የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ታላቁ ተጋድሎ



2ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሚያዝያ 12 - 18

4ኛ ትምህርት

Apr 20 - 26




ለእውነት መቆም



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዳን. 7:23–25፣ ራእ. 12:6፣ 14፣ መሳፍ. 3፣ 4፣ ራእ. 2:10፣ ሐዋ. 5:28–32፣ መዝ. 19:7– 11፣ 1ዮሐ. 5:11–13።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ሙሴ በምድረ በዳ እባብን እንደ ሰቀለ፣ የሰው ልጅም እንዲሁ ሊሰቀል ይገባዋል፤ ይኸውም በእርሱ የሚያምን ሁሉ የዘላለም ሕይወት እንዲኖረው ነው” (ዮሐ. 3:14-15)።

የዛሬዋ ዘመናዊ የቱርክ የባህር ዳርቻ ከተማ የሆነችው ኢዝሚር በአንድ ወቅት ሰምርኔስ በሚል በራእይ መጽሐፍ የተጠቀሰችው የመጽሐፍ ቅዱስ ከተማ ነበረች። ይህች ጥንታዊት ከተማ በመጀመሪያው እና በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን መገባደጃ ላይ ወደ 100,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች ነበሯት። ከተማዋ በሐብት የበለጸገች ከመሆኗ በተጨማሪ ለሮም እሴቶችና እና እምነት እውነተኛና ጥብቅ ታማኝነት ነበራት።

መላው የሰምርኔስ ነዋሪ በዓመት አንድ ጊዜ ለሮማውያን አማልክት ዕጣን እንዲያጥን ይታዘዝ ነበር። ሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ላይ ሰምርኔስ እየተስፋፋና እያደገ ይሄድ የነበረ የክርስቲያን ማኅበረሰብ ማፍራቷን ተከትሎ ብዙዎች ይህን ትእዛዝ ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበሩም። የዚያን ዘመኗ ቤተ ክርስቲያን መሪ የነበረው ፖሊካርፕ ለሮማ አማልክቶች ዕጣን በማጠን ጌታን አልክደውም በማለቱ፣ በግንድ ላይ የፍጥኝ ታስሮ በሰምርኔስ አደባባይ በእሳት ተቃጥሎ የሰማዕትነት ሞት ሞተ። አንጋፋው ፖሊካርፕ ክርስቶስን እንዲክድ ለመጨረሻ ጊዜ ለቀረበለት ጥያቄ ሲመልስ እንዲህ ነበር ያለው፡ “እርሱን ለሰማንያ ስድስት ዓመታት ሳገለግል አንዳች የበደለኝ ነገር አልነበረም። ታዲያ ባዳነኝ ንጉሤ ላይ እንዴት ክፉ ልናገር?"

ለበርካታ መቶ ዓመታት ወንዶችና ሴቶች በክርስቶስ ያላቸውን እምነት ከመተው ይልቅ ሰማዕትነትን ለመቀበል ፈቃደኞች ነበሩ። እነዚህ ወገኖች የከፈሉት መሥዋዕትነት በእኛም ዘንድ መነቃቃት በመፍጠር ወኔአችንን ያድሳል። ለክርስቶስ ቁርጠኛ የመሆናቸው ታሪክ ታማኝነታችንን እንድናድስ ይረዳናል። በዚህ ሣምንት ዋልዴንሶችን እና ኋላ ላይ ደግሞ እንደ ሁስ እና ጀሮም የመሳሰሉ የተሐድሶ አራማጆች ላይ መነሳሳት የፈጠሩ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎችን እንመለከታለን። እነዚህ ሕዝቦች ፖሊካርፕን የገደለው የሮም ኃይል (በዚህ ወቅት ደግሞ ጳጳሳዊው ሥርዓት) የሞት ዛቻ ቢያደርስባቸውም እነርሱ ግን ምንም ይምጣ ምን ለጌታ ታማኝ ሆነው ጸኑ። የዚህ ሳምንት ጥናት በታላቁ ተጋድሎ መጽሐፍ ከምዕ. 4-6 ያለውን ታሪክ ይሸፍናል።

ሚያዝያ 13
Apr 21

የስደት ገፈት ቀማሾቹ፣ ግን አሸናፊዎቹ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዳን. 7:23–25፣ ራእ. 12:6፣ 14. በጥቅሶቹ የቀረቡት ትንቢታዊ ጊዜያቶች ምንድን ናቸው?



የአምላክ ሕዝቦች ለእርሱ ታማኝ ሆነው በቆዩ ቁጥር ሰይጣን ክፉኛ ይበሳጫል።

ብዙውን ጊዜ ይህን ተከትሎ ስደት ይመጣል። ነቢዩ ዳንኤል ከእርሱ ገና ወደፊት ባለው፣ መካከለኛው ዘመን “በቅዱሳን ላይ ጦርነት” የሚታወጅበትና ስደት የሚደርስበት ጊዜ እንደሚመጣ ገልጾአል (ዳን. 7፡21፣ 25)። ዮሐንስ ይህንኑ ዘመን የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን ወደ ምድረ በዳ እንድትሸሽ የምትገደድበት ወቅት እንደሆነ የገለጸ ሲሆን፣ በዚያም “ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ በክብካቤ” ትኖራለች (ራእ. 12፡ 6)። ራእ. 12፡6 አክሎ ሲናገር “ሴቲቱም አንድ ሺሕ ሁለት መቶ ስድሳ ቀን ክብካቤ እንዲደረግላት እግዚአብሔር ወዳዘጋጀላት ስፍራ ወደ በረሓ ሸሸች።” የእግዚአብሔር ሕዝቦች በምድረ በዳ ቆይታቸው ዘመን ተገቢው እንክብካቤ ተደርጎላቸው ነበር። በዚያ ረጅም እና በጽልመት የተዋጠ ጳጳሳዊ ሥርዓት የግዛት ዘመን ከአስከፊ ቁጣ--እነሆ ቃሉ አበረታታቸው፣ ጠበቃቸውም።

የእግዚአብሔር ሕዝቦች በአምላካቸው “የተዘጋጀላቸውን ስፍራ” አገኙ። በሕይወት ዘመን ፈታኝ ሁኔታዎች ሲገጥሙ እግዚአብሔር ሁሌም ለታማኝ ተከታዮቹ መሸሸጊያ ስፍራ ያዘጋጃል። በእነዚያ እጅግ ከባድ በነበሩ የፈተና ወቅቶች፣ ሕዝቦቹ በፍቅሩና ጥንቃቄው ውስጥ ከለላ አግኝተው ነበር (መዝ. 46)።

በራእ. 12፡6፣ 14 የቀረቡት 1,260 ቀናት እና ለአንድ ዘመን፣ ለዘመናትና ለዘመን እኩሌታ--የሚናገሩት ተመሳሳይ ስለሆኑ ጊዜያቶች ነው (3½ ዘመናት ወይም ዓመታት × በ360 ቀናት/ዓመት/= 1,260)። የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢቶች ብዙውን ጊዜ የሚጻፉት ተምሳሌታዊ አቀራረቦችን ተከትሎ ነው። በዳንኤል እና ራእይ ትንቢታዊ አቀራረብ አንድ ትንቢታዊ ቀን ከአንድ ዓመት ጋር እኩል ነው። ይህ አንድ ቀንን እንደ አንድ ዓመት የመቁጠር መርኅ በዘኁ. 14፡34 እና በሕዝ. 4፡6 ላይ ቀርቦ እንመለከታለን።

የቀን-ዓመት መርኅ በእነዚህ ሁለት ጥቅሶች ላይ ብቻ የተመረኮዘ ሳይሆን፣ ሰፊ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው። የዘመን አቆጣጠር እና የብሉይ ኪዳን ምሑር የሆኑት ዶክተር ዊልያም ሺ ለዚህ መሠረታዊ መርኅ ከብሉይ ኪዳን መጻሕፍት 23 የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃዎችን ያቀርባሉ። የመጽሐፍ ቅዱስ ተርጓሚዎች ይህን መርኅ በመቶዎች ለሚቆጠሩ ዓመታት ተጠቅመውበታል።

ቪሲጎቶች፣ ቫንዳልስ እና ኦስትሮጎቶች ከይፋዊው የሮም አስተምህሮ የተለየ ኃይማኖታዊ ትምህርት የሚከተሉ ነገዶች ነበሩ። 1,260ዎቹ ቀናት የጀመሩት፣ ከእነዚህ ጎሣዎች መካከል የመጨረሻ የሆኑት ኦስትሮጎቶች በ538 ዓ.ም. ከሮም በተባረሩበት ወቅት ነበር። የናፖሊዮን የጦር አበጋዝ የነበረው ጄነራል በርቲየር ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱን ከሮም እስካስወገደበት 1798 ዓ. ም. ድረስ ይህ የመንፈሳዊ ጨለማ ዘመን ቀጠለ። በዚህ ረጅም ዘመን የእግዚአብሔርን ቃል በመታዘዛቸው ስፍር ቁጥር የሌላቸው ክርስቲያኖች የሰማዕትነትን ጽዋ ተጎነጩ። እነዚህ ወገኖች በሞታቸው እንኳ ሳይቀር አሸነፉ። ከጥፋተኝነት ስሜት እና ከኃጢአት ቀንበር በክርስቶስ ነጻ ወጥተው “በበጉ ደም” አሸነፉ። ክርስቶስ በመስቀል ላይ የተቀዳጀው ድል የእነርሱ ድል ነበር። ቢገደሉም፣ ሰማዕትነታቸው እስከ ክርስቶስ ዳግም ምጽአት ብቻ የሚቆይ እንቅልፍ ነበር። ፍጻሜ ያገኘው የመጽሐፍ ቅዱስ ትንቢት ምን ያህል እምነትዎን አበረታታው?

ሚያዝያ 14
Apr 22

ብርሃን ጨለማን ድል ይነሳል


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ይሁዳ 3፣4። በዚህ ስፍራ የተሰጠው ማስጠንቀቂያ ምንድን ነው? በኋለኛይቱ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ተግባራዊ መሆን ቻለ?



የይሁዳ መጽሐፍ “በእግዚአብሔር አብ ለተወደዱትና በኢየሱስ ክርስቶስ ለተጠበቁት” (ይሁዳ 1፡1) ታማኝ ክርስቲያኖች በ65 ዓ.ም. ገደማ ተጻፈ። እነዚህ ቅን አማኞች “ለቅዱሳን አንዴና ለመጨረሻ ስለ ተሰጠው እምነት” እንዲጋደሉ ጥብቅ ማሳሰቢያ ተሰጥቶአቸው የነበረ ሲሆን፤ ለዚህ ምክንያቱም “የአምላካችንን ጸጋ በርኩሰት የሚለውጡ አንዳንድ ሰዎች ሾልከው” ወደ ምዕመኑ በመግባታቸው ነበር--(ይሁዳ 1፡3-4)። ይህ ማሳሰቢያ አረማዊ ልማዶች ወደ ቤተ ክርስቲያን ከገቡ እና የሰዎች ወጎች የእግዚአብሔርን ቃል ከጣሱ በኋላም እንኳ በመካከለኛው ዘመን ላሉ አማኞች የበለጠ ትርጉም ነበረው። እንደ ዎልደንሳውያን ያሉ ሕዝቦች ለበርካታ መቶ ዓመታት ለቅዱሳን መጻሕፍት እውነቶች ያሳዩት ጽኑ ተፋላሚነት ወደር የማይገኝለት ነበር። ክርስቶስን እንደ ብቸኛ አማላጃቸው ያምኑ የነበረ ሲሆን፣ መጽሐፍ ቅዱስን ደግሞ እንደ ብቸኛ የሥልጣን ምንጭ ይመለከቱ ነበር። “በሁሉም ዘመን--በእግዚአብሔር እና በሰው መካከል እንደ ብቸኛ አስታራቂ አድርገው በክርስቶስ ላይ ያላቸውን እምነት ተንከባክበው የያዙ፣ መጽሐፍ ቅዱስን እንደ ብቸኛ የሕይወት መመሪያ የሚከተሉና እውነተኛውን ሰንበት በቅድስና የሚጠብቁ ምስክሮች እግዚአብሔር ነበሩት”— Ellen G. White, The Great Controversy, p. 61 ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 2፡10። እግዚአብሔር እስከ ሞት እንኳ ታማኝ ለሆኑ ወገኖች የሚሰጠው የተስፋ ቃል ምንድን ነው?



እነዚህ ቃላት የተጻፉት በሰምርኔስ ላለችው ቤተ ክርስቲያን ነበር። ከተማዋን ከክፉ እንደሚጠብቁ ተደርገው ይታመኑ ከነበሩ አማልክት አንዱ--የበዓላት እና የመራባት አምላክ የሆነው ዲዮናስዩስ ነበር። የዲዮናስዩስ ካህናት ሲሞቱ በቀብር ሥነ ሥርዓታቸው ሰልፍ ላይ በዐናቶቻቸው ዘውድ ይደፋላቸው ነበር። ዮሐንስ ይህን በሞታቸው ሥነ ሥርዓት ወቅት በዐናታቸው የሚደፉትን ምድራዊ ዘውድ፣ በክፉው ኃይሎች ላይ ድል በተቀዳጁ ሰዎች ዐናት ላይ ከሚደፋው የሕይወት አክሊል ጋር አነጻጽሮታል። የሕይወትን አክሊል የሚደፉ ለክርስቶስ ሲሉ በፈተና፣ በችግር፣ በመከራ ብሎም በሞት ሸለቆ ሳይቀር በጽናት የሚያልፉ ናቸው።

የሕይወት አክሊል--እነዚህ ታማኝ ወገኖች ለክርስቶስ ሲሉ ሞትን እንኳ ሳይቀር በጽናት ያልፉ ዘንድ መንፈሳቸውን አነሣስቷል። የሕይወት አክሊል ሁሌም ቢሆን በአስቸጋሪ ሁኔታዎች ውስጥ ለሚገኙ አማኞች መነሣሣት ይፈጥራል። የሕይወት አክሊል በአስከፊ ሥቃይና ስደት ውስጥ ለነበሩ ዋልደንሳውያን ከፈጠረላቸው መነቃቃት አኳያ አንድ ቀን የሱስን እንደሚያዩትና ከእርሱ ጋር ለዘላለም እንደሚኖሩ ያውቁ ነበር። ምንም እንኳ ዛሬ እጅግ ፈታኝ በሆኑ ፈተናዎች ውስጥ ብናልፍም፣ ዐይኖቻችን በየሱስ ላይ እስከ ተተከሉ ድረስ የሕይወት አክሊል ይጠብቀናል። ፈታኝ ጊዜያቶች ሲገጥሞት በምን ይበረታታሉ? የሚያስፈራዎ ምንድን ነው? እነዚያ ጊዜያቶች ሲከሰቱ ተስፋ የሚያደርጓቸው አምላካዊ ቃሎች የትኞቹ ናቸው?

ሚያዝያ 15
Apr 23

በጀግንነት ለመቆም የሚያስችል ድፍረት


ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ሐዋ. 5፡28-32፣ ኤፌ. 6፡10-12፣ ራእ. 3፡11። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የምናገኘው መሠረታዊ መርኅ ምንድን ነው?



ከዋልደንሳውያን እና እያንዳንዱ የተሐድሶ አራማጅ መለያ ባህሪዎች አንዱ ለእግዚአብሔር የነበራቸው ፍጹም ታማኝነት፣ ለቅዱሳት መጻሕፍት ሥልጣን መታዘዛቸው እና ለጳጳሳዊው ሥርዓት ሳይሆን ለክርስቶስ የበላይነት ቁርጠኞች መሆናቸው ነበር።

አእምሮአቸው በአዲስ ኪዳን የእምነት እና ጀግንነት ታሪኮች የተሞላ ነበር።

ከጴጥሮስ እና ሐዋርያት ጋር በመሰለፍ “ከሰው ይልቅ ለእግዚአብሔር ልንታዘዝ ይገባል!” (ሐዋ. 5፡29) ይሉ ነበር። “በጌታና ብርቱ በሆነው ኀይሉ ጠንክሩ” (ኤፌ. 6፡10) ሲል ጳውሎስ የሰጠውን ምክር አጥብቀው ያዙ። “ቶሎ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጥብቀህ ያዝ” (ራእ. 3፡11) የሚለውን የየሱስ ምክር ከልባቸው ያዙ። ራሳቸውን ለሮም ቤተ ክርስቲያን ወግ እና ልማድ ከማስገዛት ይልቅ፣ ለአምላካዊው ቃል እውነት ጥብቅና የመቆም ድፍረት ነበራቸው።

ዋልደንሳውያን መጽሐፍ ቅዱስን በራሳቸው ቋንቋ ከተረጎሙ የመጀመሪያዎቹ ቡድኖች መካከል አንዱ ነበሩ። ዋልደንሳውያን የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂን እንዴት በእጃቸው እንደጻፉ የሚያትተው ልብ የሚነካ ታሪክ በዣን ሌገር የተጻፈ ሲሆን፣ ንድፎችን ጨምሮ ስለ ሥራቸው የሚገልጹ መረጃዎች በጽሑፉ ተካተዋል። ዋልደንሳውያን ማኅበረሰባቸው ይኖርበት በነበረው ሰሜናዊ ጣሊያን እና ደቡብ ፈረንሳይ በሚገኙ ተራራማ መልክአ ምድሮች ቅዱሳን መጻሕፍትን በድብቅ ይገለብጡ ነበር። ወጣቶች ገና በለጋ ዕድሜአቸው ረዘም ያሉ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶችን በቃላቸው እንዲሸመድዱ በወላጆቻቸው ይበረታቱ ነበር።

የመጽሐፍ ቅዱስን ቅጂ የሚገለብጡ ቡድኖች ግንባር ፈጥረው ሥራቸውን በትጋት ያከናውኑ ነበር። ከእነዚህ ዋልደንሳውያን ወጣቶች መካከል በርካቶች እንደ ነጋዴ በመላው አውሮፓ እየተጓጓዙ ያለ አንዳች ኮሽታ የቅዱሳት መጻሕፍትን እውነት ያካፍሉ ነበር። አንዳንዶች በዩኒቨርሲቲ ተመዝግበው በመማር አጋጣሚው ሲከሰት አብረዋቸው ለሚማሩ ተማሪዎች የተወሰኑ የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን አካፍለዋቸዋል። በመንፈስ ቅዱስ እየተመሩ፣ በሚሠሩት የመመስከር ሥራ እውነትን ለማወቅ የሚሻው ወገን የመቀበል አዝማሚያ በሚያሳይበት ትክክለኛው ወቅት ላይ፣ የተመረጡ ጽሑፎችን በነጻ ይሰጡ ነበር። ብዙዎች ስለ ታማኝነታቸው በሕይወታቸው ዋጋ ከፍለዋል። ዋልደንሳውያን እያንዳንዱን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት በግልጽ ባይረዱም እንኳ የእግዚአብሔርን ቃል እውነት ለሌሎች በማካፈል ለብዙ መቶ ዓመታት ተጠብቀው እንዲቆዩ አድርገዋል።

“የጻድቃን መንገድ ሙሉ ቀን እስኪሆን ድረስ፣ ብርሃኑ እየጐላ እንደሚሄድ የማለዳ ውጋጋን ነው” (ምሳ. 4፡18)። ሰሎሞን እግዚአብሔር ልጆቹን የሚመራበትን መንገድ ይበልጥ እየደመቀች ከምትሔደው ጀምበር ጋር በንጽጽር ያቀርባል። እግዚአብሔር የጠፈርን ብርሃን ቢለቀውና ጸሐይዋ እንደ አምፖል ባንዴ ቦግ ብላ በሙሉ ኃይሏ ብትበራ፣ ዐይኖቻችን በታወሩ ነበር። ዓለም ለብዙ መቶ ዓመታት በጨለማ ከዳከረች በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ለቃሉ ታማኝ የሆኑና ተጨማሪ ፍተሻ ማድረጋቸውን የቀጠሉ ወንዶች እና ሴቶችን አስነሣ። የክርስቶስን ብርሃን በማኀበረሰባችን ውስጥ እንዴት ማንጸባረቅ እንችላለን?

ሚያዝያ 16
Apr 24

የተሐድሶው አጥቢያ ኮከብ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 19፡7-11፣ መዝ. 119፡140፣ ኤር. 15፡16። ዳዊት እና ኤርምያስ በእርግጥም የተሐድሶ የማዕዘን ድንጋይ ስለነበረው አምላካዊ ቃል ምን ተመሳሳይ አመለካከቶችን ተጋርተዋል?



እያንዳንዱ የተሐድሶ አራማጅ በእግዚአብሔር ቃል “ደስተኛ” ነበር። የአምላክን ፈቃድ በማድረግ አብልጠው “ደስ” ተሰኝተዋል። የእግዚአብሔርን ሕግ “ወደዱ”። ዋንኛ ከነበሩት የተሐድሶው መሠረታዊ እውነቶች አንዱ ቅዱሳን መጻሕፍትን በማጥናት ያገኙ የነበረው ደስታ ነው። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አድካሚ ወይም አታካች ነገር አልነበረም።

ሕጋውያን መሆንም አይደለም። ድርቅ ያለ ድንጋጌ ሳይሆን ደስታ ነው።

ቅዱሳት መጻሕፍትን ሲያጠኑ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተለወጡ። “የዋይክሊፍ ሕይወት፣ የቅዱሳት መጻሕፍት የማስተማርና የመለወጥ ኃይል ምስክር ነው። መሆን የቻለውን እንዲሆን ያደረገው መጽሐፍ ቅዱስ ነበር። የመገለጡን ታላቅ እውነቶች ለመረዳት የሚደረግ ጥረት ለሁሉም ብልቶች ጥንካሬና እድሳት ይለግሳል፤ አእምሮን ያሰፋል፤ መረዳትን ይስላል፤ ሚዛናዊነትን ያጎመራል። የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ማንኛውም ሌላ ጥናት ሊያደርገው በማይችል ሁኔታ እያንዳንዱን አስተሳሰብ፣ ስሜትና ምኞት ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ የዓላማ ጽናትን፣ ትዕግሥትን ጀግንነትንና ጽናትን ያላብሳል፤ ባህሪን ያነጥራል፤ ነፍስንም ይቀድሳል። በቅንነትና በአክብሮት የሚደረግ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የደቀ መዝሙሩን አእምሮ ከዘላለማዊ ሕሊና ጋር በቀጥታ በማገናኘት፣ እጅግ የተዋጣለት ከሚባል የሰዎችን ፍልስፍና መሠት ካደረገ ሥልጠና ይልቅ ጠንካራና የተሻለ የማመዛዘን ችሎታ ያላቸው ሰዎችን ለዓለም ያበረክታል”--ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 111። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ጢሞቴ. 2፡1-3። የእግዚአብሔርን ቃል ለሌሎች ማካፈልን አስመልክቶ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ያካፈለው ምክረ ሀሳብ ምን ነበር?



የእግዚአብሔር ቃል እውነትና በክርስቶስ የሚገኘው የመዳን ደስታ የተሐድሶ አራማጆችን ልብ አብልጦ በመንካቱ ይህን እውነት ለሌሎች ማካፈል እንዳለባቸው ተሰማቸው። ጆን ዋይክሊፍ የእግዚአብሔርን ቃል ወደ እንደግሊዝኛ ቋንቋ በመተርጎም ሕይወቱን ለዚህ ዓላማ ያዋለው በሁለት ምክንያቶች ነበር--ሕያው የሆነው ክርስቶስ በቃሉ አማካይነት ስለለወጠው እና የክርስቶስ ፍቅር የተማረውን ለሌሎች እንዲያካፍል ስላነሣሣው።

ከዋይክሊፍ በፊት ወደ እንግሊዝኛ የተተረጎመ የመጽሐፍ ቅዱስ ቅጂ በጣም ጥቂት ነበር። የሚገርመው ዋይክሊፍ ከሞተ ከአራት አሥርተ ዓመታት በኋላ፣ በቁጭት የነደዱት የሮም ኃይሎች መቃብሩን ቆፍረው፣ ዐጥንቱን አውጥተው በማቃጠል ዐመዱን ወንዝ ላይ በትነውታል። ነገር ግን ልክ እንደዚያ በወንዙ ላይ የተበተነ ዐመድ፣ የሕይወት ውሃ የሆነው የእግዚአብሔር ቃል ከአንዱ የምድር ጫፍ እስከ ሌላኛው ተሰራጭቷል። በዚህ መልኩ እግዚአብሔር--“የተሐድሶ ንጋት ኮከብ” አድርጎ ተጠቅሞበታል።

ሚያዝያ 17
Apr 25

ልብ በሚያሞቅ ተስፋ መሞላት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 2፡14-15። በመካከለኛው ዘመን የነበሩ አማኞች የታላቁን ተጋድሎ ተጨባጭ እውነታ የተለማመዱበት መንገድ ምን ይመስላል?



ታማኞቹ ዎልደንሳውያን በገጠሟቸው አሰቃቂ የስደት ወቅቶች ልባቸውን በሐሴት የሞላው ነገር ምን ነበር? ሁስ እና ጀሮም፣ ቲንደል፣ ላቲመር እና የመካከለኛው ዘመን ሰማዕታት የእሳቱን ነበልባል እና የተሳለውን ሰይፍ ለመጋፈጥ ድፍረት የሰጣቸው ምን ነበር? አዎ-- በእግዚአብሔር የተስፋ ቃል ላይ የነበራቸው እምነት! ክርስቶስ “እኔ ሕያው ስለሆንሁ እናንተም ሕያዋን ትሆናላችሁ” (ዮሐ. 14፡19) ብሎ በሰጠው የተስፋ ቃል ጽኑ እምነት ነበራቸው። የእርሱ ብርታት ለሕይወት ከባባድ ፈተናዎች በቂ እንደሆነ ተረድተዋል። እንደውም ከክርስቶስ ጋር ኅብረት ፈጥረው ስለ እርሱ ሥቃይ በመቀበላቸው ሐሴት አድርገዋል። በዚህም ታማኝነታቸው ለዓለም ብርቱ ምስክር ሆነ።

አሁን ካለው ባሻገር ያለውን እውነታ ተመለከቱ። ሞት በክርስቶስ ትንሣኤ የተሸነፈ ጠላት መሆኑን በሚገባ ተረድተዋል። ለእነዚህ በድፍረት የተሞሉ ወንዶች እና ሴቶች የሞት ማነቆ ተበጥሶ ነበር። በእግዚአብሔር ቃል የተሰጧቸውን ተስፋዎች አጥብቀው በመያዝ በድል አድራጊነት ወጡ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 5፡24፣ ዮሐ. 11፡25-26፣ 1ዮሐ. 5፡11-13። ጥቅሶቹ ለእርስዎ በግል የሚሰጥዎ ዋስትና ምንድን ነው? የሕይወት ፈተና ሲመጣ እንዴት ይረዱናል?





ጆን ሁስ እሥራት፣ የፍትሕ እጦት እና ሞት ቢደርስበትም፣ የሚናወጥ ሰው ግን አልነበረም። ለበርካታ ወራት በወህኒ ማቅቋል። እጅግ ከመቀዝቀዙ የተነሣ ወለልና ግድግዳው በሚያዥ እሥር ቤት ውስጥ የያዘው በሽታ ሕይወቱን ሊቀጥፍ ምንም አልቀረውም ነበር።

ሆኖም፡ “የእግዚአብሔ ጸጋ አጽንቶ አቆመው። ከመጨረሻው ቅጣቱ በፊት ባሳለፋቸው የሥቃይ ሳምንታት ሰማያዊ ሰላም ነፍሱን ሞልቶት ነበር። ‘ይህንን ደብዳቤ’፣ አለ ለአንድ ጓደኛው ሲጽፍ፣ ‘የምጽፈው እጄ በሰንሰለት ታስሮ የሞት ፍርድ ነገ እንደሚፈጸምብኝ በመጠባበቅ ነው… ወደፊት በሚመጣው ባስደሳቹና ሰላማዊ ሕይወት፣ በክርስቶስ እርዳታ እንደገና ስንገኛኝ በፈተናዎቼና በመከራዬ ውስጥ እግዚአብሔር እንዴት እንደረዳኝ፣ ጌታ እንዴት እራሱን በምሕረት እንደገለጸልኝ ያኔ ይገባሃል።’ Bonnechose, Vol. 2 ገጽ 67። በእስር ቤት ጽልመት ውስጥ ሆኖ የእውነተኛውን እምነት ድል ወደፊት ተመለከተ።” ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 126።

የሐዋርያውን ጳውሎስ ምክር ዛሬ በዚህ ዘመን ይበልጥ ጠቃሚ ሆኖ እናገኘዋለን፡ “የተስፋን ቃል የሰጠን ታማኝ ስለሆነ፣ አምነን የምንናገርለትን ተስፋ አጥብቀን እንያዝ” (ዕብ. 10፡23)። የእግዚአብሔር ተስፋዎች ባለፉት ዘመናት ህዝቡን በጽናት እንዳቆሙ ሁሉ ዛሬም ለእኛ ድጋፍና መጽናኛ ይሆኑናል። ለክርስቶስ ሁሉንም ነገር ማጣት ሲባል ምን ማለት ሊሆን ይችላል? በመጨረሻ ምን ሊያጡ ይችላሉ? (ማር. 8፡36)። በምድር ላይ በሚካሄደው የመጨረሻ ተጋድሎ ለእኛ ብርቱ መጽናኛ ሊሆኑ ከሚችሉት ዋልደንሳውያን እና የተሐድሶ አራማጆች ምን ትምህርት እናገኛለን?

ሚያዝያ 18
Apr 26


ተጨማሪ ሀሳብ


“የሮምን አብዛኞቹን ስህተቶች በመግለጥ በእነዚህ በተመረጡ ሰዎች ላይ ታላቅ የብርሐን ጮራ እንዲያንጸባርቅ የአምላክ ፈቃድ ሆነ። ለዓለም ሊሰጥ ያለውን ሁሉንም ብርሐን ግን አልተቀበሉም ነበር። በእነዚህ አገልጋዮቹ አማካይነት እግዚአብሔር ሕዝቡን ከሮማዊነት ጨለማ እያወጣ ነበረ። ነገር ግን መጠነ ሰፊና ታላላቅ መሰናክሎችን ማለፍ ነበረባቸው፤ እናም መሸከም በሚችሉት መጠን፣ ደረጃ በደረጃ እግዚአብሔር መራቸው። ሁሉንም ብርሐን በአንድ ጊዜ ይቀበሉ ዘንድ የተጋጁ አልነበሩም። በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ ይኖሩ ለነበሩ ሰዎች የቀትር ጸሐይ ብርሐን በሙላት ወገግ ቢል እንደሚሆኑት ሁሉ፣ (ሙሉው እውነት) ቢቀርብላቸው ኖሮ ፊታቸውን እንዲያዞሩ ያደርው ነበር። ስለዚህ በሕዝቡ ዘንድ ተቀባይነት በሚያገኝበት መጠን፣ እግዚአብሔር ለመሪዎቹ ጥቂት በጥቂት፣ ይገልጥላቸው ነበር። ሕዝቡን ወደ በለጠና ጥልቅ ተሐድሶ የሚመሩ፣ በየክፍለ ዘመኑ ወደፊት የሚነሡ ታማኝ አገልጋዮች ፈለጉን ተከትለው ይነሱ ዘንድ ነበራቸው።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 121-- ትርጉም፡ መታገስ አጋዤ)።

“በጻፈው ደብዳቤ፣ ውድ እና ያማረ ልብስ በመልበሱ ይሰማው የነበረውን ደስታ እየኮነነ፣ በእርባና ቢስ ሙያ ሰዓታትን ሲያባክን የነበረበትን ተግባራት እያወገዘ፣ (ኸስ ራሱ ድሮ የሠራው) በጥልቅ ትህትና ስለ ራሱ ስህተቶች ሲናገር ይስተዋላል። ከዚያም እነዚህን ልብን የሚነኩ ተግሳጾች አከለበት፡- “የሐብት ንብረትና የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ማካበት ሳይሆን የነፍሳት መዳንና የእግዚአብሔር ክብር አእምሮህን ይሙላው። ከነፍስህ ይልቅ ቤትህን እንዳታጌጥ ተጠንቀቅ፤ ከሁሉም በላይ መሻትህን ለመንፈሳዊ ሕንፃ አውለው።

ለድኾች ትሁትና የተሰጠህ ሁን፤ በመብልም ውልህን አትሳት፤ ሕይወትህን ማስተካከል አቅቶህ ከመጠን በላይ መፈለግን መተው ካልቻልህ እኔ እንደሆኑኩት ሁሉ በእጅጉ ትዋረዳለህ…” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 124)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እያደር የሚፈካ ብርሃን--ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር እውነትን እያደር እንዲፈነጥቅ አድርጎ የሚገልጠው ለምንድን ነው? እነዚህ መሠረታዊ ሥርዓቶች ዛሬ በቤተ ክርስቲያን እንዴት ይሠራሉ?

2. አዳዲስ የእውነት ግኝቶች የእግዚአብሔር ሕዝቦች ከተረዱት ከቀደሙት እውነቶች ጋር እንዴት ይዛመዳሉ? አዲስ ብርሃን ከአሮጌው ብርሃን ጋር ፈጽሞ ሊቃረን የማይችለው ለምንድን ነው?

3. በየትኛውም የዓለም ክፍል ቢኖሩ፣ የወጡበት ባህል በአንድ ወይም በሌላ መልኩ ከመጽሐፍ ቅዱስ ጋር የሚጋጩ እሴቶችን፣ አስተሳሰቦችንና የሥነ ምግባር መስፈርቶችን ማስተዋወቁ አይቀሬ ነው። የግጭት መስኮቹን ለይተው ከተገነዘቡ በኋላ እነዚህን ፈታኝ ሁኔታዎች እየተጋፈጡ ያሉትን--ራስዎን እና እኛን፣ እንደ ቤተ ክርስቲያን እንዴት ይመለከታሉ ?

4. የጆን ሁስ ደብዳቤ ዛሬ በእርስዎ አስተሳሰብ ላይ ምን ተጽዕኖ ይኖረዋል? ከዚህ ደብዳቤ ልብዎን የነካው ነገር ምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL