የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 14:6– 12; መክ. 12:13, 14; ምሣ. 28:9; ዳን. 7:25.
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት
ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው።” (ራእ. 12፡17)።
የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ጥልቅ የሆነ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት በማድረግ ሕጉ
በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን ስፍራ ውስጥ ያለውን ትርጉም መረዳት
ቻሉ። በተጨማሪ ወደ አምላካዊው ሕግ አስኳል በመመልከት የአራተኛውን ሕግ
ማለትም የሰንበትን አስፈላጊነት አስተዋሉ። እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የእውነተኛው አምልኮ
መሠረት የሆነው ይህ ትእዛዝ ከየትኞቹም በላይ እግዚአብሔር ፈጣሪያችን መሆኑን በግልጽ
ያሳያል። ይህ ርዕሰ ጉዳይ በተለይ ከምድር ታሪክ የመጨረሻ ቀናት ክስተቶች ጋር አግባብ
ያለው ግንኙነት ይኖረዋል (ራዕ. 14፡6–12)።
ከመጀመሪያው የነበረው የሰይጣን ዓላማ የእግዚአብሔርን ሕግ ቦርቡሮ ለእርሱ
የሚቀርበውን አምልኮ ማጨናገፍ ነበር። “ሕግን ሁሉ የሚፈጽም ነገር ግን በአንዱ
የሚሰናከል” “ሁሉን እንደ ተላለፈ” እንደሚቆጠር (ያዕ. 2፡10) ያውቃል። ስለዚህ
ሰዎች አምላካዊውን ሕግ ይተላለፉ ዘንድ ያበረታታል። ሰንበት የእግዚአብሔርን ፈጣሪነት
የሚያስታውስ እና ይህ አምላክ እንዴት መመለክ እንዳለበት የሚነግር ከመሆኑ አኳያ
ሰይጣን ሰንበትን አጥብቆ ይጠላል። ይሁን እንጂ በሰማያዊው መቅደስ ቅድስተ ቅዱሳን
በሚገኘው አምላዊ ሕግ ውስጥም አለ። ኃጢአትን የሚገልጸው ሕጉ እንደመሆኑ፣ ሰዎች
ለእግዚአብሔር ታማኝ ለመሆን እስከፈለጉ ድረስ የሰንበትን ትእዛዝ ጨምሮ ሕጉ ጸንቶ
መቀጠል አለበት።
የዚህ ትምህርት ዓላማ በቤተ መቅደሱ፣ በእግዚአብሔር ሕግ፣ በሰንበት እና
የአውሬውን ምልክት ተከትሎ በሚመጣው ቀውስ መካከል ያለውን ትስስር ማሳየት ነው።
በተጨማሪ ሰንበት ከመጨረሻው ዘመን ትውልድ ጋር የሚኖረውን አግባብ እንመረምራለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 11:19፣ ዘፀ. 25:16፣ ዘፀ. 31:18፣ ራእ. 12:17።
እነዚህ ጥቅሶች በቅድስተ ቅዱሳን ስፍራ በሚገኘው የቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ምን እንደ
ነበር ያመለክታሉ?
የስርየት ቀን የፍርድ ቀን ነበር። መላው እስራኤል በንስሐ፣ ነፍስን በመመርመር
እና ከማንኛውም ሥራ በመቆጠብ በዚህ ስነ ሥርዓት ላይ እንዲሳተፍ ታዝዞ ነበር (ዘሌ.
23፡29–31)። ሊቀ ካህናቱ ኃጢአትን ለማስተሰረይ ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ስፍራ የሚገባው
በዚህ ዕለት ብቻ ነበር። እዚያም፣ በመቅደሱ ውስጠኛ ክፍል የቃል ኪዳኑ ታቦት ነበረ። በታቦቱ
ውስጥ በድንጋይ ጽላቶች ላይ የተጻፈው አሥርቱ የእግዚአብሔር ትእዛዛት ሕግ ነበረ። የታቦቱ
የወርቅ ክዳን የስርየት መክደኛ ተብሎ የሚጠራ ሲሆን፣ መቅደሱን ከኃጢአት ለማንጻት ደም
ይረጭበት ነበረ። የእግዚአብሔር ሕልዎት ከስርየት መክደኛው በላይ፣ በማደሩ ክብር ተገለጠ።
ይቀርብ የነበረው መሥዋዕት ሁሉ እግዚአብሔር ለኃጢአተኞቹ የሰው ልጆች ያለውን ምህረት
ያሳየ ሲሆን፣ የስርየት ቀን ግን ኃጢአት እስከ ፍርድ ቀን ድረስ እንደሚታወስ ያሳያል (ዕብ.
10፡3)። በመሆኑም በእርግጠኝነት ሊወገድ የሚችለው ከኃጢአት በሚያነጻው በክርስቶስ
ደም በማመን ብቻ ነው (1ጴጥ. 1፡18-19)። እዚያ፣ ምሕረት እና ፍትሕ ውብ በሆነ
መልኩ በእግዚአብሔር ፊት ጥምረት ይፈጥራሉ። ወደ ሰማያዊው መቅደስ ውስጠኛ ክፍል
የተመለከተው ሐዋርያው ዮሐንስ እንዲህ ብሎ ነበር፡ “ከዚያም በሰማይ ያለው የእግዚአብሔር
ቤተ መቅደስ ተከፈተ፤ በመቅደሱም ውስጥ የኪዳኑ ታቦት ታየ” (ራእ. 11፡19)።
“መመሪያዎቹ በጽላቶቹ ላይ የተጻፉት፣ ሙሴም በኦሪት በጽሑፍ ያሰፈረው፣
በሰማያዊው ቤተ መቅደስ ውስጥ ያለው የእግዚአብሔር ሕግ፣ ዋናው ቅጂ ነው። ወደዚህ
አስፈላጊ ወደሆነ ነጥብ መረዳት የደረሱ እነርሱ የተቀደሰና ባህሪው የማይለወጥ የሆነውን
መለኮታዊ ሕግ እንዲያዩ ተመሩ፤ ከምንጊዜውም የበለጠ ያዳኙን ቃላት ኃይል ተገነዘቡ።”
(ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 496)።
ቀደምት የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ አማኞች መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ቤተ መቅደሱ
የሚያስተምረውን ትምህርት ሲያጠኑ፣ የእግዚአብሔርን ሕግ አስፈላጊነት እና በሕጉ
እምብርት የሰፈረውን የሰንበት እውነት አስተዋሉ። የእግዚአብሔር ሕግ በሰማያዊው መቅደስ የቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ መኖሩ በግልጽ እስከ ቀረበ ድረስ፣ በመስቀሉ ሊወገድ
እንደማይችል እርግጠኞች ሆኑ።
በሰዓት 1,600 ኪሎ ሜትር እየከነፈ ያለ አንዳች ልዩነት በየሣምንቱ ወደ እኛ ስለሚገሰግሰው
የሰንበት ቀን አሰብ ያድርጉ። ይህ ስለ ፍጥረት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አስተምህሮ አስፈላጊነት
ምን ሊነግረን ይገባል? ለመሆኑ እንዲህ ያለ ብርቱ አስተዋሽ አስተምሮ የትኛው ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 5:17-18፣ መዝ. 111:7-8፣ መክ. 12:13-14፣ 1ዮሐ. 5:3፣ ምሳ. 28:9። ጥቅሶቹ ክርስቲያኖች ክአምላካዊው ሕግ ጋር ስላላቸው ተዛምዶ ምን ያስተምራሉ
የሰባተኛው ቀን ዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች የእግዚአብሔርን ሕግ ቅድስና የሚደግፉትን የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች ፈለግ ይከተላሉ። የሚከተለውን የጆን ዌስሊ ብርቱ የማረጋገጫ ቃል ልብ ይሏል፡ “ሙሴ ለእስራኤል ልጆች ያስተላለፋቸውን ከአሮጌው የመሥዋዕት እና የቤተ መቅደስ አገልግሎት ጋር ተያያዥነት የነበራቸውን ድንጋጌዎች እና ሥርዓቶች ጌታችን ሊያፈርስና ሙሉ በሙሉ ሊሽር መጣ። … ይሁን እንጂ በአሥሩ ትእዛዛት ውስጥ የተካተተውን እና በነቢያት የተደነገገውን አምላካዊ ሕግ አላስወገደውም። ከእነዚህ አንዱንም ክፍል ማስወገድ የመምጣቱ እቅድ አካል አልነበረም። ይህ ‘በሰማያት ታማኝ ምስክር ሆኖ የጸና’ ፈጽሞ የማይሻር ሕግ ነው። የዚህ ሕግ እያንዳንዱ ክፍል በመላው ሰብዓዊ ዘር እና በሁሉም ዘመናት ጸንቶ መኖር አለበት። ትእዛዛቱ በእግዚአብሔር ባህሪ እና በሰው ተፈጥሮ እንዲሁም እነዚህ ሁለቱ እርስ በርስ ባላቸው የማይለወጥ ዝምድና ላይ የተመሠረቱ እንጂ፣ በጊዜ ወይም በቦታ ወይም በሌላ በማንኛውም ሊለወጡ በሚችሉ ሁናቴዎች ላይ የተመረኮዙ አይደሉም።”—Upon Our Lord’s Sermon on the Mount, Discourse V, John Wesley’s Sermons: An Anthology (Nashville, TN: Abington Press, 1991), pp. 208, 209. ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዘፀ. 34:5–7፣ ሮሜ 7:11-12፣ መዝ. 19:7–11፣ መዝ. 89:14፣ መዝ. 119:142፣ 172። ጥቅሶቹ በእግዚአብሔር ሕግ እና በእግዚአብሔር ባሕሪ መካከል ስላለው ዝምድና ምን ይነግሩናል?
የእግዚአብሔር ሕግ የባህሪው ግልባጭ፣ የዙፋኑ መሠረት እና የሰው ልጆች ሥነ ምግባር
መሠረት መሆኑን ተከትሎ ሰይጣን አጥብቆ ይጠላዋል። “ምድራዊው መቅደስ የሰማያዊው
ምሳሌ ወይም አምሳያ ከሆነ በምድር በነበረው ታቦት ውስጥ የተቀመጠው ሕግ በሰማይ ባለው
ታቦት ውስጥ ያለው ሕግ ግልባጭ እንደሆነ፣ ሰማያዊውን መቅደስ የተመለከተ እውነታ መቀበል
ለእግዚአብሔር ሕግ መጠይቅ እውቅና መስጠት፣ አራተኛውን ትእዛዝ ሰንበትን ማክበር
እንደሆነ ማንም ሊስተው አልቻለም። የክርስቶስን በሰማያዊ መቅደስ ያለበትን አገልግሎት
የሚገልጹትን፣ ስምሙ የሆኑትን የመጽሐፍ ቅዱስ ማብራሪያዎች መሪር እና ቆራጥ ተቃውሞ
የገጠማቸው ምክንያት ምስጢር እዚህ ላይ ነበር።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽጽ 497)።
ብዙውን ጊዜ ሰዎች አሥርቱን ትእዛዛት የመጠበቅ ግዴታ የለብንም ብለው
የሚከራከሩባቸው ምክንያቶች ምንድን ናቸው? ከበስተጀርባ ያለው ነገር በትክክል ምን
ይመስሎታል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14:6-7፣ ራእ. 4:11፣ ገላ. 2:1–3፣ ዘፀ. 20:8–11።
በፍጥረት ሥራ፣ በሰንበት እና በእግዚአብሔር ሕግ መካከል ያለው ዝምድና ምንድን ነው?
ፍጥረት በእግዚአብሔር ፊት ምን ያህል ዋጋ እንዳለን ይናገራል። በግዙፉ ዩኒቨርስ
ብቻችንን የምንንከላወስ ፍጡራን አይደለንም—የጠፈር ነቁጥ ብናኞች—ወይም ድንገተኛ
የጄኔቲክ ክስተት አይደለንም። በሌላ አነጋገር ሳይንስ ስለ ሕይወት አጀማመር የሚያቀርበው
ችኮ ግኝት እና የዜና አውታሮች የሚቀባበሉት ትርክት ከመጽሐፍ ቅዱሳዊው ዘገባ ጋር
በሁሉም መንገድ አይጣጣምም።
በዚህ ምድር ያለነው የሱስ ስለፈጠረን ነው። እርሱ ስለ ፈጠረን ብቻ ሳይሆን ስለ
ዋጀን ጭምር እንሰግደለት ዘንድ ይገባዋል። መፈጠር እና መቤዠት የእውነተኛው አምልኮ
አስኳል ናቸው። ስለዚህ ሰንበት የመዳንን እቅድ ለመረዳት የሚያስችለን ቁልፍ ርዕሰ ጉዳይ
ነው። ሰንበት ፈጣሪ አምላክ ስለሚያደርግልን ጥንቃቄ እና ስለ አዳኙ ፍቅር ይነግረናል።
በፍጥረት ሳምንት ማጠናቀቂያ ላይ እግዚአብሔር በፈጠረው ዓለም ውበት
እና ግርማ ውስጥ አረፈ። የእርሱ ማረፍ ለእኛም ምሳሌ ትቶልናል። ሰንበት የፈጠረንን
ለማመስገን የምናደርገው ሣምንታዊ እረፍት ነው። በሰንበት አምልኮ ስናደርግ፣ ጌታ ከዚያ
ቀን ውጪ በየትኛውም የሣምንቱ ቀን ያላስቀመጠውን ልዩ በረከት ለመቀበል ልባችንን
እንከፍታለን።
እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ዓላማ ስንርቅ እንኳ ሰንበት ከመጠን በላይ ወደ ወደደን
ወደዚህ ፈጣሪ አምላክ ያመላክተናል። ሰንበት በእርሱ የማረፋችን ዘላለማዊ ምልክት ነው።
ለፈጣሪ ታማኝ የመሆን ልዩ ምልክት ነው (ሕዝ. 20፡12-20)። የእረፍት እንጂ የሥራ
ተምሳሌት አይደለም። የጸጋ እንጂ የሕጋዊነት ቀንበር አይደለም። የእምነት ዋስትና እንጂ
ኩነኔ አይደለም። ለመዳን በራሳችን ሳይሆን በእግዚአብሔር የመመካታችን ማሳያ ነው።
እውነተኛ የሰንበት እረፍት እኛን በፈጠረን፣ በዋጀን እና ስለ እኛ ዳግም በሚገለጠው አፍቃሪ
ክንዶች እቅፍ ውስጥ በጸጋ ማረፍ ነው።
እግዚአብሔር ለዓለም የመጨረሻ ዘመን ያስተላለፈው የራእ. 14 መልእክት፣
ሰዎች በፍቅሩ እንዲያርፉ እና እያንዳንዱን ሰንበት ይጠብቁ ዘንድ ጥሪ ያደርጋል። የፈጠረንን
እንድናስታውስ እና ለእርሱ ክብር እንድንሰጥ ይጋብዘናል። በተጨማሪ ሰንበትን መጠበቅ፣
የኤደንን ፍጽምና ከሚመጣው አዲስ ሰማይና ምድር ጋር በአንድ የሚያስተሳስር እውነት
ነው። ሰንበት አንድ ቀን የኤደን ግርማ እንደሚመለስ ያስታውሰናል።
በርካታ የሰባተኛ ቀን ዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ሕግ ጠባቂዎች ናችሁ የሚል ክስ
ሲቀርብባቸው የሚስተዋል ሲሆን፤ ክሱ ደግሞ ብዙውን ጊዜ ሰንበትን ከመጠበቅ ጋር
የተያያዘ ነው። ሰንበት የመቤዠታችን እና የጽድቅ በእምነት ምልክት ከመሆኑ አኳያ
ተወያዩ። እግዚአብሔር እረፉ ብሎ የሰጠውን ትእዛዝ መጠበቃችን፣ ሰዎች በሥራችን
ወደ ሰማይ ለመሄድ እየጣርን አድርገው እንዲያስቡ ያደረጋቸው ምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 12:12፣ 17፣ ራእ. 13:7። ጥቅሶቹ የሰይጣንን ቁጣ እንዴት ይገልጻሉ? ዲያብሎስ በመጨረሻው ዘመን የእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ እንዲህ አምርሮ የተቆጣው ለምንድን ነው?
ራዕይ 12 ከዘመናት በፊት በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል በሰማይ ስለ ተካሄደው ጦርነት ይዘረዝራል። ሰይጣን በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ የሚሰነዝረው የመጨረሻ ጥቃት ተጋድሎውን የመጨረሻው ጡዘት ላይ ያደርሰዋል። ራእ. 13 የዘንዶውን ሁለት አጋሮች ማለትም ከባህር የሚወጣውን እና ከምድር የሚነሣውን አውሬውን ያስተዋውቃል። እነዚህ ሁለት ኃይሎች በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ጦርነት ለመክፈት ከእርሱ ጋር ግንባር ይፈጥራሉ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13:4፣ 8፣ 12፣ 15፣ ራእ. 14:7፣ 9-11። (በተጨማሪ፡ ራእ. 15:4፣ ራእ. 16:2፣ ራእ. 19:20. ራእ. 20:4፣ ራእ. 22:9) በእነዚህ ሁሉ ጥቅሶች ውስጥ የምናገኘው አንድ ቁልፍ ርዕሰ ነጥብ ምንድን ነው?
በንጽጽር የቀረበበትን መንገድ ልብ ይበሉ። ሰዎች ፈጣሪን ያመልካሉ አሊያም
ለሌላ ነገር ይሰግዳሉ። ሰማይንና ምድርን የፈጠረ አምላክ አምልኮ ይገባዋል (ራእ. 5፡
9)። በሰማይ--በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል የተነሣው ውዝግብ መነሾ አምልኮ ነበር፡
“ከደመናዎችም ከፍታ በላይ ዐርጋለሁ፤ ራሴንም እንደ ልዑል አደርጋለሁ።” (ኢሳ. 14፡
14)። ሰይጣን ለፈጣሪ ብቻ የተገባውን አምልኮ ለገዛ ራሱ ፈለገ። በራእ. 13 መሠረት፣
ከምድር በሚነሣው አውሬ ተግባር ስኬት ያገኛል (ራእ. 13፡4)።
ከዳንኤል 7 ጋር የተደረገው ንጽጽር እንደሚያሳየው ይህ ለ1,260 ትንቢታዊ
“ቀናት” ማለትም ለ1,260 ዓመታት በሥልጣን የሚቆየውና “ጊዜና ሕግን ለመለወጥ
ይሞክራል” የተባለው ከምድር የተነሣው አውሬ ከትንሹ ቀንድ ጋር ተመሳሳይ ነው (ዳን.
7:25 እና ራእ. 13፡5ን ያነጻጽሩ)። ከእግዚአብሔር አሥርቱ ትእዛዛት ውስጥ ከጊዜ ጋር
ቁርኝት ያለው ብቸኛ ክፍል አራተኛው ትእዛዝ ነው። ይህች ቤተ ክርስቲያን የአምልኮን ቀን
ከሰባተኛው ቀን ከቅዳሜ ወደ ሳምንቱ የመጀመሪያ ቀን እሁድ ለመቀየር ሞክራለች።
ምድራዊ የሆነ አንድ ኃይል እግዚአብሔር ራሱ የሥልጣኑ ምልክት አድርጎ የሰጠውን
ሰባተኛውን የአምልኮ ቀን ሰንበት (ዘፀ. 31፡13፣ ሕዝ. 20፡12፣ 20) ለመለወጥ
ማሰብ--በመሠረታዊ ደረጃ መለኮታዊውን ሥልጣን ለመቀማት የሚደረግ ሙከራ ነው።
ስለዚህ በእውነተኛው እና በሐሰተኛው አምልኮ መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ግጭት
በዚህ ነጥብ ላይ ያተኮረ ይሆናል።
በዚህ ምክንያት የራእይ መጽሐፍ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆኑትን ሰዎች
“የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁ" (ራእ. 12፡17፣ ራእ. 14፡12) በማለት
ለይቶ ያስቀምጣቸዋል። ይህ ደግሞ ሰባተኛውን ቀን ሰንበት እንጂ እሁድን አያካትትም።
እግዚአብሔርን በተቀደሰው ቀኑ (ኢሳ. 58፡13) አምልኩ የሚለውን የሦስቱን መላእክት
መልእክት የመጨረሻ ጥሪ የማይቀበሉ እና ሐሰተኛ ሰንበት በሆነው እሑድ ቀን አውሬውን
የሚያመልኩ፣ የአውሬውን ምልክት ይቀበላሉ (11ኛውን ትምህርት ይመልከቱ)።
በራእ. 14፡7 የመጀመሪያው መልአክ፡ “በታላቅ ድምፅም፣ ‘እግዚአብሔርን ፍሩ፤
ክብርም ስጡት፤ ምክንያቱም የፍርዱ ሰዓት ደርሷል፤ ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና የውሃ
ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ አለ።” ከሚመጣው ፍርድ አንጻር የላቀውን ታማኝነታችንን
እና ልባዊ አምልኳችንን ለፈጣሪ እናቀርብ ዘንድ ሰማይ ይማጸነናል።
ሁለተኛው መልአክ ደግሞ፡ “ ‘ሕዝቦች ሁሉ፣ የዝሙቷን ቍጣ ወይን ጠጅ
እንዲጠጡ ያደረገች ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች!” እያለ ተከተለው’ ” (ራእ. 14፡
8)። ባቢሎን የመጀመሪያውን መልአክ መልእክት ያልተቀበለውን ክህደት የፈጸመ ኃይማኖታዊ
ሥርዓት ትወክላለች። ለዚህ ነው ራእ. 14፡9-11 “ለአውሬውና ለምስሉ” እንዳንሰግድ
የሚያስጠነቅቀን። እዚህ ላይ ለየቅል የቀረቡ ሁለት ምርጫዎች አሉ-ፈጣሪን ማምለክ ወይም
ለአውሬው መስገድ። በምድር ላይ የሚኖር እያንዳንዱ ሰው ታማኝነቱ--ለየሱስ ወይስ ለሰይጣን-
-ከሁለቱ አንዱን በመምረጥ፣ የመጨረሻውን፣ የማይቀለበስ ውሳኔ ያደርጋል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 14፡12። አውሬውን ለማምለክ የሚቃወሙ ሰዎች ሁለት
መለያ ባህሪያት ምንድን ናቸው? እነዚህ ሁለቱም በጣም ወሳኝ የሆኑት ለምንድነው?
በዓለም ታሪክ በዓይነቱ ታላቅ የሚባል አስፈሪ ተቃውሞ እና ጽኑ ስደት በሚደርስበት
የመጨረሻው ዘመን ላይ፣ እግዚአብሔር ለእርሱ ታማኝ ሆነው የሚቆሙ ሕዝቦች ይኖሩታል።
በክርስቶስ የጽድቅ ስጦታ፣ በጸጋ የተሞላ ታዛዥ ሕይወት ይኖራሉ። ፈጣሪን ማምለክ
አውሬውን ከማምለክ ጋር በቀጥታ የሚቃረን ሲሆን፣ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅ
ይገለጻል። በዚህ የመጨረሻው ተጋድሎ፣ ለክርስቶስ ታማኝ መሆን ወይም ለአውሬው ኃይል
ታማኝ መሆን የሚገለጸው በአምልኮ ይሆናል። በበጎ እና በክፉ መሃል ለሚደረገው ለዚህ
ተጋድሎ ዋንኛው አስኳል ሰንበት ይሆናል።
እነዚህ አዳኙን በቁርጠኝነት የሚከተሉ ሕዝቦቹ በየሱስ ላይ እምነት ያላቸው ብቻ
ሳይሆኑ፣ የየሱስም እምነት ይኖራቸዋል።
የየሱስ እምነት በገሐነም ያሉ አጋንንትም ሆኑ በምድር ላይ ያሉ መከራዎች ሁሉ
ሊያናውጡ የማይችሉት እጅግ ጥልቅ፣ እምነት የሚጣልበትና ቁርጠኝነት የተላበሰ እምነት
ነው። የማይታይ ቢሆንም የሚያምኑት፣ ለምን ብሎ ከመሟገት ይልቅ አሜን ብለው በእምነት
የሚቀበሉት እና የማይስተዋለውን ነገር በተስፋ የሚሰንቁት ነው። ይህ “የየሱስ እምነት”
በራሱ በእምነት የምንቀበለው ስጦታ ነው። ከፊታችን በሚጠብቀን ቀውስ ውስጥ ማለፍ
እንድንችል ይረዳናል። የመጨረሻው ቀውስ ሲፈነዳና የኢኮኖሚ አድማ፣ ስደት፣ እሥራት
ብሎም ሞትም እንኳ ሲገጥመን፣ በእርሱ ላይ ያለን እምነት የሱስ ዳግም እስኪገለጥ--
በእነዚያ የምድር የመጨረሻ ሠዓታት ውስጥ ያሳልፈናል።
ወደፊት ለሚመጣው፣ እግዚአብሔር አምላክ ዛሬ እምነትዎን እንዴት እያዘጋጀ ነው?
“የመጽሐፍ ቅዱስ ምስክርነት ድጋፍ ሳይኖራቸው ብዙዎች ያለመታከት
ለፉ፤ ያው ተመሳሳይ መከራከሪያ ክርስቶስንና ሐዋርያቱን ለመቃወም ቀርቦ እንደነበረ
ረስተው “ታዲያ የዚህን ሰንበት ጥያቄ ታላላቅ ሰዎቻችን (ሊቆቻችን) ለምን አይረዱትም?
እንደናንተ የሚያምኑ በጣም ጥቂቶች ናቸው። እናንተ ትክክል ከሆናችሁ በዓለም ያሉ
የተማሩ ሰዎች ሁሉ ሊሳሳቱ አይችሉም” አሉ። እንደነዚህ ያሉ መከራከሪያዎችን ፉርሽ
ለማድረግ መጽሐፍ ቅዱስ የሚያስተምረውንና በሁሉም ዘመናት እግዚአብሔር ከሕዝቦቹ
ጋር ያለውን ግንኙነት ታሪክ መጥቀስ ብቻ በቂ ነበር።”—(ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 519)
“ነገር ግን እንዲህ በማድረጋቸው መጽሐፍ ቅዱሳዊውን ሰንበት እየጠበቁ እንደሆነ
የሚያምኑ የቀድሞው ትውልድ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ በዚህ ዘመንም እሁድ የመለኮት ተቋም
እንደሆነ ከልባቸው የሚያምኑ በሮማ አብያተ ክርስቲያናት ጭምር የሚገኙ እውነተኛ
ክርስቲያኖች አሉ። የዓላማቸውን ታማኝነት እና ቀናነታቸውን እግዚአብሔር ይቀበለዋል።
የእሁድ መከበር ግን በሕግ አስገዳጅ በሚሆንበት ጊዜ፣ መላው ዓለም ለእውነተኛው
ሰንበት ያለበትን ኃላፊነት በሚረዳበት ጊዜ፣ ሮም ካላት ሥልጣን የበለጠ ሥልጣን የሌለውን
መመሪያ በመታዘዝ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ የሚጥስ ማንኛውም ሰው፣ ጳጳሳዊው ሥርዓትን
ከእግዚአብሔር በላይ ከፍ ከፍ ያደርጋል። ለሮም የተለየ አክብሮት ይሰጣል፤ በሮም
የተቀደሰውን ተቋም ተግባራዊነት አስገዳጅ ለሚያደርገው ኃይልም ክብር ይሰጣል። አውሬውንና
ምስሉን ያመልካል። የሥልጣኑ ምልክት አድርጎ እግዚአብሔር ያቋቋመውን ተቋም ሰዎች
አንቀበልም ሲሉ፣ የበላይነቷ ምልክት አድርጋ የመረጠችውን በመተካት ሲያከብሩ፣ ያን ጊዜ
ለሮም የታማኝነት መግለጫ የሆነውን ምልክት ‘የአውሬውን ምልክት’ ይቀበላሉ። ጉዳዩ
በግልጽ ለሰዎች ቀርቦ፣ በእግዚአብሔር ትእዛዛትና በሰዎች ትእዛዛት መካከል እንዲመርጡ
ተደርገው፣ በምርጫቸው ሕግን መጣስ እስኪቀጥሉ ድረስ፣ (ይህን ከማድረጋቸው በፊት)
‘ያውሬውን ምልክት’ አይቀበሉም።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 513-514)
1. ዓለማችን በከፍተኛ ፍጥነት እና በአስገራሚ ሁኔታ እየተቀየረች ነው። የመጨረሻዎቹ
ቀናት ክስተቶች ሳንዘጋጅ እንዳይዙን ሁልጊዜ ንቁዎች መሆን ያለብን ለምንድን ነው?
2. ስለ ፍርድና ስለ እግዚአብሔር ሕግ የሚኖረን አረዳድ በጸጋ ብቻ ከመዳናችን
እውነታ ጋር ስምሙ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?
3. የእውነተኛውን ሰንበት ትርጉም ለማይረዱና የሳምንቱን የመጀመሪያ ቀን እሁድ
በቅንነት ለሚጠብቁ፣ መመስከር የሚችሉባቸው መንገዶች ምንድን ናቸው?
4. በቤተ ክርስቲያን እና በመንግሥት አካላት አንድነት ውስጥ ምን አደጋዎች አሉ?
እንደ ክርስቲያን ከመንግሥት ጋር ግንኙነት የ mሚኖረን በምን መልኩ ነው?