የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ
የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት
በሆነው በጄኔራል ኮንፍራንስ ውስጥ ሆኖ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት
መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጄኔራል
ኮንፍራንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ
መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው።
የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና
የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን
(የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።
በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
3ኛ ሩብ ዓመት
ከሰኔ 22/2016 -- መስከረም 17/2017 ዓ.ም
የማርቆስ
ወንጌል
ከማርቆስ መጽሐፍ ጅማሮ አንስቶ አንባቢው ኢየሱስ መሲህ፣
የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ያውቃል (ማርቆስ 1፡1)። ነገር ግን
በአጋንንት ከተያዙት ሰዎች በስተቀር በታሪኩ ውስጥ ያሉ ሰዎች እርሱ
ማን እንደሆነ እና ለምን እንደመጣ ለመረዳት ተቸግረው ነበር። አጋንንት ግን
እርሱ ማን እንደሆነ በትክክል አውቀው ነበር! አጋንንቶቹ አውቀውት ብርቱ በሆኑ
ቃላቱ ፊት ጠወለጉ። ነገር ግን ይህንን መረጃ ለማንም እንዳይናገሩ አስጠነቀቃቸው
(አዘዛቸው)። ይህ ጉዳይ በምስጢር እንዲያዝ ለምን አዘዘ? የመጽሐፍ ቅዱስ
ተማሪዎች በየዘመናቱ የዚህን ጥያቄ መልስ ለማግኘት ሲያወጡና ሲያወርዱ
ነበር። በትምህርታቸው ውስጥ መሲሃዊው ምስጢር የሚል ስም ተሰጥቶታል።
ስለ ኢየሱስ ማንነት ዝም እንድንል ወንጌል የሚፈልገው ለምንድር ነው?
በማርቆስ ወንጌል የጥናት ጉዞ ላይ ግልጽ የሚሆን ነገር ካለ በዚህ መጽሐፍ
ውስጥ ምስጢር ብቻ ሳይሆን አስደናቂ መገለጥም መኖሩ ነው። በትክክል መገለጥ/
የምስጢር ጭብጥ ተብሎ ሊጠራ የሚችል ሲሆን በመጨረሻ ምሥጢራዊነቱ
በሚያስደንቅ ሁኔታ አብቅቶ ኃይለኛ በሆነ የኢየሱስ መገለጥ የሚተካ ቢሆንም
በማርቆስ ወንጌል ውስጥ በሙሉ ይታያል።
የማርቆስ መጽሐፍ በሁለት ተለይተው በሚታወቁ ክፍሎች ሊከፈል
ይችላል። ከምዕራፍ አንድ ጀምሮ የስምንተኛው ምዕራፍ ማብቂያ አከባቢ
እስኪደርስ ድረስ ያለው ኢየሱስ ማን ነው? የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ ይመልሳል።
መልሱ በትምህርቶቹና በተዓምራቶቹ ውስጥ እንዲታይ ተደርጓል። በተደጋጋሚ
ክፉን አሸንፏል፣ ለተጨቆኑት ተስፋን አምጥቷል፣ ወደ ሰብአዊ ዘር የኑሮ
እምብርት ዘልቀው የሚገቡ አሳማኝ እውነቶችን አስተምሯል፡ ይህ ሁሉ
ለአንባቢው ኢየሱስ የዕብራውያን ሕዝብ ለረዥም ጊዜ ሲጠብቁት የነበረ መሲህ፣
ክርስቶስ መሆኑን ጮክ ብሎ ይናገራል። ነገር ግን አንድ በአጋንንት ያልተያዘ
ሰው የመጽሐፉን አጋማሽ እስኪደርስና ከዚህም የተነሣ የመጽሐፉ የመጀመሪያው
አጋማሽ ስለ ክርስቶስ ማንነት የሚያነሳውን ጥያቄ እስኪመልስ ድረስ እርሱ ማን
እንደሆነ በትክክል መናገር አይችልም። “አንተ ክርስቶስ ነህ” ብሎ ያወጀው ያ
ሰው ጴጥሮስ ነው(ማርቆስ 8:29)።
የማርቆስ መጽሐፍ ሁለተኛው አጋማሽ ከማርቆስ 8፡31 እስከ መጽሐፉ
መጨረሻ ያለው ክፍል ሲሆን ኢየሱስ ወዴት እየሄደ ነው? የሚለውን ሌላኛውን
ጥያቄ ይመልሳል። መልሱ አስደንጋጭ ነው። በሮም ዓለም እጅግ አዋራጅና
አሳፋሪ ወደ ሆነው ወደ መስቀል ሞት እየሄደ ነበር። ሮምን አሸንፎ እሥራኤልን
ኃይለኛ ሕዝብ አድርጎ ይመሰርታል ብለው ለሚያስቡ ተከታዮቹ የመሲሁ መዳረሻ
በፍጹም ያልተጠበቀ ነበር።
ግራ የተጋቡ የኢየሱስ ደቀ መዛሙርት እርሱ ይናገር የነበረውን ነገር
መረዳት አልቻሉም ነበር። መጽሐፉ ወደ ፊት እየቀጠለ ሲሄድ ስለዚህ የሚያም
ርዕስ ማንሳታቸው እየቀነሰ የሄደ ሲሆን በመጨረሻም በዚህ የማይወደድ እውነት
ፊት ዝም ወደማለት ደርሰው ነበር።
ኢየሱስ ስርዓተ ቀብሩን ለመፈጸም የሚዶልቱ የኃይማኖት መሪዎችን
ሲጋፈጣቸው ነገሮች ከጊዜ ወደ ጊዜ ተስፋ አስቆራጭ ይመስሉ ነበር። ባለግርማ
የሆነ መንግሥትን ተስፋ ያደርጉ የነበሩ ደቀ መዛሙርት ከጠበቁት በተቃራኒ
እርሱ ሲያዝ፣ ወደ ፍርድ ሲቀርብና ሲሰቀል እጅግ ደንግጠው ነበር።
ነገር ግን በዚህ ሁሉ ውስጥ ኢየሱስ ወዴት እየሄደ እንደሆነና እርሱ ሙቶ
ከሙታን መነሳት ማለት ምን ማለት እንደሆነ ግልጽና ዘለቄታ ያለው መልእክት
እያስተላለፈ ነበር። የመጨረሻው እራት እንጀራና ጽዋ አካሉንና ደሙን የሚወክል
ሲሆን (ማር. 14፡22-25) እርሱ ለብዙዎች ቤዛ ይሆናል (ማር. 10፡45)።
ይህ ማለት እርሱ ወደ መስቀል የሄደው ስቃዩን በማይገልጽ ጸጥታ ነው
ማለት አይደለም። በጌተሰማኔ ከውሳኔው ጋር ትግል ያደረገ ሲሆን (ማርቆስ 14፡
32-42) በመስቀል ላይ ተስፋ በመቁረጥ “ አምላኬ፣ አምላኬ፣ ለምን ተውከኝ?”
ብሎ ጩኾአል (ማር. 15:34)። የማርቆስ ወንጌል ክርስቶስ የተለማመደውን
ጨለማና ድነታችን ያስከፈለውን ዋጋ ያሳየናል። ነገር ግን መስቀል የጉዞው
መጨረሻ አይደለም። ከትንሣኤው በኋላ በገሊላ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ለመገናኘት
አቀደ። እንደምናውቀው ከዚህ የተነሣ የክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ተጀመረ።
ከወንጌል ጸሐፊው ከራሱ ምንም ተጨማሪ ሀሳብ ሳያካትት በአጭሩ
እና ፈጣን እንቅስቃሴ በሚታይበት ዘይቤ የተነገረ እጅግ አስደናቂ ታሪክ ነው።
የናዝሬቱ ኢየሱስን ሕይወትና ሞት በተመለከተ ዝም ብሎ ታሪኩን በመንገር
ቃላቶቹ፣ ሥራዎቹና ተግባሮቹ ለራሳቸው እንዲናገሩ ትቷል።
ቶማስ አር ሼፔርድ (ፒ ኤች ዲ) በአንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ ባለው የሰባተኛ
ቀን አድቬንቲስት ሰሚናሪ ውስጥ የአዲስ ኪዳን አንጋፋ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ናቸው።
እሳቸውና ባለቤታቸው ሼሪ ሁለት ጎልማሳ ልጆችና ስድስት የልጅ ልጆች አሏቸው።