የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት ፡ መዝ 23፤ ዮሐ 10:11–15፤ መዝ 22፤ መዝ 89:27–32፤ ቆላ 1:16፤
መዝሙር 2፤ ዕብ 7፡20–28ን ያንብቡ።
የመታሰቢያ ጥቅስ፡- ግንበኞች የናቁት ድንጋይ እርሱ የማዕዘን ራስ
ሆነ። ይህች ከእግዚአብሔር ዘንድ ሆነች፤ ለዓይኖቻችንም ድንቅ ናት
(መዝ 118: 22፣ 23) ።
መዝሙረ ዳዊት ስለ ክርስቶስ ማንነት እና አገልግሎት ይመሰክራል። በደኅንነት
ዕቅድ ውስጥ ያለው የሥራው ገጽታ ከሞላ ጎደል በመዝሙራት ውስጥ
ይታያል። የክርስቶስ ሕይወት እና ሥራ በእነርሱ ውስጥ ብዙውን ጊዜ
በተለያዩ መንገዶች፣ በሚያስደንቅ ትክክለኛነት ተመስለው ተተንብየዋል።
በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ የተገለጡ ርዕሶች የክርስቶስን አምላክነት፣ ልጅነቱን፣
ታዛዥነቱን፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ያለውን ቅንዓት፣ የመልካም እረኛ ማንነቱን፣
መከዳቱን፣ መከራውን፣ አጥንቱ አለመሰበሩን፣ ሞቱን፣ ትንሣኤውን፣ ዕርገቱን፣ ክህነቱን፣
እና ንጉስ መሆኑን ያካትታሉ። በሥጋ ከመምጣቱ ከብዙ መቶ ዓመታት በፊት የተተነበየው
ሁሉም ነገር በዚህ መጽሐፍ ውስጥ አለ።
ለምሳሌ፣ ኢየሱስ ስለ አገልግሎቱ በኤማሁስ መንገድ ላይ ለደቀ መዛሙርቱ
መናገሩ ምንም አያስደንቅም (ሉቃስ 24፡44)። ስለ ማንነቱ በመዝሙራት ውስጥ ማስረጃ
እንዲያገኙ ፈልጎ ነበር። በክርስቶስ ምሳሌያዊ ፍጻሜ ካላቸው መዝሙራት መካከል
መዝ 24፣ 45፣ 72 እና 101 (በጣም መልካም ንጉሥና ዳኛ)፣ 88 እና 102 (የሚሰቃይ
የእግዚአብሔር አገልጋይ ጸሎቶች) ይገኙበታል።
በሁሉም መዝሙራት ውስጥ፣ በመዝሙረኛው ልቅሶ፣ ምስጋና፣ ውዳሴ፣ ለፍትህ
እና ለድነት መጮኽ፣ ለአለም መዳን የክርስቶስን ጸሎት ገደል ማሚቶ መስማት እንችላለን።
ለየካቲት 23 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት አጥኑ።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ መጽሐፈ መዝሙረ ዳዊት
መዝ 23፤ መዝ 28:9፤ መዝ 80:1፤ መዝ 78:52፣ 53፤ መዝ 79:13፤ እና መዝሙር
100:3ን ያንብቡ። በእነዚህ ጽሑፎች ውስጥ በጌታና በሕዝቡ መካከል ያለው ግንኙነት
እንዴት ተገልጿል?
የጌታ እንደ እረኛ እና የእግዚአብሔር ሕዝብ እንደ መሰማሪያ በጎቹ መመሰል
እግዚአብሔር መመሪያ ሰጭአቸው እና በዘላቂነት የሚንከባከባቸው እና ህዝቡም
ፍላጎቶቻቸው እንዲሟላላቸው በእግዚአብሔር ላይ ጥገኛ መሆናቸውን ያጎላል። ምስሉ
እረኞች ከመንጋዎቻቸው ጋር አብረው እየኖሩ እያንዳንዱን በግ በግል እንደሚንከባከቡ
ዓይነት በእግዚአብሔር እና በህዝቡ መካከል ያለውን መቀራረብ ያመላክታል። የእረኛው
ሥዕላዊ መግለጫዎች እግዚአብሔር ለመንጋው በሁለት ጠንካራ የተረጋገጡ ማሰሪያዎች
የፍጥረት (መዝ 95፡6፣ 7፣ መዝ
100፡3) እና የቃል ኪዳን (መዝ 28፡9፣ ዕብ 13፡20) ባለቤት
መሆኑን ያጎላል።
ዮሴፍን እንደ መንጋ የሚመራው የመለኮታዊው እረኛ ምስል (መዝ 80፡1)
ምናልባት ያዕቆብ ዮሴፍን የባረከበትን ቡራኬ፤ እግዚአብሔርን እንደ እስራኤል እረኛ
አድርጎ የሚመስለውን ይጠቅሳል፣ ስለዚህም ወደዚህ ታላቅ ተስፋና በረከት ያቀርባል
(ዘፍ 49፡ 24)።
ነገሥታት ለሕዝባቸው እንደ እረኞች ይቆጠሩ ነበር (2ሳሙ 5፡2)። ሆኖም፣
አብዛኞቹ ሰብዓዊ ነገሥታት ከእንዲህ ዓይነቱ ጥሪ ጋር ተስማምተው ስላልኖሩ ይህ ማዕረግ
የሚገባው እግዚአብሔር ብቻ ነው። ይህን ያደረገው ኢየሱስ ብቻ ነው፣ ለዚህም ነው
መልካም እረኛ የተባለው።
ዮሐ 10:11–15ን ያንብቡ። ኢየሱስ እንደ መልካም እረኛ ስለ ራሱ ምን አለ?
በመለኮታዊ እረኛ እና በመንጋው መካከል ያለው የጠበቀ ትስስር የሚገለጠው
መንጋው የእረኛውን ድምፅ በማያሻማ ሁኔታ ለይቶ በማወቁ ነው (ዮሐ 10፡4፣ 27)።
የመካከለኛው ምስራቅ እረኞች እስካሁን ድረስ በጎቹ የእረኛቸውን ድምጽ ስለሚያውቁ
እና ስለሚከተሉ በጎቻቸውን በመጥራት የተቀላቀሉ መንጎቻቸውን መለየት ይችላሉ።
አንዳንድ ጊዜ ሕዝቡ የእግዚአብሔር አለመርካት እና እነርሱን የመተው ምልክት
እንደሆነ አድርገው የሚገነዘቡአቸው የተለያዩ መከራዎች በእግዚአብሔር መንጋ ላይ
ይደርሳሉ። ሆኖም፣ መልካሙ እረኛ የባዘኑትን በጎቹን ፈጽሞ አይተዋቸውም፤ ነገር ግን
እነርሱን ሊያድናቸው ይፈልጋል። ይህ እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር ያለውን ግንኙነት
የሚያሳይ ኃይለኛ ምስል ነው። እርሱ ለበጎቹ ሊሞትና (ዮሐ 10፡11፣15) ለመረዳት
በሚያስቸግር ሁኔታ በእነርሱ ፋንታ ራሱ የመስዋዕት በግ ሊሆን (ዮሐ 1፡29) ፈቃደኛ
ነው። እንዲሁም፣ ኢየሱስ በሌሎች በረት ውስጥ ያሉትን በጎቹን እንደሚጠራቸው እና
አንድ መንጋ እንደሚያደርጋቸው አረጋግጧል (ዮሐ 10፡16)።
እንደ መልካም እረኛችን ኢየሱስ ለማድረግ ቃል የገባልንን ነገር በየቀኑ በተግባር
የሚጠቀሙባቸው መንገዶች የትኞቹ ናቸው?
መዝ 22ን እና መዝ 118:22ን ያንብቡ። መሲሁ ሊያድናቸው በመጣላቸው ሕዝብ የተስተናገደው እንዴት ነበር?
ብዙ መዝሙሮች የተሰቃየው መሲህ እጅግ የተተወበትን አሰቃቂ ስሜቶች ይገልጻሉ
(ለምሳሌ መዝ 42፣ መዝ 88፣ መዝ 102)። መዝሙር 22 ውስጥ ያሉት ብዙ ዝርዝሮች
ከንጉሥ ዳዊት ጋር በታሪክ ሊገናኙ ስለማይችሉ፣ ነገር ግን ከክርስቶስ ሞት ሁኔታዎች ጋር
ፍጹም በሆነ ሁኔታ ስለሚገጥሙ፣ በቀጥታ መሲሐዊ ትንቢት ናቸው። ኢየሱስ በመስቀል
ላይ ሆኖ በመዝሙር 22፡1 ውስጥ ያሉ ቃላትን ተጠቅሞ ጸለየ (ማቴ 27፡46)።
ክርስቶስ የኣለምን ኃጢአት በሙሉ በመሸከሙ የተፈጠረው ከአባቱ የመለየት
ሥቃይ ሊለካ የሚችለው በነበራቸው ቅርበት፣ ማለትም ወደር የለሽ በሆነው አንድነታቸው
መጠን ብቻ ነው (ዮሐ 1፡1፣ 2፤ ዮሐ 10፡30)። ሆኖም እየተጋፈጠ ያለው ሊገለጽ የማይችል
የስቃይ ጥልቀት እንኳን በአብ እና በወልድ መካከል ያለውን አንድነት ሊያፈርስ አልቻለም።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ መጽሐፈ መዝሙረ ዳዊት
ሙሉ በሙሉ በተተወበት ሁኔታ እየተጋፈጠ የነበረው ተስፋ የመቁረጥ ጥልቀት ትልቅ
ቢሆንም ያለ አንዳች ቅድመ ሁኔታ ራሱን ለአባቱ አሳልፎ ሰጠ።
“ምትካችንና ዋስትናችን በሆነው በክርስቶስ ላይ የሁላችን በደል ተኖረ። ከሕግ ፍርድ
ይቤዠን ዘንድ እንደ ተላላፊ ተቈጠረ። የአዳም ዘር ሁሉ በደል ልቡን ይጫነው ነበር። አምላክ
በኃጢአት ላይ ያለው ቁጣ፣ በዓመፅ ምክንያት የተከሰተው የአምላክ ቅሬታ አስፈሪ መገለጫ
የልጁን ነፍስ በድንጋጤ ሞላው።”— Ellen G. White, The Desire of Ages, p 753።
የጠንካራ ኮርማዎች፣ የሚያገሱ አንበሶች እና ውሾች የሚያስፈራሩ ምስሎች፣
ምንም ጉዳት ከማያስከትልና ረዳተ ቢስ ከሆነው ትል ጋር የተወዳደረው ክርስቶስ
በመጨረሻዎቹ ሰዓታት ከተጋፈጠው ሁኔታ አንጻር፣ የሰዎችን ጭካኔ እና ጥላቻ አጉልተው
ያሳያሉ። በሚያስደንቅ ትክክለኛነት፣ መዝሙር 22 አብን በመጥራቱ ኢየሱስን በራሱ
ቃል ያፌዙበት ሕዝብ የሰጡትን መርዘኛ አስተያየቶች (መዝ 22:1፣ 8፤ ማቴ 27:43) እና
ወታደሮች የኢየሱስን ልብስ ሲከፋፈሉ የነበሩበትን ያሳያል (መዝ 18፣ ማቴ.27፡35)።
ህዝቡ ያኔ ሊያደቅቁት የፈለጉት “ትል” የቤተ መቅደሱ ዋና “የማዕዘን ድንጋይ” እንደሚሆን
እና መሰረቱን እንደሚያረጋግጥ አልተረዱም ነበር (መዝ 118፡22)።
ነገር ግን፣ ያ የተጠላው (ተቀባይነት ያጣው) መሲህ ከሙታን ከተነሳ በኋላ
ለእግዚአብሔር ህዝብ የድነት ምንጭ ሆነ (ማቴ 21፡42፣ ሐዋ 4፡10–12)። ክርስቶስ በሰው
ልጆች ስቃይ ደረሰበት፣ ነገር ግን እግዚአብሔር ልጁን የመንፈሳዊው ቤተ መቅደስ ሕያው
“የማዕዘን ራስ” በማድረግ አከበረው (ኤፌ 2፡20-22፣ 1 ጴጥ 2፡4-8)። የእግዚአብሔርን
የማዳን መንገድ ለሚክዱ፣ ይህ ድንጋይ የፍርድ ወኪል ይሆናል (ኢሳ 8፡14፣ ማቴ 21፡44)።
ኢየሱስ እርስዎ ለሰሩት እያንዳንዱ ኃጢአት በመስቀል ላይ ቅጣቱን በራሱ ከፈለ። እርሱ
በእናንተ ፈንታ መከራን መቀበሉ አሁን በምትኖሩበት ሕይወት ላይ ምን ተጽዕኖ ያሳድራል፣
ማለትም፣ ኃጢአት ለምን አስጸያፊ ሆኖ ይታያችኋል?
መዝ 89:27–32፤ 38–46 እና መዝ 132:10–12ን ያንብቡ። የዳዊት ኪዳን ስለ ምንድን ነው የሚናገረው? ይህን ኪዳን አደጋ ላይ የጣለው ምን ይመስሎታል?
የዳዊት ቃል ኪዳን የዳዊትን ዘር ዘላለማዊ ድጋፍ እና የእግዚአብሔር ህዝብ
ብልጽግናን ለማግኘት የእግዚአብሔርን የተስፋ ቃል ይዟል (1ሳሙ 7፡5–16፤ መዝ 89፡
1–4፣ 19–37፤ መዝ 132፡12–18)። የቃል ኪዳኑ ዘላቂነት በእግዚአብሔር የከበረ መሐላ እና
ንጉሡ ለእግዚአብሔር ታማኝ በመሆን ላይ የተመሰረተ ነው። ይሁን እንጂ እንደ ንጉሥ
ዳዊት ያሉ ለአምላክ ያደሩ ነገሥታት እንኳ ሁል ጊዜ ለጌታ ታማኝ አልነበሩም። መዝሙር
89 በዳዊት ቃል ኪዳን የተነገሩት የከበሩ ተስፋዎች መጥፋታቸውን በሚያመለክት ጨካኝ
በሆነው እውነታ ላይ በምሬት ይናገራል። እስራኤል በእግዚአብሔር ያለ ተስፋ ተተወ?
በእርግጥ መልሱ - አይደለም ነው!
የእግዚአብሔር ቁጣ የመለኮታዊ ፍርድ መግለጫ ስለሆነ እርግጥ ነው (መዝ 38፡
1፣ መዝ 74፡1)። ሆኖም ንስሐ ሲገቡ የእግዚአብሔር ዘላለማዊ ፍቅር የሰዎችን ኃጢአት
ይቅር ስለሚል ለዘላለም ቁጣው አይቆይም። ሆኖም፣ የእግዚአብሔር ፍቅር ዘለቄታ
ያለው ቢሆንም በተሳሳተ ህዝቡ ደስተኛ አለመሆኑ አሳሳቢ ነው። ሰዎቹ አለመታዘዛቸው
የሚያስከትለውን መራራ መዘዝ ይሰማቸውና የኃጢአታቸውን አስከፊነት ይገነዘባሉ
(መዝ 89፡38–46)። ነገር ግን የእግዚአብሔር ቁጣ የሚያልፈው “እስከ መቼ?” ነው
ብለው ይጠይቃሉ (መዝ 89፡46) ። እንደገና አዲስ ተስፋ የሚመጣው እግዚአብሔር
ፀጋውን “ለማስታወስ” ከሚሰጠው በእርሱ ታማኝነት ውስጥ ካለው አዲስ ማረጋገጫ ነው
(መዝ 89፡47፣ 50)።
ባጭሩ ለመግለጽ፣ በሰብአዊያን በኩል ለቃል ኪዳኑ ታማኝ መሆን ባይሳካም
ሕዝቡ የእስራኤልንና የመላው ዓለምን ጽድቅና መዳን ባካተተ በመሲሑ በኩል ባለው
የማይለወጥ የእግዚአብሔር ተስፋ ላይ ማረፍ ይችላል። ማለትም፣ በመጨረሻ፣
እግዚአብሔር ያሸንፋል፣ ዘላለማዊ መንግስቱ ለዘላለም ይመሰረታል— ያም የሚሆነው
በኢየሱስ ብቻ ነው እንጂ በእግዚአብሔር ህዝብ ታማኝ መሆን አይደለም።
ኢየሱስ ክርስቶስ የዳዊት ልጅና መሲሑ ነው (ማቴ 1፡1፣ ዕብ 1፡8)። እርሱ “የፍጥረት
ሁሉ በኵር” ተብሎ ተጠርቷል (ቆላ 1፡15)። መዝ 89፡27ን በመጥቀስ ዳዊት የክርስቶስ
ምሳሌ፣ የእግዚአብሔር በኩር ነው። “በኵር ልጄ አደርገዋለሁ፣ የምድር ነገሥታትም
ልዑል”። በግልጽ ለማየት እንደሚቻለው ዳዊት የወላጆቹ ስምንተኛ ልጅ ስለ ነበር (1 ሳሙ
16: 10፣ 11) “በኩር” የሚለው መጠሪያ የዳዊትን ባዮሎጂያዊ ብኩርና አይገልጽም። ይህ
ስለ ኢየሱስም ተመሳሳይ ነው። ይህ መጠሪያ ልዩ ክብርና ሥልጣኑን ያመለክታል (ቆላ 1፡
16፣ 20-22)። እግዚአብሔር ኢየሱስን ከሙታን ባስነሳው ጊዜ የአለም ሁሉ የበላይ ንጉሥ
አደረገው (ሐዋ 2፡30፣31)።
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ መጽሐፈ መዝሙረ ዳዊት
ቆላስይስ 1:16 20–22ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ኢየሱስ ማንነት እና ስላደረገልን
ነገር ምን ያስተምሩናል? ከዚህ ለራስህዎ ምን ተስፋ ሊወስዱ ይችላሉ?
መዝ 2ን መዝ 110:1-3፤ መዝ 89:4፣ 13–17፤ እና መዝ 110:1፣ 2፣ 5፣ 6 ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ክርስቶስ ንጉሥ ስለመሆኑ ምን ያስተምሩናል?
እግዚአብሔር እንደ የመሲሑ አባት መገለጡ ንጉሡ ከእግዚአብሔር ጋር ቃል
ኪዳን ሲገባ የንጉሱን ዘውድ መጫንን ያመለክታል (መዝ 2፡7፣ መዝ 89፡26–28)።
መዝሙር 2፡7 የክርስቶስን ትንሳኤ እና ከፍ ከፍ ማለቱን እንደ አዲስ ዘላለማዊ ቃል ኪዳን
መባቻ እና የክርስቶስ ንጉሣዊ ካህንነት (ሐዋ 13፡33–39፣ ዕብ 1፡5፣ ዕብ 5፡5) አድርጎ
አመላክቷል። መሲሑ ከዚህ በፊት ታይቶ የማይታወቅ ክብርና ሥልጣን ያለው ሰው ሆኖ
በእግዚአብሔር ቀኝ ተቀምጧል (መዝ 110:1፤ የሐዋ 7:55፣ 56)። “በተጨማሪም፣ በጌታ
እና ‘በተቀባው’ (መሲህ) መካከል ያለው መስተጋብር ይህን የዳዊት መሲሕ ከጌታ ከራሱ
ጋር ልዩነት እንዳለው ይጠቁማል። . . . በቀኝ የተቀመጠ ጌታ ከሆነ ጌታ መሲህ ነው፣
የኋለኛው ደግሞ በቀኙ በኩል ይታያል [መዝ 110:1፣ 5።]”—Jacques Doukhan, On the
Way to Emmaus Clarksville, MD: Lederer Books, 2012), pp. 26, 27።
በመጨረሻ፣ ክርስቶስ በጠላቶቹ ላይ ፍጹም ድል ይቀዳጃል። ጠላቶችን
“የእግር መረገጫ” ለማድረግ የጥንቶቹ ቅርብ ምስራቃዊ ነገስታት እግራቸውን በተሸነፉ
ጠላቶቻቸው አንገት ላይ በማሳረፍ በእነርሱ ላይ ሙሉ የበላይነትን ለማሳየት የነበራቸውን
ልማድ የሚያሳይ ምስል ነው። ሆኖም፣ እዚህ ያለው የክርስቶስ በትር የሽብር መሳሪያ
አይደለም (መዝ. 2፡9፣ መዝ 110፡2)።
በትሩ (“በትር”) በመጀመሪያ ለጎሳ መሪዎች እንደ ነገድ ምልክት ነበር (ዘኁ 17፡
2-10)። የክርስቶስ በትር የመጣችው ከጽዮን ነው፤ ምክንያቱም እርሱ የጽዮንን ሰዎች
ስለሚወክል ነው። የእርሱ በትር የመለኮታዊ ፍርድ ምልክት ነው፣ እርሱም የክፋት
አገዛዝን ያበቃል፤ የክርስቶስን ተወዳዳሪ የሌለውን አገዛዝ ያሳያል (ራዕ 2: 27፤ ራዕ 12:
5)። ክፉዎቹ ነገሥታት እንኳን ንስሐ እንዲገቡና ለመሲሑ እንዲገዙ ዕድል ተሰጥቷቸዋል
(መዝ 2፡10-12)።
የክርስቶስን የመጨረሻ ድል የሚያሳይ አንድ ሥዕላዊ መግለጫ በዳንኤል ምዕራፍ
7 ላይ በተገለጸው በቅድመ ምጽዓቱ ትዕይንት ተገልጾአል፣ ይህም የሚያሳየው “ ‘ለልዑል
ቅዱሳን ” ፍርድ ከተሰጠ በኋላ መንግሥቱ ይጸናል “‘መንግሥቱ የዘላለም መንግሥት
ነው’” (ዳን. 7፡27)። በመስቀሉ ምክንያት የመንግሥቱ ተስፋ ተረጋግጦአል።
በንጉሱ ለሚታመኑ ሁሉ በረከት እንደሚሰጣቸው ቃል ተገብቶላቸዋል፣ ህዝቡ
በመሲሑ ሉዓላዊ እና ጻድቅ ግዛት ደስ ይላቸዋል (መዝ 2:12፣ መዝ 89:15–17)።
አዎን፣ በመጨረሻ፣ መልካም ክፉን እንደሚያሸንፍ፣ ፍትህ እንደሚደረግ፣ ህመም እና
ስቃይ ለዘላለም እንደሚወገዱ ማወቅ እንዴት ደስ ይላል። በሰው እይታ ክፋት ድል ያደረገ
በሚመስልበት ጊዜ ይህ እውነት እንዴት ሊያጽናናን ይገባል?
መዝ 110፡4–7 ያንብቡ። የክርስቶስ ክህነት ልዩ የሆነው እንዴት ነው? በክርስቶስ ሰማያዊ ክህነት ውስጥ ምን ታላቅ ተስፋ እናገኛለን?
እግዚአብሔር ለመሲሑ የዘላለም ንግሥና (መዝ 110፡1–3)፣ የላቀ ማዕረግ የሆነውን
የክህነት ስልጣንና የመልከ ጼዴቅ ሥርዓትን ሰጠው (መዝ 110፡4–7)። ጌታ ቃሉን በታላቅ
ቃል ኪዳን አትሞታል (ዕብ 6፡18)። እግዚአብሔር ፍጹም የሆነ ካህን ከመስጠት ወደ ኋላ
እንደማይል የገባው መሐላ የጸጋው ምልክት ነው። የሰዎች ኃጢአትና ግልጽ ዓመፀኛነት ዘወትር
እግዚአብሔር ሕዝቡን እንዲጥል ያነሳሳዋል፣ ነገር ግን የእግዚአብሔር መሐላ የማይለወጥ እና
ንስሐ በሚገቡ ሰዎች ላይ የተረጋገጠ እንደሆነ ያሳያል (ዘፀ 32፡14፣ መዝ 106፡45)።
መለኮታዊው መሐላ መሲሑ ንጉሥም ካህንም መሆኑን በማወጅ ለዳዊት ቃል
ኪዳን እንግዳ ነገር ያስተዋውቃል (መዝ 110፡4)። የእስራኤል ነገሥታት እንደ ሌዋውያን
ካህናት ሆነው ሊሠሩ አይችሉም (ዘኍ 8፡19፣ 2ዜና 26፡16-21)። ቅዱሳት መጻሕፍት
ነገሥታትን ወይም መስዋዕቶችን የሚያቀርቡ ሰዎችን ሲጠቅስ ለካህናቱ መስዋዕት ማቅረብ
እንዳለባቸው ያሳያል። መዝሙር 110 መሲሑን ከሌሎቹ የእስራኤል ነገሥታትና ካህናት
የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት መምሪያ መጽሐፈ መዝሙረ ዳዊት
የተለየ ያደርገዋል። የክርስቶስ ዘላለማዊ ክህነት ከመልከ ጼዴቅ የተገኘ ነው፣ እሱም
የሳሌም ንጉስ (ኢየሩሳሌም) እና “የልዑል እግዚአብሔር” ካህን ነው (ዘፍ 14፡18-20)።
ብሉይ ኪዳን ከመዝሙር 110 በቀር ስለ ንጉሥ ዳዊትም ሆነ ስለ ሌላ የእስራኤል ነገስታት
እንደ መልከ ጼዴቅ ሥርዓት የክህነት ስልጣን እንዳላቸው አይናገርም። ይህ መዝሙር ግን
በግልጽ በእስራኤል ታሪክ ካህን የሆነ ንጉስ እንዳለ ይናገራል።
ዕብራውያን 7፡20–28 ያንብቡ። የክርስቶስ የላቀ ክህነት አንዳንድ እንድምታዎች ምንድን
ናቸው?
ክርስቶስ መለኮታዊ ንጉሥና ዘላለማዊ ካህን እንደመሆኑ መጠን በሰው ካህናትና
ነገሥታት ላይ ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የበላይ ነው። ስለዚህ ተስፋ እናደርጋለን።
ክርስቶስ በሰው ቃል ኪዳን ሳይሆን በእግዚአብሔር መሐላ ላይ የተመሰረተ የላቀ ቃል
ኪዳንን ይዞአል። በሰማያዊው መቅደስ ውስጥ ያገለግላል። ልክ እንደ ሰብአዊ ካህናት
የእርሱን ክህነት ኃጢአት ወይም ሞት አይነካም፤ ስለዚህ ለህዝቡ ለዘለአለም ሊያማልድ
እና ሊያድን ይችላል። ፍጹም እና ሩህሩህ ካህን የሆነው የክርስቶስ የማስታረቅ ስራ ለህዝቡ
በእግዚአብሔር ፊት የመኖር ዘላቂ ማረጋገጫ ይሰጣል (ዕብ 6፡19፣ 20)። የክርስቶስ
ንጉሣዊ ካህንነት በሰዎች ልብ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ውስጥም የክፋት አገዛዝን
ያስወግዳል። በመዝሙር 2 ላይ የገባውን ቃል ይጠብቃል፣ ሕዝቦችና እና ገዥዎች ሁሉ
ለክርስቶስ ኢየሱስ ንጉሣዊ ፍርድ ይገዛሉ (መዝ 2:6-9፤ መዝ 110:1፣ 2፣ 5፣ 6)። አስደናቂው
የኢየሱስ ንጉሣዊ ካህንነት ታዛዥነታችንን እና መታመናችንን ሙሉ በሙሉ ያረጋግጣሉ።
Ellen G. White, “God With Us,” pp. 19–26, in The Desire
of Ages. ያንብቡ።
መዝሙራት ስለ ክርስቶስ የተደረጉ ጸሎቶች እና የክርስቶስ ጸሎቶች በመሆናቸው፣
ማንነቱ እና የመዋጀት አገልግሎቱ “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ለሆነው ልዩ መገለጥ ይሰጣሉ
(ማቴ 1፡23)። ኢየሱስ በትግል እና በመከራ ጸሎቶች “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው።
ለፍትህ እና ለነጻነት ጩኸት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” ነው። ኢየሱስ ለጥፋትና ለተስፋ
መቁረጥ ሳይጥለን የእምነትን መንገድ በአሸናፊነት “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር” አሳይቶናል።
እኛን ከዘላለም የኃጢአት ፍርድ ያድነን ዘንድ የዘላለም ካህን እና ንጉሥ ሆነልን። ፍጹም
በሆነው የዳዊት ዘር በክርስቶስ፣ ሁሉም የእግዚአብሔር የመዳን ተስፋዎች ፍጻሜያቸውን
አግኝተዋል (2ቆሮ 1፡20)።
ኤለን ጂ ዋይት የክርስቶስን ከሰው ልጅ ጋር ያለውን አንድነት በማስተዋል እንዲህ
በማለት ገልጻለች፡- “ሥጋን በመልበሱ ክርስቶስ ሰብአዊነትን ተላበሰ፤ በአምላክነቱ
የእግዚአብሔርን ዙፋን ጨበጠ። እንደ ሰው ልጅ የመታዘዝ ምሳሌ ሆነ፤ እንደ
እግዚአብሔር ልጅ ለመታዘዝ ኃይልን ሰጠን። በኮሬብ ተራራ ከቍጥቋጦው ውስጥ ሆኖ
ሙሴን “እኔ እኔ ነኝ” ያለው ክርስቶስ ነው። ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፡- እኔ
ወደ እናንተ ላከኝ።’ ዘጸ 3፡14። ይህ ለእስራኤል የነጻነት ቃል ኪዳን ነበር። ስለዚህ ‘በሰው
ምሳሌ’ በመጣ ጊዜ፣ እኔ ነኝ ብሎ ራሱን አወጀ። የቤተልሔሙ ልጅ፣ ትሑት አዳኝ፣ ‘በሥጋ
የተገለጠው እግዚአብሔር ነው።’ 1 ጢሞ 3፡16። ለእኛ ደግሞ፡- መልካሙ እረኛ እኔ
ነኝ፡ ‘ሕያው እንጀራ እኔ ነኝ፡ መንገድም እውነትም ሕይወትም ነኝ ይላል። ስልጣን ሁሉ
በሰማይና በምድር ተሰጠኝ። ዮሐ 10:11፤ 6:51፤ 14:6፤ ማቴ 28፡18። እኔ የሁሉም ተስፋዎች
ማረጋገጫ ነኝ። አትፍሩ እኔ ነኝ ።”— The Desire of Ages, pp. 24, 25።
1. ሰዎች ታማኝ ባይሆኑም እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ የማይናወጥ ታማኝነቱን ያሳየው
ሰዎች ታማኝ ባይሆኑም እግዚአብሔር ለቃል ኪዳኑ የማይናወጥ ታማኝነቱን ያሳየው
እንዴት ነው? ይህ በዛሬው ጊዜ ለሚታገሉት የአምላክ ልጆች ምን ማረጋገጫ ይሰጣል?
2. በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት መሠረት ያለው የክርስቶስ ልዩ እና የላቀ ክህነት
በመልከ ጼዴቅ ሥርዓት መሠረት ያለው የክርስቶስ ልዩ እና የላቀ ክህነት
የእግዚአብሔርን ሕዝብ የመዳን እርግጠኝነት የሚያጠናክረው እንዴት ነው?
3. ወንጌሎች እንደሚያሳዩት በመዝሙራት ውስጥ የሚገኙት ብዙ መሲሐዊ ተስፋዎች
ወንጌሎች እንደሚያሳዩት በመዝሙራት ውስጥ የሚገኙት ብዙ መሲሐዊ ተስፋዎች
በኢየሱስ ክርስቶስ ፍጻሜያቸውን አግኝተዋል። ይህስ የአምላክን ቃል ትክክለኛነት
የሚያሳየው እንዴት ነው? በአምላክ ቃል ላይ ያለንን እምነት የሚያዳክም ማንኛውንም
ዓይነት ስሜት መቃወም ያለብን ለምንድን ነው?
4. “ስልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” (ማቴ 28፡18) ከሚለው የክርስቶስ
“ስልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ” (ማቴ 28፡18) ከሚለው የክርስቶስ
ቃል ምን ታላቅ መጽናኛ ማግኘት እንችላለን? ይህን የተስፋ ቃል ከራሳችን ልምድ ጋር
እንዴት እንተገብረዋለን?