የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 22:11-12፣ ኤር. 30:5-7፣ መዝ. 91:1-11፣ ኤር. 25:33፣ ራእ. 21:2፣ ራእ. 20:11-15።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ደግሞም እንዲህ የሚል ታላቅ ድምፅ ከዙፋኑ
ሲወጣ ሰማሁ፤ ‘እነሆ፤ የእግዚአብሔር ማደሪያ በሰዎች መካከል ነው፤
እርሱ ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ እነርሱም ሕዝቡ ይሆናሉ፤ እግዚአብሔር ራሱም
ከእነርሱ ጋር ይኖራል፤ አምላካቸውም ይሆናል። እንባን ሁሉ ከዐይናቸው
ያብሳል፤ ከእንግዲህ ወዲህ ሞት ወይም ሐዘን ወይም ልቅሶ ወይም ሥቃይ
አይኖርም፤ የቀድሞው ሥርዐት ዐልፏልና።’” (ራእ. 21:3-4)
የወደፊቱን ጊዜ በተስፋ በተሞላ ልበ ሙሉነት መጋፈጥ እንችላለን። ምንም እንኳ
ከመቼውም በላይ ፈታኝ ጊዜያት እየመጡ ቢሆንም፣ የትኛውም ዓይነት መከራ፣
አስቸጋሪ ሁኔታ ወይም ሐዘን ውስጥ ማለፍ ቢኖርብንም፣ የተሻለ ቀን ይመጣል ብለን
ተስፋ እስካደረግን ድረስ ዛሬ ሕይወትን ትርጉም ባለው ዓላማ እና በደስታ መኖር እንችላለን።
ፍራንክሊን ዲ ሩዝቬልት በጎርጎሮሳውያኑ ከ1933-1945 ዓ.ም. የአሜሪካ ፕሬዝዳንት
ሆነው ያገለገሉ ሲሆን፣ ይህ የእርሳቸው የፕሬዝዳንትነት ዘመን በዩናይትድ ስቴትስ ታሪክ እጅግ
አስቸጋሪ ከሚባሉት ወቅቶች አንዱ ነበር። ሩዝቬልት በፖሊዮ በሽታ ጠንቅ አካላቸው አልታዘዝ
በማለቱ ያለ እርዳታ መራመድ አይችሉም ነበር። በአንድ ወቅት የሚከተለውን ጽፈው ነበር፡
“ከአድማስ ባሻገር የተሻለ ሕይወት፣ የተሻለ ዓለም አለ የሚለውን ተስፋ እና እምነት ሁሌም
አጽንተን እንደያዝን እንኖራለን።” ከዓለማችን እጅግ ብሩህ አእምሮ ከነበራቸው ሰዎች አንዱ
የነበረው አልበርት አንስታይን “ከትናንት ተማሩ፣ ዛሬን ኑሩ፣ ነገን ተስፋ አድርጉ" ሲል
ጽፏል። በንግሥት ቪክቶሪያ የግዛት ዘመን የነበረው ታዋቂው እንግሊዛዊ ገጣሚ አልፍሬድ
ሎርድ ቴኒሰን በአንድ ወቅት የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡- “ተስፋ በአዲሱ ዓመት መግቢያ ላይ
ፈገግ ይልና ‘ከቀድሞው የበለጠ አስደሳች ዘመን ይሆናል’ ሲል ያንሾካሹካል።”
በዚህ የሩብ ዓመት የመጨረሻ ትምህርታችን፣ በዩኒቨርስ ታሪክ እጅግ አስደሳች
በሆነው በዚያ ድንቅ ወቅት የክርስቶስ ጽኑ ፍቅር ምን እንደሚመስል እናያለን። በበጎ እና
በክፉ መካከል ሲካሄድ ለኖረው ተጋድሎ እንከን የለሽ ድል አድራጊነቱንም እንቃኛለን።
የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ የሆነው ራእይ--ስለ ዛሬ፣ ስለ ነገ ብሎም እስከ
ዘላለም ላለው ሁሉ ተስፋ ይሰጠናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 22:11-12፣ ዳን. 12:1-2፣ ኤር. 30:5-7። ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ገቢራዊ የሚሆኑ ክስተቶች የትኞቹ ናቸው?
የአመክሮ ጊዜ መጠናቀቁን ተከትሎ “መንግሥታት ከተመሠረቱበት ጊዜ ጀምሮ እስከዚያ ዘመን ድረስ ታይቶ የማይታወቅ ታላቅ የመከራ ጊዜ ይሆናል።’ ” ራእይ 16 በክፉው ዓለም ላይ የሚፈሱትን ሰባት የመጨረሻ መቅሰፍቶች ይገልጻል። ነገር ግን በግብፅ ላይ እንደ ወረዱት መቅሰፍቶች ሁሉ የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከመቅሰፍቶቹ የተጠበቁ ይሆናሉ። በዳንኤል የተሰጠውን ተስፋ ልብ ይበሉ፡ “ ‘ ነገር ግን በዚያን ጊዜ ስማቸው በመጽሐፉ ተጽፎ የተገኘው ሕዝብህ ሁሉ ይድናሉ።’ ” (ዳን. 12፡1)። ጥቅሱ ስለ “ሕይወት መጽሐፍ” እየተናገረ እንደሆነ ይታመናል (ፊልጵ. 4፡3፣ ራእ. 13፡8፣ ራእ. 20፡12፣15፣ ራእ. 22፡19)። ለየሱስ ታማኝ ሆነን እስከኖርን ድረስ ስማችን ከሕይወት መጽሐፍ አይደመሰስም (ራእ. 3፡5)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ዮሐ. 3:1-3፣ ዮሐ. 8:29፣ ዮሐ. 14:30። ለሚመጣው የመከራ ወቅት ብቸኛው በቂ ዝግጅት ምንድን ነው?
በመከራው ወቅት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከየሱስ ጋር ምንም ሊለውጠው የማይችል ጥልቅ የግል ግንኙነት ይኖራቸዋል። በማንኛውም ነገር እርሱን ደስ ማሰኘት ፍጹም ፍላጎታቸው ስለሚሆን፣ እርሱ ንጹህ እንደሆነ ሁሉ እነርሱም መንፈስ ቅዱስ በውስጣቸው በሚሠራው ሥራ እንደርሱ ንጹህ ይሆናሉ። በክርስቶስ ልብ ውስጥ ለሰይጣን ማታለያዎች ምላሽ የሚሰጥ አንዳች ነገር አልነበረም። እኛም ይህን የባህሪውን ገጽታ ማንጸባረቅ እንችላለን። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 27:5፣ መዝ. 91:1-11፣ ራእ. 3:10-12። እግዚአብሔር በመከራ ወቅት እንዲያጽናኑን የሰጠን የተስፋ ቃሎች የትኞቹ ናቸው?
በመከራው ወቅት ያለ አማላጅ እንኖራለን የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በተሳሳተ
መንገድ የተረዱ አሉ። እያንዳንዱ ሰው ከየሱስ ጎን ለመቆም ወይም በተቃራኒው ለመሰለፍ
የመጨረሻውን ውሳኔ ወስኖ ሲያበቃ፣ የሱስ በሰማይ ቤተ መቅደስ የሚሰጠውን የምልጃ
አገልግሎት ያቆማል። ነገር ግን፣ በዚህ ወቅት በገዛ ራሳችን ታምነን ብቻችንን እንቆማለን ማለት
አይደለም። የሱስ ሁል ጊዜ ከእኛ ጋር እንደሚሆን ማረጋገጫ ሰጥቶናል (ማቴ. 28፡20)።
ነገሮች በድንግዝግዝ ጨለማ ቢዋጡ እና በዙሪያችን ያለው ዓለም ቢንኮታኮትም--እምነት
ግን ጸንቶ ይኖራል። በመከራው ወቅት እምነታችን ስለሚጠነክርና የለዘላለማዊነት ናፍቆታችን
ስለሚጨምር ብቸኛው ምኞታችን ከየሱስ ጋር ፍጻሜ ለሌለው ዘመን መኖር ይሆናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 14:1-3፣ ቲቶ 2:11-14። ወደፊት ከሚያጋጥሙን ፈታኝ ሁኔታዎች እና ከመጪው የመከራ ወቅት አንጻር እነዚህ ጥቅሶች ያን ያህል አጽናኝ የሆኑት ለምንድን ነው?
"ልባችሁ አይታወክ" የሚሉት የየሱስ ቃላት እርሱ ፈጽሞ እንደማይተወንና ዳግመኛ
ወደ ቤታችን ሊወስደን እንደሚመጣ ያረጋግጡልናል። ይህ ዓለም ቤታችን አይደለም። እነሆ
የተሻለው ቀን እየመጣ ነው። በአዲስ ኪዳን መጽሐፍ፣ ከእያንዳንዱ 25 ቁጥር ውስጥ
አንዱ ጥቅስ ስለ ጌታ መመለስ ይናገራል። ቀናቶቹ በጽልመት እየተዋጡ ሲመጡና የቤተ
ክርስቲያን እና የመንግሥት ጥምረት ጨቋኝ ሕግ ሕይወታችንን አደጋ ላይ ሲጥል፣ የክርስቶስ
መምጣት ልባችንን በተስፋ ይሞላል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 6:15-17፣ ኢሳ. 25:8-9። በእነዚህ ቁጥሮች ስለ ዳኑት
እና ስለ ጠፉት የተገለጹ አመለካከቶችን ያስተያዩ። በእነዚህ ሁለት የአእምሮ አወቃቀር
መካከል ያለውን ልዩነት የሚያብራራው ምንድን ነው?
ጻድቃን አስደናቂ የሆነውን የጸጋ ስጦታ ሲቀበሉ፣ ክፉዎች ግን የኃጢአትን አስከፊ
መዘዝ ይገነዘባሉ። በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ወደ ፍርሐት፣ ኩነኔ፣ የጥፋተኝነት ስሜት
እና በመጨረሻም ወደ ዘላለማዊ ውድመት ይመራል። ለእርሱ የማዳን ጸጋ የምንሰጠው
ምላሽ ወደ ይቅርታ፣ ሰላም፣ እና የዳግም ምጽአቱ ዘላለማዊ ደስታ ይመራናል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 15:3-4፣ ራእ. 19:7። የተዋጁት በክርስቶስ በነጻ
ለተሰጣቸው በክብር የተሞላ መዳን ምላሽ የሚሰጡት እንዴት ነው?
“የክርስቶስ መስቀል፣ የዳኑት ለዘላለም የሚያጠኑት ሳይንሳቸው እና ዝማሬአቸው
ይሆናል። በከበረው ክርስቶስ ውስጥ፣ የተሰቀለውን ክርስቶስ ያያሉ… የዓለማት ሁሉ ፈጣሪ፣
የመዳረሻዎች ሁሉ ዳኛ ክብሩን ወደ ጎን ብሎ ለሰው ካለው ፍቅር የተነሣ ራሱን ማዋረዱ
መቼም ቢሆን የዩኒቨርስን አድናቆትና ፍቅር የሚያተርፍ ነው” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 744)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 12:17፣ ራእ. 17:13-14፣ ራእ. 19:11-16። በጥቅሶቹ
የቀረቡትን የክስተቶች ተከታታይነት ልብ ይሏል። እነዚህ ተከታታይነት ያላቸው ክስተቶች
ስለ ምድር የመጨረሻው ጦርነት እና ስለ ክርስቶስ የመጨረሻ ድል ምን ይላሉ?
ራእ. ምዕ. 19 የሚያበቃው የየሱስን መምጣት እና የክፉዎችን መጥፋት በሚያስደንቅ ተውኔታዊ ትዕይንት በማሳየት ነው። ይሁን እንጂ ታሪኩ አላበቃም። ራእ. 20 “ሺህ ዓመት” በመባል የሚታወቀውን 1,000 ዓመታት የሚቆየውን ዘመን ያስተዋውቀናል። ጥቅሱን ያንብቡ፡ የሱስ ዳግም ሲገለጥ የሰይጣን ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል?
የራእ. 20 1-3 መልእክት ምሳሌያዊ ነው። ሰይጣን በሰንሰለት ታስሮ ጉድጓድ
ውስጥ ይቆለፍበታል የሚለውን አባባል ቃል በቃል መውሰድ አይኖርብንም። ሰይጣን ለአንድ
ሺህ ዓመታት የሚታሰረው እርሱ ራሱ በፈጠራቸው ሁናቴዎች በታጠረችው በዚህች
ባድማና ሰው ዐልባ ምድር ላይ ይሆናል። በ2ጴጥ. 2፡4 እንደምናነበው ሰይጣንና መላእክቱ
“በጨለማ ጕድጓድ ውስጥ” ለፍርድ እንዲቆዩ ይደረጋሉ። በእነዚህ አንድ ሺህ ዓመታት
የእርሱ ዓመፅ ያስከተለውን ታላቅ ውድመት እና ጥፋት ይመለከታል።
“ጥልቁ” በሚል ከግሪክኛው የተተረጎመው ቃል፣ በፍጥረት ወቅት ምድርን
ለመግለጽ ከቀረበው የብሉይ ኪዳኑ ግሪክኛ ቃል ትርጉም ጋር አንድ ዓይነት ነው። “ምድርም
ቅርጽ የለሽና ባዶ ነበረች። የምድርን ጥልቅ ስፍራ ሁሉ ጨለማ ውጦት ነበር።” (ዘፍ. 1፡
2)። ቃሉ የሚገልጸው ባድማ የሆነችውን ምድር ነው። ስለዚህ “ጥልቅ ስፍራ” ወይም
ጥልቁ--ከመሬት በታች ያሉ ዋሻዎች ወይም በዩኒቨርስ አንዱ ጥግጋት የሚገኝ ገደል
አይደለም። የሰይጣን የኃጢአት እና የውድመት ሥራ፣ ከዳግም ምጽአቱ አስቀድሞ ያሉ
ክስተቶች ከሚፈጥሩባት ታላቅ ትርምስ ጋር ተደማምሮ ምድርን በፍጥረት መጀመሪያ ላይ
ወደ ነበረችበት ጨለማ እና የተመሰቃቀለ ስብስብ ውስጥ ይመልሳታል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤር. 4:23-26፣ ኤር. 25:33፣ ኢሳ. 24:1፣ 3፣ 5። የመጽሐፍ
ቅዱስ ነቢያት ይህን ትዕይንት እንዴት ይገልጹታል?
እነዚህ ነቢያት በክርስቶስ ዳግም ምጽዓት ወቅት የሚደርሰውን አስከፊ ውድመት
እና በዚህ ሺህ ዓመት ጊዜ ውስጥ በምድር ላይ አንድም ሰው በሕይወት ስለ አለመኖሩ
አጽንኦት ይሰጣሉ። ሰይጣን እና እርኩሳን መላእክቱ አመፁ ያስከተለውን ጥፋት
እንዲያሰላስሉ ይተዋሉ። መላው አጽናፈ ዓለም የኃጢአት ደሞዝ ሞት መሆኑን በድጋሚ
ይገነዘባል። እግዚአብሔር ኃጢአት ዳግመኛ እንዳይነሣ አድርጎ ችግሩን ይፈታል (ናሆ. 1፡
9)። እግዚአብሔር ይህን የሚያደርግባቸው ሦስት ዋና ዋና መንገዶች አሉ። በመጀመሪያ፣
ገደብ የለሽ ፍቅሩን፣ ጥልቅ ፍላጎቱን እና መላውን የሰው ልጆች ለማዳን የሚያደርገውን
ያላሰለሰ ጥረት ይገልጣል። በሁለተኛ ደረጃ ፍትሐዊነቱን፣ ቅን ፈራጅነቱን እና ጻድቅነቱን
ያሳያል። በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ መላው ዩኒቨርስ ኃጢአት እና ዓመፅ የሚያስከትለውን
የመጨረሻ ውጤት እንዲያይ ይፈቅዳል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 20:4-6። ጻድቃን በአንድ ሺው ዓመታት ውስጥ ምን እየሠሩ ይቆያሉ? ይህ ለምን አስፈላጊ ሆነ?
በሺው ዓመታት ውስጥ እግዚአብሔር የኃጢአትን ችግር እንዴት ፍትሐዊ በሆነና
በፍቅር እንደፈታ በገዛ ዓይኖቻቸው መመልከት የሚችሉባቸውን አጋጣሚዎች ያገኛሉ።
እግዚአብሔርን በበርካታ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጠይቀው ጥያቄ የሌለው ማን ነው? ሆኖም
አሁን፣ የተዋጁት ጻድቃን በሰማይ በሚያሳልፏቸው ሺህ ዓመታት ውስጥ እነዚህን ጥያቄዎች
ይጠይቃሉ። የሚወዱት ወዳጅ ወይም ዘመድ በሰማይ ሳይገኝ ከቀረ፣ የዳኑት የእግዚአብሔርን
ውሳኔዎች ይበልጥ በተሟላ ሁኔታ ለመረዳት የሚችሉበት አጋጣሚ ይኖራቸዋል። የተዋጁት
ጻድቃን እግዚአብሔር በሕይወት የኖረውን እያንዳንዱን ሰው ለማዳን ያደረገውን ከፍተኛ
ጥረት፣ ከመቼውም ጊዜ በላይ አዲስ እና ጥልቅ በሆነ ማስተዋል--ግንዛቤ ያገኛሉ።
እያንዳንዱ የጠፋ ሰው ክርስቶስን በግል በመቃወሙ ምክንያት ከሰማይ እንደቀረ ይገነዘባሉ።
እግዚአብሔር በጠፉት ላይ ዘላለማዊ ጥፋት የሚያስከትለውን የመጨረሻውን ማለትም
የሁለተኛውን ሞት ፍርድ የሚሰጠው ይህ ከሆነ በኋላ ብቻ ነው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 20:7-9። አንድ ሺሁ ዓመት እንዴት ያበቃል? የሰይጣን እና
ተከታዮቹ መጨረሻስ ምን ይሆናል?
ሰይጣን ለ 1,000 ዓመታት የሚፈትነው ወይም የሚያታልለው ሰው አይኖርም።
እርሱም ሆነ ርኩሳን መላእክቱ የኃጢአትን ገዳይ መዘዞች እያሰላሰሉ ብቻቸውን ቀርተዋል።
በሺሁ ዓመት መጨረሻ ላይ የሞቱት ኃጥአን የእግዚአብሔርን ፍርድ ለመጋፈጥ እና
የመጨረሻ ቅጣታቸውን ለመቀበል ከመቃብር ይነሣሉ (ራእ. 20፡5)።
ዛሬ ሰይጣን እጅግ ብዙ ተከታይ ሠራዊት አለው። ምንም እንኳ ሰይጣን በታላቁ ተጋድሎ እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በሽንፈት ላይ ሽንፈት ቢከናነብም፣ ቁጥራቸው በባሕር
ዳርቻ እንዳለ አሸዋ የሆኑ የጠፉ ሰዎችን ሲመለከት ይበረታታል። ራሱን ከዓመፁ ለመግታት
ገና ዝግጁ ባለመሆኑ፣ እነዚህን “ሕዝቦች” ለማታለል ይወጣል። ሰይጣን የእግዚአብሔርን
መንግሥት ገርስሰው የራሳቸውን ሥርዓት የሚመሠርቱበት አንድ የመጨረሻ ወሳኝ ፍልሚያ
ያደርጉ ዘንድ ያነሣሣቸዋል። “ጎግ እና ማጎግ” የሚለው ቃል ሰይጣንን እና በሁሉም ዘመናት
በምድር የኖሩ ነገር ግን ያልዳኑ ሰዎችን ለማመልከት ጥቅም ላይ ውሏል። ሰይጣንና ተከታዮቹ
“የቅዱሳንን ሰፈርና የተወደደችውን ከተማ” ይከብባሉ (ራእ. 20፡9)።
በሺሁ ዓመት መጨረሻ ላይ ገቢራዊ የሚሆነው ያልዳኑት ኃጥአን ከሞት መነሣት
ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን ቅድስቲቱ ከተማ ማለትም አዲሲቱ የሩሳሌም ከሰማይ ወደ ምድር
ትወርዳለች! (ራእ. 21፡2)። ቅዱሳን በአዲሲቷ የሩሳሌም ከክርስቶስ ጋር ለሺህ ዓመት
ነግሠው ኖረዋል። አሁን፣ በ1,000ዎቹ ዓመታት መጨረሻ ላይ ከተማዋ ከእግዚአብሔር፣
ከየሱስ፣ ከመላእክቱና ከተቤዡት ሁሉ ጋር ወደ ምድር ትወርዳለች። ለታላቁ ተጋድሎ የመጨረሻ
ጦርነት ሁሉም ሰው ይገኛል። ከዚህ በኋላ ኃጢአት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ይወገዳል።
የመጨረሻው ፍርድ የሚሰጥበት የጊዜ ሁናቴ ስለ እግዚአብሔር ባሕሪ ምን ይላል?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 5:10፣ ሮሜ 14:10-11፣ ራእ. 20:11-15። ክፉዎች ለምን ከሞት እንደሚነሱ አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ይላሉ?
ከዚህ በኋላ ክፉ እንዳይነሣ አድርጎ የኃጢአትን ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ
ለመቋጨት፣ እግዚአብሔር በመንገዱ ሁሉ ቅን እና ፍትሐዊ አምላክ የመሆኑ ጉዳይ ሁሉንም
ሰው ማሳመን አለበት። በመጨረሻ በእነዚያ የታላቁ ተጋድሎ ዘመናት እግዚአብሔር ምን
ያህል ፍትሐዊ አምላክ እንደሆነ በመቀበል ጉልበት ሁሉ ይንበረከካል--ሰይጣንና መላእክቱ
ጭምር። በዚህም በእግዚአብሔር ላይ የተነሣውን አመፃ ፍትሐዊ አድርጎ የሚያሳይ ምንም
ምክንያት አይኖርም። “የመዝገብ መጻሕፍት እንደ ተከፈቱ የክርስቶስም ዓይን በኀጥአን
ላይ ሲያርፍ፣ የሠሩትን እያንዳንዱን ኃጢአት አስታወሱ። ከንጽህናና ከቅድስና መንገድ
እግሮቻቸው የት ላይ እንዳፈነገጡ፣ ኩራትና ዓመጽ የእግዚአብሔርን ሕግ በመጣስ ምን
ያህል ርቀት እንደወሰዷቸው አዩ። ኃጢአትን በማጣጣም ያበረታቷቸው የሚገፋፉት
ፈተናዎች፣ እንዲጣመሙ የተደረጉ በረከቶች፣ የተጠሉ የእግዚአብሔር መልእክተኞች፣
ችላ የተባሉ ማስጠንቀቂያዎች፣ ግትርና ጸጸት የለሽ በሆነ ልብ እየተመታ የሚመለሰው
የምሕረት ማዕበል እነዚህ ሁሉ በእሳት እንደተጻፉ ፊደላት ሆነው ታዩ…
“መላው የኃጥዑ ዓለም፣ በሰማይ መንግሥት ላይ ከፍተኛ የመከዳት ኃጢአት
በመፈጸም ተከሶ በእግዚአብሔር ፍርድ ሸንጎ ፊት ቆሟል። ይግባኝ የሚሉበት (ጥፋተኛ
አይደለንም ብለው የሚከራከሩበት) አንዳች ነገር የላቸውም፤ ማሳበቢያ ዐልባ ናቸው፤
የዘላለም ሞት ቅጣትም ተበየነባቸው።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 763)።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 20:9፣ መዝ. 37:20፣ ሚልክ. 4:1-2። እነዚህ ጥቅሶች
ስለ ኃጢአት እና ኃጢአተኞች የመጨረሻ ውድመት እና ስለ ጻድቃን ሽልማት ምን
ግንዛቤ ይሰጡናል?
ሰይጣን እና ርኩሳን መላእክቱ በእሳት ባሕር ውስጥ እንዲጠፉ መደረጋቸው
መልካም የምሥራች ነው። ኃጢአት እና ኃጢአተኞች ይጠፋሉ። በራእ. 20፡9 መሠረት
እሳት ከሰማይ ወርዶ ይበላቸዋል፣ ይጠፋሉ እንጂ ለዘላለም እየተሰቃዩ አይኖሩም። በቀጣዩ
ቁጥር “ከዘላለም እስከ ዘላለም” የሚል አገላለጽ ጥቅም ላይ ውሏል። እንደየ ዐውደ-
ጽሑፉ መሠረት “ለዘላለም” የሚለው ቃል ሁሌም ቢሆን “ማብቂያ የሌለው” የሚል
ፍቺ ቢኖረውም፣ ነገር ግን አንድ ነገር ሙሉ በሙሉ ፍጻሜ እስኪያገኝ ድረስ ማለት ነው።
(ዘፀ. 21:6፣ 1ሳሙ. 1:22፣ 28፣ ይሁዳ 7፣ እና 2ጴጥ. 2:4-6)። በጠፉት ሰዎች
ላይ የሚደርሰው ውድመት በራሱ እያወደማቸው የሚኖር ድርጊት ሳይሆን ዘላለማዊ ነው።
እግዚአብሔር ለዘላለም እያሰቃየ የሚኖር አምላክ አይደለም።
በመጨረሻ ከሁለቱ ዘላለማዊ አንዱ እያንዳንዱን ሰብዓዊ ፍጡር ይጠብቀዋል። የጠፉት፣
በሚያሳዝን ሁኔታ የኃጢአትን “ደሞዝ”--ይኸውም የዘላለም ሞት ይቀበላሉ። ታዲያ
ለእኛ ይገባን የነበረው ሞት እንዳይከፈለን ብቸኛው ተስፋችን በየሱስ ጽድቅ ላይ
በመታመን የሚገኘው ለምንድን ነው?
“ወደ ውብ ኮረብታማ ስፍራዎች የሚለወጡ የተነጣጠሉ መስኮች
አሉበት፤ የእግዚአብሔር ተራራዎችም ግዙፍ አናታቸውን አምጥቀው ገዝፈው ይታያሉ።
በእነዚያ ጸጥታ በሰፈነባቸው መስኮች በሕያው ምንጮች አፋፍ ለረጅም ጊዜ ተጓዥና
ተቅበዝባዥ የነበሩት የእግዚአብሔር ሕዝቦች ቤታቸውን ያገኛሉ…
“እዚያ የማይሞቱ አእምሮዎች የመፍጠር ኃይልን ታምራት፣ የሚያድነውን ፍቅር
ምስጢራት፣ በማይከስም ሐሴት ያሰላስላሉ። እግዚአብሔርን ይረሱ ዘንድ የሚፈታተኗቸው፣
የሚያታልለው ጨካኙ ባላንጣ እዚያ የለም። እዚያ ሁሉም ጉልበት ይጠነክራል፤ እያንዳንዱ
ችሎታ ይጨምራል። ዕውቀትን መቅሰም አእምሮን አያዝለውም፣ ያካላዊና የአእምሮአዊ
ኃይላትንም አያደክምም። ታላላቅ የሥራ እቅዶች ይተገበራሉ፤ የገዘፉ ምኞቶች ወደ ፍጻሜ
ይመጣሉ፤ የመጠቁ ጉጉቶች እውን ይሆናሉ። ሆኖም አሁንም እንደገና መወጣት ያለባቸው
አዳዲስ ከፍታዎች፣ የሚያስደምሙ አዳዲስ ድንቃድንቆች፣ ማስተዋል የሚጠይቁ አዳዲስ
እውነቶች፣ የአካልን የአእምሮንና የነፍስን ኃይላት የሚጋብዙ አዳዲስ ጉዳዮች ብቅ
ይላሉ።”—(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 773)።
“ባልደበዘዘ ዕይታ የፍጥረትን ክብር ያያሉ፤ ጸሐዮች እና ከዋክብት በግሩም የአሠራር
ቅንጅታቸው ሁሉም በተሰጣቸው የኃላፊነት ሥነ ስርዓት የመለኮትን ዙፋን ከብበው ሲዞሩ
ይመለከቱታል። በጥቃቅንና ታላላቅ ነገሮች ሁሉ ላይ የፈጣሪ ስም ተጽፎበታል፤ በሁሉም ላይ
የኃይሉ ጥልቀት ይገለጽባቸዋል።”--ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 773)።
“ታላቁ ተጋድሎ (ተቃርኖ) አብቅቷል። ኃጢአትና ኃጢተኞች ከእንግዲህ የሉም።
መላው ዩኒቨርስ ንጹህ ነው። አንድ የመስማማትና የደስታ ትርታ በሰፊው ፍጥረት ሁሉ
ይመታል። ወሰን በሌለው ሕዋ ዳርቾች ሁሉ ሕይወት፣ ብርሃንና ደስታ ሁሉን ከፈጠረ ከእርሱ
ዘንድ ይፈሳሉ። እጅግ ደቃቅ ከሆነችው ከፍለ-ቁስ (አተም) እስከ ግዙፉ ዓለም፣ ሕይወት
ያለውም ሆነ ሕይወት የሌለው፣ ባልደበዘዘ ውበታቸውና ፍጹም ደስታቸው፣ እግዚአብሔር
ፍቅር ነው ብለው ያውጃሉ።”—(ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 774)።
1. ኃጢአት ለረጅም ዘመን እንዲቆይ እግዚአብሔር ለምን የፈቀደ ይመስልዎታል?
በተመሳሳይ ማንም ሰው በዚህ ምድር ለረጅም ዘመን ከመኖሩ በላይ የከፋ ሥቃይ
አይደርስበትም። ይህም ከራሱ የሕይወት ዘመን የላቀ ሥቃይ የሚደርስበት ሰው
የለም እንደ ማለት ነው። የሰው ልጅ ዕድሜ በሺዎች ከሚቆጠሩት የኃጢአት
ዓመታት ጋር ሲነጻጸር ምን ያህል አጭር ነው? ይህ አመለካከት አስቸጋሪውን
የክፋት ጥያቄ መቋቋም እንድንችል እንዴት ይረዳናል?
2. ሚሊኒየም በመባል የሚታወቀው የሺህ ዓመቱ ጊዜ ከደኅንነት እቅድ ጋር እንዴት
ይጣጣማል? የተዋጁት ሁሉ የእግዚአብሔርን ፍትሐዊነት፣ ቅንነት እና ፍቅር
የማየት ዕድል ካገኙ በኋላ የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍርድ እና የመጨረሻው
ቅጣት በጠፉት ላይ መሰጠቱ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ምን እንደሚናገር አሰብ
ያድርጉ።
ማሳሰቢያ
ድርጅቱ