሰባቸውን ሰዎች በመከላከልና በመንከባከብ
ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?
መለኮታዊው ቁጣ “አስፈሪ” ቢሆንም፣ በምንም መንገድ አግባብ ያልሆነ
ወይም ፍቅር የለሽ አይደለም። በተቃራኒው፣ በብሉይ እና በአዲስ ኪዳን፣
እግዚአብሔር ከፍቅሩ የተነሳ በክፋት ላይ ቁጣውን ይገልፃል። መለኮታዊውን
ቁጣ አስፈሪ የሚያደርገው፣ ከእግዚአብሔር ፍጹም መልካምነትና ግርማ ጋር
ሲነጻጸር የክፋት ተንኮለኛ መሆን ነው።
በዚህ ረገድ ፍቅር ለእግዚአብሔር አስፈላጊ ሲሆን ቁጣ ግን አይደለም።
ክፋት ወይም ግፍ በሌለበት ቁጣ የለም። በመጨረሻም፣ የአምላክ ክፋትን ከዓለም
የማጥፋት የፍቅር እርምጃ፣ ቁጣን ያስወግዳል። ይህም የሚሆነው ዳግመኛ ግፍ
ወይም ክፋት ስለማይኖር ነው። ፍጹም በሆነ የፍቅር ግንኙነት፣ ደስታ እና ፍትሕ
ብቻ ለዘላለም ይሰፍናሉ። ዳግመኛ መለኮታዊ ቁጣ የሚያስፈልግበት ምክንያት
በጭራሽ አይኖርም። እንዴት ያለ ድንቅ ነገር ነው!
አንዳንዶች መለኮታዊው ቁጣ ሳይታሰብ ለሰዎች በቀል ፈቃድ እንደሚሰጥ
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል ብለው ይጨነቃሉ። ዘዳ. 32:35ን፣ ምሳ.
20:22ን፣ ምሳ. 24:29ን፣ ሮሜ 12:17–21ን፣ እና ዕብ. 10:30ን
ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች የሰው በቀል አላስፈላጊ መሆኑን የሚገልጹት
እንዴት ነው?
ቃሉ እንደሚናገረው፣ እግዚአብሔር ፍርድን የማምጣት መብት አለው፣
ሲፈርድም ሁልጊዜ ፍጹም በሆነ ፍትሕ ነው። ብሉይ እና አዲስ ኪዳን በቀል
የእግዚአብሔር እንደሆነ በግልፅ ይናገራሉ። ጳውሎስ በሮሜ 12፡19 “ተወዳጆች ሆይ፥
ራሳችሁ አትበቀሉ፥ ለቍጣው ፈንታ ስጡ እንጂ፤ በቀል የእኔ ነው፥ እኔ ብድራቱን
እመልሳለሁ ይላል ጌታ ተብሎ ተጽፎአልና” ይላል (ከዘዳ. 32፡35 በመጥቀስ)።
እግዚአብሔር በመጨረሻ በኢ-ፍትሐዊነትና በክፋት ላይ ፍርድን
ሲያመጣ፣ ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ መንገድን አዘጋጅቷል። በእርግጥም
“ከሚመጣው ቁጣ የሚያድነን ኢየሱስ” ነው (1 ተሰ. 1:10፤ ከሮሜ 5:8, 9 ጋር
ያስተያዩ)። ይህ ደግሞ የእግዚአብሔር እቅድ ነው፡- " እግዚአብሔር ለቍጣ
አልመረጠንምና፥ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ መዳንን ለማግኘት ነው እንጂ"
(1ኛ ተሰ. 5፡9)። መለኮታዊው ቁጣ አይሻርም፣ ነገር ግን በኢየሱስ የሚያምኑ
በክርስቶስ ምክንያት ከዚህ ቁጣ ይድናሉ።
የክርስቶስ የስርየት አገልግሎት ፍትሕን አስከብሮ እኛን ግን ከቁጣ
የሚያድነን በምን መንገድ ነው? ደካማም ብትሆን የመዳን መንገድ
ለአንተ እንደተዘጋጀልህ መገንዘብህ፣ ለሌሎች አብልጠህ ምን ያህል
ይቅር ባይ መሆን አለብህ?
አበው እና ነቢያት ከሚለው የኤለን ጂ. ዋይት
መጽሐፍ “በሲና የጣዖት አምልኮ” የተሰኘውን ርዕስ ከገጽ 315–330 ያንብቡ።
ከወርቅ ጥጃው ኃጢአት አንጻር ኤለን ጂ. ዋይት እንዲህ በማለት ጽፋለች:-
“እሥራኤላውያን አምላክን በመካድ በደለኞች ነበሩ፣ ይህንም ያደረጉት በበረከት
በሞላቸውና ለስልጣኑም በፈቃዳቸው ለመታዘዝ ቃል በገቡለት ንጉሥ ላይ ነበር።
መለኮታዊው መንግሥት እንዲጸና፣ ከሃዲዎቹ ሊፈረድባቸው ይገባ ነበር። ግን
የመለኮታዊው ፍቅር ቁጣ
እዚህም ላይ የእግዚአብሔር ምሕረት ታይቷል። ሕጉን ቢያፀናም፣ የምርጫ ነፃነትንና
ንስሐ የመግባት እድልን ለሁሉም ሰጣቸው። በዓመፅ የጸኑት ብቻ ተቀሰፉ።
“እግዚአብሔር በጣዖት አምልኮ ደስ እንደማይሰኝ በዙሪያው ላሉት አሕዛብ
ምስክር እንዲሆን በዚህ ኃጢአት ላይ እርምጃ መወሰድ ነበረበት። በበደለኞቹ ላይ
በመፍረድ፣ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነው ሙሴ፣ በወንጀላቸው ላይ የከበረ
ሕዝባዊ ተቃውሞን በመዝገብ ላይ ማስቀመጥ ነበረበት። እሥራኤላውያን ከዚህ
በኋላ በዙሪያቸው የነበሩትን ነገዶች የጣዖት አምልኮ ሲያወግዙ፣ ያህዌ አምላካችን
ነው ያለው ሕዝብ በኮሬብ የወርቅ ጥጃ ሠርቶ እንዳመለከው ይከሷቸዋል።
ምንም እንኳን አሳፋሪ የሆነውን እውነት ለመቀበል ቢገደዱም፣ እሥራኤላውያን
በተላላፊዎች ላይ የደረሰውን አስፈሪ ቅጣት በማመልከት፣ ኃጢአታቸው
እንዳልተፈቀደ ወይም እንዳልታለፈ ያስረዳሉ።
“ከፍትሕ ባልተናነሰ ሁኔታ ፍቅር ለዚህ ኃጢአት ፍርድ እንዲሰጥ አድርጓል።
. . . በሚሊዮኖች ላይ ሊመጣ ያለውን ፍርድ ለማስቀረት፣ በሺዎች የሚቆጠሩ
መሰቃየታቸው የእግዚአብሔርን ምሕረት ያሳይ ነበር። ብዙዎችን ለማዳን፣ ጥቂቶቹን
መቅጣት ነበረበት።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ አበው እና ነቢያት፣ ገጽ 324, 325
1. ብዙ ሰዎች መለኮታዊ ቁጣ የሚለውን ጽንሰ-ሐሳብ መቀበል
የሚከብዳቸው ለምን ይመስላችኋል? እንድታስተውለው የሚረዳህ
ምንድን ነው?
2. ሰዎች በቀል ሲፈልጉ የሚመጡ፣ እግዚአብሔር ሲሻ ግን የማይከሰቱ
ቁጣዎች ምን ችግሮች ያስከትላሉ?
3. ከወርቅ ጥጃው አመፅ በኋላ አምላክ በእሥራኤል ላይ ያመጣው ፍርድ
የመለኮታዊ ምሕረት ምሳሌ የሆነው እንዴት ነው? የእግዚአብሔር
ፍርድ ራሱ የፍቅር ድርጊት መሆኑን የሚያሳዩ ሌሎች የመጽሐፍ
ቅዱስ ምሳሌዎች የትኞቹ ናቸው?
4. ምንም እንኳን እግዚአብሔር በክፋት ላይ በጽድቅ እንደሚቆጣና
ፍርድን ፍጹም በሆነ ፍትሕ እንደሚያመጣ ብንገነዘብም፣ ሌሎችን
ከመኮነን መቆጠብ ምን ያህል አስፈላጊ ነው? ይህንን በተለይ ከ1ኛ
ቆሮ. 4፡5 አንፃር ተወያዩበት።