የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ኤፌ. 5:1-20፤ 1ኛ
ቆሮ. 5:1-11፤ ራዕይ 16:1-16፤ ቆላ. 4:5፤ ምሳሌ 20:1፤ ምሳሌ
23:29-35፤ የሐዋ. 16:25።
የመታሰቢያ ጥቅስ:- “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች እንጂ ጥበብ እንደሌላ ቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ፤ ቀኖቹ ክፉዎች ናቸውና ዘመኑን ዋጁ። ስለዚህ የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ።” (ኤፌሶን 5:15–17)።
ከጥቂት ዓመታት በፊት በዩናይትድ ኪንግዶም ውስጥ የብርሌ ጆግ ለጨረታ
ቀርቦ ነበር። ተጫራቾቹ የ19ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የፈረንሳይ ክላሬት
ጆግ በማለት የገለጹት ሲሆን ዋጋው 200 ዶላር ይሆናል ብለው ገመቱ።
የሰዎችን አመለካከት የመረዳት አቅም ያላቸው ሁለት ተጫራቾች ጆጉን እጅግ
ብርቅዬ፣ እስላማዊ ገምቦ እንደሆነ ተገነዘቡ። በትክክል የተገመተበት ዋጋ 5
ሚሊዮን ፓውንድ ሲሆን (6.5 ሚሊዮን የአሜሪካ ዶላር) ነበር። ያ ተጫራጭ
በዚህ ያህል እንዲጫረት ያደረገው ነገር ምን ነበር? አጫራቹ ያላወቀው ግን
ተጫራቹ ያወቀው የሆነ ነገር ነበር። እርሱም የጆጉ እውነተኛ ዋጋ ነበር።
በኤፌሶን 5:1-20 ላይ ጳውሎስ አህዛቦችና አማኞች ዋጋ የሚሰጡአቸውን
ነገሮች ልዩነት ያወዳድራል። አህዛቦች እንደ ታላላቅ የሕይወት ሀብቶች ዋጋ የሚሰጡት
ለአስደሳች ታሪክ (ኤፌ.5፡4)፣ ለስካር ፓርቲ (ኤፌ. 5፡18)፣ እና ርኩስ ለሆነ
የግብረ ሥጋ ግንኙነት (ኤፌ. 5፡3፣ 5) ነው። ነገር ግን አማኞች የሁሉም ነገር
እውነተኛ ዋጋ ግልጽ የሚሆንበትና በመጨረሻ የዋጋ ግምት የሚሰጥበት ቀን እየመጣ
መሆኑን ያውቃሉ (ኤፌ. 5፡5፣6)። የጨረታ ዋጋቸውን በግብዣና በስካር ላይ
ከማስቀመጥ ይልቅ ከብዙ ነገሮች መካከል በክርስቶስ ላለው “መልካም፣ ትክክልና
እውነት ለሆነ ነገር ሁሉ” ዋጋ ይሰጣሉ (ኤፌ 5:9)። ስለዚህ እኛ እንደምናደርገው
ሁሉ እነርሱም በዘላለም ጫፍ ላይ እየኖሩ ስለሆኑ በክርስቶስ ያለውን የዋጋ ስምምነት
እንዲቀበሉ ጳውሎስ ይገፋፋቸዋል (ኤፌ. 5፡15-17)።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለነሃሴ 20 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
ጳውሎስ አማኞች “እግዚአብሔርን እንዲመስሉ” የሚፈልገው በምን መልክ ነው? ኤፌሶን 5:1፣ 2ን ይመልከቱ።
ጳውሎስ በኤፌሶን ያሉ አማኞች በፍቅር እንዲመላለሱ ያደፋፈራቸው ሲሆን
ይህም ለዚህ ክፍል ጠቃሚ የሆነ ጥሪ ነው (ኤፌ.5፡8፣ 15ን ይመልከቱ)። ይህ
“በፍቅር መመላለስ” (ኤፌ. 5:2ን ይመልከቱ) ክርስቶስ በስርየት መስዋዕቱ
ለእኛ ባሳየው የፍቅር ምሳሌ መሆን አለበት (ከኤፌ. 4፡32 ጋር ያነጻጽሩ)። ስለዚህ
መስዋዕት አራት ነገሮችን ያረጋግጣል፡- 1. ይህ ፍቅር የተነሳሳው በእግዚአብሔር
አብ ፍቅር (ኤፌ. 5፡1) እና በራሱ በክርስቶስ ፍቅር ነው (ኤፌ. 5፡2)። 2.
ክርስቶስ በእኛ ፋንታ ስለሞተ የምትክ መስዋዕት ነው። ክርስቶስ በሂደቱ ውስጥ
ተካፋይ ያልሆነ መስዋዕት ሳይሆን ራሱን ለእኛ አሳልፎ የሰጠ መስዋዕት ነው። 3.
በብሉይ ኪዳን የቤተ መቅደስ አገልግሎት ምሳሌ የክርስቶስ ሞት ለእግዚአብሔር
የተደረገ መስዋዕትም ነው። 4. መስዋዕቱ “መልካም መዓዛ ያለው ስጦታ
ስለሆነ” በእግዚአብሔር ዘንድ ተቀባይነት አግኝቷል ((ኤፌ. 5:2ን ዘጸ.
29:18፣ ዘሌ. 2:9 ፊልጽ. 4:18 ጋር ያነጻጽሩ)።
ከዚያ በኋላ ኤፌሶን 5:3-5 የወሲብ ሥነ-ምግባርን በተመለከተ
ያለውን ጭንቀት የሚገልጸውን ክፍል ያስተዋውቃል። በኤፌሶን ያሉ አዲስ ምልስ
ክርስቲያኖች የክርስትና ጥሪያቸውን በመገልበጥ የክርስትና ምስክርነታቸውን
ወደሚቃወም ወደ ወሲብ ባህርይ የመመለስ አደጋ ነበረባቸው (ከ1ኛ ቆሮንቶስ
5፡1-11፤ 6፡12-20፤ 2ኛ ቆሮ. 12፡21)።
በሌላ በኩል በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን የነበረው የግሪክና የሮም
ዓለም በአዲስ ኪዳን ውስጥ በሌላ ቦታ የተገለጸውን የግብረ ገብ ብልሽትና ሴሰኝነት
ይፈጽም ነበር (1 ቆሮ. 6:9 ገላ. 5:19፣ ኤፌ. 4:17-19፣ ቆላ. 3:5ን
ይመልከቱ)። ለምሳሌ፣ የሀብታሞች ግብዣዎች ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡3-14
የገለጻቸውን ባህርያት በቋሚነት ያሳዩ ነበር። እነርሱም ስካር፣ የስንፍና ንግግር፣ ተገቢ
ባልሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት መዝናናት እና ኢ-ግብረገባዊ ተግባራት ናቸው። ከዚህ
በተጨማሪ የከተማ ማዕከሎች ግብረ ገብነት የጎደላቸውን የወሲብ ልምምዶችን
ለሚያሳድጉ ሳይታወቁ ለመኖርና ለወሲብ ፈቃደኛ ለመሆን ምቹ ሁኔታ ፈጠሩ። በሌላ
በኩል በዚያ ማህበረሰብ ውስጥ የነበሩ ብዙዎች ንጹህ ሕይወትን የኖሩ ሲሆን ጥብቅ
ለሆነ ግብረ ገባዊነት ጥብቅና ቁመዋል። አዲስ ኪዳን የመጥፎና የመልካም ባህርያትን
ዝርዝር እና የቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ደንቦችን ሲሰጥ ደራሲዎች እያንጸባረቁ
የነበሩት ሰፊ በነበረው የግሪክና የሮም ዓለም የነበሩ ዋና ሀሳቦችን ነበር (ለምሳሌ፣
ኤፌ. 5:21-6:9፤ ቆላ 3:18-4:1)። በተመሳሳይ ጊዜ ሴሰኛና ንጹህ
የሆነው ይህ ዓለም ጳውሎስ በአህዛብ ይተገበር የነበረውን ኢ-ግብረገባዊ ባህርይ
ስለማስወገድና አማኞች በውጭ ባሉት ዘንድ ጥሩ ስም ለማትረፍ እንዲጠነቀቁ
በመመኘት የሚሰጣቸውን ማሳሰቢያዎች ለማብራራት ይረዳል።
የወሲብ ባህርይን በተመለከተ ጳውሎስ የተናገራቸው ቃላት
እርስዎ የትም ቢኖሩ፣ ለእርስዎ ባህል ገጣሚ የሚሆኑት በምን
መንገዶች ነው?
ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፡-“ማንም በከንቱ ንግግር አያታልላችሁ፤ ከዚህ
የተነሣ በማይታዘዙት ልጆች ላይ የእግዚአብሔር ቁጣ ይመጣልና”(ኤፌ. 5:6)።
የተለያዩ ዓይነት ኃጢአቶችን ያለ እፍረት የሚፈጽሙትንና የማይናዘዙ
ሰዎችን ጳውሎስ “አመንዝራ ወይም ርኩስ ወይም የሚመኝ” በማለት
ለይቶአቸዋል (ኤፌ. 5:5)። ግልጽ ዳሰሳ አድርጓል፡- በክርስቶስ የሆኑና
ወደ ፊት ሊመጣ ባለው መንግሥት ተሳታፊ ለመሆን የተጠሩ ለዚህ መንግስት
ያልተጠሩት የሚያደርጉትን ነገር ማድረግ የለባቸውም (ኤፌ. 5፡5)። አሁን
“ባዶ ቃላት” ስለሚኖራቸው ተጽእኖ ይጨነቃል። አማኞች ግልጽ ከሚነገረው ቋንቋ
የተነሣ የምንዝር ኃጢአት አስነዋሪ እንዳልሆነ ወደማሰብ እንዳይታለሉ ወይም
ራሳቸው ወደዚህ ኃጢአት እንዳይሳቡ በመስጋት ይጨነቃል (ኤፌ. 5፡6)።
በዚህ ሁኔታ መታለል እግዚአብሔር በመጨረሻ ዘመን የሚያመጣውን ፍርድ፣
“በማይታዘዙ ልጆች ላይ የሚመጣውን የእግዚአብሔርን ቁጣ” እንዲቀበሉ
ሊያደርግ እንደሚችል በመንገር ያስጠነቅቃል(ኤፌ. 5:6)።
“የእግዚአብሔር ቁጣ” የሚለው ሀረግ ተግዳሮት ያለበት ነው። ቁጣው
የእግዚአብሔር ቁጣ መሆኑ ከተለመደውና ስሜታዊ ከሆነው ከሰብአዊ ቁጣ ጋር
ተነጻጽሮአል (ኤፌ 4፡31 ጋር አነጻጽሩ)። የእግዚአብሔር ቁጣ ዝም ብሎ ተራ
ለሆነ ስህተት የእብደት ወይም እሳተ ጎሞራዊ ምላሽ ሳይሆን ለብዙ ጊዜ የሚታገስና
ጻድቅ የሆነው እግዚአብሔር ክፉ ለማድረግ በትዕቢት ራሳቸውን ለሰጡት የሰጠ
ፍትሃዊ ምላሽ ነው።
በተጨማሪ፣ ብዙ ጊዜ መለኮታዊ ቁጣ የተጠቀሰው ስለሚመጣው
የእግዚአብሔር ፍርድ በመንፈስ ምሪት በተጻፉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ማስጠንቀቂያዎች
አውድ ነው። (ለምሳሌ ራዕይ 6:12-17፣ ራዕይ 16:1-16፣ ራዕይ
19:11-16ን ይመልከቱ)። ሰብአዊ ፍጡራን “በተፈጥሮአቸው የቁጣ ልጆች
ስለሆኑ” እግዚአብሔር የጸጋ ተግባር ስለሆነውና ስለሚመጣው የራሱ ፍርድ እና
ፍርዱ ስለሚመለከታቸው ሰዎች ያስጠነቅቃል (ኤፌ. 2:3)።
አማኖች ከኃጢአተኞች ጋር “ተባባሪዎች” ወይም “ተካፋዮች”
እንዳይሆኑ ጳውሎስ የሚያሳስበው ለምንድር ነው? (ኤፌ. 5:7-10)።
ጳውሎስ “እንደ ብርሃን ልጆች ተመላለሱ” በማለት ያሳስባል (ኤፌ.
5:8)። ከዚያም እንዲህ በማለት ተጨማሪ ትዕዛዝ ይሰጣል:- “እግዚአብሔርን
የሚያስደስት ምን እንደሆነ ለይታችሁ ለማወቅ ሞክሩ” (ኤፌ. 5:10)።
አህዛብ ደስታን የሚሹት “በፍትወትና በእርኩሰት ሁሉ ወይም በመመኘት”
ነው (ኤፌ. 5:3)። የአማኙ ግብ በሚያስገርም ሁኔታ የተለየ ሲሆን ይህም
ራሱን ሳይሆን እግዚአብሔርን ማስደሰት ነው (“ደስ የሚያሰኘውን” ወይም
“ተቀባይነት ያለውን”ተብሎ የተተረጎመውን ኢውሬስቶስ የተባለውን ተመሳሳይ
የግሪክ ቃል ከሮሜ 12:1፣ 2 ቆሮ. 5:9፣ ዕብ. 13:21 ጋር አወዳድሩ)።
አማኙ የክርስቶስን ራሱን መስዋዕት ማድረግ ለማንጸባረቅ ይሻል (“ክርስቶስ
እንደወደደንና ራሱን ለእኛ አሳልፎ እንደሰጠ በፍቅር ተመላለሱ” ኤፌ. 5:2)።
በእኛ ጊዜና ዘመን መጠንቀቅ ያለብን አንዳንድ “ባዶ ቃላት”
ምንድር ናቸው?
ኤፌሶን 5:11-14ን ያንብቡ። ጳውሎስ በዚህ ቦታ እየሰጠ ያለው ኃይለኛ ማስጠንቀቂያ ምንድር ነው? ይህ እኛ ላለንበት ለአሁኑ ሁኔታ ሊገጥም የሚችለው እንዴት ነው?
ኤፌሶን 5:11-14ን ለመረዳት ጳውሎስ ሁለት ማሳሰቢያዎችን
እያቀያየረ ደጋግሞ እንደሚሰጥ መረዳት ጠቃሚ ነው፡- (1) እንደ “የብርሃን
ልጆች” እግዚአብሔርን የሚያስከብር የአኗኗር ዘይቤን ኑሩበት (ኤፌ. 5:8፤
ደግሞ ኤፌ. 5:1፣ 2፣ 4፣ 9-10፣ 11፣ 13፣ 14ን ይመልከቱ)፤ (2)
“ፍሬ የሌለውን የጨለማ ስራ” እየሰራችሁ እግዚአብሔርን የሚቃወም የአኗኗር
ዘይቤን፣ የዝሙትን ሕይወት አትኑሩ (ኤፌ. 5:11፤ ደግሞ ኤፌ. 5:3፣ 4፣
5-8 12ን ይመልከቱ)።
ኤፌሶን 5፡11ን ለመረዳት በኤፌሶን 5፡8-10 ላይ ያሉ ተመሳሳይ
ማሳሰቢያዎችን ልንቆፍር እንችላለን። አማኞች በማያምኑ ሰዎች ፊት እንደ “በጌታ
ብርሃን” እና “የብርሃን ልጆች” (ኤፌ. 5:8) መኖር አለባቸው። ይህን
የማድረግ ዋናው ምክንያት ለመታየትና “የብርሃኑ ፍሬ መልካም፣ ትክክልና እውነት
በሆነው ነገር ሁሉ ውስጥ ይገኛልና” የሚለውን ግልጽ ለማድረግ ነው (ኤፌ.
5:9)። ስለዚህ ጳውሎስ ጥብቅና እየቆመ ያለው የእግዚአብሔርን መልካምነት
ስለምናሳይበት ስልት (እስትራቴጂ) ነው። አማኞች ሁሉም ሰው እንዲያይ የጽድቅ
አማራጭን በማሳየት ፍሬ የሌለውን የጨለማ ሥራ ማጋለጥ አለባቸው።
በተመሳሳይ ሁኔታ አማኞች “የብርሃን ፍሬ” በማሳየት (ኤፌ. 5:9)
ዓለማውያንን ወደ ክርስቶስ እምነት ማምጣት እንዲችሉ ጳውሎስ በድፍረት
ያረጋገጠውን በቁጥር 13-14 ላይ በግጥም ቋንቋ ያቀረበውን ግድድሮሽ ልንቀበል
እንችላለን:- “ሁሉ ግን በብርሃን ሲገለጥ ይታያል፤ የሚታየው ሁሉ ብርሃን
ነውና።” (ኤፌ. 5:13፣ 14)።. ወራዳ አኗኗር በብርሃን ሲገለጥ ዓለማውያን
ለወደፊት ተስፋ የሌለውንና ለቁጣ የተዘጋጀውን የራሳቸውን ባህርይ ማየት ይችላሉ
(ኤፌ. 5:5፣ 6)፤ ከዚህ የተነሣ ከጨለማ ወደ ብርሃን መለወጥን ይለማመዳሉ
(“የሚታየው ሁሉ ብርሃን ነውና” )። ይህ ደግሞ ጳውሎስ የሚናገራቸው የኤፌሶን
አንባበቢያን እንደ አማኞች ራሳቸው የተለማመዱት ለውጥ ነው(ኤፌ. 5:8)።
ሰዎችን ከመንፈሳዊ እንቅልፍ ለማንቃትና የክርስቶስን የሚለውጥ መገኘት
እንዲለማመዱ ለማድረግ በኤፌሶን 5፡14 ላይ በመጨረሻ ዘመን ከሙታን ትንሣኤ
ጋር ግንኙነት ያለውን ቋንቋ ከሚጠቀመው ግጥም ወይም መዝሙር ምን ጠቃሚ
ነገር ልናገኝበት እንችላለን? (ከኤፌ. 2:1፣ 5 ጋር ያነጻጽሩ)። ጳውሎስ
በአእምሮው እያሰበ ያለ የሚመስለው ኢሳይያስ 60፡1-3 የሚያነጣጥረው
የእግዚአብሔር ሕዝብ በሆነው እሥራኤል ላይ እስከሆነ ድረስ በኤፌሶን 5፡14 ላይ
ያለውን መዝሙር/ግጥም ክርስቲያን አማኞችን ለሚስዮናዊነት ሚና፣ በጨለማው
ዓለም የክርስቶስን ብርሃን እንዲያንጸባርቁ እንደቀረበ ኃይለኛ ተማጽኖ አድርገን
ልንመለከት እንችላለን (ከፊልጵ. 2፡14-14፣ ማቴ. 5፡16 ጋር ያነጻጽሩ)።
እርስዎ የጨለማ ሥራን ማጋለጥ የሚችል የአኗኗር ዘይቤን
መኖር የሚችሉት እንዴት ነው?
ጳውሎስ ኤፌሶን 5፡1-20ን የሚያጠቃልለው በሁለት ቡድን ማሳሰቢያዎች
ሲሆን እነርሱም በኤፌሶን 5፡15-17 እና ኤፌሶን 5፡18-20 ላይ ይገኛሉ።
ይህን ክፍል የሚጨርሰው ቀጣይነት ባለው ሁኔታ የወሲብ ንጽህና ላይ ትኩረት
በማድረግ ነው። የመጀመሪያው ክፍል የሚጀምረው “እንግዲህ እንደ ጥበበኞች
እንጂ ጥበብ እንደሌላቸው ሳይሆን እንዴት እንድትመላለሱ በጥንቃቄ ተጠበቁ”
የሚለውን ማሳሰቢያ በመስጠት ነው (ኤፌ. 5:15)። ይህንኑ ደግሞ “ስለዚህ
የጌታ ፈቃድ ምን እንደሆነ አስተውሉ እንጂ ሞኞች አትሁኑ” (ኤፌ. 5:17)
በማለት እንደገና ገልጾታል። በሁለቱ መካከል “ዘመኑን ዋጁ” የሚል ጥሪ
ቀርቧል(ኤፌ. 5:16)።
በጸሎት የተሞላና ነገሮችን መለየት የሚችል ጥበበን የሚያንጸባርቅ
ሕይወት እንዲኖሩ ጳውሎስ የሰጣቸውን ማሳሰቢያዎች ልብ ይበሉ
(ኤፌ. 5:15-17)። እንደ ሞኞች ሳይሆን እንደ “ጠቢባን” መራመድ
በሚለው መካከል ያለው ልዩነት ምንድር ነው? “ዘመኑን ዋጁ”
ማለትስ ምን ማለት ነው?
ጳውሎስ በኤፌሶን መጽሐፍ ውስጥ በብሉይ ኪዳን ዘመን ጥቅም ላይ
ይውል የነበረውን “መሄድ” የሚለውን ዘይቤአዊ አነጋገር እንዴት መኖር
እንደሚገባን ለመግለጽ በተደጋጋሚ ተጠቅሟል (ኤፌ. 2:2፣ 10፤ ኤፌ.
4:1፣ 17፤ ኤፌ. 5:2 8)። በዚህ ቦታ ዘይቤአዊ አነጋገሩን የተጠቀመው
ታስቦበት የሚደረገውን ደቀ መዝሙርነት ለማደፋፈር ነው። ወጣ ገባና ጨለማ
በሰፈነበት መንገድ ስትመላለሱ “በጥንቃቄ መመላለስ” እንደሚገባችሁ ሁሉ
አማኞችም “እንዴት በጥንቃቄ መመላለስ እንዳለባቸው መመልከት” አለባቸው
(ኤፌ. 5:15)። ኤፌሶን 5፡15 ተመሳሳዩን በኤፌሶን 5፡ 17 ላይ ስለሚያገኝ
እንደ ጠቢብ ሕዝብ መኖር ማለት ምን ማለት እንደሆነ በዚህ ቦታ መመልከት
እንችላለን። ጥበብን ለማግኘት ወደ ውስጣችን አንመለከትም። ጠቢብ መሆን
ከራሳችን ባሻገር መድረስና “የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ መረዳት” ነው
(ኤፌ. 5:17)።
ጳውሎስ ታስቦበት የሚደረገውን ደቀ መዛሙርትን ማፍራትን ግልጽ በሆነ
ስዕል በማስቀመጥ ያደፋፍራል። “ጊዜን በአግባቡ መጠቀም” (ኤፌ. 5:16፤)
በሚለው ሀረግ ውስጥ ጳውሎስ ኤግዛጎራዞ የሚለውን ግስ ይጠቀማል(ከቆላ.
4:5 ጋር አነጻጽሩ)። ይህንን አባባል “ዘመኑን መዋጀት” ከሚለው ከኒው
ኪንግ ጄምስ እትም ጋር አወዳድሩ)። ቃሉ ከገበያ ቦታ የተወሰደ እንደመሆኑ
“መግዛት” ለሚለው ግስ አጽንዖት የሚሰጥ ቃል ስለሆነ የክርስቶስን መመለስ
እየጠበቅን ሳለ “የዋጋ ስምምነቱን ፈጥኖ መቀበል” የሚል ትርጉም አለው።
እዚህ ቦታ “ጊዜ” የተባለው ቃል በግሪክ ካይሮስ ከሚል ቃል የመጣ ሲሆን
ቅጽበትን ወይም መልካም አጋጣሚን ይገልጻል። “ጊዜ” እስከ መጨረሻው እስከ
ሙላት ድረስ ጥቅም ላይ የሚውል የተስፋ ዘመን ነው። “ቀኖቹ ክፉዎች ስለሆኑ”
ተግዳሮት ያለበት ጊዜም ነው(ኤፌ. 5:16፣ ኤፌ. 6:13፣ ገላ. 1:4 ጋር
አነጻጽሩ)። ለዚህ ምክንያቱ “ይህ ዓለም እየሄደበት ያለው መንገድ” “በአየር
ላይ በሚሰራው መስፍን ኃይል” ቁጥጥር ሥር ስለሆነ ነው(ኤፌ. 2:2)።
አማኞች የክርስቶስን መመለስ እየጠበቁ ሳሉ በአስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ
ይኖራሉ። ይህንን ጳውሎስ እንደ አደገኛ ግን ትርፍ ያለበት የገበያ ቦታ አድርጎ
ይስላል። ሲገበያዩ ትልቅ የዋጋ ቅናሽ እንዲደረግላቸው እንደሚከራከሩ ሰዎች በጊዜ
አጠቃቀማቸው በጣም ጥንቁቅ መሆን አለባቸው። ምንም እንኳን ድነትን መግዛት
ባንችልም ምሳሌነቱ ግን አሁንም ተገቢ ነው፤ በክርስቶስ የተሰጠንን ነገር ፈጥነን
መቀበል አለብን።
ጳውሎስ ኤፌሶን 5:18-20ን ሲጽፍ ለአምልኮ የተሰበሰቡ ክርስቲያኖችን በዓይን ህሊናው ያስባል። በዚያ አምልኮ ውስጥ ምን እያደረጉ እንደሆነ ነው ያሳየው?
ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡1-20 ላይ ባቀረበው የመጨረሻ መከራከሪያው
አማኞች አእምሮን የሚያደነዝዘውን ወይን ከመጠቀም እንዲታቀቡና በዚህ
ፋንታ በአንድነት የመንፈስን መገኘት ኃይል እንዲለማመዱ ያደፋፍራል። ጳውሎስ
(ምናልባት በብሉይ ኪዳን የግሪክ ትርጉም ላይ ከምሳሌ 23፡ 31 በመጥቀስ)
በጥበብ ሥነ-ጽሁፍ ውስጥ እንደተመለከተው አስካሪ መጠጥን መጠቀምን
የሚቃወሙ ሀሳቦችን በአእምሮው በመያዝ ሰካራምነትን ያወግዛል። (ምሳሌ.
20:1፣ ምሳሌ 23:29-35)። በስካር ማግስት የሚመጡ ክፉ ነገሮች ያልታረመና
ስለ ወሲብ የሚነገር ግልጽ ንግግር፣ አእምሮ ቢስነት፣ የግብረ ገብ ብልሽት፣ እና ጣዖት
አምልኮ ናቸው (ኤፌ. 5፡3-14)። እነዚህ ነገሮች በአሳቢነትና እግዚአብሔርን
በመንፈስ ተሞልቶ በማምለክ መለወጥ አለባቸው። ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡19-
21 ላይ በመንፈስ ስለመሞላት የሚሰጠው ማሳሰቢያ (“መናገር፣” “መዘመርና
መልካም ጣዕመ ዜማ መፍጠር፣” “ምሥጋና ማቅረብ፣” “ራሳችሁን ማስገዛት”)
ወደሚሉ ቃላቶች እየተሻሻለ የቀረበ ቁልፍ ቃል ነው።
ጳውሎስ በዚህ ቦታ አማኞች በመንፈስ ተነሳስተው አንድነትን በሚያሳድግ
አምልኮ ለእግዚአብሔር ምሥጋና ለማቅረብ እንደተሰበሰቡ አድርጎ በማሰብ
“መንፈስ ይሙላባችሁ” ይላል (ኤፌ. 5:18)። ይህ ራስ ወዳድ ከሆነው
የአህዛብ አምልኮ በተቃራኒ ይቆማል (ኤፌ. 5፡1-18)። በዚህ የቀደምት
ክርስቲያኖችን አምልኮ በሚያሳይ ጽሁፍ ውስጥ በሙዚቃ የሚቀርብ ምሥጋና
ጎልቶ ይታያል። ቤተ ክርስቲያን የተወለደችው በዝማሬ ነው የሚል መከራከሪያ
ይቀርብ ነበር፤ ይህ አባባል ከቆላስይስ 3፡16 ጋር እንደሚስማማ ይህ ንባብ ጥሩ
ማስረጃ ይሰጣል (ከሐዋርያት ሥራ 16፡25 እና ከያዕቆብ 5፡13 ጋር ያነጻጽሩ)።
በአምልኮ ውስጥ የቤተ ክርስቲያን አባላት በዝማሬ “እርስ በርስ
እየተነጋገሩ”(ኤፌ. 5:19) እንደሆነ የሚገልጽ ስሜት ስለሚሰጥ በአምልኮ
ውስጥ “የአግድሞሽ” ግንኙነት አለ። ነገር ግን የሙዚቃው ውዳሴ ብቸኛው
ትኩረት እግዚአብሔር መሆኑ በኤፌሶን 5፡20 ላይ “ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ”
ተብሎ ተለይቷል(ከቆላ. 3:16 ጋር ያነጻጽሩ)። በኤፌሶን 5፡20 ላይ
የተገለጸው ምሥጋና ማቅረብ በኤፌሶን 5፡19 ላይ ከተገለጸው በሙዚቃ ማመስገን
ጋር ስናስተያይ ምሥጋናው መቅረብ ያለበት “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ
ስም ለእግዚአብሔር አብ” ነው። “መንፈሳዊ ዝማሬ” በሚለው ሀረግ ውስጥ
“መንፈሳዊ” የሚለው ቅጽል (በግሪክ ኒውማቲኮስ የተባለው ) በመንፈስ ቅዱስ
የተነሳሱ ወይም የተሞሉ መዝሙሮችን ስለሚገልጽ በአምልኮ ውስጥ የመንፈስ
ቅዱስን ሚና ያጎላል። ስለዚህ ጳውሎስ ስለ ቀደምት ክርስቲያኖች አምልኮ የጻፈው
ነገር የሥላሴ ሶስቱም አካላት በንቃት መሳተፋቸውን ያሳያል።
የራስዎን የአምልኮ ልምምድ እንዲያሻሽልልዎ ሙዚቃን መጠቀም
የሚችሉት እንዴት ነው?
ኤፌሶን 5፡1-20ን ተመልሰን በመመልከት ጳውሎስ
ኃጢአትንና ክፋትን፣ በተለይም ፍትወትንና ሸካራ ንግግርን በተመለከተ ጽኑ አቋም
ሲይዝ እንመለከታለን። በእግዚአብሔር ሕዝብ መካከል የተበላሸ ባህርይ መኖርን
ለመቀበል ፈቃደኛ አልነበረም። በዚህ ፋንታ በኤፌሶን ያሉ አማኞችን ወደ ከፍተኛ
የባህርይ መስፈርት እንዲደርሱና የእግዚአብሔር “ውድ ልጆች” እና “ቅዱሳን”
ወይም የተቀደሱ የሚለውን መለያቸውን እንዲቀበሉ ጥሪ ያደርግላቸዋል።(ኤፌ.
5:1-10)። በህብረተሰቡ ውስጥ ያሉ ክርስቲያኖች ይህን ሲያደርጉ
ጎረቤቶቻቸውን ራስን ለሽንፈት ከሚዳርግ የአኗኗር ዘይቤ ወደ እግዚአብሔር ጸጋና
እውነት በመሳብ በጨለማ እንደሚያበሩ ያምናል (ኤፌ. 5:11-14)።
የቤተ ክርስቲያን አባላት የክርስቶስን መመለስ እየተጠባበቁ ሳለ
(ኤፌ. 5:8፤ ደግሞ ኤፌ. 5:15፣ 16ን ይመልከቱ) “እንደ ብርሃን
ልጆች ለመመላለስ” በተደረገው የቃል እድሳት በመደሰትና በክርስቶስ መገኘት
በመባረክ (ኤፌ. 5:14) ለአምልኮ እንደሚሰበሰቡ አድርጎ ጳውሎስ
ይገምታል። በእግዚአብሔር “እንደተወደዱ ልጆች” በሚለው ማዕረግና ክርስቶስ
ለእነርሱ በመሞቱ (ኤፌ. 5:1፣ 2) እና በመንፈስ በመሞላታቸው (ኤፌ.
5፡18) በመደፋፈር በአንድ ላይ ለጌታቸው ለኢየሱስ ክርስቶስና ለእግዚአብሔር
አብ ምሥጋና የማቅረብ ውዳሴን እየዘመሩ ሳለ የጋራ አምልኮአቸው በኃይልና
በደስታ ተለይቶ ታውቋል። ሰማያዊ እውነቶችን አጥብቀው በመያዝ እግዚአብሔር
ባደረገላቸው፣ አሁን እያደረገላቸው ባለውና በጌታቸው በኢየሱስ ክርስቶስ
አማካይነት ወደ ፊት በሚያደርግላቸው ታሪክ ተመስርተው ለወደ ፊት ባላቸው
ተስፋ ይደሰታሉ (ኤፌ.5:18-20)።
ንባቡ በዚህ መንገድ ከተስተዋለ ስለ ክርስቲያን አኗኗር የተሰጡ
የተበጣጠሱ ትዕዛዞች ጥርቅም ከመሆን ያለፈ ነው። የክርስትና ማንነትን፣
መሰጠትን፣ አንድነትን እና የመጨረሻው ዘመን አምልኮን በተመለከተ ክርስቶስ
እስኪመለስ ድረስ ባሉ ቀናት “የግዥ ስምምነቱን በፍጥነት መፈጸም” ስለሚለው
በሀዘን የተሞላ ግብዣ ትንቢታዊ ጥሪ ይሆናል (ኤፌ. 5፡16)።
1. ዛሬ መገናኛ ብዙሃንን በመጠቀም የ24/7/365 (በቀን 24 ሰዓት፣
በሳምንት ሰባት ቀን፣ በዓመት 365 ቀናት) እሴቶችን የሚሰብከውን
ባህል እየተጋፈጡ ሳለ አማኞች የጳውሎስን መስፈርቶች መተግበር
የሚችሉት እንዴት ነው?
2. ዛሬ አማኞች “እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውን ነገር ለይተው
ለማወቅ”(ኤፌ. 5:10) እና “የእግዚአብሔር ፈቃድ ምን እንደሆነ
ለመረዳት”(ኤፌ. 5:17) ምን ዘዴዎችን ሥራ ላይ ማዋል ይችላሉ?
3. ጳውሎስ በአማኞች መካከል ስለ ዝሙት መናገርን መከልከሉ እኛም
ወሲብን የሚመለከቱ መጥፎ ባህርያትን ወይም የወሲብ ጥቃትን
በተመለከተ ዝም ማለት እንዳለብን ያሳያል ብሎ የሆነ ሰው ሊከራከር
ይችላል (ኤፌ. 5:3፣ 4)። ይህ ተገቢ ያልሆነ ድምዳሜ የሚሆነው
ለምንድር ነው?
4. እኛ እየኖርንበት ባለ ዘመን ያለው ማህበረሰብ ጳውሎስ በእርሱ ዘመን
የሚጠቅሳቸው ሰዎች ከነበራቸው ልምምድ ጋር ተመሳሳይ የሆነ የአህዛብ
ልምምዶችን የሚያንጸባርቀው በምን መንገዶች ነው?