የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 14:7፣ 9፣ 12፣ ራእ. 4:11፣ ራእ. 13:1-2፣ ራእ. 12:3–5፣ 17፣ ራእ. 13:11–18።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “‘ቃልህ እውነት ነው፤ በእውነትህ
ቀድሳቸው’ ” (ዮሐ. 17:17)።
ባዮቺፕ ወይም ቬሪ ቺፕ የሚባል በአንጻራዊነት ሲታይ አዲስ የሚባል የሕክምና
መሣሪያ አለ። ይህ የህክምና መሣሪያ በህመምተኛ ውስጥ የሚቀበር ሲሆን የአንዲት
ሩዝ ቅንጣት የሚያክል መጠን አለው። ይህ ባዮቺፕ ስለ ታካሚው የሕክምና ታሪክ
መረጃ በመያዙ፣ ባዮቺፑ በተቀበረበት አካባቢ ስካን በማድረግ በቀላሉ አስፈላጊውን መረጃ
ማግኘት ይቻላል። አንዳንድ ክርስቲያኖች ድርጊቱን የአውሬውን ምልክት ማስፈጸሚያ
ሴራ አካል አድርገው ይቆጥሩታል። ለሌሎች ደግሞ የአውሬው ምልክት እሽግ ምግቦች
ወይም ቁሶች ላይ ከተለጠፉ ባር ኮዶች ጋር የተያያዘ ነው። ወይም ደግሞ ድምራቸው ሲሰላ
666 የሚሰጥ በዶላር ላይ የተጻፉ ምስጢራዊ ቁጥሮች ናቸው ይላሉ። ለሌሎች ደግሞ--
ፍሪሜሴኖሪክ ኦርደር፣ ኢሉሚናቲ፣ ጥቋቁሮቹ የተባበሩት መንግሥታት ሂሊኮፕተሮች እና
የተባበሩት መንግሥታት ናቸው።
የዚህ ሣምንት ትምህርት ዓላማ ከአምልኮ ጋር በተያያዘ ወደፊት የሚከሰተውን
ግጭት መግለጥ ነው። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕግ ለማፍረስ በመሞከር አምላካዊውን
ሥልጣን ይገዳደራል። በተለይ ሰንበት ከአምልኮ ጋር በተያያዘ የዓለም አቀፍ ግጭት መንስኤ
ማዕከል ይሆናል። ሰይጣን ፈጣሪን ስለሚጠላ ሰንበትን ይጠላል። ለክርስቶስ ያለንን
ቁርጠኝነት ለማፍረስ ማስገደድ፣ ጫና እና ኃይል ይጠቀማል። በእውነተኛው እና በሐሰት
የአምልኮ ቀን ላይ የእምነት ግጭቶች ይነሣሉ። ስደት፣ የኢኮኖሚ አድማ፣ እስራት እና የሞት
አዋጅ ቢወጣም እንኳ ለክርስቶስ ታማኝ እንድንሆን እግዚአብሔር የመጨረሻውን ጥሪ
ያቀርባል። የዚህ ሣምንት ጥናት የሱስ በምድር የመጨረሻ ግጭት ውስጥ ማለፍ እንድንችል
በሚሰጠን ብርታት ዙሪያ አጽንዖት ይሰጣል።
የራእይ መልእክት ከምሥጢራዊ ምልክቶች፣ እንግዳ አራዊት እና ለየት ያሉ ተምሳሌቶችም በላይ የላቀ ነው። አፍቃሪ የሆነው አምላክ ለመጨረሻው ትውልድ ስለሰጠው ዘላለማዊ እውነት ይናገራል። በክርስቶስና በሰይጣን መካከል በሰማይ የተጀመረው ግጭት መንስኤ አምልኮ እንደመሆኑ፣ ወደ መጨረሻ መደምደሚያ የሚደርሰውም በአምልኮ ይሆናል። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ራእ. 14:7፣ 9 እና ራእ. 4:11። በዚህ በበጎ እና በክፉ መሃል በሚደረግ ውዝግብ የራእይ ዋና ጭብጥ ምንድን ነው?
በራእይ መጽሐፍ አምልኮ እና ፍጥረት የማይነጣጠሉ ሆነው የተገመዱ ናቸው። ራዕይ 14፡7 የፍጥረትን ሁሉ ጌታ እናመልክ ዘንድ ጥሪ ያደርግልናል። ባለፉት ሁለት መቶ ዓመታት ዓለምን በከባድ ወጀብ ከመታው የዝግመተ ለውጥ አስተምህሮ በተቃራኒ ሰንበት የማንነታችን ዘላለማዊ ማስታወሻ ነው። እኛ ፍጡሮች መሆናችንን እና ፈጣሪያችን ደግሞ ታማኝነታችንን እና አምልኳችንን ለመቀበል የተገባው አምላክ የመሆኑን እውነታ ያለማቋረጥ ያጠናክራል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 12:17 እና ራእ. 14:12። ፈጣሪን ማምለክ የመጨረሻውን መገለጫ የሚያገኘው እንዴት ነው?
የእግዚአብሔርን ትእዛዛት በመጠበቅ ፈጣሪን ማምለክ አውሬውን ከማምለክ
ጋር በቀጥታ ይቃረናል። በታሪክ ከፍተኛ የተባለ ተቃውሞ እና ስደት ቢደርስባቸውም እንኳ
እግዚአብሔር ለእርሱ ታማኝ የሆኑ የመጨረሻው ዘመን ሕዝቦች ይኖሩታል።
“ሰንበት የታማኝነት ታላቁ መፈተኛ ይሆናል፤ ምክንያቱም በተለየ ሁኔታ የተካደ የእውነት
ነጥብ ነውና። የመጨረሻው ፈተናም በሰዎች ላይ በሚሆንበት ጊዜ እግዚአብሔርን በሚያገለግለሉና
በማያገለግሉ መካከል የልዩነት መስመር ይሰመራል። የመንግሥትን ሕግ በመታዘዝ፣ አራተኛውን
ትእዛዝ በመጻረር የሚከበረው ሐሰተኛው ሰንበት፣ እግዚአብሔርን ለሚቃወመው ኃይል
ታማኝነትን በአደባባይ የሚገልጽ ሲሆን፣ ለእግዚአብሔር ሕግ በመታዘዝ እውነተኛውን ሰንበት
መጠበቅ ደግሞ ለፈጣሪ ላለው ታማኝነት ማስረጃ ነው።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 694)።
ራእ. 14፡12 እንደሚናገረው እነዚህ ታማኝ የአዳኙ ተከታዮች “የኢየሱስ
እምነት" ይኖራቸዋል። የየሱስ እምነት በጣም ጥልቅ ከመሆኑ የተነሣ ማየት በማንችልበት
ሁናቴ ውስጥ በእምነት የሚያጸናን ነው። ነገሮችን ማስተዋል ባንችልም እንኳ ጸንተን
እንድንቆም የሚያስችለን ነው። በእምነት የምንቀበለው ይህ የየሱስ ስጦታ፣ በቅርቡ ገቢራዊ
የሚሆነውን ግጭት በጽናት ያሳልፈናል።
የእግዚአብሔር ፈጣሪነት መሠረታዊ ምልክት የሆነው ሰባተኛው ቀን ሰንበት ከቀደመችው
ኤደን ገነት ይመዘዛል። ስለዚህ ሮም እንዳደረገው ለመንጠቅ መሞከር (ዳን. 7፡25)
የእግዚአብሔርን ሥልጣን ከሥረ-መሠረቱ ለመገርሰስ እንደ መሞከር ነው። ጉዳዩ
በመጨረሻዎቹ ቀናት ያን ያህል አወዛጋቢ የሚሆንበትን ምክንያት ማየት እንችል ዘንድ
ይህ እውነት እንዴት ይረዳናል?
በራእ. 13 ስለ አውሬው ምልክት የቀረበው ትንቢት ሰይጣን በእግዚዘብሔር
ላይ ስለሚከፍተው በቁጣ የነደደና አስከፊ ደረጃ ላይ የደረሰ ጦርነት ይነግረናል። የሱስ
በመስቀል ላይ ከሞተበት ጊዜ አንስቶ ጠላት መሸነፉን ቢያውቅም፣ ነገር ግን በተቻለው
መጠን ብዙዎችን ከእርሱ ጋር ይዞ ለመጥፋት ቆርጦ ተነሥቷል። በዚህ ዘመቻ የመጀመሪያ
ስልቱ ማታለል ሲሆን፤ ማታለል የማይሳካለት ከሆነ የኃይል እርምጃ ይወስዳል። አውሬውን
ለማምለክ ወይም ምልክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ ያልሆነ ማንኛውም ሰው ይገደላል ከሚለው
አዋጅ በስተጀርባ ያለው እርሱ ነው።
እንደ እውነቱ ከሆነ፣ የኃይማኖት ስደት አዲስ ነገር አይደለም። አቤል
የእግዚአብሔርን ትእዛዝ በመጠበቁ ምክንያት በቃየን ከተገደለበት ጊዜ አንስቶ አለ። ይህ
በአማኞች መካከል እንኳ ሳይቀር እንደሚከሰት የሱስ ተናግሯል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 16:2፣ ማቴ. 10:22፣ 2ጢሞቴ. 3:12፣ 1ጴጥ. 4:12።
የአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን ምን ደረሰባት? ይህ በተመሳሳይ በመጨረሻው ዘመን
የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ላይ እንዴት ገቢራዊ ይሆናል?
ስደት በመላው የክርስትና ታሪክ የተለመደ ክስተት ነው። በአረማዊው ሮም የደረሰ
ቢሆንም ነገር ግን በተለይ፣ በመካከለኛው ዘመን መጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ክርስቲያኖች ላይ
ግልጽ ጭካኔ የተሞላበት ስደት ደርሷል። የአውሬው ምልክት የዚህ ገሐነማዊ ሰንሰለት
የመጨረሻው አገናኝ ነው። እንደ ቀደሙት ስደቶች ሁሉ፣ እያንዳንዱን ሰው አንድ የሆነ
ዓይነት ተቀባይነት ያገኘ የአምልኮ ሥርዓት እንዲከተል ለማስገደድ ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
ስደቱ የሚጀምረው በኢኮኖሚ ማዕቀብ እንደሆነ ትንቢቱ ያመለክታል። ምልክቱ
ከሌለው በቀር ማንም መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም። ምልክቱን ለመቀበል ፈቃደኛ
ያልሆነ ማንኛውም ሰው ውሎ አድሮ በሞት አዋጁ ስር ይወድቃል (ራዕ. 13፡15፣ 17)።
ዲያብሎስ ክርስቲያን ነን የሚሉ ሰዎች በሕይወታቸው ልል የሆነ አቋም
እንዲያራምዱ በማበረታታት የመጨረሻው ፈተና ሲመጣ የአውሬውን ምልክት እንዲቀበሉ
እያዘጋጀ ይገኛል። መላው ዓለም በአድናቆት አውሬውን እየተከተለ እንደሆነ ሲስተዋል
(ራእ. 13፡3)፣ ትዕይንቱ በድንገት ይለወጥና ትንቢታዊው ካሜራ በአምላክ ሕዝቦች
ላይ ያነጠጣጥራል። ራእ. 14፡12 የሚከተለውን ምስል ይሰጠናል፡ “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ ቅዱሳን የሚታወቁት
በዚህ ነው።” የእግዚአብሔር ሕዝቦች እርሱን የመታዘዝ ሕይወት ይኖራሉ። በዙሪያቸው
ያሉ ነገሮች ሁሉ ሲናወጡ እነርሱ ግን በጸጋው ይቆማሉ። ዓለም አውሬውን ሲከተል እነርሱ
ግን “በጉ ወደሚሄድበት ሁሉ ይከተሉታል” (ራእ. 14፡4)። በክርስቶስ ኃይል በእነርሱ ላይ
በተሰለፉ የሲኦል ኃይላት ላይ ድል ይነሣሉ።
በዘጠነኛው ትምህርት እንደተመለከትነው በመልካም እና በበጎ መካከል የሚካሄደው
ግጭት ዋንኛ መንስኤ አምልኮ ነው። አውሬው ማታለልን የሚጠቀም ሲሆን፣ ይህ አልሳካ
ሲል ወደ ኃይል እና ማስገደድ ያመራል።
ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች በሰንበት አጠባበቅዎ ላይ ልል አቋም እንዲይዙ የሚያደርጉትን
ጫና ከዚህ በኋላ ይቀበላሉ?
ራእ. 13:1-2። ይህ አውሬ ከየት ይነሣል--ሥልጣንስ የሚሰጠው ማን ነው?
የራእይ መጽሐፍ ዘንዶው በዋነኝነት የሚያመለክተው ሰይጣንን እንደሆነ ይገልጻል።
ራእ. 12፡3-5 እንደሚናገረው ዘንዶው ልጁን “ለመዋጥ ፈልጎ” የነበረ ሲሆን፣ ይህ “ወንድ
ልጅ… ወደ እግዚአብሔር ዙፋን ተነጠቀ”። ክርስቶስን ለማጥፋት የሞከረው በአረማዊው ሮም
በኩል እየሠራ የነበረው ዲያብሎስ ነበር (ማቴ. 2፡16–18)። የእግዚአብሔር እና የሰው
ቀንደኛ ጠላት ዓላማውን ለማሳካት በፖለቲካዊ እና ኃይማኖታዊ ተቋማት በኩል ይሠራል።
ስለዚህ አውሬ ኃይል የሚከተለው ተነግሮናል፡ “ዘንዶው የራሱን ኀይልና የራሱን
ዙፋን እንዲሁም ታላቅ ሥልጣን ለአውሬው ሰጠው” (ራእ. 13፡2)።
የሮማው ንጉሠ ነገሥት ቆስጠንጢኖስ ዋና ከተማውን ከሮም ወደ ቁስጥንጥንያ
ተብላ የተጠራችው የአሁኗ ቱርክ ባዛወረ ጊዜ፣ ይህ ትንቢት ከብዙ መቶ ዓመታት በኋላ
በትክክል ፍጻሜ አገኘ። ይህም በሮም ንጉሠ ነገሥት ከተማ የቀድሞው ዙፋን ወይም የቄሣሮች
መቀመጫ ላይ የሥልጣን ክፍተት እንዲከሰት አደረገ።
አይዛክ ባክውስ እንዲህ ብሏል፡ “የሮምን ግዛት መቀመጫ ወደ ቁስጥንጥንያ
በማዛወር… ቆስጠንጢኖስ የሮም ኤጲስ ቆጶስ ራሱን በምድር ላይ ካሉ ሰዎች ሁሉ
ብሎም ከሰማይ አምላክ በላይ ከፍ ከፍ የሚያደርግበትን መንገድ ጠረገለት”—The
Infinite Importance of the Obedience of Faith, and
of Separation from the World, p. 16 (quoted in Le Roy
Edwin Froom, The Prophetic Faith of Our Fathers,
vol. 3, p. 213). ቶማስ ሆብስ እንዳለው “ጳጳሳዊው ሥርዓት በተገረሰሰው የሮም
መንግሥት መቃብር ላይ ዘውዱን ደፍቶ የተቀመጠ መንፈሱ እንጂ ሌላ አይደለም”—
Leviathan (New York: Oxford University Press,
1996), p. 386. በራእ. 13 የተገለጸው ከባሕር የወጣ አውሬ ከሮም ተነሥቶ
ዓለም አቀፍ የአምልኮ ሥርዓት የሚሆን ከሃዲ ኃይማኖታዊ ኃይል ስለ መሆኑ በጥንቃቄ
የተደረጉ ጥናቶች ያመላክታሉ (ራእ. 13፡ 3-4)። ይህ አውሬ ሰው አይደለም፤ ይልቁንም
የእግዚአብሔርን ቃል እውነት በሰብዓዊ ፍጡር ድንጋጌዎች የተካ ኃይማኖታዊ ተቋም ነው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡1። የአውሬውን ኃይል ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው
ቁልፍ ቃል ምንድን ነው?
እግዚአብሔርን መሳደብ ምን ማለት እንደሆነ አስመልክቶ መጽሐፍ ቅዱስ በዮሐ. 10፡
33 እና ሉቃ. 5፡21 ሁለት ምሳሌዎችን ይሰጠናል፡ (1) ሰው አምላክ ነኝ ብሎ ሲያስመስል
ወይም ሲናገር (2) ኃጢአትን ይቅር ለማለት የሚያስችል ኃይል አለኝ ሲል። የሱስ በእርግጥ
አምላክ ስለሆነ እና ኃጢአትን ይቅር የማለት መብት ስላለው እነዚህ በእርሱ ላይ የቀረቡ ክሶች
ፍትሐዊ አልነበሩም። የሮም ጳጳሳዊ ሥርዓት መጽሐፍ ቅዱስ ስድብ ብሎ የሚጠራቸው ሁለት
ልዩ አስተምህሮዎች ያሉት ሲሆን እነርሱም፡ ካህናቱ ኃጢአትን የማስተሰረይ ኃይል--ሊቃነ
ጳጳሳቱ ደግሞ በምድር ላይ አምላካዊ ሥልጣንና መብት አላቸው የሚሉ ናቸው።
የእግዚአብሔር ሕዝቦች አውሬውን ሳይሆን እግዚአብሔርን በማምለክ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። ታዛዥነታቸው በፍቅር ከተሞላ ልባቸው ውስጥ ይመነጫል። እርሱ ምን ያህል ለእነርሱ ቁርጠኛ እንደሆነ ስለሚያውቁ እነርሱም ለእርሱ ቁርጠኛ ናቸው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡5። እነዚህን መለያ ባህሪያት ከታች በተቀመጡት መስመሮች ላይ ይጻፉ።
እግዚአብሔር ትንቢታዊ ጊዜን የምናስተውልበትን ቁልፍ፣ ማለትም--አንድ
ትንቢታዊ ቀን ከአንድ ዓመት ጋር እኩል መሆኑ (ዘኁ. 14፡34፣ ሕዝ. 4፡6) ግልጽ ሆኖ
የቀረበበትን 4ኛውን ትምህርት ያስታውሱ። የዕብራውያኑን 30 ቀናት ተጠቅመን በራእ.
13፡5 የተጠቀሱትን 42 ወራት ስናሰላ 1,260 ትንቢታዊ ቀኖችን ወይም ዓመታትን
እናገኛለን።
ጳጳሳዊው ሥርዓት ከ538 ዓ.ም. እስከ 1798 ዓ.ም. ባሉት ዘመናት ከፍተኛ
ተጽእኖ አሳድሯል። ነገር ግን የናፖሊዮን የጦር አበጋዝ የነበረው ጀነራል በርቴር በ1798 ላይ
ሊቀ ጳጳሱን በምርኮ በመውሰድ የጳጳሳዊው ሥርዓት የበላይነት ሲያከትም፣ የራእይ ትንቢት
ፍጻሜ አገኘ፡ “ማንም የሚማረክ ቢኖር፣ እርሱ ይማረካል፤ ማንም በሰይፍ የሚገደል ቢኖር፣
እርሱ በሰይፍ ይገደላል። ይህም የቅዱሳን ትዕግሥትና እምነት የሚታየው በዚህ እንደ ሆነ
ያስገነዝባል” (ራእ. 13፡10)። በጳጳሳዊው ሥርዓት ላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰ ቢሆንም
ለሞት የሚዳርግ ግን አልነበረም። በራእ. 13፡12 መሠረት ለሞት ያደርስ የነበረው ቁስሉ
ይፈወሳል። የጳጳሳዊው ሥርዓት ተጽዕኖ እንደገና በመላው ዓለም ይሰፍናል።
ዛሬ የዓለም መሪዎች ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን የሮም ቤተ ክርስቲያን አምባሳደር አድርገው
በመቀበል ቫቲካንን አዘውትረው ይጎበኛሉ። ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ አለመረጋጋት
በሰፈነባት በዚህች ዓለም፣ የሮማ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ሰዎችን አንድ ላይ ማሰባሰብ የሚችሉ
የዓለም አቀፍ የሥነ ምግባር መሪ ተደርገው ይቆጠሩ ዘንድ ዝግጅቱ ከወዲሁ እየተጧጧፈ
ይገኛል። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ቤኔዲክት 16ኛ በጎርጎሮሳውያኑ ሰኔ 6 ቀን 2012 ዓ.ም. በሮም
ቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ከአሥራ አምስት ሺህ ለሚበልጡ ሰዎች ባደረጉት ንግግር፣
“እሑድ የጌታ፣ የወንዶች እና ሴቶች ልጆች ቀን ነው፤ በዚህ ቀን ሁሉም ሰው ነጻ መሆን መቻል
ይኖርበታል--ለቤተሰብ ነጻ እንዲሁም ለእግዚአብሔር ነጻ። እሁድን ስንከላከል ለሰው ልጆች
ነጻነት ጥብቅና እንቆማለን።”--—https://www.vatican.va/content/
benedict-xvi/en/au diences/2012/documents/hf_ben-
xvi_aud_20120 606.html
ታላቁ ተጋድሎ የተሰኘው መጽሐፍ ይህ እንቅስቃሴ አንድ ቀን በመጨረሻ ወዴት
እንደሚያመራ በግልጽ ያሳየናል፡ “የመጽሐፍ ቅዱስን ሰንበት የሚያከብሩ እነርሱ፣ የሕግና
የሥርዓት ጠላቶች የኅብረተሰብን ግብረገብነት ገደቦች በመሰባበር ሥርዓተ አልበኝነትንና
ብልሹነትን በማስከተል የእግዚአብሔርን ፍርድ በምድር ላይ የሚያስመጡ ተብለው
ይወገዛሉ። ትክክለኛውን ድርጊት ልቅም አድርጎ ለመፈጸም የሚያደርጉት ጥንቃቄ፣
መንቻካነት፣ ግትርነትና የሥልጣን ንቀት ይባላል። የመለኮታዊውን ሕግ መጠይቆች
(ግዴታዎች) የሚክዱ አገልጋዮች፣ በእግዚአብሔር እንደተቀቡ አድርገው ለመንግሥት
ባለሥልጣናት ስለመታዘዝ ያለውን ኃላፊነት ከመድረክ ያትታሉ። በሕግ አውጪ አዳራሾችና
ፍርድ ቤቶች፣ ትእዛዝ አክባሪዎች፣ ያልሆኑትን መልክ ተሰጥቶአቸው ይፈረድባቸዋል።”
(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 678-679)።
ምንም እንኳ አሁን እንዲህ ዓይነት ነገር ሲከሰት ማየት ከባድ ሊመስል ቢችልም፣
ዓለማችን በምን ያህል ፍጥነት እየተለዋወጠች እንደሆነ ማየቱ ግን አስፈላጊ ነው።
የመጨረሻው ዘመን ክስተቶች በምን ያህል ፍጥነት ሊደርሱብን እንደሚችሉ እነዚህ
ለውጦች ምን ሊነግሩን ይገባል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡ 11–18። ይህ ሁለተኛው አውሬ ከራእይ አሥራ ሦስቱ አውሬ በምን ይለያል?
የመጀመሪያው አውሬ ከባሕር የሚወጣ ሲሆን፣ ሁለተኛው አውሬ ደግሞ
“ከምድር” ይወጣል (ራእ. 13፡11)። ባሕር “ወገኖች፣ ሰዎች፣ ሕዝቦችና ቋንቋዎችን”
ይወክላል (ራእ. 17፡15)። በመሆኑም ምድር ብዙ ሕዝብ የማይኖርበትን የዓለም ክፍል
ይወክላል። ይህ ሁለተኛው አውሬ የሚነሣው የመጀመሪያው አውሬ ሥልጣን በሚይዝበት
ትንቢታዊ ዘመን መጨረሻ አካባቢ ነው (ራእ. 13፡5)። ይኸውም በ1798 ዓ.ም አካባቢ
እውቅና ያገኛል ማለት ነው።
ዩናይትድ ስቴትስ ኦቭ አሜሪካ ከዚህ መግለጫ ጋር በትክክል ትስማማለሽ።
በጎርጎሮሳውያኑ 1776 ነጻነቷን አወጀች። ሕገ መንግሥቷን በ1789 ካጽደቀች በኋላ
በ19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ አካባቢ የዓለም ልዕለ ኃያልነትን እውቅና አገኘች።
ዮሐንስ ሲቀጥል እንዲህ ይላል፡ “ከዚያም ሌላ አውሬ ከምድር ሲወጣ አየሁ፤
እርሱም እንደ በግ ሁለት ቀንዶች ነበሩት፤ ነገር ግን እንደ ዘንዶ ይናገር ነበር” (ራእ. 13፡
11)። ቀንድ በመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት የኃይል ተምሳሌት ነው። ይህ አውሬ ከመጀመሪያው
አውሬ በተለየ መልኩ በቀንዶቹ ላይ ዘውድ የለውም፤ ይህ ደግሞ አገዛዙ ንጉሣዊ አለመሆኑን
ያመለክታል። ሁለቱ ቀንዶች የዩናይትድ ስቴትስ ኃያልነት እና ስኬት ምንጭ የሆኑትን ሁለቱን
ዋና ዋና የአስተዳደር መርኅዎች ማለትም ፖለቲካዊና ኃይማታዊ ነፃነትን ይወክላሉ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡11-12። በዚህ አውሬ ላይ ምን ዓይነት ለውጥ
ይመለከታሉ--የሚናገረውስ እንዴት ነው?
ይህ የዋህ፣ በግ መሰል መንግሥት በመጨረሻ እንደ ዘንዶ ይናገራል። “በመጀመሪያው
አውሬ ስም በሙሉ ሥልጣን” (ራእ. 13፡12) በመሥራት የእምነት ነጻነት መርኅዎቹን
ርግፍ አድርጎ ይተውና “ምድርና በእርሷም የሚኖሩ ሁሉ፣ ለሞት ከሚያደርሰው ቍስል
የዳነውን የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልኩ” ያደርጋል (ራእ. 13፡12)። ዩናይትድ
ስቴትስ በምድር ላይ ያሉ ሁሉ ለሊቀ ጳጳሱ መንፈሳዊ እና ዓለማዊ ሥልጣን ዕውቅና በመስጠት
የመጀመሪያውን አውሬ ያመልኩ ዘንድ ግንባር ቀደም ሆና በመሰለፍ ጥያቄ ታቀርባለች።
በዚህ ትንቢት መሠረት ዩናይትድ ስቴትስ ለአውሬው ምስል በማቆም በቤተ ክርስቲያን እና
በመንግሥት መካከል ጥምረት እንዲፈጠር እና ሁሉም ሰው ለምስሉ እንዲሰግድ ፍላጎቷ
ይሆናል።
ዛሬ በአሜሪካ ስላለው የፖለቲካ አለመረጋጋት አሰብ ያድርጉ። ይህ ትንቢት አንድ ቀን
ወደ ፍጻሜው ሊያመራ የሚችለው እንዴት ነው?
ለአውሬው እና ለምስሉ መስገድን አስመልክቶ በዳን. 3 እንደተጠቀሰው-
-ሲድራቅ፣ ሚሳቅ እና አብደናጎ ከወርቅ ለተሠራው ምስል እንዲሰግዱ ያለበለዚያ ግን
በእቶን እሳት ውስጥ እንዲጣሉ የባቢሎን ንጉሥ አዝዞ ነበር። የጥንቷ ባቢሎን፣ ዘመናዊቷ
ባቢሎን—ጉዳዩ ደግሞ አምልኮ። እውነተኛ አምልኮ የሚመነጨው--ከእግዚአብሔር ቃል
ከሚማር አእምሮ፣ በፍቅሩ ከተለወጠች ነፍስ፣ እና በመንፈሱ ከተሞላ ልብ ነው። ያን ጊዜ
“ይህን ዓለም አንመስልም” ይልቁንም በቃሉ ውስጥ በሚገኘው የአምላክ ፈቃድ እንኖራለን።
ደኅንነታችን ይኸው ብቻ ነው!
“እግዚአብሔር ፈቃድንም ሆነ ሕሊናን ፈጽሞ አያስገድድም። ሰይጣን ግን
በቋሚነት የሚያዘወትረው መንገድ--ማታለል ያልቻላቸውን ሰዎች በቁጥጥሩ ስር
ለማድረግ በጭካኔ ማስገደድ ነው። በርፍርሐትም ሆነ በኃይል ሕሊናን ለመግዛትና ለራሱ
ክብር ለማትረፍ ይጥራል። ይህንም ለማሳካት በኃይማኖታዊና በመንግሥታዊ ባለ ሥልጣን
በኩል በመሥራት፣ የእግዚአብሔርን ሕግ በመገዳደር የሰብዓዊ ፍጡርን ሕግጋት አስገዳጅ
እንዲያደርጉ ያንቀሳቅሳቸዋል። (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 678)።
“ከፊታቸው ባለው ፈተና ጸንተው ለመቆም ይቻላቸው ዘንድ፣ በቃሉ የተገለጸውን
የእግዚአብሔር ፈቃድ የግድ መረዳት አለባቸው፤ በትክክል ሊያከብሩት የሚችሉት
የባህሪው፣ የመንግሥቱና የዓላማው ትክክለኛ መረዳት ሲኖራቸው፣ እነዚያም በተስማማ
ሁኔታ ሲተገበሩ ብቻ ነው። በመጨረሻው ታላቅ ጦርነት ጸንተው የሚቀሩት የመጽሐፍ ቅዱስ
እውነቶች አእምሮአቸውን ያፈረጠሙ ብቻ ናቸው።” ታላቁ ተጋድሎ ገጽጽ 680-681)።
“ነገር ግን የተሐድሶዎች ሁሉ መሠረት፣ የአስተምህሮዎች ሁሉ ደረጃ መለኪያ
አድርጎ መጽሐፍ ቅዱስን እና መጽሐፍ ቅዱስን ብቻ የሚጠብቅ ሕዝብ እግዚአብሔር
በምድር ይኖረዋል። የምሑራን አስተያየቶች፣ የሣይንስ ድምዳሜዎች፣ እንደሚወከሉአቸው
አብያተ ክርስቲያናት በቁጥር በርካታ የሆኑትና የሚጋጩት የመንፈሳዊ ጉባዔ እምነቶችና
ውሳኔዎች፣ የአብላጫ ድምፅ--እነዚህ ሁሉ፣ ማንኛቸውም ቢሆኑ አንድን ኃይማኖታዊ
ጉዳይ ለመቀበልም ሆነ ላለመቀበል አንደ መረጃ ሆነው ሊወሰዱ አይገባቸውም።
ማንኛውንም አስተምህሮ ወይም መመሪያ ከመቀበላችን በፊት፣ ድጋፍ የሚሆነው፣ ግልጽ
የሆነ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ የሚል (ቃል) መጠየቅ ይገባናል። (ታላቁ ተጋድሎ
ገጽ፡ 682)።
1. የክርስቶስን ዳግም ምጽአት በተስፋ እየተጠባበቅንና ይህን ተስፋ በሌሎች ላይ
አላስፈላጊ ጭንቀት ወይም መደናገጥ ሳንፍር ማካፈል የምንችለው እንዴት ነው?
2. በአምልኮ ዙሪያ በሚነሡ ጥያቄዎች ላይ በቂ ትኩረት ያድርጉ። የዕለት ከዕለት
ሕይወታችን እና ተግባራችን ማንን ወይም ምን እያመለክን እንደሆነ አስመልክቶ
የሚለን ነገር ይኖረዋል?
3. የወደፊቱን ጊዜ በፍርሃት ሳይሆን በልበ ሙሉነት ለመጋፈጥ፣ ራሳችንንም ሆነ
ሌሎችን መርዳት የምንችለው እንዴት ነው?
4. የመጨረሻዎቹን ቀናት ክስተቶች መረዳታችን ዛሬ በሕይወታችን ምን ተግባራዊ
ለውጥ ያመጣል?