የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚተከሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 5:17፣ 20፣ 36-40፣
46፣ 47፤ ዮሐ. 13:18፤ ዮሐ. 17:12፤ ኤር. 2:13፤ ዘካ. 9:9፤ ዮሐ. 8፡12-30።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “እኔ ግን ከዮሐንስ ምስክር የሚበልጥ
ምስክር አለኝ፤ አብ ልፈጽመው የሰጠኝ ሥራ፥ ይህ የማደርገው
ሥራ፥ አብ እንደ ላከኝ ስለ እኔ ይመሰክራልና” (ዮሐ. 5፡36)።
ኢ
የሱስ የተናገራቸውና ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ፣ አዎን መሲሑ (ሐማሺያክ)፣ ክርስቶስ
ወደ እስራኤል እንደመጣ የሚገልጹትን በዮሐንስ ወንጌል ውስጥ የተገለጹትን
ደጋግመን ማየት እንችላለን። ቅዱሳት መጻሕፍትም እንደተነበዩት በቤተልሔም
የተወለደ አይሁዳዊ፣ ከእነርሱ እንደ አንዱ ሆኖ መጥቶ ነበር።
ሆኖም፣ ዮሐንስ እንደጻፈው፣ “በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም
አላወቀውም” (ዮሐ. 1፡10)።
በዓለም ነበረ፥ ዓለሙም በእርሱ ሆነ፥ ዓለሙም አላወቀውም? በጣም የሚገርም
አባባል ነው። እናም በዮሐንስ እና በሌሎች ወንጌሎች እንደምናየው፣ ብዙ ሰዎች ኢየሱስ
ባደረጋቸው እና በተናገራቸው ነገሮች ሁሉ እርሱን ለማወቅ ምክንያት ሊኖራቸው ቢገባም
አላወቁትም ነበር። ከዚህም በላይ ደግሞ፣ የብሉይ ኪዳን ቅዱሳት መጻሕፍት ወደ እርሱ
ይጠቁሙ ነበር።
በዚህ ሳምንት ዮሐንስ ኢየሱስን መሲህ መሆኑን የገለጠባቸውን ተጨማሪ
መንገዶች እንመለከታለን፤ ደግሞም እርሱ ክርስቶስ እንደሆነ የሚያረጋግጡ ኃያል የሆኑ
ምክንያቶች ቢኖሩም አንዳንድ ሰዎች አሁንም እሱን መቃወም የቀጠሉት ለምን እንደሆነ
እናያለን።
ከእነርሱ ስሕተት የምንማረው ምንድን ነው?
*የዚህን ሳምንት ትምህርት በማጥናት ለሕዳር 14 ሰንበት ይዘጋጁ።
ዮሐንስ ኢየሱስ መሲሕ መሆኑን ለማመላከት ከተጠቀማቸው ተአምራቶች በተጨማሪ
ኢየሱስ ስላደረጋቸው ምልክቶች፣ ሥራዎችና ድንቆች የተደረጉትን ሰፋ ያለ ውይይቶች
መዝግቧል።
ምልክቶች እና ድንቆች በራሳቸው የእርሱ መሲሕነት ማረጋገጫዎች አልነበሩም፤
ምክንያቱም ብዙ ነቢያት፣ አንዳንድ ጊዜም ሐሰተኞች፣ ተአምራትን አድርገዋልና። ዮሐንስ
ምልክቶቹን እንዲያው አንድ ታላቅ ተአምር ሠሪን ብቻ ስለማመልከታቸው አልዘገበም ነበር።
ዮሐንስ የጻፋቸው ምልክቶች ኢየሱስን እንደ መሲህ የማመላከት ብሎም እርሱ በእርግጥ ከራሱ
ከእግዚአብሔር አብ እንደመጣ የሚያሳዩበት ልዩ ባህሪ ነበራቸው።
ዮሐ. 5:17፣ 20፣ 36-38ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በተለይም ከምልክቶቹ አውድ
አንፃር እንዴት በኢየሱስ እና በእግዚአብሔር አብ መካከል ያለውን ግንኙነት ይገልጻሉ?
ኢየሱስ ከአብ ጋር ያለውን የቅርብ የስራ ግንኙነት ለማሳየት ምልክቶቹን ተጠቅሟል።
ሁለቱ አንድ ነበሩ። ሥራዎቹ የሚያሳዩት “አብ በእኔ እንደ ሆነ እኔም በአብ እንደ ሆንሁ” ተብሎ
የተጻፈውን እውነታ ነው (ዮሐ. 10: 38፣ በተጨማሪም ዮሐ. 14: 10፣ 11ን ተመልከቱ)።
የኢየሱስ መምጣት አላማ የላከውን ስራ ለመስራት ነበር፤ ይህም ስራዎቹ ለአለም
ይገለጡ ዘንድ ነው። ይኸውም አብ የላከውን ሥራ ለመሥራት እርሱ መጣ፤ የሠራውም ሥራ
እርሱ ከአብ እንደሆነ በግልጽ የሚመሰክር ነበር።
ሆኖም ፣ ቀደም ብለን እንዳየነው፣ ምንም እንኳን ኃይለኛ ምልክቶች እና የብዙ ሰዎች
ምስክርነት ቢኖርም፣ ሰዎች አሁንም ላለማመን መርጠዋል።
የኃይማኖት መሪዎቹ ኢየሱስን እንዲህ ብለው ጠየቁት “እስከ መቼ ድረስ በጥርጣሬ
ታቆየናለህ? አንተ ክርስቶስ እንደ ሆንህ ገልጠህ ንገረን አሉት። ኢየሱስም መለሰላቸው፥ እንዲህ
ሲል፡- ነገርኋችሁ አታምኑምም እኔ በአባቴ ስም የማደርገው ሥራ ይህ ስለ እኔ ይመሰክራል”
(ዮሐ. 10፡24፣ 25)።
ኢየሱስ ልክ እንደመጣ እርሱ መሲሕ መሆኑን ተናግሮ ቢሆን ኖሮ፣ በእርሱ ላይ
የሚያገኙትን ማንኛውንም ነገር ለመጠቀም ሲፈልጉ የነበሩት የኃይማኖት መሪዎቹ እርሱን
ባጠቁ ነበር። ኢየሱስ ይህን ስለሚያውቅ፣ ወዳደረጋቸው ሥራዎቹ ጠቁሟል። ኢየሱስ እኔ
ክርስቶስ ነኝ ብሎ ቢሆን፣ ያንን በቀላሉ ለመካድ ይችሉ ይሆናል። ነገር ግን ምልክቶችን፣
ሥራዎቹንና ድንቆችን እንዴት ሊክዱ ይችላሉ? እነዚህ እርሱ ማን እንደነበር እና ከየት እንደመጣ
የሚያሳዩ ኃይለኛ ምስክሮች ነበሩ።
በእነዚህ የኃይማኖት መሪዎች ውስጥ እንደምናየው የደነደነ ልብ ከመያዝ
ራሳችንን እንዴት መጠበቅ እንችላለን? በገዛ ራሳችን ሕይወት የእግዚአብሔርን
ሥራ ልንዋጋ የምንችለው በምን ዓይነት መንገዶች ሊሆን ይችላል?
ዮሐንስ ኢየሱስን መሲሕ መሆኑን ለመጠቆም ከተጠቀመባቸው ልዩ ምልክቶችና
ምስክሮች በተጨማሪ፣ የብሉይ ኪዳንን ሥልጣንና የክርስቶስን ሥራ የሚተነብዩትን ትንቢቶቹንም
ይጠቅሳል። ብሉይ ኪዳን ለዮሐንስ ወንጌል ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ሐዲስ ኪዳን ማዕከል ነው።
ለኢየሱስ፣ ለማንነቱ፣ ከየት እንደመጣ፣ ላደረገው እና ወደፊት ምን እንደሚያደርግ ማረጋገጫው
በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የተመሠረተ ነው፤ ይህም ብሉይ ኪዳን ነው።
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ: - ዮሐ. 5:39፣ 40፣ 46፣ 47። እነዚህ ጥቅሶች
ኢየሱስ ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ስላለው አመለካከት ምን ያስተምሩናል?
በወንጌሎች ሁሉ፣ ኢየሱስ በተደጋጋሚ የቅዱሳት መጻሕፍትን ሥልጣን ስለ እርሱ እንደ
ቁልፍ ምስክርነት አመላክቷል። ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ብዙ ጊዜ በብሉይ ኪዳን የተከናወኑ ድርጊቶችን
ወደ ራሱ እና እርሱ የሚያደርገውን ለመጠቆም ይጠቀማል። የሚከተለው አንድ ምሳሌ ነው፤
ይህም ከዘኍልቍ 21፡5-9 አንድ ክስተትን የወሰደበት ሁኔታ ነው። “ሙሴም በምድረ በዳ
እባብን እንደ ሰቀለ እንዲሁ … የሰው ልጅ ይሰቀል ይገባዋል” (ዮሐ. 3፡14)። እዚህ ላይ፣ ኢየሱስ
ታሪኩን ብቻ ማጣቀስ ሳይሆን፣ ታሪኩን ወደ ራሱ በማመላከት፣ ታሪኩ ለማስተላለፍ የፈለገውን
መሠረታዊ የሥልጣን ትርጓሜ ይሰጠናል።
ኢየሱስን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ብሉይ ኪዳንን ተጠቅመው ኢየሱስን ያመላክታሉ።
ለምሳሌ፣ በዮሐንስ ወንጌል መጀመሪያ ላይ፣ የፊልጶስን ቃል እናነባለን፡- “ሙሴ በሕግ ነቢያትም
ስለ እርሱ የጻፉትን … አግኝተነዋል” (ዮሐ. 1፡45)።
የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ዮሐ. 13:18፤ ዮሐ. 17:12፤ ዮሐ. 19:24፣ 28፣
36። ኢየሱስና ዮሐንስ በተረዱት መሠረት ስለ ቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ምን
ያስተምራሉ? በተጨማሪም ይህ ሁሉም ቅዱሳት መጻሕፍት ለእምነታችን
ሊኖራቸው ስለሚገባው ወሳኝ ሚና ምን ሊነግረን ይገባል?
ዛሬ በመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ላይ ያለንን እምነት ለማዳከም በድብቅም ሆነ
በግልጽ የሚሠሩት ኃይሎች የትኞቹ ናቸው? መልሳችሁን በሰንበት ቀን ወደ ጥናት
ቡድን አምጡ።
ኪዳን ትንቢቶች፡ ክፍል 1
ኢየሱስ ስለ ማንነቱ ከኃይማኖት መሪዎች ጋር ባደረገው ውይይት የቅዱሳት
መጻሕፍትን ሥልጣን አረጋግጧል። በመጀመሪያ ሲታይ፣ የሃይማኖት መሪዎቹ በመጽሐፍ ቅዱስ
ስለሚያምኑ ይህን ማድረግ ለእርሱ አስፈላጊ መስሎ ላይታይ ይችላል። ነገር ግን ኢየሱስ ከእነሱ
ጋር ቢሆንም፣ ልባቸው የቱንም ያህል ቢደነድንና ምንም ያህል በጽናት ወቀሳውን ለመዋጋት
ቢሞክሩ አንኳን፣ የቅዱሳን ጽሑፎችን ሥልጣን ጎላ አድርጎ ገልጿል፤ እናም ይህንን ያደረገው
እርሱ ማን እንደሆነ ለማሳየት ነበር።
ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ዮሐንስ ኢየሱስ የብሉይ ኪዳን የመሲሑ ተስፋ ፍጻሜ መሆኑን
የሚያመለክቱ ብዙ ቀጥተኛ ጥቅሶችን ከብሉይ ኪዳን አጣቅሷል።
የሚከተሉት የሐዲስ ኪዳን እና የብሉይ ኪዳን አንቀጾች የሚገናኙት እንዴት ነው?
ማለትም፣ ሐዲስ ኪዳን ስለ ኢየሱስ ለመመስከር እነዚህን ጥቅሶች እንዴት ነው
የሚጠቀመው?
ዮሐ. 1:23፣ ኢሳ. 40:3
ዮሐ. 2:16፣ 17፤ መዝሙር 69:9
ዮሐ. 7:38፣ ኤር. 2:13
ዮሐ. 19:36፣ ዘኁ. 9:12
ዮሐንስ ብቻ ሳይሆን ጴጥሮስ፣ ጳውሎስ፣ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ሁሉም
የሐዲስ ኪዳን ጸሐፍት፣ በመንፈስ ቅዱስ መሪነት የናዝሬቱ ኢየሱስ ሕይወት፣ ሞት፣ ትንሣኤና
ወደ እግዚአብሔር ዙፋን መውጣት የብሉይ ኪዳን ትንቢቶች ፍጻሜዎች እንደሆኑ ደጋግመው
አፅንኦት ሰጥተዋል።
ምንም እንኳን ኢየሱስ አገልግሎቱን ወደተነበዩት ቅዱሳት መጻሕፍት ደቀ
መዛሙርቱን ያለማቋረጥ ያመላከተ ቢሆንም፣ በመጨረሻ ላይ ደቀ መዛሙርቱ ቅዱሳት
መጻሕፍት እርሱን እንደሚያመለክቱ የተረዱት መቼ ነበር? እነርሱ የተረዱት እርሱ ሞቶ ከተነሳና
ከተገለጠላቸው በኋላ ነበር። “ስለዚህ ከሙታን ከተነሣ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ይህን እንደ
ተናገረ አሰቡና መጽሐፍንና ኢየሱስ የተናገረውን ቃል አመኑ” (ዮሐ. 2፡22፣ ዮሐ. 20፡9ንም
ተመልከቱ)።
ኪዳን ትንቢቶች፡ ክፍል 2
ኢየሱስ የኃይማኖት መሪዎቹን “እናንተ በመጻሕፍት የዘላለም ሕይወት እንዳላችሁ ይመስላችኋልና እነርሱን ትመረምራላችሁ፤ እነርሱም ስለ እኔ የሚመሰክሩ ናቸው” ብሏቸው
ነበር (ዮሐንስ 5፡39)። ይህ ስለ ራሱ የተናገረው እንዴት ያለ አስደናቂ አባባል ነው!
ግምቶቹ ቢለያዩም፣ ነገር ግን አንዳንድ ምሁራን የናዝሬቱ ኢየሱስ በመቶዎች
የሚቆጠሩ የብሉይ ኪዳን ትንቢቶችን ፈጽሟል ብለው ይከራከራሉ። መጠኑ ምንም ይሁን ምን፣
አንድ ሰው ጥቂቶቹን ትንቢቶች ሳይቀር ለማሟላት ያለው ዕድል፣ ከጠቅላላው ትንሹን እንኳን
ቢሆንም፣ የሚያስደንቅ ነው። በየጊዜው አንድ ሰው ይህን ዓይነት ምሳሌ ይጠቀማል፤ የቴክሳስ
[የአሜሪካ አንድ ክልል] የሚያክል ቦታ፣ ከግማሽ ሜትር በላይ ቁመት ባለው ሳንቲሞች ሞልቶ፣
ከዚያም አንዱን ሳንቲም የሮዝ ቀለም በመቀባት ከሌሎቹ ጋር ስለ መደባለቅ አስቡ። ከዚያም
ዓይኑ በጨርቅ የታሰረ ሰውን ሮዙን ሳንቲም እንዲያነሳ አንድ ዕድል ብቻ ይስጡት። በአንድ
ምርጫ ብቻ እርሱ ወይም እርሷ ሮዙን ሳንቲም ለማግኘት ያለው ዕድል ምን ይመስላል?
ምንም ጥያቄ የለውም፤ የክርስቶስ ልደት፣ ሕይወት እና ሞት በብሉይ ኪዳን
ተተንብየዋል፣ እነዚህም እርሱ የሚጠበቀው መሲሕ መሆኑን የሚያሳዩ አስደናቂ ማስረጃዎች
ናቸው። ዮሐንስ እነዚህን የብሉይ ኪዳን ጽሑፎች ስለ ኢየሱስ ማንነት እና እኛ ለምን በእርሱ
አምነን እርሱ የሚያቀርበውን መዳን መቀበል እንደሚገባን ደጋግሞ ያመላክታል።
የሚከተሉት የዮሐንስ ወንጌል ጥቅሶች ኢየሱስ የመሲሐዊ ትንቢት ፍጻሜ
ስለመሆኑ ምን ያሳያሉ?
ዮሐ. 12:13፣ መዝሙር 118:26
ዮሐ. 12:14፣ 15፤ ዘካ. 9:9
ዮሐ. 13:18፣ መዝሙር 41:9
ዮሐ. 19:37፣ ዘካ. 12:10፣ ዘካ. 13:6
በምታምኑበት ነገር ምን ያህል ጠንካራ መሰረት አላችሁ? አንድ ሰው ኢየሱስን
እንደ መሲሕ አድርገህ ለምን ታምናለህ ብሎ ቢገዳደርህ ምን መልስ ልትሰጥ
ትችላለህ፣ እና ወዴትስ ትሄዳለህ፣ ይህንንስ እምነት መከላከል ምን ይጠቅማል?
እስካሁን ድረስ በዮሐንስ ወንጌል ላይ ባደረግነው ጥናት፣ ዮሐንስ በእርግጥም ኢየሱስ
እንዴት ተስፋ የተደረገበት መሲሕ እንደሆነና የአይሁድ ሕዝብ ሲናፍቀው የነበረው ታላቅ ተስፋን
እንዳመላከተ አይተናል።
ነገር ግን፣ የህዝቡ መንፈሳዊ መሪ የነበሩት፣ ብዙዎቹ የኃይማኖት መሪዎች በምትኩ
የእርሱ ትልቁ ጠላቶቹ ነበሩ።
ለምን?
ዮሐንስ 8:12-30ን ያንብቡ። በኢየሱስና በእነዚህ የኃይማኖት መሪዎች መካከል
ያለው ሁኔታ ምንድን ነው? ብዙዎች እርሱን ያልተቀበሉት ምክንያት ምን እንደሆነ
ለማብራራት የሚረዱት የትኞቹ ጥቅሶች ናቸው?
ኢየሱስ እርሱንም ሆነ አብን እንደማያውቁ ተናግሯል (ዮሐ. 8፡19)። ሁለቱንም ማወቅ
ነበረባቸው፣ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን ያታለሉ ነበሩ። በባሕላቸውና በፍልስፍናቸው
በጣም ተጠምደው ነበርና ኢየሱስ ምንም እንኳን ከፊት ለፊታቸው ቆሞ፣ ያደረጋቸውን
ነገሮች ሁሉ በማድረግ እና የተናገራቸውን ነገሮች በመናገር የአብ ኃይለኛ መገለጥ ቢሆንም
አልተቀበሉትም።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፡- “እናንተ ከታች ናችሁ” (ዮሐ. 8፡23)።
በሌላ አነጋገር፣ ምንም ያህል ኃይማኖተኛ ሊሆኑ ቢችሉም፣ እነዚህ መንፈሳዊና ፈሪሃ አምላክ
ያላቸው ሰዎች አልነበሩም። “የአምልኮት መልክ” ነበራቸው (2ኛ ጢሞ. 3፡5) የነበራቸውም ይህ
ብቻ ነበር። ውጫዊ ኃይማኖተኝነት ነበራቸው ነገር ግን ውስጣቸው የነበረው አለማመን ነበር።
ይህ አዲስ ነገር አልነበረም፡- “ይህ ሕዝብ በአፉ ወደ እኔ ይቀርባልና፥ በከንፈሮቹም
ያከብረኛልና፥ ልቡ ግን ከእኔ የራቀ ነውና፥ በሰዎች ሥርዓትና ትምህርት ብቻ ይፈራኛልና” (ኢሳ.
29: 13)። ይህንን ኢየሱስ ከብዙ መቶ ዘመናት በኋላ “የሰውም ሥርዓት የሆነ ትምህርት
እያስተማሩ በከንቱ ያመልኩኛል” በማለት አስተጋባ (ማር. 7፡7)። ሰብዓዊ ትምህርታቸው፣
ሰዋዊ ትእዛዛታቸው፣ “ከዚህ ዓለም” የሆነ (ዮሐ. 8፡23) ነበር፤ ኢየሱስ ደግሞ በዚያን ጊዜ
እንደተናገረው “እኔ ከዚህ ዓለም አይደለሁም” አለ (ዮሐንስ 8፡23)። እነዚህ ሰዎች ራሳቸውን
እያታለሉ መሆናቸው መጥፎ ነበር፤ አሳዛኙና ከዚህ የባሰው፣ ምንም እንኳን በሚያስደንቅ ሁኔታ
ዮሐንስ በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ በተገለጸው ልውውጥ ምክንያት “ብዙዎች በእርሱ አመኑ”
(ዮሐ. 8፡30) ብሎ ቢጽፍም እነርሱ ግን ሌሎች እንዲሳሳቱ አደረጉ።
ስለዚህ፣ ምንም እንኳን አመራሩ መጥፎ ቢሆንም፣ ብዙ አይሁዶች ከእነርሱ አልፈው
ኢየሱስ ማን እንደሆነ ለራሳቸው ማየት ችለዋል።
ኢየሱስ ከኃይማኖት መሪዎቹ ጋር ካደረገው ውይይት ምን ትምህርት አግኝታችኋል?
“ከታች” ሳንሆን “ከላይ” መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ልዩነቱንስ እንዴት
ማወቅ እንችላለን?
ከኤለን ጂ ዋይት የዘመናት ምኞት ከሚለው መፅሐፍ “ልባችሁ
አይታወክ” የሚለውን ከገጽ 662-680 ያንብቡ።
“እንደ ታላቅ የሐብት ክምችት እውነት ለአይሁዳዊያን ተሰጥቷቸው ነበር። የአኗኗር
ሁኔታቸው የሰማይ ማኀተም ያረፈበትና በክርስቶስ በራሱ የተቋቋመ ነበር። በጥላና አካል
እንዲሁም በምልክት ድንቅ የሆነው የመዳን ታሪክ ተገልጾላቸው ነበር። ሆኖም እነዚህ ሁሉ
ምሳሌዎች ያመላክቱ የነበረውን ክርስቶስ ሲመጣ ግን አላወቁትም። በእጃቸው የእግዚአብሔር
ቃል የነበረ ቢሆንም ከትውልድ ሲወርድ ሲዋረድ የመጣው ወግና ሥርዓት፣ ለእግዚአብሔር ቃል
የተሰጠው ሰብዓዊ (ምድራዊ) ትርጓሜ በየሱስ ውስጥ የነበረውን እውነት እንዳያዩ ጋረዳቸው።
የተቀደሰው ቃል መንፈሳዊ ሃብት ተከፍቶላቸው የነበረ ቢሆንም እነርሱ ግን ሳያውቁትና
ሳይቀበሉት ቀሩ።
“እግዚአብሔር እውነቱን ከሰዎች ደብቆ አያውቅም። ሰዎች ግን በራሳቸው ድርጊት
ቃሉ ግልጽ እንዳይሆንላቸው ያደርጋሉ። ክርስቶስ መሲሕ ስለመሆኑ ለአይሁድ በቂ ማስረጃ
ተሰጥቷቸው ነበር፤ ሆኖም ትምህርቱ ወሳኝ የሕይወት ለውጥ የሚጠይቅ ነበር። በመሆኑም
ክርስቶስን ከተቀበሉ ለዘመናት ሲደሰቱበት የነበረውን ወግ፣ ሥርዓት ራስ ወዳድና አምላካዊ
ያልሆኑ ልምምዶችን በሙሉ መተው እንዳለባቸው ተረዱ። የማይለወጠውን ዘላለማዊ
እውነት ለመቀበል መስዋዕትነት ይጠይቃል። በመሆኑም በክርስቶስ እምነት ለመመሥረት
እግዚአብሔር በማያዳግም መልኩ የሰጠውን ማስረጃ ለመቀበል አልወደዱም። በብሉይ ኪዳን
የተጻፈውን እንደሚያምኑ ሲናገሩ የነበረ ቢሆንም በዚያ ውስጥ ግን ስለ ክርስቶስ ሕይወትና
ባህሪይ የተነገረውን ምስክርነት ተቃወሙ። ከተለወጡ አስቀድመው ያከማቹትን አመለካከትና
ሃሰብ ለመተው ስለሚገደዱ ለመለወጥ ፈሩ። መንገድ፣ እውነትና ሕይወት የሆነውን የወንጌል
ሃብት ከእነርሱ ጋር የነበረ ቢሆንም ከሰማይ ሊሰጥ የሚችለውን ታላቁን ስጦታ እምቢ አሉ”
(ኤለን ጂ ዋይት፣ የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች፣ ገጽ 55)።
1. በኢየሱስ ሕይወት ውስጥ የተፈጸሙት ትንቢቶች እምነትን የሚገነቡት እንዴት ነው?
2. የኃይማኖት መሪዎቹ በኢየሱስ እንዳያምኑ ምክንያት የሆኑት ሦስት ወይም
አራት ዋና ዋና እንቅፋቶች ምንድን ናቸው? በዛሬው ዘመን እነዚህ ተመሳሳይ
መሠረታዊ መርሖዎች የተገለጡት እንዴት ነው?
3. በራስ መተማመናችሁ ዛሬ የሚገኝበትን ቦታ በየግላችሁ በዝርዝር ያዙ።
እምነታችሁን ሊያጠናክሩ የሚችሉት የትኞቹ እርምጃዎች ናቸው ብላችሁ
ታስባላችሁ?
4. በሰኞው ጥናት መጨረሻ ላይ ለቀረበው ጥያቄ የሰጣችሁት መልስ ስለ
ቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ምን ያስተምረናል? በቅዱሳን መጻሕፍት
የመጨረሻ እና ጠቅላላ ሥልጣን ላይ ጥርጣሬ የሚፈጥርን ማንኛውንም ነገር
መቃወም ያለብን ለምንድን ነው?