የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ማቴ. 22፡34–40፣ ዘካ. 7፡ 9–12፣ መዝ. 82፣ ሚክ. 6፡8፣ ማቴ. 23፡23–30፣ ሉቃ 10፡25–37።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “ማንም እግዚአብሔርን እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን
እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል?” (1 ዮሐ. 4:20)።
በመጨረሻ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደሚያስተካክል እርግጠኞች
ብንሆንም፣ እንደ ክርስቲያን በዚህ ምድር አሁን የምናደርገው ነገር
አስፈላጊ ነው። ምንም እንኳን እግዚአብሔር (በታላቁ ተጋድሎ
መርሆዎች ምክንያት) አሁን የማያስወግዳቸው ብዙ ኢ-ፍትሃዊ ድርጊቶችና
ክፋቶች ቢኖሩም፣ በምንችለው ሁሉ የምናየውን ማንኛውንም ስቃይና ክፋት
ለማቃለል መገልገያ ልንሆን አንችልም ማለት አይደለም። እንዲያውም እንደ
ክርስቲያን ይህን የማድረግ ግዴታ አለብን።
እንዳየነው ፍቅር እና ፍትሕ የተጋመዱ ናቸው፤ ሊነጣጠሉም አይችሉም።
እግዚአብሔር ፍትሕን ይወዳል። በዚህ መሠረት እግዚአብሔርን የምንወድ
ከሆነ፣ ፍትሕንም እንወዳለን።
በተመሳሳይም እግዚአብሔርን የምንወደው ከሆነ፣ እርስ በርሳችን
እንዋደዳለን። እርስ በርስ የመዋደዳችን አንዱ ክፍል ደግሞ በዙሪያችን ላሉ
ሰዎች ደህንነት ማሰብ ነው። ሌሎች በድህነት፣ በጭቆና ወይም በማንኛውም
ዓይነት ግፍ ሲሰቃዩ ሊገደን ይገባል። ሌሎች ሲጨቆኑ፣ አይቶ አንዳላየ መሆን
የለብንም። ይልቁንም፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ፍትሕ ለማስፈን ምን ማድረግ
እንደምንችል በግልም ሆነ በጋራ ራሳችንን ልንጠይቅ ይገባናል። በዚህ መልኩ
ፍፁም የሆነውን የጌታችንን ባሕርይ ያውም ጽድቁንና ፍቅሩን ለተበላሸው
አለማችን ማንጸባረቅ እንችላለን።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
*የሳምንቱን ትምህርት በማጥናት ለሰንበት ይዘጋጁ።
በዓለማችን ላይ በግልም ሆነ በጋራ የእግዚአብሔርን ፍቅር እና ፍትሕ
ለማስፈን ምን ማድረግ እንዳለብን ለማሰላሰል፣ አምላክ ባዘዘን ነገር ላይ በማተኮር
መጀመር ተገቢ ነው።
ማቴ. 22:34–40ን ያንብቡ። ኢየሱስ የሕግ አዋቂውን ጥያቄ የመለሰው
እንዴት ነው?
ኢየሱስ ራሱ እንዳለው “ፊተኛይቱና ታላቂቱ ትእዛዝ ጌታ አምላክህን
በፍጹም ልብህ በፍጹም ነፍስህም በፍጹም አሳብህም ውደድ” የምትለው
ናት። በተጨማሪም ኢየሱስ “ሁለተኛይቱም ይህችን ትመስላለች፥ ባልንጀራህን
እንደ ነፍስህ ውደድ” አለው። ይሁን እንጂ ትእዛዛቱ እነዚህ ብቻ አይደሉም።
ደግሞም ኢየሱስ “በእነዚህ በሁለቱ ትእዛዛት ሕጉም ሁሉ ነቢያትም ተሰቅለዋል
(ተንጠልጥለዋል)” ብሎ አስተማራቸው (ማቴ. 22፡37–40)። በእርግጥ እነዚህ
ራሳቸው ከብሉይ ኪዳን የተጠቀሱ ናቸው።
ማቴ. 19:16–23ን ያንብቡ። ኢየሱስ ሀብታም ለሆነው ወጣት አለቃ
ጥያቄዎች የሰጠው ምላሽ፣ በማቴ. 22 ላይ ለሕግ አዋቂው ጥያቄ
ከሰጠው መልስ ጋር እንዴት ይዛመዳል?
በዚህ ታሪክ ላይ ምን እየሆነ ነበር? ኢየሱስ ለዚህ ሰው እንደዚህ የመለሰው
ለምንድን ነው? በምንም የሕይወት ደረጃ ብንሆን፣ እነዚህ ገጠመኞች ለሁላችንም
ምን ሊያስተምሩን ይገባል?
“ክርስቶስ ወጣቱን አለቃ ፍፁም የሆነ ክርስቲያናዊ ባሕርይ ሊኖረው
የሚችልበትን ብቸኛ አማራጭ ነገረው። ምንም እንኳን የተናገራቸው ቃላት
ፍቅር እና ፍትሕ፡- ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት
ከባድና አስጨናቂ ቢመስሉም፣ የጥበብ ቃላት ነበሩ። የወጣቱ አለቃ ብቸኛ
የመዳን ተስፋው እነርሱን በመቀበልና በመታዘዝ ላይ የተመሰረተ ነበር። የነበረው
ስልጣንና ንብረት ወደ ክፋት እንዲያዘነብል በባሕርይው ላይ ስውር ተፅእኖ
እያሳደረበት ነበር። እነዚህ ነገሮች በተለየ ሁኔታ ከተወደዱ፣ የእግዚአብሔርን ቦታ
ይወስዳሉ። ከእግዚአብሔር ትንሽ ወይም ብዙ ማስቀረት፣ የሞራል ጥንካሬውንና
ብቃቱን የሚሸረሽርን ነገር ማቆየት ነበር። የዚህ ዓለም ነገሮች የማያስተማምኑና
የማይጠቅሙ ቢሆንም፣ በልባችን ውስጥ ልዩ ቦታ ከሰጠናቸው፣ ትኩረታችንን
ሁሉ የሚስቡ ይሆናሉ።”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 520.
ምንም እንኳን እንደ ሀብታሙ ወጣት አለቃ ሁላችንም ያለንን ሁሉ
እንድንሸጥ ባንጠራም፣ በውስጥህ የያዝከውና ካልተውከው በስተቀር
ወደ ዘላለማዊ ጥፋት የሚያደርስህ ምን ሊሆን ይችላል?
ኢየሱስ እንደተናገረው ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት እግዚአብሔርን
መውደድና እርስ በርስ መዋደድ ናቸው። እነዚህን ትእዛዛት መፈጸም ደግሞ
ሌሎችን በተግባር እንደምንወድ የሚያሳዩ መሥዋዕትነቶችን ያካትታል፤ ይህ ነው
የኢየሱስን ፈለግ መከተል ማለት።
እንግዲህ ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት እግዚአብሔርን እና ሌሎችን መውደድ
ከሆኑ፣ ሁለቱ ታላላቅ ኃጢአቶች ምንድን ናቸው?
መዝ. 135:13–19ን ያንብቡ። ይህ በቃሉ ውስጥ አጽንዖት ስለተሰጠው
የተለመደ ኃጢአት ምን ይገልፃል?
ብሉይ ኪዳን ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን ስለ መውደድ አስፈላጊነት ያለማቋረጥ ይናገራል (ዘዳ. 6፡5ን ይመልከቱ)። ይህ ታላቅ ከሆነውና እግዚአብሔርን ከመውደድ ከሚቃረነው የጣዖት አምልኮ ኃጢአት ጋር ጥብቅ ግንኙነት አለው። የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት ዘካ. 7፡9–12ን ያንብቡ። ነቢዩ ዘካርያስ በዚህ ክፍል እንደተናገረው፣ እግዚአብሔር የሚቃወመው ምንድን ነው? ይህና የጣዖት አምልኮ ኃጢአት ከሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ጋር ምን ግንኙነት አላቸው?
እግዚአብሔር በፍቅር ቁጣ የሚመልሰው በጣዖት አምልኮ ብቻ ሳይሆን፣
በሕዝቡ ላይ በግልም ሆነ በጋራ ለሚደርሰው በደል ጭምር ነው። እግዚአብሔር
ፍቅር ስለሆነ ግፍ ሲፈፀም ይቆጣል።
በብሉይ ኪዳን ውስጥ ትኩረት የተሰጣቸው ሁለቱ ታላላቅ ኃጢአቶች፣
ከሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት ማለትም እግዚአብሔርን እና ሌሎችን ከመውደድ አንፃር
ያሉ ድክመቶች ናቸው ። ሁለቱ ታላላቅ ኃጢአቶች እግዚአብሔርን እና ሌሎችን
አለመውደድ ናቸው። በአጭሩ እግዚአብሔርን እና ሌሎችን ካልወደዳችሁ
ትእዛዛቱን እየጠበቃችሁ አይደለም።
እርግጥ ነው 1 ዮሐ. 4:20, 21 እንዲህ ይላል:- “ማንም እግዚአብሔርን
እወዳለሁ እያለ ወንድሙን ቢጠላ ሐሰተኛ ነው፤ ያየውን ወንድሙን የማይወድ ያላየውን እግዚአብሔርን ሊወደው እንዴት ይችላል? እግዚአብሔርንም የሚወድ
ወንድሙን ደግሞ እንዲወድ ይህች ትእዛዝ ከእርሱ አለችን።”
እግዚአብሔርን መውደድ ሌሎችን ከመውደድ ሊነጠል እንደማይችል
እንዴት ሊገልፁ ይችላሉ? ይህንን የማይበጠስ ግንኙነት እንዴት
ሊረዱት ይችላሉ?
ቃሉ እግዚአብሔር ፍትሕን እንደሚወድና ክፋትን እንደሚጠላ ይናገራል (ለምሳሌ መዝ. 33፡5፣ ኢሳ. 61፡8)። የፍትሕ መጓደልም እጅግ ስለሚያሳስበው፣ በፍትሕ መጓደል ለተበደሉት ሁሉ የጽድቅ ቁጣው ይነዳል። በብሉይና በአዲስ ኪዳን ውስጥ፣ እግዚአብሔር ለተገፉና ለተጨቆኑ ያለማቋረጥ በቅናት ይነሳል፤ በበዳዮችና በጨቋኞች ላይም የጽድቅ ቁጣውን ይገልጻል። ፍቅር እና ፍትሕ፡- ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት መዝ. 82ን ያንብቡ። ይህ መዝሙር እግዚአብሔር የዚህ ዓለም ፍትሕ ግድ እንደሚለው የሚገልጸው እንዴት ነው? ዛሬስ ለእኛ ምን ትርጉም ይኖረዋል?
ብዙ የመጽሐፍ ቅዱስ ተንታኞች እንደሚረዱት፣ ይህ ክፍል በህብረተሰቡ
ውስጥ ለሚፈጠረው የፍርድ መጓደል ተጠያቂ የሆኑትን ምድራዊ ገዥዎች
የሚያወግዝ ሲሆን፣ በተጨማሪም እግዚአብሔር በዘቀጡ ምድራዊ ዳኞችና ገዥዎች
ጀርባ ባሉት የአጋንንት ኃይሎች ("አማልክት") ላይ የሚፈርድበትን ጊዜ ይጠቁማል።
በተለይ ለምድራዊ ገዥዎቹ፡- “እስከ መቼ ሐሰትን ትፈርዳላችሁ? እስከ መቼ
ለኃጢአተኞች ፊት ታደላላችሁ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦላቸዋል (መዝ. 82:2)።
በተጨማሪም “ለድሆችና ለድሀ አደጎች ፍረዱ፤ ለችግረኛውና ለምስኪኑ
ጽድቅ አድርጉ፤ ብቸኛውንና ችግረኛውን አድኑ፤ ከኃጢአተኞችም እጅ
አስጥሉአቸው” ተብለው ታዘዋል (መዝ. 82:3, 4)። በዚህና በሌሎች ጥቅሶች፣
የብሉይ ኪዳን ነቢያት ግልፅ የሆነ የፍትሕ ጥሪን አቅርበዋል። ይህ በቃሉ ውስጥ
ትኩረት የተነፈገው ጉዳይ አይደለም፤ የብሉይ ኪዳን ነቢያት መልእክት እምብርት
እና ኢየሱስ በምድር በሥጋ በነበረበት ጊዜ የተናገረው ዋና ነገር ነው።
እርሱን እንደሚወዱትና እንደሚታዘዙት ከሚናገሩት እግዚአብሔር
የሚሻውና የሚፈልገው ነገር የተሰወረ አይደለም። በሚክ. 6: 8 በግልፅ “ሰው
ሆይ፥ መልካሙን ነግሮሃል፤ እግዚአብሔርም ከአንተ ዘንድ የሚሻው ምንድር ነው? ፍርድን ታደርግ ዘንድ፥ ምሕረትንም ትወድድ ዘንድ፥ ከአምላክህም ጋር
በትሕትና ትሄድ ዘንድ አይደለምን?” በማለት አስቀምጦታል።
ይህ ሐሳብ በቃሉ ውስጥ ተስተጋብቷል። ለምሳሌ፡- ኢየሱስ “እርስ
በርሳችሁ ፍቅር ቢኖራችሁ፣ ደቀ መዛሙርቴ እንደ ሆናችሁ ሰዎች ሁሉ በዚህ
ያውቃሉ” ብሎ ተናግሯል (ዮሐ. 13፡35፤ ከ1 ዮሐ. 4፡8-16 ጋር ያስተያዩት)።
በሚክ. 6፡8 ላይ ብናተኩርና ሆን ብለን በቃልም ሆነ በሥራ
ብንተገብረው፣ ቤተሰቦቻችን እና ቤተክርስቲያኖቻችን ምን ይመስሉ
ነበር? በማንኛውም ሁኔታ ውስጥ ብትሆን፣ እነዚህ መርሆዎች እንዴት
በተሻለ ሁኔታ ሊተገበሩ ይችላሉ?
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነቢያት በማህበረሰብ መካከል ፍትሕ
እንዲኖር የእግዚአብሔርን ጥሪ ያለማቋረጥ አቅርበዋል። በተደጋጋሚ ቃሉ የኢ-
ፍትሐዊነትንና የጭቆናን አስከፊነት ከማጉላት ወደ ኋላ አይልም። በእርግጥ
እግዚአብሔርን እንዲፈርድ መጠየቅ በራሱ፣ ፍትሕን እንዲያሰፍን መለመን ነው።
ለምሳሌ ነቢዩ ኢሳይያስ በጊዜው በእሥራኤል የነበረውን ግፍ በቀጥታ
ይኮንናል። የፍትሕ ጥሪው ግልፅና ከፍ ባለ ድምፅ ዛሬም በጆሯችን ሊሰማን
ይገባል። "መልካም መሥራትን ተማሩ፥ ፍርድን ፈልጉ፥ የተገፋውን አድኑ፥ ለድሀ
አደጉ ፍረዱለት ስለ መበለቲቱም ተምዋገቱ” (ኢሳ. 1፡17)። ከዚህም በተጨማሪ
“የግፍን ትእዛዛት ለሚያዙ፣ የድሀውንም ፍርድ ለሚያጣምሙ ወዮላቸው”
በማለት ያውጃል (ኢሳ. 10:1, 2)። “በተጎበኛችሁበት ቀን፥ መከራም ከሩቅ
በሚመጣበት ዘመን ምን ታደርጉ ይሆን? ለረድኤትስ ወደ ማን ትሸሻላችሁ?
ክብራችሁንስ ወዴት ትተዉታላችሁ?” እያለም ያስጠነቅቃቸዋል (ኢሳ. 10:3)።
በተመሳሳይም ነቢዩ ኤርምያስ የእግዚአብሔርን መልእክት እንዲህ
ሲል ተናግሯል:- “ቤቱን በግፍ ሰገነቱንም በዓመፅ ለሚሠራ፥ ባልንጀራውንም
እንዲያው በከንቱ ለሚያሠራ፥ ዋጋውንም ለማይሰጠው… ወዮለት! በውኑ
አባትህ አይበላምና አይጠጣም ነበርን? ፍርድንና ጽድቅንስ አያደርግም ነበርን?
በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖለት ነበር። የድሀውንና የችግረኛውን ፍርድ ይፈርድ
ነበር፥ በዚያም ጊዜ መልካም ሆኖ ነበር። ይህ እኔን ማወቅ አይደለምን? ይላል
እግዚአብሔር።” (ኤር. 22:13, 15, 16 )
ማቴ. 23:23–30ን ያንብቡ። እዚህ ላይ ኢየሱስ በጣም አስፈላጊ
ስለሆነው ነገር ምን ያስተምረናል? “ዋና ነገሮች” ሲልስ ምን ማለቱ
ይመስልዎታል?
አንድ ሰው የፍትሕ መጓደል የብሉይ ኪዳን ነቢያት ጉዳይ ብቻ እንደሆነ
ፍቅር እና ፍትሕ፡- ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት
እንዳያስብ፣ በዚህና በሌሎች ጥቅሶች ይህ ነገር በአገልግሎቱ ወቅት ኢየሱስን
ራሱን እጅግ ያሳስበው እንደነበር በግልጽ እንመለከታለን። እንዲህ ነበር ያለው፡
- “እናንተ ግብዞች ጻፎችና ፈሪሳውያን፥ ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም
አሥራት ስለምታወጡ፥ ፍርድንና ምሕረትን ታማኝነትንም፥ በሕግ ያለውን ዋና
ነገር ስለምትተዉ፥ ወዮላችሁ፤ ሌላውን ሳትተዉ ይህን ልታደርጉ ይገባችሁ ነበር”
(ማቴ. 23፡23)። በሉቃስ ውስጥ ባለው ተመሳሳይ ክፍል፣ ኢየሱስ “ፍርድንና
እግዚአብሔርን መውደድ ስለሚተላለፉ” ያዝናል (ሉቃ. 11፡42)።
ዛሬ “በዋና ነገሮች” ላይ ማተኮር ቢኖርብዎት፣ በምትኩ ከምናተኩርበት
“ከአዝሙድና ከእንስላል ከከሙንም አሥራት ከማውጣት” በተቃራኒ፣
ምን ሊመስል ይችላል?
ሉቃስ እንደዘገበው፣ ኢየሱስ እግዚአብሔርን ስለ መውደድ እና
ባልንጀራን ስለ መውደድ ሁለቱን ታላላቅ ትእዛዛት ከተናገረ በኋላ፣ አንድ ሕግ
አዋቂ “ራሱን ሊያጸድቅ ወድዶ ኢየሱስን፡- ባልንጀራዬስ ማን ነው? አለው” ሉቃ.
10፡29)። ለዚህ ምላሽ ኢየሱስ አሁን እጅግ የሚታወቀውን፣ በዚያን ጊዜ ግን
አስደንጋጭ የነበረውን፣ የመልካሙን ሳምራዊ ምሳሌ ተናገረ።
በሉቃ. 10፡25-37 ላይ የሚገኘውን የመልካሙን ሳምራዊ ምሳሌ
ያንብቡ። ይህ ክፍል፣ ነቢያት ለምሕረትና ለፍትሕ እንዲሁም የተለያዩ
ቡድኖች በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ "በሌሎች" ላይ ስላደረሱት ግፎች
ካስተጋቡት ጩኸት አንፃር፣ ምን እያለ ነው?
ኢየሱስ ስለ ፍትሕ ለመናገር ብቻ ሳይሆን፣ ፍትሕን ሊያሰፍን መጣ።
እርሱ ያኔም ሆነ ወደፊት የነቢያት የፍትሕ ጥሪና ናፍቆት ፍጻሜ ነው (ሉቃ. 4፡
16–21ን ከኢሳ. 61፡1, 2 አንፃር ይመልከቱ)። እርሱ የአህዛብ ሁሉ ምኞት ነው –
በተለይም አዳኝ እንደሚያስፈልጋቸው ለሚገነዘቡ ሰዎች።
ሥልጣን ለመያዝና የእግዚአብሔርን ዙፋን በኃይል ለመቀማት ከፈለገው
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት
ጠላት በተቃራኒ፣ ኃጢአት የሌለበት ኢየሱስ ራሱን ዝቅ በማድረግ በኃጢአት፣
በግፍና በጭቆና ሥር ከነበሩት ጋር ተቆጠረ። ፍትሕን ያሰፍን ዘንድ፣ ጻድቅ
እንዲሆንና በእርሱም የሚያምኑትን ሁሉ ያጸድቅ ዘንድ፣ በፍቅር ራሱን አሳልፎ
በመስጠት ጠላትን ድል አደረገ። ክርስቶስ የሕጉ ዋና ነገሮች ብሎ ለሚጠራቸው
ደንታ ከሌለን፣ ክርስቶስ ሊያፀናው ለሞተው ሕግ ግድ ይለናል ማለት የምንችለው እንዴት ነው?
መዝ. 9:8, 9 “እርሱም ዓለምን በጽድቅ ይፈርዳታል፥ አሕዛብንም በቅንነት
ይዳኛቸዋል። እግዚአብሔርም ለድሆች (ለተጨቆኑ) መጠጊያ ሆናቸው፥ እርሱም
በመከራቸው ጊዜ ረዳታቸው ነው” ይላል። በተመሳሳይም መዝ. 146:7–9 እንዲህ
በማለት ያክላል፡- እግዚአብሔር “ለተበደሉት የሚፈርድ፥ ለተራቡ ምግብን
የሚሰጥ ነው። እግዚአብሔር የታሰሩትን ይፈታል፤ እግዚአብሔር የወደቁትን
ያነሣል፤ እግዚአብሔር ዕውሮችን ጥበበኞች ያደርጋቸዋል፤ እግዚአብሔር
ጻድቃንን ይወድዳል፤ እግዚአብሔር ስደተኞችን ይጠብቃል፤ ድሀ አደጎችንና
ባልቴቶችን ይቀበላል፤ የኃጢአተኞችንም መንገድ ያጠፋል።”
በዙሪያችን የተቸገሩትንና የሚሰቃዩትን ለማገልገል መፈለግ እንዳለብን፣
የእግዚአብሔር ቃል ከዚህ በላይ ምን ያህል ግልጽ ሊሆን ይችላል?
የተቸገሩትን ለመርዳት ከኢየሱስ ሕይወትና አገልግሎት ምን እንማራለን?
ምንም እንኳን እንደርሱ ተአምራትን ማድረግ ባንችልም፣ ለሚሰቃዩ
ብዙ ሰዎች የእኛ እርዳታ እንዴት "ተአምር" ሊሆን ይችላል?
የዘመናት ምኞት ከተባለው የኤለን ጂ. ኋይት መጽሐፍ
“ሰንበት” የተሰኘውን ርዕስ ከገጽ 281–289 ያንብቡ።
“ሰላዮቹ ችግር እንዳይገጥማቸው በመፍራት፣ በሕዝቡ ፊት
ለክርስቶስ መልስ ለመስጠት አልደፈሩም። እውነትን እንደተናገረ ያውቁ
ነበር። ወጋቸውን ከመተላለፍ ይልቅ አንድን ሰው እንዲሰቃይ ይተውት ነበር፤
ነገር ግን ችላ ከተባለ በባለቤቱ ላይ የገንዘብ ኪሳራ ስለሚያደርስ እንሰሳውን
ይንከባከቡ ነበር። በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረው ሰው ይልቅ ለእንስሳ
የበለጠ ጥንቃቄ ይደረግለት ነበር። ይህም የሐሰተኛ ሃይማኖቶችን ሥራ
ፍቅር እና ፍትሕ፡- ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት
ያሳያል። እነርሱ የሚመነጩት የሰው ልጅ ራሱን ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ
ለማድረግ ካለው ፍላጎት ነው፣ ነገር ግን ሰውን ከእንሰሳ በታች ያዋርዳሉ።
የእግዚአብሔርን ሉዓላዊነት የሚቃወም ማንኛውም ሃይማኖት፣ ሰው በፍጥረት
ጊዜ የተጎናፀፈውንና በክርስቶስ የሚመለስለትን ክብር ይገፈዋል። ማንኛውም
የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮቹን ለሰዎች ችግር፣ ስቃይና መብት ግድየለሾች
እንዲሆኑ ያስተምራል። ወንጌል በክርስቶስ ደም ለተገዛው የሰው ልጅ ከፍ
ያለ ዋጋ ይሰጠዋል፣ እናም ለሰው ልጅ ችግርና አበሳ እንድንራራ ያስተምራል።
ጌታ፡- ‘ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበሩ ይሆናሉ፥ ሰውም ከኦፊር ወርቅ ይልቅ የከበረ
ይሆናል’ ይላል (ኢሳ. 13፡12)።
“ኢየሱስ ፈሪሳውያንን በሰንበት ቀን መልካም ወይስ ክፉ ማድረግ፣
ሕይወት ማዳን ወይስ መግደል ተፈቅዶ እንደሆነ ሲጠይቃቸው፣ የነበራቸውን ክፉ
ዓላማ እየተገዳደረ ነበር። እርሱ ሕይወትን እያዳነ ለብዙዎች ደስታን ሲያመጣ፣
እነርሱ ግን በመራር ጥላቻ ህይወቱን ለማጥፋት ያሳድዱት ነበር። በሰንበት እርሱ
እንዳደረገው ድውያንን መፈወስ ወይስ እነርሱ ሊያደርጉ እንዳሰቡት መግደል
ይሻል ነበር? በእግዚአብሔር ቅዱስ ቀን በልብ ውስጥ ያለ የመግደል ሐሳብ፣
ከፍቅር የተነሳ ለሰው ሁሉ በርኅራኄ ከሚገለጽ መልካም ሥራ ይልቅ ጽድቅ
ነበርን?”—ኤለን ጂ. ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 286–287
ፍቅር እና ፍትሕ፡- ሁለቱ ታላላቅ ትእዛዛት
1. “ማንኛውም የሐሰት ሃይማኖት ተከታዮቹን ለሰዎች ችግር ግድየለሾች
እንዲሆኑ ያስተምራል” የሚለው እውነት የሆነው ለምንድን ነው?
በቤተ-ክርስቲያናችንም ሆነ በውጭ እንደዚህ አይነት ግድየለሽነትን
ለማስወገድ ሆን ብለን እንዴት መንቀሳቀስ እንችላለን?
2. ባልንጀራዬ ማን ነው? ባልንጀራህስ ማን ነው? ክርስቶስን
መከተላችን፣ ፍቅርን በተግባር ለማሳየት በዘመኑ የነበረውን የጥል
ግድግዳ እንዳፈረሰው ሳምራዊ እንድንሆን የሚያደርገን በምን በምን መንገዶች ነው?
3. እግዚአብሔር ፍትሕንና ምሕረትን የሚወድ ከሆነ፣ በእርሱ ዘንድ
አስፈላጊ የሆኑ ነገሮችን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ኢየሱስ
“የሕጉ ዋና ነገሮች” ባላቸው ላይ ይበልጥ የምናተኩረው እንዴት ነው?
4. ስለ ፍርድ ስናስብና ስንነጋገር፣ ኢየሱስ ስለ ፍርድ የተናገረበት
ዋናው መንገድ ሌሎችን በተለይም የተጨቆኑትንና የተገፉትን
በተግባር መውደድን አስመልክቶ መሆኑን ምን ያህል አጽንዖት
እንሰጠዋለን? ይህንን ከማቴ. 25፡31-46 አንፃር ያሰላስሉ።