የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የማርቆስ መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሰኔ 29 - ሐምሌ 5

2ኛ ትምህርት

Jul 6 - 12




አንድ ቀን በኢየሱስ አገልግሎት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ማር. 1:16–45፣ ዮሐንስ 1:29–42፣ ማር. 5:41፣ ሉቃስ 6:12፣ ዘሌ. 13።


የመታሰቢያ ጥቅስ:-“ኢየሱስም፦ በኋላዬ ኑና ሰዎችን አጥማጆች እንድትሆኑ አደርጋችኋለሁ አላቸው።” (ማር. 1:17)።

እያንዳንዱ ወንጌል የኢየሱስን አገልግሎት መጀመር በተለየ ሁኔታ ያስተዋውቃል። ማቴዎስ ኢየሱስ ደቀ መዛሙርቱን ሲጠራ ያቀርብና ቀጥሎ የተራራውን ስብከት ያቀርባል። ሉቃስ ኢየሱስ ናዝሬት በነበረው ምኩራብ የአገልግሎቱ መጀመሪያ የሆነውን ስብከት በሰንበት ቀን የሰበከበትን ታሪክ ይነግራል።

ዮሐንስ ከቀደምት ደቀ መዛሙርት የአንዳንዶቹን መጠራትና ኢየሱስ የመጀመሪያውን ተዓምራት የሰራበትን የቃናን ሰርግ ይነግረናል። የማርቆስ ወንጌል የአራት ደቀ መዛሙርትን መጠራት ይነግርና በቅፍርናሆም ስለነበረው የሰንበት ቀንና ምን ተከትሎ እንደመጣ መግለጫ ይሰጣል።

ይህ በማርቆስ መጽሐፍ ጅምር ላይ “ሰንበት ከኢየሱስ ጋር” የሚለው ሀሳብ አንባቢው ኢየሱስ ማን እንደሆነ እንዲረዳ የሚያደርግ ስሜት ይሰጣል። በዚህ ሳምንት ትምህርት በሁሉም ክፍሎች ውስጥ ከእርሱ ቃላት የተመዘገቡት እጅግ ጥቂት ናቸው፡- ለደቀ መዝሙርነት የቀረበው አጠር ያለ ጥሪ፣ አጋንንትን ማዘዙ፣ ሌሎች ቦታዎችን የመጎብኘት ዕቅድ እና ስለ መንጻቱ ራሱን ለካህን እንዲያሳይ የታዘዘው የለምጻሙ መንጻት ናቸው። አጽንዖት የሰጠው በተግባር ላይ፣ በተለይም ሰዎችን በመፈወስ ላይ ነው። የወንጌል ጸሐፊው ኢየሱስ ለአገልግሎት ያደርግ የነበረውን ፈጣን የተግባር እንቅስቃሴ ለማሳየት ወዲያውኑ የሚለውን ቃል መጠቀምን ይወዳል። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሀምሌ 6 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሰኔ 30
Jul 07

“ተከተሉኝ”


ማርቆስ 1:16–20ን ያንብቡ። ኢየሱስ እንደ ደቀ መዛሙርት የጠራቸው ሰዎች እነማን ነበሩ? ምላሻቸውስ ምን ነበር?



ማርቆስ ምዕራፍ 1 ላይ የኢየሱስ ቃላት በብዛት አልተመዘገቡም። ነገር ግን ማርቆስ 1፡ 17 ላይ ለሁለት አሣ አጥማጆች፣ ኋላ ጴጥሮስ ለተባለው ስምዖንና ለወንድሙ እንድሪያስ የተናገራቸው ቃላት አሉ። ሁለቱ ሰዎች መረቦቻቸውን እየጣሉ በገሊላ ባህር ዳርቻ ቆመው ነበር።

ጀልባም ሆነ ሌሎች ዓሣ ለማጥመድ የሚያገለግሉ ዕቃዎች አለመጠቀሳቸው ሁለቱ ሰዎች ገንዘብ ያልነበራቸው ሰዎች እንደሆኑ ሊያመለክት ይችላል። ማርቆስ 1፡ 19ና 20 ላይ ያዕቆብና ዮሐንስ ከአባታቸው ጋር በጀልባ ውስጥ መሆናቸው የሚያመለክተው በገንዘብ አቅም ከጴጥሮስና ከእንድሪያስ የተሻሉ መሆናቸውን ነው። ጴጥሮስ ጀልባ እንደነበረውና ያዕቆብና ዮሐንስ ከጴጥሮስና ከእንድሪያስ ጋር በሽርክና ይሰሩ እንደነበር ሉቃስ አመልክቷል (ሉቃስ 5፡1-11ን ይመልከቱ)። ነገር ግን የማርቆስ ወንጌል በሁለቱ ቡድን ወንድማማቾች መካከል ያለውን ልዩነት እያሳየ ሊሆን እንደሚችል የሚገመት ሲሆን ልዩነቱን ለማሳየት ኢየሱስ አነስተኛም ሆነ ከፍተኛ ሀብት ያላቸውን ሁለቱንም ቡድኖች ለደቀ መዝሙርነት ጠርቷቸዋል።

ኢየሱስ ለእነዚህ ሰዎች ያቀረበው ጥሪ ቀላል፣ ቀጥተኛና ትንቢታዊ ነው።

እርሱ የጠራቸው እንዲከተሉት ነው፤ ይህ ማለት ደቀ መዛሙርቱ እንዲሆኑ ማለት ነው። ለጥሪው ምላሽ ከሰጡ እነርሱን ሰው አጥማጆች የማድረግ ሥራን ይሰራል።

እነዚህ ሰዎች ሁሉን ነገር ትተው ወዲያውኑ (ማር. 1፡16-20) ኢየሱስን ለምን እንደተከተሉ አስቡ።



የዮሐንስ ወንጌል ስዕሉን የበለጠ ሙሉ ያደርገዋል (ዮሐ. 1፡ 29-42ን ይመልከቱ)። ወንድማማቾቹ የመጥምቁ ዮሐንስ ደቀ መዛሙርት የነበሩና ኢየሱስ “የዓለምን ኃጢአት የሚያስወግድ የእግዚአብሔር በግ” (ዮሐ 1:29) ስለመሆኑ ዮሐንስ ያወጀውን አዋጅ የሰሙ ይመስላል። ኢየሱስን አግኝተው በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ አብረውት ጊዜን አሳልፈዋል። ከዚህ የተነሣ ኢየሱስ ለአገልግሎት ያቀረበላቸውን ጥሪ መቀበላቸው የሆነ ቀልድ ወይም በሞቅታ የተፈጸመ ክስተት አይደለም። በደንብ አስበውበታል። ነገር ግን ማርቆስ ተጨማሪ ዝርዝሮችን ያልሰጠው ለምንድር ነው? በኢየሱስ ኃይል ላይ አጽንዖት ለመስጠት ሊሆን ይችላል። እርሱ ሲጠራቸው ፈቃደኛ የነበሩ ዓሣ አጥማጆች መልስ ከመስጠታቸው የተነሣ ሕይወታቸውም ሆነ ዓለም ራሱ በፍጹም ከዚህ በፊት እንደነበረው አልሆነም።

ኢየሱስን ለመከተል እንድተዉት ጥሪ የቀረበልዎ ምን ነገር አለ? (ሌላ ምንም ነገር ማሰብ ካልቻሉ ስለ መልሶችዎ እንደምታ ያስቡ)

ሐምሌ 1
Jul 08

የማይረሳ የአምልኮ አገልግሎት


ማርቆስ 1:21–28ን ያንብቡ። በቅፍርናሆም ምኩራብ የተከሰተው ምን ሊረሳ የማይችል ተሞክሮ ነበር? ከዚህ ዘገባ (መግለጫ) ምን መንፈሳዊ እውነቶችን መውሰድ እንችላለን?



አብዛኞቹ ክርስቲያኖች በክርስትና ጉዞአቸው የሆኑ የማይረሱ ጊዜያቶች (ቅጽበቶች) አሉአቸው። እነዚህም ኢየሱስን ለመከተል ያደረጉት ውሳኔ፣ የጥምቀታቸው ቀን፣ የእግዚአብሔር መገኘት በጥልቀት እንዲሰማቸው ያደረገ ኃይለኛ ስብከት ሊሆኑ ይችላሉ። ከእነዚህ ጊዜያት አንዳንዶቹ የማይረሱ ብቻ ሳይሆኑ ሕይወትንም የሚለውጡ ሊሆኑ ይችላሉ።

በማርቆስ 1 ላይ በተገለጸው የሰንበት ዕለት በቅፍርናሆም ለነበሩ አንዳንድ ሰዎች የሆነው እንደዚህ ሊሆን ይችላል። “እንደ ባለ ሥልጣን ያስተምራቸው ነበር እንጂ እንደ ጻፎች አይደለምና በትምህርቱ ተገረሙ።” (ማርቆስ 1:22)። ኢየሱስ እያስተማረ ሳለ በአጋንንት የተያዘ ሰው፣ በእርግጠኝነት በኢየሱስ ትምህርት ኃይል የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ተነክቶ እንዲህ በማለት ጮኸ፡- “ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄአለሁ፥ የእግዚአብሔር ቅዱሱ ብሎ ጮኸ።” (ማርቆስ 1:24)። ኢየሱስም አጋንንቱ ከሰውዬው እንዲወጡ አደረገ።

አጋንንት ስለተናገሩአቸው ስለ እነዚህ ቃላት አንደምታ ያስቡ። በመጀመሪያ፣ አጋንንቱ ኢየሱስ “የእግዚአብሔር ቅዱስ” መሆኑን ተገነዘበ። ከረከሱና ካልተቀደሱ የሰይጣን ሰራዊት በተቃራኒ ኢየሱስ ቅዱስ የእግዚአብሔር መልእክተኛ ለመሆኑ እውቅና ሰጠ። ሰዎች በአምልኮ ቦታ ቅዱስ ነገሮችንና ግለሰቦችን እንጂ እርኩስና ያልተቀደሱ ነገሮችን አይጠብቁም። ከዚህ የተነሣ በዚህ ታሪክ ውስጥ በመልካምና በክፉ ኃይላት መካከል ግልጽ የሆነ ልዩነት አለ። በዚህ ቦታ የታላቁ ተጋድሎን እርግጠኝነት ማየት እንችላለን። ሰዎች ኢየሱስ ማን እንደሆነ እስካሁን ድረስ ላያውቁ ይችላሉ፣ ነገር ግን ሰይጣን በእርግጠኝነት ስለሚያውቅ በሕዝብ ፊት እውቅና ሰጠ።

ሁለተኛ፣ ከሰውዬው እንዲወጣ ትዕዛዝ መሰጠቱ መረዳት የሚቻል ነገር ነው፣ ነገር ግን “ጸጥ በል” የሚለው ትዕዛዝ ለምን አስፈለገ? የእርሱን ማንነት በተመለከተ ዝም እንዲል ኢየሱስ ማዘዙን በተመለከተ በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ከጅምሩ ላይ አስደናቂ የሆነ ዓላማ አለ። ምሁራን ይህንን ጉዳይ “መሲሃዊ ምስጢር” ብለው ይጠሩታል። ኢየሱስ ዝም እንዲል ያቀረበው ጥሪ ትርጉም የሚሰጠው በእርሱ ዘመን ስለ መሲሁ መምጣት ከነበረው ፖለቲካዊ ስሜት የተነሳ ነው።

መሲህ መሆን አደጋ ነበረው። ሆኖም ይህ ለጸጥታ (ለዝምታ) ከቀረቡ ጥሪዎች ጋር ተቀላቅሎ ኢየሱስ ማን ስለመሆኑ ግልጽ የሆኑ መገለጦች ናቸው። በሂደት ግልጽ የሚሆነው ነገር ቢኖር የኢየሱስ ማንነት ሊደበቅ አለመቻሉ ሲሆን የእርሱ ማንነት እውነት የወንጌል መልእክት ማዕከል ይሆናል። ሰዎች ማወቅ ያለባቸው ኢየሱስ ማን መሆኑን ብቻ ሳይሆን ስለ ዳግም ምጽዓቱና ይህ ለእነርሱ ምን ማለት እንደሆነ ስለሚመልሱበት መንገድ ውሳኔ ስለማድረግም ማወቅ አለባቸው።

ለሌሎች ለመመስከር ስንፈልግ “የወቅቱን እውነት” በተመለከተ የምናምነውን ነገር ሁሉ ማቅረብ ተገቢ የማይሆንበት ጊዜ መቼ ይሆን?

ሐምሌ 2
Jul 09

ተጨማሪ የሰንበት አገልግሎት


ማርቆስ 1:29–34ን ያንብቡ። ኢየሱስ የጴጥሮስን ቤተሰብ የረዳው እንዴት ነበር? ከዚህ ዘገባ ምን መንፈሳዊ ትምህርት ማግኘት እንችላለን?



አስደናቂ ከነበረው የምኩራብ አገልግሎት በኋላ ኢየሱስ ከጥቂት የደቀ መዛሙርቱ ቡድን ጋር (ጴጥሮስ፣ እንድሪያስ፣ ያዕቆብና ዮሐንስ) ቀሪውን የሰንበት ዕለት የወዳጅነት ግብዣ ላይ ለመሳተፍና አብሮ ለመሆን ወደ ጴጥሮስ ቤት ሄደ።

ነገር ግን በቦታው የሆነ ችግር የመኖሩ ወሬ ተሰራጨ፡- የጴጥሮስ አማት በንዳድ ታማለች። የዚህ ዓይነት ችግር በዚያን ዘመን በራሱ ሊሻል ወይንም ሊገድል ይችል ነበር። ለኢየሱስ ስለ ህመሙ ነገሩት። ኢየሱስም የጴጥሮስን አማት እጇን ይዞ አቆማት። እሷም ወዲያውኑ ተነስታ አገለገለቻቸው። ይህ በኢየሱስ የዳኑና የተፈወሱ ሰዎች ሌሎችን እንዲያገለግሉ ስለተሰጠው መርህ እንዴት ያለ ኃይለኛ ምሳሌ ነው!

ኢየሱስ የታመመውን ግለሰብ በመንካት መፈወስ በመላው የማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ተጠቅሷል (ማርቆስ 1፡41፤ 5፡41ን ይመልከቱ)። አንዳንዴ ደግሞ ሳይነካ የፈወሳቸው ጊዜያቶችም ተጠቅሰዋል (ማርቆስ 2፡1-12፤ 3፡1-6፤ 5፡7-13)።

የኢየሱስ አገልግሎት በዚያን ቀን አላበቀም። ብዙዎች ፀሐይ ከጠለቀች በኋላ ፈውስ እየፈለጉ ወደ ጴጥሮስ ቤት መጥተው ነበር። ለመምጣታቸው ምክንያቱ በዚያን ቀን በምኩራብ የሆነውን ከመመልከታቸው ወይም ከመስማታቸው የተነሣ እንደሚሆን ምንም ጥርጥር የለውም። ሰዎች ሳይመጡ የዘገዩበት ምክንያት ሰንበት እስከሚያልፍ ስለመሆኑ የወንጌል ፀሐፊው አለመግለጹ የሚያመለክተው አንባቢዎቹ ስለ ሰንበት ያውቃሉ ብሎ ስላሰበ ነው። ይህ የማርቆስ አቀራረብ አንባቢዎቹ ሰንበት ጠባቂዎች ከመሆናቸው ጋር የተጣጣመ ነው።

በዚያን ምሽት የከተማው ሕዝብ በሙሉ በደጅ ላይ መሰብሰቡን ማርቆስ ይናገራል (ማር. 1፡33)። ይህን ሕዝብ በሙሉ ለመርዳት ለኢየሱስ የተወሰነ ጊዜ እንደሚወስድበት የተረጋገጠ ነው። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

“በቀጣዩ ቀን ፈዋሹ በመካከላቸው ስለመገኘቱ ማንም እርግጠኛ ስላልነበር በየሰዓቱ ወደ እርሱ እየመጡ ይሄዱ ነበር። ቅፍርናሆም የዚህን ዓይነት ቀን ከዚህ በፊት አታውቅም ነበር። አየሩ በድልና ነጻ በመውጣት ድምጽ ተሞልቶ ነበር።

አዳኙ በሰዎቹ ውስጥ ከቀሰቀሰው ደስታ የተነሣ ተደስቶ ነበር። ወደ እርሱ የመጡ ሰዎችን ስቃይ ሲመለከት ልቡ በሀዘኔታ ተነክቶ ስለነበር እነርሱን ወደ ጤንነትና ደስታ መመለስ በመቻሉ ሀሴት አደረገ።

“ከሚሰቃዩት ሰዎች መካከል የመጨረሻው እፎይታ እስኪያገኝ ድረስ ኢየሱስ ሥራውን አላቆመም ነበር። ሕዝቡ ተለይቶ የሄደው ከሌሊቱ ረፋድ ሰዓት ላይ ስለነበር በስምዖን ቤት ጸጥታ ሆነ። ረዥሙ አስደሳች ቀን ስላለፈ ኢየሱስ እረፍት ማድረግ ፈለገ። ነገር ግን የከተማው ሕዝብ ገና እንቅልፍ ላይ ሳለ አዳኙ ‘ከመንጋቱ በፊት ተነስቶ ገለልተኛ ወደሆነ ስፍራ በመሄድ ጸለየ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 259.

ሐምሌ 3
Jul 10

የኢየሱስ አገልግሎት ምስጢር


ማርቆስ 1:35–39ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ኢየሱስ ካደረገው ምን ጠቃሚ ትምህርቶችን ማግኘት ይቻላል?





ኢየሱስ ለመጸለይ ጎህ ሳይቀድ ተነስቶ ወደ ገለልተኛ ስፍራ ሄደ። ጸሎት ኢየሱስ የሚያተኩርበት ነገር ስለመሆኑ ማርቆስ 1፡35 አጽንዖት ይሰጣል።

በአረፍተ ነገሩ ውስጥ ሌሎቹ በግስ መልክ የቀረቡ ሀሳቦች አጠር ባለ መልክ ተነሳ፣ ሄደ፣ ተለየ በማለት ተገልጸዋል (እነዚህ የቀረቡበት ሁኔታ በግሪክ ቋንቋ ሂደቱ መጠናቀቁን የሚገልጽ ነው)። ነገር ግን በዚህ ቦታ “ይጸልይ ዘንድ” የሚለው ግስ ፍጹማዊ ያልሆነ ሲሆን ሂደቱ ቀጣይነት ያለው መሆኑን ያመለክታል። እየጸለየ ነበረ፣ መጸለዩን ቀጠለበት። ደግሞ ጥቅሱ ኢየሱስ ምን ያህል በማለዳ ለጸሎት ይሄድ እንደነበር አጽንዖት መስጠቱ የሚያመለክተው ኢየሱስ ለጸሎት ሰፊ ጊዜ ይሰጥ እንደነበር ነው።

በሁሉም ወንጌላት ውስጥ ኢየሱስን የምናገኘው እንደ ጸሎት ሰው ነው (ማቴ. 14፡23፤ ማር. 6፡46፤ ዮሐ. 17ን ይመልከቱ)። የኢየሱስ አገልግሎት በኃይል የተሞላ እንዲሆን ካደረጉ ቁልፍ ምስጢሮች መካከል አንዱ ይህ ይመስላል።

ሉቃስ 6:12ን ያንብቡ። ይህ ስለ ኢየሱስ የጸሎት ሕይወት ምን ያስተምራል?





ብዙ ክርስቲያኖች ለጸሎት የተለየ ጊዜ መድበዋል። ይህ ልምምድ ጥሩና ትክክለኛም ነው፣ ነገር ግን በቃል የሚደገም የተለመደ ነገር ሊሆንም ይችላል።

ከዚህ ከተለመደው ቅርጽ መውጣት ከሚቻልባቸው መንገዶች አንዱ አልፎ አልፎ የጸሎት ጊዜን መቀየር ወይም አንዳንድ ጊዜ ከዚህ በፊት ከሚደረገው ረዘም ላለ ጊዜ መጸለይ ነው። ነጥቡ ራስዎን በፍጹም ሊለወጥ በማይችል በሆነ ቀመር ውስጥ ላለመቆለፍ ነው።

ጴጥሮስና ጓደኞቹ ኢየሱስን ወደ ጸሎት ስፍራ አላጀቡትም ነበር። ኋላ ፈልገው ስላገኙት የሚጸልይበትን ቦታ የሚያውቁ ይመስላል። ሰው ሁሉ ኢየሱስን ይፈልግ እንደነበር መናገራቸው ባለፈው ቀን ያደረገውን የማዳንና የማስተማር አስደሳች ተሞክሮ በበለጠ ሁኔታ ማስቀጠሉን ነው። በሚያስገርም ሁኔታ በማቅማማት በሌሎች ቦታዎች ሊሰራ የሚገባ ሰፊ የስራ መስክ መኖሩን ጠቆመ።

“እርሱም፦ በዚያ ደግሞ ልሰብክ ወደ ሌላ ስፍራ በቅርብ ወዳሉ መንደሮች እንሂድ ስለዚህ ወጥቻለሁና አላቸው።” (ማር. 1:38)።

ኢየሱስ ራሱ ይህን ያህል ሰዓት በጸሎት ማሳለፍ ካስፈለገው እኛስ ምን ያህል ጊዜ በጸሎት ማሳለፍ አለብን? የኢየሱስ ምሳሌ ለእርስዎ ምን ይነግሮታል?

ሐምሌ 4
Jul 11

ምስጢር መጠበቅ ይችላሉ?


ማርቆስ 1:40–45ን ያንብቡ። ይህ ስለ ኢየሱስ እና እርሱ በሕብረተሰቡ ውስጥ ከተገለሉት ጋር እንዴት ግንኙነት እንደፈጠረ ምን ያስተምረናል?



የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

የሥጋ ደዌ በሽታ በዚህ ንባብ ውስጥና በመላው ብሉይ ኪዳን ውስጥ ዛሬ የሃንሴን በሽታ (በተለምዶ የሥጋ ደዌ በሽታ) ተብሎ የሚገለጸውን ብቻ አያመለክትም። መጽሐፍ ቅዱሳዊው ቃል በተሻለ ሁኔታ “አስፈሪ/አሰቃቂ የቆዳ በሽታ” ተብሎ ሊተረጎም የሚችል ሲሀን ሌሎች የቆዳ በሽታዎችንም ሊያካትት ይችላል። የሃንሰን በሽታ ወደ ጥንቱ የቅርብ ምሥራቅ የመጣው ከክርስቶስ ልደት በፊት በ3ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አካባቢ ነበር። (ዴቪድ ፒ ራይት እና ሪቻርድ ኤን ጆንስ በአንከር የመጽሐፍ ቅዱስ መዝገበ ቃላት ቅጽ 4 ላይ ስለ “የሥጋ ደዌ” የጻፉትን ይመልከቱ [New York: Doubleday, 1992], pp. 277–2

82)። ስለዚህ ግለሰቡ ይሰቃይ የነበረው በሽታ በትክክል ምን እንደነበር እርግጠኞች መሆን ባንችልም በዚህ ንባብ ውስጥ የተመለከተው የሃንሰን በሽታ ሊሆን እንደሚችልና ክፉ በሽታ እንደነበር እናውቃለን።

ለምጻሙ ኢየሱስ ሊያነጻው እንደሚችል አመነ። ዘሌዋውያን ምዕራፍ 13 ላይ እንደተገለጸው ለምጻም እርኩስ ስለሆነ ከሌሎች ሰዎች ጋር መገናኘት የለበትም (ዘሌ. 13፡ 45፣ 46ን ይመልከቱ)።

ነገር ግን ኢየሱስ ለሰውዬው አዘነለትና ነካው። “ኢየሱስም አዘነለት እጁንም ዘርግቶ ዳሰሰውና፦ እወድዳለሁ፤ ንጻ አለው።” (ማር. 1:41)። ይህ ድርጊት እንደገና ንጹህ ለመሆን ገላውን መታጠብን እስኪጠይቀው ድረስ እስከ ምሽት እርኩስ ያደርገው ነበር (ከዘሌ. 13-15 ጋር ያነጻጽሩ)። ነገር ግን የኢየሱስ ህመምተኛውን የመንካት ተግባር ከለምጹ እንደሚያነጻው ማርቆስ ብዥታ አልነበረውም። ስለሆነም ኢየሱስ ሰውዬውን በመንካቱ አልረከሰም ነበር።

ሙሴ የዚህ ዓይነት ክስተቶች ሲከሰቱ ግለሰቡ እንዲያቀርባቸው በዘሌዋውያን 14 ላይ ያዘዛቸውን መስዋዕቶች እንዲያቀርብ መመሪያ በመስጠት ኢየሱስ ይህን ሰው ወደ ካህን ላከው። በመላው የማርቆስ ወንጌል ውስጥ ኢየሱስ ሙሴ ላዘዛቸው ነገሮች እንደ ከጥቃት ተከላካይና ደጋፊ ሆኖ ቆሟል (ማር. 7፡10፤ 10፡3፣ 4፤ 12፡26፣ 29-31)። ይህ አመለካከት በማርቆስ 7፡10 እና 12 ውስጥ በሙሴ አማካይነት የተሰጡ ትምህርቶች የነበራቸውን የመጀመሪያ ዕቅዳቸውን ከሚያዛቡ የኃይማኖት መሪዎች አመለካከት በተቃራኒ ይቆማል። እነዚህ ዝርዝሮች ኢየሱስ በማርቆስ 1፡ 44 ላይ ሰውዬው ዝም እንዲል ያዘዘበትን ምክንያት ያብራራል።

ኢየሱስ እንደፈወሰው እንዲናገር ተፈቅዶለት ቢሆን ኖሮ ካህኑ ለኢየሱስ ከነበረው ጥላቻ (የተዛባ አመለካከት) የተነሣ የውሳኔውን ሚዛናዊት ያበላሽ ነበር።

ነገር ግን የነጻው ለምጻም ይህን የተረዳ አይመስልም፤ ከዚህ የተነሣ የኢየሱስን ትዕዛዝ ባለመታዘዝ ዜናውን በሁሉም ስፍራ ከማሰራጫቱ የተነሣ ኢየሱስ ለአገልግሎት ወደ ከተሞች በግልጽ መግባት አልቻለም ነበር።

አንድን ነገር የምናደርግበት ዓላማ ምንም ያህል መልካም ቢሆንም የወንጌልን ሥርጭት የሚገቱ ነገሮችን እንዳንፈጽም መጠንቀቅ የምንችለው እንዴት ነው?

ሐምሌ 5
Jul 12


ተጨማሪ ሀሳብ


“በቅፍርናሆም” እና “ልታነጻኝ ትችላለህ” የሚሉ ርዕሶችን ኤለን ጂ ኋይት ከጻፈችው የዘመናት ምኞት ከሚለው መጽሐፍ ገጽ 252–266ን ያንብቡ። ማርቆስ ምዕራፍ 1 የሚያቀርበው የኢየሱስ ምስል ምንድር ነው? ኢየሱስ ደቀ መዛሙርትን የመጥራት ስልጣን ሲኖረው እነርሱም ለጥሪው ምላሽ ይሰጣሉ።

ከሰይጣን ሥር ካሉ እርኩሳን መናፍስት በተቃራኒ እርሱ ቅዱስ ነው። በመልካምና በክፉ መካከል ታላቅ ጦርነት እየተካሄደ ሲሆን ኢየሱስ ከአጋንንት የበለጠ ኃይል አለው። ኢየሱስ ለህመምተኞች ርኅራኄ ስላለው ምናልባት ማንም ሊነካቸው በማይፈልግበት እርሱ ቀርቦ በመንካት ይረዳቸዋል። “ኢየሱስ ሊመሰርት ስለመጣው መንግሥትና የሰይጣን ምርኮኞችን ነጻ ለማውጣት ስላለው ተልዕኮ በምኩራብ ተናገረ። ከመሸበር ከሚመጣ የጩኸት ድምጽ የተነሣ ንግግሩ ተቋረጠ። ከሕዝቡ መካከል አንድ እብድ ሰው ‘ተው፥ የናዝሬቱ ኢየሱስ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለን? ልታጠፋን መጣህን? ማን እንደ ሆንህ አውቄሃለሁ፥ አንተ የእግዚአብሔር ቅዱሱ’ እያለ በመጮህ ወደ ፊት ሮጠ።

“አሁን ሁሉም ነገር የሚያወዛግብና የሚያስደነግጥ ነው። የሰዎች ትኩረት ከኢየሱስ ወደ ሌላ አቅጣጫ እንዲመለስ ተደርጓል፣ ቃላቶቹም ተሰሚነት አላገኙም። ምርኮኞቹን ወደ ምኩራብ ሲመራ ይህ የሰይጣን ዓላማ ነበር። ነገር ግን ኢየሱስ አጋንንቱን እንዲህ በማለት ገሰጸው፡- ‘ኢየሱስም፦ ዝም በል ከእርሱም ውጣ ብሎ ገሠጸው። ጋኔኑም በመካከላቸው ጥሎት ሳይጐዳው ከእርሱ ወጣ።’ . . . በምድረ በዳ ሰይጣንን ድል ያደረገው እርሱ አሁን እንደገና ከጠላቱ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጧል። አጋንንት ግዳዩን በቁጥጥሩ ሥር አድርጎ ለማቆየት ኃይሉን ሁሉ ተጠቀመ። በዚህ ቦታ መሸነፍ ኢየሱስ ድል እንዲያደርግ መፍቀድ ነው።… ነገር ግን አዳኙ በሥልጣን በመናገር ምርኮኛውን ነጻ አወጣ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, pp. 255, 256. የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ይህ እየሆነ ሳለ ጌታችን ከቦታ ቦታ እየተንቀሳቀሰ ያለማቋረጥ ከሰዎች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ሥራ የበዛበትን አገልግሎት አከናወነ። ማገልገልና ለሕዝብ እርጋታንና ቀጣይነት ያለውን አቀራረብ ጠብቆ ማቆየት የቻለው እንዴት ነበር? ይህን ማድረግ የቻለው በየዕለቱ ከነበረው የጸሎት ልምምድ የተነሣ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም።

ጸሎትንና ቅዱሳት መጻሕፍትን ማጥናትን በተመለከተ ለእርስዎ ሊሰራ የሚችል የጊዜ ሰንጠረዥ ምን ሊሆን እንደሚችል ያስቡ። ለእርስዎ የሚሰራውን ያግኙና በመንፈስና በእግዚአብሔር ቃል የተመራ ሰላማዊ መንፈስን ለማጎልበት ያንን ጊዜ ይውሰዱ።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ስለ ፀሎት ጥያቄና በክርስትና ሕይወት ስለሚኖረው አስፈላጊነት በክፍል ውስጥ ተነጋገሩ። ስለ ጸሎት ዓላማና ውጤት የማምጣት ኃይል ሰዎች ካሏቸው ጥያቄዎች አንዳንዶቹ ምንድር ናቸው?

2. አንዳንድ ጊዜ ስለ እምነታችን ከልክ በላይ ማውራት ጥሩ ስለሚሆንባቸው ሁኔታዎች በክፍላችሁ ውስጥ ተነጋገሩ። እንደዚህ ማድረግ ተገቢ የሚሆንበት ጊዜ መቼ ሊሆን ይችላል? በምስክርነታችን ላይ ሳንደራደር ይህን እንዴት ማድረግ እንችላለን?

3. ዘሬ በእርስዎ ባህል ለምጻሞች እነማን ናቸው? የእርስዎ ቤተ ክርስቲያን እነዚህን ግለሰቦች ‹‹መንካትና›› ወንጌልን ለእነርሱ ማድረስ የምትችለው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL