የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የማርቆስ መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2024


ጳጉሜ 2 - መስከረም 3

11ኛ ትምህርት

Sep 7 - 13




የተወሰደ እና የተፈተነ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- : ማር.14፣ ዮሐ. 12:4– 6፣ ሮሜ 8:28፣ ዘጸ. 24:8፣ ኤር. 31:31–34፣ ዘካ. 13:7።


የመታሰቢያ ጥቅስ: “አባ አባት ሆይ፥ ሁሉ ይቻልሃል፤ ይህችን ጽዋ ከእኔ ውሰድ፤ ነገር ግን አንተ የምትወደው እንጂ እኔ የምወደው አይሁን አለ።” (ማርቆስ 14:36)።

ከማርቆስ 14 እስከ 16 ያሉ ምዕራፎች የኢየሱስን መከራ፣ ሞትና ትንሣኤ ስለሚገልጹ “የስቃይ ታሪክ” በመባል ይታወቃሉ። በ9ኛው ትምህርት ላይ እንደተመለከተው የማርቆስ የመጨረሻዎቹ ስድስት ምዕራፎች የሚሸፍኑት በአንድ ሳምንት ውስጥ የሆነውን ነገር ብቻ ነው። ከማርቆስ 14-16 ባለው ክፍል ውስጥ ያሉ አብዛኞቹ ክስተቶች በዚህ የመከራ ሳምንት ሀሙስና አርብ ላይ ይገኛሉ። ኢየሱስ የሞተው አርብ ዕለት ሲሆን የተነሣው ደግሞ እሁድ ነበር።

የዚህ ሳምንት ትምህርት ከኢየሱስ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ሁለት ተቃራኒ ተግባሮችን በሚያገናኝ ሁለት ታሪኮች መካከል በሚገኝ አምስተኛው ታሪክ በመጀመር ማርቆስ 14 ላይ ትኩረት ያደርጋል። ከዚህ ቀጥሎ የመጣው የመጨረሻው እራት ሲሆን የመጨረሻውን እራት ተከትሎ የመጣው በጌትሰማኔ ያደረገው ትግል ነበር። በዚያ ቦታ ተይዞ ወደ ሕዝብ አለቆች በመወሰድ ለፍርድ ቀርቧል። የፍርድ ሂደት የተካሄደበት ቦታ ጴጥሮስ ኢየሱስን ከካደበት ክስተት ጋር በመገናኘት በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ያለውን ስድስተኛውንና የመጨረሻውን በአንድ ታሪክ መካከል ያለን ታሪክ ይመሰርታል። እንደገና ሁለት ተቃራኒ ድርጊቶች ይከሰታሉ፤ ነገር ግን ምጸታዊ በሆነ መልክ ያንኑ እውነት ያጸናሉ።

በትረካው ውስጥ ሁለት ተጻራሪ የሆኑ ታሪኮች ጎን ለጎን ይሄዳሉ። ማርቆስ የኢየሱስን ድል እየገለጠ ሳለ ጉልህ በሆነ መልኩ በአንባቢው ፊት የሚጋጩ ታሪኮችን ያስቀምጣል። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመስከረም 4 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ጳጉሜ 3
Sep 08

የማይረሳ


ማር. 14:1–11ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ተጋምደው ያሉት ሁለት ታሪኮች ምንድር ናቸው? እርስ በርሳቸው የሚወዳደሩትስ እንዴት ነው?



ማርቆስ 14፡1 ፋሲካ ከሁለት ቀን በኋላ እንደሚሆን ያመለክታል።

ምናልባት ይህ ስብሰባ የተካሄደው በዚያ ሳምንት ማክሰኞ ማታ ወይም ረቡዕ ሊሆን ይችላል። የኃይማኖት መሪዎች ዕቅድ ነበራቸው፣ ዕቅዱን የሚፈጽሙበትን ጊዜም ወስነው ነበር። እቅዳቸውን ከግቡ ለማድረስ መንገድ ይፈልጉ ነበር። ይህ ደግሞ ከሚያስደንቅ ክፍል ይመጣል።

ይህ ንባብ በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ አምስተኛው በሌላ ታሪክ መካከል የተቀመጠ ታሪክ ነው (3ኛውን ትምህርት ይመልከቱ)። በኢየሱስ ላይ የተደረገው የክፋት ዕቅድ ታሪክ የኢየሱስን ራስ በውድ ሽቶ ከቀባችው ሴት ታሪክ ጋር ተገናኝቷል። ሁለት ትይዩ ገጸ ባህሪያት ምጸታዊ ንጽጽርን በማሳየት ተቃራኒ ተግባራትን ይፈጽማሉ።

ሴትዮዋ ማን እንደሆነች ማርቆስ በዚህ ቦታ አልገለጸም። እርሷ ለኢየሱስ የሰጠችው አስደናቂ ስጦታ ከይሁዳ ጌታውን አሳልፎ ከመስጠት ታሪክ ጋር በንጽጽር ተቀምጦአል። እርሷ ስሟ አልተጠቀሰም፤ እርሱ ግን ከአሥራ ሁለቱ አንዱ ተብሎ ስም ተሰጥቶታል። የእርሷ ስጦታ ዋጋ ተዘርዝሯል፤ የእርሱ ዋጋ ገንዘብ ለመስጠት የተገባ ቃል ነው።

እርሷ ላደረገችው ነገር ግልጽ የሆነ ምክንያት አልተሰጠም፣ ነገር ግን በእራት ግብዣው ላይ የነበሩ እንግዶች የአንድ ሰራተኛ የዓመት ደሞዝ የሚያክልን ሽቶ በኢየሱስ ላይ ማፍሰሷ ከፍተኛ ብክነት ነው ብለው በማሰባቸው በጣም ተረብሸዋል። ነገር ግን ኢየሱስ እርሷን ለመከላከል ጣልቃ በመግባት እርሷ ያደረገችው ነገር መታሰቢያዋ እንዲሆን በወንጌል አዋጅ ውስጥ ይካተታል አለ።

ሊረሳ የማይችል ነገር ነው። በርግጥ አራቱም ወንጌላት ይህንን ታሪክ በአንድ ወይም በሌላ መንገድ ይነግሩናል፣ ምናልባት ለዚህ ምክንያቱ ኢየሱስ የእርሷን ሥራ መታሰቢያ እንዲሆን በማድረጉ ሊሆን ይችላል። የይሁዳ አሳልፎ መስጠትም የማይረሳ ተግባር ነው። ይህን እንዲያደርግ የመራው ነገር ስስት እንደሆነ ማርቆስ በተዘዋዋሪ አመልክቷል። የዮሐንስ ወንጌል ግልጽ ያደርገዋል። (ዮሐንስ 12:4–6)።

በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ ሁለት የተለያዩ ተመላልሰው የሚመጡ ሀሳቦችን፣ ወይም ታሪኮችን ለማብራራት ማርቆስ “መልካም” በሚል ቃል ይጫወታል። ኢየሱስ የሴትዮዋን ድርጊት ማርቆስ 14፡6 ላይ “መልካም/ያማረ” ብሎ ጠርቷል። ድሆች ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ስለሆኑ ለእነርሱ ሁልጊዜ መልካም ማድረግ ትችላላችሁ አለ (ማር. 14፡7)። ስለዚህ ማርቆስ 14፡9 ላይ የእርሷን ድርጊት “የምስራቹ/የወንጌል” አካል እንደሆነ ተናገረ። ማርቆስ 14፡11 ላይ ኢየሱስን አሳልፎ ለመስጠት ይሁዳ “ምቹ ጊዜ” ይፈልግ ነበር። ይህ የቃላት ጨዋታ የሚያሳየን ነገር ቢኖር መሲህን ለማጥፋት ያሴሩት የሰዎች ሴራ እግዚአብሔር ሰብአዊ ዘርን ለማዳን ልጁን በመስጠቱ የእርሱ ፈቃድ ፍሬ እንዲያፈራ ስለሚያደርግ የወንጌል ታሪክ አካል ይሆናል።

ሮሜ 8፡28 እዚህ የሆነውን ነገር ለማብራራት የሚረዳው እንዴት ነው?

ጳጉሜ 4
Sep 09

የመጨረሻው ራት


ማር. 14:22–31ን ያንብቡና ዘጸ. 24:8ን ያብራሩ። በዚህ ዘገባ ውሰጥ ለክርስቲያን እምነት ምን እጅግ ወሳኝ የሆነ ነገር ይገኛል?



ይህ ቀን የፋሲካው በግ የሚታረድበትና ያልቦካ ቂጣ የሚበላበት ቀን መሆኑን ማርቆስ 14:12 ይገልጻል። ምግቡ የሚበላው ሀሙስ ምሽት ነው።

በመጨረሻው ራት ኢየሱስ አዲስ የመታሰቢያ አገልግሎት መሰረተ። ከአይሁዶች የፋሲካ በዓል ወደ ሌላ ሽግግር ስለነበር እሥራኤላውያን ግብጽን ለቀው ከመውጣትና በሲና የእግዚአብሔር የቃል ኪዳን ሕዝብ ከመሆን ጋር በቀጥታ ተገናኝቷል። ዘጸአት 24፡8 ላይ ቃል ኪዳኑን ሲያትም ሙሴ በሕዝቡ ላይ የመስዋዕቱን ደም ከረጨ በኋላ እንዲህ ይል ነበር፡-“በእነዚህ ቃላት ሁሉ መሰረት እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ያደረገው የቃል ኪዳኑ ደም እነሆ አለ።” የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

ኢየሱስ በዚህ ቦታ በሚያቋቁመው የጌታ ራት ላይ በፋሲካው ምግብ ውስጥ በግ ጥቅም ላይ አለመዋሉ የሚያስገርም ነው። ይህ የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ የእግዚአብሔር በግ ስለሆነ ነው (ከዮሐ. 1፡29 ጋር አነጻጽሩ)። የጌታ ራት ህብስት አካሉን ይወክላል። አዲሱ ኪዳን (ከኤር. 31፡31-34 ጋር አነጻጽሩ) በኢየሱስ ደም ስለታተመ ጽዋው የሚወክለው ይህን ነው። ኢየሱስ እንዲህ አለ፣ “ይህ ስለ ብዙዎች የሚፈስ የአዲስ ኪዳን ደሜ ነው” (ማር. 14:24)።

ከዚያ በኋላ፣ በዚህ ሁሉ መካከል፣ ደቀ መዛሙርቱ በሙሉ ትተውት እንደሚሸሹ ተነበየ። እረኛውን ስለሚመታው ሰይፍና ስለ በጎቹ መበተን የሚናገረውን ዘካርያስ 13፡7ን ጠቀሰ። ኢየሱስ እረኛ ሲሆን ደቀ መዛሙርቱ ደግሞ በጎች ናቸው። ይህ አስደንጋጭና ተስፋ የሚያስቆርጥ መልእክት ነው። ነገር ግን ኢየሱስ የትንሣኤውን ትንቢት በመድገም የተስፋ ቃልን ጨመረበት። ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ በፊት ወደ ገሊላ እንደሚሄድ አከለበት። ይህ ትንቢት ማርቆስ 16፡7 ላይ በኢየሱስ መቃብር አጠገብ በነበረው ወጣት ስለሚጠቀስ በዚህ ቦታ ልዩ ክብደት ይኖረዋል።

ነገር ግን ይህ ሁሉ ለደቀ መዛሙርቱ፣ በተለይም ሁሉም ቢክዱህ እኔ አልክድህም ላለው ጴጥሮስ፣ ለመቀበል እጅግ ከባድ ነበር። ቢሆንም ኢየሱስ ጥብቅ የሆነ ንግግሩን በመቀጠል ዶሮ ሁለት ጊዜ ከመጮኹ በፊት ጴጥሮስ ሶስት ጊዜ እንደሚክደው ተነበየ። ትንቢቱ ኢየሱስ በፍርድ ፊት ቀርቦ በሚከሰስበት ስፍራና በጴጥሮስ ክህደት ላይ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። በዚህ ቦታም ወሳኝ ሚና ይጫወታል።

እርስዎ የሆነ ነገር ለማድረግ ወይም ላለማድረግ ለእግዚአብሔር ቃል ከገቡ በኋላ አላደርግም ያሉትን በማድረግና አደርጋለሁ ያሉትን ባለማድረግ ካጠናቀቁዋቸው ጊዜያት ምን መማር ይችላሉ?

ጳጉሜ 5
Sep 10

ጌቴሴማኒ


ማር. 14:32–42ን ያንብቡ። ኢየሱስ በጌቴሴማኒ የጸለየው ለምን ነበር? ጸሎቱ መልስ ያገኘው እንዴት ነበር?





ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ፋሲካን የበሉበትን በግንብ የታጠረችውን ኢየሩሳሌምን ለቀው በመውጣት የቄድሮንን ሸለቆ በማቋረጥ በደብረ ዘይት ተራራ አቀበት ላይ ወዳለው የአትክልት ቦታ መጡ። ጌቴሴማኒ ማለት የዘይት መጭመቂያ ማለት ሲሆን በአካባቢው የወይራ ዘይት የሚጨመቅበት መጭመቂያ መኖሩን ያመለክታል። ሮማውያን በ70 ዓ.ም ኢየሩሳሌምን በከበቡአት ጊዜ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ የነበሩ ዛፎችን በሙሉ ቆርጠው ስለነበር ቦታው በትክክል አይታወቅም።

ኢየሱስ ወደ አትክልት ቦታው ሲገባ ደቀ መዛሙርቱን እዚያው ትቶ ከጴጥሮስ፣ ከያዕቆብና ከዮሐንስ ጋር ጥቂት ራቅ ብሎ ሄደ። ነገር ግን አሁን ሶስቱንም ትቶ ብቻውን ጥቂት ረቅ ብሎ ሄደ። ይህ የሚያሳየው እየመጣ ባለው መከራ ኢየሱስ የበለጠውን እየተነጠለ እና ብቸኛ እየሆነ እየሄደ መሆኑን ነበር።

ኢየሱስ የመከራው ጽዋ እንዲያልፍ ጸለየ፣ ነገር ግን ይህ የሚሆነው የእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ብቻ ነው (ማር. 14፡36)። አባ የሚለውን የአራማይክ ቃል የተጠቀመ ሲሆን ትርጉሙ ‹‹አባት›› ማለት ነው። ቃሉ ብዙዎች እንደሚናገሩት የሥጋ አባትን ለመጥራት የሚጠቀሙት ቃል አይደለም። በአረማይክ ልጅ አባቱን ለመጥራት የሚጠቀመው ቃል አቢ የሚል ነበር። (see Raymond E. Brown, The Death of the Messiah, Anchor Bible Reference Library [New York: Double- day, 1994], vol. 1, pp. 172, 173). ነገር ግን አባ፣ አባት የሚለውን ቃል መጠቀም መጥፋት የሌለበትን ቤተሰባዊ ግንኙነት ይይዛል።

ኢየሱስ ይጸልይ የነበረው የመከራውን ጽዋ እንዲያሳልፍለት ነበር። ነገር ግን ራሱን ለእግዚአብሔር ፈቃድ አሳልፎ ሰጠ (ማቴ. 6፡10 ላይ ካለው የጌታችን ጸሎት ጋር አነጻጽሩ 6:10)። ከቀሪው የመከራው ታሪክ ውስጥ እንደምንረዳው እግዚአብሔር ለኢየሱስ ጸሎት የመለሰው መልስ “አይደለም” የሚል መሆኑ ግልጽ ነው። በዚህ ልምምድ አማካይነት ድነት ለዓለም ስለተሰጠ የመከራ ጽዋውን አያሳልፍለትም።

መከራ ሲገጥምዎ የሚደግፉዎትን ወዳጆችን ማግኘት የሚያበረታታ ነው። ጳውሎስ ፊልጵስዩስ 4፡13 ላይ ኃይልን በሚሰጥ በክርስቶስ ሁሉን እንደሚችል ይናገራል። ሐዋርያው “ሆኖም” ብሎ የሚጀምርበትን ፊልጵስዩስ 4፡14ን ብዙዎች ይረሳሉ። እንዲህ ይነበባል፡- “ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ።” ኢየሱስ በጌተሴማኒ የተመኘው ይህን ነበር። ከደቀ መዛሙርቱ ማጽናኛን እየፈለገ ሶስት ጊዜ መጣ። ሶስቱንም ጊዜ እየተኙ ነበር። በመጨረሻ ፈተናውን ለመጋፈጥ አብረውት እንዲሄዱ ቀሰቀሳቸው። እርሱ ዝግጁ ነበር፤ እነርሱ ግን አልተዘጋጁም ነበር። የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ

መስከረም 1
Sep 11

ከኢየሱስ ለመሸሽ ሁሉን መተው


ማር. 14:43–52ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ ለድነት እቅድ ወሳኝ የሆነ ምን ተከሰተ?



የቅርብ ወዳጆቹ ከሆኑት አንዱ ኢየሱስን ለጠላቶች አሳልፎ መስጠቱ አስደንጋጭ ነው። ይሁዳ ኢየሱስን አሳልፎ እንዲሰጥ ስላነሳሰው ነገር ወንጌላት በዝርዝር አይናገሩም። ነገር ግን ኤለን ጂ ኋይት እንዲህ በማለት ጽፋለች፡- “ይሁዳ በተፈጥሮው ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ፍቅር ነበረው፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ይህንን የመሰለ ተግባር እስከማድረግ የሚመራው የተበላሸ ማንነት አልነበረውም። ገንዘብ ለማግኘት ያለው ጠንካራ ፍላጎት የሕይወቱ ገዥ ሀሳብ እስኪሆን ድረስ ገንዘብን የመውደድ መጥፎ መንፈስ አሳድጓል። የገንዘብ ፍቅር ለክርስቶስ ካለው ፍቅር በለጠበት። ለአንድ የግብረገብ ድክመት ባሪያ በመሆን በኃጢአት እስከፈለገበት ርቀት ድረስ እንዲነዳው ራሱን ለሰይጣን አሳልፎ ሰጠ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 716.

ክህደትን የሚጠቀሙ ሰዎችን ጨምሮ ክህደት በሁሉም የተጠላ ነገር ነው (ማቴ. 27፡3-7)። ነገር ግን የይሁዳ ተግባር በተለየ ሁኔታ የከፋ የሚሆነው የወዳጅነት ጭንብል ለብሶ ክህደቱን ለመደበቅ መፈለጉ ነበር። መያዝ ያለባቸው እርሱ የሚስመውን ሰው እንደሆነ ለሕዝቡ መመሪያ ሰጥቶ ነበር። ይሁዳ አሳልፎ የመስጠት ተግባሩን ከኢየሱስና ከሌሎች ደቀ መዛሙርት ለመደበቅ የፈለገ ይመስላል።

ኢየሱስን በያዙት ጊዜ በሕዝቡ ውስጥ ሕውከት ተፈጠረ። የሆነ ሰው ሰይፉን አንስቶ (ዮሐ. 18፡10 ይህን ያደረገው ጴጥሮስ ነው ይላል) የሊቀ ካህኑን አገልጋይ ጆሮ ቆረጠ። በመቅደስ እያስተማረ ሳለ በቁጣ የመጡ ሰዎችን በግልጽ ለማድረግ የፈለጉትን ነገር በምስጢር ስላደረጉ ገሰጻቸው። ነገር ግን ኢየሱስ ንግግሩን የጨረሰው መጻህፍት እየተፈጸሙ እንደሆነ በመጥቀስ ነው። ይህ በኢየሱስ የመከራ ታሪክ ውስጥ እየታየ ያለ ሌላ ታሪክ ነው። እርሱም የሰው ሥራ መሲሁን ለማጥፋት እየሰራ ሳለ የእግዚአብሔር ፈቃድ እየተፈጸመ ነው።

ኤየሱስን በርቀት እየተከተለ በመጨረሻ ራሱ ችግር ውስጥ የገባውን ጴጥሮስን ጨምሮ ደቀ መዛሙርት በሙሉ ሸሹ። ነገር ግን ማር. 14፡51፣ 52 በዚህ ቦታ ብቻ እንጂ በየትኛውም ሌላ ቦታ የሌለውን ኢየሱስን ስለተከተለ ወጣት ሰው የተነገረውን ታሪክ ይነግረናል። አንዳንድ ሰዎች ይህ ሰው ማርቆስ ራሱ ነው ብለው ያስባሉ፣ ነገር ግን ይህን ማረጋገጥ አይቻልም። አስደናቂ የሆነው ነገር ቢኖር እራቁቱን መሸሹ ነው።

ወጣቱ ሰው ኢየሱስን ‹‹ለመከተል›› ሁሉን ከመተው ይልቅ ከኢየሱስ ‹‹ለመሸሽ›› ሁሉን ተወ።

የአንድ መጥፎ ባህሪይ ባሪያ መሆን ይሁዳ ያደረገውን ነገር እንዲያደርጉ ስለመራበት አስፈሪ ሀሳብ ያስቡ። ይህ ኃጠአትን ስለመጥላትና በእግዚአብሔር ጸጋ ስለማሸነፍ ምን ሊነግረን ይገባል?

መስከረም 2
Sep 12

አንተ ማን ነህ?


ማር. 14:60–72ን ያንብቡ። ጴጥሮስ ካደረገው በተቃራኒ ኢየሱስ ለክስተቶች እንዴት ምላሽ እንደሰጠ ያወዳድሩ። ከልዩነቶቹ ምን ትምህርቶችን መማር እንችላለን?



ማር. 14:53–59 ኢየሱስ ወደ መማክርት ጉባኤ ቀርቦ የክሱ የመጀመሪያው ክፍል ሲካሄድበት ይገልጻል። ድርጊቱ ተስፋ የመቁረጥ ተግባር ነበር። መሪዎቹ በኢየሱስ ላይ የሚያቀርቡት ውንጀላ ተቀባይነት እንዲያገኝ ደጋግመው ሞክረዋል። የወንጌል ጸሐፊው ምስክሮች የተናገሩአቸው ቃሎች እንዴት ውሸት እንደሆኑና እርስ በርሳቸውም በፍጹም የማይስማሙ እንደሆኑ አመልክቷል።

በመጨረሻ ሊቀ ካህኑ በመነሳት ኢየሱስን በቀጥታ አናገረው። በመጀመሪያ ኢየሱስ አልመለሰለትም። ነገር ግን ሊቀ ካህኑ ኢየሱስን በእግዚአብሔር መሃላ ሥር በማድረግ (ማቴ. 26፡63ን ይመልከቱ) አንተ መሲህ ነህን በማለት ቀጥተኛ የሆነ ጥያቄ ጠየቀው። ኢየሱስ በግልጽና ያለ አንዳች ማመንታት መሲህ መሆኑን በመቀበል ዳንኤል 7፡13፣ 14 ላይ የሰው ልጅ በሰማይ ደመና በመምጣት በአባቱ የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ ቀኝ የተቀመጠበትን ጠቀሰ። ይህ ሊቀ ካህኑ ሊታገሰው ከሚችለው በላይ ስለነበር ቀሚሱን በመቅደድ ኢየሱስ እንዲፈረድበት ጥያቄ ያቀረበ ሲሆን መማክርቱም ወዲያውኑ የሊቀ ካህኑን ሀሳብ ተቀበሉ። መሪዎቹ በኢየሱስ ላይ በመትፋት፣ ፊቱን በመሸፈን፣ በመምታትና ትንቢት እንዲናገር በመጠየቅ ማዋረድ ጀመሩ።

ኢየሱስ በውስጥ ሆኖ እየተመረመረ እና ታማኝ ምስክርነት እየሰጠ ሳለ ጴጥሮስ በውጭ ሆኖ የሀሰት ምስክርነት እየሰጠ ነበር። ይህ በማርቆስ መጽሐፍ ውስጥ ያለ ስድስተኛውና የመጨረሻው በአንድ ታሪክ መካከል የገባ ታሪክ ስለሆነ ምጸቱ በተለየ ሁኔታ የተመለከተ ነው። በዚህ ቦታ ተቃራኒ ተግባሮችን የሚያከናውኑ ሁለት ትይዩ ገጸ-ባህሪያት፣ ኢየሱስና ጴጥሮስ፣ አሉ። ኢየሱስ እውነተኛ ምስክርነት ሲሰጥ ጴጥሮስ የውሸት ምስክርነት ይሰጣል። ጴጥሮስን አንዲት አገልጋይ ወይም በዚያ የቆሙ ሰዎች ሶስት ጊዜ ያናገሩት ሲሆን በእያንዳንዱ ሰዓት ከኢየሱስ ጋር ግንኙነት እንደሌለው እየተራገመ በመሃላ ካደ።

ዶሮ ለሁለተኛ ጊዜ የጮኸው በዚህ ጊዜ ሲሆን ጴጥሮስ በዚያ ሌሊት ሶስት ጊዜ እንደሚክደው ጌታው የተነበየውን ትንቢት አስታወሰ። ልቡ ተነካና አለቀሰ።

አስገራሚ ምጸት ያለው ከዚህ ላይ ነው፤ ኢየሱስ በፍርድ ፊት ቀርቦ ከተመረመረ በኋላ ፊቱን ሸፍነው በመምታት ትንቢት እንዲናገር አዘዙት። ሀሳባቸው ማን እንደመታው ስለማያይ ሊቀልዱበት ነበር። ነገር ግን ይህን እያደረጉ በነበሩበት በዚያው ሰዓት ጴጥሮስ ከኢየሱስ ትንቢቶች አንዱን በመፈጸም በግቢው ውስጥ ኢየሱስን እየካደ ነበር።

ከዚህ የተነሣ፣ ጴጥሮስ ኢየሱስን በመካድ፣ እርሱ መሲህ መሆኑን እያሳየ ነበር።

ኢየሱስን ለመከተል እየፈለገ አንዳንድ ጊዜ እንደዚያ ማድረግ ለማይችል ሰው እርስዎ ምን የተስፋ ቃላት መስጠት ይችላሉ? አንዳንድ ጊዜ ኢየሱስ እንድናደርግ እንደሚፈልግ የምናውቀውን ነገር ለመከተል ያላቃተው ከእኛ መካከል ማን ነው?

መስከረም 3
Sep 13


ተጨማሪ ሀሳብ


ኤለን ጂ ኋይት የዘመናት ምኞት በሚለው መጽሐፏ ገጽ 698-722 ላይ “በአናንያና ቀያፋ ፍርድ ፊት” እና “ይሁዳ” የሚሉ ክፍሎችን ያንብቡ።

“አዋራጅ መሃላዎች በጴጥሮስ ከናፍር ገና ትኩስ እንዳሉ እና የዶሮ ጩኸት ጆሮው ላይ ገና እያስተጋባ ሳለ አዳኙ ከተኮሳተሩ ዳኞች ፊቱን ዘወር በማድረግ ምስኪኑን ደቀ መዝሙር ፊት ለፊት ተመለከተው። በተመሳሳይ ጊዜ የጴጥሮስ ዓይኖች ወደ ጌታው ተስበው ነበር። በዚያ ጨዋ በሆነ ፊት ላይ ጥልቅ የሆነ ጸጸትንና ሀዘንን ተመለከተ፣ ነገር ግን በዚያ ቁጣ አልነበረም።

“ያንን የገረጣና ስቃይ ያለበትን ፊት መመልከት፣ እነዚያን የሚንቀጠቀጡ ከንፈሮችን እና የርኅራኄና የይቅርታ እይታን መመልከት ልቡን እንደ ቀስት ወጋው።

ከጥቂት ሰዓታት በፊት ከጌታው ጋር ወደ ወህኒም ሆነ ወደ ሞት ለመሄድ የገባውን ቃል ጴጥሮስ አስታወሰ። በዚያን ሌሊት ጌታውን ሶስት ጊዜ እንደሚክደው አዳኙ በላይኛው ክፍል ሲነግረው የነበረውን በሀዘኔታ አስታወሰ። ጴጥሮስ ኢየሱስን እንደማያውቅ ተናግሯል፣ ነገር ግን ጌታው እንዴት አሳምሮ እንደሚያውቀውና ውሸታምነቱ ለራሱ እንኳን የማይታወቀውን ልቡን እንዴት በትክክል እንዳነበበ አሁን መራር በሆነ ሀዘን ተገነዘበ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, pp. 712, 713. የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ማርቆስ 14፡9 ላይ ኢየሱስ የተነበየውን ትንቢት ዝም ብሎ በማንበብ ብቻ- -ትንቢቱ የተነገረበትን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ስናስገባ ተፈጻሚ የመሆን ዕድሉ እጅግ አነስተኛ ሆኖ ሳለ-- ሌሎች የኢየሱስ ትንበያዎች ሲፈጸሙ እየተመለከትን ያለነው እንዴት ነው?

2. ይሁዳንና ጴጥሮስ አነጻጽሩና አወዳድሩ። በኢየሱስ ስቃይ ታሪክ ላይ በተጫወቱት ሚና የሚመሳሰሉትና የሚለያዩት እንዴት ነው?

3. በጌታ ራት ትርጉም ላይ ተወያዩ። ይህንን በቤተ ክርስቲያናችን የበለጠ ትርጉም ያለው ማድረግ የምንችለውና በበዓሉ ላይ ብዙ አባላትን ማሳተፍ የምንችለው እንዴት ነው?

4. ኢየሱስ በጌተሴማኔ ለጸለየው ጸሎት እግዚአብሔር ‹‹አይሆንም›› ብሎ በመለሰበት እውነታ ላይ ተወያዩ። እግዚአብሔር ለእኛም ‹‹አይሆንም›› ሲል ምን ማለት ነው?

5. ጴጥሮስ በመካዱ ኢየሱስን እጅግ ቢያሳዝነውም ኢየሱስ ግን አልጣለውም። ከዚህ እውነታ ለራስዎ ምን ተስፋ መውሰድ ይችላሉ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL