የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 11:3–
6፣ ዘካ. 4:14፣ ራእ. 12:5-6, 14-15፣ ዳን. 7:25፣ ኢሳ. 54:17፣ መዝ.
119:89፣ ራእ. 11:15–18።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ሣሩ ይደርቃል፤ አበባውም ይረግፋል፤
የአምላካችን ቃል ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል” (ኢሳ. 40፡8)።
በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት የእግዚአብሔር ቃል ሲሰነጠቅ፣ ጥርጣሬ እንዲፈጥር
ሲደረግና ሲወገድ ኖሯል። በየገዳማቱ ሲከረቸምበት፣ በየዐደባባዩ ሲቃጠል እና
ሲቀዳደድ ኖሯል። የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ተፌዞባቸዋል፣ መሳለቂያ ሆነዋል፣
ታስረዋል አልፎ ተርፎም ሰማዕት ሆነዋል። በዚህ ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ቃል በአሸናፊነት
ገስግሷል።
የመካከለኛው ዘመኗ ቤተ ክርስቲያን ታማኝ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ክርስቲያኖችን
አሳድዳለች። ይህም ሆኖ የእግዚአብሔር ቃል ድቅድቁን ጨለማ በብርሃን ሞላ። ጭቆናና
ስደት የእግዚአብሔርን ቃል ከመታወጅ መግታት አልተቻለውም ነበር። መጽሐፍ ቅዱስን ወደ
እንግሊዝኛ የተረጎመው እንግሊዛዊው ዊልያም ቲንደል የእግዚአብሔርን ቃል በማሰራጨት
አብልጦ የረዳው ማን እንደሆነ ችሎት ላይ ተጠይቆ ነበር። ቲንደል ጥቂት ካሰላሰለ በኋላ
“የደርሃሙ ጳጳስ” ሲል መለሰ። ዳኞቹ በሰሙት ነገር ክፉኛ ተደናገጡ።
በአንድ ወቅት ቲንደል ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ የተረጎማቸውን በርካታ የመጽሐፍ
ቅዱስ ቅጂዎች ጳጳሱ ገዝተው በሕዝብ ፊት እንዳቃጠሏቸው ገለጸላቸው። ጳጳሱ በወቅቱ
የእውነትን ዓላማ በእጅጉ እየረዱ እንደ ነበር አልተገነዘቡም። እርሳቸው መጽሐፍ ቅዱስን
የገዙት ከመሸጫው እጅግ በተጋነነ ዋጋ ነበር። ይህን ከፍተኛ ግዢ ተከትሎ ቲንደል ከተቃጠሉት
የመጽሐፍ ቅዱሶች ቅጂዎች በብዙ እጥፍ የሚልቁ መጽሐፍ ቅዱሶችን ማተም ቻለ። እውነት
በትቢያ ብትሸፈንም የተጫናትን ምናምንቴ እያራገፈች ደግማ ደጋግማ ማብራት ችላ ነበር።
በዚህ ሳምንት በቅዱሳት መጻሕፍት እና በክርስትና እምነት ላይ ከተፈጸሙ እጅግ
አስከፊ ጥቃቶች መካከል አንዱን እንመረምራለን። በፈረንሳይ አብዮት ወቅት የሰው ልጅ
ደም በፈረንሳይ ጎዳናዎች እንደ ጅረት ፈሰሰ። ጊለቲን በመባል የሚታወቀው የሰዎችን አንገት
የሚቀላ ስል ምላጭ ያለው ማሽን በፓሪስ አደባባይ ተተክሎ የነበረ ሲሆን፣ በሺ የሚቆጠሩ
ሰዎች አናት በዚህ ማሽን ውስጥ እንዲገባ እየተደረገ ታርደዋል። አምላክ የለም የሚለው
ፍልስፍና እንደ ፈረንሳይ ኃይማኖት ተደርጎ ቢደነገግም፣ የእግዚአብሔር ቃል ምስክርነት
ዝም ማለት አልተቻለውም ነበር።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 11፡3-6። በጥቅሶቹ ያገኟቸውን የሁለቱ ምስክሮች መለያ የሆኑ አምስት ባህሪያትን ይዘርዝሩ።
በዘካርያስ 4 ነቢዩ--በወርቅ መቅረዙ ግራና ቀኝ ሁለት የወይራ ዛፎች እንደ
ተመለከተ የምናነብ ሲሆን፣ ተመሳሳይ መግለጫ በራእ. 11 ተዘግቧል። ይህ የሚወክለውን
አስመልክቶ፡ “ ‘እነዚህ ሁለቱ የምድርን ሁሉ ጌታ ለማገልገል የተቀቡ ናቸው’ ” (ዘካ.
4፡14) የሚል መልእክት ለዘካርያስ ተሰጥቶታል። የወይራ ዛፎቹ ብርሃን መስጠታቸውን
ይቀጥሉ ዘንድ በመቅረዙ ውስጥ ያለውን ዘይት ይመገባሉ። እዚህ ላይ ባለ መዝሙሩ፡ “ሕግህ
ለእግሬ መብራት፣ ለመንገዴም ብርሃን ነው” (መዝ. 119፡105) ሲል የጻፈውን ልብ
ይሏል። ዘይት መንፈስ ቅዱስን ይወክላል (ዘካ. 4፡2፣6)። ዮሐንስ በምዕ. 11 ያየው ራእይ፣
ዓለምን ያበራ ዘንድ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የሚታወጀውን የእግዚአብሔር ቃል ይገልጻል።
እነዚህ ሁለት ምስክሮች ትንቢት መናገር እና ዝናብ እንዳይዘንብ ማድረግ ይችላሉ።
ውሆችን ወደ ደም ለመለወጥና ምድርን በማንኛውም መቅሰፍት ለመምታት ሥልጣን
አላቸው። ኤልያስ በእስራኤል ላይ ዝናብ እንዳይዘንብ አጥብቆ መጸለዩን ተከትሎ ለጸሎቱ
ምላሽ ለሦስት ዓመት ከመንፈቅ ዝናብ አለመዝነቡ በእግዚአብሔር ቃል ተዘግቦ እናገኛለን
(ያዕ. 5፡17)። ከዚያም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። የበዓል ሐሰተኛ ነቢያት ድርቁን ማስቆም
ካቃታቸው በኋላ እንደገና ዝናብ ጣለ (1ነገሥ. ምዕ. 17-18)። ሙሴ በእግዚአብሔር
ቃል አማካይነት፣ ውሃውን ወደ ደም መቀየርን ጨምሮ በግብፃውያን ላይ ሁሉንም ዓይነት
መቅሰፍቶች አመጣ። ይህ የሆነበት ምክንያት ፈርዖን የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመልቀቅ
ፈቃደኛ ስላልነበር ነው (ዘፀ. 7)።
መጽሐፍ ቅዱስን ለመጉዳት የሚፈልጉ ሰዎች ከአፍህ በሚወጣው እሳት ይጠፋሉ።
“የሰራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል ‘ሕዝቡ ይህን ቃል ስለ ተናገረ፣ ቃሌን በአፍህ
ውስጥ የሚፋጅ እሳት፣ ይህንም ሕዝብ ማገዶ አደርጋለሁ፤ እሳቱም ይበላቸዋል’ ” (ኤር.
5፡14)። የእግዚአብሔርን ቃል የሚቃወሙ ሁሉ ፍርድ እንደሚጠብቃቸው ይናገራል።
የእርሱ ቃል በአፍ ውስጥ እንዳለ እሳት ነው።
የብሉይ ኪዳን መጻሕፍት ስለ እርሱ እንደሚመሰክሩ የሱስ በዮሐ. 5፡39 ይናገራል።
በተጨማሪም ወንጌል “ምስክር” ይሆን ዘንድ ለዓለም ሁሉ እንደሚሰበክ ተናግሯል (ማቴ.
24፡14)። በመሆኑም አዲስ ኪዳን ከብሉይ ኪዳን ጋር በመሆን የዚያ ምስክር መሠረት ነው።
እነዚህ ሁለት ምስክሮች እነማን ናቸው? ከእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ነጥቦች
እና በራእ. 11 ከተሰጡት ባህሪያት አንጻር (ቀኖናዊ ሳይሆን) ሁለቱ ምስክሮች
የእግዚአብሔርን ብርሃንና እውነት ለዓለም የሚያስተላልፉት የብሉይ እና የአዲስ ኪዳን
ቅዱሳት መጻሕፍት ናቸው ብለን መደምደም እንችላለን።
ዛሬ በርካታ ክርስቲያኖች ብሉይ ኪዳንን አቅልለው በመመልከት፣ አዲስ ኪዳን ስላለን
አስፈላጊ አይደለም የሚል ፍረጃ ሰጥተውታል። የዚህ አመለካከት ዘግናኝ ስህተት
ምንድን ነው?
ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ራእ. 11:3፣ ራእ. 12:5-6፣ 14-15 እና ዳን. 7:25። በእነዚህ ትንቢታዊ ጊዜያቶች ምን ዓይነት መመሳሰል ይመለከታሉ?
ሁለቱ ምስክሮች “ ‘ማቅ ለብሰው አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ትንቢት
ይናገራሉ’ “ (ራእ. 11፡3)። ይህ “አሕዛብ” (የእግዚአብሔርን እውነት የሚቃወሙ)
የተቀደሰችውን ከተማ ለአርባ ሁለት ወር ከሚረግጡበት ጊዜ ጋር ተመሳሳይ ነው (ራእ.
11፡2)። የእግዚአብሔር ጠላቶች ለ1,260 ቀናት የእግዚአብሔርን እውነት የሚረግጡ
ሲሆን፣ (42 x 30 = 1,260፤ እያንዳንዱ ቀን አንድ ትንቢታዊ ዓመትን ይወክላል)
ሁለቱ የእግዚአብሔር ምስክሮች የሆኑት ብሉይ እና አዲስ ኪዳን መጻሕፍት በዚህ ጊዜ
በእነርሱ ላይ ትንቢት ይናገራሉ።
ቀደም ሲል እንደተመለከትነው (አራተኛ ትምህርት) ከሮም ግዛት ፍርስራሽ
ውስጥ የሚነሣው የትንሹ ቀንድ ኃይል “ ‘ለዘመን፣ ለዘመናት፣ ለዘመን እኩሌታም’ ”
የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ያሳድዳል። “ዘመን” አንድ ዓመት ነው (360 ቀናት)። ስለዚህ
ሦስት ዓመት ከመንፈቅ--1,260 ቀናት ይሆናል።
ራእ. 12፡6፣13 በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ለ1,260 ቀናት ስለሚደርሰው
ስደት ይናገራል። ራእ. 12፡14 ስለ አንድ ዘመን፣ ዘመናት እና የዘመን እኩሌታ ይናገራል።
ራእ. 13፡5 ደግሞ ስለ 42 ወራት ይናራል። እነዚህ ሁለቱም ማለትም--42 ወራት እና
1,260 ቀናት የተጠቀሱት በራእ. 11፡2-3 ነው። እነዚህ ሁሉ ትንቢቶች የአንድን ታሪካዊ
ዘመን የተለያዩ ገጽታዎች ይገልጻሉ።
የቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን ቸል በተባለ ቁጥር፣ በምትኩ ሌሎች (ሰብዓዊ)
ትእዛዛት ብቅ ይላሉ። ይህ ብዙውን ጊዜ የእግዚአብሔርን ቃል በሚደግፉ ሰዎች ላይ ስደት
የሚያስከትል ሲሆን፣ የመካከለኛው ዘመን ቤተ ክርስቲያን ወደ ጥልቅ መንፈሳዊ ጽልመት
በገባችበትና የጳጳሳዊው ሥርዓት የበላይነት በሰፈነባቸው ከ538 እስከ 1798 ዓ.ም.
በነበሩት በርካታ መቶ ዓመታት ገቢራዊ ሆኖ ታይቷል። የእግዚአብሔር ሕግጋት በሰብዓዊ
ድንጋጌዎች ተተኩ። ሰብዓዊ ወግና ልማዶች ግልጽ ሆኖ በቀረበውና በቀላሉ በሚስተዋለው
ወንጌል ላይ ጥላቸውን አጠሉ። የሮም ቤተ ክርስቲያን ሥልጣኗን በመላው አውሮፓ
ማንሰራፋት ያስችላት ዘንድ ከዓለማዊ ኃይላት ጋር አንድነት ፈጠረች።
በእነዚህ 1,260 ዓመታት የአምላክ ቃል ማለትም ሁለቱ ምሥክሮቹ ማቅ ለብሰው
ነበር። የያዟቸው እውነቶች በበርካታ ወጎችና የአምልኮ ሥርዓቶች ስር ተሸሽገው ነበር።
እነዚህ ሁለት ምስክሮች እስከዚያን ወቅት የወደፊቱን ይተነብዩ፣ መጽሐፍ ቅዱስም ይናገር
ነበር። በእነዚያ መንፈሳዊ ጽልመት ዘመናት እንኳ የእግዚአብሔር ቃል ተጠብቆ እንዲቆይ
ሆኖ ነበር። ቃሉን ተንከባክበው የያዙና የኖሩት ሰዎች ነበሩ። ይሁን እንጂ በአውሮፓ
ከነበረው ሕዝብ አኳያ ሲነጻጸሩ ጥቂት ነበሩ። ዋልደንሳውያን፣ ጆን ሁስ፣ ጀሮም፣ ማርቲን
ሉተር፣ ኡልሪክ ዝዊንሊ፣ ጆን ካልቪን፣ ጆን እና ቻርለስ ዌስሊ እና ሌሎች በርካታ የተሐድሶ
አራማጆች የአምላክን ቃል በተረዱበት መንገድ በታማኝነት ጸንተዋል።
ዛሬ በእግዚአብሔር ቃል ላይ ሳይሆን በወግና ልማድ ላይ የተመሠረቱ እና በበርካታ
ክርስቲያኖች ዘንድ ተቀባይነት ያገኙ፣ ትምህርቶች የትኞቹ ናቸው?
ጥቅሶቹን ያንብቡ ራእ. 11:7–9። የቋንቋውን ተምሳሌታዊ ባህሪ ሳንዘነጋ፣ ጥቅሶቹ ሁለቱ የእግዚአብሔር ምስክሮች በሆኑት ብሉይ እና አዲስ ኪዳን መጻሕፍት ላይ ምን ይደርሳል ሲሉ ይተነብያሉ?
ከክርስቶስ ልደት በኋላ 538 ላይ አረማዊው የሮም መንግሥት ተገረሰሰ። የሮም
ንጉሠ ነገሥት የነበረው ጀስቲንያን የሲቪል፣ የፖለቲካውንና ኃይማኖታዊውን ሥልጣን
ለሊቀ ጳጳሱ ቪጂሊስ አስረከበ። ይህን ተከትሎ ረጅም ዘመናት ያስቆጠረው የመካከለኛው
ዘመን የቤተ ክርስቲያን የበላይነት ተጀመረ። ከፍታው እስከ 1798 ዓ.ም. ድረስ ቀጠለ።
የፈረንሳይ ጄኔራል የነበረው በርቲየር በናፖሊዮን ትእዛዝ በጎርጎሮዋውያኑ የካቲት 10
ቀን 1798 ዓ.ም. ያለአንዳች ተቀናቃኝ ሰተት ብሎ ሮም ገባ። ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፒየስ
ስድስተኛ በምርኮ ወደ ፈረንሳይ ከተወሰዱ በኋላ በእዚያው አረፉ። ይህ ቀን በዳንኤል እና
ራእይ (የትናንቱን ጥናት ይመልከቱ)፣ የተተነበየው የ1,260 ቀናት ወይም ዓመታት የሮም
ቤተ ክርስቲያን ዓለማዊ ሥልጣን ዘመን ፍጻሜ ሆነ።
የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢትን ሐቀኝነት የሚያሳይ እንዴት ያለ ብርቱ መግለጫ ነው!
ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመታት በፊት የተጻፈው ትንቢተ ዳንኤል፣ ከ2,300 ዓመታት
በኋላ ስለሚከሰቱ ክስተቶች በትክክል ተንብዮአል። በመጽሐፍ ቅዱስ በተነገሩ ትንቢቶች ላይ
ሙሉ እምነት መጣል እንችላለን።
በዚህ ሁሉ ዘመን የወንጌል እውነት በቃሉ ምስክርነት ሕያው ሆኖ ተጠብቆ ቆየ።
ይሁን እንጂ ግዙፍ ተግዳሮቶች በመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ላይ አስጊ የሆኑበት አጋጣሚ
ነበር። ከጥልቁ የወጣው አውሬ (ሰይጣን) በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ ውጊያ አካሂዷል።
በ1789 የፈነዳውን የፈረንሳይ አብዮት ተገን አድርጎ በመጽሐፍ ቅዱስ ሥልጣን ላይ
አዳዲስ ጥቃቶችን ሰንዝሯል።
በፈረንሣይ አብዮት ወቅት፣ በመንግሥት ይደገፍ የነበረው “በዕውቀትና ፀረ-ክህነት
መርኅዎች ላይ የተመሠረተ” የተባለ ፍልስፍና [Le Culte de la Raison,
(The Cult of Reason)] የክርስትና እምነትን እንዲተካ ተደርጎ በይፋ
ተቋቋመ። በዚህም ይኸው ፍልስፍና በአገር አቀፍ ደረጃ ህዳር 10/ 1793 ዓ.ም.
በፌስቲቫልነት ደምቆ እንዲከበር ተደረገ። በመላው ፈረንሳይ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት
ወደ ዕውቀትና ፀረ-ክህነት መርኅ መስበኪያ መቅደስነት የተቀየሩ ሲሆን፣ አንዲት ሴት
(Sophie Momoro) የዕውቀትና አመክንዮ ጽንሰ ሃሳብን የምትወክል አማልክት
ተደርጋ በመመረጥ በታላቅ ሥነ ሥርዓት ዙፋን ላይ እንድትቀመጥ ተደረገ። መጽሐፍ ቅዱስ
በየመንገዱ ተቃጠለ። አምላክ የሚባል የለም የሚል ዐዋጅ ታወጀ። ሞት ለእም-ቅድማ’ለም
ማብቂያ የሌለው እንቅልፍ እንደሆነም ተነገረ። ሰይጣን ፈሪሃ እግዚአብሔር በሌላቸው
ሰዎች ተጠቅሞ የእግዚአብሔርን ሁለት ምስክሮች ለመግደል ሠራ። “ሬሳቸውም በታላቂቱ
ከተማ አደባባይ ይጣላል፤ ይህች ከተማ ሰዶምና ግብፅ እየተባለች በምሳሌ የምትጠራውና
የእነርሱም ጌታ የተሰቀለባት ናት” ራእ. 11፡8)።
ግብጽ እውነተኛውን አምላክ የካዱ በርካታ አማልክት መናኸሪያ ነበረች (ዘፀ.
5፡2)። ሶዶም ከባድ የሆነ የሥነ ምግባር ማሽቆልቆልን ይወክላል። አብዮት ሲፈነዳ
የሚሰከሰተውን የገደብ ጥሰትና የደም መፋሰስ ተከትሎ በፈረንሳይ አብዮት የእግዚአብሔር
ሁለት ምስክሮች የሆኑት ብሉይ እና አዲስ ኪዳን በኢ-አማኒነት እና የሥነ ምግባር ጽልመት
ጠንቅ እንዲገደሉ ተደረጉ።
ሁለቱ የእግዚአብሔር ምስክሮች ሬሳ ሳይቀበር “ሦስት ቀን ተኩል” ይቆያል
ሲል ራእ. 11፡9 ይናገራል። እነዚህ ትንቢታዊ “ቀናት” ሦስት ዓመት ተኩል ይሆናሉ።
ኢ-አማኒነት በፈረንሳይ አብዮት ቢያንስ ለሦስት ዓመት ተኩል ከፍተኛውን ደረጃ ይዞ ነበር።
ኃይማኖትን የሻረው ድንጋጌ በፓሪስ ከወጣበት ከኅዳር 26/ 1793 አንስቶ የፈረንሳይ
መንግሥት ገደብ የተጣለባቸውን ኃይማኖታዊ ሕጎች እስካስወገደበት ሰኔ 17/ 1797
ድረስ ዘልቋል።
ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 11:11። ይህ ጥቅስ ስለ እግዚአብሔር ቃል የሚናገረው ትንቢት ምንድን ነው?
በፈረንሳይ አብዮት ማብቂያ ላይ፣ የእግዚአብሔር ቃል ዳግም ሕያው እንደሚሆን
በተምሳሌታዊው መልእክት ቀርቦ እንመለከታለን። ከዚያም ታላቅ መነቃቃት ይመጣል።
የእግዚአብሔር ቃል ሰዎች የሚድኑበት ሕያው ኃይል መሆኑን ዳግም በተመለከቱት ላይ
ታላቅ ፍርሐት ይወድቅባቸዋል። በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ፣ እግዚአብሔር
ወንጌልን እስከ ምድር ዳርቻ ለማድረስ ቁርጠኞች የነበሩ ወንዶችና ሴቶች ልጆቹን አስነሣ።
ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስን መልእክት በፍጥነት ያሰራጩ ሲሆን፣ ለምሳሌ ዊልያም ኬሪ ወደ
ሕንድ ተጉዞ መጽሐፍ ቅዱስ በደርዘን በሚቆጠሩ የሕንድ ቋንቋዎች እንዲተረጎም አደረገ።
በመጽሐፍ ቅዱስ ኃይል የተገፋፉ ሚስዮናውያንም በዓለም ዙሪያ ተላኩ።
እነዚህ ዓለም አቀፍ የሚስዮናዊ ሥራዎች ከፈረንሳይ አብዮት በኋላ እንደ አሸን
የፈሉት እንዲሁ በአጋጣሚ አልነበረም። የእግዚአብሔር ቃል ሕያው ነው። ምንም እንኳ
ለብዙዎች “የሞተ” ቢመስልም በአማኞች ልብ ውስጥ ግን ሕያው ነበር። የራእይ መልእክቶች
በተነበዩት መሠረት እንደና ሙሉ ሕይወት ዘርቶ አንሰራራ። “ኃይማኖት የለሹ ቮልቴር በአንድ
ወቅት በኩራት ‘የክርስትናን እምነት የጀመሩ አስራ ሁለት ሰዎች ናቸው እያሉ ሰዎች ሲያወሩ
መስማት ደከመኝ። ለመገልበጥ ግን አንድ ሰው እንደሚበቃ አረጋግጥላችኋለሁ’ ብሎ ነበር።
እርሱ ከሞተ በኋላ ትውልድ አልፎ ትውልድ ተተክቷል። በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠራውን
ጦርነት በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ተቀላቅለውታል። መጽሐፍ ቅዱስ ግን ሊደመሰስ
አልቻለም። በቮልቴር ጊዜ ቁጥሩ መቶ ያህል ነበር፤ አሁን አስር ሺህ ነው፤ አዎን መቶ
ሺህ የእግዚአብሔር መጽሐፍ አለ። የክርስትና ቤተ ክርስቲያንን በተመለከተ በአንድ ቀዳሚ
የተሐድሶ አራማጅ ቃል ሲገለጽ “መጽሐፍ ቅዱስ ብዙ መዶሻዎችን የጨረሰ መስፍ [ባለ’ጅ
ብረት ለመቀጥቀጥ ከሥር አድርጎ የሚጠቀምበት]” ነው።”--(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ፡ 334)
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 119: 89 እና መዝ. 111:7-8። ጥቅሶቹ ስለ መጽሐፍ
ቅዱስ እና ለምን ልናምነው እንደሚገባ ምን ይነግሩናል?
የእግዚአብሔር ቃል ጥቃት ወይም ጫና ሊደርስበት ቢችልም ፈጽሞ አይጠፋም።
በርካታ ክርስቲያን ነን ባዮች ሳይቀሩ በአንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ላይ ጥያቄ
በማንሣት ወይም በመጽሐፉ የቀረቡ ሰዎችን ስብዕና በማግዘፍ--መለኮታዊ ማኅተሙን ግን
በማኮስመን በተለያዩ መንገዶች የእግዚአብሔርን እውነት ሲያጣጥሉ ይስተዋላሉ።
ምንም ይሁን ምን፣ በእግዚአብሔር ቃል ላይ በሚሰነዘሩ እንዲህ ያሉ ጥቃቶች
እንታለል ዘንድ መፍቀድ የለብንም። መጽሐፍ ቅዱስ ለሰዎች ልብ እየተናገረ፣ ቃሉን
ለመስማትና ትምህርቱን ለመከተል ፈቃደኞች ለሆኑ አዲስ የሕይወት እስትንፋስ እየሰጠ
እነሆ ዛሬም ሕያው ሆኖ አለ።
በተለይ እርስዎን በግል እየተናገሩ ያሉ ትንቢቶች የትኞቹ ናቸው? ለምን?
ምንም እንኳ የጠላት ጥቃቶች ቢኖሩም፣ በዚህ ምድር ገቢራዊ የሆነው የእግዚአብሔር
ሥራ በክብር ወደ ተሞላ የከፍታ ድምዳሜ ይደርሳል። ወንጌል “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና
ለወገን ሁሉ” (ራእ. 14፡6) ይሰበካል። በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል እየተካሄደ
ያለው ታላቁ ተጋድሎ በክርስቶስ የሲኦልን ኃይላት አሸናፊነት ይጠናቀቃል። የእግዚአብሔር
መንግሥት በክፉው ላይ ድል ይቀዳጃል፣ ኃጢአትም ከጽንፈ ዓለም ለዘላለም ይወገዳል።
ራእ. 11 ሰይጣን በፈረንሳይ አብዮት አማካይነት የክርስትናን እምነት ለማጥፋት እና
በእግዚአብሔር ላይ ያለውን እምነት ለማስወገድ ያደረገውን ሙከራ በማሳየት የሚጀምር
ሲሆን፣ ነገር ግን ምእራፉ የሚያበቃው የእግዚአብሔር መንግሥት በክፉው ገዢዎች እና
ኃይሎች ላይ በሚቀዳጀው ድል ነው። ምዕራፉ ለክርስቶስ እና ለእርሱ እውነት ሲሉ በከባድ
መከራ ውስጥ ለሚያልፉ ሁሉ ማበረታቻ ይሰጣል።
ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 11፡15-18። በእነዚህ ጥቅሶች መሠረት ሰባተኛው መለከት
በሚነፋበት በመጨረሻው ጊዜ ላይ ምን ዓይነት ክስተቶች ይስተዋላሉ?
የዚህ ዓለም መንግሥታት የጌታችን መንግሥታት ሆነዋል። ክርስቶስ ድል ሲያደርግ፤ ክፉው ደግሞ ተሸንፏል። ተጋድሎው በየሱስ አሸናፊነት እና በሰይጣን ተሸናፊነት ተደምድሟል። ጽድቅ ድል ተቀዳጅቷል። እውነት ነግሷል። የሚከተለውን መመሪያ ተግባራዊ ማድረጋችን ጠቃሚ ይሆናል፡ “በሰው ሥልጣን ላይ ተመርኩዞ የተሠራ ሁሉ ፈራሽ ነው፤ በማይለወጠው የእግዚአብሔር ቃል ቋጥኝ ላይ የተመሠረተው ግን ለዘላለም ጸንቶ ይኖራል”— (ታላቁ ተጋድሎ፣ ገጽ 334)። ጥቅሱን ያንብቡ። ራእ. 11፡19። ዮሐንስ ሰማይ ተከፍቶ ያየው ምን ነበር? ወደ ውስጥ በተመለከተ ጊዜ ምን አየ?
ሰማያዊው ቤተ መቅደስ ለዮሐንስ እይታ ክፍት ተደርጎ ነበር። ወደ ቅድስተ ቅዱሳኑ
ሲመለከት የቃል ኪዳኑን ታቦት አየ። የሰማያዊው መቅደስ ምሳሌ በሆነው የብሉይ ኪዳን
ቤተ መቅደስ፣ የቃል ኪዳኑ ታቦት መክደኛ ላይ በነበሩት ሁለቱ መላእክት መካከል፣ በክብር
የተሞላው አምላካዊ መገኘት ተገልጧል። በታቦቱ ውስጥ የእግዚአብሔር ሕግ ነበረ። ምንም
እንኳ በእምነት ብቻ በጸጋው ብንድንም፣ ለእግዚአብሔር ሕግ መታዘዛችን እምነታችን
በሐቅ ላይ የተመሠረተ መሆኑን ያሳያል። የእግዚአብሔር ሕግ የፍርዱ መሠረት ነው (ያዕ.
2፡12)። ይህ እውነታ በተለይ በጊዜው መጨረሻ ላይ አስፈላጊ እና ጠቃሚ ይሆናል (ራዕ.
12፡17፣ ራእ. 14፡12)።
በፈረንሳይ አብዮት ኢ-አማኒነት እና በራእይ 11 በተገለጸው አስደናቂ መደምደሚያ
መካከል ያለው ገራሚ ንጽጽር ዛሬ እኛን ምን ያሳያል?
መጽሐፍ ቅዱስ በኃይማኖታዊና በዓለማዊ ሥልጣን ሲወገዝ፤ ምስክርነቱ
ሲጣመም፣ የሰዎች አዕምሮ ከመጽሐፍ ቅዱስ ይርቅ ዘንድ ሰዎችና አጋንንት የፈጠራ ሥራ
እንዲያደርጉ የተቻለው ሁሉ ጥረት ሲደረግ፤ የያዛቸውን የከበሩ እውነቶች ያውጁ ዘንድ
የደፈሩት ሲታደኑ፣ ሲካዱ፣ ሲገረፉ፣ ከመሬት በታች ባሉ ወህኒ ቤቶች ሲቀበሩ፣ ለእምነታቸው
መሥዋዕት ሲሆኑ ወይም ለመገኘት ወደሚያስቸግሩ ተራራዎች፣ ጉድጓዶችና ዋሻዎች
እንዲሸሹ በተገደዱበት ጊዜ… ያኔ ታማኝ ምስክሮች ማቅ ለብሰው ትንቢት ተናገሩ። ያም
ሆኖ በ1260 ዓመታት ሁሉ ምስክርነታቸውን ቀጠሉ። በድቅድቅ ጨለማ ዘመናት ውስጥ
የእግዚአብሔርን ቃል የሚወዱ፣ ለአምላክ ክብር የሚቀኑ ታማኝ ሰዎች ነበሩ። በዚህ ሁሉ
ዘመን የእርሱን እውነት ያውጁ ዘንድ ለእነዚህ ታማኝ አገልጋዮች ጥበብ፣ ኃይልና ሥልጣን
ተሰጣቸው።”—(ታላቁ ታድሎ፡ ገጽ 310-311)።
“ፈረንሳይ በአደባባይ መጽሐፍ ቅዱስን ስትከለክል፣ የእግዚአብሔር ሕግ
ከሚያስቀምጣቸው ገደቦች ነጻ የሆነ የመንግሥት መመስረት የረጅም ዘመን ፍላጎታቸው
የነበረ እርጉም ሰዎች እና የጽልመት መናፍስት እቅዳቸው ተሳክቶ በማየታቸው ፈነደቁ…
በሰይጣን ጨካኝ ኃይል ላይ ክትር የሚያበጀው፣ የሚገታው የእግዚአብሔር መንፈስ
በአብዛኛው በመነሣቱ ብቸኛ ደስታው የሰዎች ጉስቁልና የሆነው እርሱ ፈቃዱን እንዲያደርግ
ተፈቀደለት። ከአሰቃቂነቱ የተነሣ ብዕር ወረቀት ላይ ያሰፍረው ዘንድ በሚከብድ ስቃይ
ምድሪቱ እስክትሞላ ድረስ የአመጽን አገልግሎት የመረጡ አነርሱ መከሩን እንዲሰበስቡ
ተተዉ። ከጠፉ ክፍለ አገራትና ከወደሙ ከተማዎች የሰቆቃ ዋይታ፣ የመራር ስቃይ ጩኸት
ይሰማ ነበር። መሬት መንቀጥቀጥ የመታት ያህል ፈረንሳይ ተናወጠች። ኃይማኖት፣ ሕግ፣
ማህበራዊ ሥርዓት፣ ቤተሰብ አገርና ቤተ ክርስቲያን፣ ሁሉም በእግዚአብሔር ሕግ ላይ
በተነሣው አምላክን በሚያዋርድ እጅ ተመቱ።”—(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 331+332)።
"ቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያውን ዕድል (አቅርቦት) በመጠቀም እያንዳንዱን
የብርሐን ጮራ ተቀብላ፣ የሚገለጸውን እያንዳንዱን ኃላፊነት ካላከናወነች በስተቀር ኃይማኖት
ቀስ በቀስ ወደ ወግና ሥርዓት መጠበቅ ማሽቆልቆሉ አይቀሬ ነው፤ እጅግ አስፈላጊው
እግዚአብሔርን የመምሰል መንፈስም ይጠፋል”—(ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 365)።
1. የታላቁ ተጋድሎ መርኅዎች በፈንረንሳይ አብዮት የተገለጹት እንዴት ነበር?
2. አምላክ የለም ሲል የሚከራከር አንድ ሰው የሚከተለውን ጽፎ ነበር፡ “የሕግ ጥሰትን
የሚያሳይ ምልክት በሌለበት ሁናቴ ያለ ምንም የአስተሳሰብ ገደብ የገዛ ራሳችንን
እቅዶች እና ሙከራዎች እናቋቁም ዘንድ ነጻ ነን።” በዚህ አባባል “የሕግ ጥሰትን
የሚያሳይ ምልክት በሌለበት ሁናቴ” የሚለው ሃረግ ብዙዎች እግዚአብሔርን
የመቃወማቸውን ሰበብ ምክንያት ለማስተዋል ወሳኝ የሆነው ለምንድን ነው?
3. ዮሐንስ ስለ መቅደሱ ያየው ራእይ ከመጨረሻዎቹ ክስቶች በተያያዘ ያለው ፋይዳ
ምንድን ነው?