የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ማቴ. 10:28፣
መክ. 9:5፣ ኢሳ. 8:19-20፣ ዮሐ. 11:11–14፣ 21–25፣ 1ተሰ. 4:16-17፣
ራእ. 16:13-14፣ ማቴ. 24:23–27፣ 2ተሰ. 2:9–12።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ጌታ ራሱ በታላቅ ትእዛዝ፣ በመላእክት
አለቃ ድምፅና በእግዚአብሔር የመለከት ድምፅ ከሰማይ ይወርዳልና።በክርስቶስ የሞቱትም አስቀድመው ይነሣሉ። ከዚያም በኋላ እኛ የቀረነው፣ በሕይወትም የምንኖረው ጌታን በአየር ላይ ለመቀበል ከእነርሱ ጋር በደመና እንነጠቃለን፤ በዚህም መሠረት ለዘላለም ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ በዚህ ቃል እርስ በርሳችሁ ተጽናኑ።” (1ተሰ. 4፡16-17)።
ከጥቂት አሥርተ ዓመታት በፊት በሞት አፋፍ ላይ የነበሩ ወይም ከነጭራሹ “ሞተዋል”
ተብለው ግን ደግሞ ያንሰራሩ ሰዎች ስላዩት እና ስለ ሰሙት የተናገሯቸው በሚል
በርካታ ታሪኮች ይናፈሱ ነበር። በሺዎች የሚቆጠሩ ተመሳሳይ ታሪኮች በሰነድነት
ተዘጋጅተው ጥናት ተደርጎባቸዋል። የክርስቲያኑን ዓለም ጨምሮ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ
በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች፣ እነዚህ ዘገባዎች ሙታን በእርግጥም እንዳልሞቱ የሚያሳዩ
ማስረጃዎች እንደሆኑ ያምናሉ። ይህ መንፈስ ከአካል ተለይቶ መኖሩን ይቀጥላል የሚለው
መሠረታዊ እምነት በእጅጉ ከተስፋፉና ውጤታማ ከሆኑ የሰይጣን ማታለያዎች አንዱ ነው።
በመሠረቱ ነፍስ ከአካል ተለይቶ ይኖራል የሚለው የመናፍስታዊነት አስተምህሮ
የጀመረው በኤደን ሲሆን፣ ይኸውም እባቡ አዳምና ለሔዋንን “መሞት እንኳ አትሞቱም”
(ዘፍ. 3፡4) ብሎ በሐሰት በሸነገላቸው ጊዜ ነበር። በዘመናት ጉዳዩ የተለያዩ ቅርጾች
ቢይዝም ነገር ግን ሕይወት ከሞት በኋላ ይቀጥላል ለሚለው ንድፈ ሀሳብ አጽንኦት ይሰጣል።
በተጨማሪም በ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ከታዩ ታላላቅ ሐሳዊ ኃይማኖታዊ እንቅስቃሴዎች
መካከል አንዱ የሆነው የፎክስ እህቶች የዚህ ጽንሰ ሐሳብ አራማጅ ነበር። ለጥያቄዎች
መልስ የምናገኘው ከሙታን መናፍስት ነው የሚለው ይህ እንቅስቃሴ፣ በማጭበርበር ድርጊት
ውስጥ ተገኝቶ ነበር።
በምድር መጨረሻ አካባቢ እውን በሚሆኑ ተጋድሎዎች፣ ሰይጣን ይህን የሐሰት
አስተምህሮ ተጠቅሞ በሚፈጽማቸው አስደናቂ ክስተቶች በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን
ያታልላል። ሰይጣን ዓለምን በቁጥጥሩ ሥር ለማዋል የሚሞክርበት አንዱ መንገድ ይኸው
እንደሆነ የራእይ መጽሐፍ ይጠቁማል። የዚህ ትምህርት ዓላማ ከሰይጣን የመጨረሻዎቹ
ቀናት ማታለያዎች ልንጠበቅ የምንችለው ከክርስቶስ ጋር በሚኖረን የግል ግንኙነት እና
በመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮዎች ላይ በሚኖረን ጠንካራ መሠረት ብቻ እንደሆነ ማሳየት
ነው። ይህ ደግሞ ዓይናችን፣ ጆሮአችን እና ልባችን ስለ ሞት ሊል የሚችለውንም ይጨምራል።
ሞት ማለት ሕይወት ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚሸጋገርበት ክስተት ነው፣ የሚለው
ትርክት በነፍስ ተፈጥሯዊ አለመሞት ጽንሰ-ሀሳብ ላይ የተመሠረተ ነው። ይህ አረማዊ ጽንሰ
ሀሳብ ሰርጎ ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባው ገና ከማለዳው ሲሆን፣ ይኸውም ቤተ ክርስቲያን
ከመጽሐፍ ቅዱስ መሠረቷ ገሸሽ ብላ እምነቷ በመላው የሮም ግዛት ተደራሽ እንዲሆን
ጥረት ታደርግ በነበረበት ወቅት ነው። “የነፍስ አትሞትም ጽንሰ ሀሳብ ሮም ከእምነት
የለሽነት (ፓጋኒዝም) በመዋስ ወደ ክርስትናው ዓለም ኃይማኖት ከቀላቀለቻቸው የሐሰት
አስተምህሮዎች አንዱ ነው” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 628)።
“ ‘ሥጋን መግደል እንጂ ነፍስን መግደል የማይችሉትን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንና
ሥጋን በገሃነም ማጥፋት የሚቻለውን ፍሩ’ ” (ማቴ. 10፡28)። ስለ ነፍስ አትሞትም
አባባል ይህ ጥቅስ ብቻውን ምን ሊነግረን ይገባል?
ሕዝቡ በየትኛውም ዓይነት የባዕድ መናፍስታዊ አሠራር ውስጥ እንዳይሳተፍ ጌታ
ከልክሎ ነበር። በመካከላቸው “በድግምት የሚጠነቍል፣ መናፍስት ጠሪ ወይም ሙት
አነጋጋሪ” (ዘዳ. 18፡11) ቢኖር ምሕረት አይደረግለትም። እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች
በድንጋይ ተወግረው ይገደሉ ነበር (ዘሌዋ. 20፡27)። ቅጣቱ በጣም ከባድ ቢመስልም
እስራኤላውያን የሐሰት አማልክትን ከማምለክ እንዲጠበቁ ታስቦ የተዘጋጀ ነበር።
ጥንቆላ አጋንንታዊ ነው። ሰዎችን አታልሎ ወደ ሐሰት አምልኮ በማስገባት፣
ብዙዎች ከትክለኛው አምላክ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው ሆኖ እንዲሰማቸው ቢያደርግም፣
ነገር ግን የልብን ጥልቅ ፍላጎቶች ፈጽሞ ማርካት አይችልም። ስፕሪችዋሊዝም የሰይጣን
ዓለምን በግዞቱ የማዋል እቅድ አስኳል ነው። የሱስ ግን በጸጋው እና በኃይሉ ሰዎችን እጅ-
ከወርች ከጠፈነገው የክፉው ሰንሰለት ነጻ ያወጣል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መክ. 9:5፣ ኢዮ. 7:7–9፣ ኢሳ. 8:19-20። እነዚህ የመጽሐፍ
ቅዱስ ክፍሎች ስለ ሞት እና ከሙታን ጋር ስለ መነጋገር ምን ያስተምሩናል?
ሰዎች ሲሞቱ በቀጥታ ወደ ሰማይ ይሄዳሉ የሚለው እምነት ምንም እንኳ መጽሐፍ
ቅዱሳዊ ባይሆንም፣ ነገር ግን ልክ እንደ እሑድ “ሰንበት” ለረጅም ዘመን የኖረ እና ጥልቅ
ሥር የሰደደ ከመሆኑ አኳያ፣ ይህን እምነት መልቀቅ ለብዙዎች እጅግ አዳጋች ነው።
ሰዎች ይህን እምነታቸውን ለማጽናት ይረዳል በሚል ጥቂት ጥቅሶችን ከዐውዳቸው ውጪ
በመውሰድ ሲጠቅሱ ይስተዋላል። ይሁን እንጂ ይህ የሐሰት ትምህርት በተለይ የመጨረሻው
የምድር ቀውስ በሚሰከትበት ወቅት፣ ሰይጣን ሊያሳድርባቸው ከሚችለው የማታለያ ጫና
ያለ ምንም ከለላ እንዲቀሩ ያደርጋቸዋል።
የሙታንን ሁኔታ ለሌሎች ክርስቲያኖች ለማስረዳት በሚሞክሩበት ወቅት ምን አጋጠሞት?
ውጤታማ ሆኖ ያገኙት አካሄድ ካለ ቢያካፍሉ?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 6:5፣ መዝ. 115:17፣ 1ነገሥ. 2:10፣ 1ነገሥ. 11:43፣ 1ነገሥ. 14:20። ጥቅሶቹ የሞቱ ሰዎች ስለሚኙበት ሁኔታ ምን ያስተምሩናል?
የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ ነፍስ አትሞትም የሚል አስተምህሮ የለውም። ወይም
ከሞት በኋላ፣ ታማኞች ለዘላለም ወደ መንግሥተ ሰማያት ደስታ፣ ታማኝ ያልሆኑት ደግሞ
ሲኦል ወርደው ለዘላለም ይቃጠላሉ ብሎ አያስተምርም። ይልቁንም ሞት እንቅልፍ እንደሆነ
ያስተምራል። መጽሐፈ ነገሥት የኃይማኖት አባቶችን ሞት ሲገልጽ፡ “ከአባቶቻቸው
ጋር አንቀላፉ” ይለናል። ባለ መዝሙሩ “የሞት እንቅልፍ” (መዝ. 13፡3) ሲል
ይጠራዋል። ኢዮብ ስለ ሞት ሲናገር ከእንቅልፍ ስለ አለመንቃት ይጠቅሳል (ኢዮ. 14፡
12)። ባለ መዝሙሩ አከል አድርጎ እንዲህ ይላል፡ “እኔ ግን በጽድቅ ፊትህን አያለሁ፤
ስነቃም ክብርህን አይቼ እረካለሁ” (መዝ. 17፡15)።
የአሦራውያን ሠራዊት ተሸንፎ ሲደመሰስ የወታደሮቹ ሞት “ጭልጥ ብለው
ተኝተዋል” (መዝ. 76፡6) በሚል ተገልጾአል። የሞቱ ሰዎችን ከአካላቸው ተነጥለው ወዲህ
ወዲያ እያንዣበቡ በሕይወት ካሉ ጋር ግንኙነት እንደሚያደርጉ መናፍስት አድርጎ የማቅረቡ
ጽንሰ ሀሳብ፣ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሳይሆን ሙልጭ ያለ የአረማውያን አስተምህሮ ነው።
የሞትን ተጨባጭ ሁኔታ መረዳት አለመቻል ለሰይጣን የማታለያ በር ይከፍታል።
“የተወደዱ ዘመዶቻቸውን ወይም ጓደኞቻቸውን መስለው በሚቀርቡ፣ እጅግ አደገኛ የሆኑ ኑፋቄዎችን በሚናገሩ የዲያብሎስ መናፍስት ብዙዎች ግድድሮሽ ይገጥማቸዋል። እነዚህ ጎብኚዎች ስስ ብልቶቻችንን በመኮርኮር አስመሳይነታቸውን ያስቀጥሉ ዘንድ ተአምራትን ይሠራሉ። ሙታን
ምንም እንደማያወቁ መስለው የሚገለጡትም የአጋንንት መናፍስት እንደሆኑ በመጽሐፍ ቅዱስ
እውነት እንቋቋማቸው ዘንድ መዘጋጀት የግድ ያስፈልገናል።” ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 640።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 12:2፣ ኢዮ. 19:25-26። ሙታን የሚገኙበትን ሁኔታ
አስመልክቶ በጥቅሶቹ የታከሉ አላባዎች ምንድን ናቸው?
ሞት እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ድረስ የሚዘልቅ የእንቅልፍ ጊዜ ነው። ከዚህ
ውጪ በሕይወት ካሉት ጋር ግንኙነት ለመፍጠር እዚህም እዚያም የሚሰፍፉ አካል አልባ
መናፍስት የሉም። ምንም እንኳ አረማውያን በሙታን መንፈሳዊ ዓለም ቢያምኑም፣
እስራኤላውያን ግን ሞት እስከ ትንሣኤ ጠዋት የሚቆይ እንቅልፍ እንደሆነ ተረድተው ነበር።
ምንም እንኳ በሞት ስለተለዩን ሰዎች ብናዝንም፣ በክርስቶስ ስለሚሞቱ ግን
እንዲህ እናስብ፡ በሞት ዓይኖቻቸውን ይጨፍናሉ፣ ከዚያም የሱስ ዳግም እስኪመለስ የቱንም
ያህል ጊዜ ሊፈጅ ቢችልም፣ በቀጣይ የሚያውቁት ዳግም ምጽአቱን ነው። በትንሣኤ ወቅት
ሊኖራቸው የሚችለው የመጀመሪያው ሀሳብ--እንዴት ግሩም ነው! የሱስ ተመልሶ መጣ!-
-የሚል ይሆናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 11:11–14፣ 21–25 2ጢሞቴ. 1:10፣ 1ቆሮ. 15:51– 54፣ 1ተሰ. 4:15-17። የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች ስለ ሞት የሰጡት መግለጫ ከብሉይ ኪዳን ጋር እንዴት ይነጻጸራል?
ብሉይ ኪዳንም ሆነ አዲስ ኪዳን ሞትን በእንቅልፍ ተምሳሌት ያስቀምጡታል።
“እንቅልፍ” በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢያንስ ለሃምሳ ሦስት ጊዜ ሞትን ለመግለጽ እንደ አቻ
ቃል ቀርቦአል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች በሞት ወቅት አካልን በፍጥነት ለቅቃ ሕያው ሆና
መኖሯን የምትቀጥል ነፍስ ባለመኖሯ ይስማማሉ።
አዲስ ኪዳን በብሉይ በተገለጸው ላይ አንድ ተጨማሪ ብርሃን የሚፈነጥቅ ሲሆን
ይኸውም--በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ወቅት ገቢራዊ ስለሚሆነው በታላቅ ክብር የተሞላ
ትንሣኤ ነው። ዘላለማዊ ሕይወት የሚገኘው በክርስቶስ ብቻ መሆኑን ወንጌላት አጽንኦት
ይሰጣሉ። በገሐነም ያሉ አጋንንት የአማኞችን ዘላለማዊ ሕይወት ዋስትና ሊነጥቁ አይችሉም።
ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሞትን ድል ነስቷል። መቃብር የጥቃት ሰለባዎቹን በዚያው አፍኖ
ማስቀረት አይቻለውም። የክርስቶስ ትንሣኤ ሁሉም አማኞች አንድ ቀን በክርስቶስ ዳግም
ምጽአት ከመቃብር ለመነሣታቸው ዋስትና ነው።
ጳውሎስ እንዲህ ይላል፡ “ምክንያቱም ሙታን ካልተነሡ፣ ክርስቶስም
አልተነሣም። ክርስቶስም ካልተነሣ እምነታችሁ ከንቱ ነው፤ እናንተም እስከ አሁን ድረስ
ከነኀጢአታችሁ አላችሁ ማለት ነው። እንዲህም ከሆነ፣ በክርስቶስ ያንቀላፉት ጠፍተዋል
ማለት ነው።” (1ቆሮ. 15፡16-18)። የሞቱ ሰዎች ወዲያውኑ የሰማይ ደስታ ውስጥ
የሚገቡ ከሆነ፣ አንድ ሰው አነዚህን ጥቅሶች እንዴት ሊረዳ ይችላል? እነዚህ ሰዎች
ቀድሞውኑ የሚገኙት በሰማይ ከሆነ “ጠፍተዋል” ሲል ጳውሎስ ምን ማለቱ ነው?
ይልቁንም የጳውሎስ አጠቃላይ ነጥብ፣ የክርስቶስ ትንሣኤ የትንሣኤያችን መሠረት
እንደሆነና ያለ ትንሣኤ "እምነታችሁ ከንቱ ነው፣ አሁንም ከነኃጢአታችሁ አላችሁ”
የሞቱም በምድር ውስጥ ጠፍተው ይቀራሉ--የሚል ነው።
እነዚህ ጥቅሶች በየሱስ ዳግም ምጽአት ወቅት ስለምናገኘው የትንሣኤ ተስፋ
ከሚናገሩ ሌሎች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ጋር ፍጹም ይስማማሉ። የማይጠፋውን፣
የማይበላሸውንና የማይለወጠውን ርስት በሰማይ እንቀበላለን (1ጴጥ. 1፡4)። ይሁን እንጂ
ሙታን በሰማይ የሚገኙ ከሆነ፣ ጴጥሮስ “በሰማይ ስለተዘጋጀልን ርስት” ለምን ይናገራል?
በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው፣ የአዲስ ኪዳን አማኞች የክርስቶስን ዳግም ምጽአት እና
የሙታንን ትንሣኤ በጉጉት ይጠባበቁ ነበር፤ እናም ይህ ተስፋ በሕይወት ፈተናዎች ውስጥ
ታማኝ እንዲሆኑ አነሳስቷቸዋል።
ትንሣኤ ለክርስትና እምነት ያን ያህል ጠንካራ ተስፋ የሆነው ለምንድን ነው? መስቀል
ኖሮን ነገር ግን ትንሣኤ ባይኖረን ምን ተስፋ ይኖረን ነበር? እንግዲያው ትንሣኤ
የእምነታችን አስፈላጊ ክፍል የሆነው ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24:5፣ 11፣ 24፣ 2ተሰ. 2:7–9፣ ራእ. 13:13-14፣ ራእ. 16:13-14። ሰዎች በመጨረሻዎቹ ቀናት የሚገጥሟቸው ማሳቻዎች ምንድን ናቸው?
ዲያብሎስ የሱስ ዳግም ከመገለጡ በፊት ሰዎችን ለማታለል ልዩ ልዩ “ምልክቶችና
አስደናቂ” ታምራቶችን ያደርጋል። አንከል ሮድሪጌዝ ስለ አጋንንታዊ መናፍስት የማሳት
ኃይል እንዲህ ሲሉ ይናገራሉ፡ “የእነርሱ የማሳመን ኃይል የሚገኘው በመልእክታቸው ይዘት
ላይ ሳይሆን ‘ምልክቶች’ ወይም ‘ታምራት’ በሚባሉ ልዕለ ተፈጥሮ መገለጫዎች ነው።
ምልክቶችን ያደርጋሉ፤ በዚህም የሰው ልጆችን የማስተዋልና የማመዛዘን ችሎታ ሳይሆን
ስሜት ላይ ተጽእኖ ያለውን ገጽታ ይማርካሉ። እነዚህ ምልክቶች በአጋንንት መፈጸማቸው፣
የሦስቱን አጋንንት መልእክት አንድነት እንዲፈጠር የሚያደርገው ኃይል (ዘንዶው፣
አውሬው እና ሐሰተኛው ነቢይ) የመናፍስትነት ባህሪ ያለው እንጂ እግዚአብሔር ምንጩ
ወይም መሠረቱ አለመሆኑን ያሳያል። ለዘመናት የዘለቀው ተጋድሎ ወደ መዝጊያው
ሲቃረብ የአጋንንት ኃይል ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ ፍልሚያው መድረክ
ይመጣል። ነፍስ አትሞትም የሚለው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ያልሆነ አስተምህሮ መሠረት
የሆነው መናፍስታዊነት፣ በቅርቡ ዓለምን ምርኮው ያደርጋል።—“The Closing
of the Cosmic Conflict: Role of the Three Angels’
Messages,” unpublished manuscript, p. 6.
በገዛ ስሜታችን ላይ እምነት መጣል አደገኛ የሆነው ለምንድን ነው? ስሜት፣ ጥሩም ሆነ
መጥፎ በእምነታችን ውስጥ ምን ሚና ይጫወታል? ሰይጣን አስተሳሰባችንን በማለፍ
ስሜታችንን ሊማርክ የሚችለው እንዴት ነው?
“ዓለምን ያስት ዘንድ መጨረሻ ለሚያደርገው ጥረቱ ሰይጣን ዝግጅት ሲያደርግ
ቆይቷል… መናፍስታዊነትን በመኮትኮት ወደር የሌለው ማታለያው ለሆነው ስልቱ ቀስ በቀስ
መንገዱን ሲጠርግ ቆይቷል። ወደ ንድፎቹ ሙሉ አፈጻጸም ላይ ገና አልደረሰም፤ በመጨረሻዎቹ
ጭላጭ ቀናት ግን የሚደርስበት ይሆናል… በቃሉ ካላቸው እምነት የተነሣ በእግዚአብሔር ኃይል
ከሚጠበቁት በቀር ዓለም ሁሉ ወደ ማወናበጃው ተርታ ተጠርጎ ይወሰዳል። የእግዚአብሔር
ቁጣ ወርዶ እስኪያነቃቸው ድረስ በአደገኛ የደኅንነት ስሜት ውስጥ ሰዎች በጥድፊያ
እንዲያንቀላፉ እየተደረጉ ነው።” ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 642-643።
ደኅንነታችን በብቸኝነት የተጠበቀ ሊሆን የሚችለው በየሱስ እና በቃሉ ነው። የሞቱ
ሰዎች የሚገኙበትን ሁኔታ የማይረዱ በሚልዮን፣ አልፎ ተርፎም በቢልዮን የሚቆጠሩ
ሰዎች ከሞት በኋላ በሕይወት ይኖራሉ በሚሉ ማታለያዎች እንዴት ተጠራርገው ሊወሰዱ
እንደሚችሉ መረዳት አያዳግትም።
ዛሬም እንኳ፣ በመቃብር ያሉ ማንቀላፋታቸውን የተገነዘቡ ሰዎች ከየትኞቹ የተለመዱ
ማታለያዎች የተጠበቁ ናቸው?
የመዳን ተስፋችን በክርስቶስ ላይ የተመሠረተ ነው። ዘላለማዊ ዋጋ ተከፍሎበት በነጻ
የቀረበልንን መሥዋዕትነት እንቀበል ዘንድ በደም የተነከሩ እጆቹ ይጣራሉ። በቅርቡ ክርስቶስ
የእርሱ ለሆኑት ባለ መብትነቱን ሊገልጽ ተመልሶ ይመጣል። ቲቶ፡ 2፡13 ይህን የክርስቶስ
ዳግም ምጽአት “የተባረከ ተስፋችን” ሲል ይጠራዋል።
የሰይጣን ዓላማ ይህንን ተስፋ ማጥፋት ነው። ሰዎችን ከመጽሐፍ ቅዱስ እውነት
እና በክርስቶስ ከሚገኘው መዳን ሊያርቁ የሚችሉ ማንኛውንም ዓይነት ታምራቶችን፣
ምልክቶችንና ድንቅ ነገሮችን ያደርጋል።
“የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት በዚህ ነው” (ራእ. 14፡12)። በመጨረሻው ፍልሚያ
ሰይጣን ሰዎች “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች” እንዳይጠብቁ ወይም “የኢየሱስ እምነት”
እንዳይኖራቸው ወይም ደግሞ ከሁለቱም እንዳይሆኑ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል። ስለዚህ
በምልክቶች፣ በድንቃድንቅ እና ታምራቶች ቢታጀብም፣ ከእነዚህ ከሁለቱ የትሩፋን ባህሪያት
ሊያርቀን ከሚችል አስተምህሮ መጠንቀቅ ይኖርብናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24:23–27፣ 2ቆሮ. 11:13-14፣ 2ተሰ. 2:9–12።
ጥቅሶቹ ስለ ሰይጣን የማታለል ኃይል እና አሠራር ምን ይነግሩናል?
በዘመኑ መጨረሻ ላይ ሰይጣን የመጨረሻውን የማታለል ድርጊት ይፈጽማል፡
“ልዕለ ተፈጥሮ ባህሪ ያላቸው ታምራት የሚሠሩ የአጋንንት ኃይላት አስፈሪ ምልክቶች
በቅርቡ በሰማያት ይገለጣሉ። የዲያብሎስ መናፍስት ወደ ምድር ነገሥታትና ወደ መላው
ዓለም በማምራት በማታለያቸው በማጥመድ እና በማሳቻቸው ጠፍንገው በመያዝ፣ በሰማይ
መንግሥት ላይ በሚደረገው የመጨረሻ ግብግብ ከሰይጣን ጎን እንዲተባበሩ ይገፋፏቸዋል።
በእነዚህ ወኪሎቻቸው አማካይነት ገዢዎችም ሆኑ ተገዢዎች በተመሳሳይ ይታለላሉ።
ግለሰቦች ክርስቶስ ነን ብለው በመነሣት የዓለም ቤዛ የሆነውን ጌታ ክብርና አምልኮ ለራሳቸው
ይወስዳሉ። አስደናቂ የፈውስ ታምራቶችን ያደርጋሉ፣ ከቅዱሳት መጻሕፍት ምስክርነት ጋር
የሚቃረኑ የሰማይ መገለጦች እንዳላቸውም ይናገራሉ።
“በሚመጣው የማጠቃለያ የማታለል ትወና፣ ሰይጣን ራሱ ክርስቶስን መስሎ
ይቀርባል። የተስፋው መደምደሚያ አድርጋ ወደ መሲሑ መምጣት እንደምታንጋጥጥ፣ ቤተ
ክርስቲያን ለረጅም ጊዜ መስክራለች። አሁን ታላቁ አታላይ ክርስቶስ እንደመጣ ያስመስላል።
ሰይጣን፣ በራእይ መጽሐፍ በዮሐንስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ልጅ ባሕሪያት ተመስሎ
በሚያስደንቅ ብርሐን ወይም ነጸብራቅ ግርማ ሞገስ ተላብሶ በተለያዩ የምድሪቱ ክፍሎች
በሰዎች ዘንድ ራሱን ይገልጣል። (ታላቁ ተጋድሎ ገጽጽ 715)።
ክርስቶስ የሚመለስበትን ሁናቴ እንዲሁም ሙታን የሚገኙበትን እውነታ መረዳታችን፣
ከመታለል ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
በቅርቡ ሊ ስትሮቤል በተባሉ ጸሐፊ ለንባብ የበቃው ዘ ኬዝ ኦቭ ሄቨን
የተባለው መጽሐፍ “የሞት አፋፍ ተሞክሮዎች” የተባሉትን መነሻ ሀሳቦች በመውሰድ
ሰዎች ሲሞቱ በሆነ ዓይነት ራሳቸውን የሚያውቁበት ሁናቴ ውስጥ ይቆያሉ በሚል እነዚህን
“ተሞክሮዎች” እንደ “ምስክር” አቅርበዋል። ከመጽሐፋቸው አንድ ምሳሌ ለመጥቀስ
ያህል፡ “የልብ ቀዶ ጥገና እያደረገች የነበረች አንዲት ሴት ከሕይወት በኋላ በነበራት
ተሞክሮ ከወንድሟ ጋር ተገናኝታ ነበር። ጉዳዩ እጅግ አስገርሟት ነበር። ምክንያቱ ወንድም
አልነበራትም። ኋላ ላይ ከህመሟ አገግማ ጉዳዩን ለአባቷ ስትነግራቸው ወንድም እንደነበራት
ለመጀመሪያ ጊዜ ነገሯት። ሆኖም እርሷ ከመወለዷ በፊት መሞቱንም ገለጹላት።””—
Lee Strobel, The Case for Heaven (Grand Rapids, MI:
Zondervan Books, 2021), p. 69. ይሁን እንጂ ስትሮቤል ክርስቲያኖች
የመጨረሻ ሽልማታቸውን የሚቀበሉት ክርስቶስ ዳግም ሲመለስ ብቻ ነው ከሚለው ግልጽ
የመጽሐፍ ቅዱስ አስተምህሮ ጋር ለማስማማት ይቸገራሉ።
እንዲህ የሚል ማስጠንቀቂያ ተሰጥቶናል፡ “የተወደዱ ዘመዶቻቸውን ወይም
ጓደኞቻቸውን መስለው በሚቀርቡ፣ እጅግ አደገኛ የሆኑ ኑፋቄዎችን በሚናገሩ የዲያብሎስ መናፍስት ብዙዎች ግድድሮሽ ይገጥማቸዋል። እነዚህ ጎብኚዎች ስስ ብልቶቻችንን
በመኮርኮር፣ አስመሳይነታቸውን ያስቀጥሉ ዘንድ ታምራትን ይሠራሉ። ሙታን ምንም
እንደማያውቁ እና እነርሱን ተመስለው የሚታዩት የአጋንንት መናፍስት መሆናቸውን
በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት እንቋቋማቸው ዘንድ ዝግጁ መሆን አለብን።
“ ‘በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ያለው የፈተናው
ሰዓት’ (ራእ. 3፡10) ከፊታችን ነው። እምነታቸው በእግዚአብሔር ቃል ላይ በጽናት
ያልተመሠረተ ሁሉ ይታለላሉ፤ ይሸነፋሉ። የሰውን ልጆች መቆጣጠር ይችል ዘንድ ሰይጣን
‘በአመጽ ማታለል ሁሉ’ ይሠራል፤ ማጭበርበሪያዎቹም በቀጣይነት እየጨመሩ ይሄዳሉ።
ዓላማውን የሚያሳካው ግን ሰዎች በፍቃዳቸው ለፈተናዎቹ እጅ መስጠት ሲመርጡ ብቻ
ነው። ከልባቸው የእውነትን ዕውቀት ለማግኘት የሚሹ፣ በመታዘዝም ነፍሳቸውን ለማንጻት
የሚፍገመገሙ፣ የሚችሉትን ሁሉ በማድረግ ለፍልሚያው የሚዘጋጁ እነርሱ፣ ያለ ጥርጥር፣
በእውነት አምላክ በኩል ምሽግ ያገኛሉ። ‘የትግዕሥቴን ቃል ስለጠበቅክ እኔም ደግሞ
እጠብቅሃለሁ’ (ራእ. 3፡10) የሚለው የአዳኙ ቃል ኪዳን ነው። በእርሱ የሚታመን
አንድ ነፍስ በሰይጣን እንዲሸነፍ ከሚተው ይልቅ ሕዝቦቹን ይጠብቅ ዘንድ እያንዳንዱን
መልአክ ፈጥኖ ከሰማይ ቢልክ ይመርጣል።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 640-641)።
1. ሰይጣን በአእምሮ ላይ ተጽዕኖ ለማሳደር የሚጠቀምባቸው ስውር መንፈሳዊ
ተጽዕኖዎች የትኞቹ ናቸው? የመገናኛ ብዙሃን ሚና ምን ይመስላል?
2. አንድ የሚወደውን ሰው በሞት ለተነጠቀና፣ የሞተው ሰው በሰማይ እንደሆነ
ለሚያምን ወዳጅዎ እምነትዎን እንዴት ያካፍሉታል? ተገቢ የሆነው፣ ደግሞም
ያልሆነው አነጋገር የቱ ነው?