የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ታላቁ ተጋድሎ



2ኛ ሩብ ዓመት 2024


መጋቢት 28 - ሚያዝያ 4

2ኛ ትምህርት

Apr 6 - 12




ወሳኙ ጉዳይ፡ ለሌሎች ፍቅር ማሳየት ወይስ ራስ ወዳድ ሆኖ መቅረት?



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሉቃ. 19:41– 44፣ ማቴ. 23:37-38፣ ዕብ. 11:35–38፣ ራእ. 2:10፣ ሐዋ. 2:44–47፣ ዮሐ. 13:35።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “እኔ ከአንተ ጋር ነኝና አትፍራ፤ አምላክህ ነኝና አትደንግጥ። አበረታሃለሁ፤ እረዳሃለሁ፤ በጽድቄም ቀኝ እጄ ደግፌ እይዝሃለሁ።” (ኢሳ. 41፡10)

በደብረ ዘይት ተራራ ዳርቻ ፍየሎችዎን አሰማርተው የሩሳሌም ከተማን አሻግረው የሚመለከቱ እረኛ ነዎት እንበል። ድምጽ ይሰማሉ። ድምጹም የየሱስ መሆኑን ወዲያውኑ ይገነዘባሉ። በሚናገረው ነገር ይገረማሉ። ለደቀ መዛሙርቱ፣ ይህን መረዳት አስቸጋሪ ነበር። እየጠለቀች የነበረችው ጀምበር በወርቃማው የቤተ መቅደሱ ጉልላት ላይ እያንጸባረቀች ነበር። ከዚያ የተነሣው ነጸብራቅ ዕጹብ ድንቅ በሆነው የእብነበረድ ግድግዳ ላይ አርፎ ጥጥ የመሰለ የብርሃን ጸዳል በፈነጠቀበት በዚያ ገራሚ ቅጽበት የሱስ እንዲህ ሲል ተናገረ፡ “ይህን ሁሉ ታያላችሁ? እውነት እላችኋለሁ፤ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ተክቦ የምታዩት፣ ሳይፈርስ እንዲሁ እንዳለ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ አይኖርም” (ማቴ. 24፡2)። ደቀ መዛሙርቱ በዚህ አነጋገሩ ግራ ተጋቡ። መቼም እርስዎም ይህን ስሜታቸውን ሳይጋሩ አይቀሩም። የየሱስ ደቀ መዛሙርት ከጠየቁት የዓለም መጨረሻ ክስተት ጋር ይህን እንዴት ማያያዝ ይችላሉ?

የሱስ የየሩሳሌምን ጥፋት እርሱ ዳግም ከመገለጡ አስቀድሞ እውን ከሚሆኑ ሌሎች ተጓዳኝ ክስተቶች ጋር አያይዞ እጅግ ትኩረት በሚስብ አአኳኋን ሲያቀርብ እናደምጣለን።

በመጨረሻው ዘመን ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለማታለል ወይም ለማጥፋት በየሩሳሌም ላይ ያደረሰውን የጥፋት ስልት ይጠቀማል። በመሆኑም ይህ ስለ ወደፊቱ ክስተት እንደ ማስጠንቀቂያ ወይም እንደ ማሳያ ሆኖ ቀርቦልናል። የሱስ በማቴ. 24 የሰጠው መመሪያ የመጨረሻዎቹን ቀናት ክስተቶች ከየሩሳሌም ጥፋት ዐውድ ያቀረበ ነበር።

ሰይጣን የእግዚአብሔርን ሕዝቦች ለማታለል እና ለማጥፋት የሚጠቀማቸውን እነዚህን መንታ ስልቶች እናጠናለን። ክፉው ስደት በማድረስ ማሳካት ያልቻለውን መሰሪ እቅዱን በድርድር እጁ ያስገባ ዘንድ ተስፋ ያደርጋል። ለእግዚአብሔር ዱብ-ዕዳ የሆነ አንዳች ነገር ካለመኖሩ አኳያ፣ በጣም ፈታኝ በሆኑ ጊዜያቶች እንኳ ሕዝቡን ይጠብቃል።

የዚህ ሣምንት ጥናት መሠረት ያደረገው ታላቁ ተጋድሎ በመባል በሚታወቀው መጽሐፍ ምዕ. 1-2 ነው። ምዕራፎቹን በማንበብ ይዘጋጁ።

መጋቢት 29
Apr 07

ልቡ የተሰበረው አዳኝ


የሱስ በደብረ ዘይት ላይ ተቀምጦ የየሩሳሌምን ከተማ አሻግሮ ሲመለከት ልቡ በሐዘን ተሰበረ። የዮሐንስ ወንጌል “ወደ ራሱ ወገኖች መጣ፤ የገዛ ወገኖቹ ግን አልተቀበሉትም” (ዮሐ. 1፡11) በማለት ይናገራል። የሱስ በነዋሪዎቿ ዘንድ ተወዳጅ ከነበረችው ከተማ ጥፋት ሕዝቡን ለማዳን የተቻለውን ሁሉ አድርጓል። የሱስ ለሕዝቦቹ የነበረው ፍቅር የመነጨው ወሰን ከሌለው አፍቃሪ ልብ ነበር። ንስሐ እንዲገቡ እና የምህረት ጥሪውን ይቀበሉ ዘንድ ደጋግሞ በፍቅር ተማጽኖአቸዋል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሉቃ. 19፡41-44፣ ማቴ. 23፡37-38፣ ዮሐ. 5፡40። የሱስ ለሕዝቡ ስለነበረው አመለካከት እና ለዚያ በፍቅር የተሞላ የጸጋ እና የምሕረት ግብዣው ሕዝቡ ስለሰጠው ምላሽ ጥቅሶቹ ምን ይነግሮታል? የትኛውን ተገልጦ የቀረበ አምላካዊ ባሕሪ ይመለከታሉ?



ከእግዚአብሔር አፍቃሪ ባህሪ አንጻር የየሩሳሌምን ጥፋት የመሰለ ክስተት ለመረዳት ያስቸግራል። ሮማዊው ጄኔራል ቲቶ ሠራዊቱን በከተማይቱ ላይ ለውጊያ ባሰማራበት ወቅት በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች እንደሞቱ ታሪክ ይናገራል። የሩሳሌም ፈራረሰች። ወንዶች፣ ሴቶች እና ሕፃናት ታረዱ። ይህን ያህል መከራ በሕዝቡ ላይ ሲደርስ ለመሆኑ እግዚአብሔር የት ነበር? መልሱ ግልጽ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ለመረዳት ግን ቀላል አይደለም። ልቡ ተሰብሮ ነበር። ዐይኖቹ በዕንባ ተሞልተው ነበር። ለዘመናት ወደ ሕዝቡ ለመድረስ ጥሯል። አፍቃሪ በሆነው ደግነቱ ላይ በማመጻቸው መለኮታዊ ጥበቃውን አጡ። እግዚአብሔር የሕዝቡ ምርጫ የሚያስከትለውን ውጤት ለመገደብ ሁል ጊዜ ጣልቃ አይገባም። ዓመጽ የሚያስከትላቸው ተፈጥሯዊ መዘዞች እንዲጎለብቱ ይፈቅዳል። በየሩሳሌም ጥፋት ወቅት ለደረሰው የንጹሐን ሕፃናት መቀጠፍ ምክንያቱ ድርጊቱን የፈጸመው ሰይጣን እንጂ እግዚአብሔር አልነበረም። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ማቴ. 24፡15-20። ሕዝቡ ከሚመጣው የየሩሳሌም ጥፋት ይድን ዘንድ የሱስ ምን ዓይነት መመሪያ ሰጥቶአቸው ነበር?



በ70 ዓ.ም. ላይ በየሩሳሌም ይኖሩ የነበሩት አብዛኞቹ ክርስቲያኖች ከአይሁድ እምነት የመጡ መሆናቸውን ማስታወሱ ተገቢ ነው። አፍቃሪው አምላክ በተቻለ መጠን አብዛኛውን ሕዝብ ከዚህ ውድመት ማዳን ፈልጓል። ለዚህም ነው የሮም ሠራዊት ወደ ከተማይቱ ሲቃረብ ከየሩሳሌም እንዲሸሹ መመሪያ የሰጠው። የሚከተለውን ሀሳብ ያሰላስሉ። የእግዚአብሔርን ባህሪ በዙሪያችን ከምናያቸው ክስተቶች አኳያ አንፈርጅም። ይልቁንም የምናያቸውን ሁነቶች በሙሉ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ከተገለጠው አፍቃሪ ባህሪው አኳያ አጣርተን እንመለከታለን። ይህ ማለፊያ ምክረ ሃሳብ የሆነው ለምንድን ነው?

መጋቢት 30
Apr 08

ክርስቲያኖች ከደረሰው ጥፋት ተርፈው ነበር


የየሩሳሌም ጥፋት ከመድረሱ አስቀድሞ በተስተዋሉ ክስተቶች ውስጥ የእግዚአብሔር ምሕረት፣ ጸጋ፣ ቸርነት እና ወደፊት የሚሆነውን የማወቅ ችሎታው በግልጽ ቀርቦአል። ሴስቲየስ ጋለስ እና የሮም ሠራዊት ከተማዋን ከበቧት። ሆኖም ጥቃት ለመፈጸም በሚያስችላቸው ሁኔታ ውስጥ እያሉ ባልተጠበቀ ሁኔታ አፈገፈጉ። ይህን ተከትሎ የአይሁዳውያኑ ሰራዊት እነርሱን አሳዶ ታላቅ ድል ተቀዳጀ።

ሮማውያን እየሸሹ፣ አይሁዳውያንም እያሳደዷቸው በነበረበት ወቅት፣ በየሩሳሌም የነበሩ ክርስቲያኖች ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር በፐርያ ምድር ወዳለችው ከተማ ወደ ፔላ ገሰገሱ። “ይጠብቁ ለነበሩት ክርስቲያኖች ቃል የተገባው ተስፋ ተሰጠ፤ የአዳኙን ማስጠንቀቂያ ለሚሰሙና ለሚታዘዙ ሁሉ አሁን ዕድል ተበረከተ። ክስተቶች ሁሉ ተገለባብጠው ምስቅልቅላቸው ወጥቶ ስለነበር ሮማውያንም ሆኑ አይሁዳውያን የሚሸሹትን ክርስቲያኖች ያስቀሩ ዘንድ እንዳይችሉ ተደርገው ነበር።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 37) ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ መዝ. 46፡1፣ ኢሳ. 41፡10። ጊዜውን ጠብቆ እውን ስለሆነው መለኮታዊ ጥንቃቄ ጥቅሶቹ ምን ይነግሩናል?



የዓለማት ገዢ እግዚአብሔር አምላክ፣ ውሎ አድሮ መለኮታዊ ዓላማዎቹን በምድር ተፈጻሚ ሊያደርግ በሚችል አኳኋን እያንዳንዱን ክስተት በበላይነት ይቆጣጠራል። ምንም እንኳ አንዳንድ ጊዜ እግዚአብሔር በእኛ ሰብዓዊ ምርጫዎች ላይ እየተመረኮዘ የመጀመሪያ እቅዶቹን ቢቀይርም፣ ለዚህች ፕላኔት ያለው የመጨረሻው ዕቅድ ግን ተፈጻሚነት ያገኛል።

የእግዚአብሔር ሕዝቦች ስለ ክርስቶስ መከራ፣ ስደት፣ እስራት እና ሞት የሚቀበሉበት ጊዜ ይመጣል። ነገር ግን በጣም አስቸጋሪ በሆነ እና የሰይጣን አረመኔያዊ ጥቃት በሚያይልበት ጊዜም እንኳ እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያኑን ይጠብቃታል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 11፡35-38 እና ራእ. 2፡10። እነዚህ ጥቅሶች ከክፋት ኃይሎች ጋር ስለምናደርገው ትግል የሚገልጡልን እውነታ ምንድን ነው? ጥቅሶቹ ቀደም ሲል ከቀረበው የአምላካዊ ጥበቃ ጽንሰ ሀሳብ ጥያቄ ጋር ኅብር የሚፈጥሩት እንዴት ነው? አንዳንዶች ከባድ ሥቃይ እንዲደርስባቸው፣ አልፎ ተርፎም የሰማዕትነት ሞት ይሞቱ ዘንድ እግዚአብሔር ይፈቅዳል በሚለው እና በአምላካዊው ጥበቃና ጥንቃቄ ጽንሰ ሀሳብ መካከል የሚጋጭ ነገር አለ ወይ?



የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ያጠፉ ዘንድ በኀይል የተሞከሩት የሰይጣን ጥረቶች ከንቱ ሆኑ። የየሱስ ደቀ መዛሙርት ሕይወታቸውን የሰውለት ታላቁ ተጋድሎ፣ እነዚህ ታማኝ፣ ደረጃቸውን ያስጠበቁ አማኞች በተሰለፉበት ሲወድቁ አላበቃም፤ በመሸነፍ ድል ነሱ። የእግዚአብሔር ሠራተኞች ተሰዉ፣ ሥራው ግን በቀጣይነት ወደፊት ተራመደ።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 49)። ሥቃይንና መከራን ጠንቅቀው ያውቁ የነበሩት የመጽሐፍ ቅዱስ ጸሐፊዎች ስለ እግዚአብሔር ፍቅር እውነታ ደግመው፣ ደጋግመው መጻፍ መቻላቸው ለእኛ ምን ትርጉም ሊኖረው ይገባል? እኛስ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር ሊኖረን የሚችለው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 1
Apr 09

በስደት ውስጥ ታማኝ መሆን


በክርስትና የመጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት ቤተ ክርስቲያን እሥራት፣ ሥቃይ እና ስደት ቢደርስባትም በፍጥነት እያደገች ነበር። ራሳቸውን ሙሉ ለሙሉ ለክርስቶስ አሳልፈው የሰጡ ታማኝ አማኞች በመንፈስ ቅዱስ ተሞልተው ቃሉን በኃይል ዐወጁ። የሰዎች ሕይወት ተቀየረ፤ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖችም ወደ ክርስትና እምነት መጡ። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 2:41፣ ሐዋ. 4:4፣ 31፣ ሐዋ. 5:42፣ ሐዋ. 8:1–8።

እነዚህ ጥቅሶች የአዲስ ኪዳን ቤተ ክርስቲያን ስላጋጠሟት ተግዳሮቶች እና በፍጥነት ስላደገችበት ምክንያት ምን ያስተምሩናል?



ሐዋርያት--ዛቻና ማስጠንቀቂያ (ሐዋ. 4፡17)፣ እሥራት (ሐዋ. 5፡17-18)፣ ስደት (ሐዋ. 8፡1) እንዲሁም ሞት እንኳ (ሐዋ. 7፡59፣ ሐዋ. 12፡2) ቢደርስባቸውም፣ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ተሞልተው የክርስቶስን ትንሣኤ በድፍረት ዐወጁ። በዚህም በይሁዳ፣ በገሊላ እና በሰማርያ የነበሩ አብያተ ክርስቲያናት በእጥፍ አደጉ።

የገሃነም ጥብቅ ምሽጎች ተናወጡ። የሰይጣን እስራት ተሰበረ። የአረማውያን ባዕድ አምልኮ ከሞት በተነሣው ክርስቶስ ኃይል ፊት እንኩትኩቱ ወጣ። ወንጌል መጠነ ሰፊ በሆነ የበላይነት ላይ ድል ተቀዳጀ። ደቀ መዛሙርት ይኖሩበት በነበረው ሰገነት ኮስምነው መቀመጣቸው አከተመ። እንደ ጥላ ይከተላቸው የነበረ ፍርሐትም ደብዛው ጠፋ።

በምትኩ የደቀ መዛሙርቱ ልብ በጽኑ እምነት ተሞላ። ከሞት የተነሣው አዳኛቸው አንድ የዐይን ውልብታ መላ ሕይወታቸውን ቀየረ። የሱስ ለመኖራቸው አዲስ ምክንያት ሰጣቸው። ጌታችን ታላቁን ተልዕኮ ብቻ ሳይሆን (ማር. 16፡15) ታላቁን ተስፋ ጭምር ሰጣቸው “ ‘ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ በእናንተ ላይ በሚወርድበት ጊዜ ኀይልን ትቀበላላችሁ፤ በኢየሩሳሌም፣ በይሁዳና በሰማርያ ሁሉ፣ እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ምስክሮቼ ትሆናላችሁ’ ” (ሐዋ. 1፡8)።

ወንጌል እጅግ በጣም ሩቅ ወደ ሆኑ የምድር ዳርቻዎች ደረሰ (ቆለ. 1፡23)።

ከደቀ መዛሙርቱ በመጨረሻ ላይ የሞተው ዮሐንስ ሲሆን፣ ጊዜውም በመጀመሪያው ምዕተ ዓመት መገባደጃ ላይ ነበር። በቀጣይ፣ ሌሎች የእውነትን ችቦ ከፍ አድርገው ሕያው የሆነውን ክርስቶስ ዐወጁ። በዘመናዊቷ ቱርክ ሰሜናዊ ጠረፍ ላይ የምትገኘው ቢቲኒያ የሮማ ግዛት አገረ ገዢ የሆነው ትንሹ ፕሊኒ ከክርስቶስ ልደት በኋላ 110 ዓ.ም. አካባቢ ለንጉሠ ነገሥት ትራጃን ደብዳቤ ጻፈ። የፕሊኒ መልእክት ትልቅ ትርጉም ነበረው። ምክንያቱም መልእክቱ የተጻፈው ከክርስቶስ ሥቅለት ሰማንያ ዓመት በኋላ አካባቢ ነበር። ፕሊኒ ክርስቲያኖችን ለማሰስና ለመግደል ሲያደርግ ለነበረው እንቅስቃሴ በይፋ ይመራ ስለነበረው ችሎት ተናግሮአል፡ “በየትኛውም የዕድሜ ክልል፣ የሕብረተሰብ ደረጃ እና ጾታ የሚገኙ ሰዎች በሚቀርብባቸው ክስ መሠረት እርምጃ የሚወሰድባቸው ሲሆን ይህ ደግሞ ይቀጥላል።

ይህ እንደ ወረርሽኝ እየተዛመተ ያለ አጉል እምነት (ክርስትና) በከተሞች ብቻ ሳይሆን በመንደሮችና በገጠር አውራጃዎችም ተስፋፍቷል።”--—Henry Bettenson, Documents of the Christian Church (New York: Oxford University Press, 2011), p. 4.

ዲያብሎስ እጅግ አሰቃቂ ጥቃቶች ቢፈጽምም ቤተ ክርስቲያን ግን በፍጥነት እያደገች ነበር። እኛ ለምንገኝባት የዘመኑ መጨረሻ ቤተ ክርስቲያን ሊረዳ የሚችል ምን ዓይነት ትምህርት ከቀደመችው ቤተ ክርስቲያን መማር እንችላለን?

ሚያዝያ 2
Apr 10

ማኅበረሰብን መንከባከብ


የጥንቷ ቤተ ክርስቲያን ያደገችው አባሎቿ ወንጌልን ስለሰበኩ ብቻ ሳይሆን ወንጌልን ስለኖሩ ጭምር ነበር። አማኞች “በምኵራቦቻቸው እያስተማረ፣ የእግዚአብሔርን መንግሥት የምሥራች ቃል እየሰበከ፣ በሕዝቡ መካከል ማንኛውንም ደዌና ሕመም እየፈወሰ በመላው ገሊላ ይዘዋወር” (ማቴ. 4፡23) የነበረውን የክርስቶስ አገልግሎት አርአያቸው አድርገው ነበር። የሱስ አብልጦ ለሰዎች ችግር ይቆረቆር እንደ ነበር ሁሉ የአዲስ ኪዳኗ ቤተ ክርስቲያንም ተመሳሳይ ተግባር ታከናውን ነበር። በመጀመሪያዎቹ ምዕተ ዓመታት በዓለም ላይ እንደዚያ ዓይነቱን ተጽእኖ ማምጣት የቻለው--ከራስ ወዳድነት የጸዳውና ቁርጠኝነት የተላበሰው ለሰዎች ችግር የሚቆረቆር ፍቅር፣ የወንጌልን መልካም የምሥራች በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ከማካፈል ጋር ቅንጅት በመፍጠሩ ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 2:44–47፣ ሐዋ. 3:6–9፣ ሐዋ. 6:1–7። ምንም እንኳ ሁኔታዎች ቢለያዩም፣ ከጥቅሶቹ ስለ እውነተኛው ክርስትና መሠረታዊ መርኅዎች ምን እንማራለን?



እነዚህ የአዲስ ኪዳን አማኞች የክርስቶስን አርዓያ የተከተሉ ሲሆን ጴጥሮስ እንደተናገረው እነርሱንም--እግዚአብሔር በመንፈስ ቅዱስና በኀይል ቀባቸው፤ እግዚአብሔር ከእነርሱ ጋር ስለ ነበረ በደረሱበት ሁሉ መልካም እያደረጉ በዲያብሎስ ሥልጣን ሥር የነበሩትን ሁሉ ፈወሱ (ሐዋ. 10፡38)። የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን በምድር ያለች አካሉ ነበረች።

በመሆኑም እርሷም በእነዚያ የቀደሙ ምዕተ ዓመታት ለተጎዳውና ከአምላክ ለተነጠለው ሰብዓዊ ዘር ግድ ያላትና የክርስቶስን መሥዋዕታዊ ፍቅር የገለጸች ነበረች።

በአጽናፈ ዓለም እየተፋፋመ ባለው ታላቅ ተጋድሎ ዲያብሎስ በሰብዓዊው ፍጡር ውስጥ ያለውን አምላካዊ አምሳል ለማበላሸት ይፈልጋል። የወንጌል ዓላማ የእግዚአብሔርን አምሳል በሰው ልጆች ውስጥ ማደስ ነው። ይህ መታደስ--አካላዊ፣ አእምሯዊ፣ ስሜታዊ እና መንፈሳዊ ፈውስን ያካትታል።

የሱስ ለእያንዳንዳችን ያለውን ዕቅድ እንዲህ ሲል በዮሐ. 10፡10 ይገልጻል፡ “ ‘ሌባው ሊሰርቅ፣ ሊገድልና ሊያጠፋ ብቻ ይመጣል፤ እኔ ግን ሕይወት እንዲኖራቸውና እንዲትረፈረፍላቸው መጥቻለሁ’ ”። ጤነኛ አካል፣ ንቁ አእምሮ፣ የተረጋጋ ስሜት እና ጤናማ መንፈሳዊ ሕይወት ኖሮን ለማየት ይናፍቃል።

ይህ በተለይ ከዳግም ምጽአቱ ተስፋ አኳያ ሲታይ እውነትነት አለው። ይህች ዓለም መጠነ ሰፊ ቀውስ እየገጠማት ይገኛል። የሱስ በማቴ. 24 እና ሉቃ. 21 አስቀድሞ የሰጣቸው መልእክቶች ዳግም ከመመለሱ በፊት በምድር ላይ ስለሚፈጸሙ ጥፋቶች ይተነብያሉ። ክርስቶስ በፈውስ ጸጋው ሲነካን፣ ሌሎችም የዚህ ጸጋ ተቋዳሽ ይሆኑ ዘንድ እርሱ በነካን መንገድ ሌሎችን ለመንካት እንናፍቃለን። እኛም በእርሱ ፍቅር ሌሎችን እንነካ ዘንድ፣ የሱስ የክርስቶስ አምባሳደሮች አድርጎ ከእርሱ ጋር የተቋረጠ ግንኙነት ወዳለው ዓለም ይልከናል። የአዲስ ኪዳን ክርስትና አንዱ ለሌላው ብሎም ለማኅበረሰቡ የሚኖረው ፍቅር ዓይነተኛ መለያው ነበር። ተወያዩበት፡ የሰይጣን ክስ ስህተት መሆኑን ለማረጋገጥ፣ ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር በመተባበር ረገድ ምን ሚና አላት?

ሚያዝያ 3
Apr 11

የፍቅር ውርስ


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 13:35 እና 1ዮሐ. 4:21። በታላቁ ተጋድሎ ውስጥ ሰይጣን በእግዚአብሔር መንግሥት ላይ ካቀረበው ተግዳሮት አኳያ እነዚህ ክፍሎች ምን ያሳያሉ? ስለ እውነተኛው ክርስትና መሠረታዊ ነጥብ ምን ይነግሩናል?



በመጀመሪያዎቹ ጥቂት ምዕተ ዓመታት ፍቅር በክርስቲያን ማኅበረሰብ ውስጥ የተለመደ ነገር ነበር። ይህን አስመልክቶ ተርቱሊያን እንዲህ ሲል ተናግሯል፡ “ብዙዎች ይህን እንደ መለያ ምልክት እንዲወስዱ ያደረጋቸው በተግባር የተገለጠው በእጅጉ የከበረው ፍቅር ነው። እርስ በርሳቸው እንዴት እንደሚዋደዱ ተመልከቱ።”--(See Terullian’s Apology 39 as translated by S. Thelwall at https://www. logoslibrary.org/tertullian/apology/39.htm19 l.)

ከክርስቶስ ልደት በኋላ 160 እና 265 ዓ.ም. ላይ ሁለት አውዳሚ ወረርሽኞች በተከሰቱበት ወቅት የእግዚአብሔር ፍቅር ከፍ ባለ ሁኔታ ተገልጦ ነበር። ክርስቲያኖች ወደ ኋላ ሳይሉ የታመሙትን እና ለመሞት የሚያጣጥሩ ወገኖችን ያገለግሉ ነበር። ወረርሽኙ በአሥር ሺ የሚቆጠሩ ሰዎችን ገድሎ መንደሮችን እና ከተሞችን ያለ ሰው ወና አስቀርቶ ነበር። የክርስቲያኖች ከራስ ወዳድነት የጸዳ መሥዋዕትነት፣ መተሳሰብ እና የፍቅር አገልግሎት በህዝቡ ላይ ግዙፍ ተጽዕኖ ማሳደር ችሎ ነበር። በእነዚህ ሁለት የወረርሽኝ ወቅቶች በጊዜ ሂደት በሺዎች፣ በመቶ ሺዎች ብሎም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በሮም ግዛት ውስጥ የነበሩ ሕዝቦች የየሱስ አማኞች ለመሆን ችለዋል። ፍቅር፣ የሌላውን ችግር እንደ ራስ ማየት እንዲሁም ለታመመውና በሞት አፋፍ ለሚገኘው በተቀናጀ መንገድ ራስ ወዳድ ያልሆነ እንክብካቤ ማድረግ--በእነዚህ አማኞች እና እነርሱ በሚወክሉት ክርስቶስ ላይ አድናቆት ፈጥሮአል።

ዘ ራይዝ ኦቭ ክርስቲያኒቲ በሚል ርዕስ በ ሮድኒ ስታርክ የተጻፈው የታሪክ መጽሐፍ እነዚህን ታሪካዊ ክስተቶች በአዲስ እና የተሻሻለ ብርሃን አቅርቦአል። መጽሐፉ በሁለተኛው ወረርሽኝ ወቅት (260 ዓ.ም.) አሁንም በአብዛኛው ይሁዲ-ክርስቲያን የነበረው ማኅበረሰብ በሥቃይ ውስጥ የነበረው ሰብዓዊ ወገን ያንሰራራ ዘንድ መሠረታዊ ነገሮችን በማቅረብ እንዴት ተግባራዊ የነርስ ሥራ እንደሠራ ይገልጣል። “ሁለተኛው ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት በ260 ዓ.ም. ገደማ ዲዮናስዮስ በጻፈው ደብዳቤ የአካባቢው ክርስቲያኖች ላደረጉት በጀግንነት የተሞላ አረጋውያንን የመንከባከብ ትጋት ረዘም ያለ የምስጋና ጽሑፍ ያሰፈረ ሲሆን፤ ከእነዚህ ክርስቲያኖች መካከል ብዙዎቹ ሌሎችን በመንከባከብ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

“አብዛኞቹ ክርስቲያን ወንድሞቻችን ወሰን የለሽ ፍቅርና ታማኝነት አሳይተዋል፤ ለራሳቸው ፈጽሞ አይጨነቁም፤ ይልቁንም አንዱ ለሌላው ብቻ ያስባል። በእነርሱ ላይ ሊደርስ የሚችለውን አደጋ ችላ ብለው ለታመመው ይተጉ ነበር። የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ በማሟላት በክርስቶስ ያገለግሏቸው የነበረ ሲሆን፣ በሽታውን ተጋርተው የምድር ዘመናቸው በመቋጨቱ ውስጣቸው የተረጋጋና ደስተኞች ነበሩ። ምክንያቱም ያንን የባልንጀሮቻቸውን ህመም ተጋርተዋልና”——Rodney Stark, The Rise of Christianity (Princeton, New Jersey: Princeton University Press, 1996), p. 82. እዚህ ላይ ግልጽ ሆኖ የቀረበው መልእክት ምንድን ነው? እኛም ይህን ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነ መንፈስ ማሳየት እንችል ዘንድ ስለ እኔነት መሞት ምን እንማራለን? ጉዳዩ ቀላል ይሆን?

ሚያዝያ 4
Apr 12


ተጨማሪ ሀሳብ


“የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን ያጠፋ ዘንድ በኃይል የተሞከሩት የሰይጣን ጥረቶች ከንቱ ሆኑ። የየሱስ ደቀ መዛሙርት ሕይወታቸውን የሰውለት ታላቁ ተጋድሎ፣ እነዚህ ታማኝ፣ ደረጃቸውን ያስጠበቁ አማኞች በተሰለፉበት ሲወድቁ አላበቃም፤ በመሸነፍ ድል ነሱ። የእግዚአብሔር ሠራተኞች ተሰዉ፣ ሥራው ግን በቀጣይነት ወደፊት ተራመደ።

ወንጌሉ መስፋፋቱን ቀጠለ፣ የሚደግፉትም ቁጥር ይጨምር ጀመር። የሮም ንሥሮች እንኳ ወደማይደፍሯቸው ስፍራዎች ጭምር ሰርስሮ ገባ። ማሳደዱ እንዲቀጥል ሲጎተጉቱ የነበሩትን የአሕዛብ መሪዎች በምክንያት ሲገዳደር አንድ ክርስቲያን እንዲህ አለ ‘ልታሰቃዩን፣ ልትጎዱንና ልታስጨንቁን ትችላላችሁ… ጭካኔአችሁ ግን ምንም አይፈይድም። ሌሎች ይቀላቀሉን ዘንድ ለማሳመን ጠንካራ ግብዣ ከመሆን አልዘለለም። መታጨዳችን ሲጨምር፣ ማቆጥቆጣችን የበለጠ ይበዛል፤ የክርስቲያኖች ደም ዘር ነው።’ ”-- Tertullian, Apology, paragraph 50.--ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 49።

“ጸድቃን በኃጢአተኞች እጅ ስደት ይደርስባቸው ዘንድ የሚፈቅደው ምስጢራዊው አቅርቦት በእምነት ደካማ ለሆኑ ለብዙዎች ታላቅ ግራ መጋባት ምክንያት ሆኖ ታይቶአል።

በመልካምነታቸውና በንጽህናቸው ተወዳዳሪ የሌላቸው እነርሱ በጨካኝ ኃይላት ሲጎሳቆሉ ሳለ፣ እጅግ ወራዳ ተግባር የሚፈጽሙትን በማበልጸጉ ምክንያት፣ አንዳንዶች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን አመኔታ እስከ መተው ድረስ የተዘጋጁ ሆነዋል። እውነተኛ ፈራጅና ርኅሩኅ አምላክ በኃይሉም መጠን-የለሽ የሆነው ጌታ፣ እንዲህ ዓይነት የፍርድ መጓደልና ጭቆናን እንዴት ይታገሳል? የሚል ጥያቄ ይነሣል። ይህ እኛን የሚመለከት ጥያቄ አይደለም። እግዚአብሔር ስለ ፍቅሩ አጥጋቢ ማስረጃ ሰጥቶናል፣ በመሆኑም የፈቃዱን አሠራር ስለማንረዳው ብቻ መልካምነቱን ልንጠራጠር አይገባንም” (ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 55)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ስደት ምን ጥቅም አለው? እግዚአብሔር ሕዝቦቹ ላይ መከራ እንዲደርስ የሚፈቅደው ለምንድን ነው?

2. ጓደኛዎ ይህን ጥያቄ ቢጠይቅዎ እንዴት ይመልሱለታል፡ መከራ በደረሰብኝ ወቅት እግዚአብሔር የት ነበር? እርሱ የሚወደኝ ከሆነ በእንደዚያ ያለ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ለምን አልፋለሁ?

3. አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናችሁ በዓለም ላይ ተጽእኖ ታሳድር ዘንድ ለሌሎች አሳቢ ማኅበረሰብ ማፍራት የምትችለው እንዴት ነው? የዚህን ሳምንት ጥናት ተግባራዊ ማድረግ በምትችሉባቸው ተጨባጭ መንገዶች ዙሪያ ተወያዩ።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL