የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የዮሐንስ ወንጌል ዋና ዋና ሐሳቦች



4ኛ ሩብ ዓመት 2024


ህዳር 21 - 27

10ኛ ትምህርት

Nov 30 - Dec 6




መንገድ፣ እውነትና ሕይወት



ሰንበት ከሰዓት በኋላ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 13:1-20፤ ዮሐ. 14:1-3፤ ዳን. 7:27፤ ዮሐ. 14:5-11፤ ዮሐ. 1:14፤ ቆላ. 1:16፣ 17፤ ዮሐ. 5፡38-40።


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድ ስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ተረከው” (ዮሐ. 1፡18)።



ዮሐንስ ወንጌል በአራት ዋና ዋና ክፍሎች የተከፈለ ነው፡ መቅድም (ዮሐ. 1፡1-18)፣ የምልክቶች መጽሐፍ (ዮሐ. 1፡19-12፡50)፣ የክብር መጽሐፍ (ዮሐ. 13፡1-20፡ 31) ) እና መደምደሚያው (ዮሐ. 21፡1-25)። እስካሁን የተደረገው ጥናት በዋናነት በመደምደሚያው እና በምልክቶቹ መጽሐፍ ላይ ትኩረት ያደረገ ነው፤ በዚህም ኢየሱስ ማን እንደሆነ ለመግለጽ በተአምራቶቹ (በምልክቶቹ)፣ በንግግሮቹ እና በትምህርቶቹ ላይ ትኩረት ያደርጋል። ቀጥለው የሚመጡት የሰንበት ትምህርቶች፣ አሁን በተለይ ወደ ዮሐንስ ሦስተኛው ክፍል፣ ወደ ክብር መጽሐፍ ይሸጋገራሉ።

የሚገርመው፣ ታዋቂዎቹ ሰባት “እኔ ነኝ” የሚሉ ሐረጎች በምልክት እና በክብር መጽሐፍ መካከል ድልድይ የሚፈጥሩ ናቸው። እነዚህም “የሕይወት እንጀራ” (ዮሐ. 6:35፣ 41፣ 48፣ 51)፣ “የዓለም ብርሃን” (ዮሐ. 8:12፣ ዮሐ. 9:5)፣ “በሩ” (ዮሐ. 10:7፣ 9)፣ “መልካም እረኛ” (ዮሐ. 10:11፣ 14)፣ “ትንሣኤና ሕይወት” (ዮሐ. 11:25)፣ “መንገድ፣ እውነትና ሕይወት” (ዮሐ. 14:6) እና “እውነተኛው የወይን ግንድ” (ዮሐ. 15:1፣ 5) ናቸው።

የዚህ ሳምንት ትምህርት የሚጀምረው የኢየሱስ የስንብት ንግግሩ ዓላማ እና መግቢያው እንዲሁም የደቀ መዛሙርቱን እግር ካጠበበት ጉልህ ክፍል ይሆናል። ከዚያም ወደ ምዕራፍ 14 “እኔ ነኝ” (“እኔ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነኝ”) ወደሚለው ሐረግ ይመለሳል። *የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለሕዳር 28 ሰንበት ይዘጋጁ።

ህዳር 22
Dec 1

ምሳሌ ሰጥቼአችኋለሁ


የመሰናበቻው ንግግር (ዮሐ. 13-17) ለኢየሱስ ደቀ መዛሙርት ስለ ወደፊቱ ጊዜ መመሪያ የሚሰጥ ነው። የአጻጻፍ ዘይቤው በዘዳግም ውስጥ ከሙሴ ስንብት ወይም ያዕቆብ ልጆቹን ከባረከበት (ዘፍ. 47-49) ወይም ዳዊት ለሰለሞን መመሪያ ከሰጠበት (1ኛ ዜና 28- 29) ጋር ተመሳሳይ ነው። ኢየሱስ በመሄጃው ጊዜ ላይ ደቀ መዛሙርቱን አጽናንቷቸዋል። እርሱን ስለሚወክለው ምትክ ቃል ገብቷል (መንፈስ ቅዱስ፤ ዮሐ. 14-16)። ሐዘን እንደሚመጣ ተንብዮአል (ዮሐ. 15–16)፣ እና ደቀመዛሙርቱን በታማኝነት እንዲቆዩ አሳስቧቸዋል (ዮሐ. 15)። ዮሐ. 13:1-20ን ያንብቡ። እዚህ ላይ የተከሰተው ምንድነው፣ እናም ይህ ታሪክ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው? ኢየሱስ ምን ዓይነት ትምህርቶችን ለመስጠት ፈልጎ ነበር?



በኢየሱስ ዘመን በነበረው ዓለም ሰዎች እንደ ሰንደል ዓይነት ጫማ ያደርጉ ወይም በባዶ እግራቸው ይሄዱ ነበር። እግሮችም አቧራማ እና ቆሻሻ ይሆናሉ። ምግብ ለመመገብ የሚመጡትን ሰዎችንም እግር ማጠብ ለአገልጋይ ወይም ለባሪያ የተለመደ ተግባር ነበር።

ነገር ግን ኢየሱስ ከመያዙ በፊት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር የመጨረሻውን ምግብ በበላበት ምሽት ይህንን ተግባር ለመፈፀም የተገኘ አገልጋይ አልነበረም።

ሁሉንም ሰው በሚያስገርም ሁኔታ፣ ኢየሱስ ራሱ ከእራት ተነሥቶ እግራቸውን ሁሉ አጠበ። ዮሐ. 13:4፣ 5 የኢየሱስን ድርጊቶች ደረጃ በደረጃ ይነግረናል። መምህሩ ይህንን የማይታመን የትሕትና ተግባር ማድረጉን ለማጉላት በዝርዝር ተነግሯል።

የጴጥሮስ ምላሽ ምን እንደሆነ በመንገር፣ ዮሐንስ 13፡8-11 ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ድርጊት የተሰማቸውን ጭንቀት እና ያለመረዳት እውነታ ያጎላል። እንዴት ጌታ፣ መሲሕ የሆነው ኢየሱስ ይህን ያህል ዝቅተኛ የሆነውን ሥራ ይሠራል? ጴጥሮስ ኢየሱስ እግሩን እንዲያጥብ አልፈቀደለትም ነበር፤ ነገር ግን ከኢየሱስ ጋር ካልተባበረ ከኢየሱስ ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው ኢየሱስ ነገረው። ከዚያም ጴጥሮስ ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት የመፍጠር ፍላጎት እንዳለው እንዲገልጽ በተጨማሪ ጠየቀ።

የኢየሱስ ድርጊት አስፈላጊነት ከማንነቱ ጋር የተያያዘ ነው። በዮሐንስ 13፡13 ላይ እርሱ መምህርና ጌታ እንደሆነ ተናግሯል። እርሱንም ሲጠሩት የነበረው እንደዚያው ነውና እርሱም ያ ትክክል እንደ ሆነ ሲጠቁም ነበር። እነዚህ ማዕረጎች ሥልጣንን እና ኃይልን ይገልጻሉ። ሆኖም ኢየሱስ ኃይልና ሥልጣን ለአገልግሎት እንጂ ራስን ከፍ ከፍ ለማድረግ እንዳልሆነ አስተምሯል።

የአድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ይህንን የኢየሱስን አርአያነት ስሜት ተቀብላለች፣ የትህትና ስርአት ተብሎ ለሚጠራው ለጌታ እራት፣ እግር እጥበትን እንደ ቅድመ ዝግጅት አገልግሎት ወስዳለች። የኢየሱስን ፈለግ ስለመከተል እና ሌሎችን እንዴት በትህትና ስለማገልገል ይህ የትህትና ስርአት (የጌታ እራት) ምን ያስተምራችኋል?

ህዳር 23
Dec 2

በእርግጥ ዳግም እመጣለሁ


ዮሐንስ 14:1-3ን ያንብቡ። ኢየሱስ እነዚህን ቃላት የተናገረው በምን ዓይነት አውድ ውስጥ ነው?



በዮሐንስ ወንጌል 13 መጨረሻ ላይ፣ ኢየሱስ እንደሚሄድ ተናግሯል (ዮሐ. 13፡33)።

ይህም ጴጥሮስን እርሱ ወዴት እንደሚሄድ እንዲጠይቀው አነሳስቷል (ዮሐ. 13፡36)። ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ እየተናገረ ያለው ስለ ሞቱ፣ ትንሳኤው እና ዕርገቱ እንደሆነ አልተረዱም ነበር። ጴጥሮስ ነፍሱን ስለ እርሱ አሳልፎ ሊሰጥ መዘጋጀቱን ተናግሯል (ዮሐ. 13፡37)። በዚህ ጊዜ ነው ኢየሱስ ጴጥሮስ እንደሚክደው የተነበየው (ዮሐ. 13፡38)።

ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ልባቸው እንዳይታወክ የነገራቸው በዚህ አውድ ውስጥ ነው (ዮሐ. 14፡1)። አይታወክ የሚለው ግስ በግሪክ “ታራሶ” (tarassō”) ከሚለው የተተረጎመ ሲሆን፣ ትርጉሙም መቀስቀስ፣ ማወክ፣ አለመረጋጋት፣ ወደ ግራ መጋባት ውስጥ መጣል ማለት ነው። ታዲያ ደቀ መዛሙርቱ በኢየሱስ ቃላት ግራ መጋባታቸው ምንም አያስደንቅም።

ነገር ግን ፍርሃታቸውን በመቃወም፣ ብዙ ክፍሎች ስላሉበት ስለ አባቱ ቤት ይናገራል (ይህ ቤት እንደ ቪላ ቤቶች ሳይሆን እንደ ማደሪያ ዓይነት ቤቶች ማለት ነው)። ቦታ ሊያዘጋጅላቸው ወደዚያ እየሄደ ነው። ቃላቶቹ እየመጣ ከነበረው የመስቀል ማዕበል ባሻገር ሕዝቡን ለመቤዠት የሚመለስበትን ጊዜ የሚያመላክቱ ናቸው። እርሱ ይህ ሁሉ ከኃጢአት ጋር ተያይዞ የተከሰተው አሳዛኝ ሁኔታ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ የሚጠናቀቅበትን ጊዜ እየተመለከተ ነው (ዳን. 7፡27 ተመልከቱ)።

ኢየሱስ “ሄጄም … እኔ ባለሁበት እናንተ ደግሞ እንድትሆኑ ሁለተኛ እመጣለሁ ወደ እኔም እወስዳችኋለሁ” አለ (ዮሐ. 14፡3)። ይህ በግልጽ የእርሱ ዳግም ምፅአት የተስፋ ቃል ነው።

በዚህ ተስፋ ላይ ለመተማመን መሠረቱ ምንድን ነው? ብዙዎቹ ለዚህ ጥያቄ የመፅሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜያቸውን ማግኘታቸው ነው ብለው ሊመልሱ ይችላሉ፤ ይህ ደግሞ እውነት ነው። ነገር ግን በዮሐንስ 14፡3 ላይ መሠረቱ በተለየ መንገድ ተቀምጧል። በዚህ ቁጥር እኔ እመጣለሁ ተብሎ በግሪክ የተቀመጠው፣ እየመጣሁ ነው የሚልና የአሁን ጊዜ ግስ (pres- ent tense) ውስጥ የተቀመጠ ነው። በግሪክ የአሁን ጊዜ አባባል፣ አጠቃቀሙ የወደፊት ግስ ተብሎ የሚጠራ ነው። በሌላ አባባል ወደፊት የሚሆነውን ክስተት አሁን እንደተከሰተ አድርጎ በእርግጠኝነት የሚገልጽ ማለት ነው። ስለዚህም፣ በእርግጠኝነት እንደገና እመጣለሁ ብሎ ሐረጉን መተርጎም ተገቢ ነው ማለት ነው።

በጌታችን ዳግም ምጽአት ላይ ያለን ተስፋ መሠረት የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ፍጻሜ ብቻ አይደለም። በተጨማሪ ተስፋውን በሰጠው ሰው ባለን እምነት ላይ በይበልጥ የተመሠረተ ነው። እርሱ ለገዛ ሕዝቡ ሲል በእርግጥ እመለሳለሁ አለ። ከተናጋሪው የተነሳ በዚህ ተስፋ ላይ እምነት ልንጥልበት እንችላለን። መስቀሉ ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት እርግጠኝነት ምን ያስተምረናል? ያለ ዳግም ምጽአት፣ በመጀመሪያ ምጽአቱ የተፈፀመው የኢየሱስ ሞት ምንድን ነው የሚያደርግልን?

ህዳር 24
Dec 3

እኔ መንገድ እውነትና ሕይወት ነኝ


ዮሐንስ 14:5፣ 6ን ያንብቡ። ቶማስ ኢየሱስ ወዴት እንደሚሄድ አስመልክቶ ምን ጥያቄ አቀረበ? ኢየሱስስ እንዴት ነው የመለሰው?



የቶማስ ጥያቄ በበቂ ሁኔታ ምክንያታዊ ይመስላል። አንድ ሰው ወዴት እንደሚሄድ የማታውቁ ከሆነ ያንን ሰው የምትከተሉበትን መንገድ እንዴት ልታውቁ ትችላላችሁ? ኢየሱስ ራሱ መንገድ መሆኑን በማመልከት ጥያቄውን በአንድ ደረጃ ከፍ አደረገው። መንገዱ ወዴት የሚወስድ ነው? ወደ አብ የሚያደርስ ነው። በመቅድሙ (ዮሐ. 1፡1-18) በቃሉ (ሎጎስ)፣ በኢየሱስ ክርስቶስ እና በአብ መካከል ያለው የጠበቀ ግንኙነት አጽንዖት ተሰጥቶበት ነበር።

ዮሐንስ 1፡18 አንድያ ልጅ የሆነው (እዚህ ላይ “ልዩ” ተብሎ ቢተረጎም ይሻላል) እግዚአብሔር አብን ማን እንደሆነ እንዳስታወቀ ይናገራል። በዚህ ጽሑፍ ውስጥ ማስታወቅ (“exēgeomai”) የሚለው የግሪክ ግስ ሲሆን ትርጓሜውም ማብራራት፣ መተርጎም፣ መግለጥ ማለት ነው። ጥቅስን ማብራራት (exegesis) የሚለውን ቃል ያገኘነው ከዚህ ነው።

ትርጓሜውም ትርጉሙን ማውጣት ማለት ነው። ስለዚህም፣ ኢየሱስ ክርስቶስ ከአብ ጋር የሚያገናኝ፣ አብን ለወደቀው ዓለም የሚያስረዳ ወይም የሚያብራራ ነው ማለት ነው። ከዚህም የተነሳ እርሱ ወደ አብ የሚያደርስ መንገድ ሆነ። ያለ እርሱ በመረዳታችን የተገደብን ነን። ዮሐንስ 14:7-11ን ያንብቡ። ኢየሱስ የፊልጶስን አለመረዳት ያስወገደው እንዴት ነበር?



ፊልጶስ አብን ለማየት ጠይቋል፤ ይህም ማንም ኃጢአተኛ የሆነ ሰው ሊያደርገው እና ቀጥሎም አይቶት በሕይወት ሊኖር የማይችለው ነገር ነው (ከዘጸ. 33፡17 - 34፡9፣ ዮሐ. 1፡18 ጋር አነጻጽሩ)። ኢየሱስ የማስተዋል ጉድለትን ገሥጾ፣ እርሱን ማየት ማለት አብን ማየት እንደሆነ አመላክቷል (ዮሐ. 14፡9)። ስለዚህም ኢየሱስ ወደ እግዚአብሔር የሚወስደው መንገድ መሆኑ ግልጽ ነው። ያለ እርሱ መንገዱ ጨለማ እና እርግጠኝነት የሌለው ይሆናል። እርሱ ወደ እግዚአብሔር የሚወስደውን መንገድ የሚያበራ ብርሃን ነው።

ኢየሱስ ሦስት ቃላትን በአንድነት ያገናኛል፤ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት። መንገድ የሚለው ቃል በዮሐንስ 1፡23 ላይ፣ መጥምቁ ዮሐንስ ለኢየሱስ መንገድ ማዘጋጀቱን በሚናገረው ቦታና በዚህ በዮሐንስ 14፡6 ውስጥ ብቻ ጥቅም ላይ ውሏል። ነገር ግን እውነት እና ህይወት የሚሉት በወንጌል ውስጥ ዋና መሪ ሃሳቦች ናቸው። የረቡዕ እና የሐሙስ ጥናታችን የእውነት ፅንሰ-ሀሳብ ላይ አፅንዖት ይሰጣሉ፤ ይህ በተለይም “እውነት” የሚለው ሀሳብ በጥያቄ ውስጥ በገባበት ዓለም ውስጥ ስላለን ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ ነው። በዚህ ምድር ላይ ስንኖር ሳለን ኢየሱስ ማለት እግዚአብሔር አብ ምን እንደሚመስል የምናገኘው ከሁሉ የተሻለ መገለጥ መሆኑን ማወቁ የሚያጽናናው ለምንድን ነው?

ህዳር 25
Dec 4

እኔ እውነት ነኝ


ዮሐንስ 1:14፣ 17፤ ዮሐንስ 8፡32፣ ዮሐንስ 14፡6 እና ዮሐንስ 15፡26ን ያንብቡ።

ዮሐንስ የእውነትን ፅንሰ-ሀሳብ በቀጥታ ከኢየሱስ ጋር የሚያገናኘው እንዴት ነው?



እውነት በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ በተደጋጋሚ ከኢየሱስ፣ ከአባቱ እና ከመንፈስ ቅዱስ ጋር የተገናኘ ነው። እውነት ከኢየሱስ፣ ከቃሉ (ሎጎስ) እና ከጨለማ ተቃራኒ ከሆነው ከብርሃንም ጋር የተገናኘ ነው (ዮሐ. 1፡1-14፣ ዮሐ. 3፡19-21)። ደግሞ ውሸት ከዲያብሎስና ከኃጢአት ጋር የተያያዘ ነው (ዮሐ. 8፡44-46)። ስለዚህ በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የምናገኘው እውነት ዝም ብሎ የመረጃና የቁጥር ጉዳይ አይደለም ማለት ነው። አዎን እንደ መረጃ ያሉ ነገሮችን ያካትታል፣ ነገር ግን ከዚህ በላይ፣ የእውነት ፅንሰ ሐሳብ ለእግዚአብሔር እና ለፈቃዱ ታማኝነት ያለውን የግብረ ገብ ገጽታ የያዘ ነው።

“የመለኮትን መገለጥ በመሻት ወደ ሕያው አምላክ የሚያለቅሱ በርካታዎች ናቸው።

የፍልስፍና ቲዎሪዎችና (ፅንሰ ሐሳቦች) የሥነ ፅሑፍ ዓምዶች የቱንም ያህል አስደናቂ ቢሆኑም የልብን ጥማት ማርካት አይችሉም። የሰዎችን ንግግርና የፈጠራ ሥራዎችም ዋጋ ስለሌላቸው የእግዚአብሔር ቃል ለሰዎች (ልብ) እንዲናገር ሊደረግ ይገባል። በሕይወት ዘመናቸው የሰዎችን ትምህርት፣ ትውፊትና ወግ ብቻ ሲማሩ የኖሩ ሁሉ ነፍስን ወደ ዘላለማዊ ሕይወት ሊለውጥ የሚችለውን የእርሱን ድምጽ እንዲሰሙ መደረግ አለበት” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 17-18)።

ለኢየሱስ እውነት መሆን ምን ማለት እንደሆነ አስቡ። ኢየሱስ ሎጎስ ነው፣ ከመጀመሪያው አንስቶ በእግዚአብሔር ዘንድ የነበረው ቃል እና የፍጥረታት ሁሉ ፈጣሪ ነው (ዮሐ. 1፡1-4)። ከዘላለም እስከ ዘላለም ከአብ ጋር አንድ የሆነው ኢየሱስ የአብ ባህሪያት አሉት፣ ስለዚህም ደግሞ እርሱ “እኔ ነኝ” ነው። ማንነቱ ለማንም ሆነ ለምንም አይገዛም። እውቀትን ጨምሮ ያለው ምንም ነገር ቢሆን ከእርሱ ውጭ አይደለም። ያለው ሁሉ፣ የተፈጠረውም፣ በኢየሱስ ብቻ ተፈጥሯል፤ በእርሱም ውስጥ ብቻ አለ። “እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው።

የሚታዩትና የማይታዩትም፥ ዙፋናት ቢሆኑ ወይም ጌትነት ወይም አለቅነት ወይም ሥልጣናት፥ በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ በእርሱ ተፈጥረዋልና ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኵር ነው። ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል። እርሱም ከሁሉ በፊት ነው ሁሉም በእርሱ ተጋጥሞአል” (ቆላ. 1:16-17)።

ኢየሱስ እውነትን የተላበሰ (የእውነት መገለጫ) ብቻ አይደለም። እርሱ እውነት ነው።

እውነት ጽንሰ ሐሳብ ማለት አይደለም። እውነት ማለት ግለሰብ ነው!

እውነት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለምን ከምታበራው ፀሐይ ጋር ሊመሳሰል ይችላል (ዮሐ. 8፡12)። ይህ ሲ.ኤስ. ሉዊስ የሚባል ሰው ስለ ክርስትና ከተናገረው ጋር ይመሳሰላል።

“ፀሐይ ወጥታለች ብዬ እንደማምነው በክርስትና አምናለሁ፤ ስላየኋት ብቻ ሳይሆን በእርሷ የተቀረውን ነገር ሁሉ ስለማይ ነው” (Is Theology Poetry?” (n. p.: Samizdat University Press, 2014), p. 15, originally presented 1944)። በዙሪያችን ያለውን ዓለም በትክክል ልንተረጉም የምንችለው እውነት በሆነው በኢየሱስ ነው።

ህዳር 26
Dec 5

ቅዱሳት መጻሕፍትና እውነት በወንጌል ውስጥ


ቅዱሳት መጻሕፍት መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ስለሆነው በመናገር ትልቅ ሚና ይጫወታሉ። በወንጌላት ሁሉ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ፣ በብሉይ እና በሐዲስ ኪዳን ውስጥ ሁሉ እንደሆነው፣ ቅዱሳት መጻሕፍት እውነትን ከመግለጥ አኳያ ቁልፍ ሚና ይጫወታሉ። ይህ ስለ ኢየሱስ ማንነት እና ምን ሊሰራ እንደመጣ እኛን ከማስተማር አንጻር በተለየ ሁኔታ እውነት የሆነ ነው። ዮሐንስ 5:38-40ን ያንብቡ። ኢየሱስ ስለ ቅዱሳት መጸሐፍት ምን እያለ ነው?



ኢየሱስ እና ደቀ መዛሙርቱ፣ እርሱ መሲሕ መሆኑን ለማረጋገጥ በተደጋጋሚ ወደ ቅዱሳት መጻሕፍት አመላክተዋል። “ክርስቶስ ሙሴንስ ብታምኑት እኔን ባመናችሁ ነበር፤ እርሱ ስለ እኔ ጽፎአልና። መጻሕፍትን ካላመናችሁ ግን ቃሌን እንዴት ታምናላችሁ?” አለ (ዮሐ. 5፡ 46-47)። ሉቃስ 24:27ን ያንብቡ። ኢየሱስ የአገልግሎቱን አስፈላጊነት ለመግለጥ በመጀመሪያ ወደ ቅዱሳን መጻሐፍቶች ማመላከቱ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?





በሌላ ቦታ ደግሞ ክርስቶስ ከዘፀአት መጽሐፍ እየጠቀሰ እንዲህ ብሏል:- “ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን …?” (ማቴ. 22:31)።

ዘካርያስ የእግዚአብሔርን ተስፋዎች ጠቅሷል፤ “[እግዚአብሔር] ከጥንት ጀምሮ በነበሩት በቅዱሳን ነቢያት አፍ እንደ ተናገረ” በማለት (ሉቃስ 1፡70)። ጴጥሮስ በጴንጤቆስጤ ዕለት በስብከቱ ላይ “መንፈስ ቅዱስ አስቀድሞ በዳዊት አፍ የተናገረው የመጽሐፍ ቃል ይፈጸም ዘንድ ይገባ ነበር” ብሏል (ሐዋ. 1፡16)።

መጽሐፍ ቅዱስ የሳይንስ መማሪያ መጽሐፍ አይደለም። ቅንጣት [atom] እንዴት እንደሚከፈል ወይም የአንጎል ቀዶ ጥገና እንዴት እንደሚደረግ አይገልጽም። ነገር ግን የበለጠውን ጉልህ ነገር ያደርጋል። ስለ አጽናፈ ዓለማችን ትርጉም ያለውን አውድ ያቀርባል። መጽሐፍ ቅዱስ ብርሃንን ለማየት የሚያስችለውን በር የሚከፍት ቁልፍ ነው። ያለ እርሱ፣ ስለ አምላክ መኖር፣ በሕዋ (አጽናፈ ዓለም) ውስጥ ስላለው ሚና፣ ስለ ራሳችን አመጣጥ፣ ስለ ሕይወት ትርጉም እና ስለ ወደፊቱ ጊዜ ጨለማ ውስጥ እንገባ ነበር። ሳይንስ በንድፈ ሐሳብ ደረጃም ቢሆን ፈጽሞ ሊያስተምረን የማይችላቸው፣ መጽሐፍ ቅዱስ ግን የሚያስተምረን አንዳንድ እውነቶች የትኞቹ ናቸው?

ህዳር 27
Dec 6


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ከሚለው መፅሐፍ “የሕይወት ብርሃን” ገጽ 463-475፤ ከኢ ኤድዋርድ ዚንኬ ደግሞ “The Authority of the Bible and the Certainty of the Second Coming,” The Certainty of the Second Coming, pp. 23-36” ያንብቡ።

የሱስ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ያለው “የዳሱን በዓል ለማካሄድ በተዘጋጀው የቤተ መቅደስ አደባባይ ላይ ነው። በዚህ አደባባይ መካከል ትልልቅ የመብራት መቅረዞች የሚገኙባቸው ሁለት ግዙፍ አምዶች ነበሩ። የማታው አገልግሎት እየተጠናቀቀ ፋኖሶቹ ይቀጣጠሉና በኢየሩሳሌም ላይ ያበራሉ። ይህ አገልግሎት የእሥራኤል ልጆች በምድረ በዳ ጉዞአቸው ይመራቸው የነበረው ብርሃን አምድ መታሰቢያ ሲሆን በተጨማሪም የመሲሑን መምጣት ያመላክት ነበር። ማታ ፋኖሶቹ በሚበሩበት ጊዜ አደባባዩ ትልቅ የደስታ ትእይንት ይሆን ነበር።…

“[ለሕዝቡ] በዚያ በዓል ወቅት በኢየሩሳሌም ላይ የሚታየው ብርሃን መሲሑ ለእሥራኤል ብርሃን ለመስጠት እንደሚመጣ የነበራቸው ተስፋ መግለጫ ነበር። ለየሱስ ግን ያ ትእይንት ጥልቀት ያለው ትርጉም ነበረው። የቤተ መቅደሱ ፋኖሶች ለአከባቢው ብርሃን እንደሰጡ ሁሉ እንዲሁም የመንፈሳዊ ብርሃን ምንጭ የሆነው የሱስ በጨለማው ውስጥ ላለው ዓለም ብርሃን ይሰጣል። ቢሆንም ምሳሌው የተሟላ አይደለም። ለየሱስ ተልዕኮ ክቡርነት እውነተኛው ምሳሌ እርሱ በእጁ በሰማይ ላይ ያስቀመጠው ትልቁ ብርሃን ነው።

“የሱስ ወደ ጥዋት ጀንበር እያመለከተ “እኔ የዓለም ብርሃን ነኝ” ባለ ጊዜ ጸሐይዋ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ብቅ ብላ ስለነበር ጨረርዋ በሚያንጸባርቀው በቤተ መንግሥቱ ዕብነ በረድና በቤተ መቅደሱ የወርቅ ግድግዳ ላይ ፈንጥቆ ነበር” (ኤለን ጂ ዋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ 476-477)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በጥናት ቡድናችሁ ውስጥ፣ ለሐሙስ የመጨረሻ ጥያቄ በሰጣችሁት መልስ ላይ ተወያዩ። በመርሕ ደረጃ እንኳ ከሳይንስ ልንማር የማንችላቸው፣ ነገር ግን መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምራቸው ወሳኝ እውነቶች የትኞቹ ናቸው? ለምሳሌ መስቀል? ወይስ ትንሣኤ? ወይስ ዳግም ምጽአት? እኛ ፈጽሞ ልናውቃቸው የማንችላቸው ምን ሌሎች ጠቃሚ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ሊገለጡልን ይገባል?

2. ስለ እግዚአብሔር እና እግዚአብሔር ደግሞ ምን እንደሚመስል ብዙ የሚያውቀውና ፍጹም ስለነበረው የሉሲፈር ውድቀት አስቡ። ያም ሁሉ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ላይ አመፀ። ይህ እኛ በተመሳሳይ መልኩ ስላለን ነፃ ምርጫ እውነታ ምን ይነግረናል፣ እናም ለምን በየቅጽበቱ ይህን ፈቃድ ለእግዚአብሔር አሳልፈን ለመስጠት መምረጥ ያስፈልገናል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL