የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ታላቁ ተጋድሎ



2ኛ ሩብ ዓመት 2024


መጋቢት 21 - 27

1ኛ ትምህርት

Mar 30 - Apr 5




ከጦርነቶች ሁሉ ጀርባ ያለው ጦርነት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ራእ. 12:7–9፣ ሕዝ. 28:12–15፣ ኢሳ. 14:12–14፣ ዘፍ. 3:15፣ ዮሐ. 17:24–26.


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “በሰማይም ጦርነት ሆነ፤ ሚካኤልና መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ፤ ዘንዶውና መላእክቱም መልሰው ተዋጓቸው፤ ነገር ግን ድል ተመቱ፤ በሰማይም የነበራቸውን ስፍራ ዐጡ።” (ራእ. 12፡7-8)፡፡

እግዚአብሔር እጅግ መልካም አምላክ ከሆነ፣ ዓለም አብልጦ ክፉ የሆነው ለምንድን ነው? የፍቅር አምላክ በዚህ መጠን ክፋት ይኖር ዘንድ እንዴት መፍቀድ ይቻለዋል? በጥሩ ሰዎች ላይ ለምን መጥፎ ነገር ይከሰታል? በዚህ ሳምንት ትምህርት፣ በመልካም እና በክፉ መካከል እየተካሄደ ያለውን ዘመን ጠገብ ግጭት እንመረምራለን።

ሉሲፈር በሰማይ ካመጸበት ጊዜ አንስቶ የተከሰተውን የክፋት መጠንሰስ እና እግዚአብሔር የኃጢአትን ችግር ለመፍታት ያሳየውን ብርቱ ትዕግሥት እንመረምራለን።

እግዚአብሔር የአስደናቂ ፍቅር አምላክ ሲሆን፣ ባህሪው በራሱ ፍቅር ነው (1ዮሐ. 4፡7-8)። ድርጊቶቹ ሁሉ አፍቃሪነቱን ፍንትው አድርገው ያሳያሉ (ኤር. 31፡3)። ፍቅር ፈጽሞ ሊገደድ፣ ሊጠመዘዝ ወይም በጉልበት ሊጸና አይችልም። “ፍቅር በፍቅር ብቻ ይነቃቃል” ስትል ኤለን ኋይት በዘመናት ምኞት ገጽ 22 ላይ ትናገራለች። የመምረጥን ኃይል መከልከል የመውደድን ችሎታ ማስወገድ ሲሆን፣ የመውደድን ችሎታ ማስወገድ ደግሞ እውነተኛውን ደስተኝነት መደምሰስ ነው። ለእግዚአብሔር ታማኝ እንሆን ዘንድ እነሆ እርሱ ልባችንን በፍቅሩ ያሸንፋል። ኃጢአት ፈጽሞ ዳግመኛ በዩኒቨርስ እንዳይነሣ በማድረግ ረገድ፣ በዚህ በመልካም እና በክፉ መካከል እየተካሄደ ባለ ፍልሚያ ውስጥ እርሱ ተገቢውን እርምጃ እየወሰደ ይገኛል። የእግዚአብሔር ዓላማ ለፍጥረታቱ ምንጊዜም የሚበጀውን እርምጃ እየወሰደ መሆኑን በመላው ጽንፈ ዓለም ፊት ማሳየት ነው። በመልካም እና በክፉ መካከል እየተካሄደ ባለው ፍልሚያ ላይ የብርሃን ጮራ በሚፈነጥቅልን በእግዚአብሔር ፍቅር መነጽር ዓለምን መመልከታችን፣ በጎው ክፉውን እንደሚያሸንፍና ድሉም ለዘላለም ጸንቶ እንደሚኖር ለእያንዳንችን ማረጋገጫ ይሆነናል።

መጋቢት 22
Mar 31

በሰማይ የተካሄደው ጦርነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ራእ. 12፡7-9። ይህ ክፍል በሰማይ ሰፍኖ የሚገኘውን ነጻነት እና የኃጢአትን መጠንሰስ እንዴት ይገልጸዋል? ሉሲፈር ባመፀ ጊዜ እግዚአብሔር ምን ዓይነት ምላሽ መስጠት ይችል ነበር?



እነዚህ ጥቅሶች በመልካም እና ክፉ ኃይላት መካከል የተከሰተውን ዩኒቨርስ አቀፍ ግጭት ይገልጻሉ። ሰይጣንና መላእክቱ ከክርስቶስ ጋር ተዋጉ፤ በመጨረሻም ከሰማይ ተባረሩ። በዚያ ፍጹም በሆነ ሰማያዊ ሥርዓት መሃል ጦርነት የመፈንዳቱን ወሬ መስማት ፍጹም እንግዳ ነገር ይመስላል። ስለ ምን ጦርነቱ ተከሰተ? ጦርነቱን ያስጀመረው አፍቃሪው አምላክ የፈጠረው ዲያብሎስ ነው? ይህን መልአክ እንዲያምጽ ያነሣሣው በአፈጣጠሩ ላይ የነበረ እንከን ይሆን? መጽሐፍ ቅዱስ የክፋትን ሥረ መሰረት በግልጽ ያብራራል። አምላካዊው ቃል መጋረጃውን ገልጦ የዚህን በመልካም እና ክፉ መካከል የተከሰተ ውዝግብ ያስቃኘናል ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ሕዝ. 28፡12-15 እና ኢሳ. 14፡12-14። በዚህ ሉሲፈር ተብሎ በተጠራ መልአክ አእምሮ ውስጥ ወደ አመጽ ሊመራ የሚችል ምን ነገር ተከሰተ?



እግዚአብሔር ዲያብሎስን አልፈጠረም። ይልቁንም እርሱ በአንጸባራቂ ብርሃን የተሞላውንና ሉሲፈር የሚል ስያሜ የተሰጠውን መልአክ ፈጠረ። ይህ መልአክ ፍጹም ሆኖ ተፈጠረ። በፍጹምነቱ ውስጥ የመምረጥ ነጻነት የተካተተ ሲሆን፣ ይህም በግዳጅ ሳይሆን በፍቅር የሚመራው የአምላካዊው መንግሥት መሠረታዊ መርኅ ነው። ሉሲፈር በሰማይ እያለ ኃጢአት በገዛ አእምሮው ውስጥ ተጠነሰሰ። ይህ ፍጹም መልአክ ትዕቢት እና ቅናት በልቡ ውስጥ ሥር ሰድዶ በፈጣሪው ላይ እስከ ማመጽ እንዲያደርሰው ለምን እንደፈቀደ የሚያትት አንዳችም አመክኖአዊ ማብራሪያ የለም።

ፍጡር የሆነው ሉሲፈር ፈጣሪ ለሆነው አምላክ ብቻ የተገባውን መመለክ ለገዛ ራሱ ተመኘ። የእግዚአብሔርን ሥልጣን ጥያቄ ውስጥ በማስገባት አምላካዊውን ዙፋን ለመንጠቅ ሞከረ። የእርሱ አመፃ በሰማይ ጦርነት እንዲፈነዳ መንስዔ ሆነ። ምንም እንኳ እግዚአብሔር ሉሲፈርን ለብዙ ጊዜ ቢታገሰውም፣ ሰማያዊውን መንግሥት በአመጹ እንዲያረክስ ግን አልፈቀደለትም። “ሰማያዊ መማክርት ሉሲፈርን ተማጸኑት። የፈጣሪን ታላቅነት፣ መልካምነትና ፍትሕ፣ የተቀደሰውንና መለወጥ የማይችለውን የሕጉን ባሕሪ የእግዚአብሔር ልጅ አቀረበለት። የሰማይን ሥርዓት የዘረጋው ራሱ እግዚአብሔር ነበር፤ ሉሲፈር ለአምላካዊው ሥርዓት ጀርባውን መስጠቱ--በፈጣሪው ላይ ውርደት፣ በራሱም ላይ ውድመት ያስከትላል። መጠን በሌለው ፍቅርና ምኅረት የተሰጠው ማስጠንቀቂያ፣ የእንቢተኝነትን መንፈስ የበለጠ ከማነሣሣት ውጪ አንዳች የፈየደው ነበር አልነበረም።”— Ellen G. White, The Great Controversy, pp. 494, 495. ከክፉ ጋር በተጎዳኘ ስለ እግዚአብሔር ባህሪ ምን ትምህርት ማግኘት ይችላሉ?

መጋቢት 23
Apr 01

ሉሲፈር ያታልላል፡ ክርስቶስ ደግሞ አሸናፊ ያደርጋል


ይህ ሉሲፈር በመባል ይታወቅ የነበረ ፍጹም መልአክ ኩራት እና ምቀኝነት በልቡ ውስጥ ሥር ሰድዶ በፈጣሪው ላይ እንዲያምጽ ለምን እንደ ፈቀደ ይፋ የሚያደርግልን አንዳችም አመክኖአዊ ማብራሪያ አናገኝም። የሰይጣን መታበይ ወደ ግልጽ አመጻ ተሸጋገረ። እግዚአብሔርን- -ኢፍትሐዊ አምላክ ሲል ከሰሰው። መላእክትን በጥርጣሬው እና በክሱ በከላቸው። ጥቅሱን ያንብቡ፡ ራእ. 12፡4። ጥቅሱ ስለ ሰይጣን የማታለል ችሎታ ምን ፍንጭ ይሰጠናል? እርሱ ስለ እግዚአብሔር የተናገረውን ውሸት ተቀብለው ስንቶቹ መላእክት ወደቁ?



በሰማይ ጦርነት በፈነዳበት ወቅት መላእክት የሱስን ወይም ሉሰፈርን ይከተሉ ዘንድ መወሰን ነበረባቸው። ይህ በሰማይ የተካሄደ ጦርነት ምን ዓይነት ተፈጥሮ ነበረው? አካላዊ ወይስ መርኅ አዘል ጦርነት? ወይስ ሁለቱንም ያካተተ? ዝርዝር ጉዳዮችን ባናውቅም ነገር ግን በስተ መጨረሻ ሰይጣን እና መላእክቱ “በሰማይ የነበራቸውን ስፍራ አጡ” ወደ ምድርም “ተጣሉ” (ራእ. 12፡8-9) ተብሎ መነገሩ፣ ግጭቱ አካላዊ ጭምር እንደነበር ያሳየናል። እንደውም ይህ ጦርነት አንዳንድ አካላዊ ክፍሎችን ማካተቱ እሙን ነው።

በሰማይ ስለተካሄደው ጦርነት በአንድ ነገር ላይ እርግጠኛ መሆን የሚቻል ሲሆን፣ ይኸውም እያንዳንዱ መልአክ ከክርስቶስ ጋር ወይም ከእርሱ በተቃራኒ ይሰለፍ ዘንድ መወሰን ነበረበት። ማን ማንን ይከተል? የማንንስ ድምጽ ይስማ? ታማኞቹ መላእክት ለክርስቶስ አፍቃሪ ትእዛዛት ታማኝ መሆንን ሲመርጡ፣ ከመላእክቱ ሲሶው ግን የሉሲፈርን ድምጽ ሰምተው እግዚአብሔርን ሳይታዘዙ በመቅረታቸው ሰማይን አጡ። እኛም በዚህ ወሳኝ የምድር ታሪክ ዘመን ውሳኔአችን ከክርስቶስ ጋር መቆም ነው ወይስ በተቃራኒው መሰለፍ? ይህን ይፋ እናደርግ ዘንድ ጥሪ ቀርቦልናል። ከየትኛው ወገን እንደ ተሰለፍን ይፋ ማድረግ እነሆ ከእኛ ይጠበቃል። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 2:15–17፣ ዘፀ. 32:26፣ ኢያ. 24:15፣ 1ነገሥ. 18:20- 21፣ ራእ. 22:17። ጥቅሶቹ በታላቁ ተጋድሎ ወስጥ ስላለው መሠረታዊ መርኅ ምን ያስተምሩናል?



