የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የማርቆስ መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሰኔ 22 - 28

1ኛ ትምህርት

Jun 29 - Jul 5




የወንጌሉ ጅማሬ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- የሐዋ. 13:1–5፣ 13፤ የሐዋ. 15:36–39፤ ማር. 1:1–15፤ ኢሳ. 40:3፤ ዳን. 9:24–27።


የመታሰቢያ ጥቅስ:- “ዮሐንስም አልፎ ከተሰጠ በኋላ ኢየሱስ የእግዚአብሔርን መንግሥት ወንጌል እየሰበከና 'ዘመኑ ተፈጸመ የእግዚአብሔርም መንግሥት ቀርባለች ንስሐ ግቡ በወንጌልም እመኑ' እያለ ወደ ገሊላ መጣ።” (ማርቆስ 1:14፣15)

የማርቆስን ወንጌል የጻፈው ማን ነው? የተጻፈውስ ለምንድር ነው? የትኛውም ወንጌል የደራሲውን ስም አይገልጽም። ከሌሎቹ እጅግ የሚቀርበው ተወዳጅ ደቀ መዝሙር የሚል ስም የተሰጠው ዮሐንስ ነው (ዮሐንስ 21፡ 20፣ 24ን ይመልከቱ)። ሆኖም ከጥንት ጀምሮ ቀኖናዊ ወንጌላት ከሐዋርያ ጋር (ማቴዎስ፣ ዮሐንስ) ወይም ከሐዋርያው ጓደኛ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ቀርበዋል። ለምሳሌ የሉቃስ ወንጌል ከጳውሎስ ጋር ተገናኝቷል (ቆላ. 4፡14፣ ፊልሞና 1፡24ን ይመልከቱ)። የማርቆስ ወንጌል ከጴጥሮስ ጋር ተገናኝቷል (1ኛ ጴጥ. 5፡13ን ይመልከቱ)። የማርቆስ ወንጌል ፀሐፊ በመጽሐፉ ውስጥ ስሙን በፍጹም ባይጠቅስም የቀደምት ቤተ ክርስቲያን ወግ ደራሲው በሆነ ጊዜ ከጳውሎስና ከበርናባስ ጋር አብሮ ይጓዝ የነበረው (የሐዋ. 13፡2፣5) እና ኋላ የጳውሎስ የሥራ አጋር የነበረው (1ኛ ጵጥ. 5፡13) ዮሐንስ ማርቆስ መሆኑን ያመለክታል።

በዚህ ሳምንት የመጀመሪያ እርምጃ የሚሆነው ስለ ማርቆስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተመለከተበት ሁኔታ የመጀመሪያ ውድቀቱንና ኋላ ከውድቀቱ መነሳቱን ማጥናት ነው። ከዚያ በኋላ የማርቆስ መጽሐፍ መክፈቻ ወደሆነው ክፍል በመመለስ ታሪኩ ወደ ፊት ወዴት እንደሚያመራ መመልከትና በአንድ አጋጣሚ የወደቀና ወደ ሚስዮናዊነት የተመለሰ ግለሰብ ለምን የዚህን ዓይነት ጽሁፍ እንደጻፈ ወደ ኋላ ዞር ብሎ መመልከት ነው። *የዚህን ሳምንት ጥናት ለሰኔ 29 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሰኔ 23
Jun 30

የወደቀው ሚስዮናዊ


የሐዋ. ሥራ 12:12ን ያንብቡ። በሐዋርያት ሥራ መጽሐፍ ውስጥ ማርቆስ የተዋወቀው እንዴት ነው?



የማርቆስ ወንጌል ፀሐፊ እንደሆነ የሚገመተው ዮሐንስ ማርቆስ በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 12 ላይ የተጠቀሱ ክስተቶች በተፈጸሙ ጊዜ፣ ምናልባት በ40 ዓ.ም አጋማሽ ላይ፣ ወጣት ሰው የነበረ ይመስላል። በቁጥር 12 ላይ እናቱ ማርያም የተባለች እንደሆነ ተዋውቋል። ይህቺ ሴት ሀብታም የቤተ ከክርስቲያን ደጋፊ መሆኗ የተረጋገጠ ሲሆን በቤቷ የጸሎት ስብሰባዎችን በማካሄዷ በሐዋርያት ሥራ 12 ላይ ታዋቂ ሴት ሆናለች። የጴጥሮስ ከወህኒ ቤት ማምለጥና ተከትለው የተፈጸሙ ድርጊቶች እና የሄሮድስ ሞት አስደናቂ በሆኑና እንዲያውም በጴጥሮስና በንጉሡ መካከል ከተከሰቱ ነገሮች የተነሳ አስቂኝ በሆኑ ንጽጽሮች የተሞላ ነው። ዮሐንስ ማርቆስ በታሪኩ ውስጥ ምንም ሚና አልተጫወተም፣ ነገር ግን በዚህ ነጥብ ላይ እርሱን ማስተዋወቁ ኋላ ከበርናባስና ከሳውል ጋር ለሚኖረው ግንኙነት ያዘጋጀዋል።

የሐዋ. ሥራ 13:1–5፣ 13ን ያንብቡ። ዮሐንስ ማርቆስ ከሳውልና ከበርናባስ ጋር የተገናኘው እንዴት ነበር? ውጤቱስ ምን ነበር?



የሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 13 ከ46 ዓ.ም ጀምሮ የተካሄደውን የሳውልና የበርናባስ የመጀመሪያውን ሚስዮናዊ ጉዞ ይገልጻል። እስከ ምዕራፍ 5 ድረስ ዮሐንስ ማርቆስ ያልተጠቀሰ ሲሆን ሚናው የረዳትነት ወይም የአገልጋይነት ሚና ነበር። እርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ስለመመለሱ አጠር ያለ ዘገባ እስከተሰጠበት እስከ ቁጥር 13 ድረስ ስለ ወጣቱ ሰው ምንም ነገር አልተጠቀሰም።

ለመሄዱም ምንም መግለጫ ያልተሰጠ ሲሆን በዚያን ጊዜ ስለነበረው ስሜትና ስላነሳሳው ነገር ምንም መግለጫ አለመኖሩ ያለ አንዳች ጥርጥር አደጋና ግድድሮሽ ከሞላበት ሚስዮናዊ ጉዞ እንዲወጣ ያነሳሳው ምን እንደሆነ ሰዎች እንዲገምቱ እድል ሰጥቷል። ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ ገልጻለች፡- “ማርቆስ በፍርሃትና ተስፋ መቁረጥ ተሸንፎ ራሱን ከሙሉ ልቡ ለእግዚአብሔር ሥራ አሳልፎ ከመስጠት ዓላማ ለጊዜው ዋዥቋል። ከችግር ጋር ካለመለማመዱ የተነሣ ይህ መንገድ የሚያስከትላቸውን አደጋዎች በማየት ልቡ ፈራ።”— The Acts of the Apostles, p. 169። በአጭሩ፣ ነገሮች እጅግ ስለከበዱበት መውጣት ፈለገ።

ከሆነ ነገር፣ በተለይም መንፈሳዊ ከሆነ ወይም የክርስትና ጉዞን ከሚያካትት ነገር፣ ወደ ኋላ ስለማፈግፈጉ ወይም መፈጸም ስለ አለመቻሉ መናገር የማይችል ማን ነው? ከልምምዱ ምን ተማሩ?

ሰኔ 24
Jul 01

ሁለተኛ ዕድል


የሐዋ. ሥራ 15:36–39ን ያንብቡ። ጳውሎስ ዮሐንስ ማርቆስን አልቀበል ያለው ለምን ነበር? በርናባስ ሁለተኛ ዕድል የሰጠውስ ለምን ነበር?



ጳውሎስ ወጣቱን ሰው አልቀበል ያለበት ምክንያት በሐዋርያት ሥራ 15፡ 38 ላይ ተሰጥቷል። ማርቆስ ከእነርሱ ተለይቷል፣ በአገልግሎት ሥራም ከእነርሱ ጋር አልቀጠለም። ጳውሎስ ይህን የመሰለ የማያወላውል እርምጃ እንዲወስድ ያደረገውን አመለካከት ማስተዋል የሚቻል ነው። ሚስዮናዊ ሕይወት፣ በተለይም በጥንቱ ዓለም፣ አስቸጋሪና ብዙ ጥረት ማድረግን የሚጠይቅ ነበር (ከ2ኛ ቆሮ. 11፡ 23-28 ጋር ያወዳድሩ)። የዚህ ዓይነቱን ተግዳሮት ያለበትን ሥራና ሁኔታዎች ሸክም ለመሸከም እንዲረዱት ጳውሎስ እንደ እርሱ ባሉ ሚስዮናውያን ይደገፍ ነበር። በእርሱ አመለካከት እንደዚህ ባለ ሁኔታ በፍጥነት ትቶአቸው የሄደ ሰው ከክፉ ኃይሎች ጋር የሚደረገውን የጨበጣ ውጊያ ለመዋጋት በተሰለፈው ሚስዮናዊ ቡድን ውስጥ ቦታ ሊሰጠው የሚገባ አይደለም።

በርናባስ በዚህ ሀሳብ አልተስማማም። በማርቆስ ውስጥ ያለውን ዕምቅ ኃይል ስላየ ወጣቱን ሊተወው አልፈለገም። ዮሐንስ ማርቆስን በተመለከተ በጳውሎስና በበርናባስ መካከል ይህን የመሰለ ጥልቅ አለመስማማት ከመፈጠሩ የተነሣ ሁለቱም ተለያይተው በተለያየ መንገድ ሄዱ። ጳውሎስ አብሮት እንዲሄድ የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ሲላስን የመረጠ ሲሆን በርናባስ ደግሞ ማርቆስን ወሰደ።

በርናባስ ማርቆስን ከእርሱ ጋር ይዞ ለመሄድ ለምን እንደመረጠ የሐዋርያት ሥራ አያብራራም። እንዲያውም በሐዋርያት ሥራ ውስጥ ሁለቱ ሰዎች የታዩበት የመጨረሻው ቦታ ይህ ነው። ነገር ግን በሚያስገርም ሁኔታ ይህ ቦታ በአዲስ ኪዳን ውስጥ ማርቆስ የተጠቀሰበት የመጨረሻው ቦታ አይደለም።

ቆላ. 4፡10፤ 2ኛ ጢሞ. 4፡11፤ ፊልሞና 24፣ 1ኛ ጴጥ. 5፡:13ን ያንብቡ። ስለ ማርቆስ ወደ ቀድሞ አገልግሎቱ ስለመመለሱ እነዚህ ጥቅሶች ምን ዝርዝር ይጠቅሳሉ?



በማርቆስ ውስጥ አስደናቂ የሆነ ለውጥ የተከሰተ ይመስላል። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ማርቆስ ለእርሱና ለአገልግሎቱ ያለውን ዋጋ ጳውሎስ ያመለክታል።

ጳውሎስ አብረውት ከሚሰሩ ሰራተኞች እንደ አንዱ በመቁጠር ጢሞቴዎስ ይዞት እንዲመጣ ይፈልጋል። ጴጥሮስም ከማርቆስ ጋር የቅርብ ግንኙነት እንደነበረው 1ኛ ጴጥሮስ ያመለክታል። እነዚህ በጳውሎስና በጴጥሮስ የተጻፉ መጻሕፍት የተጻፉት በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ 15 ላይ ከተጠቀሰው ልምምድ ከ15-20 ዓመት በኋላ በ60 ዓ.ም ጅምር ላይ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል። ማርቆስ ከውድቀቱ ሙሉ በሙሉ ያገገመ ሲሆን ለዚህ ምክንያቱ በእርግጠኝነት ዘመዱ የሆነው በርናባስ በእርሱ ላይ እምነት ከመጣሉ የተነሳ ሊሆን ይችላል።

እርስዎ የወደቁበትን ወይም ወዳጅዎ የወደቀበትንና ሁለተኛ እድል የተሰጣችሁን ጊዜ ያስቡ። ያ ልምምድ እርስዎንና እርስዎን የረዱ ሰዎችን የለወጠው እንዴት ነበር? ለሌሎች የሚያደርጉትን አገልግሎትዎን ያሻሻለውስ እንዴት ነበር?

ሰኔ 25
Jul 02

መልእክተኛው


ማር. 1:1–8ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ገጸ ባህሪያቱ እነማን ናቸው? ምን ይላሉ? ምንስ ያደርጋሉ?





እነዚህ ቁጥሮች ሶስት ዋና ባህርያት አሏቸው፡- ማርቆስ 1፡1 ላይ የተጠቀሱት ኢየሱስ፣ እግዚአብሔር አብ (በማርቆስ 1፡ 2 ላይ በተዘዋዋሪ የተመለከተው) እና የዚህ መልእክት የመጨረሻው ክፍል ዋና ርዕሰ ጉዳይ የሆነው መልእክተኛና ሰባኪ መጥምቁ ዮሐንስ ናቸው። ማርቆስ 1፡ 2ና 3 ማርቆስ በታሪኩ ውስጥ ምን እንደሚሆን ለመግለጽ ያቀረበውን ከብሉይ ኪዳን የተጠቀሰ ጥቅስ ይዟል። ማርቆስ የጠቀሰው ሀሳብ ከሶስት ንባቦች የወሰዳቸው ሀረጎች ጥምረት ነው፡- ዘጸአት 23፡ 20፣ ኢሳይያስ 40፡3፣ እና ሚልክያስ 3፡1።

ዘጸ. 23:20፤ ኢሳ. 40:3፤ ሚል. 3:1ን ያንብቡ። እነዚህ ሶስት ንባቦች ያላቸው የጋራ የሆነ ነገር ምንድር ነው?



ዘጸአት 23:20 እሥራኤልን ወደ ከነዓን እንዲያመጣ እግዚአብሔር ከፊታቸው የሚልከውን መልአክ ያመለክታል። ኢሳይያስ 40፡3 እግዚአብሔር በፊቱ በተዘጋጀው አውራ ጎዳና በምድረ በዳ ስለመገለጡ ይናገራል። ሚልክያስ 3፡ 1 ለእግዚአብሔር መንገድ ለማዘጋጀት ከፊቱ ስለሚሄደው መልእክተኛ ይናገራል።

እነዚህ ሶስቱም ንባቦች ስለ ጉዞ ይናገራሉ። በኢሳይያስ መጽሐፍ ውስጥ ያለው ጥቅስ ከመጥምቁ ዮሐንስ አገልግሎት ጋር ብዙ ግንኙነቶች ያሉት ሲሆን በጌታ መንገድ ላይም ትኩረት ያደርጋል። በማርቆስ ወንጌል ውስጥ ጌታ ኢየሱስ በጉዞ ላይ ነው። በፍጥነት እየተከናወነ የነበረው ትረካ ወደ መስቀልና ለእኛ ወደሚፈጽመው የመስዋዕትነት ሞት የሚመራውን የዚህን ጉዞ ስሜት ያፋጥናል።

ነገር ግን ወደ መስቀል ከመድረሱ በፊት ብዙ ነገሮች መከሰት አለባቸው።

ጉዞው ገና እየጀመረ ሲሆን ማርቆስ ስለዚህ ጉዞ ሁሉንም ነገር ይነግረናል። ማርቆስ 1፡2ና 3 ላይ ማርቆስ ከብሉይ ኪዳን የወሰደውን ጥቅስ በአእምሮው በመያዝ መጥምቁ ዮሐንስ ለንስሃ፣፣ ከኃጢአት ለመራቅና ወደ እግዚአብሔር ለመመለስ ጥሪ ያደርጋል (ማርቆስ 1፡4)። እንደ ጥንቱ ነብይ ኤልያስ ለብሶ (ከ2ኛ ነገሥት 1፡8 ጋር ያነጻጽሩ) በማርቆስ 1፡7፣8 ላይ ከእርሱ በኋላ ስለሚመጣውና ከእርሱ ስለሚበረታው ይናገራል። የሚመጣውን መሲህ የጫማውን ጠፍር እንኳን ሊፈታ እንደማይገባ ለመግለጽ የተናገረው አረፍተ ነገር እርሱ ለኢየሱስ ያለውን ከፍ ያለ አመለካከት የሚያሳይ ነው። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ሰኔ 26
Jul 03

የኢየሱስ ጥምቀት


ማርቆስ 1:9–13ን ያንብቡ። በኢየሱስ ጥምቀት ላይ የነበረው ማን ነበር? ምንስ ሆነ?



ዮሐንስ ኢየሱስን በዮርዳኖስ ወንዝ አጥምቆታል፣ ነገር ግን ከውኃው ሲወጣ ሰማይ ሲከፈትና መንፈስ ቅዱስ በርግብ መልክ በእርሱ ላይ ሲወርድ ይመለከታል። ከሰማይ እንዲህ የሚለውን የእግዚአብሔርን ድምጽ ሰማ፡-

“ ‘አንተ የምወድህ ልጄ ነህ፤ በአንተ እጅግ ደስ ይለኛል’ ” (ማርቆስ 1:11)። እነዚህ ክስተቶች ወደ ኢየሱስ ጥምቀት አስፈላጊነት ያመላክታሉ። አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ የኢየሱስን አገልግሎት ጅምር ለማረጋገጥ አብረው ነበሩ።

የዚህ ክስተት አስፈላጊነት በማርቆስ 15 ላይ ባለው ትዕይንት ላይ ያስተጋባል። የዚያው ታሪክ አብዛኞቹ አላባዎች (ስረ ነገሮች) በትዕይንቱ ውስጥ ተደጋግመው ይመጣሉ።

መንፈስ ኢየሱስን ወደ ምድረ በዳ ወሰደው። “ወሰደው” የሚለው ቃል ኤክባሎ ከሚል የግሪክ ቃል የመጣ ሲሆን በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ አጋንንትን ማውጣትን ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለ ቃል ነው። በዚህ ቦታ የመንፈስ መገኘት የሚያሳየው መንፈስ ቅዱስ በኢየሱስ ሕይወት ያለውን ኃይል ነው። ጌታ የአገልግሎት ጉዞውን እየጀመረ ሲሆን ወዲያውኑ ሰይጣንን ተጋፈጠ። በቦታው የነበረው የተጋድሎው ስሜት የታየው 40ዎቹን የፈተና ቀናት፣ የዱር አራዊትን መገኘት እና የመላእክት ኢየሱስን ማገልገልን በመጥቀስ ነው።

የማርቆስ ወንጌል ትዕይንት የተጀመረበት ያልተለመደ ባህርይ ኢየሱስ መለኮታዊና ሰብአዊ ባህርይ ይዞ መቅረቡ ነው። በመለኮታዊነት እርሱ ክርስቶስ፣ መሲህ (ማርቆስ 1፡1)፣ በመልእክተኛ የተዋወቀው ጌታ (ማር. 1፡2፣3)፣ ከዮሐንስ የሚበረታ (ማር. 1፡7) እና መንፈስ የወረደበት የተወደደ ልጅ (ማር. 1፡10፣11) ነው።

ነገር ግን በሰብአዊ ጎኑ የሚከተሉትን ነገሮች እንመለከታለን፡- በዮሐንስ ተጠምቋል (የዚህ ተገላቢጦሽ ግን አልሆነም፣ ማርቆስ 1፡9)፣ በመንፈስ ተነድቷል (ማርቆስ 1፡ 12)፣ በሰይጣን ተፈትኗል (ማር. 1፡13)፣ ከዱር አራዊት ጋር አሳልፏል (ማር.1:13)፣ መላእክት አገልግለውታል (ማር. 1፡13)።

እነዚህ ንጽጽሮች ለምን ያስፈልጋሉ? ይህ ጌታችንና አዳኛችን፣ እንዲሁም አምላካችን ወደሆነውና ደግሞም ሰብአዊ ፍጡር፣ ወንድማችንና ምሳሌያችን ወደሆነው የክርስቶስ አስደናቂ እውነታ ያመለክታል። በዚህ ሀሳብ ዙሪያ ሀሳባችንን ሙሉ በሙሉ መጠቅለል የምንችለው እንዴት ነው? ማድረግ አንችልም። ነገር ግን በእምነት በመቀበል ይህ እውነት እግዚአብሔር ለሰብአዊ ዘር ስላለው ፍቅር በገለጸው ነገር እንደነቃለን።

ኢየሱስ አምላክ ቢሆንም እኛን ለማዳን ሲል ሰብአዊነትን መልበሱ ስለ እግዚአብሔር አስደናቂ ፍቅር ምን ይነግረናል?

ሰኔ 27
Jul 04

ወንጌል ኢየሱስ እንደተናገረው (የኢየሱስ ወንጌል)


ማርቆስ 1:14፣ 15ን ያንብቡ። ኢየሱስ ያወጀው የወንጌል መልእክት ሶስቱ ክፍሎች ምንድር ናቸው?



ማርቆስ በዚህ ቦታ የኢየሱስን ቀላልና ቀጥተኛ የሆነ መልእክት አሳጥሮ ያቀርባል። የዚህ መልእክት ሶስቱ ክፍሎች በሚቀጥለው ሰንጠረዥ ላይ ተብራርተዋል፡-




ኢየሱስ እየጠቀሰ ያለው የጊዜ ትንቢት ዳንኤል 9፡24-27 ላይ ያለው የሰባ ሳምንታት ትንቢት ነው። ይህ ትንቢት ተፈጻሚነት ያገኘው ኢየሱስ በመንፈስ ቅዱስ በተቀባበትና አገልግሎቱን በጀመረበት በጥምቀቱ ነበር (የሐዋ. 10፡38)።

አስደናቂው የ70 ሳምንት ትንቢት በሚከተለው ሰንጠረዥ ላይ ተብራርቷል፡-


የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

በዚህ ትንቢት አንድ ቀን ለአንድ አመት ይቆማል (ዘሁልቁ 14፡34፤ ሕዝ. 4፡6)። ትንቢቱ የጀመረው በ457 ዓ.ዓ የፋርስ ንጉሥ በነበረው በአርጤክስስ አዋጅ ሲሆን በኢየሩሳሌም እንደገና መሰራት ይጠናቀቃል። (ዕዝራ ምዕራፍ 7ን ይመልከቱ)።

ስልሳ ዘጠኝ ሳምንታት ኢየሱስ በአገልግሎቱ ጅማሮ እስከተጠመቀበትና እስከተቀባበት እስከ 27 ዓ.ም ይደርሳል።

ስቅለቱ የተፈጸመው ከሶስት ዓመት ተኩል በኋላ ነበር። በመጨረሻ፣ ሰባኛው ሳምንት የተጠናቀቀው እስጢፋኖስ ተወግሮ የወንጌል መልእክት ወደ አህዛብና ወደ አይሁዶች መወሰድ በጀመረ ጊዜ ነበር።

የ70 ሳምንታት ትንቢትን ያጠኑበት የመጨረሻው ጊዜ መቼ ነበር? ይህን ትንቢት ማወቅዎ በኢየሱስ ብቻ ሳይሆን በትንቢታዊ ቃሉ እውነተኛነትም እንዲያምኑ እንዴት ሊረዳዎ ይችላል?

ሰኔ 28
Jul 05




ተጨማሪ ሀሳብ


የዘመናት ምኞት ከሚለው የኤለን ጂ ኋይት መጽሐፍ “ድምጽ በምድረ በዳ” የሚለውን ርዕስ ከገጽ 97–108 እና የሐዋርያት ሥራ ከሚለው መጽሐፍ “የወንጌል አዋጅ” የሚለውን ርዕስ ከገጽ 166–176 ያንብቡ።

ራዕይ 14፡6ና 7 ላይ ያለው የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ማርቆስ 1፡15 ላይ ኢየሱስ ከሰጠው የወንጌል መልእክት ጋር መመሳሰሉ ምንኛ የሚያስደስት ነው።

የመጀመሪያው መልአክ በመጨረሻ ዘመን ያለው ዓለም ለክርስቶስ ዳግም ምጽዓት እንዲዘጋጅ የሚያደርገውን ዘላለማዊ ወንጌል ያመጣል። ልክ እንደ ኢየሱስ መልእክት የመልአኩ የፍጻሜ ዘመን ወንጌል ከዚህ በታች በሰንጠረዡ እንደተብራራው ተመሳሳይ የሆኑ ሶስት ዋና ሀሳቦች አሉት፡-




የመጀመሪያው መልአክ መልእክት በ1844 ዓ.ም የተጀመረውንና ዳንኤል 8፡ 14 ላይ የተጠቀሰውን የ2300 ቀናት ትንቢትና ከዳግም ምጻት በፊት የሚሆነውን ፍርድ ያስተዋውቃል። ፍርዱ ለተሰደደው ሕዝቡ የእግዚአብሔርን መንግሥት ያመጣል (ዳን. 7፡22)። የመጀመሪያው መልአክ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈሩ፣ እንዲያከብሩና እንዲሰግዱለት ያቀረበው ጥሪ በራዕይ ምዕራፍ 13 ላይ የተጠቀሱ የአውሬው ኃይላት የውሸት አምላክን እንዲፈሩ፣ እንዲያከብሩና እንዲያመልኩ በሚያቀርቡበት በመጨረሻው ጊዜ ለዓለም የሚሰጥ ለደቀ መዝሙርነት የቀረበ ጥሪ ነው።

ኢየሱስ በማርቆስ ምዕራፍ 1 ላይ ያቀረበው መልእክት በወንጌል አዋጅ መጀመሪያ ላይ ከዳንኤል ትንቢቶች ጋር እጅና ጓንት እንደሆነ ሁሉ በምድር ታሪክ መዝጊያ ላይም የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ከዳንኤል ጋር በቅርበት የተሳሰረ ነው። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ማርቆስ 1፡1-13 ላይ በመጥምቁ ዮሐንስና በኢየሱስ መካከል ያለውን ልዩነትና መመሳሰል ያነጻጽሩ። እነርሱ ከቀረቡበት መንገድ ምን የተለዩ ትምህርቶችን መማር ይችላሉ?

2. የጥምቀትን ትርጉም ያስቡ። ሮሜ 6፡1-4ን እና ዮሐንስ 3፡1-8ን ያንብቡና ማርቆስ 1፡9-13 ካለው የኢየሱስ ጥምቀት ጋር ያነጻጽሩ። ምን መመሳሰልና ልዩነት ተመለከቱ? ይህ የጥምቀትን ትርጉም ጥርት ባለ ሁኔታ እንዲረዱ የረዳዎት እንዴት ነው?

3. ማርቆስ 1፡ 14ና 15 ላይ ያለውን የኢየሱስን ወንጌል ራዕይ 14፡ 6ና 7 ላይ ካለው የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ጋር ያነጻጽሩ። እነዚህን መልእክቶች መረዳት ለዛሬ ያለዎትን ተልዕኮ በተሻለ ሁኔታ ማየት እንዲችሉ የረዳዎት እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL