የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ታላቁ ተጋድሎ



2ኛ ሩብ ዓመት 2024


ሚያዝያ 5 - 11

3ኛ ትምህርት

Apr 13 - 19




ብርሃን በጨለማ ውስጥ ያበራል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ዮሐ. 8:44፣ ምሳ. 23:23፣ ሐዋ. 20:27–32፣ 2ተሰ. 2:7–12፣ መዝ. 119:105፣ 116፣ 130፣ 133፣ 160፣ ምሳ. 16:25፣ 2ቆሮ. 4:3–6።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ኢየሱስም እንዲህ ሲል ተናገራቸው፤ ‘ከእንግዲህ ለጥቂት ጊዜ ብርሃን አለላችሁ፤ ጨለማ ሳይመጣባችሁ፣ ብርሃን ሳለላችሁ ተመላለሱ፤ በጨለማ የሚመላለስ ወዴት እንደሚሄድ አያውቅም’ ” (ዮሐ. 12፡35)።

የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻ መጽሐፍ በሆነው በዮሐንስ ራእይ ዲያብሎስ በዘንዶ እና በእባብ ገጽታ ቀርቦአል (ራእ. 12፡9)። እርሱ ዘንዶ ነው፤ ምክንያቱም የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለማጥፋት ይመኛል። ደግሞም እርሱ እባብ ነው--ሕዝቡን ለማሳት ሁሉንም ማታለያ ውሸቶቹን ይጠቀማልና። ክርስቶስ ከሞተ በኋላ በነበሩት ዓመታት ክርስቲያኖች የንጉሣዊውን ሮም ሥርዓት “አማልክት” ለማምለክ ፈቃደኞች ስላልነበሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ተሠቃይተዋል፣ አናብስት ጉድጓድ ውስጥ ተጥለዋል እንዲሁም በግንድ ላይ የፊጥኝ ታስረው ተቃጥለዋል። ሆኖም ይህ ሁሉ አረመኔያዊ ቅጣት ቢፈጸምባቸውም እንኳ ብዙዎች በታማኝነታቸው ጸኑ፣ ወንጌል መሰራጨቱን ቀጠለ፣ ቤተ ክርስቲያንም አደገች።

በዚህ ምክንያት ሰይጣን ስልቱን ለወጠ። በርካታ አረማውያን የተጠመቁ ቢሆንም፣ የተሟላ የመጽሐፍ ቅዱስ እውነት ግን አልተማሩም ነበር። መሪዎች የቅዱሳት መጻሕፍት እውነቶች ታዋቂ ከሆኑ አረማዊ ሥርዓቶችና ልማዶች ጋር ውህደት እንዲፈጥሩ ሲያደርጉ የስህተት አስተምህሮ ሰተት ብሎ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ። አራተኛው እና አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን፣ የቤተ ክርስቲያን መሪዎች የክርስትና አስተምህሮ ከአረማዊ ልማዶች ጋር ድብልቅ እንዲሆን የተደራደሩባቸው ዘመናት ነበሩ።

ሆኖም በጣም አስቸጋሪ በሆኑ ወቅቶች እንኳ፣ እግዚአብሔር ያለማቋረጥ ከህዝቡ ጋር ነበር። “መንገድ፣ እውነት እና ሕይወት” የሆነውን የሱስ ስላገኙት፣ ሕያው እምነታቸውን እንዲተዉ ከፍተኛ ጫና ቢደርስባቸውም እንኳ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል በጽናት ቆሙ። በግልጽም ሆነ በስውር የቱንም ዓይነት ተጽዕኖ ቢደርስባቸውም፣ በቅዱሳት መጻሕፍት ለተገለጠው አምላካዊ እውነት በጀግንነት ጸኑ።

ሚያዝያ 6
Apr 14

ድርድር፡ የሰይጣን ረቂቅ ዘዴ


ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዮሐ. 14፡6 እና ዮሐ. 8፡44። በጥቅሶቹ እንደቀረበው፣ በየሱስ እና በሰይጣን ባህሪ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?



የሱስ የተናገረው እውነት ነው ምክንያቱም እርሱ የእውነት ምንጭ ነው። እውነት የሚፈሰው--ጥበበኛ፣ አፍቃሪና ሁሉን ከሚያውቅ የአምላክ ልብ ውስጥ ነው። እርሱ እውነት እና የእውነት ሁሉ መሠረት ነው።

በአንጻሩ ሰይጣን ሐሰተኛ እና የሐሰት አባት ነው። ሐሰት በመናገር፣ በማታለል፣ የተሳሳተ መረጃና የተዛባ እውነት በማቀበል የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለማሳት ዝግጁ ነው።

በዔደን የአትክልት ስፍራ ለነበረችው ሔዋን እውነትን አዛብቶ በማቅረብ፣ በውስጧ ጥርጣሬ በመፍጠር እና እግዚአብሔር የተናገረውን ዓይኑን በጨው አጥቦ በመካድ እነሆ አሳታት።

ፍሬውን ከመብላት ጋር ተያይዞ ሰይጣን “መሞት እንኳ አትሞቱም” ሲል የተናገረው ቃል፣ እግዚአብሔር ከተናገረው ጋር በግልጽ የሚቃረን ነበር። ሰይጣን ለብዙ ምዕተ ዓመታት ተመሳሳይ ስልት ሲጠቀም ኖሯል። በአምላካዊው ቃል ላይ ያለንን እምነት ያዳክማል፣ ከእግዚአብሔር ፈቃድ ጋር ይጋጫል፣ ቅዱሳት ጽሑፎችን ያጣምማል እንዲሁም አንዳንዴ ለእርሱ የሚጠቅም ሆኖ እስካገኘው ድረስ መጽሐፍ ቅዱስን በተሳሳተ መንገድ ይጠቅሳል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ምሳ. 23፡23፣ ዮሐ. 17፡17፣ ዮሐ. 8፡32። የእግዚአብሔርን ቃል እውነትነት አስመልክቶ በእነዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ውስጥ ምን ዓይነት ዝምድና ይመለከታሉ? የመልእክታቸው አስኳል ምንድን ነው?



“ማታለያዎቹን ያውቁ ዘንድ፣ ብሎም ኃይሉን ይቋቋሙ ዘንድ የሚያስችላቸው መጽሐፍ ቅዱስ እንደሆነ ሰይጣን ጠንቅቆ ያውቅ ነበር። የዓለም መድኃኒት እንኳ ጥቃቱን የተቋቋመው በቃሉ ነበር። “ተጽፏል” በማለት እያንዳንዱን ጥቃት በዘላለማዊው እውነት ጋሻ ይመክት ነበር። ጠላት ለሚያቀርበው እያንዳንዱ ሃሳብ ተቃውሞውን የሚመልሰው በቃሉ ጥበብ ኃይል ነበር። በሰዎች ላይ ያለውን ተጽእኖና የመቆጣጠር ኃይል ጠብቆ ለማቆየት፣ ብሎም የነጣቂውን ጳጳሳዊ ሥልጣን ለማደላደል ሰዎች የመጽሐፍ ቅዱስ እውቀት ገልቱ ሆነው እንዲቀሩ የግድ ማድረግ አለበት። መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔርን ከፍ ከፍ ያደርጋል፤ ውሱን ሰብዓዊ ፍጡራንንም በትክክለኛ ስፍራቸው ያስቀምጣቸዋል። ስለዚህ የመጽሐፍ ቅዱስ የተቀደሱ እውነቶች መደበቅና መጨቆን ይኖርባቸዋል። ይህ አስተሳሰብ በሮማ ቤተ ክርስቲያን ተተግብሯል። ለብዙ መቶ ዓመታት የመጽሐፍ ቅዱስ ስርጭት ተከልክሎ ኖሯል።

ሕዝቡ መጽሐፍ ቅዱስን እንዳያነቡ፣ በቤታቸውም እንዳያስቀምጡ ተከልክለው ሳለ፣ መርኅ ዐልባዎቹ ካህናትና ባለሥልጣናት የራሳቸውን አስመሳይ ሀሳቦች እንዲደግፍ አድርገው ይተረጉሙት ነበር። በዚህም ምክንያት ቤተ ክርስቲያንንና አገር የመግዛት ሥልጣን ተችሮት፣ ሊቀ ጳጳሱ የእግዚአብሔር ወኪል በምድር ተደርጎ በሁሉም የዓለም ሕዝብ ማለት ይቻላል፣ እውቅና ተሰጠው”--ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 61)።

ሰይጣን በዚህ ዘመን አምላካዊውን ቃል ለማጣመም ወይም በተሳሳተ መንገድ ለመተርጎም በሚሞክርባቸው መንገዶች ዙሪያ ተወያዩ።

ሚያዝያ 7
Apr 15

አረመኔዎቹ ተኩላዎች


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 20፡27-32። ሐዋርያው ጳውሎስ ወደፊት የሚመጣውን ክህደት አስመልክቶ በኤፌሶን ላሉት የቤተ ክርስቲያን መሪዎች ምን የተለየ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷቸዋል?



የጳውሎስ ምክር ዓላማ ቤተ ክርስቲያንን ለሚመጣው ነገር ማዘጋጀት ነበር።

በእነዚህ ጥቅሶች ሁለት አሳሳቢ ጉዳዮችን ይገልጻል።

በቀዳሚነት አሳስቦት የነበረው ጉዳይ “ነጣቂ ተኵላዎች መጥተው በመካከላችሁ ሰርገው እንደሚገቡና ለመንጋውም እንደማይራሩ ዐውቃለሁ” (ሐዋ. 20፡29) ሲል የተናገረው ነው። በሌላ አነጋገር አማኞች ከባድ ስደት የሚደርስባቸው ሲሆን፤ ስደቱ ደግሞ የሚመነጨው ከዚያው ከቤተ ክርስቲያን ውስጥ ነው። ይህ ትንቢት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ፍጻሜ አግኝቷል። ለሮም አማልክቶች በመስገድ ንጉሠ ነገሥቱን ለማምለክ ፈቃደኛ ያልሆኑ ክርስቲያኖች ተሠቃይተዋል፣ ታሥረዋል እንዲሁም በግንድ ላይ ተጠፍንገው ተቃጥለዋል።

ሐዋርያው ሁለተኛውን ስጋቱን ሲገልጽ እንዲህ ይላል፡ “ከእናንተው መካከል እንኳ የራሳቸውን ደቀ መዛሙርት ለማፍራት እውነትን የሚያጣምሙ ይነሣሉ” (ሐዋ. 20፡30)።

መናፍቃን ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ። የሐሰት ኃይማኖታዊ አስተምህሮዎች በመለኮታዊ እውነቶች ይተካሉ። የአረማውያን ልማድና ሥርዓቶች እውነትን ደፍጥጠው ይገንናሉ። በአራተኛው እና አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሰጥቶ የመቀበል ጽንሰ ሀሳብ ሾልኮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባ።

ሰጥቶ የመቀበል ጽንሰ ሀሳብ ለወንጌል መስፋፋት መልካም አጋጣሚ እንደፈጠረ ተደርጎ ታይቶ ነበር። ይሁን እንጂ ከአምላካዊው ቃል የመራቅን አስከፊ ውጤት ይዞ ከተፍ አለ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ተሰ. 2፡7-12። ሐዋርያው መጪውን ክህደት የገለጸበት መንገድ ምን ይመስላል? ምን ዓይነት መለያ ባህሪዎችን ማጤን ነበረባቸው?





ጳውሎስ “የዐመፅ ምስጢር አሁንም እንኳ እየሠራ ነውና” በማለት የሰጠው ሐሳብ እጅግ ወሳኝ ጉዳይ ነው። በጳውሎስ ዘመንም እንኳ፣ አምላካዊውን ሕግ መታዘዝን አስመልክቶ ውሎ አድሮ ከቃሉ እውነት እየራቁ የመሄድ ሁኔታ ይስተዋል ነበር። ይህ ሁኔታ በቀጣዮቹ ምዕተ ዓመታት ይበልጥ እየጋመ ይሄዳል።

ከሁለተኛው አምላካዊ ትእዛዝ በተቃራኒ ጣዖታት ወደ ክርስትና አምልኮ እንዲገቡ ተደረገ። በሺህ ለሚቆጠሩ ዓመታት በሁሉም አረማዊ ቤተ አምልኮዎች ግንባር ቀደም ሆነው የሚሰለፉት ጣዖቶች ነበሩ። ክርስትናን ወደ እምነቱ በሚመጡ አረማውያን ዘንድ ይበልጥ ተቀባይነት ያለው ለማድረግ ሲባል፣ የአረማውያን አማልክት ቅዱሳት በሚል ስያሜ ተቀየሩ።

የአረማውያኑ የጸሐይ አምላክ ይመለክ የነበረበት የጸሐይ ቀን (ሰንዴይ) የትንሣኤውን ዕለት ለማክበር በሚል ሰበብ ውሎ አድሮ የክርስትና አምልኮ ቀን ሆኖ ተቀየረ። ይህ የቅዱሳት መጻሕፍት ድጋፍ የሌለው ሐሰተኛ ቀን እነሆ ዛሬም ተንሰራፍቶ ይገኛል። ዛሬ ወደ ቤተ ክርስቲያን ስንገባ ምን ዓይነት የአቋም መላላቶችን እናያለን? ከሁሉም በላይ--እርስዎ በግል አቋሞትን እያላሉባቸው ያሉ ጉዳዮች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? እውነትን ከሐሰት ማቀላቀል?

ሚያዝያ 8
Apr 16

በቃሉ መጠበቅ


ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ዮሐ. 17፡15-17 እና ሐዋ. 20፡32። ከሰይጣን ማታለያዎች እንዴት መጠበቅ እንዳለብን አስመልክቶ የሱስ እና ሐዋርያው ጳውሎስ የሰጡን ዕውቀቶች ምንድን ናቸው?





መጽሐፍ ቅዱስ እንከን የለሽ የአምላካዊው ፈቃድ መገለጥ ነው። ቃሉ ለሰው ልጆች መዳን በሰማይ የቀረበውን እቅድ ያቀርባል። “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ያለባቸው ናቸው፤ ለማስተማር፣ ለመገሠጽ፣ ለማቅናት በጽድቅም መንገድ ለመምከር ይጠቅማሉ” (2ጢሞቴ. 3፡16)። ይህ ማለት በእግዚአብሔር መንፈስ የተጻፉት የተወሰኑ ክፍሎች ብቻ ናቸው ወይም አንዱ ክፍል ከሌላው ይበልጣል ሳይሆን “ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ” የእርሱ መንፈስ አለባቸው። እያንዳንዱ የመጽሐፍ ቅዱስ ገጽ እንደ እግዚአብሔር ቃል መታየት አለበት። አለበለዚያ ግን የመታለያው በር ሰፊ ነው።

መጽሐፍ ቅዱስ ከታላቁ ተጋድሎ አንጻር የእግዚአብሔርን ወሰን የለሽ ፍቅር ፍንትው አድርጎ ያሳያል። በተጨማሪም የሰይጣንን ማታለያዎች ከማጋለጥ አልፎ ማሳቻ መንገዶቹንም ይፋ ያደርጋል። ዲያብሎስ የእግዚአብሔርን ቃል አጥብቆ ይጠላል። በዚህ የተነሣ ባለፉት ምዕተ ዓመታት የቃሉን ኃይል ለማጥፋት ያልወጣው አቀበት የለም።

ለነገሩ፣ ያለ መጽሐፍ ቅዱስ ስለ ደኅንነት እቅድ ምን የምናውቀው ነገር ሊኖር ይችል ነበር? ደግሞስ ስለ የሱስ መወለድ፣ ምድራዊ ሕይወት፣ አስተምህሮ እና አገልግሎት ምን ያህል እናስተውል ነበር? ቅዱሳት መጻሕፍት ባይኖሩ ኖሮ የክርስቶስን የመሥዋዕትነት ጥልቀት፣ የትንሣኤውን ክብር፣ የምልጃውን ኃይል፣ እና የዳግም ምጽአቱን ግርማ ቅንጣት ታክል እንኳ መረዳት ይኖረን ነበር?

እነዚህ ሁሉ ወሳኝ እውነቶች በአምላካዊው ቃል ውስጥ ተገልጠዋል፣ ማስተማሪያ ሆነዋል፣ አጽንዖትም ተሰጥቶአቸዋል። ሁሉንም የተቀደሱ እውነቶች ለመረዳት ብቸኛው መስፈርት መሆን ያለበት መጽሐፍ ቅዱስ እና መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ ነው።

ስለዚህ፣ ሌላው ቀርቶ በመጽሐፍ ቅዱስ የተገለጠውን ታላቅ ፍቅር እየተናገሩ እንኳ በረቀቀ መንገድ ጥርጣሬ የሚጭሩትን፣ ሥልጣኑን ወይም በመንፈስ አነሳሽነት መጻፉን ለማዳከም የሚደረጉትን ማንኛውንም ሙከራዎች መዋጋት አለብን። የሚያሳዝነው ዘመናዊውን የጥላቻ አስተሳሰብ ጥቃት ተከትሎ፣ አብዛኞቹ የነገረ መለኮት ምሑራን እና ክርስቲያኖች አበክረው ድምቀት የሚሰጡት በዘመኑ ለነበሩ ሰዎች ሁኔታ እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ቃል ሆኖ ከቀረበበት ዐውድ አይደለም። የመጽሐፍ ቅዱስ ገጾች-- ነገሥታት፣ እረኞች፣ ዓሣ አጥማጆች፣ ካህናት፣ ባለቅኔዎች እና ሌሎች ስለ እግዚአብሔር፣ ስለ ተፈጥሮ እና ስለ ነበሩበት ተጨባጭ ሁኔታ፣ ስለ ዘመናቸው፣ ስለ አካባቢያቸው በጥልቀት የተረዱባቸው ጽሑፎች ናቸው ብለው ይሞግታሉ።

ይህ እውነት ከሆነ እኛ ዛሬ በ21ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የምንኖር ስለ እነዚህ ሰዎች አስተምህሮ ለምን እንጨነቃለን? ይባስ ብሎ የእነርሱን አስተሳሰብ የዘላለማዊ ተስፋችን መሠረት እናድርግ? አይገባም! ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 119፡105፣ 116፣ 130፣ 133፣ 160። ባለ መዝሙሩ የእግዚአብሔር ቃል በመዳን እቅድ ውስጥ ያለውን ትርጉም አስመልክቶ የሚሰጠን ዕውቀት ምንድን ነው?

ሚያዝያ 9
Apr 17



ከቅዱሳት መጻሕፍት ባሻገር ያለው ሰብዓዊ አመክንዮ


መንፈስ ቅዱስ በአእምሮአችን አማካይነት ይሠራል። የአጽናፈ ዓለማትን ምስጢር እንመረምር ዘንድ ይጋብዘናል። የሰው ልጅ የማመዛዘን ችሎታ ብቻውን የመለኮታዊውን ቅዱሳት መጻሕፍት እውነቶች መፈተሸ እና መገንዘብ አይችልም። እውነት የሰብዓዊው ፍጡር ግላዊ አመለካከት ሳይሆን መለኮታዊ መገለጥ ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ምሳ. 16፡25፣ መሳ. 21፡25፣ ኢሳ. 53፡6። ስለ ሰይጣን ማታለያ ስልት ምን ይነግሩናል?



ከዲያብሎስ እጅግ ውጤታማ ማታለያዎች አንዱ በመንፈስ ቅዱስ ባልተደገፈ እና የእግዚአብሔር ቃል ግንዛቤ በሌለው ሰብዓዊ አስተሳሰብ አምላካዊውን ፈቃድ መረዳት ይቻላል ብለን እንድናምን ማድረግ ነው። ጉዳዩ ከእኛ ወይም ከአጠቃላዩ ባህልና ትውፊት አኳያ ቀና መንገድ መስሎ ቢታይም፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ዐይን ሙሉ በሙሉ የተሳሳተ ሊሆን ይችላል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት እኔና ባለቤቴ ለአንድ ምሽት ባረፍንበት ሆቴል አቅራቢያ በሚገኝ ደን ውስጥ የእግር ጉዞ ለማድረግ ወሰንን። በተለምዶ እኔ አቅጣጫዎችን በመለየት ረገድ ጥሩ ችሎታ አለኝ። እናም ቁልቁለቱን፣ አቀበቱንና ጠመዝማዛውን የደን ክፍል ለአንድ ሰዓት ገደማ በእግራችን ተጓዝን። መንገዳችንን ከጥቂት ውጣ ውረድ በኋላ አግኝተን መመለስ እንደምችል ሙሉ እምነት የነበረኝ ቢሆንም፣ ነገር ግን ተስፋ በሚያስቆርጥ አኳኋን በደኑ ውስጥ ጭልጥ ብለን ጠፋን። ጸሐይዋ እየጠለቀች ስለ ነበር የባሰው እንዳይመጣ በማሰብ ፈራሁ። ደስ የሚለው ነገር፣ መንገዱን የሚያውቁ ሌሎች የእግር ተጓዦችን አገኘን።

ከመንገዳችን ቢያንስ ስምንት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የነበርን ቢሆንም፣ ለዋናው መንገድ ቅርብ ነበርን። ያገኘናቸው ተጓዦች መኪና በዋናው መንገድ አቅራቢያ ቆሞ ስለነበር እስከ ሆቴላችን አደረሱን። መንገዱን የሚያውቅና ወደምንፈልግበት ቦታ ሊመልሰን የሚችል ሰው ማግኘታችን ለእኛ በእጅጉ ወሳኝ ነበር።

ከምድር ወደ ሰማይ በምናደርገው ጉዞ እግዚአብሔር ብቻችንን አልተወንም።

መንፈስ ቅዱስ ወደ ሰማያዊው ቤት የሚመሩንን ቅዱሳት መጻሕፍት ይጠቁመናል። እውነት እና ሐሰት፣ ትክክል እና ስህተት፣ መልካም እና ክፉ--እነዚህ በትክክል ሊስተዋሉ የሚችሉት የእግዚአብሔር ቃል በሚፈነጥቀው ብርሃን ብቻ ነው። ከእግዚአብሔር እና ከቃሉ ጋር የሚጋጭ ስህተት የሆነ ነገር ነው። እናም ስህተት ሁል ጊዜም ቢሆን አደገኛ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር የሚስማማው እውነት እና በጎነት ነው። የእግዚአብሔርን ቃል የእውነት እና የሥነ ምግባር የመጨረሻው ዳኛ ማድረጋችን ምን ያህል ወሳኝ ነው! ሰብዓዊው አእምሮ ያለ መንፈስ ቅዱስ እርዳታ መለኮታዊውን እውነት ማወቅ የማይችለው ለምንድን ነው? በሰብዓዊው አመክንዮ ወይም የማሰብ ኃይል እና በመለኮታዊ መገለጥ መካከል ባለው ግንኙነት ዙሪያ ተወያዩ። የማሰብ ችሎታ መለኮታዊውን መገለጥ እንድናስተውል የሚረዳን እንዴት ነው? በዳን. 2 ከባቢሎን ዘመን አንስቶ እስከ ወደፊቱ ጊዜ ያለውን የዓለም ታሪክ የሚዳስሰውን ትንቢት እንደ አብነት ይመልከቱ። እንዲህ ያለው ትንቢት የሰውን ልጅ የማሰብ ችሎታ አብልጦ የሚስበው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 10
Apr 18

የአእምሮ ውጊያ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ 2ቆሮ. 4፡3-6። ሐዋርያው ጳውሎስ “የዚህ ዓለም አምላክ የማያምኑትን ሰዎች ልቡና አሳውሯል” (2ቆሮ. 4፡4) ሲል ምን ማለቱ ነው? ለመሆኑ እንዴት ነው ዓይኖቻቸው የሚታወሩት? የሚከፈቱትስ?



በዚህ ጥቅስ “አእምሮ” ተብሎ የተተረጎመው የግሪክ ቃል ኖኤማ ሲሆን፣ ጥሬ ትርጉሙ ግንዛቤአችን ወይም የአዕምሮ ችሎታችን ማለት ነው። የ-ኤስ.ዲ.ኤ. የመጽሐፍ ቅዱስ ሐተታ ለዚህ ጥቅስ ብርሃን ፈንጣቂ መግለጫ ይሰጣል። “በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል የሚደረገው ውጊያ በሰዎች አእምሮ ውስጥ የሚደረግ ውጊያ ነው። (ሮሜ. 7:23፣ 25፣ 12:2፣ 2ቆሮ. 3:14፣ 11:3፣ ፊልጵ. 2:5, 4:7-8)። ዋንኛው የሰይጣን ሥራ የሰዎችን አእምሮ ማሳወር ወይም ማጨለም ነው። ለዚህ የሚጠቀመው ስልት--አዕምሮን ቅጥ ባጣ የሥጋ ምኞት በማሳወር ከአምላካዊው ቃል ጥናት ማስተጓጎል፤ አዕምሮ በዚህ ዓለም ነገሮች እንዲጠመድ በማድረግ ወደ ትዕቢትና ራስን ከፍ ከፍ ወደማድረግ መምራት””—Volume 6, p. 854.

በጠፉት በኩል የተጠቀሰው የዕውቀት ማነስ ማወቅ ስላልቻሉ ነው ማለት አይደለም። ለማወቅ የሚችሉበት አቋም ላይ ስላልሆኑ ነው። ብዙዎች እውነትን የሚያወቁበት ዕድል ቢያገኙም ነገር ግን ላለማመን መረጡ፤ ሰይጣንም ዓይኖቻቸውን አሳወረ። የሰይጣን መንግሥት የጨለማ መንግሥት ነው። ዘ ኤስ.ዲ.ኤ. የመጽሐፍ ቅዱስ ሐተታ እንዲህ ሲል አክሎ ይናገራል፡ “የሰይጣን ዲያቢሎሳዊ ሴራዎችና ማታለያዎች የሚጋለጥበት እንዲሁም ሰዎች ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚወስደውን ጎዳና የሚያዩበት ብቸኛው መንገድ ወንጌል ነው።”--—Vol. 6, p. 854.። የአዲስ ኪዳን መልእክት መሠረታዊ ነጥብ የየሱስ ሕይወት፣ ሞት እና ትንሣኤ ነው። የሱስ የወንጌል እምብርት፣ የቅዱሳት መጻሕፍት አስኳል ነው። ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ስለ እርሱ ይመሰክራሉ (ዮሐ. 5፡39)። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 1፡4-5፣9፣14። ጥቅሶቹ የሱስን እንዴት ይገልጹታል? በተለይ በዮሐ. 1፡14 የቀረበውን መልእክት ልብ ይበሉ።



በቤተ ክርስቲያን የመጀመሪያዎቹ መቶ ዓመታት የአዲስ ኪዳን አማኞች የጨለማቸው ብርሃን ለነበረው ክርስቶስ ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ አሳልፈው ሰጥተው ነበር። በጸጋው ተዋጅተው፣ በኃይሉ ተለውጠው እና በፍቅሩ ተደፋፍረው ነበር። ሌላው ቀርቶ ሞት እንኳ ለክርስቶስ የነበራቸውን ታማኝነት መበጠስ አልተቻለውም ነበር። የዲያቢሎስን ማታለያዎች ከወንጌል በፈነጠቀው ብርሃን መረዳት ችለው ነበር። ክርስቶስ ሁሌም ቢሆን በጸጋው አማካይነት ለእውነት በድፍረት የሚቆሙ ወንዶች እና ሴቶች ልጆች አሉት። በነዚህ የመጀመሪያ መቶዎቹ ክፍለ ዘመናት--የክርስቶስ ፍቅር፣ ጸጋ እና እውነት በጨለማው ውስጥ አበራ።

ሚያዝያ 11
Apr 19


ተጨማሪ ሀሳብ


“ይህን ዕውቀት በመቃወም የሚንጸባረቀው የጥላቻና የተቃርኖ መንፈስ የእግዚአብሔርን ጠላቶች በየዘመኑ ሲያነሳሳ ይኖራል፤ ተመሳሳይ ንቃትና ታማኝነትም ከባሪያዎቹ ሲጠበቅ ቆይቷል። ክርስቶስ ለመጀመሪያዎቹ ደቀ መዛሙርት የተናገራቸው ቃላት ለተከታዮቹ እስከ ዘመን ፍጻሜ ጥቅም ላይ የሚውሉ ናቸው። ‘ለእናንተ የምነግራችሁን ለሰው ሁሉ እናገራለሁ፤ ተግታችሁ ጠብቁ!’ (ማር. 13፡37) ”—(ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 67)።

በርካታ በሆኑ የዓለም ክፍሎች፣ በተለይ ደግሞ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን በቀላሉ ማግኘት በሚችሉባቸው ቦታዎች ሰይጣን የቃሉን ተጽዕኖ ለማዳከም ሌሎች ዘዴዎችን ጥቅም ላይ አውሏል። በጣም ውጤታማ ከሆኑት አካሄዶች አንዱ የተለያዩ ሳይንሳዊ ጥረቶችን ወይም ራሳቸውን የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራንን በመጠቀም ሰዎች በእግዚአብሔር ቃል ላይ ያላቸው መተማመን እንዲቀንስ ማድረግ ነው። ለምሳሌ የዳንኤል መጽሐፍ ከክርስቶስ ልደት 500 ዓመታት በፊት ቢጻፍም፣ ነገር ግን በርካታ የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ከክርስቶስ ልደት በኋላ በሁለተኛው መቶ ክፍለ ዘመን አጋማሽ ላይ በማስቀመጥ፣ መጻፍ የሚችለው በዚህ ዘመን ነው ብለው ይሞግታሉ። እንደዚያ ከሆነ ብቻ ነቢዩ የወደፊቱን በትክክል መናገር ይችላል እንጂ ከዚህ ውጪ ሊሆን አይችልም። ስለዚህ የዳንኤል መጽሐፍ የተጻፈበትን ዘመን መጽሐፉ እንደሚናገረው ሳይሆን ከበርካታ መቶ ዓመታት በኋላ ነው ብለው ይከራከራሉ።

የሚያሳዝነው ይህ ስለ መጽሐፍ ቅዱስ የሚነገር የሐሰት ትርክት የዘመኑ ምሑራን በእኛ ላይ በግድ ለመጫን ከሚፈልጓቸው ድሪቶዎች አንዱ ነው። ደግሞም ገና ለገና የመጽሐፍ ቅዱስ ምሑራን ተናገሩት በሚል፣ በሚያሳዝን ሁኔታ በርካቶች ይህን ስህተት ሲቀበሉ ይታያል።

ጳውሎስ፡ “ነገር ግን ሁሉን ነገር ፈትኑ፤ መልካም የሆነውን ያዙ” (1ተሰ. 5፡21) ብሎ መናገሩ ብዙም የሚገርም አይሆንም።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በማክሰኞ ትምህርት፣ በትምህርተ ጥቅስ የቀረበውን ጽሑፍ እንደ ማጣቀሻ በመመልከት የሚከተሉትን ነጥቦች ያጢኑ፡ ሰይጣን የመጽሐፍ ቅዱስን ሥልጣን ለማዳከም ዛሬም ተመሳሳይ ረቂቅ ተንኮሉን እየተጠቀመ ያለው እንዴት ነው?

2. የእግዚአብሔርን ቃል በተሳሳተ መንገድ እንዳንተረጉም በብርቱ የሚጠብቁን መከላከያዎቻችን ምንድን ናቸው?

3. ሰይጣን በመልካም እና በክፉ መካከል ባለው ታላቅ ተጋድሎ ውስጥ ዋንኛ ጥረቱ የእግዚአብሔርን ባህሪ ማጉደፍ እና እርሱን እንደ ፈላጭ ቆራጭ፣ ፍቅር የሌለው አምባገነን አምላክ አድርጎ ማቅረብ ነው። ክፉው ይህን ለማድረግ የሚሞክረው እንዴት ነው? ደግሞስ ለዚህ ውሸቱ የእግዚአብሔር ምላሽ ምንድ ነው?

4. ሐዋርያው ጴጥሮስ “በመጽሐፍ ያለው የትንቢት ቃል ሁሉ ማንም ሰው በገዛ ራሱ መንገድ የሚተረጕመው አይደለም” (2ጴጥ. 1፡20) ሲል አጽንኦት ይሰጣል። የገዛ ራሳችንን ፍላጎት ለማሳካት ብለን የቅዱሳት መጻሕፍትን ትርጉም ላለማጣመማችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን? ይህን ማድረግ ከምናስበው በላይ ቀላል ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ራሳችንን ከዚህ ሁኔታ መጠበቅ የለብንምን? ራሳችንን እንዴት ከዚህ መጠበቅ እንችላለን?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL