የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 8:32፣ ሕዝ. 20:12፣ 20፣ ራእ. 7:1-2፣ ራእ. 14:1፣ ኢዮኤል 2:21–24፣ ሆሴ. 6:3፣ ያዕ. 5:7-8፣ ራእ. 18:1–4።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “እውነትን ግዛት እንጂ አትሽጣት፤ ጥበብን፣
ተግሣጽንና ማስተዋልን ገንዘብህ አድርግ” (ምሳ. 23፡23)
ለእረፍት ዩኒቨርሲቲ ሲዘጋ መኪናዋን እያሽከረከረች ወደ ቤት እየመጣች ያለች
ሴት ልጅ አለችዎት እንበል። ቤት መድረሷን እየተጠባበቁ እያሉ፣ ሜትሪዮሎጂ ስለ
አየሩ ሁኔታ የሚሰጠውን ትንታኔ በጭንቀት ይከታተላሉ። የአየሩ ጠባይ በፍጥነት
እያሽቆለቆለ መሄዱን ሲረዱ ሀሳብ ይገባዎታል። አውሎ ነፋስ አዘል ደመና ሰማዩን ሸፍኖታል።
ኃይለኛ ነፋስ ይነፍሳል። ሰማያት ተከፍተው ዝናቡ እንደ ጉድ ይወርዳል። ነፋሱና ውሽንፍሩ
ዛፎቹን እዚህም እዚያም ገነዳድሶ መጣል ጀምሯል። ብዙም ሳይቆይ ወደ ቤት የሚያደርሰው
ዋናው መንገድ እንደማያሳልፍ ሆኖ ተዘጋ። ከዚያም፣ ከጎረቤትዎ አንዱ ሁለተኛ አማራጭ
መንገድ በመጠቀም መምጣት እንደሚቻል ሲናገሩ ይሰማሉ። መኪኖች አንዳንድ መንገዱ
ላይ የወደቁ ዛፎች ቅርንጫፎችን እየታከኩ ማለፍ ይችላሉ። ምንም እንኳ ስልክ ደውሎ
በድምፅ መነጋገር አስቸጋሪ ቢሆንም፣ ከልጅዎ ጋር የጽሑፍ መልእክት እየተለዋወጡ
እንዴት ቤት መድረስ እንደምትችል አስፈላጊውን መረጃ ማድረስ ችለዋል።
የሱስ ከምንም ነገር በላይ በሕይወት ወጀቦች መካከል አሳልፎ ወደ ቤት ሊያደርሰን
ይፈልጋል። ኤለን ጂ. ኋይት በዚህ ዙሪያ እንዲህ ትላለች፡ “ምሕረት የለሽ ቁጡ ወጀብ
ከፊታችን እየመጣ ነው። ይህን ለመጋፈጥ ዘጋጅተናል?— Testimonies for
the Church, vol, 8, p. 315. የክርስቶስ ሕይወት፣ ሞት፣ ትንሣኤ እና
የሰማያዊው መቅደስ አገልግሎት ዓላማ ቤታችን መድረሳችንን የተረጋገጠ ማድረግ ነው።
የዳንኤል እና የራእይ ትንቢታዊ መልእክቶች በተለይ በመጨረሻው ዘመን ለሚገኙ ሕዝቦች
የተሰጡ መለኮታዊ መመሪያዎች ሲሆኑ፤ በሕይወት ወጀቦች ውስጥ አልፈን አንድ ቀን
በአፍቃሪው አዳኝ እቅፍ ውስጥ እንገባ ዘንድ እኛን ለመርዳት ተበርክተዋል።
የዚህ ሳምንት ትምህርት ዓላማ ትንቢታዊው ቃል ስለ ምድር ታሪክ መደምደሚያ
ክንውኖች የሚናገረውን መግለጥ እና በምድር የመጨረሻ ውዝግብ ውስጥ አሳልፎ ወደ ቤት
የሚያደርሰንን ተጨማሪ የክርስቶስ ብርታት ማግኘት ነው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ምሳ. 23:23፣ ዮሐ. 8:32፣ ዮሐ. 17:17። በጥቅሶቹ ውስጥ የምናገኘው የጋራ ነጥብ ምንድን ነው?
በእውነት እና በሐሰት መካከል ለዘመናት የማያባራ ተጋድሎ ሲደረግ ኖሯል። ሰይጣን
ሐሰተኛ እና የሐሰት አባት ነው (ዮሐ. 8፡44)። የእውነት ሁሉ አመንጪ የሆነው የሱስ
እንዲህ ሲል ተናግሯል፡ “ ‘እኔ መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት ነኝ’ ” (ዮሐ. 14፡
6)። ከሰይጣን ማታለያዎች ነፃ የሚያወጣን እውነት በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ ይገኛል።
መጽሐፍ ቅዱስ የሰይጣንን ስልት ጭምብል በመግለጥ አምላካዊውን እቅድ ይፋ ያደርጋል።
አምላካዊው ቃል ለእግራችን ብርሃን ነው (መዝ. 119፡105)። ባለ መዝሙሩ እንዲህ
ሲል ያውጃል፡ “የቃልህ ትርጓሜ ያበራል፤ አላዋቂዎችንም አስተዋዮች ያደርጋል” (መዝ.
119፡130)። “ቃልህ በሙሉ እውነት ነው፤ ጻድቅ የሆነው ሕግህም ዘላለማዊ ነው።”
(መዝ. 119፡160)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጴጥ. 1፡16-21። ሐዋርያው ትንቢትን አስመልክቶ ምን ማረጋገጫ
ሰጥቶናል? የአምላካዊውን ትንቢታዊ ቃል አስፈላጊነት ለማሳየት የትኛውን ምሳሌ
ተጠቅሟል?
“በሰዎች ጥበብ የተፈጠረውን ጥበብ” አልተከተልንም። የአምላካዊው ቃል
ትንቢቶች ከፊታችን ባለው መንገድ ላይ ያበሩልናል። እውነትን ከስህተት እንድንለይ
ይረዱናል። መጽሐፍ ቅዱስ ባይኖረን ኖሮ ለሰብዓዊው ፍላጎት የተተውንና በቀላሉ መታለል
የምንችል በሆንን ነበር። “ከሐሰተኛ መምህራንና ከጨለማ መናፍስት አሳሳች ኃይል ተጽእኖ
መከላከያቸው ይሆን ዘንድ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ወደ መጽሐፍ ቅዱስ ተመርተዋል።
የመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ንግግሮች ማጭበርበሪያዎቹን ስለሚገልጥበት፣ ሰዎች የመጽሐፍ
ቅዱስ እውቀት እንዳያገኙ ለማገድ ሰይጣን ማግኘት የሚችለውን እያንዳንዱን መሣሪያ
ይጠቀማል… የመጨረሻው ታላቅ ማታለያው በቅርቡ በፊታችን ይከፈታል። የክርስቶስ
ተቃዋሚ ወይም አንቲ ክራይስት አስደናቂ ሥራዎቹን ሊሠራ በቅርቡ በፊታችን ሊገለጥ
ነው። አስመስሎ የሚሠራው እውነትም እጅግ ስለሚመስለው፣ በቅዱስ መጻሕፍት ካልሆነ
በስተቀር በሁለቱ መካከል ያለውን ልዩነት ማወቅ የማይቻል ይሆናል። እያንዳንዱ ዓርፍተ
ነገር፣ እያንዳንዱ ተአምር በምስክሩ (በመጽሐፍ ቅዱስ) መፈተን አለበት… በመጨረሻው
ታላቅ ጦርነት ጸንተው የሚቀሩት በመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች አእምሮአቸውን ያፈረጠሙ
ብቻ ናቸው። የሚበረብረው ፈተና ወደ እያንዳንዱ ነፍስ ይመጣል። ከሰዎች ይልቅ
እግዚብሔርን ልታዘዝን? ወሳኙ ሰዓት ደርሷል፤ እግሮቻችን በማይለወጠው በእግዚአብሔር
ቃል ቋጥኝ ላይ ተተክለዋልን? የእግዚአብሔርን ትእዛዛትና የየሱስን ኃይማኖት በመደገፍ
ጸንተን ለመቆም ተዘጋጅተናልን?” ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 680-681)።
ከላይ በትምህርተ ጥቅስ የቀረቡትን ጥያቄዎች ልብ ብለው ይመልከቱ። በመጨረሻው ቀውስ
ውስጥ ለመቆም የሚያስችለን ምንድን ነው? የእግዚአብሔርን ቃል እንዳናጠና ሐሳባችንን
የሚያዛባው ምንድን ነው? ለግል ደስታ ብለን እውነትን የምናቃልላት እንዴት ነው?
አምልኮን መሠረት ባደረገው ከፊታችን ባለው የቀውስ ወቅት፣ የእግዚአብሔር ታማኝ ሕዝቦች በዓለማዊ ተጽእኖዎች አይሸነፉም (ራእ. 14፡12)። በመንፈስ ቅዱስ ይታተማሉ (ኤፌ. 4፡30) በመሆኑም፣ ሊናወጡ አይችሉም። በጥንት ዘመን ማኅተሞች የሰነዶችን ሕጋዊ ትክክለኛነት ይመሰክሩ ነበር። ማኅተሞቹ በዓይነታቸው የተለዩ፣ የዚያ አካል ምልክቶች ነበሩ። የመጨረሻው ውዝግብ አምልኮን ማዕከል የሚያደርግና በሕጉ ውስጥ በተገለጠው የእግዚአብሔር ሥልጣን ላይ የሚያተኩር እንደመሆኑ፣ የእግዚአብሔር ማኅተም በሕጉ ውስጥ ይካተታል ብለን እንጠብቃለን (ኢሳ. 8፡16)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 20፡8-11። በሰንበት ትእዛዝ ውስጥ ምን ዓይነት የማኅተም ባህሪያት ተካትተዋል?
በመቀጠል እንደቀረበው አንድ ሕጋዊ ማኅተም ሦስት ባህሪያት አሉት፡ (1) የማኅተሙ ባለቤት ስም፡ “እግዚአብሔር አምላክ” (2) ማዕረግ፡ “ፈጣሪ”፣ (3) ግዛት “ሰማይና ምድር፤ ባሕርና በውስጡም ያሉት ሁሉ”። ማኅተም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አንዳንዴ ምልክት በሚል ተጠቅሷል (ሮሜ 4፡11)። ሁለቱ ቃላት--አንዱ ሌላውን የሚተካ ከመሆኑ አኳያ ተለዋዋጭ ናቸው። በሕጉ አማካይ ላይ የሚገኘው የእግዚአብሔር ምልክት ወይም ማኅተም የሆነው ሰንበት፣ አምልኮን መሠረት አድርጎ ለሚነሣው የመጨረሻው ውዝግብ ማዕከል ይሆናል (ሕዝ. 20:12፣ 20፣ ራእ. 12:17)። ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ራእ. 7፡1-2፣ ራእ. 14፡1፣ ራእ. 13፡16-17። ሰዎች የእግዚአብሔርን ማኅተም እንዲሁም የአውሬውን ምልክት የሚቀበሉት በምናቸው ላይ ነው? ልዩነት የኖረው ለምን ይመስሎታል?
የእግዚአብሔር ማኅተም የሚታተመው በግንባር ላይ ነው። ግንምባር የአእምሮ
ተምሳሌት እንደመሆኑ፣ ታስቦበት የሚደረግ ውሳኔን ያመለክታል።
የአውሬውን ምልክት በግምባር ወይም በእጅ መቀበል፣ ሰዎች የማሰብ ችሎታ
እንዳላቸውና በራሳቸው ምርጫ የሰይጣንን ውሸት እንደሚቀበሉ አሊያም፣ በሌላ በኩል
እንዳይገደሉ ሲሉ ከሐሰት አምልኮ ጋር የሚፈጥሩትን ስምምነት ይጠቁማል።
ዲያብሎስ ለእግዚአብሔር ታዛዥ የሆኑ ወገኖችን ይጠላል። ዘንዶው (ሰይጣን)
“የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስም ታማኝ ሆነው በትዕግሥት የሚጸኑ”
(ራእ. 14፡12) ትሩፋን ላይ ጦርነት ያውጃል። እነርሱ ለክርስቶስ ባላቸው ታማኝነት
ጸንተው የቆሙ ሕዝቦች ናቸው።
የመጨረሻው ቀውስ ሲመጣ ተዘጋጅቶ ለመገኘት በየዕለቱ ለጌታ ታማኝ መሆን ቁልፍ
ተግባር የሆነው ለምንድነው?
በመጨረሻዎቹ ቀናት አምልኮን መሠረት ያደረገ ከፍተኛ ውዝግብ ይነሣል።
ፈጣሪን እናመልካለን ወይስ ለአውሬው እና ለምስሉ እንሰግዳለን? መሃል ሰፋሪ የሚባል
ነገር የለም። በራእ. 14 የቀረበው የመጀመሪያው መልአክ “ሰማይንና ምድርን፣ ባሕርንና
የውሃ ምንጮችን ለፈጠረው ስገዱ” (ራእ. 14፡7) ሲል አጥብቆ ያሳስባል። ሦስተኛው
መልአክ ለሰማያዊው ተማጽኖ የላቀ አጽንኦት በስጠት አውሬውን ማምለክ የሚያስከትለውን
አስከፊ መዘዝ ይገልጻል። “እርሱ ደግሞ ምንም ነገር ሳይቀላቀልበት በቍጣው ጽዋ ውስጥ
የተሞላውን የእግዚአብሔርን ቍጣ ወይን ጠጅ ይጠጣል” (ራእ. 14፡10)። በአንጻሩ፣
ፈጣሪን የሚያመልኩ ወገኖች፡ “የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና ለኢየሱስም
ታማኝ” (ራእ. 14፡12) የሆኑ--በሚል ተገልጸዋል።
ፍጥረት የእውነተኛው አምልኮ መሠረት ነው (ራእ. 4፡11)። እግዚአብሔር
ሁሉንም ነገር በየሱስ ክርስቶስ መፍጠሩን ተከትሎ (ኤፌ. 3፡9) ሰይጣን ፈጣሪን
ይጠላል፤ በዚህ የተነሣ በምድራዊ ኃይሎች አማካይነት የፍጥረት መታሰቢያ የሆነውን ሰንበት
ለመለወጥ ሞከረ (ዳን. 7፡25)። በእግዚአብሔር ሕግ ላይ የሚያነጣጥረው መጪው
የግጭት ትኩረት--ሥልጣን ይሆናል። ሰይጣን የሰንበትን አምልኮ ማስወገድ ከቻለ፣ የእርሱ
ሥልጣን ከእግዚአብሔር የላቀ መሆኑን በይፋ ያውጃል። ይህንንም ለማሳካት ሰይጣን መላው
ዓለም ሐሰተኛውን ሰንበት እንዲቀበል ለማሳመን ወይም ለማስገደድ ይሞክራል።
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው ይህ ሁኔታ ሲከሰት ማየት ለጊዜው ከባድ ቢመስልም፣
ዓለም በአስገራሚ ሁኔታ እየተለወጠች ትገኛለች። የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ዓለማችን በአንድ
ጀንበር የተለየች ስፍራ ልትሆን እንደምትችል አሳይቶናል። ምንም እንኳ ወደ አውሬው ምልክት
የሚያደርሰውን ዝርዝር ሁኔታ ባናውቅም፣ ለመገመት ግን እጅግ ከባድ አይደለም። ዓለም በጣም
ያልተረጋጋ ሁኔታ ላይ ትገኛለች። እናም አሁን ካለው አስደናቂ የቴክኖሎጂ ግስጋሴ አኳያ መጽሐፍ
ቅዱስ የሚያስጠነቅቀው ነገር ሁሉ ዛሬ ከምንገምተው በላይ በፍጥነት ሊፈጸም ይችላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 13፡13-17። የአውሬውን ምልክት በማይቀበሉ ሰዎች ላይ ምን
ዓይነት ልዩ ቅጣቶች ይደርስባቸዋል?
አውሬውን እና ምስሉን ከመከተል በተቃራኒ ለክርስቶስ ታማኝ የሆኑ ሰዎች ኢኮኖሚ
ነክ ቅጣቶችና የሞት ዛቻ ይደርስባቸዋል። ሙሰኝነት፣ የሥልጣን ጥም፣ ጠባጫሪነት--ሁሌም
ቢሆን ከሰብዓዊው ፍጡር ጋር ሳይነጣጠሉ ይኖራሉ። ምንም እንኳ የመጨረሻዎቹ ክስተቶች
እንዴት ፍጻሜ እንደሚያገኙ እስካሁን ባናውቅም፣ የመጨረሻውን የስደት ወቅት በዓይነ
ኅሊናችን ለመቃኘት ግን ያን ያህል ከባድ መሆን የለበትም። ምንም እንኳ የተጻፉት ሙሉ
በሙሉ በሌላ ዐውድ ቢሆንም፣ በዮሐንስ መልእክት ላይ የምናገኛቸው እነዚህ ቃላት ሁሉንም
ይገልጻሉ። ዮሐንስ ስለ የሱስ ሲናገር የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡ “በሰው ውስጥ ያለውን ያውቅ
ስለ ነበር፣ ማንም ስለ ሰው እንዲመሰክርለት አላስፈለገውም” (ዮሐ. 2፡25)።
ስለ ሰብዓዊው ፍጡር ምግባረ ብልሹነት እና ሰዎች ሊፈጽሙት ስለሚችሉት ክፋት አሰብ
ያድርጉ። ይህ ሁኔታ የመጨረሻዎቹ ክስተቶች ምን ያህል በቀላሉ መፈጸም እንደሚችሉ
እንዴት ያሳየናል? በተጨማሪ፣ ይህ አሳዛኝ እውነት የገዛ ልቦቻችንን ስለ መጠበቅ ምን
ሊያስተምረን ይገባል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢዮኤል 2:21–24፣ ሐዋ. 2:1–4፣ 41–47። በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን ፍጻሜ ያገኘው ትንቢት የቱ ነበር? ምን ዓይነት ተጽእኖ ነበረው?
በበዓለ ሃምሳ የፈሰሰው መንፈስ ቅዱስ ቤተ ክርስቲያንን በከፍተኛ ኃይል አስጀመረ።
በአንድ ቀን ብቻ 3ሺ ሰዎች ጌታን ተቀበሉ። የሰዎችን ልብ ይለውጥ በነበረው አምላካዊ ጸጋ
በታምራት ላይ ታምራት ይፈጸም እንደነበር የሐዋርያት ሥራ ዘግቧል፡ “ይሁን እንጂ ቃሉን ከሰሙት
መካከል ብዙዎቹ አመኑ፤ የወንዶቹም ቍጥር ወደ አምስት ሺሕ ከፍ አለ” (ሐዋ. 4፡4)።
ለመጸለይ የተሰበሰቡት 120 ምእመናን ብቻ ቢሆኑም፣ ጸሎት ታላቅ ለውጥ አስከተለ። ቤተ
ክርስቲያኗ በአሰገራሚ ፍጥነት በሺህ የሚቆጠሩ አማኞችን ጨመረች። “የእግዚአብሔርም
ቃል እየሰፋ ሄደ፤ የደቀ መዛሙርቱም ቍጥር በኢየሩሳሌም እጅግ እየበዛ ሄደ፤ ከካህናትም
ብዙዎቹ ለእምነት የታዘዙ ሆኑ” (ሐዋ. 6፡7)። ደቀ መዛሙርቱ በየሩሳሌም ጽኑ ስደት
በደረሰባቸው ጊዜ፣ “የተበተኑትም በሄዱበት ሁሉ ቃሉን ሰበኩ” (ሐዋ. 8፡4)። በይሁዳ፣
በሰማርያና በገሊላ ሁሉ አብያተ ክርስቲያናት ተተከሉ (ሐዋ. 9፡31)። ሐዋርያው ጳውሎስ
ከተለወጠ በኋላ ክርስቶስን በመላው የሜድትራንያን ዓለም አወጀ። በተሰሎንቄ ወንጌልን
ይቃወሙ የነበሩ አንዳንድ አይሁዶች የሚከተለውን አስገራሚ ቃል ሲናገሩ ተደምጠው ነበር፡ “
‘እነዚህ ሰዎች ዓለሙን ሁሉ ሲያውኩ ቆይተው፣ አሁን ደግሞ ወደዚህ መጥተዋል’ ” ሐዋ.
17፡6)። ደቀ መዛሙርቱ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አማካኝነት፣ በአንጻራዊ ሲታይ አጭር በሆነ
ጊዜ ውስጥ በዚያን ዘመን ይታወቅ ወደ ነበረው ዓለም ደረሱ። ኢዩኤል ስለ መጀመሪያው
ዝናብ የተናገረው ትንቢት በጴንጤቆስጤ ዕለት ፍጻሜ ያገኘ ሲሆን፣ ነገር ግን የኋለኛው ዝናብ
የምድርን የመጨረሻ መከር ለማዘጋጀት ከዚያ በላቀ ኃይል ይወርዳል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘካ. 4:6፣ ዘካ. 10:1፣ ሆሴ 6:3፣ ያዕ. 5:7-8። በነዚህ
ጥቅሶች መሠረት በዚህ ምድር የእግዚአብሔር ሥራ የሚጠናቀቀው እንዴት ነው?
“የፊተኛው” እና “የኋለኛው” ዝናብ የተሰኙት ቃላት የተወሰዱት ከእስራኤል
የመኸር ዑደት ነው። የመጀመሪያው ወይም የፊተኛው ዝናብ ዘሩን ለማብቀል ይዘንብ
ነበር። ሁለተኛው ወይም በጸደይ ወራት የሚዘንበው የኋለኛው ዝናብ፣ መኸሩ እንዲደርስ
ያደርጋል… ይህ ደግሞ ወንጌልን ለማወጅ በመንፈስ ቅዱስ የተሠራውን ሥራ ይገልጻል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 18:1–4፣ ዕንባቆ. 2:14፣ ማቴ. 24:14። በምድር ላይ ያለው የእግዚአብሔር ሥራ ፍጻሜ የሚያገኘው እንዴት ነው?
ስለ ባቢሎን መውደቅ የተናገረው መልአክ “ታላቅ ሥልጣን” አለው። እንደ ራእይ
14 መላእክት ሁሉ ይህ መልአክም ሰብዓዊ መልእክተኞችን ይወክላል። ይህ መልአክ
የእግዚአብሔርን ክብር በሙላት መግለጹን ተከትሎ ምድር ታበራለች። በአዲስ ኪዳን
ሥልጣንን ወይም ኃይልን የሚወክለው የግሪክ ቃል ኤግሶሲያ በመባል ይታወቃል። ቃሉ
ክርስቶስ በገሐነም ኃይላት እና ሥልጣናት ላይ የተቀዳጀውን ድል ለመጥቀስ ተደጋግሞ ጥቅም
ላይ ውሏል። የሱስ ደቀ መዛሙርትን ለአገልግሎት ከመላክ አኳያ ይህን ቃል በማቴዎስ ወንጌል
ላይ ሲጠቀም እንመለከታለን። በማቴ. 10፡1 እንደቀረበው የሱስ በገሐነም አለቆችና ኃይላት
ላይ ለደቀ መዛሙርቱ ሥልጣን ሰጣቸው። በበጎና በክፉ መካከል በሚካሄደው ውጊያ ድል
ይቀዳጁ ዘንድ በመለኮታዊ ኃይል ላካቸው። የሱስ በማቴ. 28 አሁንም ለደቀ መዛሙርቱ
“ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር” ሰጥቶ የሄደው “ሕዝቦችን ሁሉ ደቀ መዛሙርት”
(ማቴ. 28፡18-19) እንዲያደርጉ ይልካቸዋል።
በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልታ፣ በሕይወቱና በሞቱ የገሐነምን አለቆችና ሥልጣናት
ድል ባደረገው በሕያው ክርስቶስ ሥልጣን ወደፊት በመገስገስ፣ የአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያን
በእግዚአብሔር ክብር ምድርን አበራች። በአጭር ዓመታት ውስጥ ደቀ መዛሙርቱ በወቅቱ
ይታወቅ ለነበረው ዓለም ወንጌልን አወጁ (ቆለ. 1፡23)።
በመጨረሻው ዘመን፣ መንፈስ ቅዱስ ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ኃይል ይፈስሳል፣
ይህን ተከትሎ ወንጌል እስከ ምድር ዳርቻ በፍጥነት ይሰራጫል። በአንድ ቀን ውስጥ በሺዎች
የሚቆጠሩ ሰዎች ይህን እውነት ይቀበላሉ፤ የእግዚአብሔር ጸጋ እና አምላካዊው እውነት
በመላዋ ምድር ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል። ዓለም በዚህ መልኩ ማስጠንቀቂያ የሚደርሰው
ሲሆን፣ ወንጌል እና ወንጌል የሚሰጠው ተስፋ በዓለም ዙሪያ ይናኛል።
“የወንጌሉ ታላቅ ሥራ፣ ሲጀመር ከታየው የእግዚአብሔር ኃይል መገለጥ ባነሰ ሁኔታ
የሚደመደም አይሆንም። በወንጌሉ መክፈቻ ላይ በፊተኛው ዝናብ መውረድ የተፈጸሙ
ትንቢቶች በመጨረሻ ደግሞ በኋለኛው ዝናብ እንደገና ፍጻሜ ያገኛሉ።
“የእግዚአብሔር አገልጋዮች በቅዱስ መቅደስ ፊታቸው ፈክቶና እያንጸባረቀ ከሰማይ
የመጣውን መልእክት ለማወጅ ከቦታ ቦታ ይራወጣሉ። በምድር ሁሉ በሺህዎች በሚቆጠሩ
ድምፆች መልእክቱ ይሰጣል። ተአምራት ይደረጋሉ፣ ሕሙማን ይፈወሳሉ፣ ድንቅና ታምራት
አማኞችን ይከተላቸዋል።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 701-702)።
የመንፈስ ቅዱስን በኃይል መፍሰስ፣ የኋለኛውን ዝናብ እና ጽኑ የሆነውን የማስጠንቀቂያ
ጥሪ የገታው ነገር ምንድን ነው? እንደ ግለሰብ ያለን ድርሻ የቱንም ያህል አነስተኛ
ቢሆንም፣ ለሚፈሰው መንፈስ ቅዱስ ግልጽ እና ተቀባይ በመሆን ረገድ ምን ሚና ሊኖረን
ይችላል?
በጎርጎሮሳውያኑ 1851 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ የዳግም ምጽአቱ
ተጠባባቂ ፈር ቀዳጅ አማኞች በራእ. 13፡11–17 የቀረበው ሁለተኛው አውሬ ዩናይትድ
ስቴትስ ኦፍ አሜሪካን የሚወክል መሆኑን ደርሰውበታል። ነገር ግን በዚያን ጊዜ ዩናይትድ
ስቴትስ መላው ዓለም የመጀመሪያውን አውሬ እንዲያመልክ ማድረግ የምትችልበትን መንገድ
ለመረዳት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል (ራእ. 13፡12)። በጎርጎሮሳውያኑ
1880 ዎቹ እንኳ፣ አጠቃላዩ የዩናይትድ ስቴትስ የባሕር ኃይል 48 ያረጁ መርከቦች ብቻ
ነበሩት።
ነገር ግን ከቀዝቃዛው ጦርነት ማብቂያ አንስቶ፣ በወታደራዊ አቅም የትኛውም
ዓይነት ኃይል ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር አይወዳደርም። አሜሪካውያን አስደናቂ የሆኑ ነጻነቶች
ባለቤት ቢሆኑም፣ ጊዜያቶች እየከበዱ በሄዱ ቁጥር፣ እነዚያ ነጻነቶች ሲረገጡ ወይም ሙሉ
በሙሉ ሲገፈፉ ማየት ከባድ አይሆንም። ብዙዎች ዛሬም እንኳ ይህ ሲሆን እያዩ እንደሆነ
ሲናገሩ ይደመጣል።
“ይህንን ለመከተል እምቢ በሚሉ ላይ ሕጋዊ መቀጮዎች ይወሰዳሉ፤ ከዚያም
በመጨረሻ ሞት የሚገባቸው እንደሆኑ ይታወጃል። በሌላ በኩል ደግሞ የፈጣሪን የእረፍት
ቀን የያዘው የእግዚአብሔር ሕግ ይከበር ዘንድ ይጠየቃል፤ መመሪያዎቹን የሚሰጡትም ሁሉ
ቁጣ እንደሚደርስባቸው ያስጠነቅቃል።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 693)።
“ማዕበሉ እየተቃረበ ሲመጣ፣ የሦስተኛውን መልአክ መልእክት እንደሚያምኑ
የመሰከሩ፣ ነገር ግን እውነትን በመታዘዝ ያልተቀደሱ ሰፊ መደቦች አቋማቸውን ለቅቀው፣
የተቃዋሚውን ጎራ ይቀላቀላሉ። ከዓለም ጋር በመተባበር የመንፈሱም ተካፋይ በመሆን፣
ተመሳሳይ ሊባል በሚችል ብርሃን ነገሮችን ይመለከታሉ፤ ፈተናም በመጣ ጊዜ በቀላሉ፣
ሕዝባዊውን ጎራ ለመምረጥ የተዘጋጁ ናቸው። ተሰጥኦ ያላቸው፣ ባለ ግሩም ሙያ በአንድ
ወቅት በእውነቱ ሐሴት ያደርጉ የነበሩ እነርሱ ነፍሳትን ያታልሉና ያሳስቱ ዘንድ ኃይላቸውን
ይተገብራሉ። የቀድሞው ወንድሞቻቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው እጅግ መራር ጠላቶች ይሆናሉ።
ሰንበት ጠባቂዎች ስለ እምነታቸው ይናገሩ ዘንድ ፍርድ ቤት ሲቀርቡ፣ ያልሆኑትን እንደሆኑ
በማድረግና በመክሰስ፣ በሐሰተኛ ዘገባዎችና በይሆናሎች ገዢዎችን የሚያነሣሡባቸው፣
ተወዳዳሪ የሌላቸው ስኬታማ የሰይጣን እንደራሴዎች የሚሆኑት እነዚህ ከሃዲዎች ናቸው።”
(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 698)።
1. የመጨረሻዎቹን የቀውስ ጊዜያት ክስተቶች መረዳት በጣም አስፈላጊ የሆነው
ለምንድነው? መጽሐፍ ቅዱስ ከመታለል ሊጠብቀን የሚችለው እንዴት ነው?
2. በዓለም ዙሪያ ያሉ በዲሞክራሲ ሥርዓት የሚመሩ ማኅበረሰቦች ለመቶዎች ዓመታት
የዘለቀ የኃይማኖት ነፃነት መናኸሪያ ሆነው ኖረዋል። ይህ ሁኔታ በፍጥነት መለወጥ
የሚችለው እንዴት ነው?
3. ከላይ የቀረበውን የኤለን ጂ. ኋይት መግለጫ ይመልከቱ። ነገ ከእነዚያ የዳግም
ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ጎን ይሰለፉ ዘንድ የዛሬ ምርጫዎ ምን ይመስላል?
4. በዚህ ምድር የእግዚአብሔርን ሥራ ለመጨረስ የሚያስችለውን የኋለኛውን ዝናብ
ለመቀበል ማድረግ ያለብን የግል ዝግጅት ምንድን ነው?