የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የማርቆስ መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሐምሌ 6 - 12

3ኛ ትምህርት

Jul 13 - 19




ተቃርኖዎች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ማር. 2:1–3:6፣ ሚክያስ 6:6–8፣ 1ኛ ሣሙ. 21:1–6፣ ማር. 3:20–35፣ ሉቃስ 12:53፣ ሉቃስ 14:26።


የመታሰቢያ ጥቅስ:- “ደግሞ፦ ሰንበት ስለ ሰው ተፈጥሮአል እንጂ ሰው ስለ ሰንበት አልተፈጠረም፤ እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበት እንኳ ጌታዋ ነው አላቸው።” (ማር. 2:27፣ 28)።

ማርቆስ 2:1–3:6 የኃይማኖት መሪዎች ከሚያስተምሩት ትምህርት ጋር በማነጻጸር የኢየሱስን ትምህርት የሚገልጹ ታሪኮችን ይዟል። እያንዳንዱ ቀጣይ ታሪክ አስቀድሞ ከነበረው ታሪክ ጋር ግንኙነት እንዲኖረው ተደርጎ በተለየ ሁኔታ ርዕስ ባለው ንጽጽር ቀርቧል። የመጨረሻው ታሪክ ክብ ሰርቶ ከመጀመሪያው ጋር ተመልሶ ይገናኛል።

ከእነዚህ ታሪኮች እያንዳንዱ ማርቆስ 2፡10፣ 17፣20 እና 28 ላይ በቀረቡ አረፍተ ነገሮች በምሳሌነት እንደቀረበው ኢየሱስ ማን ስለመሆኑ የተለያዩ አመለካከቶችን ይገልጻል። የእሁድ፣ የሰኞና የማክሰኞ ትምህርቶች ወደ እነዚህ ዘገባዎች ትርጉምና በውስጣቸው ወዳሉ የክርስቶስ ንግግሮች ጠልቀው ይገባሉ።

የረቡዕና ሀሙስ የትምህርት ርዕስ ማርቆስ 3:20–35 ይሆናል።

ቀጥሎ የምንመለከተው የወንጌል ጸሐፊው የሚጠቀመውን “ሳንድዊች ታሪኮች” ማለትም በአንድ ታሪክ መካከል ሌላ ታሪክን ማስገባት የሚለውን ዘዴ ምሳሌ ነው። የዚህ ትረካ ዘዴ በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ቢያንስ ስድስት ጊዜ ጥቅም ላይ ውሏል። በእያንዳንዱ ሁኔታ የኢየሱስ ተፈጥሮና የመሲህነቱ ሚና ወይም የደቀ መዝሙርነት ተፈጥሮ ጠቃሚ (ወሳኝ) ገጽታ ትኩረት ተሰጥቶታል።በዚህ ሳምንት ስለ ኢየሱስ የተጻፉ አንዳንድ ዘገባዎችን እናነብና ከእነርሱ ምን መማር እንደምንችል እንመለከታለን። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሀምሌ 13 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሐምሌ 7
Jul 14

ሽባ የነበረውን ሰው መፈወስ


ማርቆስ 2:1–12ን ያንብቡ። ሽባው ሰው ወደ ኢየሱስ ሲያመጡት ይፈልግ የነበረው ምን ነበር? የተቀበለውስ ምን ነበር?





ሰውዬው ሽባ ነበር፤ ስለዚህ አራቱ ጓደኞቹ ወደ ኢየሱስ ተሸክመው መውሰድ ነበረባቸው። ጣሪያውን ነድለው በኢየሱስ ፊት ካስቀመጡት በኋላ ኢየሱስ እምነታቸውን እንደተመለከተ ማርቆስ 2፡5 ላይ ተጽፏል። እምነት ሊታይ የሚችለው እንዴት ነው? የሽባው ጓደኞች ያሳዩት ጽናት በግልጽ እንዳሳየው ልክ እንደ ፍቅር እምነትም ሊታይ የሚችለው በተግባር ነው።

የሰውዬው ግልጽ ፍላጎት አካላዊ ነበር። ነገር ግን ወደ ኢየሱስ ፊት በመጣ ጊዜ ኢየሱስ የተናገራቸው የመጀመሪያዎቹ ቃላት የጠቀሱት የኃጢአት ይቅርታን ነበር። ከትዕይንቱ መጀመሪያ አንስቶ እስከ ፍጻሜው ድረስ ሰውዬው አንድ ቃል እንኳን አልተናገረም ነበር። ከዚህ ይልቅ ኢየሱስ ያለውን ነገር የተቃወሙት (በአእምሮአቸው) የኃይማኖት መሪዎች ነበሩ። የኢየሱስን ቃላት እግዚአብሔርን እንደመሳደብና የእግዚአብሔር ብቻ የሆነውን ስልጣን እንደመቀማት አድርገው ቆጠሩ።

ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን የተጋፈጠው “ከትንሹ ወደ ትልቁ” የሚባለውን ልዩ የአይሁድ መምህራን ዘዴን በመጠቀም ነበር። የአንድ ሰው ኃጢአት ይቅር ተብሎልሃል ማለት አንድ ነገር ሲሆን ሽባ የነበረን ሰው በእግሩ ቆሞ እንዲሄድ ማድረግ ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ኢየሱስ በእግዚአብሔር ኃይል ሽባ ሰው ቆሞ እንዲሄድ ማድረግ ከቻለ ኃጢአትን ይቅር ማለት ስለመቻሉ ለተናገረው ማረጋገጫ ይሆናል።

ሚኪያስ 6:6–8ን ያንብቡ። በኢየሱስና በመሪዎች መካከል እየሆነ ስለነበረው ነገር ይህ ጥቅስ እንዴት ነው የሚያብራራው?





እነዚህ የኃይማኖት መሪዎች በእርግጠኝነት ወሳኝ የሆኑ ነገሮችን፡-ፍትህን፣ ምህረትን እና በእግዚአብሔር ፊት በትህትና መሄድን ማየት አቃታቸው። ስለ እግዚአብሔር ያላቸውን መረዳት ለመከላከል ካላቸው ቁርጠኝነት የተነሣ እግዚአብሔር በዓይናቸው ፊት እየሰራ ላለው ነገር ታውረው ነበር።: ኢየሱስ አእምሮአቸውን ማንበብ እንደሚችል እንዲያውቁ በመፍቀድ ብቻ ሳይሆን መካድ በማይችሉበት ሁኔታ በፊታቸው ሽባውን በማዳን ከእግዚአብሔር ስለመሆኑ ከበቂ በላይ የሆነ ማስረጃ ቢሰጣቸውም ሰዎቹ ስለ እርሱ ያላቸውን አመለካከት እንደለወጡ የሚያመለክት ምንም ነገር አልነበረም።

እነዚህ ሰዎች በወደቁበት ወጥመድ፣ ማለትም በእውነተኛ ኃይማኖት ውስጥ ወሳኝ የሆነው ነገር ምን እንደሆነ ማየት ባልቻሉበት ወጥመድ ውስጥ እንዳንወድቅ መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው (ያዕቆብ 1:27ን ይመልከቱ)?

ሐምሌ 8
Jul 15

ሌዊን መጥራትና የጾም ጥያቄ


ማር. 2:13–22ን ያንብቡ። የእልፍዮስ ልጅ የነበረው ሌዊ ማን ነበር? እርሱ የኢየሱስ ደቀ መዝሙር እንዳይሆን ተቃውሞ የሚኖረው ለምንድር ነው?





በኢየሱስ ዘመን ቀረጥ ሰብሳቢዎች በአከባቢው አስተዳደር ወይም በሮም መንግሥት ሥር የመንግሥት ሰራተኞች ነበሩ። ሕጉ ከሚፈቅደው በላይ በመሰብሰብ በአከባቢያቸው ካሉ ሰዎች ይልቅ ሀብታም ስለነበሩ በአይሁድ ሕዝብ መካከል ተቀባይነት አልነበራቸውም። በኃይማኖት ሕግ ላይ የተሰጠ ሚሽናህ ትራክቴት ቶሆሮት የተባለ የአይሁዶች ተጨማሪ ሀተታ (የመጀመሪያው የተጻፈ የአይሁድ ባህሎች ስብስብ) እንዲህ ይላል፡- “ቀረጥ ሰብሳቢዎች ወደ አንድ ቤት ከገቡ [በቤቱ ውስጥ ያለው ሁሉ] ይረክሳል። . . .”

ስለዚህ ጸሐፍት “ከቀራጮችና ኃጢአተኞች ጋር ለምን ይበላል?” ብለው እውቅና ባለመስጠት መጠየቃቸው የሚያስገርም አይደለም።

ኢየሱስ ለጥያቄአቸው መልስ የሰጠው እንዴት ነበር? ጥያቄአቸውን አልቀበልም አላለም። ከዚህ ይልቅ ሐኪም የሚያስፈልጋቸው በሽተኞች እንጂ የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ጤነኞች አይደሉም በማለት መለሰላቸው። ከዚህ የተነሣ በኃጢአት የታመመችን ነፍስ የሚያድን መንፈሳዊ ሀኪምነት ማዕረግ እንዳለው ገለጸላቸው። ሐኪም ህመምተኞች ወዳሉበት መሄድ የለበትምን? ማርቆስ 2፡18-22 አዲስ ርዕሰ ጉዳይ ይዞ ይነሳል። የተቃርኖ ጉዳይን ከሚመለከቱ ከእነዚህ አምስት ታሪኮች መካከል ማዕከላዊ ታሪክ ነው። አስቀድሞ የነበረው ክፍል ሌዊ ያዘጋጀውን ግብዣ ያካተተ ሲሆን ይህኛው ቀጣይ ታሪክ በጾም ጥያቄ ዙሪያ ይሽከረከራል። የመጥምቁ ዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ሲጾሙ ሳለ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት የማይጾሙት ለምንድር ነው የሚለውን ጥያቄ ያካትታል። ኢየሱስ የእርሱን መገኘት ከሰርግ ግብዣ ጋር ያወዳደረበትን መግለጫ ወይም ምሳሌ በመስጠት ምላሽ ሰጠ።

እንግዶቹ በሙሉ የሚጾሙ ቢሆን ሰርጉ እጅግ ያልተለመደ (ወጣ ያለ) ይሆን ነበር። ነገር ግን ሙሽራው ስለሚወሰድበት ቀን ተነበየ። ይህም በተዘዋዋሪ ስለ መስቀሉ የሚጠቅስ ነበር። ከዚያ በኋላ ለመጾም ብዙ ጊዜ ይኖራል።

ኢየሱስ በእርሱና በኃይማኖት መሪዎች ትምህርቶች መካከል ያለውን ልዩነት አጉልተው የሚያሳዩ ሁለት መግለጫዎችን በመስጠት ይቀጥላል። እነዚህ መግለጫዎች በአሮጌ ልብስ ላይ አዲስ እራፊ አለማኖርንና በአሮጌ አቁማዳ አዲስ ወይንን አለመጨመርን የሚገልጹ ናቸው። የክርስቶስንና የኃይማኖት መሪዎችን ትምህርቶች ለማነጻጸር እንዴት ያለ ደስ የሚል መንገድ ነው። የመምህራኑ መንገዶች ምንኛ የተበላሹ መሆናቸውን ያሳያል። ሰዎች ካልተጠነቀቁ እውነተኛ ኃይማኖትም ወደ ጨለማነት ሊለወጥ ይችላል።

በኢየሱስ ዘመን ቀራጮች ይታዩ እንደነበር ዛሬ የሚታዩት እነማን ናቸው? እነርሱን በተመለከተ አመለካከታችንን ማስተካከል የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 9
Jul 16

የሰንበት ጌታ


በማርቆስ 2:23ና 24 ላይ ፈሪሳውያን ሰንበትን ሽረዋል በማለት ደቀ መዛሙርትን ከሰዋል። እንደ አይሁዶች ወግ በሰንበት ቀን 39 ዓይነት ሥራዎች እንዳይሰሩ የተከለከሉ ሲሆን በፈሪሳውያን አእምሮ ደቀ መዛሙርት ያደረጉትንም ያካትታል።

ማር. 2:23–28ን ያንብቡ። ፈሪሳውያን ያመጡትን ክስ ኢየሱስ የመከተው እንዴት ነበር?





ዳዊት ቅዱስ እንጀራን የበላበትን ታሪክ በመንገር ኢየሱስ መልስ ሰጣቸው (1ኛ ሳሙ. 21:1–6)። ሕብስቱ በሰንበት ቀን ከጠረጴዛው ላይ ይነሳ ነበር፤ ስለዚህ ዳዊት በሰንበት ቀን ያደረገው ጉዞ ድንገተኛ የሆነ የማምለጫ ጉዞ ሊሆን ይችላል።

ዳዊትና ከእርሱ ጋር የነበሩ ሰዎች የተቀደሰውን እንጀራ በመብላታቸው ትክክል እስከሆኑ ድረስ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርትም እሸትን ቀጥፈው በመብላታቸው ትክክል ናቸው (ሊኮነኑ አይችሉም)።

ኢየሱስ አክሎም ሰንበት ለሰብአዊ ዘር ጥቅም መፈጠሩን እንጂ ሰው ለሰንበት እንዳልተፈጠረ ያመለከተ ሲሆን እርሱ የሰንበት ጌታ እንደሆነ ለገለጸበት ሀሳብ መሰረቱ ይህ ነወ።

ማርቆስ 3:1–6ን ያንብቡ። ሰንበት ለሰው መፈጠሩን ኢየሱስ የተናገረበትን ነጥብ ይህ ታሪክ እንዴት ይገልጸዋል?





ኢየሱስ በሰንበት ጉዳይ ላይ በድጋሚ ከኃይማኖት መሪዎች ተቃርኖ ገጠመው። (ነገር ግን ተቃርኖው በራሱ በሰንበት ቀን ላይ እንዳልሆነ ልብ ይበሉ።) የኃይማኖት መሪዎች ኢየሱስ በሰንበት ቀን ከፈወሰ ሊከሱት ፈለጉ። ኢየሱስ በዚህ ጉዳይ ሊጋፈጣቸው አልፈራም። መልካም ማድረግ ወይስ መጥፎ፣ ሕይወትን ማዳን ወይስ ማጥፋት የሚሉ ንጽጽሮችን አቀረበላቸው። እርሱ ለጠየቀው ጥያቄ መልሱ ግልጽ ነው፤ መልካም ማድረግና ሕይወትን ማዳን እጅግ ተገቢ የሆኑ የሰንበት ተግባራት ናቸው።

ኢየሱስ የታመመውን ሰው ፈወሰው። ይህ ተቃዋሚዎቹን ስላናደዳቸው ወዲያውኑ እርሱን የሚያጠፉበትን መንገድ ማቀድ ጀመሩ። የታሪኩ ምጸት ሰንበትን ሽሯል ብለው ኢየሱስን መያዝ ይፈልጉ የነበሩ ሰዎች ራሳቸው እርሱን ለመግደል በማቀዳቸው ሰንበትን እየሻሩ መሆናቸው ነበር።

ከእነዚህ ሀሳቦች ስለ ሰንበት አጠባበቅ ምን መርሆዎችን መውሰድ ይችላሉ? ሰንበትን መጠበቅን በተመለከተ በአሁኑ ዘመን የሚገጥሙን ተግዳሮቶችስ ምንድር ናቸው? የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሐምሌ 10
Jul 17

ሳንድዊች ታሪክ (በአንድ ታሪክ መካከል


የገባ ሌላ ታሪክ)፡-ክፍል 1 ማር. 3:20–35ን ያንብቡ። በዚህ ንባብ ውስጥ ተያይዘው ባሉ በሁለቱ ታሪኮች መካከል ስላለው ግንኙነት ምን ተመለከቱ?





ይህ ንባብ አንድ ታሪክ ተጀምሮ በሌላ ታሪክ ከተቋረጠ በኋላ የመጀመሪያው ታሪክ ቆይቶ የተጠናቀቀበት በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ የቀረበ የመጀመሪያው “ሳንድዊች ታሪክ” ነው።

ውጫዊው ታሪክ የኢየሱስ ዘመዶች ኢየሱስ ማሰብ አቁሟል ብለው ስላሰቡ (ማር. 3፡21) እርሱን ለመፈለግ መሄዳቸውን የሚገልጽ ታሪክ ነው።

ውስጣዊው ታሪክ ደግሞ ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር ድብቅ ስምምነት እንደፈጠረ የሚከሱ የፈሪሳውያን ታሪክ ነው። (የዛሬው ትምህርት ማርቆስ 3፡22-30 ላይ በሚገኘው ውስጣዊ ታሪክ ላይ ትኩረት ያደርጋል።)

ማርቆስ 3:22 ላይ ጸሐፍት የኢየሱስ የመፈወስ ኃይል የመጣው ከሰይጣን ነው በማለት ከሰሱት። ኢየሱስ በመጀመሪያ “ሰይጣን እንዴት ሰይጣንን ማውጣት ይችላል?” የሚል ሁሉን የሚያቅፍ ጥያቄ በመጠየቅ መልስ ሰጠ። ከዚያም ኢየሱስ ስለ መንግስት፣ ስለቤትና ስለ ሰይጣን ራሱ መከፋፈል መናገሩን በመቀጠል የዚህ ዓይነቱ ክፍፍል ለስኬታቸው እንዴት ያለ ያልተገባ ተግባር እንደሆነ አሳየ። ነገር ግን የአንድን ብርቱ ሰው ቤት ለመዝረፍ መጀመሪያ እርሱን ማሰር እንደሚያስፈልግ በመናገር ነገሩን ወደ ራሳቸው መለሰ። በዚህ የመጨረሻው ምሳሌ ውስጥ ኢየሱስ በሰይጣን ምርኮ ሥር ያሉትን ነጻ ለማውጣት የጨለማውን መስፍን አስሮ ወደ እርሱ ቤት እንደሚገባ ሌባ ሆኖ ቀርቧል።

ማርቆስ 3:28–30ን ያንብቡ። ይቅርታ የሌለው ኃጢአት ምንድር ነው? ይህ ማለት ምን ማለት ነው?





ይቅርታ የሌለው ኃጢአት የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሰይጣን ሥራ ነው በማለት መንፈስ ቅዱስን መቃወም ነው። ኢየሱስ ማርቆስ 3፡ 28ና 29 ላይ የተናገረውን አረፍተ ነገር የተናገረው እርሱ ያለው ቅዱስ መንፈስ ሆኖ ሳለ ጸሐፍት ግን እርኩስ መንፈስ አለበት ስላሉ እንደሆነ ማርቆስ 3፡30 ላይ ይመልከቱ። የመንፈስ ቅዱስን ሥራ የሰይጣን ሥራ ነው ብላችሁ ከጠራችሁ ማንም ጤናማ አእምሮ ያለው ሰው በሰይጣን መመራት ስለማይፈልግ የመንፈስ ቅዱስን ምሪት መከተል አትችሉም።

“ይቅርታ የሌለው ኃጢአት” ፈጽሜ ይሆናል የሚለው ፍርሃት አለመፈጸምዎን የሚገልጠው ለምንድር ነው? ፍርሃቱ ራሱ ላለመፈጸምዎ ማስረጃ የሚሆነው ለምንድር ነው?

ሐምሌ 11
Jul 18

ሳንድዊች ታሪክ (በአንድ ታሪክ መካከል


የገባ ሌላ ታሪክ)፡-ክፍል 2 ማር. 3:20፣ 21ን ያንብቡ። ኢየሱስ የአስተሳሰብ ችግር እንዳለው አድርገው ቤተሰቦቹ እንዲያስቡ የመራቸው ልምምድ ምን ነበር?



አንድን ሰው አእምሮው የተረጋጋ አይደለም ማለት አሳሳቢ ጉዳይ ነው።

ይህ ጉዳይ የሚነሳው ግለሰቡ/ቧ ለራሱ/ሷ ደህንነት አስጊ ሲሆን/ስትሆን ነው። የኢየሱስ ቤተሰቦች እንዲህ ብለው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ነገር ኢየሱስ ሥራ ይበዛበት ስለነበር ለመመገብ እንኳን ጊዜ ስላልነበረው ነበር። ቤተሰቦቹ ለእርሱ ለመጠንቀቅ ጉዞ በመጀመራቸው ውጫዊው የሳንድዊች ታሪክ ይቋረጥና ጸሐፍት ከሰይጣን ጋር ስምምነት ፈጥሮአል ብለው የከሰሱበት ውስጣዊው የሳንድዊች ታሪክ ይጀምራል። በእነዚህ ውጫዊና ውስጣዊ የሳንድዊች ታሪኮች መካከል ከተለመደው ውጭ የሆነ መመሳሰል አለ። የኢየሱስ ቤተሰብ ስለ እርሱ የነበራቸው አመለካከት ጸሐፍት ከነበራቸው አመለካከት ጋር የሚመሳሰል ይመስላል።

ቤተሰቡ አእምሮውን ስቷል ይላሉ። ጸሐፍት ደግሞ ከሰይጣን ጋር ስምምነት ፈጥሯል ይላሉ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ማር. 3:31–35ን ያንብቡ። የኢየሱስ ቤተሰቦች ይፈልጉ የነበሩት ምን ነበር? እርሱ ምላሽ የሰጠው እንዴት ነበር?





ይህ ትዕይንት እንግዳ ነገር ሊመስል ይችላል። እናትህ/ሽ ወይም ሌሎች የቤተሰብ አባላት ሊያገኙህ/ሽ ሲመጡ ማግኘት የለብህምን/የለብሽምን? ችግሩ የኢየሱስ ቤተሰብ በዚያን ጊዜ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ተስማምተው እየሄዱ አልነበሩም። ኢየሱስም ይህንን እውነት ተረድቶ ስለነበር በዚህ ንባብ ውስጥ ለቤተሰብ አዲስ ትርጉም ይሰጣል። የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ ወንድሙ፣ እህቱና እናቱ ናቸው። እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ስለሆነ ራሳቸውን ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር የሚያስማሙ ሁሉ የእርሱ ቤተሰብ ይሆናሉ።

በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ በቀረበው በዚህ ሳንድዊች ታሪክ ውስጥ ያሉ ሁለቱ ታሪኮች ጥልቅ የሆነ ምጸት የያዙ ናቸው። በውስጠኛው ታሪክ ውስጥ እርስ በርሱ የሚከፋፈል ቤት አይጸናም ብሎ ኢየሱስ ተናግሯል። በመጀመሪያ እይታ የኢየሱስ የራሱ ቤት ውጫዊ ታሪክ፣ የእርሱ ቤተሰብ፣ እርስ በርሱ የተከፋፈለ ይመስላል! ነገር ግን ኢየሱስ ለቤተሰብ እንደገና ትርጉም በመስጠት ይህንን እንቆቅልሽ ፈታው። የእርሱ እውነተኛ ቤተሰቦች ከእርሱ ጋር የእግዚአብሔርን ፈቃድ የሚያደርጉ ናቸው (ሉቃስ 12፡ 53፤ ሉቃስ 14፡26ን ይመልከቱ)። በታሪክ ዘመን ሁሉ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ ራሳቸውን ከዘመዶቻቸው ለይተዋል (አግልለዋል)። ይህ ከባድ ልምምድ ነው። በማርቆስ መጽሐፍ ላይ የተጠቀሰው ይህ ንባብ ኢየሱስ ተመሳሳይ በሆነ ችግር ውስጥ ማለፉን ይገልጻል። ከቤተሰብ መለየት (መገለል) ምን እንደሚመስል ለማወቅ ስለሚረዳ ይህ የሚያም ብቸኝነት (መገለል) እየተሰማቸው ያሉትን ሰዎች ማጽናናት ይችላል።

ሐምሌ 12
Jul 19


ተጨማሪ ሀሳብ


የዘመናት ምኞት ከሚለው የኤለን ጂ ኋይት መጽሐፍ በእንግሊዘኛው እትም ላይ ከገጽ 272-280 “ሌዊ ማቴዎስ” የሚለውን እና ከገጽ 281-289 ላይ “ሰንበት” የሚለውን ክፍል አንብቡ።

“ኢየሱስ ‘በሰንበት ማዳን ተፈቅዷልን?’ ተብሎ ሲጠየቅ እንዲህ በማለት መለሰ፡- ‘ከእናንተ መካከል አንድ በግ ያለው ሰው ያ በግ በሰንበት ቀን ወደ ጉድጓድ ቢወድቅበት ያንን በግ ከጉድጓድ የማያወጣ ማን ነው? ስለዚህ በሰንበት መልካም ማድረግ ተፈቅዷል።’ ማቴ. 12:10–12። “ሰላዮቹ ራሳቸውን በችግር ውስጥ እንዳያስገቡ በመፍራት በሕዝቡ ፊት ለክርስቶስ መልስ ለመስጠት አልደፈሩም ነበር። እውነት መናገሩን አውቀዋል። ችላ ከተባለ ለባለቤቱ ከሚገጥመው ኪሳራ የተነሳ እንስሳውን እየረዱ ወጋቸውን ከመጣስ ይልቅ ሰው እንዲሰቃይ ዝም ይላሉ። ስለሆነም በእግዚአብሔር አምሳል ከተፈጠረው ሰው ይልቅ የማይናገር እንስሳ ከፍተኛ ጥንቃቄ ይደረግለታል። ይህ የሁሉንም የሀሰት ኃይማኖቶች አሰራር ያሳያል። መነሻቸው ሰው ከእግዚአብሔር በላይ ራሱን ከፍ ከፍ ለማድረግ ያለው ፍላጎት ነው፤ ነገር ግን ሰውን ከእንስሳ በታች ዝቅ ያደርጉታል። በእግዚአብሔር ሉአላዊነት ላይ ጦርነት የሚያስነሳ ማንኛውም ኃይማኖት ሰው ሲፈጠር የእርሱ የነበረውንና በክርስቶስ የሚመለስለትን ክብር አጭበርብሮ ይወስድበታል።

እያንዳንዱ የሀሰት ኃይማኖት ተከታዮቹ ለሰው ችግሮች፣ ሥቃዮችና መብቶች ግድ የለሽ እንዲሆኑ ያስተምራል። ወንጌል ግን ሰብአዊ ዘር በክርስቶስ ደም የተገዛ መሆኑን በመግለጽ ትልቅ ዋጋ በመስጠት ለሰው እጦትና ሰቆቃ ቦታ ይሰጣል። ጌታ እንዲህ ብሏል፡- ‘ሰውን ከጥሩ ወርቅ ይልቅ የከበረ፣ ከኦፊር ወርቅም ይልቅ የከበረ አደርገዋለሁ።’ ኢሳ. 13:12።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, pp. 286, 287. የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እርስዎና አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ በማርቆስ ምዕራፍ 2 ላይ እንደተጠቀሰው ሽባ በዝምታ እየተሰቃዩ ላሉ ሰዎች ሀዘኔታ እንዲሰማችሁ ምን ስልቶችና ልምምዶች ሊረዱአችሁ ይችላሉ?

2. ኢየሱስን አልቀበል ያሉ የኃይማኖት መሪዎች በጥላቻ፣ በወግ፣ በቀኖና እና በኃይማኖት ከመታወራቸው የተነሣ አእምሮአቸውን ለእርሱ እንዲከፍቱ ሊያደርጉ የሚችሉ ተዓምራቶቹን እንኳን እንዴት መቀበል እንዳልቻሉ አስቡ። እኛ እንደ ሕዝብ ከዚህ ጋር ተመሳሳይ የሆነ ነገር በእኛ ሕይወት እንዳይከሰት እንዴት መጠንቀቅ እንችላለን?

3. የእርስዎ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን በእምነታቸው ምክንያት በዘር የሚገናኝ ቤተሰብ አልቀበል ላላቸው ሰዎች “ቤተሰብ” መሆን የምትችለው እንዴት ነው?

4. “ይቅርታ የሌለው ኃጢአት” በሚለው ጥያቄ ላይ ጊዜ ውሰዱ። ይቅርታ የሌለው ኃጢአት ማለት ምን ማለት እንደሆነ እና የዚህን ዓይነት ኃጢአት ላለመስራታችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንደምንችል በክፍላችሁ ተወያዩ።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL