የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የማርቆስ መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሐምሌ 20 - 26

5ኛ ትምህርት

Jul 27 - Aug 2




ተዓምራቶች በሐይቅ ዙሪያ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ማር. 4:35–41፣ መዝ. 104:1–9፣ ማር. 5:1–43፣ ዘሁ. 27:17.


የመታሰቢያ ጥቅስ፡ “አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” መዝ. 119፡ 11)።

የኢየሱስ አገልግሎት በከፍተኛ ደረጃ ትኩረት ያደረገው ገሊላ በሚባል አገር፣ በተለይም በግምት 13 ማይል (21 ኪ.ሜ) ርዝመት እና 8 ማይል (13 ኪ.ሜ) ስፋት በነበረው በገሊላ ባህርና በዙሪያው ነበር። በአካባቢው ከነበሩ የውኃ አካሎች ትልቁ እንደመሆኑ በአካባቢው ለሚኖሩ ሰዎች የሕይወት ማዕከል ነበር።

ማርቆስ ምዕራፍ 4 የሚያበቃው ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የገሊላ ባህርን አቋርጠው ሲሄዱ ነበር። ኢየሱስ በመገሰጽ ጸጥ ያደረገው ወጀብና አውሎ ነፋስ ተነሣ። ማርቆስ ምዕራፍ ስድስትም በተመሳሳይ ትዕይንት ያበቃል፣ ነገር ግን በዚህን ጊዜ ኢየሱስ በጀልባ ውስጥ ወደነበሩ ደቀ መዛሙርቱ በውኃ ላይ እየተራመደ በመሄዱ ነበር። በውኃው ላይ በተፈጸሙ በእነዚህ ትዕይንቶች መካከል በምድር ላይ የተፈጸሙ በርካታ የኢየሱስ ተአምራቶችና የደቀ መዛሙርቱ የመጀመሪያ ሚስዮናዊ ተግባር ይገኙበታል። እነዚህ ታሪኮች የዚህ ሳምንት ትምህርት ርዕሶች ናቸው።

የእነዚህ ትዕይንታዊ ታሪኮች ሁሉን አካታች ባህሪያት አንባቢው ኢየሱስ ማን እንደሆነ እንዲያይ ማድረግ ነው። እርሱ አውሎ ነፋሱን ጸጥ ማድረግ፣ በአጋንንት የተያዘውን መፈወስ፣ ልብሱን ብቻ የነካችውን ሴት ማዳን፣ የሞተችውን ልጅ ከሙታን ማስነሳት፣ በአገሩ መስበክ፣ ደቀ መዛሙርቱን ለስብከት ተልዕኮ መላክ፣ በጥቂት እንጀራና ዓሳ 5000 ሰዎችን መመገብ እና በውኃ ላይ መሄድ የሚችል ነው። እነዚህ ነገሮች ደቀ መዛሙርቱ እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ወደ መረዳት እንዲቀርቡ የሚያደርጉ አስደናቂ የኃይል መግለጫዎች ናቸው። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሀምሌ 27 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሐምሌ 21
Jul 28

አውሎ ነፋስን ጸጥ ማድረግ


ማርቆስ 4:35–41ን ያንብቡ። በዚህ ታሪክ ውስጥ ምን ሆነ? ከዚህ ታሪክ ስለ ኢየሱስ ማንነት ምን ትምህርቶችን መውሰድ እንችላለን?



በማርቆስ ምዕራፍ 4 መጀመሪያ ላይ በባህር ዳርቻ ላይ ያለውን ሕዝብ ለማስተማር ኢየሱስ ወደ ጀልባዋ ገባ። ማርቆስ 4፡10-12 ላይ ከጀልባዋ በመውጣት ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለብቻቸው ያወራ ይመስላል። ከረዥም የዕለቱ ትምህርት በኋላ አሁን “እርሱ በነበረበት ሁኔታ” ኢየሱስን በጀልባ ወሰዱት፣ በሌላ አገላለጽ እርሱ እጅግ ደክሞት ነበር። በጀልባዋ ምቹ በሆነው ክፍል ተኝቶ ወዲያውኑ እንቅልፍ ወሰደው፣ ይህ የሆነው በጀልባዋ ጠንካራው ክፍል ሊሆን ይችላል።

በባህሩ ላይ ብርቱ አውሎ ነፋስ ከመነሳቱ የተነሣ ደቀ መዛሙርቱ ሲቀሰቅሱት ጀልባዋ በመስመጥ አደጋ ውስጥ ነበረች። አስገራሚ በሆነ ሁኔታ ኢየሱስ ነፋሱና ወጀቡ ጸጥ እንዲሉ አዘዘ። በባህሩ ላይ ታላቅ ጸጥታ ሆነ። ከዚህ መረዳት እንደሚቻለው ደቀ መዛሙርቱ በመለኮታዊው ኃይል መገለጥ ጥልቅ የሆነ ፍርሃት ገጥሞአቸው ነበር።

መዝ. 104:1–9ን ያንብቡ። አውሎ ነፋሱን ጸጥ ካደረገው ከክርስቶስ ጋር የያህዌህ ምስል ሊወዳደር የሚችለው እንዴት ነው?



ማርቆስ 4:35–41 ላይ ያለው ታሪክ በተለመደው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ንድፍ፣ በ“ሥነ-መለኮት”—እግዚአብሔር ወይም ከመላእክቱ አንዱ በመገለጥ ውስጥ ይገጥማል። በእነዚህ ክስተቶች ውስጥ አምስት ባህሪያት የተለመዱ ናቸው፡- (1) የመለኮት ኃይል መታየት፣ (2) ሰብአዊ ፍርሃት፣ (3) “አትፍራ” የሚለው ትዕዛዝ፣ (4) እግዚአብሔር ወይም መልአኩ የተገለጠበት የመገለጥ ቃላት፣ (5) ለራዕዩ (ለመገለጡ) ሰብአዊ ምላሽ። ከአምስቱ አራቱ በዚህ ታሪክ ውስጥ አሉ—አውሎ ነፋሱን ጸጥ ማድረግ የመለኮት ኃይል የታየበት ነው፣ የደቀ መዛሙርቱ ፍርሃት ሰብአዊ ፍርሃት ነው። “ለምን ትፈራላችሁ?” የሚለው ጥያቄ “አትፍሩ” ማለት ነው። “ይህ ማን ነው?” የሚለው የደቀ መዛሙርት ጥያቄ ሰብአዊ ምላሽ ነው።

በዚህ ውስጥ የጎደሉት (የሌሉት) የመገለጥ ቃላት ናቸው። ይህ የጎደለው ዝርዝር ስለ ኢየሱስ እውነቱ በሚገለጥበት በመላው መጽሐፍ ውስጥ በሚታየው ራዕይ/ ምስጢራዊነት ዓላማ ውስጥ ይጫወታል። በዚህ ቦታ “እንግዲህ ነፋስና ባህር የሚታዘዙለት ይህ ማን ነው?” የሚለው የደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ የጎደሉ የመገለጥ ቃላትን መልስ--እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ፣ ራሱ ጌታ ነው--የሚለውን እንዲሞላ አንባቢውን ይገፋዋል።

ስለ እግዚአብሔር ኃይል ያስቡ። ስለዚህ ኃይል ለመማርና በሕይወትዎ በሚገጥሙዎ ነገሮች ሁሉ በዚህ ኃይል ለመታመን መማር የሚችሉት እንዴት ነው?

ሐምሌ 22
Jul 29

ከጩኸት በላይ ሹክሹክታን መስማት ትችላለህ?


ማር. 5:1–20ን ያንብቡ። ከዚህ አስደናቂ ታሪክ ስለ ታላቁ ተጋድሎ ምን መማር እንችላለን? ደግሞ ስለ ኢየሱስ ኃይልስ ምን መማር እንችላለን?



