የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ታላቁ ተጋድሎ



2ኛ ሩብ ዓመት 2024



ሚያዝያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ 2016 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Mar 30 - Jun 28




አዘጋጅ : ማርክ ፊንሊ

ትርጉም : ዘላለም አስረስ



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም። በተለየ ካልተጠቀሰ በቀር በዚህ ሰንበት ትምህርት ጥቅም ላይ የዋሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች በሙሉ የተወሰዱት ከአዲሱ መደበኛ ትርጉም ነው።


2ኛ ሩብ ዓመት
ከመጋቢት 21 እስከ ሰኔ 21 2016 ዓ.ም.


በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ መግቢያ

“የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክት ዐበይት ጭብጥ ምንድን ነው?” ተብለው ቢጠየቁ መልስዎ ምን ይሆናል? የሱስ? የደኅንነት እቅድ? መስቀሉ? ሦስቱም በትክክል መልስ መሆን ይችላሉ። ሆኖም እነዚህ ሦስት ወሳኝ ርዕሰ ጉዳዮች ሁሉን አቀፍ በሆነው “ታላቁ ተጋድሎ” ይበልጥ ተገልጠዋል። ይህ ጭብጥ ከዘፍጥረት አንስቶ እስከ ራእይ ባሉት የመጽሐፍ ቅዱስ መልእክቶች በስፋት ናኝቷል።

ታላቁ ተጋድሎ ሉሲፈር በእግዚአብሔር ላይ ባመፀ ጊዜ በሰማይ ተጀመረ። በዚህ ዩኒቨርስ አቀፍ ተጋድሎ አስኳል ውስጥ ከእግዚአብሔር ፍቅር ጋር በተያያዘ የሚነሣ ጥያቄ አለ። ለመሆኑ እርሱ ሙሉ በሙሉ አፍቃሪ አምላክ ነው? ለፍጡራኑ የሚበጀውን ጥቅም እና ፍላጎት ከግምት ያስገባል--ወይስ የራሱን ጥቅም ብቻ የሚፈልግ አምባገነን መሪ ነው?

የዚህ ሩብ ዓመት የሰንበት ትምህርታችን የዓለምን ታሪክ ከአምላካዊው አመለካከት አኳያ በማስቃኘት፣ ትንቢትን ተንተርሶ ከክርስቶስ ዘመን አንስቶ በርካታ መቶ ዓመታትን አልፎ፣ እስከ ዘመናችን ብሎም ከዚያ ባሻገር ያለውን ሳይቀር ይዳስል። የእግዚአብሔር ባህሪ ፍቅር፣ ድርጊቶቹ ሁሉ በፍቅር የተሞሉ ቢሆኑም፣ ነገር ግን ይህ እውነታ ውሱን ለሆኑት የሰው ልጆች--ሌላው ቀርቶ ለመላእክትም እንኳ ሁሌም ግልጽ ላይሆን ይችላል። ነገር ግን ታላቁ ተጋድሎ እየተገለጠ ሲመጣ፣ የእግዚአብሔርም ፍቅር ደረጃ በደረጃ መታየት ይጀምራል።

በቀራንዮ መስቀል የፍቅሩን ቁመትና ጥልቀት በግልጽ እናያለን። ክርስቶስ በቀራኒዮ መስቀል የሰውን ልጅ ለመቤዠት ሕይወቱን አሳልፎ በሰጠ ጊዜ፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በመላው ዩኒቨርስ ፊት ታየ። የሰይጣንም የመጨረሻ ሽንፈት የተረጋገጠ ሆነ።

ሆኖም ጦርነቱ ግን እንደ ተፋፋመ ቀጠለ። ሰይጣን የሱስን ከመስቀል ላይ ለማስወረድ ሞክሮ እንደ ነበር ሁሉ፣ ባለፉት በርካታ መቶ ዓመታት በእግዚአብሔር ሕዝቦች ላይ ተመሳሳይ ድርጊት ሲፈጽም ይስተዋላል። ምንም እንኳ ሰይጣን የክርስቶስን ቤተ ክርስቲያን በአሰቃቂ ሁኔታ ቢያሳድድና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ወገኖችን ቢያርድም፣ እግዚአብሔር ግን ምንጊዜም ከሕዝቡ ጋር ነበር፤ እርሱ ፈጽሞ አይተዋቸውም።

በዚህ ሩብ ዓመት በሰማይ ከተቀሰቀሰው ዓመፅ ጀምሮ የተስተዋሉ የታላቁ ተጋድሎ ዐበይት ክንውኖች ይዳሰሳሉ። በክርስቶስ እና በሰይጣን መካከል ያሉ አንኳር የግጭት መንስኤዎች ይመረመራሉ። ከባድ ስደት ቢደርስባቸውም ዎልደንሳውያን ያሳዩትን አይበገሬ ልበ ሙሉነት እንዲሁም የተሐድሶ አራማጆች ሥቃይ፣ እስራት፣ በእንጨት ላይ ታስሮ መቃጠል አልፎ ተርፎም የሰማዕትነትን ጽዋ ቢጎነጩም እንኳ፣ የመጽሐፍ ቅዱስን እውነት ለመከተል የነበራቸውን ቁርጠኝነት እንመለከታለን።

ኤለን ጂ ኋይት ስለእነዚህ የእምነት ጀግኖች የሚከተለውን አስተያየት ትሰጣለች፡ “የእነርሱ የበላይ መጽሐፍ ቅዱስ ነበር፤ በእርሱም ትምህርት አማካኝነት ሁሉንም አስተምህሮዎች እና መጠይቆች ፈተኑ። እነዚህ ቅዱሳን ሰዎች ሕይወታቸውን በማቃጠያ ስፍራው ሲሰጡ በእግዚአብሔር እና በቃሉ የነበራቸው እምነት በጽናት አቆማቸው።” ታላቁ ተጋድሎ፡ ገጽ 288-289)።

የተሐድሶ አራማጆች የለኮሱት የእውነት ችቦ እነሆ ዛሬም ደምቆ እየበራ ይገኛል።

የተሐድሶ አራማጆች በቅዱሳት መጻሕፍት ላይ የነበራቸው የማይናወጥ እምነት እና የጽድቅ በእምነት የመዳን ጽኑ ዋስትናቸው፣ በዊልያም ሚለር እና በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ሌሎች በርካታ ወገኖች ለተመሠረተው የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ንቅናቄ መነሣት መንገድ ጠርጓል።

ሰባተኛው ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ቤተ ክርስቲያን፣ ለበርካታ መቶ ዓመታት ተሰውረው የነበሩትን የመጽሐፍ ቅዱስ እውነቶች ለመመለስ በተሐድሶ አራማጆች በተጣለው መሠረት ላይ ትገነባ ዘንድ እነሆ በእግዚአብሔር ተነሣች። የቤተ ክርስቲያኗ ተልዕኮ ዋነኛ ዓላማ፣ በራእ. 14፡ 6-12 የሚገኘውን የሦስቱን መላእክት መልእክት የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ በቅርቡ ወደ ፍጻሜ ለምትመጣው ዓለም ማወጅ ነው።

ይህ የማወጅ ሥራ በሐዋርያው ዮሐንስ መልእክት በዘንዶ የተመሰለውን የሰይጣንን ቁጣ ይቀሰቅሳል፡ “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጣ፤ ከቀሩት ልጆቿም ጋር ሊዋጋ ሄደ፤ እነርሱ የእግዚአብሔርን ትእዛዞች የሚጠብቁና የኢየሱስን ምስክር አጥብቀው የያዙ ናቸው።” (ራእ. 12፡7)። በተጨማሪም አዲስ ሰማይ እና አዲስ ምድር ወደሚፈጠርበት መንገድ የሚያገባው፣ የእግዚአብሔር ፍቅር በሲኦል አለቆች እና ሥልጣናት ላይ የሚቀዳጀውን አሸናፊነት የሚያካትቱትን የታላቁን ተጋድሎ የመጨረሻ ዘመን ክስተቶች እጠናለን።

የዚህ የሩብ ዓመት የሰንበት ትምህርት መሠረት መጽሐፍ ቅዱስ ቢሆንም፣ ይህን አስደናቂ ርዕስ ለማጥናት በኤለን ጂ. ኋይት የተዘጋጀውን ታላቁ ተጋድሎ የተሰኘ መጽሐፍ እንጠቀማለን። እያንዳንዱ ትምህርት የተመሠረተባቸው የመጽሐፉ ምዕራፎች ለ

ተጨማሪ ሀሳብ


እንደ አጋዥ ለመጠቀም እና ሙሉ ለሙሉ “ከመታወቅ በላይ የሆነውን የክርስቶስን ፍቅር” እናውቅ ዘንድ (ኤፌ. 3፡19) እንደሚረዳን ልብ ይሏል።

በዩናይትድ ስቴትስ ኮነቲከት የተወለዱት ማርክ ፊንሌይ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚታወቁ ወንጌላዊ ሲሆኑ፣ በጎርጎሮሳውያኑ ከ2005–2010 ዓ.ም. በጀነራል ኮንፈረንስ ምክትል ፕሬዚዳንት ሆነው አገልግለዋል። ጡረታ ከወጡ በኋላም የጀነራል ኮንፈረንስ ፕሬዝዳንት ረዳት ሆነዋል። ፓስተር ፊንሊ እና ባለቤታቸው ኧርነስቲን ሦስት ልጆች እና አምስት የልጅ ልጆች አሏቸው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA Union SSL