የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ 1ተሰ. 4:13–18፣ ማቴ.
24:27፣ 30-31፣ 2ጴጥ. 1:19–21፣ ዳን. 8:14፣ ዳን. 9:20–27፣ ዕዝ. 7:7–13።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ። “በዚያን ቀን እንዲህ ይባላል፤ “እነሆ፤
አምላካችን ይህ ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ እርሱም አዳነን፤ እግዚአብሔር ይህ
ነው፤ በእርሱ ታመንን፤ በማዳኑም ደስ ይበለን፤ ሐሤትም እናድርግ።”
(ኢሳ. 25፡9)።
የየሱስ ዳግም ምጽአት ከቅዱሳት መጻሕፍት መሪ ጭብጦች አንዱ ነው። በቅዱሱ
አምላካዊ መልእክት ገጾች ውስጥ የሚንሸራሸር ወርቃማ ሰበዝ ነው። በብሉይ
ኪዳን መጻሕፍት ውስጥ ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት የሚናገሩ 1,845 ጥቅሶች
ስለ መኖራቸው አንድ ምሑር ግምታቸውን አስቀምጠዋል። በአዲስ ኪዳን ከሚገኙ 260
ምዕራፎች ውስጥ፣ ከ300 በላይ ማጣቀሻዎች ስለ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ይናገራሉ።
በአማካይ ሲሰላ ከ25 ቁጥሮች አንዱ እንደ ማለት ነው። ከ27ቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት
ውስጥ ሃያ ሁለቱ ይህን ታላቅ ክስተት ይጠቅሳሉ።
በአውሮፓ የተካሄደው የተሐድሶ እንቅስቃሴ ቁልቁል ወርዶ በመከፋፈልና ግጭት
ከተደናቀፈ በኋላ የፕሮቴስታንት እንቅስቃሴ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በአዲሱ ዓለም
ስር እየሰደደ ሄደ። በዚህም ብዙዎች የዳግም ምጽአቱን እውነት ጨምሮ ሌሎች አያሌ
አስተምህሮዎችን የመቀበል ፍላጎት አደረባቸው።
ከእነዚህ መካከል በግብርና ሙያ ይተዳደር የነበረው የባፕቲስት እምነት ተከታዩ
ዊልያም ሚለር አንዱ ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ካጠና በኋላ የሱስ በቅርቡ፣ እንደውም እርሱ
በሕይወት እያለ እንደሚመጣ አመነ። ከዚያም ይህን መልእክት መስበክ ጀመረ። ምንም
እንኳ እንቅስቃሴው ለከፍተኛ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ቢዳርግም፣ ለዚህ ዘመን ሳይቀር
አግባብነት ያለውን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ለብዙዎች መክፈት ችሏል።
በዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናታችን የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ለዘመናት
የአማኞችን ልብ በደስታ የሞላበትን ምክንያት እና ለዚያ ታላቅ ክስተት እንዴት መዘጋጀት
እንዳለብን እንመረምራለን።
ከሆላንድ ወደ አዲሱ ዓለም የሄዱት የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች እና
የኃይማኖት ተጓዦች የየሱስን ዳግም ምጽአት በናፍቆት ይጠባበቁ ነበር። ለእነሱ የክርስቶስ
ዳግም ምጽአት በጉጉት ይጠብቁት የነበረው አስደሳች ክስተት ነበር። ጆን ዋይክሊፍ
የክርስቶስን ምጽአት እንደ ተባረከ የቤተ ክርስቲያን ተስፋ በጽኑ ይጠባበቅ ነበር።
ካልቪን የክርስቶስን የክብር ዳግም ምጽአት “ከሁሉም ክስተቶች ሁሉ እጅግ አስደሳች”
ሲል ለተሐድሶ አራማጆች ተናግሯል። ለታማኝ የእግዚአብሔር ወንዶችና ሴቶች ልጆች፣
የክርስቶስ ዳግም ምጽአት ሊጠማጠሙት የሚገባ እንጂ የሚፈራ ጉዳይ አልነበረም።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 14፡1-3፣ 1ተሰ. 4፡13-18፣ ቲቶ 2፡11-14። እነዚህ
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት እንዲህ ያለውን ተስፋ
ለክርስቲያኖች የሰጡት ለምንድን ነው?
በክርስቶስ ዳግም ምጽአት ማመን መጽሐፍ ቅዱስን ለሚቀበሉ ክርስቲያኖች እንዲህ
ያለውን ተስፋና ደስታ ለምን እንዳስገኘ ለመረዳት እምብዛም አይከብድም። ይህ መጽሐፍ
ወደፊት--በሽታ፣ መከራና ሞት እንደሚወገድ ያመላክታል። ድኸነት፣ ኢፍትሐዊነት እና
ጭቆና ወደ ፍጻሜ ይመጣሉ ሲል ያስተምራል። ሁከት፣ ግጭት እና ጦርነት እንደሚያከትሙ
ያስገነዝባል። በወደፊቱ ዓለም--ሰላም እና ደስታ እንዲሁም ከክርስቶስ እና በዘመናት
ከተቤዡ ወገኖች ጋር ስለሚኖር ዘላቂ ኅብረት ይተነብያል።
“የክርስቶስ መምጣት ለእውነተኛ ተከታዮቹ ለዘመናት ሁሉ ተስፋቸው ሆኖ
ኖሮአል። እንደገና እንደሚመጣ የተናገረበት፣ የአዳኙ የደብረ ዘይት የመሰናበቻ ተስፋ
በፊታቸው ያለውን የደቀ መዛሙርቱን ዘመን አፈካው፤ ሐዘን ሊያዳፍነው፣ ፈተና
ሊያደበዝዘው በማይችል ሁኔታ ልባቸውን በደስታና በተስፋ ሞላው። በሥቃይና በስደት
መሃል ‘የታላቁ አምላካችንና የመድኃኒታችንን የየሱስ ክርስቶን ክብር መገለጥ’ መጠባበቅ
‘የተባረከው ተስፋ’ (ቲቶ 2፡13) ነበር። የክርስቶስን መምጣት በሕይወት እያሉ ማየት
ይመኙ የነበሩትን ወገኖቻቸውን ሲቀብሩ የተሰሎንቄ ክርስቲያኖች በሐዘን በትር ሲመቱ
ሳለ፣ መምህራቸው ጳውሎስ በክርስቶስ ምጽአት ስለሚሆነው ትንሣኤ አመላከታቸው።
ከዚያም በክርስቶስ የሞቱ ይነሣሉ፤ በሕይወት ካሉት ጋራም ሆነው ጌታን በአየር ይገናኙታል።
‘እንዲሁም’ አለ ‘ሁልጊዜ ከጌታ ጋር እንሆናለን። ስለዚህ እርስ በርሳችሁ በዚህ ቃል
ተጽናኑ።’ (1ተሰ. 4፡ 16-18)።”—(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 350)።
ዳግም ምጽአቱ ለእምነታችን እጅግ ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው? በተለይ ደግሞ
በመቃብር ያሉ በእንቅልፍ ውስጥ መሆናቸውን ከመገንዘባችን አኳያ ይህ አስተምህሮ ትልቅ
ግምት የሚሰጠው ለምንድን ነው? ያለበለዚያ ግን ጳውሎስ እንዳለው ፍጹም ተስፋ በሌለው
ሁኔታ ውስጥ ልንወድቅ የምንችለው እንዴት ነው? (1ቆሮ. 15፡15-18)።
ምንም እንኳ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች ቃል በቃል የቀረበውን፣ ዓይኖች
ሁሉ የሚያዩትን፣ ጆሮዎች የሚሰሙትን እና በታላቅ ክብር የተሞላውን የክርስቶስ ዳግም
ምጽአት አምነው የነበረ ቢሆንም፣ እያደር የዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት አረዳዳቸው
ተለወጠ። የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ታዋቂ ሰባኪዎች ክርስቶስ መንግሥቱን በምድር ላይ
ለመመሥረት እና ለ1,000 ዓመታት ሰላም ለማስፈን እንደሚመጣ አስተምረው ነበር።
ይህ ደግሞ የመንፈሳዊ ሕይወት መልፈስፈስ ብሎም ለመንፈሳዊ እሴቶች ግዴለሽና ቁርጠኛ
አለመሆንን አስከተለ።
በተመሳሳይ የክርስቶስ ደቀ መዛሙርት የመሲሑን የመጀመሪያ ምጽአት ባህሪ
በተሳሳተ መንገድ ተረድተው ነበር። እርሱ የሮማውያንን የባርነት ቀንበር እንደሚሰብር
ጄኔራል ሆኖ እንደሚመጣ እንጂ፣ ከኃጢአት ፍርድ እና እሥራት ነፃ የሚያወጣቸው
አድርገው አላሰቡም። በዚህም መሲሑ የሚመጣበትን መንገድ መረዳት ተሳናቸው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 1፡9-11፣ ራእ. 1፡7፣ ማቴ. 24፡27፣ 30፣ 31። ጥቅሶቹ
ጌታችን በምን ዓይነት ክስተት ዳግም ይገለጣል ሲሉ ያስተምሩናል?
በቤተልሔም ግርግም ውስጥ የነበረውን ሕፃን ማንነት ማስተዋል የቻሉት በጣም ጥቂት
ሰዎች ብቻ ነበሩ። ለሁለተኛ ጊዜ ሲመጣ ግን “ዓይን ሁሉ ያየዋል”። ጆሮ ሁሉ የመመለሱን
መለከት ድምፅ ይሰማል። በምድር ላይ ያለ ሰው ሁሉ ክብሩን ያያል። መታለል አይኖርብንም።
ቅዱሳት መጻሕፍት ከመመለሱ ጋር በተያያዘ የተገለጹትን ነገሮች በግልጽ አስፍረዋል።
“እጅግ ክቡር ብሎም እጅግ አንጸባራቂ ከሆኑ፣ ከተገለጹ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች
መካከል አንዱ፣ ታላቁን የመቤዠት ሥራ ለማጠናቀቅ የሚመጣበት የክርስቶስ ዳግም ምጽአት
ነው። ‘በሞት አገርና ጥላ’ (ማቴ. 4፡16) ይቀመጡ ዘንድ ለረጅም ዘመን ለተተዉት
የእግዚአብሔር የእምነት መንገደኛ ሕዝቦች፣ ‘ትንሣኤና ሕይወት’ (ዮሐ. 11፡25)
የሆነው ‘የተሳደደውን እንደና ወደቤቱ ይመልስ ዘንድ’ (2ሳሙ. 14፡13) ውድ እና ደስታን
የሚያፋፍመው የመገለጡ ተስፋ ተሰጥቶአል። የዳግም ምጽአቱ አስተምህሮ የተቀደሱት
መጻሕፍት አንኳር ጭብጥ ነው። የመጀመሪያዎቹ ጥንዶች የሐዘን እርምጃቸውን ከኤደን
ካደረጉበት ቀን አንስቶ የአጥፊውን ኃይል ሰባብሮ ወደ ታጣችው ገነት እንደገና ያመጣቸው
ዘንድ የእምነት ልጆች የክርስቶስን ምጽአት ሲጠብቁ ኖረዋል” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 347)።
ከቀደሙት የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ መሪዎች አንዱ የነበሩት ሉተር ዋረን ወጣቶችን
እንዲህ ይሉ ነበር፡ “ለክርስቶስ ዳግም ምጽአት ዝግጁ መሆን የሚቻልበት ብቸኛው መንገድ
መዘጋጀት እና ዝግጁ ሆኖ መጠባበቅ ነው”። የክርስቶስ ዳግም ምጽአት መልእክት እያንዳንዳችን
ልባችንን እንድንመረምር እና መንፈሳዊ ሕይወታችንን እንድንገመግም የቀረበልን አስቸኳይ ጥሪ
ነው። እግዚአብሔርን የመምሰል ሕይወት እንድንመራ የተሰጠን መልእክት ነው። በአንጸባራቂ
ብርሃን በተሞላው የክርስቶስ ዳግም ምጽአት የገለልተኝነት አቋም ሊኖር አይችልም።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ተሰ. 5፡2-5፣ ዕብ. 9፡28። የክርስቶስን ዳግም ምጽአት ክስተት
አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ማበረታቻ ይሰጡናል?
እግዚአብሔር የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆችን ተጠቅሞ ተሸፍኖ የነበረውን
በክርስቶስ ብቻ በማመን የሚገኝ ጽድቅ ይፋ እንዳደረገ ሁሉ፣ ዊልያም ሚለርን ተጠቅሞ
የተረሳውን የክርስቶስ ዳግም ምጽአት እውነት እንደገና ገለጠ። ሚለር ቅዱሳት መጻሕፍትን
ሲያጠና፣ ሊያስበውና ሊገምተው ከሚችለው በላይ የሚወደውን ክርስቶስ አገኘ። መጽሐፍ
ቅዱሱን፣ ብዕርና ማስታወሻ ደብተሩን ይዞ የዘፍጥረት መጽሐፍን ማንበብ ቢጀምርም፣ በፊቱ
ያለውን ጥቅስ በቅጡ እየተረዳ በፍጥነት መሄድ አልቻለም። አንዱን ጥቅስ ከሌላው ጋር
በማስተያየት መጽሐፍ ቅዱስ ራሱን በራሱ እንዲያብራራ ፈቀደ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኢሳ. 28፡9-10፣ ምሳ. 8፡8-9፣ ዮሐ. 16፡13፣ 2ጴጥ. 1፡19-21።
በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን ዓይነት የመጽሐፍ ቅዱስ አተረጓጎም መርኅዎችን ያገኛሉ?
ዊልያም ሚለር አንዱን ጥቅስን ከሌላው እያስተያየና እያወዳደረ ሲያጠና፣
ምስጢራዊ የነበረው የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ተገለጠለት። በስውር ተሸሽጎ የተቀመጠን
የከበረ ነገር ለማግኘት እንደሚጥር አሳሽ ያደረገው ፍለጋ ተሳክቶ እነሆ በብዙ ተካሰ።
መንፈስ ቅዱስ እንዲገባው አድርጎ የእግዚአብሔርን ቃል ምስጢር ገለጠለት። ሚለር
እንደ ሌሎቹ የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች ሁሉ፣ ትንቢታዊ ጽሑፎችንም በተመሳሳይ ትጋት
ማጥናቱን ቀጠለ።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 1፡17፣ ዳን. 2፡45፣ 1ጴጥ. 1፡10-11፣ ራእ. 1፡1-3። እነዚህ
ጥቅሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶችን እንዴት ማስተዋል እንዳለብን አስመልክቶ ምን
ያስተምሩናል?
በትንቢት መጻሕፍት የምናገኛቸው ተምሳሌታዊ አቀራረቦች በምሥጢር የተቆለፉ
አይደሉም። አፍቃሪ የሆነው አምላክ በቅርቡ በዚህ ዓለም ለሚፈጸሙ ዐበይት ክስተቶች
እንዘጋጅ ዘንድ እነሆ ትንቢታዊ መልእክቶቹን ሰጠን። ትንቢታዊው መልእክት እጹብ ድንቅ
በሆነ መልኩ ራሱን በራሱ ፈቺ እና ተርጓሚ መሆኑን ዊልያም ሚለር በግልጽ ተረድቶ ነበር።
ተምሳሌታዊዎቹ ትንቢታዊ መልእክቶች በራሳቸው በመጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ሆነው ቀርበዋል።
አውሬ--ነገሥታትን ወይም መንግሥታትን ይወክላል (ዳን. 7፡17፣23)። ነፋስ--ጥፋትን
ይወክላል (ኤር. 49፡36)። ውሃ--ሕዝቦችን ወይም መንግሥታትን ይወክላል (ራእ.
17፡15)። ሴት--ቤተ ክርስቲያንን ትወክላለች (ኤር. 6፡2፣ ኤፌ. 5፡22–32)። ጊዜን
አስመልክተው የተሰጡት የዳንኤልና የራእይ ትንቢቶችም በምሳሌያዊ አነጋገር የቀረቡ
ሲሆን፣ አንድ ትንቢታዊ ቀን አንድ ዓመትን ይወክላል (ዘኁል. 14፡34፣ ሕዝ. 4፡6)።
ዊልያም ሚለር እነዚህን የመጽሐፍ ቅዱስ መፍቻ መርኅዎች በሥራ ላይ እያዋለ እያለ፣
ክርስቶስ ዳግም የሚመለስበት ጊዜ ነው ብሎ ያመነበትን ጊዜ ሲያገኝ በእጅጉ ተደናገጠ።
የትንቢታዊ ተምሳሌት ትክክለኛ ግንዛቤ ለእምነታችን በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው
ለምንድነው?
ዊልያም ሚለር በነቢያት የተተነበዩ ክስተቶች በትክክል እንደተፈጸሙ ተመልክቷል።
400 ዓመታት የፈጀው የአብርሃም ትውልድ የግብጽ ቆይታ፣ እስራኤላውያን በምድረ በዳ
የተቅበዘበዙባቸው 40 ዓመታት፣ የእስራኤላውያን 70 ዓመት የምርኮ ዘመናት እንዲሁም
ለእስራኤል የተመደበው 70 ሱባዔ (ዘፍ. 15:13፣ ዘኁ. 14:34፣ ኤር. 25:11፣
ዳን. 9:24) ለአብነት የሚወሱ ናቸው።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማር. 1፡15፣ ገላ. 4፡4፣ ሮሜ 5፡6። ጥቅሶቹ ስለ መጀመሪያው
ምጽአት አምላካዊው የጊዜ ሠሌዳ ምን ይነግሩናል?
ሚለር ቅዱሳት መጻሕፍትን ከቅዱሳት መጻሕፍት ጋር እያነጻጸረ ትንቢቶችን ሲያጠና፣ እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ መለኮታዊ የጊዜ ሰሌዳ ካለው፣ የጌታችንን ዳግም ምጽአት አስመልክቶም እንዲሁ መለኮታዊ የጊዜ ሰሌዳ መኖሩ የግድ ይሆናል የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሰ። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዳን. 8፡14። በ2,300 ቀናት መጨረሻ ላይ ምን ክስተት ገቢራዊ ይሆን ነበር?
ልያም ሚለር “የቤተ መቅደሱ መንጻት” የምድር በእሳት መንጻት ነው የሚለውን
ታዋቂ አመለካከት ተቀበለ። ይህን የመሰለ ጥልቅ ጠቀሜታ ያለውን ክስተት ይረዳ ዘንድ
ቅዱሳን መጻሕፍትን በትጋት አጥንቷል። በዳን. ምዕ. 8 እና 9 መካከል ያለውን ትስስር
አስተዋለ። በዳን. 8 “ለዚህ ሰው የራእዩን ትርጕም ንገረው” (ዳን. 8፡16) ተብሎ
መልአኩ ታዝዟል። በምዕራፉ መጨረሻ፣ ከዳን. 8 አጠቃላይ ራእይ ሳይገለጽ የቀረው
ብቸኛው ክፍል (ዳን. 8፡27 ይመልከቱ) ስለ 2,300 ቀናት የሚናገረው ክፍል ነበር።
ቆየት ብሎም፣ መልአኩ ወደ ዳንኤል ተመልሶ ይመጣና “ ‘አሁን ጥበብንና ማስተዋልን
ልሰጥህ መጥቻለሁ’ ” ሲለው ይደመጣል (ዳን. 9፡22፣ 9፡23፣ 25-27)። ይህም ስለ
2,300ዎቹ ቀናት እንዲገነዘብ ለመርዳት ነበር።
መልአኩ “ ‘መልእክቱን ልብ በል፤ ራእዩንም አስተውል’ ” (ዳን. 9፡
23) ብሎ ዳንኤልን ካዘዘው በኋላ ከመልአኩ አንደበት የወጣው የመጀመሪያ ቃል “
‘በሕዝብህና በቅድስት ከተማህ ላይ ሰባ ሱባዔ ተቀጥሮአል’ ” (ዳን. 9፡24፡ 1962
ትርጉም) እንደሚል እናውቃለን። “ተቀጥሮአል” በሚል የተተረጎመውን ቃል ፍቺ ቃል
በቃል ስንወስደው--ተቆርጦለታል የሚል ትርጉም አለው። በመሆኑም ሰባ ሳምንታት
ማለትም 490 ዓመታት ተቆርጦ ይወጣል። ከምን ላይ? የ2,300 ቀናት ራእይ ዳንኤል
ያልተረዳው ብቸኛው የዳን. 8 ክፍል ሲሆን፣ መልአኩም እነሆ ሊያስረዳው መጣ።
70 ሱባዔው የሚጀምረው “ኢየሩሳሌምን መጠገንና መሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት
ጀምሮ’ ” (ዳን. 9፡25) እንደመሆኑ ሚለር ይህን ቀን የሚያውቅ ከሆነ፣ የ70
ሳምንታት መጀመሪያ እና የ2,300 ቀናትን ትንቢት ማስተዋል እንደሚችል ገብቶታል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕዝ. 7፡7-13። በፋርስ የነበሩት እስራኤላውያን ምርኮኞች ቤተ መቅደሳቸውን መልሰው እንዲገነቡ የሚፈቅድ አዋጅ የወጣው መቼ ነበር?
አዋጁ የወጣው በፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ ሲሆን ጊዜውም ከክርስቶስ ልደት በፊት 457 ላይ ነበር። ይህ አዋጅ አይሁዳውያን የሩሳሌምን መልሰው እንዲገነቡና የቤተ መቅደሱን አምልኮ ዳግም እንዲያቋቁሙ ፈቃድ ከሰጧቸው ሦስት ድንጋጌዎች መካከል የመጨረሻው ነው። ይህ ሦስተኛው አዋጅ እጅግ የተሟላ ከመሆኑ አኳያ የ2,300 ቀን/ ዓመት ትንቢት ጅማሮን ያመለክታል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 9፡25-26። ይህ አጠቃላይ የትንቢት ጊዜ የሚጀምረው መቼ ነው? እነዚህ ጥቅሶች የትኞቹን ዋና ዋና ክስተቶች ይተነብያሉ?
በዚህ አስደናቂ ትንቢት “ኢየሩሳሌምን ለመጠገንና ለመሥራት ትእዛዙ ከሚወጣበት”
ጊዜ አንስቶ እስከ መሲሑ ድረስ 69 ትንቢታዊ ሳምንታት ወይም 483 ትንቢታዊ ቀኖች
ወይም ቃል በቃል የተነገሩት ዓመታት እንደሚሆኑ ዳንኤል ተንብዮአል። አዋጁ የወጣው
ከክ.ል.በ. 457 መጸው ላይ እንደመሆኑ እስከ 27 ዓ.ም. ድረስ ማለትም ለ483 ዓመታት
ዘልቋል። “መሲሕ” የሚለው ቃል “የተቀባው” የሚል ፍቺ አለው። በ27 ዓ.ም. መጸው
ክርስቶስ ተጠመቀ፣ በመንፈስ ቅዱስም ተቀባ (ሐዋ. 10፡38)። የሱስ ከተጠመቀ በኋላ
ወደ ገሊላ በመሄድ “ ‘ጊዜው ደርሷል፤ የእግዚአብሔር መንግሥት ቀርባለች፤ ንስሓ ግቡ፤
በወንጌልም እመኑ’ ” እያለ ይሰብክ ነበር” (ማር. 1፡ 14-15)።
በ31 ዓ.ም. የጸደይ ወራት፣ ማለትም በዚህ የመጨረሻው የትንቢት ሳምንት
አጋማሽ፣ የሱስ ከተጠመቀ ከሦስት ዓመት ተኩል በኋላ ተሰቀለ። ወደ እግዚአብሔር በግ
ያመላክት የነበረው የመሥዋእት ሥርዓት በክርስቶስ የቀራንዮ መሥዋእት አበቃ።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ዳን. 9፡27። የሰባ ሳምንቱ ትንቢት እንዴት ያበቃል?
በተለይ ለአይሁዶች የተመደበው ሰባው ሳምንት ወይም 490 ዓመት--በ34
ዓ.ም. የወንጌልን መልእክት በሳንሄድሪን በመቃወም አበቃ (ሐዋ. 6፡8-7፡60)።
ከ2,300 የትንቢት ዓመታት ላይ 490 ስንቀንስ፣ ትንቢቱ ፍጻሜ የሚያገኝበት
1,810 ዓመታት የሚቀሩን ሲሆን፣ ይህ ደግሞ 1844 ዓ.ም. ላይ ያደርሰናል። ዊልያም
ሚለር እና የቀደሙት የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች በዳን. 8፡14 የተጠቀሰው መቅደስ
ምድር ናት ብለው ያምኑ ስለነበር፣ ክርስቶስ በ1844 ዓ.ም. ላይ ምድርን በእሳት ሊያነጻ
ይመጣል የሚል ግምት ነበራቸው ።
ትንቢቶቹ የሚጀምሩት ከክ.ል.በ. 457 ላይ ሲሆን፣ የ70
ሳምንቱ ትንቢት የተመሠረተበትን በ“ልዑሉ መሲሕ” ዙሪያ ያሉ ክንውኖችን ይተነብያሉ።
በዚህ ጽኑ መሠረት ላይ የተጣለው የ2,300 ቀናት ትንቢት 1844 ዓ.ም. ላይ ያበቃል።
“እንደ መጀሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት ሁሉ ዊልያም ሚለር እና ግብረ አበሮቹ
እራሳቸው የተሸከሙትን መልእክት ቁም ነገር በሙሉ አልተረዱትም ነበር። በቤተ
ክርስቲያን ሥር ሰድደው የነበሩ ስህተቶች በትንቢት ውስጥ አስፈላጊ ነጥብ ወደሆነው
ትክክለኛ ፍቺ ላይ እንዳይደርሱ አገዷቸው። ስለሆነም ለዓለም ያደርሱ ዘንድ እግዚአብሔር
በአደራ የሰጣቸውን መልእክት ማወጅ ቢችሉም፣ ትርጉሙን በትክክል አለመረዳታቸው
ቅሬታ እንዲገጥማቸው ምክንያት ሆነ።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 404)
“የፍርድ ማስጠንቀቂያው እንደነበረ እንዲታወጅ በመፈቀዱ ግን እግዚአብሔር
መልካም የሆነውን ዓላማውን አሳክቷል። ታላቁ ቀን ቅርብ ነበር፣ በልባቸው ያለውን
ይገልጽላቸው ዘንድ በምሪቱ በግልጽ ወደ ታወቀ የጊዜ ፈተና እንዲደርሱ አደረገ። መልእክቱ
የተነደፈው ለቤተ ክርስቲያን መፈተኛ መንጻት እንዲሆን ነበር። መሻቶቻቸው በዚህ ምድር
ላይ ወይስ በክርስቶስ እና በሰማይ ላይ ያረፉ መሆናቸውን እንዲያዩ መመራት ነበረባቸው።
አዳኙን እንደሚወዱት መስክረዋል፤ አሁን ፍቅራቸውን በተግባር ማሳየት ነበረባቸው።
ዓለማዊ ተስፋዎቻቸውን እና ምኞቶቻቸውን ትተው የጌታቸውን መምጣት በደስታ ይቀበሉት
ይሆን? መልእክቱ መንፈሳዊ ደረጃቸው በትክክል ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ማስተዋል እንዲችሉ
እንዲያደርጋቸው የታሰበ ነበር፤ በንስሐ እና ራስን በማዋረድ ጌታን ይፈልጉ ዘንድ እንዲነቃቁ
በምህረት የተላከ ነበር።” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ፡ 406)
1. ከዊልያም ሚለር ተሞክሮ ምን እንማራለን? ለመሆኑ እግዚአብሔር አንዳንዴ
የተሳሳተውን ግንዛቤአችንን ይቀለብሰዋል?
2. በዳን. 9፡24-27 ላይ በቂ ግንዛቤ መፍጠር፣ የመጽሐፍ ቅዱስን ታማኝነት እና
የክርስቶስን አምላክነት በማረጋገጥ ረገድ ጠቃሚ የሆነው ለምንድነው?
3. ትንቢትን መረዳት በመዳን እቅድ ምን ሚና ይኖረዋል? ትንቢት በእግዚአብሔር
እቅድ ውስጥ ያን ያህል ግዙፍ አንደምታ ያለው ለምንድን ነው?