የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዘፀ. 25:8- 9፣ 40፣ ዕብ. 8:1–6፣ ዘሌዋ. 16:21፣ 29–34፣ ዘሌዋ. 23:26–32፣ ዕብ. 9:23– 28፣ ዳን. 7:9-10፣ ማቴ. 25:1–13፣ ራእ. 11:19።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “እንግዲህ የምንናገረው ዋናው ነገር ይህ
ነው፤ በሰማያት በግርማው ዙፋን ቀኝ የተቀመጠ እንዲህ ያለ ሊቀ ካህናት
አለን፤ እርሱም በሰው ሳይሆን በጌታ በተተከለችው፣ እውነተኛ ድንኳን
በሆነችው ቤተ መቅደስ አገልጋይ ነው።” (ዕብ. 8፡1-2)።
በወርሐ ጥቅምት 22/ 1844 ዓ.ም. ከባድ ቅሬታ እና ተስፋ መቁረጥ ቢደርስባቸውም፣
ብዙም ሳይቆዩ፣ አንዳንድ ሚለራውያን ከጸለዩና ቃሉን ካጠኑ በኋላ ስህተታቸውን
ተረዱ። የ2,300 ቀናት ትንቢት ፍጻሜ በወቅቱ በስፋት በተያዘው አመለካከት መሠረት
የየሱስ ዳግም ምጽአት እውን የሚሆንበት ሳይሆን፣ ይልቁንም ከክርስቶስ ሰማያዊ መቅደስ
ሥራ ጋር የተሳሰረ ስለ መሆኑ በዕብራውያን መጽሐፍ በጉልህ ተገልጿል።
በዘሌዋውያን መጽሐፍ ላይ እንደተገለጸው በሰማይ ያለው መቅደስ መንጻት
የምድራዊው መቅደስ መንጻት ፍጻሜ ነበር። ይህን አስፈላጊ እውነት በተሻለ ለመረዳት
በዳን. 7 እና 8 መካከል ያለውን ተመጋጋቢነት ይመልከቱ።

እነዚህ ተመጋጋቢ ነጥቦች የቤተ መቅደሱ መንጻት እውነተኛ ባህሪ የሆነውን ታላቁን
ቅድመ ምጽአት የፍርድ ምርመራ ለማሳየት ይረዳሉ። በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን
ወሳኝ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት የሆነውን የክርስቶስ ሰማያዊ መቅደስ አገልግሎት እንመረምራለን።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፀ. 25፡8-9፣ 40፣ ዕብ. 8፡1-6። በጥቅሶቹ የተገለጹት ሁለት ቤተ መቅደሶች የትኞቹ ናቸው?
የቀደሙት የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ አማኞች ከ1844 በኋላ በነበሩት ወራት ቅዱሳን
መጻሕፍትን ሲመረምሩ፣ በመጽሐፍ ቅዱስ የተጠቀሱ ሁለት ቤተ መቅደሶች መኖራቸውን
ተገንዝበው ነበር--የሙሴ መገናኛ ድንኳን እና ሰማያዊው ቤተ መቅደስ። በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ “መቅደስ” የሚለው ቃል ለመጀመሪያ ጊዜ ጥቅም ላይ የዋለው በሙሴ የተሠራውን
የማደሪያ ድንኳን እንደ ሰማያዊ ነገሮች “ምሳሌ” አድርጎ በማቅረብ ሲሆን፤ በሁለተኛ ደረጃ
ደግሞ ምድራዊው መቅደስ በሰማይ ያለውን “እውነተኛ ማደሪያ” እንደሚያመላክት ሆኖ
ነበር። በክርስቶስ ሞት፣ የተምሳሌታዊው አገልግሎት አስፈላጊነት አከተመ። በሰማይ ያለው
“እውነተኛው ማደሪያ” የአዲሱ ኪዳን መቅደስ ነው። ዳን. 8፡14 በዚህ ዘመን ላይ ፍጻሜ
ሲያገኝ፣ በትንቢቱ የተጠቀሰው መቅደስ የአዲሱ ኪዳን መቅደስ እንደሆነ ይታመናል።
“2300 ቀናቱ ባለቁበት ጊዜ፣ በ1844 ዓ.ም. ለብዙ መቶ ዓመታት በምድር ላይ
ቤተ መቅደስ አልነበረም። ስለዚህም ‘እስከ 2300 ማታ እና ጠኋት ድረስ ነው፤ ከዚያም
መቅደሱ ይነጻል’ (ዳን. 8፡14) የሚለው ትንቢት የሚያመለክተው ያለ ምንም ጥርጥር
ሰማያዊውን ቤተ መቅደስ ነው።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡4 78)።
የምድረ በዳው መገናኛ ድንኳን የሰማያዊው መቅደስ ምሳሌ ነበር። በምድራዊው
መቅደስ ይካሄዱ የነበሩ አገልግሎቶች የእግዚአብሔር መለኮታዊ የማዳን እቅድ ጥላ ነበሩ።
እያንዳንዱ ይቀርብ የነበረ መሥዋእት የየሱስን የቀራንዮ መስቀል መሥዋእት ይወክል ነበር
(ዮሐ. 1፡29)። እነሆ በክርስቶስ መሥዋእትነት ከኃጢአት ኩነኔ ነፃ ወጣን። ምሕረትም
አገኘን። የሱስ ስለ እኛ የከፈለውን መሥዋእትነት ስንቀበልና ኃጢአታችንን ስንናዘዝ
(1ዮሐ. 1፡9) በደላችን ይደመሰሳል። የሱስ ስለ እኛ የሞተው በግ ብቻ ሳይሆን፣ ስለ እኛ
የሚኖረው ካህንም ጭምር ነው።
ዕብራውያን 7፡25 እንዲህ ሲል ያብራራል፡ “ስለዚህ ስለ እነርሱ እየማለደ ሁልጊዜ
በሕይወት ስለሚኖር፣ በእርሱ በኩል ወደ እግዚአብሔር የሚመጡትን ፈጽሞ ሊያድናቸው
ይችላል።” እርሱ የኃጢአትን ጥፋተኝነት ስሜት አስወግዶ ከኃጢአት ኃይል ያድነናል
(ሮሜ. 8፡1–4፣ 2ቆሮ. 5፡21)። የሱስ ለእኛ ሲል በሰማያዊው መቅደስ አገልግሎት
እየሰጠ ይገኛል። ከእርሱ ምልጃ የተነሣ፣ ሕይወታችንን ጠፍንጎ ይዞ የነበረው ኃጢአት
ተሰበረ። ከእንግዲህ በባርነት ቀንበር ሥር የምንኖር ወይም ለኃጢአተኛ ተፈጥሯችን ተገዢ
ባሪያዎች አይደለንም። በክርስቶስ የሱስ--ከኃጢአት ኩነኔም ሆነ ከኃጢአት ቁጥጥር ነፃ
ነን። ክርስቶስን በእምነት ስንጠማጠም ለመዳናችን ማረጋገጫ አለን!
የሱስ በሰማይ ስለ እርስዎ እያገለገለ የሚገኝ መሆኑን ማወቅዎ ለእርስዎ ምን ትርጉም
አለው--ማለትም የእርሱ በዚያ ስፍራ እያማለደሎት መገኘት? ስለ እርስዎ የሚማልድ
ለምን አስፈለጎት? ይህ እውነት ምሥራች የሆነው ለምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘሌዋ. 16፡21፣ 29-34፣ ዘሌዋ. 23:26–32፣ ዕብ. 9:23–28። በጥንቷ እስራኤል የሥርየት ቀን በእጅጉ አስፈላጊ የነበረው ለምን ነበር?
ካህናቱ ዓመቱን በሙሉ በየቀኑ ያገለግሉ ነበር፤ ሆኖም በዕብራይስጥ ዮም ኪፑር
በሚል ስያሜ በሚጠራው የሥርየት ቀን የእስራኤል ዓይኖች ሁሉ ወደ መቅደሱ ያማትራሉ።
ዘሌዋ. 16 እና 23 በሥርየት ቀን ዙሪያ ግልጽ መመሪያዎች ይሰጣሉ። ሁሉም ዓይነት
መደበኛ እንቅስቃሴ ይገታል። ሰው ሁሉ ይጾማል። ሊቀ ካህኑ ስለ ሕዝቡ ወደ እግዚአብሔር
መገኛ ቅድስተ ቅዱሳኑ የውስጠኛ ክፍል ሲገባ፣ ሕዝቡ ልቡን ይመረምራል። በትሕትና እና
ከልብ በመነጨ አኳኋን ኃጢአታቸውን በመናዘዝ እግዚአብሔርን ይሹ ነበር።
በሥርየት ቀን ሰውነቱን “የማያጎሳቁል” ማንኛውም ሰው “ተለይቶ ይጠፋል”፤
በዚህም የተመረጠው ሕዝብ ክፍል መሆኑ ያከትም ነበር (ዘሌዋ. 23፡27፣29)።
በሥርየት ቀን ሊቀ ካህኑ የጌታን ፍየል ደም ወደ መቅደሱ ወስዶ በስርየት መክደኛው ላይ
ከረጨው በኋላ ደሙን በወርቁ መሠዊያ ቀንዶች እና በናሱ መሠዊያ ላይ ይቀባዋል፤ በዚህ
ሁኔታ ለቅድስተ ቅዱሳኑ መሉ በሙሉ ያስተሰረይለታል። ሊቀ ካህኑ “የስርየት” ሥራውን
ከፈጸመ በኋላ እጆቹን በሚለቀቀው ፍየል ላይ ይጭንና የእስራኤልን ኃጢአት ይናዘዝበታል።
ከዚያም ከእስራኤላውያን ሰፈር ለዘላለም እንዲለይ ሆኖ ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ ይለቀቃል
(ዘሌዋ. 16፡20-22)።
ደሙ በዘወትር አገልግሎቱ ወደ መቅደሱ ይተላለፍ የነበረ ሲሆን፣ ይህም የኃጢአትን
በመዝገብ ላይ መስፈርና እግዚአብሔር ለመጨረሻው ባህሪ ኃላፊነት እየወሰደ መሆኑን
የሚያሳይ ነው (ኤር. 17፡1)። አሁን፣ በዚህ የስርየት ቀን፣ ከመቅደሱ ወጥቶ ለኃጢያት
ችግር የመጨረሻውን ኃላፊነት በሚወስደውና ሰይጣንን በሚወክለው የሚለቀቅ ፍየል፣
አዛዜል ራስ ላይ እንዲቀመጥ ይደረጋል።
ይህ ፍየል ወደ ምድረ በዳ ተወስዶ ርቆ መለቀቁን ተከትሎ፣ በስርየት ቀን መገባደጃ
ላይ እግዚአብሔር ከኃጢአት የነጻ መቅደስ እና ንጹህ ህዝብ ነበረው። ክርስቶስ መጀመሪያ
በሰማያዊው መቅደስ ቅዱሱ ክፍል፣ ከ2,300 ቀናት ፍጻሜ ማለትም ከ1844 አንስቶ
ደግሞ በቅድስተ ቅዱሳን እያገለገለን ይገኛል።
በእኛ ምትክ መሥዋእት በሆነው በየሱስ ምክንያት ታላቁን ፍርድ በሰላም እናልፋለን።
ኤለን ኋይት እንደተናገረችው፡ “አንዳችም የእኛ ድርሻ ወይም አበርክቶ በሌለበት--በእርሱ
ጽድቅ ብቻ ጻድቅ ሆነናል”--—The Desire of Ages, p. 25። ጻድቅ ሆነን
በተቆጠርንበት በእርሱ ጽድቅ ምክንያት ከኃጢአት በመራቅ ነፍሳችንን እናጎሳቁላለን። ይህ
ማለት የተጠራነው ክፉው ምቾት እንዲሰጠን ወይም ምክንያት እየፈጠርን ከኃጢአት ጋር
ተጣብቀን እንድንኖር ሳይሆን በጸጋ እያደግን የቅድስና ሕይወት እንድንመራ ነው።
የስርየት ቀን ዛሬ በሕይወታችን ምን ትርጉም አለው? በሕይወታችን ላይ ለውጥ ሊያመጣ
የሚገባው ለምንድን ነው?
ሁለቱን ጥቅሶች ያስተያዩ፡ ዳን. 7:9-10 እና ራእ. 14:6-7። እነዚህን ሁለት ጥቅሶች ምን ያመሳስላቸዋል?
ፍርድ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ትልቅ ቦታ የሚሰጠው ርዕሰ ጉዳይ ነው። “መልካምም ይሁን ክፉ፣ ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ ማንኛውንም ሥራ እግዚአብሔር ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።” (መክ. 12፡14)። የሱስ ስለ ወደፊቱ ፍርድ ለአድማጮቹ ሲናገር እንዲል ብሎ ነበር፡ “ ‘ነገር ግን እላችኋለሁ፤ ሰዎች ስለ ተናገሩት ከንቱ ቃል ሁሉ በፍርድ ቀን ይጠየቁበታል።’ ” (ማቴ. 12፡36)። ሐዋርያው ጳውሎስ በዚህ ላይ የሚከተለውን አክሏል፡ “እርሱ በጨለማ ውስጥ የተሰወረውን ወደ ብርሃን ያመጣዋል፤ በሰዎች ልብ ውስጥ ያለውንም ሐሳብ ይገልጠዋል።” (1ቆሮ. 4፡5)። ወደ ዮሐንስ ተልኮ የነበረው መልአክም “የፍርዱ ሰዓት ደርሷል” (ራእ. 14፡7) ሲል ተናግሮ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 22፡10-12። የሱስ ዳግም ሲገለጥ የሰብዓዊው ዘር ዕጣ ፈንታ ምን ይሆናል? ለዮሐንስ በግልጽ የተነገረው ነገር ምንድን ነው?
ክርስቶስ የመጨረሻ ሽልማቱን ለመስጠት የሚገለጥ ከመሆኑ አኳያ፣ በምጽአቱ ወቅት ማን ምን ሽልማት እንደሚቀበል ለማሳየት ከዚያ በፊት ፍርድ ሊኖር ይገባል። ክርስቶስ ሲመለስ ሁለተኛ ዕድል የለም። እያንዳንዱ ሰው ከክርስቶስ ጎን ወይም በተቃራኒው በመሰለፍ የመጨረሻውንና የማይቀለበሰውን ውሳኔ ለመወሰን የሚያስችል በቂ መረጃ ይኖረዋል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 25፡ 1-13። የሱስ ሁለቱን የተለያዩ አማኝ ቡድኖች በተለየ መንገድ ያስቀመጣቸው ለምድን ነው?
“የምርመራው ሥራ ሲያልቅ የዘመናት ሁሉ የክርስቶስ ተከታዮች እንደሆኑ
የመሰከሩት ሁሉ ጉዳያቸው ተመርምሮ ውሳኔ ሲያገኝ፣ ከዚያ በፊት ሳይሆን፣ ያ ጊዜ ሲደርስ፣
የምህረት (የአመክሮ) ጊዜ ያበቃል። የምህረት ደጅም ይዘጋል። እኛም ‘ተዘጋጅተው
የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሠርግ ገቡ ደጁም ተዘጋ’ በሚለው በአንድ አጭር አርፍተ ነገር
ውስጥ፣ በአዳኙ የመጀጨረሻ አገልግሎት አማካኝነት፣ ለሰው ልጅ መዳን የተሠራው ታላቅ
ሥራ ወደሚጠናቀቅበት ወደዚያ ጊዜ እንመለሳለን።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 489-490)።
በክርስቶስ በኩል ይቅርታ ማግኘት፣ ከጥፋተኝነት ስሜት ነጻ መውጣት፣
እግዚአብሔርን እየመሰሉ የመኖር ኃይል እና የመጨረሻው ድል የእኛ እንደመሆኑ--
ፍርዱን አንፍራው!
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 4:14–16 እና ዕብ. 10:19–22። እነዚህ ጥቅሶች ለእያንዳንዳችን የሚሰጡን ማረጋገጫና መለኮታዊ ግብዣ ምንድን ነው?
ጳውሎስ በዚህ የዕብራውያን መልእክቱ ባስቀመጠው ነጥብ “አጥብቀን እንያዝ”፣
“በድፍረት” በፊቱ “እንቅረብ” በማለት እምነታችን በታላቁ ሊቀ ካህናችን በየሱስ ላይ
ያተኮረ እንዲሆን ይነግረናል። የሚያስፈልገን ሁሉ በእርሱ በየሱስ አለን። በእምነት ወደ
ሰማያዊው መቅደስ እንገባ ዘንድ እርሱ “አዲስና ሕያው መንገድ” ከፈተልን።
ወደ አደባባዩ ስንመለከት በናሱ መሠዊያ ቀንዶች ላይ ደም እናያለን። በቅዱሱ ስፍራ
በዕጣኑ መሠዊያ ወርቃማ ቀንዶች ላይ ደም እናያለን። ደግሞም በስርየት መክደኛው ፊት
በመጋረጃው ላይ የተረጨውንም ደም እንመለከታለን።
የየሱስ ደም በእያንዳንዱ እርምጃ መንገዱን ያዘጋጃል። ይህ ተስፋ ይሰጠናል፤
ምክንያቱም የሱስ ይቅር ሲለንና ኃጢአታችንን ሲደመስስ ብቻ ከእግዚአብሔር ጋር መገናኘት
እንችላለን። የእግዚአብሔር ምህረት የትዬለሌ፣ ፍርዱም ፍትሐዊ ነው። የሱስ በመጀመሪያ
ኃጢአታችንን ይቅር ለማለት፣ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ኃጢአታችንን ለመደምሰስ ዋስትና
ካልሰጠ በቀር አምላካዊው ፍትሕ የክርስቶስን መሥዋእት ለበደላችን ማስተሰረያ አድርጎ
መቀበል አይችልም።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 11፡19። ከታላቁ ተጋድሎ አንጻር፣ የዚህ ራእይ አንደምታ ምንድን ነው? በሕግ እና በወንጌል መካከል ያለውን የማይነጣጠል ትስስር እንዴት ያሳያል?
የእግዚአብሔር የዙፋኑ መቀመጫ በሆነው፣ በብሩህ አብረቅራቂ ብርሃን ክብር
በተሞላው የእርሱ መገኛ የዩኒቨርስ መሠረት ቅጥር ውስጥ--አምላካዊውን ሕግ በቃል
ኪዳኑ ታቦት ውስጥ እናገኘዋለን። በዚህ ቅድስተ ቅዱሳን ክፍል የእግዚአብሔር ፍትሕ እና
ምህረት ተገልጦአል። ማንኛውም ምድራዊ ኃይል የአምላክን ሕግ ሊለውጥ አይችልም፤
ምክንያቱም ይህ ሕግ በሰማያዊው የቃል ኪዳኑ ታቦት ውስጥ ተቀምጧል። “ከዚያን ጊዜ
በኋላ፣ ከእስራኤል ቤት ጋር የምገባው ኪዳን ይህ ነው፤ ይላል ጌታ፤ ሕጌን በአእምሯቸው
አኖራለሁ፤ በልባቸውም እጽፈዋለሁ። እኔ አምላካቸው እሆናለሁ፤ እነርሱም ሕዝቤ
ይሆናሉ።” (ዕብ. 8፡10)። በእምነት ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ ውስጠኛው የመቅደሱ
ክፍል ስንገባ ላለፈው ኃጢአታችን ይቅርታን እንቀበላለን። ለእኛ በሞተልን ብሎም ሕጉን
በልባችን በጻፈው በክርስቶስ ታዛዥ ሕይወት ለመኖር የሚያስችል ኃይል እንቀዳጃለን። የሱስ
“ፈጽሞ” (7፡25) ሊያድነን ይችላል። የሱስ ከኃጢአት ቅጣት እና ኃጢአት በእኛ ላይ
ካለው አቅም--ሙሉ በሙሉ ያድነናል።
የየሱስ አማላጅነት እጅግ አስደናቂ የምሥራች የሆነው ለምንድን ነው? ወንጌል ባይኖር
ኖሮ የጽድቅ መለኪያ በሆነው ሕግ ፊት ስንቆም ምን ተስፋ ይኖረን ነበር?
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 10፡9-14። በምድራዊው ካህን የመቅደስ አገልግሎት እና በየሱስ ሰማያዊ የመቅደስ አገልግሎት መካከል ስላለው ልዩነት ጥቅሱ ምን ይገልጥልናል?
ክርስቶስ ለኃጢአት ፍጹም መሥዋእት ሆኖ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በመስቀል ላይ ሞተ። በሰማያዊው መቅደስ ውስጥ ያከናወነው የክህነት አገልግሎት እኛን ይቀድሰናል። ወደ ቅድስተ ቅዱሳን የገባው የሱስ በፍርድ ፊት ጠበቃችን ሆኖ ቆሞአል (1ዮሐ. 2፡1)። “ክርስቶስ የብዙ ሰዎችን ኀጢአት ለመሸከም፣ እንዲሁ አንድ ጊዜ መሥዋዕት ሆኗል፤ ሁለተኛ ጊዜም ይገለጣል፤ ይህም ለሚጠባበቁት ድነትን ለማምጣት እንጂ ኀጢአትን ለመሸከም አይደለም።” (ዕብ. 9፡23)። በእርሱ መሥዋዕትነት አማካይነት ኃጢአት መፍትሔ አግኝቷል። አሁን ደግሞ “መገለጡን ለሚወዱ” ዳግመኛ ይመጣል (2ጢሞ. 4፡8)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 6፡9፣20። የሱስ እንድንከተለው ለምን ይጋብዘናል--ደግሞስ እርሱን ስንከተል ምን ከወትሮ የተለየ አዲስ ነገር እናገኛለን?
“ክርስቶስ ለሰዎች ሲል በሰማይ መቅደስ የሚያከናውነው የማማለድ ሥራ ልክ
በመስቀል ላይ የመሞቱን ያህል ለመዳን እቅድ አስፈላጊ ነው። በሞቱ ያንን ሥራ ጀመረ፤
በሰማይ ይፈጽመው ዘንድም ከሞት ከተነሣ በኋላ አረገ። ‘ስለ እኛ ቀዳሚ ሆኖ’ (ዕብ. 6፡
20) ወደ ገባበት ማጋረጃው በእምነት መግባት አለብን። እዚያ የቀራኒዮ መስቀል ብርሃን
ያንጸባርቃል። በዚያ ስፍራ የመዳንን ምስጢራት በተመለከተ የተሻለ መረዳት እናገኛለን።
የሰው ልጅ መዳን የተከናወነው ሊታመን የማይችል ዋጋ ሰማይን አስከፍሎ ነው፤ የተሰዋው
መሥዋዕት፣ የተጣሰው የእግዚአብሔር ሕግ ሊጠይቀው ከሚችለው ሰፊ መጠይቅ ጋር እኩል
ነው (መሥዋዕቱ = የሕጉ መጠይቅ)። ወደ አባት ዙፋን የሚወስደውን መንገድ ክርስቶስ
ከፍቶታተል፤ በመካከለኛነቱ (በአስታራቂነቱ) አማካኝነት ወደ እርሱ በእምነት የሚመጡ
እውነተኛ መሻታቸው ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ይቀርባል።” ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 557)።
የደህንነት እቅድ የታላቁን ተጋድሎ እንቆቅልሽ ለመፍታት እና ይህችን ምድር
ከሰይጣን መዳፍ ፈልቅቆ ለማውጣት የሚያስችል የተሟላ እቅድ ነው። የየሱስ ሕይወት
እግዚአብሔር በሰቆቃ ለሚማቅቀው ምድር እና ትዕይንቱን በአንክሮ እየተከታተለ ለሚገኘው
ዩኒቨርስ ያለውን ፍቅር ያሳየ ነበር። የእርሱ ሞት የኃጢአትን አስከፊነት ገልጦ ያሳየና
ለመላው ሰብዓዊ ዘር ድነትን ያመጣ ነበር። እርሱ በሰማያዊው መቅደስ እየሰጠ ያለው
የምልጃ አገልግሎት፣ በእምነት ይቀበል ዘንድ ለሚጠማጠም ለእያንዳንዱ ነፍስ የሥርየትን
ጥቅሞች ያስገኛል።
የክርስቶስ የመስቀል ላይ ሞት በሰማያዊው መቅደስ ካለው የምልጃ አገልግሎት ጋር
እንዴት ይዛመዳል? ፍርዱ ለመዳን እቅድ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድነው?
የሱስ በፍርድ ወቅት የሚሠራልን ሥራ እና የእኛ ሚና የተገለጠበትን
መንገድ ልብ ይበሉ፡ “
“የሱስ ለኃጢአታቸው ማስተሰሪያ አያቀርብም፤ ነገር ግን ጸጸታቸውንና
እምነታቸውን ያሳያል፤ ይቅርታ ሲጠይቅላቸው ሳለም የቆሰሉ እጆቹን በአባቱና በመላእክት
ፊት አንስቶ፣ “በስማቸው አውቃቸዋለሁ፤ በእጄ መዳፍ ላይ ቀርጬአቸዋለሁ፤” በማለት
ያውጃል። “የእግዚአብሔር መሥዋዕት የተሰበረ መንፈስ ነው፤ አቤቱ ሆይ የተሰበረውንና
የተደቆሰውን ልብ አትንቅም” (መዝ. 51፡17)። የሕዝቦቹም ከሳሽ ለሆነው እንዲህ
ይናገራል፡- “ሰይጣን ሆይ እግዚአብሔር ይገስጽህ”—(ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 552)
በእግዚአብሔር ፊት እውቅና ያላቸው ሕዝቦቹ በጌታ ፊት ባደፉ ልብሶች የመቆማቸው
እውነታ፣ ራሳቸውን ወደ ማዋረድ እና ልባቸውን በጥልቅ ወደ መፈለግ ሊመራቸው ይገባል።
እውነትን በመታዘዝ ነፍሶቻቸውን የሚያነጹ ሁሉ፣ በየግላቸው ታማኝ አቋም ይኖራቸዋል።
የክርስቶስን እንከን የለሽ ባህሪ በቅርበት በተመለከቱ ቁጥር፣ እርሱን የመምሰል ምኞታቸው
የዛኑ ያህል ስለሚበረታ፣ ለራሳቸው ንጽህና እና ቅድስና ዝቅ ያለ ግምት ይሰጣሉ። ነገር ግን
ኃጢአተኛውን ሁኔታችንን መገንዘብ እንደሚኖርብን ሁሉ--ክርስቶስን እንደ ጽድቃችን፣
ቅድስናችን እና ቤዛችን አድርገን በመቁጠር በእርሱ ላይ መታመን ይኖርብናል። ሰይጣን
በእኛ ላይ ለሚያቀርባቸው ክሶች መልስ መስጠት አንችልም። ስለ እኛ ሕጋዊ ይግባኝ ማቅረብ
የሚችለው ክርስቶስ ብቻ ነው። የእኛ ሳይሆን ነገር ግን የእርሱ የጽድቅ ሥራ የከሳሹን
ሙግት ጸጥ ማሰኘት ይችላል፡—Ellen G. White, Testimonies for
the Church, vol. 5, pp. 471, 472.
“አሁን እየኖርን ያለነው በታላቁ የስርየት ቀን ነው። በምሳሌና ጥላው (በብሉይ
ኪዳን) አገልግሎት ሊቀ ካህኑ ለእስራኤል ስርየት እያካሄደ በሚሆንበት ጊዜ ከሕዝቡ
መካከል እንዳይቀሰፉ፣ ኃጢአታቸውን በመናዘዝና በእግዚአብሔር ፊት ራሳቸውን በማዋረድ
ነፍሳቸውን ያሰቃዩ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ ስሞቻቸው ከሕይወት መጽሐፍ (ሳይፋቁ)
እንዲቀሩላቸው የሚፈልጉ ሁሉ፣ አሁን በቀሩት ጥቂት የምሕረት ቀኖቻቸው ስለ ኃጢአት
በማዘንና በእውነተኛ ጸጸት በእግዚአብሔር ፊት ነፍሳቸውን ቢያሰቃዩ ይበጃቸዋል።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 558)።
1. የሱስ ስለ እኛ የቆሰሉ እጆቹን በአብ ፊት ያሳይልናል የሚለው ሐሳብ ምን ያህል
ስሜትዎን ነክቶታል? በአምላካዊው ፍርድ ፊት በምንቆምበት ወቅት ይህ ብቸኛ
ተስፋችን የሆነው ለምንድን ነው?
2. ዛሬ እየኖርን ያለነው የፍርድ ምርመራ እየተካሄደ ባለበት ወቅት ነው። ሥርየት
የጠፉ ኃጢአተኞችን ለማዳን የተሠራ የእግዚአብሔር ሥራ ነው። ታዲያ አምላክ
ኃጢአተኞችን ለማዳን ለሠራው ሥራ እያንዳንዱን ዕለት ማዋል መቻል መልካም
የምሥራች አይሆንምን?
3. “ስለ እኛ ሕጋዊ ይግባኝ ማቅረብ የሚችለው ክርስቶስ ብቻ ነው። የእኛ ሳይሆን ነገር ግን የእርሱ የጽድቅ ሥራ የከሳሹን ሙግት ጸጥ ማሰኘት ይችላል”—Advent
Review and Sabbath Herald, January 2, 190
8. ይሄን
ተስፋ እንዴት የራስዎ ማድረግ ይችላሉ?