በባህር ላይ የነበረው የመጀመሪያው ሌሊት የማይረሳ ከሆነ በቀጣዩ ንጋት ወደ ጌንሰርጥ መድረስም በተመሳሳይ ሁኔታ አስደናቂ ነው። በአጋንንት ተይዞ የነበረው ሰው ታሪክ ልብን በሚሰብር ሁኔታ ተቀምጧል። የሚገድቡ ነገሮችን በሙሉ በማሸነፍ በመቃብር ቦታ ይኖርና ገላውን በድንጋይ ይቆራርጥ ነበር።

“ሊያሸንፈውም የሚችል አልነበረም” (ማር. 5:4)—ከዚያም ከኢየሱስ ጋር ተገናኘ። ሰውየው ወደ ኢየሱስ ሮጠ—ስለ ደቀ መዛሙርቱ የተባለ ነገር የለም (ምናልባት ሸሽተው ሊሆን ይችላል)። ሰውዬው ከኢየሱስ አጠገብ በደረሰ ጊዜ ሰገደለት (በፊቱ ወደቀ)። “በፊቱ ወደቀ” የሚሉ ቃላት ፕሮስኪኒዮ (proskyneō) ከሚለው የግሪክ ግሥ የተተረጎሙ ሲሆኑ ቃሉ “መስገድ” የሚል ትርጉም አለው።

ሰውዬው ኢየሱስ ሊረዳው የሚችል ሰው መሆኑን የተገነዘበ ይመስላል።

ነገር ግን አፉን በከፈተ ጊዜ በውስጡ ከነበሩ አጋንንት ጩኸት በላይ የሰውዬውን ለእርዳታ የሚቀርበውን የልመና ሹክሹክታ ሊሰማ በሚችለው በኢየሱስ ላይ የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ጮኹ። ወደ አሳማው መንጋ ለመግባት እንዲፈቅድላቸው በጠየቁት ጊዜ ወደ አሳማዎቹ እንዲገቡ ኢየሱስ ፈቀደላቸው። ወደ 2000 የሚጠጋ የአሳማ መንጋ በሙሉ ወደ ገደል በመሮጥ በውኃ ውስጥ ሰመጡ። ለአሳማዎቹ ባለቤቶች ከፍተኛ የገንዘብ ቀውስ ያስከተለ ክስተት ነበር።

አስደናቂው ነገር አጋንንት ኢየሱስ ማን እንደሆነ በትክክል ማወቃቸውና በእርሱ ፊት አቅመ ቢስ መሆናቸውን ማወቃቸው ነው። እነርሱ የጠየቁትን ነገር እንዲያደርግላቸው ሁለት ጊዜ “መለመናቸው” (ማር. 5፡10፣12) ለዚህ ማስረጃ ነው። የእርሱ ኃይል ከእነርሱ በላይ መሆኑን በግልጽ አውቀው ነበር።

ይህ ታሪክ ሁለት ጠቀሜታ ያላቸው ባህሪያት አሉት። በመጀመሪያ፣ ንጽህና በጎደላቸው ነገሮች ወይም እንደ ብሉይ ኪዳን ሕግ ሥርዓታዊ በሆኑ የመርከስ ተግባራት የተሞላ ነው። መቃብሮችና ሙታን እርኩስ ናቸው (ዘሁ. 19፡11፣ 16)።

መድማት አንድን ሰው ያረክሰዋል (ዘሌ. 15)። እሪያዎች እርኩስ ናቸው (ዘሌ. 11፡7)።

ነገር ግን፣ ሁለተኛው ሁሉን የሚያቅፍ የእርኩሰት ዝርዝር በመልካምና በክፉ ኃይሎች መካከል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተመላለሰ የሚደረግ ጦርነት ነው።

ኢየሱስ አጋንንትን አወጣ (ለኢየሱስ ሁለት ነጥቦች ይያዙለታል)፣ አጋንንቶቹ አሳማዎቹን ገደሉ (ለሰይጣን ሁለት ነጥብ ይያዝለታል)። የከተማው ሰዎች ኢየሱስ እንዲሄድላቸው ጠየቁት (ሰይጣን ሁለት ነጥቦችን አገኘ)፣ ነገር ግን ኢየሱስ የተፈወሰውን ሰው ምስክሩ አድርጎ ላከው (ለኢየሱስ ሶስት ነጥቦች ይያዙለታል)።

በአንዳንድ መንገዶች ይህ ሰው ይሆናል ተብሎ የማይጠበቅ ሚስዮናዊ ነበር፣ ነገር ግን የሚነግረው አስደናቂ ታሪክ ነበረው።

እየተጋደላችሁ ያላችሁት ማንኛውም ነገር ቢኖር ሊረዳችሁ ስለሚችለው ስለ ኢየሱስ ኃይል ከዚህ ታሪክ ምን ትምህርት ማግኘት ቻላችሁ?

ሐምሌ 23
Jul 30

ከኢየሱስ ጋር በፍጥነት በሚሄድ ጀልባ ላይ


ማር. 5:21–24ን ያንብቡ። ስለ ኢያኢሮስ ጎልተው የሚታዩ ልዩ ባህሪያት ምንድር ናቸው?





እንደ ኢያኢሮስ ያሉ ኃይማኖታዊ መሪዎች በተለየ ሁኔታ የኢየሱስ ወዳጆች አልነበሩም (ማር. 1፡22፤ 3፡2፣6፤ ሉቃስ 13፡14)። ደግሞ ይህ ሰው ተስፋ የቆረጠ (ምርጫ ያልነበረው) ሰው ይመስላል። ይህ ተስፋ ቢስነቱ በኢየሱስ እግር ሥር በመንበርከኩ ታይቷል። ልመናው ወላጅ የሆነ ሰው ሁሉ የሚያስተውለው ነገር ነው። ምክንያቱም ልጁ እየሞተችበት ነው። ነገር ግን ኢየሱስ መርዳት እንደሚችል እምነት ነበረው። ኢየሱስ አንድም ቃል ሳይናገር ከልጅቷ አባት ጋር ወደ ቤቱ ለመሄድ ተነሳ።

ማርቆስ 5:25–34ን ያንብቡ። ወደ ኢያኢሮስ ቤት የሚደረገው ጉዞ እንዲቋረጥ ያደረገው ነገር ምንድር ነው?



ታሪኩ በድንገት በሌላ የሚያሳዝን ትዕይንት ይቋረጣል። ይህም ለአሥራ ሁለት አመታት አሰቃቂ የሆነ ህመም ስትለማመድ የነበረች ሴት ታሪክ ነበር። ይህ የኢያኢሮስና የሴትዮዋ ታሪክ በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ሁለተኛው በሌላ ታሪክ መሃል የገባ ታሪክ ነው (በ3ኛው ትምህርት ውስጥ የተጠናውን ማርቆስ 3፡20- 35ን ይመልከቱ)። በዚህ ታሪክ ውስጥ ተነጻጻሪ የሆኑ ገጸ ባህሪያት፣ ኢያኢሮስና ሴትዮዋ፣ ወደ ኢየሱስ እርዳታ ፈልገው መጡ።

ሴትዮዋ ከኋላው መጥታ የኢየሱስን ልብስ ነካች። ወዲያውኑ ከበሽታዋ ዳነች። ነገር ግን ኢየሱስ ቆም ብሎ “ልብሴን የነካው ማን ነው?” ብሎ ጠየቀ።

እጅግ ታማሚ የነበረችው ሴት በድንገት ደህና ሆነች። በሆነው ነገር ኢየሱስ የተቆጣ ስለመሰላት ፈራች። ይህ ስሜቶቿ የመሯት መንገድ ነው። ነገር ግን ኢየሱስ አካሏን ብቻ ሳይሆን መንፈሷንም ለመፈወስ ፈለገ።

ከዚያ በኋላ ወደ ኢያኢሮስ እንመለስ (ማርቆስ 5፡35-43ን ይመልከቱ)።

የምኩራብ አለቃ ለሆነው ሰውም ይህ ጉዳይ ያልተጠበቀ የስሜት ጉዞ ነበር። ኢየሱስ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ በቀር ማንም ከእርሱና ከልጅቷ ወላጆች ጋር አብሮ እንዲሄድ አልፈቀደም። ኢየሱስ ልጅቷ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አለ። አልቃሾቹን በሙሉ ወደ ውጭ አስወጥቶ የሞተችው ልጅ ወደነበረችበት ክፍል ሄደ። እጇን በመያዝ “ጣሊታ ቁሚ” አለ። ማርቆስ እነዚህን ቃላት “አንቺ ብላቴና፣ ተነሽ” ብሎ ተርጉሟል። ጣሊታ ማለት “ጠቦት” ማለት ሲሆን ልጅቷ የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ለወላጆቿ ብርቅዬ እንደሆነች የሚገልጽ ቃል ነው። ነገሮችን በምስጢር እንዲይዙ የተሰጠው ትዕዛዝ በመላው የማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ የሚገኝ የመገለጥ/ የምስጢራዊነት ዓላማ አካል ሲሆን ኢየሱስ ማን እንደሆነ ያመለክታል፤ ሆኖም በመጨረሻ ተደብቆ መቆየት አይችልም።

ሐምሌ 24
Jul 31

ተቀባይነትን ማጣትና ተቀባይነት ማግኘት


ማር. 6:1–6ን ያንብቡ። ኢየሱስ ይኖርበት የነበረው ከተማ ሰዎች እርሱን ያልተቀበሉት ለምን ነበር?



በተለምዶ ከትንሽ ከተማ የሆነ ሰው ዝነኛ ሲሆን በአገር ቤት ያሉ ሰዎች ትኩረት በማግኘቱ ደስ ይላቸዋል። በናዝሬት የሆነው ግን ይህ አይደለም። ኢየሱስ እንደ መምህርና ፈዋሽ ባገኘው ስኬት ተከፍተዋል ተደንቀዋልም። ከግንበኝነት ወደ መምህርነት ያሳየው ለውጥ ለመቀበል ከባድ መስሎ ታያቸው። ምናልባትም አብዛኞቹን ተዓምራቶች ያደረገው በቅፍርናሆም መሆኑ የሆነ ጠላትነት ስላለ ሊሆን ይችላል (ሉቃስ 4፡23ን ይመልከቱ)። ከቤተሰቡ ጋርም አለመስማማት ተፈጥሮአል (ማርቆስ 3:31–35). ማር. 6:7–30ን ያንብቡ። የአሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ተልዕኮ የመጥምቁ ዮሐንስን አንገት ከመሰየፍ ጋር የሚነጻጸረው እንዴት ነው?



ይህ በማርቆስ ወንጌል ውስጥ በሌላ ታሪክ መካከል የገባ ሶስተኛው ታሪክ ነው (3ኛውን ትምህርት ይመልከቱ)። አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት የኢየሱስን መልእክት ወደ ሁሉም ስፍራ የመውሰዳቸው ተልዕኮ መጥምቁ ዮሐንስን ከማሰርና ጸጥ ማሰኘት ጋር ይነጻጸራል። ደቀ መዛሙርቱ ሸክም እንዳይሸከሙና ከሌሎች ድጋፍ እንዲያገኙ ተነግሮአቸዋል። ይህ ስልት ሚስዮናውያን በሚያገለግሉአቸው ሰዎች ላይ እንዲደገፉ ስልት ያስቀምጣል። ይህም መልእክታቸውን ከሚፈለጉ ሰዎች ጋር ትስስር እንዲኖራቸው ይረዳል።

ነገር ግን መጥምቁ ዮሐንስ ከሄሮድስና ከቤተሰቡ ጋር የዚህ ዓይነት ትስስር አልነበረውም። ሴረኛዋ ሄሮዲያዳ የሄሮድስን እርስ በርሱ የሚቃረን ሀሳብና ፍትወተኛነት በመጠቀም ዮሐንስን ማስገደሏ አስደንጋጭ በሆነ ዝርዝር ተነግሮአል። የሄሮዲያዳ ልጅ የዮሐንስ ራስ በወጭት ተደርጎ እንዲሰጣት ባደረገችው እንግዳ ጥያቄ አሳፋሪ በሆነው ዕቅድ ላይ ተጨማሪ ነገር ሆኗል። የአጥማቂውን የማስጠንቀቂያ ድምጽ ጸጥ ማድረግ የተከሰተው ልክ መጥምቁ ዮሐንስ እንዳደረገው አሥራ ሁለቱ ሐዋርያት ንስሃን እያወጁ ሳለ ነበር። ዮሐንስ ተገድሎ የተቀበረ ሲሆን ኢየሱስ ከሙታን አንደሚነሳ ሁሉ (ማርቆስ ምዕራፍ 15 እና 16) እርሱም ከሙታን እንደተነሣ ሪፖርት ቀርቦ ነበር (ማር. 6፡14-16፣ 29)። እነዚህ ትይዩ የሆኑ ታሪኮች ለኢየሱስና ለተከታዮቹ ሊመጣ ያለውን ችግር የሚያመለክቱ ነበሩ።

ኢየሱስ ተቀባይነት አጥቶ እንደሚያውቅ እርስዎም ተቀባይነት አጥተው ያውቃሉ? ወይም ለመረዳት አስቸጋሪ በሆነ ችግር ውስጥ አልፈው ያውቃሉ? ከእነዚህ ልምምዶች ምናልባት በቀጣዩ ጊዜ ያንን የሚመስል ነገር ሲከሰት ሊረዳዎ የሚችል ምን ነገር ተማሩ?

ሐምሌ 25
Aug 01

የተለየ ዓይነት መሲህ


ማርቆስ 6:34–52ን ያንብቡ። ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ የተጋፈጡት ችግር ምን ነበር? ችግሩ የተፈታው እንዴት ነበር?



ደቀ መዛሙርት ከተልዕኮአቸው ከተመለሱ በኋላ ለእረፍት በገሊላ ባህር ምዕራባዊ ዳርቻ ወዳለው ገለልተኛ ስፍራ ሄዱ። ነገር ግን እነርሱ ከቦታው ከመድረሳቸው በፊት 5000 ሕዝብ ደርሶ ጠበቃቸው። ኢየሱስ እረኛ እንደሌለው መንጋ ሆነው አገኛቸው። ቀኑን ሙሉ አስተማራቸው። ቀኑ ሲመሽ ሕዝቡ ምግብ ለመፈለግ እንዲበተን ደቀ መዛሙርት ሀሳብ ሰጡ፣ ነገር ግን እነርሱ እንዲመግቡአቸው ነገራቸው። ደቀ መዛሙርቱ ችግሩን እንዴት እንደሚፈቱ ያስቡ የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ እንደነበር የተነሳው ክርክር (ማር. 6፡35-38) ያሳያል።

ነገር ግን ኢየሱስ ብዙ ሕዝብን ተአምራዊ በሆነ ሁኔታ በአምስት እንጀራና በሁለት ዓሣ በመመገብ ችግሩን ፈታው። የዚህ ታሪክ ባህሪያት በኢየሱስ ዘመን በነበረው ታዋቂ የመሲህ ጽንሰ ሀሳብ ውስጥ ይጫወታሉ። ይጠበቅ የነበረው መሲሁ እሥራኤልን ከጠላቶቿ ነጻ በማድረግ ጽድቅንና ሰላምን እንደሚያመጣ ነበር። ብዙ ቁጥር ያላቸው ወንዶች በስሜቶቻቸው በበረሃማ ቦታ የሚደረግ ወታደራዊ አመጽን ይዘው ይንቀሳቀሱ ነበር። (ከዮሐንስ 6:14፣ 15፤ የሐዋ. 21:38 ጋር ያወዳድሩ)።

ይህ አስተሳሰብ ሙሴ ከእርሱ በኋላ እሥራኤልን የሚመራ ሰው እንዲሾም እግዚአብሔርን ከጠየቀበት ከዘሁልቁ 27፡17 በከፊል በተወሰደውና ኢየሱስ ሕዝቡን “እረኛ እንደሌላቸው በጎች” መመልከቱን በሚያመለክተው ሀሳብ ተጠናክሯል። ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ እረኛ የሚገልጽ ይህ ሀረግ በብሉይ ኪዳን ውስጥ በሌላ ቦታ፣ በተለይም እሥራኤል መሪን ወይም ንጉሥን ከማጣት አንጻር ተጠቅሶ ይገኛል (ከ1ኛ ነገሥት 22፡17፤ 2ኛ ዜና 18፡16፤ ሕዝ. 34፡5፣6 ጋር ያነጻጽሩ)።

ሆኖም ኢየሱስ በውሸት ይጠብቁ የነበሩትን ሁኔታ አላሟላም። ከዚህ ይልቅ ደቀ መዛሙርቱን ወደ ሌላ ቦታ ከላከ በኋላ ሕዝቡን በተናቸው። በሮም ላይ አመጽ እንዲነሳ ከመምራት ይልቅ ምን አደረገ? ለጸሎት ወደ ተራራ ሄደ።

ሕዝቡ የጠበቁትን ነገር አላደረገም።

መሲሁ እሥራኤልን ነጻ እንደሚያወጣ ንጉሥ ተደርጎ ይታይ በነበረው ዝነኛ አመለካከት ቦታ፣ ሕዝቡን ከኃጢአት ባርነት ነጻ ለማውጣት መጣ። የእርሱ በባህር ላይ መራመድ በርግጠኝነት እርሱ የተፈጥሮ ጌታ መሆኑን ለደቀ መዛሙርቱ አሳይቷል። ነገር ግን እርሱ የመጣው ለመግዛት ሳይሆን ነፍሱን ለብዙዎች ቤዛ አድርጎ ለመስጠት ነበር (ማር. 10፡45)።

ትንቢትን በትክክል ማስተዋል ለምን እንደሚያስፈልግ ይህ ታሪክ ምን ሊነግረን ይገባል? የክርስቶስን የመጀመሪያ ምጽዓት በተሳሳተ መልክ መረዳት አንዳንዶችን ወደ አደጋ (ጥፋት) እንዲገቡ ከመራ ደግም ምጽዓቱን በተመለከተ የሚከሰተው የተሳሳተ መረዳት ለአንዳንዶች ምን ያህል አደጋ (ጥፋት) ያመጣባቸው ይሆን?

ሐምሌ 26
Aug 02


ተጨማሪ ሀሳብ


የዘመናት ምኞት ከሚለው የኤለን ጂ ኋይት መጽሐፍ “ሰላም፣ ጸጥ በል” እና “የእምነት መንካት” የሚሉ ርዕሶችን ከእንግሊዝኛው መጽሐፍ ገጽ 333-348 ላይ ያንብቡ።

“በእግዚአብሔር ሥልጠና ሥር ባሉ ሰዎች ሕይወት ውስጥ ከዓለምና ከወጎቹ ወይም ከልምምዶቹ ጋር የማይጣጣም ሕይወት መታየት አለበት።

እያንዳንዱ ሰው የእግዚአብሔርን ፈቃድ እውቀት የማግኘት የግል ልምምድ ሊኖረው ይገባል። እያንዳንዳችን ለልባችን ሲናገር በግል መስማት አለብን።

እያንዳንዱ ሌላ ድምጽ ጸጥ ሲልና በጸጥታ በፊቱ ስንጠብቅ የነፍስ ጸጥታ የእግዚአብሔር ድምጽ ከሌላ ድምጽ ተለይቶ እንዲሰማ ያደርጋል። ‘ጸጥ በሉ፣ እኔም አምላክ እንደሆንኩ እወቁ’ በማለት ይለምነናል (መዝ. 46:10)።

እውነተኛ እረፍት የሚገኘው እዚህ ብቻ ነው። ይህ ለእግዚአብሔር ለሚሰሩ ሁሉ ውጤታማ የሆነ ዝግጅት ነው። በጥድፊያው ውስጥ ባለው ሕዝብ እና አድካሚ በሆኑ የሕይወት እንቅስቃሴዎች መካከል በዚህ መልክ የታደሰ ነፍስ በብርሃንና በሰላም ከባቢ አየር ይከበባል። ሕይወት መልካም መዓዛ ያለውን አየር ይተነፍሳል፤ የሰዎችን ልብ የሚደርስ መለኮታዊ ኃይልንም ይገልጣል።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 363.

“እርካታ ያላገኘው ልባቸው ኢየሱስ እነርሱ የተመለከቱአቸውን እጅግ ብዙ አስደናቂ ሥራዎችን መስራት ከቻለ ለሕዝቡ ሁሉ ጤናን፣ ብርታትንና ሀብትን መስጠት አይችልምን? ከጨቋኞቻቸው ነጻ በማድረግ ወደ ሥልጣንና ክብር ከፍ ሊያደርጋቸው አይችልምን? የሚሉ ጥያቄዎችን አነሳ። ከእግዚአብሔር እንደተላከ ቢናገርም የእሥራኤል ንጉሥ ለመሆን እምቢ ማለቱ መረዳት ያልቻሉት ምስጢር ነበር። እምቢ ማለቱ የተሳሳተ ትርጉም ተሰጥቶት ነበር። ብዙዎች ስለ ተልዕኮው መለኮታዊ ባህሪይ እርሱ ራሱ ጥርጣሬ ስላለበት ከእግዚአብሔር ስለመላኩ ማረጋገጫ መስጠት አልደፈረም ከሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ። ከዚህ የተነሣ ልባቸውን ለአለማመን ክፍት በማድረጋቸው ሰይጣን የዘራው ዘር ያንኑ ዘር የሚመስል በስህተት የመረዳትና የክህደት ፍሬ አፈራ።”—The Desire of Ages, p. 385. የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ


የመወያያ ጥያቄዎች




1. የሆነ ሰው ኢየሱስ እርስዎን ከምን ነጻ አደረገዎት ብሎ ቢጠይቅዎ ምን መልስ ይሰጣሉ?

2. አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር እንደ መጥምቁ ዮሐንስ ያሉ መልካም ሰዎችን በወህኒ ቤት እንዲጣሉና እንዲገደሉ የሚፈቅደው ለምን እንደሆነ ተወያዩ። እነዚህ ከባድ ነገሮች ቢደርሱም ምን መጽናኛ ወይም ተስፋ ማግኘት እንችላለን?

3. ጥቂት ሀብት ላለው የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ 5000 ሰዎችን ኢየሱስ መመገቡ ምን ትምህርት ይሰጣል?

4. በማርቆስ ምዕራፍ 5 እና 6 ላይ ለኢየሱስ ከተሰጠው ስዕል አንጻር ዛሬ ስለ ኢየሱስ ያሉ ዝነኛ አመለካከቶችን ያወዳድሩ። የፖሊቲካ ሥልጣን ለመፈለግና ሌሎችን ለመጨቆን ኢየሱስን ስለሚጠቀሙት ሰዎችስ ምን ይላሉ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL