የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ማር. 12:41–44፣ ማር.
13:1–32፣ ዳን. 9:24–27፣ ዳን. 7:25፣ 1ኛ ተሰ. 4:13–18ን ያንብቡ።
የመታሰቢያ ጥቅስ: “በዚያን ጊዜም የሰው ልጅ በብዙ ኃይልና
ክብር በደመና ሲመጣ ያዩታል። በዚያን ጊዜም መላእክትን
ይልካል ከአራቱ ነፋሳትም ከምድር ዳርቻ እስከ ሰማይ ዳርቻ
የተመረጡትን ይሰበስባቸዋል።” (ማር. 13:26, 27)።
የዚህ ሳምንት ትምህርት የሚጀምረው ባልቴቷ ስላደረገችው ነገር ኢየሱስ
ጥልቅ የሆነ ንግግር ባደረገበት ማርቆስ ምዕራፍ 12 ላይ ባለው በጣም
አጭር የሆነ ታሪክ ነው። ነገር ግን የዚህ ሳምንት ትምህርት ዋናው ክፍል
የሚመለከተው ስለ ኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ዕጣ ፋንታና ከዚያም ለሚበልጥ
ነገር ስለ ተነገረው አስደናቂ ትንቢት ነው። ይህ ምዕራፍ ከማቴዎስ ምዕራፍ 24
እና ሉቃስ ምዕራፍ 21 ጋር ስለ ኢየሩሳሌም መውደቅና ከዚያም ባሻገር እስከ
ዓለም ፍጻሜ ስላለው ነገር ይናገራል። ማርቆስ ምዕራፍ 13 ግልጽ የሚያደርገው
ነገር ቢኖር ትንቢቱ ከነቢዩ፣ ከኢየሱስ ጊዜ አንስቶ እስከ ፍጻሜ ዘመን፣ እስከ
ዳግም ምጻቱ ድረስ እንደሚሄድ ነው። ይህ አቀማመጥ እነዚህን ትንቢቶች ከዚህ
በፊት እንደተፈጸሙ ወይም ገና ወደ ፊት ከረዥም ዘመናት በኋላ እንደሚፈጸሙ
አድርገው ከሚተረጉሙት በተቃራኒ “ታሪክን መሰረት በማድረግ የፍጻሜ ዘመን
ትንቢትን የሚተረጉሙ ሰዎችን” መንገድ ይከተላል።
በማርቆስ ውስጥ እንዳሉ ብዙ የኢየሱስ ትምህርቶች ጌታ የሰጠው መመሪያ
ለደቀ መዛሙርቱ ጥያቄ ወይም የተሳሳተ መረዳት ምላሽ ነበር። እነዚህ ጥያቄዎች
ወይም የመረዳት ስህተቶች ኢየሱስ ለክርስቲያን ሕይወትና ልምምድ ወሳኝ የሆኑ
እውነቶችን ለማስተማር ዕድል ይሰጡታል። ኢየሱስ ወደ ፊት ስለሚሆነው
ነገር የሚተነብይ ብቻ ሳይሆን ደቀ መዛሙርቱ ሊመጡ ስላሉ ፈተናዎች እንዴት
እንደሚዘጋጁ ያኔ እና አሁንም ያስተምራል።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለጳጉሜ 2 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ
የተጣሉ ሁለት ሳንቲሞች ማር. 12:41–44ን ያንብቡ። መበለቷ የሰጠችው ምን ያህል ነበር? ስለዚያ ስጦታ ኢየሱስ ምን አለ?
የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ አስደናቂ የሆነ ውበት የነበረው ሕንጻ ነበር።
ቤተ መቅደሱ የነበረበት ተራራ በከተማው ጎልቶ የሚታይ ሲሆን በሕንጻው
ግንባታ ላይ ጥቅም ላይ የዋሉ ግዙፍ ድንጋዮች፣ አንዳንዶቹ በመቶዎች የሚቆጠሩ
ቶኖችን የሚመዝን ክብደት የነበራቸው፣ የዘመኑ ድንቅ ነበሩ። ቤተ መቅደሱን
ቅርጽ የማስያዝና የማስፋፋት ሥራ እና የቤተ መቅደስ ተራራው ሥራ የጀመረው
ከክርስቶስ ልደት በፊት በ20 ዓ.ዓ አከባቢ በታላቁ ሄሮድስ ዘመነ መንግሥት
ሲሆን ሕንጻውን የመገንባትና የማስዋብ ሥራ ከክርስቶስ ልደት በኋላ እስከ
ስልሳዎቹ ቀጥሎ ነበር።
ብዙ ሰዎች በቤተ መቅደስ አጠገብ በነበረው በሴቶች አደባባይ በተቀመጡ
13 ሳጥኖች ውስጥ ለማስገባት ትላልቅ ስጦታዎችን ያመጡ ነበር። አንዲት መበለት
ሁለት የነሃስ ሳንቲሞችን ስትጥል ኢየሱስ ቁጭ ብሎ የተመለከተው እዚህ ነበር። እሷ
የጣለችው ገንዘብ ለቀን ሰራተኛ የተለመደ ደሞዝ የነበረው የአንድ ዲናር 1/32ኛው
ያህል ነበር። ከዚህ የምንረዳው መበለቷ የሰጠችው ገንዘብ በጣም ትንሽ ነው።
ነገር ግን ኢየሱስ በዚህች ሴት ስጦታ ተደምሟል። ብዙ ሀብታም
ግለሰቦች በመሰብሰቢያ ሳጥኑ ውስጥ ብዙ ገንዘብ ይጨምሩ ነበር፣ ነገር ግን
እነርሱ ስለሰጡት ገንዘብ አስተያየት አልሰጠም። ነገር ግን የዚህች መበለት ስጦታ
ከእርሱ ምሥጋናን አትርፎላታል። ከሁሉ አብልጣ ሰጠች አለ። ይህ እንዴት ሊሆን
ይችላል? ኢየሱስ የተገነዘበው ነገር ቢኖር እነርሱ ከትርፋቸው ሲሰጡ እርሷ ግን
ከድህነቷ መስጠቷን ነበር። እነርሱ ብዙ ለራሳቸው የቀረ ገንዘብ ነበራቸው፤ እርሷ
ግን ለኑሮዋ ያላትን በሙሉ ሰጠች። እርሷ የሰጠችው ገንዘብ በገንዘብነቱ ጥቂት
ቢሆንም እንኳን ይህ እውነታ ስጦታዋን እጅግ ውድ (ከመጠን ያለፈ) ያደርገዋል።
ይህ ታሪክ ስለ ግብዓቶች አያያዝ ጥልቅ ትምህርት ይዟል። ለእግዚአብሔር ሥራ
መስጠት ማረጋገጫ እንዲኖረው በመሪዎች እርምጃ አይደገፍም። የቤተ መቅደሱ
ኃይማኖታዊ አመራር ብልሹ ነበር፣ ነገር ግን ከዚህ የተነሳ ስጦታዎችን መከልከልን
ኢየሱስ አላረጋገጠም። በሙስና የተዘፈቁ የኃይማኖት መሪዎች (ቀያፋ? አናኒያ?)
ከዚህ በፊት የነበሩ ቢሆንም በዚህ ወቅት የነበሩት እጅግ ከከፉት መካከል ነበሩ።
ኢየሱስም ይህን አውቆ ነበር።
መሪዎች ግብዓቶችን እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የመጠቀም ቅዱስ
ሀላፊነት ያለባቸው መሆኑ እውነት ቢሆንም፣ ይህን ባያደርጉም እንኳን፣ እንደዚህች
ሴት ለእግዚአብሔር ሥራ የሚሰጡ ሰዎች አሁንም በመስጠታቸው ተባርከዋል።
በሌላ በኩል መሪዎች የሆነ የሚያስቀይም ነገር ሲያደርጉ አሥራትንና
ስጦታን አለመመለስ ማለት እግዚአብሔርን በማመስገን በመስጠት ፋንታ
ከእነርሱ ተግባር ጋር ተገናኘ ማለት ነው። ሁኔታው ይህንን ለማድረግ የሚፈትን
ቢሆንም ስህተት ነው።
ለእግዚአብሔር ሥራ በምንሰጠው ነገር ታማኝ ስለመሆን አስፈላጊነት ይህ ታሪክ ምን
ሊያስተምረን ይገባል?
ማር 13:1–13ን ያንብቡ። ደቀ መዛሙርቱ ስለ ቤተ መቅደሱ ስለተናገሩት ነገር ኢየሱስ መልስ የሰጠው እንዴት ነበር? ኢየሱስ ለእነርሱ የሰጠው መልስ ያለው ጠቀሜታ ምንድር ነው?
አስቀድመን እንደተመለከትነው የቤተ መቅደሱ ህንጻ በእውነት
የሚያስደንቅ ነበር። በሕንጻው በስተ ደቡብ መግቢያ በኩል ያሉ ጣሪያ ደጋፊ
ባለግርማ ሞሶሶዎች ቁጥራቸው 162 መሆኑን ጆሴፋስ የተባለ ጸሐፊ የገለጸ ሲሆን
እያንዳንዱ ምሶሶ ሶስት ሰዎች እጅ ለእጅ ተጨባብጠው ዙሪያውን መሸፈን
አይችሉም ነበር (Antiquities, 15.11.5 §§413– 414)። ኢየሱስ ይህ ይፈርሳል
አለ። ስለዚህ አስደናቂ ሕንጻ የተነገረው የዚህ ዓይነት ትንቢት ለአድማጩ ኢየሱስ
እየተናገረ ያለው ስለ ፍጻሜ ዘመን እንደሆነ እንዲሰማው ያደርጋል።
የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ
“የክርስቶስ ትኩረት ወደ ቤተ መቅደሱ ውበት ተስቦ ሳለ እነዚያ
ተቀባይነት ያጡት በቃላት ያልተገለጹ ሀሳቦች ምን ይሆኑ ይሆን! እያየው የነበረው
ነገር በርግጥም ውብ ነበር፣ ነገር ግን በሀዘኔታ ምንም ነገር አያስደንቀኝም
አለ። ሕንጻዎቹ በርግጥ አስደናቂ ናቸው። ወደ እነዚህ ግንቦች የምታመለክቱት
እንደማይፈርሱ አድርጋችሁ ነው፤ ነገር ግን ቃላቶቼን አድምጡ፡- ‘ድንጋይ
በድንጋይ ላይ ሳይፈርስ የማይቀርበት’ ቀን ይመጣል።”—Ellen G. White, The
Desire of Ages, p. 627. ደቀ መዛሙርቱ ይህ የኢየሱስ ትንቢት መቼ ተፈጻሚ
እንደሚሆን ማወቅ ይፈልጋሉ። በመሆኑም ማርቆስ 13፡4 ላይ ጴጥሮስ፣ ያዕቆብ፣
ዮሐንስና እንድሪያስ የነበሩበት ትንሽ ቡድን ስለ ጊዜው ጠየቁት። እነዚህ ነገሮች
ሁሉ መቼ እንደሚሆኑና ሊሆኑ ያሉበትን ጊዜ የሚያመለክቱ ምልክቶች ምን
እንደሚሆኑ ማወቅ ፈለጉ።
ማርቆስ 13፡5-13 ውስጥ የሚያስደንቀው ነገር ቢኖር ኢየሱስ አብዛኛውን
ጊዜውን ያሳለፈው ለደቀ መዛሙርቱ የኢየሩሳሌምን መውደቅ እየገለጸ ሳይሆን
የቀደምት ቤተ ክርስቲያንን በመመስረት አገልግሎታቸው ይሆናል ብለው መጠበቅ
ስለሚችሉት ነገር እያስጠነቀቃቸው ነበር። ቀላል የሚሆን አይመስልም ነበር።
በርግጥ ይሰደዳሉ፣ ይወነጀላሉ፣ አንዳንዶችም ይገደላሉ። ነገር ግን በዚህ
ሁሉ ውስጥ ጊዜው ገና እንደሆነ ነገራቸው። ህውከት በበዛባቸው ክስተቶች
መታለል የለባቸውም። ከዚህ በተጨማሪ ቤተሰብና ወዳጆች በተዉአቸው ጊዜ
እንኳን መንፈስ ቅዱስ የሚናገሩአቸውን ቃላት ይሰጣቸዋል።
በኢየሱስ ትንቢት ውስጥ ካሉ ከእነዚህ የመግቢያ ቃላት የሚወሰደው ፍሬ
ነገር የእግዚአብሔር ሕዝብ ህውከትንና ውንጀላን መፍራት እንደሌለባቸው ነው።
የእግዚአብሔር መንፈስ በችግር (መከራ) ውስጥ ስለሚያሻግራቸው መንቃት
አለባቸው።
ኢየሱስን ከመከተልዎ የተነሳ ስለሚመጡ ፈተናዎች የእርስዎ ልምምድ ምን ነበር?
ፈተና ገጥሞዎት የማያውቅ ከሆነ እርሱን በትክክል እየተከተሉ ስለመሆንዎ መጠየቅ
ይኖርብዎት ይሆን?
ማር. 13:14–18ን ያንብቡ። “የጥፋት እርኩሰት” ምንን እንደሚመለከት እንዲለዩ ኢየሱስ ምን ፍንጭ ሰጣቸው?
ማርቆስ 13፡14 ላይ ኢየሱስ ስለ ኢየሩሳሌም መፍረስ ማዕከላዊ ወደሆነው
ነጥብ መጣ። “የጥፋት እርኩሰትን” ጠቀሰ። ጌታ አንባቢው ያስተውል አለ።
በእነዚህ ቃላት ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ ወደ ዳንኤል መጽሐፍ እያመለከተ ነው።
ይህ አገላለጽ ዳንኤል 9፡27፤ 11፡31፤ እና 12፡11 ከዳንኤል 8፡13 ጋር በንጽጽር ይታያል።
ዳንኤል 9:26፣ 27ን ያንብቡ። “የተቀባው” ማን ነው? “ሊመጣ ያለው ልዑልስ
ማን ነው?”
ዳንኤል 9፡26 ላይ “የተቀባው” የሚለው ቃል በዕብራይስጥ መሲህ
የሚል ሲሆን በአማርኛም መሲህ ተብሏል። ዳንኤል 9፡24-27ን በጥንቃቄ ስናጠና
ቃሉ የሚያመለክተው የኢየሱስ ክርስቶስን መምጣት ነው።
ነገር ግን የኢየሩሳሌም ከተማን ጥፋት የሚያመጣው “የሚመጣው
ልዑል” ማን ነው? ከተማዋ የሮም ጀነራል በነበረው በታይተስ ወድማለች።
ስለዚህ በዳንኤል 9፡26፣27 ላይ የተጠቀሰው “የሚመጣው ልዑል” እርሱ ነው
መባሉ ምክንያታዊ ይመስላል። ሁለቱ ግለሰቦች የተገናኙበት ምክንያት መሲሁን
የያዙበት መንገድ የከተማዋን ጥፋት ከማምጣቱ የተነሳ ነው።
ኢየሱስ ዳንኤልን በመጥቀስ እየተናገረ ያለው ይህ “የጥፋት እርኩሰት”
ምንድር ነው? እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ ምሁራን ይህ እርኩሰት አንቲዮከስ
ኤፕፋነስ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ2ኛው ምዕተ ዓመት ቤተ መቅደሱን እንዳረከሰ
የሚያመለክት ነው በማለት ያምናሉ። ነገር ግን ይህ አባባል አይሰራም። ኢየሱስ
“የጥፋት እርኩሰት” እርሱ እዚህ ከነበረበት ጊዜ በኋላ የሚመጣ እንደሆነ
የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ
ይገልጻል። ስለዚህ ኢየሱስ በምድር ላይ ካገለገለበት ከሁለት መቶ ዓመታት በፊት
የነበረውን ነገር ሊያመለክት አይችልም።
ከዚህ ይልቅ እርኩሰት ከ60ዎቹ መጨረሻ አከባቢ ኢየሩሳሌም በሮም
በተከበበች ጊዜ የሮም አረመኔያዊ መስፈርቶችን በእሥራኤል መትከልን
ሊያመለክት ይችላል። ይህ ክርስቲያኖች እንዲሸሹ ምልክት የነበረ ሲሆን በዚህ
መሰረት ከኢየሩሳሌም ሸሽተው ነበር።
ኢየሱስ እንደተነበየው ኢየሩሳሌም ወደቀች። በትንበያዎቹ ሁሉ እርሱን እና መጽሐፍ
ቅዱስን ማመንን መማር የምንችለው እንዴት ነው?
ማር. 13:19ን ያንብቡ። ይህ ጥቅስ የሚያመለክተው ምንድር ነው?
የጥፋት እርኩሰትን በተመለከተ ማርቆስ 13:14 ምዕራፉ የሚሽከረከርበት
አማካይ ቦታ ነው (የማክሰኞ ትምህርትን ይመልከቱ)። ማርቆስ 13:19 የመሸጋገሪያ
ነጥብ ሆኖ ያገለግላል። ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ሆኖ የማያውቅ ታላቅ የመከራ
ጊዜን ይጠቅሳል። ይህ በኢየሩሳሌም መፍረስ ጊዜ ከተከሰተው የሚበልጥና ሰፊ
ስደትን አስቀድሞ ያሳውቃል። ማርቆስ 13፡19 ወደ መጪ ጊዜ በመቀየር ከኢየሱስ
ጊዜ ገና እጅግ ርቀው ወዳሉ ነገሮች ይጠቁማል።
ማርቆስ 13፡14 የዳንኤል ምዕራፍ 9ን ትንቢት እንደሚያስተጋባ ሁሉ ማርቆስ
13፡19-23 ላይ የተገለጸው ታላቁ ስደት የትንሹ ቀንድ ኃይል የእግዚአብሔርን
ሕዝብ ‹‹ለዘመን፣ ለዘመናትና ለእኩሌታ ዘመን›› ያሳደደበትን የዳንኤል 7 እና
8 ትንቢቶችን ያስተጋባል (ዳንኤል 7፡25)። ይህ የ1260 ትንቢታዊ ቀናት ወቅት
1260 ዓመታትን ይወክላል (ዘሁ.14፡34፣ ሕዝ. 4፡6)። ይህ ጊዜ ከ538 ዓ.ም እስከ
1798 ዓ.ም ይደርሳል። ናፖሊዮን በ1798 ዓ.ም ጳጳሱን እንዲማርክ ጀኔራሉን
ላከው። በእነዚህ የ1260 ዓመታት ወቅት ትንሹ ቀንድ በእርሱ የቤተ ክርስቲያን
አስተዳደራዊ ሥርዓት ጋር ያልተስማሙትን አሳድዶአል፣ ገድሎአልም።
ማር. 13:20–23ን ያንብቡ። እግዚአብሔር በስደት ጊዜ ለሕዝቡ የሚሰጠው
ተስፋ ምንድር ነው? ስደቱ ሲዘጋስ ምን ማስጠንቀቂያ ይሰጣቸዋል?
ስደቱ ለእግዚአብሔር ሕዝብ ሲባል እንደሚያጥር ማርቆስ 13:20
ይናገራል። ከታሪክ እንደምንረዳው ከፕሮቴስታንት ተሃድሶ መነሳት በኋላ
የስደት እሳት በመቀነሱ የጭንቀት ጊዜውንም አሳጥሯል። የትንሹ ቀንድ ኃይል
ሲቀንስ ብዙ ሰዎች ተሃድሶውን ተቀላቀሉ። ነገር ግን የራዕይ ምዕራፍ 13 ትንቢት
እንደሚያመለክተው የትንሹ ቀንድ ኃይል እንደገና ሥልጣኑ ይጨምራል።
ማርቆስ 13:21–23 ላይ ስለ ሌላ ስጋት፣ እርሱ ከመመለሱ በፊት ስለሚነሱ
ሀሰተኛ ነቢያትና ክርስቶሶች አስጠንቅቋል። ከእነዚህ እንዲጠበቁ ኢየሱስ
ተከታዮቹን ያስጠነቅቃል።
ክርስቶስ ስለ ሀሰተኛ ክርስቶሶች ባስጠነቀቀበት ጊዜ የእርሱ እንቅስቃሴ ገና ያልተጀመረ
ቢሆንም ኋላ እውነተኛነቱ የተረጋገጠውን አስደናቂ የሆነ ትንቢት መናገር ችሎ ነበር
(ዛሬ እንኳን ሰዎች ኢየሱስ ነን እያሉ ናቸው)። ይህ ትንቢት በእግዚአብሔር ቃል
ላይ ያለንን መታመን መጨመር ያለበት እንዴት ነው?
ማር. 13:24–32ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ የተገለጸው ትልቅ ክስተት ምንድር ነው?
የፀሐይ፣ የጨረቃና የክዋክብት ምልክቶችን ተከትሎ የሚመጣው
የኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ምጻት ነው። አዲስ ኪዳን ወደዚህ አስደናቂ ክስተት
በሚያመለክቱ ትንቢቶች የተሞላ ነው። ሐዋርያው ጳውሎስ በክርስቶስ ያንቀላፉት
ክርስቶስን በአየር ለመገናኘት በመነሳት ከሕያዋን ጋር የሚነጠቁበትን በገለጸበት
በ1ኛ ተሰሎንቄ 4፡13-18 ላይ ይህን ጉዳይ በዝርዝር ይገልጻል። በ1ኛ ቆሮንቶስ
ምዕራፍ 15 ላይ በክርስቶስ መመለስ ስለሚፈጸመው የሙታን ትንሣኤ እውነታ
የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ
በዝርዝር ይናገራል።
ጴጥሮስ በ2ኛ ጴጥሮስ 3፡3-13 ላይ ጌታ ስለ ተስፋ ቃሉ እንደማይዘገይ
ነገር ግን ሁሉም ወደ ንስሃ እንዲመጡ እንደሚፈልግ በማብራራት ያንን ታላቅ
ቀን ይገልጻል። የራዕይ መጽሐፍ ደግሞ ስለ ክርስቶስ መመለስ ግልጽ የሆኑ
መግለጫዎችን ይሰጣል (ራዕይ 1፡7፤ 6፡12-17፤ 14፡14-20፤ እና 19፡11-21ን
ይመልከቱ)። ተለዋዋጭ ያልሆነው የአዲስ ኪዳን አስተምህሮ የሚገልጸው
የክርስቶስ ዳግም ምጻት በአካል የሚገለጽ፣ እውን፣ የሚታይና የሚሰማ እንደሆነ
ነው። እርሱ ሲመጣ ሁሉም ያየዋል።
ታዲያ ኢየሱስ “ይህ ትውልድ” እና “ያን ቀን” ወይም “ያቺን ሰዓት” ሲል
ምን ማለቱ ነው? ኢየሱስ ይህንን ሀሳብ የተናገረለት ትውልድ ከብዙ ዓመታት
በፊት ስለሞተ እነዚህ ቃላት ብዙ ሰዎችን ግራ አጋብተዋል።
ለዚህ ንባብ በርካታ የመፍትሄ ሀሳቦች ተሰጥተዋል። አንዳንዶች
‹‹ትውልድ›› የሚለው ቃል የሚያመለክተው የሰው ዘርን፣ በዚህ አጋጣሚ
አይሁዶችን ነው ብለው ይከራከራሉ። ይህ ማለት ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት
የአይሁድ ዘር አይጠፋም እንደማለት ነው። ሌላኛው እንደ መፍትሄ የቀረበው
ሀሳብ ይህ ክፍል የሚናገረው ክርስቶስ ከመመለሱ በፊት ስለማይሞትና ሁሉም
ምልክቶች ሲፈጸሙ ስለሚመለከት ትውልድ ነው የሚል ነው።
ነገር ግን ቀላሉ መፍትሄ ማርቆስ 13፡30 ላይ ‹‹ይህ›› የሚለውን ቃል ‹‹ይህ
ትውልድ›› ለሚለው መጠቀሙን እና በማርቆስ 13፡32 ላይ ‹‹ስለዚያች›› የሚለውን
ቃል ‹‹ስለዚያች ቀንና ሰዓት›› ለሚለው መጠቀሙን ልብ ማለት ነው። ማርቆስ 13
ላይ ‹‹ይህ›› የሚለው ቃል (houtos, hautē, touto) እስከ ኢየሩሳሌም ጥፋት
ድረስ በመምራት ከቁጥር 1-13 በብዛት ቀርቧል። ቃሉ የምዕራፉን የኋለኛውን
ክፍል የሚገልጽ ነው።
ስለዚህ “ይህ ትውልድ” የሚለው ቃል ማርቆስ 13፡30 እንደሚገልጸው
በ1ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረውንና የኢየሩሳሌምን ጥፋት ያየውን ትውልድ
የሚመለከት ሊሆን ይችላል። ነገር ግን ማርቆስ 13፡32 ወደ ፊት ሊሆን ያለውንና
ከ1ኛው መቶ ክፍለ ዘመን እጅግ ርቆ ያለውን ዳግም ምጻትን ያመለክታል። ከዚህ
የተነሳ ማርቆስ 13፡32 ከመጀመሪያው ምዕተ ዓመት እጅግ ርቀው ስላሉ ክስተቶች
ለመናገር ‹‹ያቺን›› የሚለውን ቃል ይጠቀማል።
ኤለን ጂ ኋይት ከጻፈችው የዘመናት ምኞት ከሚለው መጽሐፏ
“በደብረ ዘይት ተራራ ላይ” የሚለውን ርዕስ ገጽ 627-636 ላይ ያንብቡ።
በዓለም ላይ እጅግ የሚረብሹ ብዙ ነገሮች እየተከሰቱ ናቸው። እንደ
እውነቱ ከሆነ እየሆነ ያለው ነገር ሰዎችን በፍርሃት ቆፈን እንዲያዙ አድርጎአቸዋል።
እኛ፣ እንደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስትነታችን፣ በክስተቶች ላይ ‹‹የተለየ አቋም›› ያለን
እንደመሆናችን በኢየሱስ ወዳለን ተስፋና ወደ ምጻቱ ተስፋ ሰዎችን ለማመልከት
እነዚህን ነገሮች መጠቀም የምንችለው እንዴት ነው?
“የመምጫውን ትክክለኛ ጊዜ ስለማናውቅ ነቅተን እንድንጠብቅ
ታዘናል። ‘ጌታቸው በመጣ ጊዜ ሲተጉ የሚያገኛቸው እነዚያ ባሪያዎች ብፁዓን
ናቸው።’ ሉቃስ 12:37። የጌታን መምጣት ተግተው የሚጠብቁ ሥራ ፈትተው
አይጠብቁም። የክርስቶስን መምጣት መጠበቅ ሰዎች እግዚአብሔርን እንዲፈሩና
በኃጢአት ላይ የሚያመጣውን ፍርድ እንዲፈሩ ሊያደርጋቸው ይገባል። የእርሱን
የምህረት ስጦታ ያለመቀበል ታላቅ ኃጢአት ስለሚያስከትለው ነገር እንዲነቁ
ሊያደርጋቸው ይገባል። ጌታን ተግተው የሚጠብቁ ሰዎች ለእውነት በመታዘዝ
ነፍሳቸውን እያነጹ ናቸው። ነቅቶ ከመጠበቅ ጋር ተግቶ መስራትን ያጣምራሉ።
ጌታ በደጅ እንደሆነ ስለሚያውቁ ለነፍሳት ድነት ለመስራት ከመለኮታዊ
ወኪሎች ጋር ለመተባበር ቅንዓታቸው ተነሳስቷል። እነዚህ ለጌታው ቤተሰብ
ምግባቸውን በወቅቱ የሚሰጡ ታማኝና ጠቢብ ባሪያዎች ናቸው። ሉቃስ 12:42።
ለወቅቱ በተለየ ሁኔታ ገጣሚ የሆነ እውነትን እያወጁ ናቸው። ሄኖክ፣ ኖህ፣ አብርሃምና
ሙሴ እያንዳንዳቸው ለዘመናቸው ገጣሚ የሆነ የወቅቱን እውነት እንዳወጁ ሁሉ
አሁን የክርስቶስ ባሪያዎችም እነርሱ ላሉበት ትውልድ የሚሆን የተለየ ማስጠንቀቂያ
ይሰጣሉ።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 634.
የጎልማሶች ሰንበት ትህርት የማርቆስ መጽሐፍ
1. ለእግዚአብሔር ሥራ የሚያስፈልግ ነገርን መስጠት አንድ ነገር ነው።
በመስዋዕትነት መንፈስ መስጠት ደግሞ ሌላ ነገር ነው። ልዩነቱ ምንድር ነው? ያ
ልዩነት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?
2. እግዚአብሔር በዘመናት ውስጥ እና በዛሬው ዓለም ስደትን ያልከለከለው
ለምንድር ነው? ስደት ለምን እንደሚኖር እንድንረዳ የታላቁ ተጋድሎ ዋና ሀሳብ
የሚረዳን እንዴት ነው?
3. በዛሬው ዓለም ለእርስዎ በተለየ ሁኔታ ጎልተው የሚታዩት ምን የክርስቶስ መምጫ
ምልክቶች ናቸው?
4. ስለ ሙታን ሁኔታ እና ሙታን ክርስቶስ እስኪመለስ ድረስ አንቀላፍተው
ስለሚቆዩበት ሁኔታ ያስቡ። ሰዎች በሞት ዓይኖቻቸውን ይጨፍናሉ፤ ከዚያ ቀጥለው
የሚያውቁት ነገር ምንድር ነው? ይህ ሀሳብ ለእያንዳንዱ ሰው በግል የክርስቶስ
መምጣት ሁልጊዜ እጅግ ቅርብ መሆኑን እንድናይ የሚረዳው እንዴት ነው?