የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የማርቆስ መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሐምሌ 13 - 19

4ኛ ትምህርት

Jul 20 - 26




ምሳሌዎች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ማር. 4:1–34፣ ያዕቆብ 1:21፣ ኢሳ. 6:1–13፣ መዝ. 104:12፣ ዳን. 4:10–12።


የመታሰቢያ ጥቅስ:- “አላቸውም፦ ምን እንድትሰሙ ተጠበቁ። በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል ለእናንተም ይጨመርላችኋል። ላለው ይሰጠዋልና፤ ከሌለውም ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል።”(ማርቆስ 4:24፣ 25)።

የዚህ ሳምንት ጥናት የሚያተኩረው በማርቆስ ምዕራፍ 4 በተጠቀሱ ምሳሌዎች ላይ ነው። በብዛት ተመሳሳይ የሆኑ ታሪኮችን ከያዙት ከማቴዎስ፣ ማርቆስና ሉቃስ ወንጌሎች መካከል የማርቆስ ወንጌል አነስተኛ ምሳሌዎችን ይዟል። ምሁራን ለበርካታ ዓመታት በኢየሱስ ምሳሌዎች ትርጉምና አተረጓጎም ላይ ሲከራከሩ ነበር። እንዴት መተርጎም እንዳለባቸው፣ ምን ማለታቸው እንደሆነ፣ ኢየሱስ ለምን እንደተጠቀማቸው፣ ምን ዓይነት ትምህርት እንዲያስተላልፉ እንደታቀደ እና እንዴት ቃል በቃል መወሰድ እንዳለባቸው ወይም ሙሉ በሙሉ ምሳሌያዊ ስለ መሆናቸው፣ ወዘተ ሲከራከሩ ኖረዋል።

በዚህ ሳምንት ጥናት እነዚህን ጉዳዮች በሙሉ ማቃለል እንደማንችል ግልጽ ነው። ከዚህ ይልቅ ምሳሌዎቹን በመመልከት በእግዚአብሔር ጸጋ በምሳሌዎቹ አማካይነት ኢየሱስ ያስተላለፋቸውን መልእክቶች ወደ ማስተዋል እንደርሳለን።

ማርቆስ 4 አምስት ምሳሌዎች አሉት። እነርሱም የዘሪው ምሳሌ፣ የመብራት ምሳሌ፣ የመስፈሪያ ምሳሌ፣ የዘር ምሳሌ እና የሰነፍጭ ቅንጣት ምሳሌዎች ናቸው። የምዕራፉ አብዘኛው ክፍል የሚሽከረከረው በዘሪው ምሳሌ ዙሪያ ነው። በመጀመሪያ ታሪኩ የተነገረ ሲሆን በመቀጠልም ምሳሌዎቹ የተሰጡበት ምክንያትና የምሳሌው ትርጉም ተሰጥቷል። ይህ ሶስት ደረጃ ያለው አቀራረብ የእሁድ፣ የሰኞና የማክሰኞ ጥናቶች የሚያተኩሩበት ይሆናል። ከዚያም ሌሎቹ ምሳሌዎች ረቡዕና ሀሙስ የሚጠኑ ርዕሶች ይሆናሉ። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሀምሌ 20 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሐምሌ 14
Jul 21

የዘሪው ምሳሌ


ማር. 4:1–9ን ያንብቡ። የተለያዩ የአፈር ዓይነቶች ምን ይመስላሉ? በእነዚህ የአፈር ዓይነቶች ላይ የሚወድቁ ዘሮች ምን ይሆናሉ?





ሰዎች በወንጌላት ውስጥ ያሉ የኢየሱስ ምሳሌዎችን ሲያነቡ ብዙ ጊዜ ኢየሱስ ወደሚሰጠው ትርጉም መዝለል ይፈልጋሉ። የእነዚህ ታሪኮች ዋና ነጥብስ ቢሆን ለክርስትና ሕይወት የሚሆን መንፈሳዊ ትምህርት ማስተማር አይደለምን? አዎን፣ ግን አንዳንድ ጊዜ “የእግዚአብሔር መንግሥት ይህን ትመስላለች” ወይም “ሰሚ ጆሮ ያለው ይስማ” የሚሉ አጫጭር አስተያየቶችን ከመስጠት ያለፈ ኢየሱስ ምሳሌዎቹን አያብራራቸውም።

ከዚህ የተነሣ የምሳሌው የተለያዩ የትረካ ባህርያት የሚያመለክቱትን አቅጣጫ ለማወቅ ቀስ ማለትና ታሪኩን ራሱን መተንተን መልካም ነው። ለዘሪው ምሳሌ ይህንን ማድረግ የተለያዩ ሀሳቦችን ያስገኛል። በእያንዳንዱ ሁኔታ ዘሩ ተመሳሳይ ነው፣ ነገር ግን ይህ ዘር በአራት የተለያዩ ዓይነት መሬቶች (አፈር) ላይ ይወድቃል። የአፈሩ ዓይነት ዘሩ በሚያመጣው ውጤት ላይ ከፍተኛ ተጽእኖ አለው። ምሳሌው ቀጣይነት ያለው አንድ ታሪክ ከመሆን ይልቅ በእያንዳንዱ አውድ የተነገሩ አራት ራሳቸውን የቻሉ ታሪኮች ናቸው። ታሪኩን ለመጨረስ የጊዜ ርዝመት በእያንዳንዱ ቀጣይ ታሪክ ላይ እየጨመረ ይሄዳል።

በመንገድ ዳር የወደቀው ዘር ወዲያውኑ በወፎች ተበልቷል። “ ሲዘራም አንዳንዱ በመንገድ ዳር ወደቀና ወፎች መጥተው በሉት።” (ማር. 4:4)።

በጭንጫ መሬት ላይ የወደቀው ዘር ጸሐይ አቃጥሎት ውጤት አልባ ሆኖ ለመቅረት የወሰደበት ጊዜ ጥቂት ቀናት ወይም ሳምንታት ብቻ ነበር።

አረም ባለበት መሬት (በእሾክ መካከል) የወደቀው ዘር በእሾክ በመታነቁ ውጤት ወደሌለው ፍጻሜ ለመድረስ ረዘም ያለ ጊዜ ወስዶበታል። በመልካም መሬት ላይ የወደቀው ዘር ለአዝርዕት እድገት የተለመደውን ከሁሉም ረዘም ያለ ጊዜ፣ ያውም መላውን የእድገት ወቅት ወስዶበታል።

ከታሪኮቹ መካከል ሶስቱ ስለ ውድቀት የሚገልጹ ናቸው። የመጨረሻው ብቻ ስለ ስኬት፣ መልካም ስለሆነው የተትረፈረፈ ምርት የሚገልጽ ነው።

የታሪኮቹ ርዝመት፣ እያንዳንዱ ቀጣይ ታሪክ ከመጀመሪያው ይልቅ ረዘም ያለ ጊዜ እየወሰደ መሄድና አንዱ ታሪክ ብቻ ስለ ስኬት መሆኑ ከዚህ ከአንዱ የተትረፈረፈ ስኬት ካስገኘው በቀር ሁሉም የውድቀትን አደጋ የሚጠቁሙ ናቸው። ታሪኩ ደቀ መዝሙርነት ስለሚያስከፍለው ዋጋና ከዚህ ጋር አብረው ስላሉ አደጋዎች፣ በተቃራኒው ደግሞ ኢየሱስን መከተል ስለሚያስገኘው የተትረፈረፈ ሽልማት የሚጠቁም ይመስላል።

ከተፈጥሮ መማር የምንችላቸው ሌሎች ተጨማሪ መንፈሳዊ ትምህርቶች ምንድር ናቸው?

ሐምሌ 15
Jul 22

ኢየሱስ የሰጠው ትርጉም


ኢየሱስ ለምሳሌዎቹ ወዲያውኑ ትርጉም ሳይሰጥ ምሳሌዎቹን ተናግሮ ጨረሰ። ጥቅሱ እንደሚገልጸው (ማር. 4፡1) ኢየሱስ የተናገረው “በብዙ ሕዝብ” ፊት ነበር። ምሳሌው ምን ማለት እንደሆነ ኋላ ያብራራው ለትንሽ ቡድን ብቻ ነበር (ማር. 4፡10)።

ማር. 4:13–20ን ያንብቡ። ኢየሱስ የዘሪውን ምሳሌ የተረጎመው እንዴት ነበር?



ኢየሱስ ምሳሌውን የተረጎመው በታሪኩ ውስጥ ያሉ በርካታ ዝርዝሮች የሚወክሉትን ከታሪኩ ውጭ የሆኑ ነገሮችን በመለየት ነበር። ትርጉሙ የታሪኩን እያንዳንዱን ተናጥል ዝርዝር የሚያመለክት ሳይሆን በተጨባጭ ዓለም ውስጥ ያለውን ነገር የሚያመለክት ልል ምሳሌ ነው።

ኢየሱስ ዘሩ “ቃሉ” እንደሆነ አመልክቷል። ይህ በተለየ ሁኔታ በኢየሱስ በተሰበከው ሁኔታ የእግዚአብሔርን ቃል ያመላክታል። ያዕቆብ 1፡ 21 እንዲህ ይላል፡- “ስለዚህ ርኵሰትን ሁሉ የክፋትንም ትርፍ አስወግዳችሁ፥ ነፍሳችሁን ማዳን የሚችለውን በውስጣችሁም የተተከለውን ቃል በየዋህነት ተቀበሉ።” የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

የተለያዩ የአፈር ዓይነቶ የተለያዩ ዓይነት አድማጮች ናቸው። ኢየሱስ በተረጎመው መሰረት ሁሉም ቃሉን ሰምተዋል፤ ሁሉም የአፈር ዓይነቶች ዘር ተዘርቶባቸዋል። ነገር ግን አቀባበላቸው ላይ ልዩነት አለ። በመንገድ ዳር የተወከለው መሬት ጠንካራ ስለነበር ዘሩን ወፎች በሉት። ኢየሱስ ይህንን ክስተት ሰይጣን እውነትን ከሰዎች ከመውሰድ ጋር አገናኝቶታል። ጭንጫው አፈር ጥልቀት አልነበረውም። ኢየሱስ ይህንን ጥልቀት የሌለው መሰጠት ካላቸው ሰዎች ጋር አገናኝቷል። ደቀ መዝሙርነት የሚያስፈልገውን ዋጋ በትክክል አልተረዱትም። አረም የሞላበት አፈር የተዘራበትን ዘር አነቀው። ይህ ቃሉን የሚያንቀውን የሕይወት ጭንቀትና ሀብት እንደሚወክል ኢየሱስ አብራራ። ነገር ግን መልካሙ መሬት (አፈር) የሚወክለው አድጎ የተትረፈረፈ ምርት እንዲሰጥ ቃሉን የሚሰሙትንና የሚቀበሉትን ሰዎች ነው።

ከሁሉ ረዥም ማብራሪያ የተሰጠው ስለ ጭንጫው መሬትና አረም ስለሞላበት መሬት ነው። ኢየሱስ በጭንጫ መሬት የተወከሉ አድማጮችን ሲገልጽ እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ ነገሮችን--ቃሉን በደስታ የሚቀበሉ ግን ጊዜያዊ ደቀ መዛሙርት መሆናቸውን--አመልክቷል። ስደት ሲመጣ ወደ ኋላ ያፈገፍጋሉ። አረም በሞላበት መሬት የተመሰሉት አድማጮች የዚህ ተቃራኒ ናቸው። አስቸጋሪ ጊዜ ሲመጣ ወደ ኋላ አያፈገፍጉም፣ ነገር ግን ከሁኔታዎች መመቻቸት የተነሣ ትኩረታቸው በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ ከመሆን ይልቅ በዓለማዊ ጉዳዮች ላይ ነው። ጭንቀታቸውና ስጋታቸው የሚያተኩረው ዓለም በሚሰጣቸው ነገር ላይ ነው።

ስለ ራስዎ ሕይወት ያስቡ። ከዚህ መንገድ ባህሪያት፣ ከእሾሃማው ወይም ከጭንጫው መሬት ባህርያት ውስጥ አንዱም ቢሆን ወደ ሕይወት ልምምድዎ ሾልኮ እየገባ ነው? ይህ የሚሆነው እርስዎ በማይገነዘቡት ረቂቅ በሆነ መንገድ ነው። አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ ለመለወጥ ምን ምርጫ ማድረግ ይችላሉ?

ሐምሌ 16
Jul 23

ምሳሌዎቹ የተሰጡበት ምክንያት


ማር. 4:10–12ን ያንብቡ። ኢየሱስ በምሳሌ ያስተማረው ለምን ነበር?





እነዚህን ጥቅሶች ላይ ላዩን ማንበብ ኢየሱስ በምሳሌዎች ያስተምር የነበረው የውጭ ሰዎችን በጨለማ ውስጥ ለማቆየት ነው የሚል ስሜት ይሰጣል።

ነገር ግን የዚህ ዓይነቱ አመለካከት በማርቆስ መጽሐፍ ሌሎች ቦታዎች ከተፈጸሙ የኢየሱስ ተግባሮች ጋር አይገጥምም። ማርቆስ 3፡ 5ና 6 ላይ በኃይማኖት መሪዎች ልበ ደንዳናነት እንዳዘነ እንመለከታለን። ማርቆስ 3፡22-30 ላይ ኢየሱስ ለጸሐፍት መከራከሪያ ትኩረት በመስጠት የተሳሳቱበትን ምክንያት በዝርዝር ያብራራል።

ማርቆስ 12፡1-12 ላይ ኢየሱስ ስለ ገበሬዎቹ የተናገረው ምሳሌ ስለ እነርሱ እንደሆነ የኃይማኖት መሪዎች ተረዱ። ምሳሌው በእርሱ ላይ ያሰቡት ተንኮል ወዴት እያመራ እንደሆነና ይህንን ተከትሎ ስለሚመጣው አሰቃቂ መዘዝ ማስጠንቀቂያ ነበር። ለእነርሱ ግድ ባይኖረው ኖሮ አያስጠነቅቃቸውም ነበር። ከዚህ የተነሣ በማርቆስ ምዕራፍ 4 ላይ የተጻፉ የኢየሱስ ቃላት እርሱ ሊያስተላለፍ የፈለገው ነጥብ ምን እንደሆነ ለመገንዘብ በቅርበት መመርመርን ይሻሉ። ኢየሱስ ኢሳይያስ 6፡9ና 10ን በራሱ አገላለጽ እያቀረበ ነው።

ኢሳ. 6:1–13ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ኢሳይያስን የገጠመው ነገር ምንድር ነው? ለእሥራኤል ሕዝብ እንዲያደርስ የተሰጠው መልእክት ምንድን ነው?



ኢሳይያስ በራዕይ እግዚአብሔርን በቤተ መቅደስ ውስጥ በመመልከቱ የእግዚአብሔር ክብርና የራሱ እርኩሰት ከአቅሙ በላይ ሆኑበት። እግዚአብሔር አንጽቶት አስደንጋጭ የሆነ መልእክት እንዲያስተላልፍ ላከው። ልክ እንደ ማርቆስ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ብዙ ማጽናኛ ካለበት ከሌላው የኢሳይይስ መጽሐፍ ክፍል ጋር አብሮ የማይሄድ ሀሳብ ያቀርባል።

በኢሳይያስ ምዕራፍ 6 ላይ የቀረበው መልእክት ሰዎች ከክፉ መንገዳቸው እንዲመለሱ ለማድረግ የቀረበ አስደንጋጭ መልእክት ነው። በማርቆስ ውስጥ የኢየሱስን ቃላት ለመረዳት ቁልፉ ያለው በማርቆስ 3፡ 35 ላይ ነው። አንድ ሰው የኢየሱስን ቃላትና ትምህርቶች ለመረዳት የእግዚአብሔርን ፈቃድ መፈጸም አለበት (ማር. 3፡35)። ይህ ግለሰቡን የኢየሱስ ቤተሰብ አባል እንዲሆን ያደርገዋል።

ኢየሱስ በአጋንንት ተይዟል ብለው የወሰኑ ሰዎች አይሰሙትም።

ኢየሱስ ከኢሳይያስ ምዕራፍ 6 የጠቀሰበት ምክንያት እግዚአብሔር የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ሰዎችን በውጭ እያስቀራ ስለሆነ ሳይሆን የራሳቸው አስቀድመው የያዙአቸው አስተሳሰቦችና የልባቸው ድንዳኔ የሚያድነውን እውነት እንዳይቀበሉ ስለሚከለክላቸው ነው። ይህ እውነት የዘሪው ምሰሌ ሙሉ ሀሳብ ነው። እያንዳንዱ ሰው የትኛው ዓይነት መሬት መሆን እንዳለበት ይመርጣል። ለኢየሱስ ራሳቸውን አሳልፈው ለመስጠት ወይም ላለመስጠት ሁሉም ለራሳቸው ይወስናሉ።

በመጨረሻ እያንዳንዳችን እንመርጣለን።

ሐምሌ 17
Jul 24

መብራት እና የመስፈሪያ ቅርጫት


ማር. 4:21–23ን ያንብቡ። በመብራቱ ምሳሌ ኢየሱስ የተለየ አጽንዖት የሰጠበት ነገር ምንድር ነው?



በኢየሱስ ዘመን እርሱ በነበረበት የዓለም ክፍል የነበሩ ቤቶች እንደየቦታውና የሀብት መጠን በመጠንና በአሰራራቸው ልዩነት ነበራቸው። ቤቶቹ ግሪኮች ዙሪያው በታጠረ ግቢ ዙሪያ የሚገነቡበትን ምሳሌ የተከተሉ ቢሆኑም የቅንጡነት ደረጃቸው ይለያይ ነበር። ወይም ኢየሱስ ገበሬዎች ስለሚኖሩባቸው ትናንሽ ቤቶች እየተናገረ ሊሆን ይችላል። ቤቱ ትልቅ ቢሆን ወይም ትንሽ ጉዳዩ መርሁ ነው። ያውም አንድ ቀን ስለ ኢየሱስ እውነቱ የሚገለጥ መሆኑ ነው።

ማርቆስ 4፡21 ላይ ኢየሱስ ሁለት ጥያቄዎችን ይጠይቃል። የመጀመሪያው “መብራትን ከዕንቅብ ወይም ከአልጋ በታች ሊያኖሩት ያመጡታልን?” የሚለው ጥያቄ አሉታዊ መልስ እንዲሰጥ የሚጠብቅ ነው። ሁለተኛው “በመቅረዝ ላይ ሊያኖሩት አይደለምን?” የሚለው ጥያቄ አዎንታዊ መልስ የሚጠብቅ ነው።

ኢየሱስ ይህንን ነጥብ ለማብራራት የማይመስልና የሚያስቅ ሁኔታ ያቀርባል። መብራቶች ተግባራቸው ብርሃን መስጠት ነው፤ ይህ ካልሆነ ግን ጥቅም አይኖራቸውም። ማርቆስ 4:22 ምሳሌውን የሚያብራራው ወደ አደባባይ እየወጡ ያሉ ምስጢሮችን በመጥቀስ ነው። ኢሜይሉ ወይም ኮምፒዩተሩ በጠላፊዎች የተጠለፈበት ሰው ምስጢሮቹ ወደ አደባባይ እየወጡ መሆናቸውን ያውቃል! ነገር ግን ኢየሱስ እየተናገረ የነበረው ስለ ወንጌል ነው። ማርቆስ 4:24፣ 25ን ያንብቡ። ኢየሱስ በመስፈሪያ ቅርጫቱ ምሳሌ እያስተላለፈ ያለው መልእክት ምን ነው?



በዓለም ላይ በብዙ ቦታዎች ትኩስ ምርቶች ክፍት በሆኑ የገበያ ቦታዎች ይሸጣሉ። ሻጮች ምርቶቻቸውን የሚመዝኑባቸው መሣሪያዎች ነበሩአቸው።

ገዥው በጥሩ ሁኔታ እንደተስተናገደ እንዲሰማው ሻጮች በሚሸጡት ነገር ላይ መመረቅ የተለመደ ነበር። ኢየሱስ ለእውነት ክፍት የመሆንን ነጥብ ለማስጨበጥ ጥሩ ሻጮች ገዦቻቸውን እንዴት ይይዙ እንደነበር ይጠቅሳል። አንድ ሰው ግልጽ ከሆነና እውነትን ከተከተለ የበለጠውን ያገኛል። ነገር ግን ብርሐንን አልቀበል ካለ ከዚህ በፊት የነበረውም ይወሰድበታል።

በምትሰፍሩበት መስፈሪያ ይሰፈርላችኋል የሚለውን መርህ መማር የምንችለው እንዴት ነው? ከሌሎች ጋር በሚኖራችሁ ግንኙነት ሁሉ ስለዚህ ነገር አስቡ።

ሐምሌ 18
Jul 25

የሚያድግ ዘር ምሳሌዎች


ማር. 4:26–29ን ያንብቡ። የዚህ ምሳሌ ቀዳሚ ትኩረት ምንድን ነው?



አብዛኛው የማርቆስ ወንጌል ተመሳሳዩ በማቴዎስ ወይም በሉቃስ ወንጌል ወይም በሁለቱም ውስጥ አለ። ነገር ግን ይህን ምሳሌ በተመለከተ እንደዚህ አይደለም። ይህ ምሳሌ በማርቆስ ወንጌል ብቻ የሚገኝ ነው። የዚህ አጭር ምሳሌ ትኩረት የእድገት ሂደት ነው። ይህ የእግዚአብሔር መንግሥት የሚሰራበት መንገድ እንደሆነ ኢየሱስ ያመለክታል። ሰብአዊ ፍጡራን የሚጫወቱት ሚና ቢኖርም እውነተኛ እድገት የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ማብቂያ የሌለው ሂደት አይደለም። በዘሩ ለፍሬ መድረስ ታሪኩ በድንገት ወደ ፍጻሜው ይመጣል።

በተመሳሳይ ሁኔታ የክርስቶስ ዳግም ምጽዓት የዓለምን ታሪክ በድንገት ወደ ፍጻሜ ያመጣዋል። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ማር. 4:30–32ን ያንብቡ። የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ በደንብ አጽንዖት የሰጠው በምን ላይ ነው?



ይህ ምሳሌ አንድ እጅግ ጥቃቅን የሆነ ነገር እንዴት አስደናቂ ወደሆነ ትልቅ ነገር እንደሚያድግ አጽንዖት በመስጠት ይገልጻል። የሰናፍጭ ቅንጣት የመሀል ርዝመት ከአንድ እስከ ሁለት ሚሊ ሜትር (ከ0.039-0.079 ኢንች) ይሆናል።

ምናልባት በዚህ ቦታ የተገለጸው የሰናፍጭ ቅንጣት ትንንሽ ዘሮች (በአንድ ግራም ውስጥ ከ700 በላይ ዘሮች) ያሉት ጥቁሩ የሰናፍጭ ቅንጣት (ብራሲካ ኒግራ) ሳይሆን አይቀርም። በዓለም ላይ ካሉ ዘሮች ሁሉ ትንሾቹ ባይሆኑም ዘሮቹን ከሚሰጠው እስከ 3 ሜትር (አሥር እግር) ከፍታ ከሚያድግ ተክል ጋር ሲወዳደሩ ትንሽ ናቸው። በሰናፍጭ ዛፍ ሥር ወፎች እንኳን ጎጆአቸውን እንደሚሰሩ ኢየሱስ አመልክቷል። የመጨረሻው ጥቅስ ከመዝሙር 104፡ 12 እና ከዳንኤል 4፡10-12 የተጠቀሰ ነው። መዝሙር 104 ዓለምን ስለፈጠረው የእግዚአብሔር ኃይል የሚናገር ሲሆን ዳንኤል 4 ናቡከደነፆርን ዓለም በሙሉ ከሥሩ መጠለያና ምግብ ባገኘበት ታላቅ ዛፍ ይወክለዋል።

ኢየሱስ ማሳወቅ የፈለገው ነጥብ እጅግ ትንሽ ሆኖ የጀመረው የእግዚአብሔር መንግሥት ታላቅና አስደናቂ ይሆናል። በኢየሱስ ዘመን የነበሩ ሰዎች ጥቂት ደቀ መዛሙርትን ያስከተለውንና ከአቧራማው ገሊላ የነበረውን ተጓዥ ሰባኪ ንቀውት ሊሆን ይችላል፣ ነገር ግን የእርሱ የጸጋ መንግሥት በመላው ዓለም መስፋፋቱን ጊዜ አሳይቷል።

“ ‘ለአሕዛብም ሁሉ ምስክር እንዲሆን ይህ የመንግሥት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል፥ በዚያን ጊዜም መጨረሻው ይመጣል።” (ማቴ. 24:14)።

ኢየሱስ ትንቢቱን በተናገረ ጊዜ ቤተ ክርስቲያን ምን ትመስል እንደነበር ያስቡ። ይህ ለእኛ አስደናቂና እምነትን የሚያጸና ትንቢት የሚሆነው ለምንድር ነው?

ሐምሌ 19
Jul 26


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ጂ ኋይት የክርስቶስ ምሳሌያዊ ትምህርቶች ከሚለው መጽሐፍ “ ‘ዘሪ ሊዘራ ሄደ’ የሚለውን ርዕስ በእንግሊዝኛው ከገጽ 33–61 የንብቡ።

“እውነተኛ ቅድስና በእግዚአብሔር አገልግሎት ሙሉ ሆኖ መገኘት ነው።

ይህ የእውነተኛ ክርስቲያን የአኗኗር ሁኔታ ነው። ክርስቶስ ላልተቆጠበ ቅድስና እና ላልተከፋፈለ አገልግሎት እየጠየቀን ነው። እርሱ ልባችንን፣ አእምሮአችንን፣ ነፍሳችንን እና ብርታታችንን እንድንሰጠው እየጠየቀን ነው። ራስ ወዳድነት መኖር የለበትም። ለራሱ የሚኖር ሰው ክርስቲያን አይደለም።

“ፍቅር የተግባር መርህ መሆን አለበት። ፍቅር በሰማይና በምድር የእግዚአብሔር መንግሥት መርህ ነው፤ የክርስቲያን ባህርይ መሰረትም መሆን አለበት። ራስን ሰጥቶ እንዲያገለግል የሚያደርገው ይህ ብቻ ነው። ፈተናና ችግርን መቋቋም እንዲችል የሚያደርገው ይህ ብቻ ነው።

“ፍቅር የሚገለጠው በመስዋዕትነት ነው። የድነት ዕቅድ የተመሰረተው በመስዋዕትነት ነው። ይህ መስዋዕትነት ሊለካ እስከማይቻል ድረስ እጅግ ሰፊ፣ ጥልቅና ከፍ ያለ ነው። ክርስቶስ ሁሉን ስለሰጠን ክርስቶስን የሚቀበሉ ለአዳኛቸው ብለው ሁሉን መስዋዕት ለማድረግ ዝግጁ ይሆናሉ። የእርሱን ክብርና ግርማ ሀሳብ ከማንኛውም ነገር ያስቀድማሉ።”—Ellen G. White, Christ’s Object ትምህርትs, pp. 48, 49. የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ


የመወያያ ጥያቄዎች




1. “ፍቅር የተግባር መርህ መሆን አለበት። ፍቅር በሰማይና በምድር የእግዚአብሔር አስተዳደር መርህ ነው።” መስቀል ይህንን አስደናቂ እውነት የሚገልጥልን እንዴት ነው? በሕይወታችን የዚህን ዓይነት ፍቅር ማንጸባረቅ የምንችለው እንዴት ነው? ይህን ማድረግ ያለብን ለምንድር ነው?

2. ኢየሱስ በምሳሌ ይናገር የነበረው ከሕብረተሰቡ ውጭ የሆኑ ሰዎችን በጨለማ ውስጥ ለመተው ነው ብሎ ለሚከራከር ሰው እንዴት ይመልሱለታል? ለሰብአዊ ዘር በሙሉ የሞተው ኢየሱስ (1ኛ ዮሐ. 2፡2ን ይመልከቱ) ሊያድናቸው በመስቀል ላይ የሞተላቸውን ሰዎች እንዴት ሆነ ብሎ በጨለማ ውስጥ ይተዋቸዋል?

3. መብራት ከእንቅብ ሥር ሳይሆን በመቅረዝ ላይ መሆን አለበት (ማር. 4፡21)። ይህንን መርህ ቤተ ክርስቲያንዎ ከአከባቢው ህብረተሰብ ጋር ላላት ግንኙነት ሥራ ላይ ያውሉ። ብርሃንን ከፍ አድርገው ማሳየት የሚችሉት እንዴት ነው?

4. የሚያድገውን ዘር ምሳሌ ይመልከቱ (ማር. 4:26–29)። የወንጌል ዘር እንዲያድግ ሰዎች የሚጫወቱት ድርሻ ምንድር ነው? የእግዚአብሔር ድርሻስ ምንድር ነው? የምንጫወተው ሚና መኖሩ ግልጽ ቢሆንም ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር መደገፋችንን እርግጠኛ መሆን የምንችለው እንዴት ነው? ምናልባት ይህ ሙሉ በሙሉ የመደገፍ አመለካከት ለማደግ ማድረግ የሚያስፈልገን ነገር አካል ይሆን ይሆን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL