የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ታላቁ ተጋድሎ



2ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሚያዝያ 19 - 25

5ኛ ትምህርት

Apr 27 - May 3




በሁሉም ተግዳሮቶች ፊት ጸንቶ የሚቆም እምነት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ መዝ. 119:162፣ ዮሐ. 16:13–15፣ 2ጴጥ. 1:20-21፣ ኤፌ. 2:8-9፣ ሮሜ 3:23፣ 24፣ ሮሜ 6:15–18።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “አንተን እንዳልበድል፣ ቃልህን በልቤ ሰወርሁ” መዝ. 119፡ 11)።

የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች ለ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በእጅጉ የሚያሻው- -ዓላማ መር ሕይወት ነበራቸው። ታዋቂው አሜሪካዊ የሥነ ልቡና ባለሙያ ፊሊፕ ኩሽማን ዘ ኤምፕቲ ሰልፍ በተሰኘው መጽሐፋቸው ዓላማ የለሽ ሕይወት ስለሚኖሩ ሰዎች ይናገራሉ። እነዚህ ሰዎች እምነታቸው ጥልቀት የለውም። ትርጉም ያለው ነገር እነርሱን እምብዛም አይኮረኩራቸውም። ስለዚህ መሥዋዕትነት ሊከፍሉለት የሚችሉት አንዳችም ነገር የለም። በጥቅሉ በሕይወታቸው ውስጥ የከበረ ዋጋ ሊቸረው የሚችል ነገር ወይም ግብ የለም።

ይሁን እንጂ የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጅ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች ፍጹም የተለዩ ነበሩ። አብሯቸው የሚኖር ዓላማ መር ሕይወት ነበራቸው። ያመኑበት ነገር ለእነርሱ ልዩ ትርጉም ስለነበረው በያዙት እውነት ላይ መደራደር ፈጽሞ አይታሰብም።

እነዚህን እምነቶች መካድ የገዛ ማንነታቸውን እንደ መካድ ነበር። የአስፈሪውን ሞት ጽዋ በሚጎነጩበት ጊዜ እንኳ በውስጣዊ ሰላም የተሞሉ ነበሩ።

በዚህ ሳምንት ጥናታችን የተሐድሶ አራማጆችን ምሳሌ በመጠቀም፣ ሕይወት የሚለውጡት የቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮዎች እንዴት ለሕይወት እውነተኛ ዓላማ እና ትርጉም መሠረት እንደሚሆኑ እንመረምራለን። እነዚህን ዘላለማዊ እውነቶች መረዳታችን፣ በመልካም እና በክፉ መካከል ለሚካሄደው ታላቁ ተጋድሎ የመጨረሻ ቀውስ እንድንዘጋጅ ይረዳናል። የእነዛ ተሐድሶ አራማጆች ውጊያ ገና አልተጠናቀቀም፤ በመሆኑም እኛም ካቆሙበት እንድንቀጥል ተጠርተናል። እንደ እነርሱ ሁሉ፣ እኛም ለሚገጥሙን ፈታኝ ሁኔታዎች ከበቂ በላይ የሆነውን፣ ትርጉም ያለው እና ዓላማ መር ሕይወት ሊሰጥ የሚችለውን አምላክ ከቀድሞው አብልጠን ማወቅ እንችላለን። እርሱ የሚሰጠውን በዓለም ያለ ማንኛውም ነገር ሊሰጥ አይችልም። የዚህን ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ከታላቁ ተጋድሎ መጽሐፍ ከምዕ. 7-11 ያጥኑ።

ሚያዝያ 20
Apr 28

የእግዚአብሔር ቃል ብቻ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 119፡103፣104፣ መዝ. 119፡147፣ 119፡ 162። ዳዊት ለእግዚአብሔር ቃል የነበረው አመለካከት ምን ይመስላል? ይህ በተሐድሶ አራማጆች ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ምን ነበር? ዛሬስ በሕይወታችን ላይ ያለው ተጽዕኖ ምን ይመስላል?



መጽሐፍ ቅዱስ የተሐድሶ አራማጆች እምነት መሠረት እና የትምህርታቸው አስኳል ነበር። በመንፈስ ቅዱስ ምሪት የተጻፈውን ሕያው እና ጸንቶ የሚኖር የእግዚአብሔር ቃል--(1ጴጥ. 1፡23) ለሌሎች እያካፈሉ እንደ ነበር አስተውለዋል። እያንዳንዱን ቃል የከበረ አድርገው በልባቸው ሰንቀው ነበር። ገጾቹን እየገለጡ ሲያነቡና በውስጡ የሰፈሩትን የተስፋ ቃሎች ሲያምኑ እምነታቸው ጠነከረ፣ ድፍረታቸውም ታደሰ። “በእነዚያ በተሰጡን የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች እያንዳንዳችንን በግል ያናግረናል፣ ድምፁን የምንሰማ ያህል በቀጥታ ያወራናል። ክርስቶስ ጸጋ እና ኃይሉን ወደ እኛ የሚያስተላልፈው በእነዚህ የተስፋ ቃሎች አማካይነት ነው። እነርሱ ‘ሕዝቦች የሚፈወሱባቸው’ (ራእ. 22:2) የዛፉ ቅጠሎች ናቸው። ከተቀበሏቸውና ከተዋሀዷቸው በኋላ የባህሪ ጥንካሬ እና የመንፈስ ተነሳሽነት ከማምጣታቸው ባሻገር ሕይወትን ደግፈው ይይዛሉ። እንዲህ ያለ የመፈወስ ኃይል ሊኖረው የሚችል ሌላ አንዳችም ነገር የለም። ከዚህ ውጪ በሕያው ጉልበት የተሞላ ወኔ እና እምነት መስጠት የሚችል ከቶ ምንም ነገር የለም።”—Ellen G. White, The Ministry of Healing, p. 122.

ቅዱሳት መጻሕፍት በሐዘናችን ላይ ደስታ፣ በተስፋ መቁረጣችን አለኝታ በመሆን በጨለማችን ላይ የብርሐን ጸዳል ይፈነጥቃሉ። ግራ ገብቶን ውሉ ሲጠፋብን መንገዱን ያሳዩናል፤ ስንወላውል ማረጋገጫ፣ ስንደክም ደግሞ ብርታት ይሆኑናል፤ አላዋቂነታችንን ሸፍነው ጥበበኞች ያደርጉናል። በአምላካዊው ቃል ላይ ማሰላሰል ስናደርግና እነዚያ የተሰጡንን የተስፋ ቃላት በእምነት አጥብቀን ስንይዝ፣ ሕይወት ሰጭ የሆነው የእግዚአብሔር ኃይል መላው አካላችንን፣ አእምሮአችንን፣ ስሜታችንን እና መንፈሳችንን በኃይል ይሞላል።

የተሐድሶ አራማጆች አእምሮአቸውን በአምላካዊው ቃል የተሞላ እንዲሆን አድርገውት ነበር። በቃሉ ኖሩ፣ ብዙዎችም በቃሉ ምክንያት የሞት ጽዋን ተጎነጩ።

የተሐድሶ አራማጆች--ግዴለሽ፣ በራሳቸው የሚኩራሩ፣ ቸልተኞችና በታይታ እምነት የተጀቦኑ ክርስቲያኖች አልነበሩም። ያለ እግዚአብሔር ቃል ኃይል በተጻራሪ የተሠለፈውን የክፋት ኃይል መቋቋም እንደማይችሉ ያውቁ ነበር።

ጆን ዋይክሊፍ መጽሐፍ ቅዱስን ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ለመተርጎም የተነሣሣው፣ ተራው ሰው አምላካዊውን ቃል በቀላሉ ማንበብና መረዳት እንዲችል ከማሰብ የተነሣ ነበር።

ይህን ማድረግ ሕገወጥ ስለነበር በእምነቱ ምክንያት ችሎት ፊት ቀረበ፤ መናፍቅ በሚል ጥፋተኛ ሆኖ ተገኘ፤ በመጨረሻም ሞት ተፈረደበት። ዋይክሊፍ በወቅቱ እንዲህ ሲል ለችሎቱ ይግባኝ ብሎ ነበር፡ “ከማን ጋር ነው እየታገላችሁ ያላችሁት? እግሮቹ መቃብር አፋፍ ከቆሙት ሽማግሌ ጋር? በፍጹም አይደለም! ከእውነት ጋር--ከእናንተ ይልቅ ከበረታው እና ከሚያሸንፋችሁ እውነት ጋር!”—Wylie, book 2, chapter 13, quoted in Ellen G. White, The Great Controversy, p. 90. የእግዚአብሔር እውነት ብርሃን የመካከለኛውን ዘመን ጨለማ ሲገፍ፣ ዋይክሊፍ ሞት አፋፍ ላይ ቆሞ የተናገራቸው ቃላቶች ፍጻሜ አገኙ። አስቸጋሪ ጊዜ በገጠሞት ወቅት እንዴት ነበር አምላካዊው ቃል ያጸናዎት?

ሚያዝያ 21
Apr 29

የእግዚአብሔርን ቃል ማስተላለፍ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 4፡1-6፣ 2ቆሮ. 2፡14። ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት በሚያውጅበት ወቅት ፈታኝ ሁኔታዎች ቢገጥሙትም እንኳ፣ ስለ ልበ ሙሉነቱ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?



ሐዋርያው ጳውሎስ ወንጌልን በማስፋፋት ሥራው በርካታ ተግዳሮቶች ገጥመውት ነበር። ይሁን እንጂ ውሎ አድሮ የእግዚአብሔር ቃል እንደሚያሸንፍ እምነት ነበረው፡ “ለእውነት እንጂ በእውነት ላይ ምንም ማድረግ አንችልምና” (2ቆሮ. 13፡8)።

የተሐድሶ አራማጆችም ተመሳሳይ ፈተናዎች ገጥመዋቸዋል፤ ሆኖም በእምነት ለአምላካዊው ቃል በታማኝነት ጸንተዋል። ለመቋቋም አዳጋች የሚመስል ነገር ሲገጥም ዊሊያም ቲንደል ጥሩ የድፍረት ተምሳሌት ሆኖ እናገኘዋለን። የቲንደል ትልቁ ፍላጎት ትክክለኛና ሊነበብ የሚችል የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም ለእንግሊዛውያኑ መስጠት ነበር።

መጽሐፍ ቅዱስን በመጀመሪያ ከተጻፉባቸው ቋንቋዎች በቀጥታ በመተርጎም ከ200 ዓመታት በፊት በዋይክሊፍ የተሠሩ ግድፈቶችን ለማረም ቆርጦ ተነሣ።

በመጨረሻም ቲንደል ተይዞ በፍርድ ፊት ቀረበ። በዎርምስ፣ ጀርመን ታትመው የወጡት አብዛኞቹ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞቹ ተሰብስበው በዓደባባይ እንዲቃጠሉ ተደረገ። የፍርድ ሂደቱ የተካሄደው በቤልጅየም ሲሆን፣ ጊዜው 1536 ዓ.ም. ላይ ነበር።

ቲንደል በመናፍቅነት ክስ ከቀረበበት በኋላ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተፈረደበት። የሞት ቅጣት አስፈጻሚዎቹ ከግንድ ጋር እያሰሩት እያለ አንቀው ገደሉት፣ ከዚያም በድኑን በእሳት አቃጠሉ። በሞት አፋፍ ላይ እያለ፡ “ጌታ ሆይ፣ የእንግሊዝን ንጉሥ ዐይኖች ክፈት!” ሲል ከልብ በመነጨ ቅንአት ድምጹን ከፍ አድርጎ መናገሩ ተዘግቧል። እግዚአብሔርም ታምራዊ በሆነ መንገድ የቲንደልን ጸሎት መለሰ።

እርሱ በሞተ በአራት ዓመት ውስጥ--አራት የእግሊዝኛ ቋንቋ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂዎች ታተሙ። በ1611 ዓ.ም. ኪንግ ጀምስ በመባል የሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም የታተመ ሲሆን፣ መጽሐፉ በዋነኝነት የተመሠረተው በቲንደል ሥራ ላይ ነበር።

ትርጉሙ የተዘጋጀው በ54 ሊቃውንት አማካኝነት ሲሆን፣ የሚገርመው ነገር ተርጓሚዎቹ በከፍተኛ ደረጃ የተመረኮዙት በቀደመው የቲንደል ትርጉም ላይ ነበር። የ1611 ዓ.ም. የብሉይ ኪዳኑ የኪንግ ጀምስ መጽሐፍ ቅዱስ 76 ከመቶ የቲንደል ትርጉም ሲሆን፣ ከአዲስ ኪዳን ደግሞ 83 ከመቶ የሚሆነው የእርሱ ሥራ እንደሆነ ይገመታል። ኪንግ ጄምስ በመባል የሚታወቀው የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም አንድ ቢሊዮን መጽሐፍ ቅዱሶችን በማተም በጎርጎሮሳውያኑ 2011 ላይ የተመሠረተበትን 400ኛ ዓመት አከብሯል። ኪንግ ጀምስ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም በ2,454 ቋንቋዎች የተተረጎመ ሲሆን በዓለም ዙሪያ በአሥር ሚልዮን በሚቆጠሩ ሕዝቦች ላይ ከፍተኛ ተጽዕኖ አሳድሯል። የዊልያም ቲንደል መሥዋዕትነት የሚያስቆጭ ሳይሆን በብዙ እጥፍ የካሰ ነበር።

እነ ዊልያም ቲንደል የነበሩበት ሁናቴ የቱንም ያህል አስቸጋሪና ፈታኝ ቢመስልም እርሱም ሆነ መጽሐፍ ቅዱስ አማኝ ጓዶቹ፣ እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር እንደ ፈቃዱ እንደሚፈጽም እምነት ነበራቸው። የቲንደል ሕይወት ለዘላለም ለውጥ አምጥቶ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 12፡3 እና ራእ. 14፡13። ጥቅሶቹ ከቲንደል ሕይወት ጋር በጠንካራ መንገድ የሚሠሩት እንዴት ነው? አሁን ደግሞ ስለራስዎ ሕይወትና በሌሎች ላይ ሊያሳድሩ ስለሚችሉት ተጽዕኖ አሰብ ያድርጉ። እነዚህ ጥቅሶች እርስዎ በሌሎች ላይ ለዘላለም ተጽዕኖ ማሳደር የሚችሉ መሆንዎን አስመልክቶ ምን ማበረታቻ ይሰጣሉ?

ሚያዝያ 22
Apr 30

በመንፈስ ቅዱስ የበራለት


አንድ ቀን ማርቲን ሉተር በዩኒቨርሲቲ ቤተ መጻሕፍት ውስጥ እያጠና እያለ ለሕወቱ አዲስ ምዕራፍ ከፋች የሆነ ወሳኝ ነጥብ ላይ ደረሰ። በላቲን ቋንቋ የተጻፈ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ አገኘ። እንደዚህ ያለ መጽሐፍ ከእነ አካቴው ስለመኖሩ ከዚህ በፊት ፈጽሞ የማያውቀው ሉተር፣ በከፍተኛ ደስታ ሆኖ ከምዕራፍ እስከ ምዕራፍ፣ ከቁጥር እስከ ቁጥር ማንበቡን ተያያዘው። በእግዚአብሔር ቃል ግልጽነት እና ኃይል ተገረመ። ገጾቹን እየገለጠ ጥናቱን በጥንቃቄ በሚያደርግበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ አእምሮውን አበራለት። በወግ የተሸፈኑ እውነቶች ከቅዱሳት መጻሕፍት ገጾች ጋር ያለ ትስስር መቀመጣቸውን በመንፈስ ቅዱስ ምሪት አስተዋለ። ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር ስለ ነበረው የመጀመሪያ ተሞክሮ “ምን አለ አምላክ እንዲህ ያለ መጽሐፍ ለራሴ ቢሰጠኝ!” በማለት ስለመመኘቱ ጽፏል። መጽሐፍ ቅዱስን እንዴት መተርጎም እንዳለብን አስመልክቶ ከሚከተሉት ጥቅሶች ምን መርኅዎችን መውሰድ ይችላሉ?
ዮሐ. 14:25- 26



ዮሐ. 16:13–15



2ጴጥ. 1:20-21



ለመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ምሪት የሰጠው ያው መንፈስ ቅዱስ እነሆ እኛም መጽሐፉን ስናነብ ይመራናል። ይህ በጥቅሶቹ የምናገኘው ብርቱ መልእክት ነው። እርሱ የመለኮታዊው እውነት ፍቺ ሰጭ--መለኮታዊ ተርጓሚ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ፣ ዛሬ ክርስቲያን ነን የሚሉ ብዙዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የሚገኘውን ልዕለ ተፈጥሮ ባሕሪ እያቀለሉ፣ ሰብዓዊውን አላባ ደግሞ እያገነኑ እንደሆነ ይስተዋላል። ሰይጣን ከዚህ በኋላ መጽሐፍ ቅዱስን ከእጃችን መንጠቅ የማይችልበት ሁኑታ መፈጠሩን በመረዳቱ የተሻለ ያለውን ቀጣይ ስልት ይዞ ብቅ ብሏል፡ ልዕለ ተፈጥሮ ባህሪውን ገፍፎ እንደ ማለፊያ የሥነ ጽሑፍ ሥራ እንዲቆጠር ወይም ከዚያ በባሰ ብዙሃኑን ለመቆጣጠር የሚያስችል ኃይማኖታዊ መጨቆኛ መሣሪያ ማድረግ።

የቅዱሳት መጻሕፍት እንከን-የለሽ ተርጓሚ መንፈስ ቅዱስ እንጂ ካህናቱ፣ ቀሳውስቱና ሊቃነ ጳጳሳቱ አለመሆናቸውን የተሐድሶ አራማጆች በግልጽ መመልከት ችለው ነበር። በስኮትላንዳዊው የተሐድሶ አራማጅ ጆን ኖክስ እና በስኮትስ ንግሥት ሜሪ መካከል አስደሳች ውይይት መካሄዱ ተዘግቧል። “ ‘አንተ መጽሐፍ ቅዱስን በአንድ መንገድ ስትተረጉመው እነርሱ ደግሞ (የሮም አስተማሪዎች) በሌላ መንገድ ይተረጉሙታል፤ የማንን ልመን፤ ማንስ ፈራጅ ይሁን?’ ስትለው ‘እርስዎ በቃሉ አማካኝነት በግልጽ የሚናገረውን እግዚአብሔርን ይመኑ’ አለ ተሐድሶ አድራጊው፤ ‘ቃሉ ከሚያስተምረው ውጪ ይህንንም ያንንም ያምኑ ዘንድ አይገባዎትም። የእግዚአብሔር ቃል በራሱ ግልጽ ነው። ግልጽ ያልሆነ ነገር በአንድ ስፍራ ቢኖር እንኳ፣ በድንቁርናቸው መቀጠል ከሚፈልጉት በስተቀር፣ ምንም ዓይነት መጠራጠር እንዳይኖር ከራሱ ጋር የማይቃረነው መንፈስ ቅዱስ ግልጽ ያልሆነውን ያንኑ ሃሳብ በሌላ ስፍራ የበለጠ ግለጽ ይሆን ዘንድ ያብራራዋል’”—David Laing, The Collected Works of John Knox, vol. 2, pp. 281, 284, quoted in፡ ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 291)

ሚያዝያ 23
May 01

ክርስቶስ ብቻ ጸጋው ብቻ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 2:8- 9፣ ሮሜ 3:23- 24፣ ሮሜ 6:23፣ ሮሜ 5:8–10።

ጥቅሶቹ ስለ ደኅንነት እቅድ ምን ያስተምራሉ?



እግዚአብሔር ድነትን በስጦታ ሰጥቷል። ክርስቶስ በቀራንዮ መስቀል ላይ በሞቱ በነጻ የሰጠንን በእምነት እንቀበል ዘንድ መንፈስ ቅዱስ ይመራናል። መለኮታዊው የእግዚአብሔር ልጅ የሱስ፣ ፍጹም የሆነ ሕይወቱን ለኃጢአታችን ሥርየት አቀረበ።

መለኮታዊው ፍትሕ ፍጹም የሆነ ታዛዥነትን ይጠይቃል። ፍጹም የሆነው የክርስቶስ ሕይወት ፍጽምና በጎደለው ሕይወታችን ምትክ ይቆማል። የጣስነው መለኮታዊ ሕግ ዘላለማዊ ሞት ያስፈርድብናል። በዚህ ዙሪያ መጽሐፍ ቅዱስ ግልጽ ነው። በኃጢአተኛ ምርጫዎቻችን የተነሣ እግዚአብሔር ለሕይወታችን ካቀደው ሳንደርስ በአጭሩ ተሰናክለን ቀረን። ኃጢአት ሠርተናል። እንዲሁ በራሳችን የምንተው ከሆነ፣ ቅዱስ የሆነውን አምላክ ተገቢ የጽድቅ ጥያቄዎች ማሟላት አንችልም። በዚህም ምክንያት የዘላለም ሞት የሚገባን ሆንን። ይሁን እንጂ አንድ የምሥራች አለ። ሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ የሚል ማረጋገጫ ይሰጠናል፡ “የኀጢአት ደመወዝ ሞት ነውና፤ የእግዚአብሔር ስጦታ ግን በጌታችን በክርስቶስ ኢየሱስ የዘላለም ሕይወት ነው።” (ሮሜ 6፡23)። ይህ ስጦታ ነው--የማይገባን ስጦታ! ከዚህ ውጪ ድነትን በሥራችን ማግኘት እንደማንችል ወንጌል አበክሮ ይነግረናል።

ማርቲን ሉተር እና የፕሮቴስታንት ተሐድሶ አራማጆች የመዳናቸው ምንጭ ክርስቶስ እና ክርስቶስ ብቻ መሆኑን ተገነዘቡ። ሉተር የክርስቶስን የማዳን ጸጋ መልእክት መስበክ የጀመረው በዚህ ጊዜ ነበር። የእርሱን ልብ የሚነኩና ሕይወት የሚቀይሩ መልእክቶች ለመስማት ብዙዎች ጎረፉ። ከአንደበቱ ይወጡ የነበሩ ቃላት የተጠማ የምድረ በዳ ሕይወታቸውን አረሰረሰው። ሕዝቡ በመካከለኛው ዘመን የቤተ ክርስቲያን ወግና ልማድ እግር ከወርች ታስሮ አንዳችም መንፈሳዊ ሕይወት በማይሰጡና ለበርካታ መቶ ዓመታት በዘለቁ ሥርዓቶች ቀንበር ሥር ወድቆ ነበር። የሉተር መጽሐፍ ቅዱሳዊ መልእክቶች ልቦችን መንካታቸውን ተከትሎ የብዙዎች ሕይወት ተለወጠ።

ሉተር የአዲስ ኪዳን መጽሕፍትን ሲያነብ ልቡ አብልጦ በእግዚአብሔር ቸርነት ተነካ። እግዚአብሔር የሰው ልጆችን በሙሉ ለማዳን ባለው ፍላጎት ተደነቀ። የወቅቱ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች በነበራቸው አስተምህሮ መሠረት መዳን በከፊል የሰው በከፊል ደግሞ የአምላክ ሥራ እንደሆነ ተደርጎ ይቆጠር ነበር።

የክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ለሰው ልጆች ሁሉ በቂ እንደሆነ ሉተር ተገንዝቦ ነበር።

“ለእርሱ የሚገባው ለእኛ ይሆን ዘንድ በዓመጻችን ምክንያት በእኛ ላይ ሊደርስብን የሚገባው ሁሉ በእርሱ ለይ ደረሰበት። ምንም ጥፋት ሳይኖረው በእኛ ኃጢአት ተወገዘ፤ እኛም የማይገባንን በእርሱ ቅድስና ተዋጀን። የእርሱን ሕይወት እናገኝ ዘንድ ለእኛ ይገባን በነበረው ሞት ተሰቃየ።”--የዘመናት ምኞት ገጽ 15 መዳን እግዚአብሔር በክርስቶስ የሠራው ሥራ ከሆነ መልካም ሥራችን በክርስትና ሕይወት ውስጥ ምን ሚና ይኖረዋል? መልካም ሥራችንን የተስፋችን መሠረት ሳናደርግ፣ ነገር ግን ለአስፈላጊነቱ አጽንኦት የምንሰጠው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 24
May 02

መታዘዝ፡ የእምነት ፍሬ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሮሜ 3:27–31፣ ሮሜ 6:15–18፣ ሮሜ 8:1-2። በክርስቶስ ጽድቅ ብቻ የሚኘውን መዳን አስመልክቶ ጥቅሶቹ ምን ያስተምሩናል?



በሉተር ዘመን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አዲስ ነፋስ እየነፈሰ ነበር። በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከኃጢአተኛ ማንነታቸው ርቀው በምትኩ ወደ የሱስ እንዲመለከቱ ተምረዋል። እነዚህ ሰዎች ወደ ራሳቸው ሲመለከቱ--የሚያዩት ተስፋ ሊያስቆርጧቸው የሚችሉ ነገሮችን ብቻ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ዛሬስ ቢሆን ተመሳሳይ ተሞክሮ የማይጋራው አማኝ የቱ ነው? በዚህ የተነሣ ወደ የሱስ መመልከት ይኖርብናል። የእግዚአብሔር ጸጋ ይለውጠናል። በአንድ ወቅት ጆን ዌስሊ ሎንዶን በተደረገ የሞራቪያ ስብሰባ ላይ ተገኝቶ ነበር። ሉተር የሮሜን መጽሐፍ መግቢያ ሲያነብ ሲሰማ ተደነቀ። በሕይወቱ ለመጀመሪያ ጊዜ ወንጌልን መረዳት ጀመረ። በውስጡ የሆነ የመነሣሣት ስሜት ተሰማው።

እናም እንግዳ በሆነ ስሜት ሕይወቱን ለእርሱ ወደ ሰጠው ወደዚህ ክርስቶስ ተሳበ። “ለመዳን ክርስቶስንና ክርስቶስን ብቻ እንዳመንኩ ተሰማኝ፤ እርሱ ኃጢአቴን በሙሉ ወሰደ--ያውም የእኔን ኃጢአት--ከዚያም ከኃጢአትና ከሞት ሕግ እንዳዳነኝ ማረጋገጫ ተሰጠኝ”—John Whitehead, The Life of the Rev. John Wesley, M.A. (London: Stephen Couchman, 1793), p. 331. ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 1ጴጥ. 2:2፣ 2Pጴት. 3:18፣ ቆለ. 1:10፣ ኤፌ. 4:18–24።

እነዚህ ጥቅሶች ስለ ክርስትና ሕይወት የሚያሳዩአቸው ጠቃሚ እውነቶች ምንድን ናቸው?



የተሐድሶ አራማጆች ተጨማሪ እውነቶችን ለማግኘት ቃሉን በዘዴ ያጠኑ ነበር። ነገሮች በነበሩበት ሁናቴ ወይም ይህ ነው በማይባል ዕድገት በሌለው ግትር ኃይማኖዊ ተሞክሮ ውስጥ በመመላለስ እርካታ ባለማግኘታቸው፣ ክርስቶስን ይበልጥ ለማወቅ ያለማቋረጥ ይተጉ ነበር።

በመካከለኛው ዘመን የነበሩ በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ አማኞች ለነበራቸው ቁርጠኝነት እጅግ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል። ተሠቃይተዋል፣ ታሥረዋል፣ በግዞት ተወስደዋል እንዲሁም ተገድለዋል።

ንብረታቸው ተዘርፏል፣ ቤታቸው ተቃጥሏል፣ መሬታቸው ተሞጭልፏል፣ ቤተሰቦቻቸውም ለስደት ተዳርገዋል። ከምድራቸው ሲባረሩ “እግዚአብሔር የሠራትንና የፈጠራትን ከተማ” (ዕብ. 11፡10) ተጠባበቁ። ሥቃይ ሲደርስባቸው የሚያሠቃዩአቸውን ሰዎች ባረኩ፤ እንዲሁም በጨለማ የተዋጡ የሚያዡ ጉድጓዶች ውስጥ ሲማቅቁ ነገ ብሩህ እንደሚሆን በእግዚአብሔር የተሰጠውን የተስፋ ቃል ሰነቁ። አካላቸው ቢታሰርም እነርሱ ግን በክርስቶስ አርነት ወጥተው ነበር፣ በቃሉ እውነት ከእሥራት ተፈትተው በዳግም ምጽአቱ ተስፋ ተሞልተው ነበር። ወደ ራስዎ ሲመለከቱ የሚታይዎት የመዳን ተስፋ ምንድን ነው?

ሚያዝያ 25
May 03


ተጨማሪ ሀሳብ


“የእግዚአብሔር ታማኝ አገልጋዮች ብቻቸውን አልለፉም። ‘ከአለቆች እና ከሥልጣናት በሰማያዊውም ስፍራ ያለ የክፋት መንፈሳውያን’ (ኤፌ. 6፡12) ተባብረው ቢቃወሟቸውም እግዚአብሔር ግን ሕዝቦቹን አልጣለም። ዓይናቸው ቢከፈትና ቢያዩ ኖሮ ለጥንቱ ነቢይ እንደተደረገለት ሁሉ የመለኮትን መገኘት ማረጋጫ በተመለከቱ ነበር። አገልጋዩ ለኤልሳዕ እየከበባቸው ያለውን ሠራዊት ሲያመላክተው ማምለጫውንም ሁሉ ሲዘጉት ነቢዩ፣ ‘አቤቱ ያይ ዘንድ ዐይኖቹን እባክህ ግለጥ ብሎ ጸለየ’ (1ነሥ. 6፡ 17)። እነሆ ተራራው በእሳት ፈረሶች እና ሠረገሎች ተሞልቶ ነበር፣ የእግዚአብሔርን ሰው ይጠብቅ ዘንድ የሰማይ ጭፍራ ሰፍሮ ነበር። እንዲሁም መላእክት የተሐድሶውን እንቅስቃሴ ይጠብቁ ነበር።” (ታላቁ ታድሎ፡ ገጽ፡ 242)።

“የተሐድሶውን እምነት ለመገልበጥ ኃያል ጠላቶች ሲያብሩ፣ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰይፎች ተመዝዘው የተቀሰሩበት ሲመስል፣ ሉተር፡ ‘ሰይጣን እጅግ ተቆጥቶአል፤ እዚአብሔርን የማይመስሉ ቀሳውስት በአንድ እየመከሩ፣ ጦርነት እንደሚከፈትብንም እያስፈራሩን ነው።

ጠላቶቻችን በእዚአብሔር መንፈስ ተሸንፈው ወደ ሰላም ይመጡ ዘንድ፣ በጌታ ዙፋን ፊት፣ ከልባቸው ተደፍተው በእምነት እና በጸሎት ይሟገቱ ዘንድ ሕዝቡን ተማጸኑ። የሚያስፈልገን አጣዳፊው ነበር፣ መጀመሪያ ማድረግ የሚጠበቅብን ነገር፣ መጸለይ ነው። በዚህ ሰዓት ለሠይፍ ስለትና ለሰይጣን ቁጣ ተጋልጠው እንዳሉ ሕዝቡ እንዲያውቁት ይደረግ፣ ይጸልዩ።’ ” አለ።- D’Aubigne, p. 10, ch. 14--ታላቁ ታጋድሎ፡ ገጽ 242-243።

ጽድቅ በእምነት--ሉተር እንደገና በአዲስ መልክ ያገኘው ታላቅ እውነት ሲሆን፣ ይህ እውነት የመዳን ተስፋችን የሚያርፍበት የወንጌል መሠረት ነው። “ኃያል ምሽግ” የተሰኘው መዝሙሩ ወንጌልን በብርቱ መንገድ ይገልጣል፡ “በራሳችን ጉልበት ለመታመን ብንጥር፣ ልፋታችን ሽንፈት፣ ከንቱ በሆነ ነበር። የእግዚአብሔር የራሱ፣ የምርጫው ሰው እርሱ፣ ቆመ ከጎናችን በአምሳል በሥጋችን፤ አርሱ ማን ነው--ብለን ብንጠይቅ፣ ስሙ ጸባኦት ጌታ፤ ክርስቶስ የሱስ እንደሆነ እንወቅ፣ ከዘመን ዘመን ያው የሆነው፣ የተጋድሎው አሸናፊ ጌታ እኮ እርሱ ነው።” —Seventh-day Adventist Hymnal (Hagerstown, MD: Review and Herald Publishing Association, 1985), No. 506.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በጸጋና በሕግ እንዲሁም በእምነትና በመልካም ሥራ መካከል ያለውን ሚዛናዊነት እንዴት መግለጽ እንችላለን?

2. አእምሯችን ሕግን ብቻ ጠብቆ መዳን ወደ ተሰኘው ሕጋዊነት ጭልጥ ብሎ እንዲገባ ማድረግ በጣም ቀላል የሆነው ለምን ይመስልዎታል? ሕጋዊነትን እንዴት ይገልጹታል? በክርስትና እምነታችን ላይ ከፍተኛ ጉዳት የሚያስከትል ሆኖ የምናገኘው ለምንድን ነው?

3. "በጸጋው መዳን" የሚለውን ጽንሰ ሐሳብ በትክክል አለመረዳት አደጋ አለው? ይህ የተሳሳተ አረዳድ ወዴት ሊያመራ ይችላል?

4. አንዳንዶች “ርካሽ ጸጋ” ሲሉ ይደመጣሉ። ምን ማለታቸው ነው? ለመሆኑ አምላካዊው ጸጋ ርካሽ ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL