የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 1:4 ዮሐ. 10:10፤ ዮሐ. 1:12፣ 13፤ ዮሐ. 6፡61-68፤ ዘኁ. 13፡23-33፤ ማቴ. 4፡1-4።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም
ነኝ፤ በእኔ በቀር ወደ አብ የሚመጣ የለም” (ዮሐ. 14፡6)።
በ
ዮሐንስ ወንጌል ውስጥ፣ ኢየሱስ ማን እንደሆነ ሲጠየቅ፣ መለኮትነትን በሚያመላክት
ቃል መለሰ። “እኔ ነኝ” የሚለው በሚቃጠለው ቁጥቋጦ ውስጥ ለሙሴ የተገለጠለት
ጌታ እራሱ እንደሆነ የማያሻማ ማጣቀሻ ነበር። ሙሴን “እኔ እኔ ነኝ” ብሎ ተናገረ (ዘጸ.
3፡14)። ይህ “እኔ ነኝ” ያለው አምላክ “ቃልም ሥጋ ሆነ፤ ጸጋንና እውነትንም ተመልቶ በእኛ አደረ፥
አንድ ልጅም ከአባቱ ዘንድ እንዳለው ክብር የሆነው ክብሩን አየን” (ዮሐ. 1፡14)።
“እኔ ነኝ” የሚለው ጭብጥ በመላው ዮሐንስ ወንጌል ውስጥ አለ። የዚህ ሳምንት
መሪ ጥቅስ ያንን ጭብጥ ያንፀባርቃል፡- “እኔ መንገድና እውነት ሕይወትም ነኝ” (ዮሐንስ 14፡
6)። “እኔ ነኝ” የዓለም ብርሃን፣ የሕይወት እንጀራ፣ በሩ ወይም የበጎች በር፣ መልካም እረኛና
እውነተኛው የወይን ግንድ ነው።
የዚህ ሳምንት ጥናት በዮሐንስ እንደተሰጠን ስለ እግዚአብሔር መገለጥ ማስተማሩን
ይቀጥላል። ኢየሱስ መሲህ መሆኑን የሚያሳዩ ጠንካራ ማስረጃዎች ቢኖሩም፣ አንዳንዶች እሱን
ያልተቀበሉበትን፣ የነገሮችን ግልባጭ በጥልቀት እንመረምራለን። ይህንን ሃሳብ የምናጠናው
በሁለት ምክንያቶች ነው፡- ተመሳሳይ ስህተትን ለማስወገድ፣ ነገር ግን ያንን ስህተት የመፈጸም
አደጋ ውስጥ ያሉትን ሰዎች እንዴት መድረስ እንደምንችልም በግምት ውስጥ ከማስገባት
አንጻር ነው።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለሕዳር 21 ሰንበት ይዘጋጁ።
በዮሐንስ ወንጌል 1፡1 ላይ ሐዋርያው በግልጽ ኢየሱስ እግዚአብሔር እንደሆነ
ይጠቅሳል። ከዚህም የተነሳ በዮሐንስ 1፡14 ላይ “በእርሱ ሕይወት ነበረች፥ ሕይወትም የሰው
ብርሃን ነበረች” ይላል። በዚህ ጥቅስ ላይ ሕይወት ለሚለው ማመሳከሪያው መለኮታዊ ሕይወት
መሆን አለበት፤ ይህም ከሌላው የተወሰደ ማለት ሳይሆን ለዘላለም ራሱን ችሎ የሚኖር ማለት
ነው። እርሱ በራሱ ውስጥ ሕይወት ስላለው ነፍሱን ሊያስቀምጥ እንደገናም ሊያነሳ ይችላል
(ዮሐ. 10፡17)። በውስጡ ሕይወት ስላለ ለሚሻው ሕይወትን መስጠት ይችላል (ዮሐ. 5፡21፤
ይህንን ከዮሐንስ 14፡19 ጋር አነጻጽሩ)።
ይህ ሕይወት (“ዞዊ” “zoē”) የሚለው ቃል በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ 36 ጊዜ
ተጠቅሷል፤ ከመቶ 25 እጅ የሚሆነው ጥቅም ላይ የዋለው በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ነው።
በዮሐንስ 1፡4፣ 5 ላይ፣ ቃሉ በምድራችን ላይ ያለውን የህይወት ምንጭ ከመጥቀስ በተጨማሪ
ከመዳን ጋር የተያያዘ ነው። በቀሪው የዮሐንስ ወንጌል ክፍል ውስጥ፣ ይህ ሕይወት የሚለው
(“ዞዊ”) ሃሳብ ብዙውን ጊዜ የሚገልጸው የዘላለም ሕይወትን ነው፤ ይህም የመዳን ተስፋ ማለት
ነው (ዮሐ. 3:15፣ 16፣ 36፤ ዮሐ. 4:14፣ 36፤ ዮሐ. 6:27፣ 40፣ 47፣ 54፣ 68፤ ዮሐ. 10:27፣ 28
ተመልከቱ)። ስለዚህ በፍጥረት ሕይወትን የሰጠው እርሱ፣ መዳንን፣ የዘላለምንም ሕይወት ወደ
ጠፋው ዓለም የሚያመጣው ያው እርሱ ነው።
የሱስ ወደዚህ ምድር የመጣው ለምንድን ነው? ዮሐ. 1:29፣ ዮሐ. 3:16፣ ዮሐ.
6:40፣ ዮሐ. 10:10፣ ዮሐ. 12:27።
“ሙሴም በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት
እንዲኖረው እንጂ እንዳይጠፋ የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” (ዮሐ. 3:14-15)።
በእባቦች የተነደፉትን እስራኤላውያንን ቦታ የነሐሱ እባብ እንደተካው ሁሉ፣ በኃጢአት
የተመታነውን እኛንም ኢየሱስ ተክቶአል። የእርሱ የሆነውን ሕይወት እንድናገኝ የእኛ የሆነውን
ቅጣት ተቀበለ።
ክርስቶስ ደግሞ ሕይወት እንዲኖረንና እንዲበዛልን ይፈልጋል (ዮሐ. 10፡10)።
ስለዚህም “ለተቀበሉት ሁሉ ግን፥ በስሙ ለሚያምኑት ለእነርሱ የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ
ዘንድ ሥልጣንን ሰጣቸው፤ እነርሱም ከእግዚአብሔር ተወለዱ እንጂ ከደም ወይም ከሥጋ
ፈቃድ ወይም ከወንድ ፈቃድ አልተወለዱም” (ዮሐ. 1:12፣ 13)።
ስለ አብ ባሕርይ ከኢየሱስ ሕይወት ምን እንማራለን? ይህ መገለጥ ይህን ያህል
የምሥራች የሆነው ለምንድን ነው?
ዮሐንስ 6፡61-68 ያንብቡ። ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ትተውት ይሄዱ እንደሆነ ሲጠይቃቸው የጴጥሮስ መልስ ምን ትርጉም ነበረው?
ጴጥሮስ ስለ “ዘላለማዊ ሕይወት” የተናገረው ሐሳብ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ
ያለውን ጭብጥ የሚነካ ነው። ስለ ዘላለማዊ ሕይወት የተነገረው ሐረግ ትኩረት በዮሐንስ 6
ላይ፣ በ5,000 ሰዎች አመጋገብ አውድ ውስጥ የሚታይ ነው (ዮሐ. 6፡27፣ 40፣ 47፣ 54፣
68)። ኢየሱስ እርሱ የሕይወት እንጀራ እንደሆነ ተናግሯል (ዮሐ. 6፡35)፤ ትርጉሙም የእርሱ
ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤው የዘላለም መዳን ምንጭ ነው ማለት ነው።
የዘላለም ሕይወት ወይም ተመሳሳይ ሐረግ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ቢያንስ 17 ጊዜ
ተጠቅሷል። ይህ ቃል የመንፈስ ህላዌን ወይም ዘላለማዊ የሆነ ወይም ሌላ ከተፈጥሮአዊው
ውጭ የሆነ አካል ክፍል የመሆንን ፅንሰ-ሀሳብን አያመላክትም። ይልቁንም መዳንንና ለአሁኑ
ኑሮአችን ትርጉም የሚሰጠውን ሕይወት ሰጪ ኃይል እና ጌታችን በሚመለስበት ጊዜ ማለቂያ
የሌለውን ሕይወት ያመላክታል። ኢየሱስ ሥጋ እንደ ሆነ ሁሉ፣ ኢየሱስም የተናገረለት ትንሣኤ
በጊዜና በኅዋ እንዲሁም በሥጋዊ አካል ውስጥ ሆኖ የሚከናወን ነው። ይህ ከሙታን መነሣት፣
እኛ በአንድ ጊዜ በኤደን የነበረንን ሕይወት መታደስ የሚያመላክት ነው።
የዘላለም ሕይወትን እንዴት እንቀበላለን? ዮሐ. 3:15፣ 16፤ ዮሐ. 5:24፤ ዮሐ.
6:40፣ 47፤ ዮሐ. 8:31፤ ዮሐ. 12:46፤ ዮሐ. 20፡31።
በእምነት ብቻ ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ እኛ ሲል ሊኖርና ሊሞት እንደ መጣ እናምናለን።
ይህ እምነት እንደ ስጦታ ሆኖ ወደ እኛ ይመጣል፣ ነገር ግን እኛ አውቀን ራሳችንን ለኢየሱስ
አሳልፈን ለመስጠት፣ ንስሐ ለመግባት እና ደሙን ለኃጢአት ይቅርታ እና መንጻት ለመጠየቅ
መምረጥ አለብን።
ኢየሱስ ጴጥሮስን እርሱም ትቶት ይሄድ እንደሆነ ሲጠይቀው፣ “ጌታ ሆይ፣ ወደ ማን
እንሄዳለን? አንተ የዘላለም ሕይወት ቃል አለህ” በማለት ጴጥሮስ የመለሰው (ዮሐንስ 6፡68)
የመዳንን ትርጉም እና እንዴት እንደምናገኘው የሚያመላክት ነው። መዳን ከፍልስፍና፣ ከታሪክ፣
ከሳይንስ፣ ከሁሉም የሰው ልጆች የትምህርት ዓይነቶች አይመጣም። መዳን የሚመጣው
ከኢየሱስ ነው፣ እሱም በራሱ የዘላለም ህይወት ባለቤት የሆነው፣ ለመንፈስ ቅዱስ ምላሽ
ለሚሰጡ ሁሉ ይቀበሉ ዘንድ በነጻ ይሰጣል።
የዘላለም ሕይወት የማግኘት ተስፋ እኛ ጊዜያዊ ሕይወታችንን የምንመለከትበት
ሁኔታ ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? ይህ በአመለካከታችን ላይ እንዴት
ተጽዕኖ ሊያሳድር ይገባዋል?
ዮሐንስ 1:12፣ 13ን ያንብቡ። ክርስቲያን ከመሆን ጋር ተያይዞ የተገለጹት ደረጃዎች የትኞቹ ናቸው?
ዮሐንስ ወንጌሉን የጻፈው በኢየሱስ እንድናምንና በማመንም በስሙ የዘላለም ሕይወት
እንዲኖረን ነው (ዮሐ. 20፡31)። በዮሐንስ 1፡12፣13፣ ይህ ሂደት በሁለት ደረጃዎች ተገልጿል።
በመጀመሪያ፣ እርሱን እንቀበላለን፣ በእርሱም እናምናለን። በሁለተኛ ደረጃ በቁጥር 13 ላይ
“ከእግዚአብሔር ተወለዱ” ተብሎ እንደተገለጸው፣ እርሱ የእግዚአብሔር ልጆች እንድንሆን
ሥልጣንን ወይም ኃይልን ይሰጠናል። ስለዚህም ክርስቲያን ከመሆን ጋር ተያይዞ ሰብዓዊና
መለኮታዊ ገጽታ አለ። እኛ በእምነት እርምጃን በመውሰድ፣ እርሱን መቀበል፣ ለብርሃን ራስን
ክፍት ማድረግ ሲገባን፣ ልብን ግን የሚያድሰው እርሱ ይሆናል ማለት ነው።
በእርግጥ እምነት ራሱ ቃሉን በመስማት የሚገኝ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው (ሮሜ.
10፡17)። “በክርስቶስ ላይ እውነተኛና ዘላቂ የሆነ እምነት እንዲኖረን፣ እርሱን በቃሉ ውስጥ
እንደተገለጸው ማወቅ ይኖርብናል” (Ellen G. White, Fundamentals of Chris-
tian Education, p. 433)። “በሰዎች አእምሮ ላይ የሚሠራው እና የሚያበራው መንፈስ፣
በእግዚአብሔር ላይ እምነት ይፈጥራል” (Ellen G. White Comments, The Sev-
enth-day Adventist Bible Commentary, vol. 7, p. 940)።
ወልድን እንደ መሲህ ያመኑ ወይም የተቀበሉ የዘላለም ሕይወት ያገኛሉ። ዮሐንስ ኢየሱስ
የተናገረውን ቃል በመቀበል ወይም በማመን ላይ አጽንዖት ይሰጣል (ዮሐ. 5፡24፣ 38፣ 47)።
እምነትን ማምጣት የመንፈስ ቅዱስ ድርሻ ነው (ዮሐ. 16፡7፣ 8፤ ከሮሜ 8፡16 ጋር አነጻጽሩ)።
ሮሜ 8፡16ን ያንብቡ። እዚህ ላይ በኢየሱስ ስለ መዳን አስመልክቶ ምን መሠረታዊ
መርሖ ይገኛል?
እምነት፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው እምነት፣ በልባችን ውስጥ ባለው የመንፈስ ቅዱስ
ሥራ ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህ የእምነታችን መሠረት ነው። “እምነት . . . ታላቁ በረከት ነው፤
የሚያየው ዓይን፣ የሚሰማው ጆሮ እርሱ ነው” (Ellen G. White, In Heavenly
Places, p. 104)። ስለ እምነት ያለው ሰብአዊው አቀራረብ፣ መሰረቱን መጀመሪያ ማግኘት
እንዳለብን፣ የእምነት መስፈርቶችን መፈለግ እና ከዚያም ማመን እንዳለብን ይናገራል።
በአንጻሩ ደግሞ መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆነው አቀራረብ፣ እምነት መሠረት ሆኖ ከእግዚአብሔር
ዘንድ የሚመጣ ስጦታ እንደሆነ ያስቀምጣል (ኤፌ. 2፡8፣ 1ኛ ቆሮ. 1፡17-24፣ 1ኛ ቆሮ. 2፡
1-6)። ከእምነት መሠረት እንጀምራለን ከዚያም በማስተዋል እና በጸጋ እናድጋለን።
አንድ ሰው እምነታችሁ በምን ላይ እንደተመሰረተ ቢጠይቃችሁ እንዴት ምላሽ
ትሰጣላችሁ?
በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ ካሉት እጅግ አሳዛኝ ዘገባዎች መካከል አንዳንዶቹ
የተፈጸሙት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ ነው። “ብርሃንም በጨለማ ይበራል፥ ጨለማም
አላሸነፈውም። … [ብርሃንም] በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም።
የእርሱ ወደ ሆነው መጣ፥ የገዛ ወገኖቹም አልተቀበሉትም” (ዮሐ. 1፡5፣ 10፣ 11)። “እኔ ነኝ”
ብዙ በሆኑት የራሱ ወገኖች ተቀባይነትን አላገኘም ነበር።
ጳውሎስ በኋላ ላይ “ድፍረታችሁን አትጣሉ” ብሎ ማስጠንቀቁ የሚያስደንቅ
አልነበረም (ዕብ. 10:35)። ደጋግመን እንዳየነው፣ ሰዎች ክርስቶስን የተቃወሙት ቃሉን
ስላልተቀበሉ ነው።
የዘመኑ የሰው ልጅ አስተሳሰብ በጥርጣሬ ይጀምራል። ሰዎች እውነት የሆነውን
ለመወሰን ሁሉንም ነገር ይጠይቃሉ። ከጥያቄ እሳት የተረፈውን እንደ አለት ጠንካራ እውቀት
አድርገው ይቀበላሉ። ይህም የአንድ ሰው እምነት የሚጣልበት ነገር ይሆናል ማለት ነው።
አንዳንዶች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እውነት ምን እንደሆነ ለማወቅ፣ ከሳይንሳዊ፣ ታሪካዊ፣ ሥነ
ልቦናዊ፣ ፍልስፍናዊ፣ ስነ ቅርሳዊ ወይም ስነ ምድራዊ አተያይ በመነሳትና ሁሉንም ነገር በጥያቄ
ውስጥ በማስገባት ተመሳሳይ ዘዴ ለመጽሐፍ ቅዱስ ይጠቀማሉ። ይህ ዘዴ በራሱ በቅዱሳት
መጻሕፍት ትክክለኛነት ላይ ከጥርጣሬ ተነስቶ በጥርጣሬ ላይ ይገነባል። ክርስቶስ እንዲህ
ሲል ጠየቀ፡- “የሰው ልጅ በመጣ ጊዜ በምድር እምነትን ያገኝ ይሆንን?” (ሉቃስ 18፡8) (E.
Edward Zinke and Roland Hegstad, The Certainty of the Second
Coming, (Hagerstown, MD: Review and Herald Publishing Asso-
ciation, 2000) p. 96)።
ዘኍልቍ 13፡23-33ን ያንብቡ። ሰላዮቹ ስለ ከነዓን ባመጡት ሁለቱ ዘገባዎች
መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?
ዕብራውያን በቃዴስ በርኔ በነበሩ ጊዜ የሠሩት ኃጢአት የእግዚአብሔርን ቃል
መጠራጠር ነበር። እግዚአብሔር ወጥተው ምድሪቱን እንዲወስዱ ጠይቋቸው ነበር።
ምድሪቱን እንዲሰልሉ አሥራ ሁለት ሰላዮች ወደ ከነዓን ተላኩ። ሁለት ዓይነት ዘገባዎችን ይዘው
ተመለሱ። አብዛኞቹ አሉታዊውን ዘገባ ሰጥተዋል። በምድሪቱ ላይ ግዙፍ ሰዎች፣ በቅጥር
የተከበቡ ከተሞች፣ ከዚህ በፊት አይተነው የማናውቀው የጦር መሳሪያ እና በደንብ የሰለጠኑ
ሠራዊቶች አሉ። በአንጻሩ እኛ በግብፅ ምድር ብዙም የውትድርና ልምድ ሳይኖረን ባሮች ሆነን
ቆይተናል የሚል ዓይነት ነበር። ከሰው ሚዛን ከሚደፋ እይታ አንጻር ሲታይ አስር ሰላዮች እምቢ
ብለው ድምጽ ሰጥተዋል። ሁለት ሰላዮች በእግዚአብሔር ቃል ላይ ባላቸው እምነት መሰረት
አዎን [ይቻላል] ብለው ድምጽ ሰጥተዋል።
እዚህ ላይ እንደተፈጸመው ተመሳሳይ ዓይነት ስህተት ከመሥራት እንዴት እንቆጠባለን?
በአንጻሩ ደግሞ እኛ ደግሞ የእግዚአብሔርን ፈቃድ እየሠራን እንዳለን በማመን፣
ልንወድቅ አንችልም ከሚል ትምክህተኝነት መራቅ የምንችለው እንዴት ነው?
“በእርሱ በሚያምን አይፈረድበትም፤ በማያምን ግን በአንዱ በእግዚአብሔር ልጅ ስም ስላላመነ አሁን ተፈርዶበታል። … ክፉ የሚያደርግ ሁሉ ብርሃንን ይጠላልና፥ ሥራውም እንዳይገለጥ ወደ ብርሃን አይመጣም፤ እውነትን የሚያደርግ ግን … ወደ ብርሃን ይመጣል” (ዮሐ. 3፡18-21፤ ከዮሐ. 1፡10 ጋር አነጻጽሩ)። ሰዎች ወደ ፍርድ የሚመጡት ለምንድን ነው? ዮሐ. 3:18፣ 36፤ ዮሐ. 5:24፣ 38፤ ዮሐ. 8:24፤ ዮሐ.12:47።
የዓለም ብርሃን የሆነውን ኢየሱስ ክርስቶስን አለመቀበል ለጥርጣሬ እና ለዲያብሎስ
ፈተናዎች ክፍት ያደርገናል። ይህ ከብርሃን ወደ ጨለማ መዞር ነው።
ሔዋን በአትክልቱ ስፍራ መኃል ስላለው ዛፍ እንዴት ማድረግ እንደሚገባት ብርሃን
ተሰጥቷት ነበር። ሰይጣን ብርሃኑን በጥያቄ ውስጥ እንድታስገባ ፈተናት። የፍቅር አምላክ
የሆነው የፈጠራቸውን ፍጥረታት አያጠፋም ብላ የእግዚአብሔርን ቃል ፈተነች። በተጨማሪም
የራሷ የስሜት ህዋሳት መረጃ ላይ ተመረኮዘች። እባቡ ከፍሬው በልቷል እናም አሁን የመናገር
ኃይል አለው። ምናአልባት እባቡ ትክክል ይሆናል። ከፍሬው ብበላ እንደ እግዚአብሔር ልሆን
እችላለሁ! ተታልላ ከብርሃኑ ተመለሰች። እናም ባሏም ተመሳሳይ መንገድ መረጠ።
ማቴዎስ 4:1-4ን ያንብቡ። ክርስቶስ በምድረ በዳው ፈተና የሰይጣንን ማታለያዎች
ለመዋጋት ምን ዓይነት መርሖዎችን ተጠቀመ?
አዳምና ሔዋን፣ በውሃ ጥፋት ወቅት የነበሩትና በቃዴስ በርኔ አጠገብ እስራኤላውያን
የተጠቀሙበት የሰብዓዊ አስተሳሰብ መሳሪያ በክርስቶስ እጅ ላይም ነበረ። የፍቅር አምላክ
ልጁን ያለ ምግብና ጥበቃ ለ40 ቀንና ሌሊት በምድረ በዳ ለምን እንደተወው መጠየቅ ይችል
ነበር። እነዚህን ድንጋዮች ወደ ዳቦ እቀይራለሁ በማለት ልጅነቱንም ለማረጋገጥ መወሰን
ይችል ነበር! ከዚህ ይልቅ በእግዚአብሔር ቃል መልስ ሰጠ። ከምድራዊ የአስተሳሰብ ዘይቤዎች
ይልቅ በሰማያዊ ነገሮች ደረጃ ላይ ተመርኩዞ ሠርቷል። ብዙዎች፣ ማለትም የእምነት ሰዎችም
ቢሆኑ፣ ብዙውን ጊዜ ወደ ተሳሳተ ውሳኔ የሚመሩበትንና ሰበብ የሚሰጡበትን መንገድ በቀላሉ
ሊሄድበት ይችል ነበር።
ከኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት ከሚለው መፅሐፍ “እግዚአብሔር
ከኛ ጋር ነው” ገጽ 19-26፤ “ክርክር” ገጽ 601-609 ያንብቡ።
“ራሱን ዝቅ አድርጎ የሰብአዊ ሥጋ በመልበሱ ክርስቶስ ከሰይጣን ጠባይ ተቃራኒ
የሆነውን ባሕርይ ገለጸ፤ በትህትና ጎዳናም ይበልጥ ራሱን አዋረደ። “በምስሉም እንደ ሰው
ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ” (ፊሊ. 2፡8)። ሊቀ
ካህን እንደመሆኑም መጠን በጣም የሚያምርና በቀለም ያሸበረቀ የሊቀ ካህናትን ልብሰ ተክህኖ
በመልበስ ፋንታ ከተልባ እግር የተሠራውን ነጭ የተራ ካህን ልብስ ተጎናጽፎ የክህነት ተግባሩን
አከናወነ። ስለዚህ ክርስቶስ አገልጋይ በመምሰል መስዋዕት አቀረበ። ራሱ ካህን ሆኖ ተሰዋ።
“እርሱ ግን ስለ መተላለፋችን ቈሰለ፥ ስለ በደላችንም ደቀቀ፤ የደኅንነታችንም ተግሣጽ በእርሱ
ላይ ነበረ፥ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን” ይላል (ኢሳ. 53፡5)።
“ለእርሱ የሚገባው ለእኛ ይሆን ዘንድ በዓመጻችን ምክንያት በእኛ ላይ ሊደርስብን
የሚገባው ሁሉ በእርሱ ላይ ደረሰበት። ምንም ጥፋት ሳይኖረው በእኛ ኃጢአት ተወገዘ፤ እኛም
የማይገባንን በእርሱ ቅድስና ተዋጀን። የእርሱን ሕይወት እናገኝ ዘንድ ለእኛ ይገባን በነበረው
ሞት ተሰቃየ። “በእርሱ ቁስል እኛ ተፈወስን” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 15)።
1. ዓለምን ለማዳን ሲል ኢየሱስ የሰጠው ብዙ ነው። ሌሎች ይህን አስደናቂ
እውነት እንዲያዩ እና በእምነት ወደ እርሱ እንዲመጡ ለመርዳት የትኞቹ
መንገዶች ምርጥ ናቸው ብላችሁ ታስባላችሁ?
2. በሰው ልጅ ማለትም በአለማዊ ደረጃ እና በመለኮታዊ መገለጥ ላይ
በመመስረት ውሳኔዎችን በማድረግ መካከል ያሉት ዋና ዋና ልዩነቶች
ምንድን ናቸው?
3. እንደ አመክንዮ ወይም ምክንያታዊነት ያላቸው ነገሮች የእግዚአብሔርን ቃል
ከመረዳት ጋር እንዴት ይጣጣማሉ? ወደ እምነት ለመምጣት ምን ዓይነት
ምክንያታዊ የሆኑ ነገሮች አሉን? እንደ ትንቢት ፍጻሜ ወይም አስደናቂ
ውበትና ውስብስብነት ያለው ተፈጥሮአዊው ዓለም እንዴት ስለ አምላክ
መኖር እና ስለ መዳን እቅድ እውነት ምክንያታዊ በሆነ መልኩ ያመለክታሉ?
4. በጥናት ቡድናችሁ ውስጥ በማክሰኞው ጥናት መጨረሻ ላይ ለተጠየቀው
ጥያቄ በሰጣችሁት መልስ ዙሪያ ተነጋገሩ። እምነታችሁ በምን ላይ ነው
የተመሰረተው? አንድ ሰው በኢየሱስ እና በወንጌል የተነገረውን ለምን
እንደምታምኑ ቢጠይቃችሁ እንዴት ትመልሳላችሁ?