እግዚአብሔር የሰውን ልጅ ሲፈጥር የማሰብ፣ የማመዛዘንና የመምረጥ ችሎታን በአእምሮው ውስጥ አኖረ። ስብእናዊ ማንነታችን ከነጻ የመምረጥ ችሎታ ጋር የተዋቀረ ነው። እኛ ተራ ሮቦቶች አይደለንም። ነጻ የመምረጥ ችሎታችንን ተጠቅመን በዘላለማዊ መንፈሳዊ መርኅዎች እንኖር ዘንድ፣ እነሆ ከእንስሳት ፍጥረት በተለየ በእግዚአብሔር አምሳል ተፈጠርን። ሉሲፈር በሰማይ ካመፀበት ጊዜ ጀምሮ ህዝቡ ለፍቅሩ ምላሽ እንዲሰጥና እርሱን ለማገልገል በመምረጥ ትእዛዙን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቦአል። እኛ ከክፉው ኃይል ጋር በየቀኑ በግል ከምናደርገው ውጊያ አኳያ በሰማይ ስለ ተካሄደው ጦርነት ምን ትምህርት እናገኛለን? ሰይጣን እነዚህን ጻድቅና ቅዱሳን ሰማያዊ ፍጡራን ማታለል መቻሉ፣ እኛን ለማሳት ስለሚያደርጋቸው በክፋት የተሞሉ ሙከራዎች ምን ይነግረናል?

መጋቢት 24
Apr 02

ምድርም የዚሁ አካል ሆነች


እግዚአብሔር ምድርን ሲፈጥር ፍጹም አድርጎ ሠራት። “እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፤ እነሆም፣ እጅግ መልካም ነበረ።” (ዘፍ. 1፡31)። በየትኛውም ቦታ የኃጢአት ወይም የክፋት እንከን አልነበረም። ነገር ግን ለሉሲፈር ሰጥቶት የነበረውን የመምረጥ ነፃነት በተመሳሳይ ለእነርሱም ሰጥቶአቸው ነበር። በሰማይ ሮቦቶች እንዲኖሩት እንዳልፈለገ ሁሉ፣ በምድርም እንዲኖሩት አልፈለገም ነበር።

እንደ እውነቱ ከሆነ፣ ይህን ነፃነት ግልጽ ለማድረግ ከተለመደው አካሄድ እልፍ ብሎ ነበር። በአታክልቱ ስፍራ አንዲት ዛፍ ከተከለ በኋላ መልካም እና ክፉን መለየት የምታስችል የዕውቀት ዛፍ ብሎ ጠራት። አዳም እና ሔዋን የመምረጥ ነፃነት እንዳላቸው እንዲያውቁ ለማድረግ ስለፈለገ፣ ስለ ጉዳዩ ሊነግር የሚችልበትን መንገድ ቀየሰ።

ሰይጣን ወደ ዛፉ ሲመጣ፣ በስፍራው ያልተለመደ ረዘም ያለ ቆይታ ያደረገችውን ሔዋን “መሞት እንኳ አትሞቱም፤ ከፍሬው በበላችሁ ጊዜ ዐይናችሁ እንደሚከፈትና መልካምና ክፉን በማወቅ፣ እንደ እግዚአብሔር እንደምትሆኑ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ ነው” (ዘፍ. 3፡4-5) አላት። ከዚህ ዛፍ ብትበሉ በዓይነቱ አዲስ ወደ ሆነ የሕይወት ከፍታ ትመነጠቃላችሁ። በደስታ የተሞላችሁ ትሆናላችሁ። ከዚህ ቀደም አይታችሁ በማታውቁት የደስታ ስሜት ትጥለቀለቃላችሁ። ሔዋን፣ እግዚአብሔር አንቺን የሆነ ነገር ደብቆሻል።

ከዚህ የተከለከለ ፍሬ ቅጠፊና ብዪ። በመጀመሪያ ሔዋን ቀጥሎም አዳም ይህን ምርጫ ሲመርጡ፣ እግዚአብሔር ለዘላለም ተዘግቶ እንዲቀር የፈለገውን በር ወለል አድርገው ከፈቱ። ይህ የተከፈተ በር--የኃጢአት በር፣ የሥቃይ በር፣ የልብ መሰበር በር፣ የበሽታ በር እና የሞት በር ነበር። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡1-3፣ ሮሜ 3፡23፣ ሮሜ 5፡12። እነዚህ ጥቅሶች ምን የሚያመሳስላቸው ነገር አለ? ውሎ አድሮ መላውን ሰብአዊ ዘር በቸነፈር የመታውን የኃጢአት ውጤት ይግለጹ።



የኃጢአት አስኳሉ በእግዚአብሔር ላይ ማመጽ ነው። ከእግዚአብሔር ጋር ወደ መለያየት ያመራል። እግዚአብሔር የሕይወት ምንጭ እንደመሆኑ፣ ከእርሱ መለየት ሞት ያስከትላል። በተጨማሪ ወደ ጭንቀት፣ ትካዜ፣ ሕመም እና በሽታ ይመራል። በዓለማችን ላይ እየደረሰ ያለው መከራ በኃጢአት ውድመት ስር የመኖር ውጤት ነው። ይህ ማለት የሥቃይ ወይም የበሽታ ገፈት የመቅመሳችን መንስዔ ኃጢአት የመሥራታችን ውጤት ነው ማለት አይደለም። ይልቁንም እያንዳንዳችን የኃጢአት ውድመት በደረሰባት ፕላኔት ውስጥ በመኖራችን የጉዳት ሁሉ ሰለባ ሆነናል ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዘፍ. 3፡15፣ ዘሌዋ. 5፡5-6፣ ዮሐ. 1፡29። አዳምና ሔዋን ኃጢአት ከሠሩ በኋላ ለጥፋተኝነት ስሜታቸው እና ለተስፋ መቁረጣቸው ማጽናኛ የሚሆን ምን የተስፋ ቃል በዚያው በገነት ተሰጣቸው? ለኃጢአት ችግር የቀረበውን መፍትሔ አያሌ ምዕተ ዓመታትን አሻግረው ወደፊት እንዲመለከቱ ያስቻለው፣ እግዚአብሔር በኤደን የቀየሰው አገልግሎት ምን ነበር?

መጋቢት 25
Apr 03

ፍቅር መንገድ አያጣም


አዳምና ሔዋን ኃጢአት መሥራታቸውን ተከትሎ መኖሪያ ስፍራቸው የነበረውን የአትክልት ስፍራ መልቀቅ እንዳለባቸው እግዚአብሔር ነገራቸው። ከዚያች ቅጽበት አንስቶ ድካም እና ሥቃይ ዕጣ ፈንታቸው ይሆናል። መከራ መቀበል፣ እናም በመጨረሻ ያለ አንዳች ተስፋ መሞት? ለመሆኑ ሞት የሁሉም ነገር መጨረሻ ነው?

እንግዲህ እግዚአብሔር በዘፍ. 3፡15 ላይ የተጻፈውን የተስፋ ቃል የሰጣቸው በዚህ ወቅት ነበር። በቀጥታ ወደ ሰይጣን ይኸውም ወደ እባቡ እየተመለከተ እንዲህ አለ፡ “ ‘በአንተና በሴቲቱ፣ በዘርህና በዘሯ መካከል፣ ጠላትነትን አደርጋለሁ፤ እርሱ ራስህን ይቀጠቅጣል፤ አንተም ተረከዙን ትቀጠቅጣለህ።” በወቅቱ ይህ ምን ማለት እንደሆነ በትክክል ባይረዱም፣ እንደገና ተስፋ ማድረግ እንደሚችሉ ግን አውቀዋል። በሆነ መንገድ “በዘሯ” በኩል እነሆ ቤዛቸው ይመጣል።

እርግጥ ነው፣ የሴቲቱ ዘር የተባለው የሱስ ክርስቶስ ነው (ገላ. 3፡16)።

በመስቀል ላይ ሰይጣን የክርስቶስን ተረከዝ ቀጥቅጦ ነበር። ነገር ግን አንድ ቀን የእባቡ ራስ እንደሚቀጠቀጥና አዳምና ሔዋን የከፈቱት የመከራና የሞት በር እንደሚዘጋ የየሱስ ድል ዋስትናችን ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 2፡9፣ ገላ. 3፡13፣ 2ቆሮ. 5፡21። ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስላቀረበው መሥዋእት ግዝፈት ምን ይነግሩናል?



ፈጣሪ አምላክ በእርግጥ ይወደኝ ይሆን ብለው አስበው ያውቃሉ? እስቲ ወደ መስቀሉ ይመልከቱ፤ ዐናቱ ላይ ወደ ተደፋው የእሾህ አክሊል፣ እጆቹንና እግሮቹን ወደ ቸነከሩት ምስማሮች ይመልከቱ። የሱስ በቀራኒዮ ባፈሰሰው እያንዳንዱ የደም ጠብታ እግዚአብሔር እወድሃለሁ እያለ ነው። ያለ አንተ በሰማይ መሆን አልፈልግም። አዎ ኃጢአት ሠርተሃል፣ ራስህን ለጠላት አሳልፈህ ሸጠሃል፣ አዎ አንተነትህ ዘላለማዊ ሕይወት የማይገባው ነው። እኔ ግን አንተን እንደገና ለማግኘት ቤዛውን ከፈልኹ። ወደ መስቀሉ በመመልከትህ ከተወደድህ፣ እንግዲህ ዳግመኛ መባዘን የለብህም።

መጽሐፍ ቅዱስ ወደዚህ ዓለም መጥቶ ከማንኛውም ሰው በተመሳሳይ የልብ መሰበር፣ ተስፋ መቁረጥ እና ሥቃይ ስለ ደረሰበት የሱስ ይናገራል። እኛን ከሚያጋጥሙ ተመሳሳይ ፈተናዎች ጋር የተጋፈጠውን ክርስቶስ ይገልጥልናል። ክርስቶስ በሕይወቱና በመስቀል ላይ ሞቱ--ስለ እኛ ስለ እያንዳንዳችን በግል--በጨለማ ዓለም ገዦች፣ በሥልጣናት እና ኃይላት ላይ ባለ ድል ሆነ።

ያስቡበት፡ አጽናፈ ሰማይን የፈጠረው የሱስ (ዮሐ. 1፡3) ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ወደዚህ የወደቀ ዓለም መምጣት ብቻ ሳይሆን ማናችንም ብንሆነ ልንፈቅድ በማንችለው አኳኋን መከራ ተቀበለ (ኢሳ. 53፡1-5)። ይህን ያደረገው እያንዳንዳችንን ስለወደደን ነው። ይህ እንዴት ያለ ብሩህ ተስፋ እንዲኖረን የሚያደርግ ጠንካራ ምክንያት ነው! ክርስቶስ በመስቀል ላይ የሰይጣንን ክሶች እንዴት መለሰ? በመልካም እና በክፉ መካከል ላለው ታላቅ ውዝግብ የእርሱ ሞት ምን አከናወነ?

መጋቢት 26
Apr 04

ሊቀ ካህናችን


የሱስ በመስቀል ላይ ያደረገልን ነገር በሰማይም ስለ እኛ እንዲማልድ አስችሎታል።

ከሙታን የተነሣው ጌታችን ለመዳን እና በእግዚአብሔር መንግሥት ለዘላለም ለመኖር የሚያስፈልገንን ሁሉ የሚሰጠን ታላቁ ሊቀ ካህናችን ነው። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዕብ. 4፡15-16፣ ዕብ. 7፡25። በዚህ--ፈተና፣ መከራ፣ በሽታ እና ሞት በተንሰራፋበት ዓለም እነዚህ ጥቅሶች ማረጋገጫ የሚሰጡን እንዴት ነው?



ጥቅሱ እንዲህ ይላል፡ “ነገር ግን እንደ እኛ በማንኛውም ነገር ተፈተነ… ይሁን እንጂ ምንም ኀጢአት አልሠራም” (ዕብ. 4፡15)። አክሎ ሲናገር፡ “እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበልና በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፣ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብ. 4፡16)።

ነገሩን ቀለል አድርጎ ለማቅረብ ያህል፡ የሱስ እኛን በሞቱ የዳንን እና በደሙ የተዋጀን አድርጎ የጽድቅ ልብስ በማልበስ በዩኒቨርስ ፊት ያቀርበናል። በእኛ ላይ ሊደርስ የሚችለው ነገር ሁሉ በእርሱ ላይ ደርሶአል። በክርስቶስ ስንሆን በቀደመው ኃጢአታችን ኩነኔ የለብንም። ከጥፋተኝነት ስሜት ነጻ ነን። በእርሱ ታላቅ የምልጃ ሥራ ህይወታችንን ቀፍድዶ የነበረው የኃጢአት ሰንሰለት ተሰበረ እኛም ነጻ ወጣን። ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ዮሐ. 17፡24-26። በመልካም እና በክፉ መካከል እየተካሄደ ባለው ታላቅ ተጋድሎ ክርስቶስ አጥብቆ የሚመኘው ምንድን ነው?



“ታላቁ መሥዋዕትነት ከተጠናቀቀ በኋላም ‘እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝ እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ’ (ዮሐ. 17፡24) ብሎ ልመናውን እስኪያቀርብ ድረስ የመልአክቱን አክብሮት አልቀበልም ብሎ ክርስቶስ ወደ ላይ ዐረገ። ከዚያም በማይገለጽ ፍቅርና ኃይል መልስ ከአብ ዙፋን እንዲህ ሲል መጣ ‘የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉም ለእርሱ ይስገዱ’ (ዕብ. 1፡6)። አንድ ነቁጥ እንኳ በየሱስ ላይ አልነበረም። መዋረዱ አብቅቶ መሥዋዕትነቱ ተጠናቆ፣ ከስም ሁሉ በላይ የሆነው ስም ተሰጠው።” ታላቁ ተጋድሎ ትርጉም ገጽ 272 [መታገስ አጋዤ]።

የሱስ ከምንም ነገር በላይ በሰማይ ከእርሱ ጋር እንድንሆን ይፈልጋል። የልቡ ምኞት፣ የሞቱና የአማላጅነቱ ምክንያት እኛን ማዳን ነው። በሕይወትዎ በልዩ ሁኔታ የሚፈልጉት ነገር አለ? ለየሱስ ይንገሩት። ሐዘን ባለበት እርሱ መጽናናት ያመጣል። ፍርሐት ባለበት ሰላም ያመጣል። የጥፋተኝነት ስሜት ባለበት ምህረት ያመጣል። ድክመት ባለበት ብርታት ያመጣል። ክርስቶስ ራሱን ስለ እኛ መሥዋዕት ያደረገው ለምንድን ነው ብለው ያስባሉ? በፊቱ የከበረ ዋጋ እንዲኖረን ያደረገን ምንድን ነው?

መጋቢት 27
Apr 05


ተጨማሪ ሀሳብ


“ሰይጣንን ከሰማይ በማስወገዱ እግዚአብሔር የእርሱን ፍትሕ ዐወጀ፤ የዙፋኑንም ክብር ጠበቀ። ሆኖም ለዚህ ከዳተኛ መንፈስ ማታለያዎች እጅ ሰጥቶ ሰው ኃጢአት ሲሠራ፣ ለወደቀው ዘር አንድያ ልጁን አሳልፎ በመስጠት፣ እግዚአብሔር ያለውን ፍቅር በመረጃ በሚታይ፣ በተግባር ገለጸ። በማስተሰርያው ሥነ ሥርዓት ውስጥ የእግዚአብሔር ባህሪ ተገልጦአል። ሉሲፈር ለመረጠው የኃጢአት መንገድ በምንም ዓይነት መልኩ የእግዚአብሔር መንግሥት ሊኮነን እንደማይገባው ኃያሉ የመስቀሉ መከራከሪያ በዓለማት ሁሉ በተግባር አሳይቷል።” (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 571 [መታገስ አጋዤ እንደተረጎመው])።

“የቀራኒዮ መስቀል ሕጉ መቀየር እንደማይችል ሲናገር ሳለ፣ የኃጢአት ዋጋ ሞት መሆኑን ለዩኒቨርስ ሁሉ ያውጃል። ‘ተፈጸመ’ በሚለው ላንቃው እየተዘጋ በነበረው የአዳኙ ጬኸት ውስጥ፣ የሰይጣን ሞት ደወል ተደውሎአል። ለረጅም ጊዜ ሲካሄድ የነበረው ታላቁ ተጋድሎ ተወሰነ፤ የመጨረሻው የኃጢአት ማስወገድ ሥራም ተረጋገጠ። “እርሱ ደግሞ በሞት ላይ ሥልጣን ያለውን በሞት እንዲሽር” የእግዚአብሔር ልጅ በመቃብር በሮች ውስጥ አለፈ፣ ‘ይኸውም ዲያብሎስ ነው’ (ዕብ. 2፡14)። (ታላቁ ተጋድሎ ገጽ 574 [መታገስ ትርጉም አጋዤ]


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እግዚአብሔር ሉሲፈር እንደሚያምጽ አስቀድሞ የሚያውቅ ከሆነ ለምን የመምረጥ ነጻነት ሰጠው? ወይም--ሉሲፈር እንዳመጸ እግዚአብሔር ወዲያውኑ ያላጠፋው ለምንድን ነው? እግዚአብሔር ሉሲፈርን ወዲያው ቢያስወግደው ኖሮ ያልወደቀው ዓለም ምን ዓይነት ምላሽ ሊኖረው ይችል ነበር? ታላቁን ተጋድሎ በውል ለመረዳት-- የዩኒቨርስ የደኅንነት እቅድ ፍላጎት ጽንሰ ሀሳብ በእጅጉ አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው (1ጴጥ. 1:12፣ ራእ. 5:13፣ ራእ. 16:7)?

2. ለክርስቶስ በመስቀል ላይ መሞት ምክንያት ወይም ምክንያቶች ምን ሊሆን ይችላል ብለው ያስባሉ? የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለመግለጥ ብቻ ነበር? ወይስ ለኃጢአት መቀጮ ቤዛ ለመሆን? እንደዚያ ከሆነ መቀጮው ለማን ተከፈለ? ሐሳብዎን ያካፍሉ። ለሚሰጡት ሐሳብ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ያቅርቡ።

3. “ታላቁ ተጋድሎ” የሚለውን አገላለጽ ስንጠቀም ምን ማለታችን ነው? ስለ ታላቁ ተጋድሎ ልዩ ልዩ ገጽታዎች እና የዚህን ሳምንት ትምህርት እንዴት በህይወትዎ መተግበር እንደሚችሉ ይወያዩ።

4. ስለ ታላቁ ተጋድሎ ተጨባጭ እውነታ የሚነግሩን የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች የትኞቹ ናቸው (የሚከሉትን ጥቅሶች እንደ አብነት ይመልከቱ፡ ኢዮ. 1፣2፣ ኤፌ. 6፡12)

5. የሰባተኛው ቀን አድቬንቲስት መጽሐፍ ቅዱሳዊ አረዳድ ከሌሎች የክርስቲያን ቤተ እምነቶች ጋር ሲነጻጸር ልዩ የሆነው እንዴት ነው? አድቬንቲስቶችን ከሌሎች እንዲለዩ የሚያደርገው የዚህ ታላቅ ተጋድሎ ጭብጥ ምድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL