የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


ነሐሴ 20 - 26

10ኛ ትምህርት

Aug 26 - Sep 1




ባሎችና ሚስቶች፡- በአንድነት ከመስቀሉ ሥር



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ኤፌ. 5:21-33፤ ፊልጵ. 2:3, 4፤ ሕዝ. 16:1-14፤ 2 ቆሮ. 11:1-4፤ ዘፍ. 2:15-25።


የመታሰቢያ ጥቅስ:- “ባሎች ሆይ፣ ክርስቶስ ደግሞ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ወደዳት ሚስቶቻችሁን ውደዱ፤ በውኃ መታጠብና ከቃሉ ጋር አንጽቶ እንዲቀድሳት ስለ እርስዋ ራሱን አሳልፎ ሰጠ። እድፈት ወይም የፊት መጨማደድ ወይም እንዲህ ያለ ነገር ሳይሆንባት ቅድስትና ያለ ነውር ትሆን ዘንድ ክብርት የሆነች ቤተ ክርስቲ ያን ለራሱ እንዲያቀርብ ነው” (ኤፌ. 5:25–27)።

በኤፌሶን 5:21-33 ላይ ጳውሎስ አማኞች ለእርስ በርሳቸው መገዛት አለባቸው በሚለው ሀሳብ ላይ ይገነባል (ኤፌ. 5፡21)። ከዚያ በኋላ ለክርስቲያን ሚስቶች (ኤፌ. 5፡22-24) እና ባሎች (ኤፌ. 5፡25-32) ምክር ይሰጣል። ከዚያ በኋላ ለሁለቱም የሰጠውን ምክር በማጣራት ምክሩን ያጠቃልላል (ኤፌ. 5፡33)።

በዚህ ምክር ውስጥ ዛሬ ያሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎች ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ስለ ግንኙነቶቻችን እየተናገረ ሊሰሙ ይችላሉ። ኤፌሶን 5፡21-6፡ 9 ያለውን ክፍል ጳውሎስ የደብዳቤውን ታላቅ ርዕሰ ጉዳይ፣ አንድነትን ተጨባጭ ለማድረግ የተጠቀመበት መንገድ አድርገን ስንረዳ ይህንን ለማድረግ ራሳችንን ያዘጋጀን ቢሆንም አሁን ግን ትኩረታችን የሚሆነው በክርስቲያን ቤተሰብ ላይ ነው። የሰብአዊነት ጉድለት ያለበትን አሮጌውን ማህበራዊ መዋቅር አጠንክሮ እየተቸ ሳለ (ኤፌ. 2፡22ን ይመልከቱ)፣ ጉድለት ያለበት ማህበራዊ መዋቅር ካለው ከሰፊው ሰብአዊነት ውስጥ በተቀመጠው በአዲሱ ሰብአዊነት መፈጠር ደስታውን ይገልጻል (ኤፌ. 2፡15)።

ከእነዚህ መዋቅሮች ውስጥ እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለዓለም ያለው ዕቅድ በመጨረሻ ወደተፈጸመበት የሚያመለክት አዲስ ኃይል፣ መንፈስ ቅዱስ (ኤፌ. 2:22፤ ኤፌ. 3:16፤ ኤፌ. 5:18-21፤ ኤፌ. 6:17፣ 18) እና በክርስቶስ ምሳሌ የሆነ አዲስ ሥነ-ምግባር (ኤፌ. 4:13፣ 15፣ 20-24፣ 32፤ ኤፌ. 5:2፣ 10፣ 17፣ 21-33) እንደተለቀቁላቸው አማኞች ያሳያሉ። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለነሃሴ 27 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ነሐሴ 21
Aug 27

ምክር ለክርስቲያን ሚስቶች


ጳውሎስ ኤፌሶን 5፡1-20ን ከኤፌሶን 5፡22-33 ጋር አገናኝ በሆነ ንባብ፣ በኤፌሶን 5፡ 21 የጀመረ ሲሆን የቤተ ክርስቲያን አባላት ለእርስ በርስ መገዛት እንዳለባቸው ይናገራል (ከማርቆስ 10:42-45፤ ሮሜ 12:10፤ ፊልጵ. 2:3፣ 4 ጋር ያነጻጽሩ)። አማኞች ይህንን ማድረግ ያለባቸው “ለክርስቶስ ካላቸው አክብሮት” የተነሣ ነው(ኤፌ. 5:21)። ይህም ጳውሎስ ከክርስቶስ ጋር ያለውን ግንኙነት ለአማኞች እጅግ ወሳኝ አድርጎ ከገለጸባቸው በርካታ ጊዜያቶች የመጀመሪያው ነው።

ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን አባላት ለእርስ በርስ እንዲገዙ ሲናገር ምን ማለቱ ነው? ይህን ሀሳብ ማስተዋል ያለብን እንዴት ነው? ኤፌ. 5:21።



ጳውሎስ ለክርስቲያን ሚስቶችም “ለጌታ እንደምትገዙ ለባሎቻችሁ ተገዙ” (ኤፌ. 5:22) ይላቸዋል። በዚህም እርሱ እየተወያየ ያለው ሚስቶች ለራሳቸው ባሎች መገዛት እንዳለባቸው እንደሆነ ግልጽ እያደረገ ነው (1ኛ ጴጥ. 3፡1፣ 5ን ደግሞ ይመልከቱ)። ጳውሎስ ሚስቶች “ለጌታ እንደሚያደርጉ” ለባሎቻቸውም ያድርጉ ሲል ሚስት ባሏን ክርስቶስ እንደሆነ አድርጋ ትገዛለት ማለቱ ነው? ወይስ የመገዛቷ እውነተኛውና ከፍተኛው የትኩረት ነጥብ ክርስቶስ ነው ማለቱ ነው?

ባሪያዎች በኤፌሶን 6፡7 ላይ በተገለጸው መሰረት “ለሰው ሳይሆን ለጌታ እንደሚገዙ ”ጌቶቻቸውን እንዲያገለግሉ የተገለጸበትን እና በቆላስይስ 3:18 ላይ ሚስቶች “በጌታ እንደሚገባ” ለባሎቻቸው እንዲገዙ የተጠየቁበትን ስናነጻጽር የኋለኛው አመለካከት ተመራጭ ይሆናል። ሚስቶች ራሳቸው ከባሎቻቸው በላይ ክርስቶስን ማክበር ያለባቸው ናቸው።

በቆላስይስና በኤፌሶን መጻሕፍት በሁለቱም ውስጥ ክርስቶስና ክርስቶስ ብቻ ቅዱስ አካል የሆነችው የቤተ ክርስቲያን ራስ ሆኖ ተገልጾአል (ኤፌ. 1:22፣ ኤፌ. 5:23፣ ቆላ. 1:18):- “ክርስቶስ ደግሞ የቤተ ክርስቲያን ራስ የአካሉም አዳኝ ነው” (ኤፌ. 5:23)። ባል “የሚስት ራስ ነው” (ኤፌ. 5:23) የሚለው አባባል ሚስት ለባሏ ታማኝ እንድትሆን ለተጠየቀችው ምሳሌ ሆኖ ከሚያገለግለው የቤተ ክርስቲያን ለክርስቶስ ታማኝ መሆን ጋር ይመሳሰላል። ንባቡ የሚገልጸው የተበላሸ ትዳርን ሳይሆን ፍቅርና እንክብካቤ ያለበትን ትዳር ነው። ይህ ጥቅስ ማንኛውንም ዓይነት የቤተሰብ ጠብ እንደሚፈቅድ ተደርጎ መተርጎም የለበትም።

አሁን ባነበብነው ንባብ ብርሃን ቀጥሎ ያለውን ምክር ማስታወስ እጅግ አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው? ባልየው “ያልታረመ፣ ሸካራ፣ የሚጮህ፣ ጉረኛ፣ ራስ ወዳድ፣ ጨካኝና ትዕቢተኛ ሰው ከሆነ ባል የሚስት ራስ ነው የሚለውንና ሚስት በሁሉም ነገር ለባሏ ትገዛ የሚለውን ቃል በፍጹም መናገር የለበትም፤ ለዚህ ምክንያቱ ቃሉ በሚገልጸው መሰረት በትክክል ጌታ ስላልሆነና ትክክለኛ ባል ስላልሆነ ነው።”-Ellen G. White, The Adventist Home, p. 117.

ነሐሴ 22
Aug 28



ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ ሙሽራ፡- ክፍል 1


ኤፌሶን 5:25-27፣ 29ን በሕዝቅኤል 1፡1-14 ካለው መሰረታዊ ታሪክ ጋር ያነጻጽሩ። ጳውሎስ በራሱ ጽሁፍ ውስጥ የሚያንጸባርቃቸው የዚያ ታሪክ መሰረታዊ ነገሮች ምንድር ናቸው?



ጳውሎስ በኤፌሶን 5:25-27፣ 29 ላይ ጋብቻን የተመለከተውን ዘይቤያዊ አነጋገሩን የተጠቀመው ስለ ቤተ ክርስቲያንና እሷ ከክርስቶስ ጋር ስላላት ግንኙነት ሲሆን ፈጠራ በታከለበት ሁኔታ ከጥንቱ የጋብቻ ወግና ሚናዎች ሀሳቦችን ይወስዳል። ቤተ ክርስቲያን እንደ ሙሽራይቱ የተጠቀሰችበትን ግንኙነት በተመለከተ ክርስቶስ የሚከተሉትን ነገሮች የሚያደርግ መለኮታዊ ሙሽራ ነው፡-
1. ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሙሽራ ይወዳል (ኤፌ. 5:25)። ይህ ነገር ለኢየሱስ የልብ ሥራ እንደሆነ በፍጹም መርሳት የለብንም። እርሱ ይወደናል!
2. ራሱን እንደ ጥሎሽ (የሙሽሪት ዋጋ) አድርጎ ይሰጣል። በጥንቱ የጋብቻ ስምምነት አውድ ሙሽራው “ጥሎሽን (የሙሽራይቱን ዋጋ)” በመክፈል ሙሽራይቱን ይገዛል። ይህም በተለምዶ ብዙ ገንዘብና የከበሩ ነገሮችን የሚያካትት ሲሆን የጥንቶቹ የሰፈር ኢኮኖሚዎች እስከሚደገፉባቸው ድረስ ትልቅ ነበር። ክርስቶስ “ራሱን ለእርሷ አሳልፎ እስከሰጠ ድረስ” (ኤፌ. 5:25) ለቤተ ክርስቲያን እንደ ሙሽራው የመጨረሻውን ዋጋ ይከፍላል።
3. ሙሽራውን ያጥባታል። ሙሽራዋን ማዘጋጀት የጥንት የጋብቻ ዝግጅት ወሳኝ ክፍል ነበር። ዛሬም እንደሚደረገው በዚያን ዘመን ሙሽራይቱን ለሥነ ሥርዓቱ የሚያዘጋጇት ሚዜዎቿና ሴት ዘመዶቿ ነበሩ። ነገር ግን ጳውሎስ መለኮታዊው ሙሽራ ሙሽራይቱን ለሰርጉ እንደሚያዘጋጃት ያስባል! “በውኃ ማጠብ” የሚቀድሳትና የሚያነጻት እርሱ ነው (ኤፌ. 5:26)፤ ይህ የሚያመለክተው ምናልባት ጥምቀትን ነው።
4. የተስፋ ቃል ይናገራል። ይህ መንጻት የሚፈጸመው “በቃሉ” ነው(ኤፌ. 5:26)። ይህ የሚያመለክተው መለኮታዊው ሙሽራ፣ ምናልባት በማጨት ሥነ ሥርዓት አውድ፣ ለሙሽራይቱ የሚናገረውን የተስፋ ቃል ነው (እግዚአብሔር ለአማኞች በሚለወጡበት ሰዓት ሊያደርግላቸው የገባላቸውን ተስፋ በማስታወስ ከኤፌ. 1:3-14፣ ኤፌ. 2:1-10 ጋር ያነጻጽሩ)። የጥንቱ ማጨት የዘመናዊው የቀለበት ሥነ-ሥርዓት ሌላኛው ገጽታ ቢሆንም ባልየው ለሚስቱ ስለሚከፍለው ጥሎሽና ሙሽራይቱ ከቤተሰቧ ይዛ ስለምትመጣቸው ንብረቶች በተመለከተ የተጻፈ ሰነድን የሚያካትቱ እጅግ ጥብቅ የሆኑ ድርድሮች ስብስብ ነው።
5. ሙሽራይቱን ያዘጋጃታል ይሸልማታልም (ያስጌጣታል)። በመጨረሻ ሙሽራይቱ ለሙሽራው ስትሰጥ እጅግ ስለተዋበች እንከን በሌለው ድምቀት ትታያለች (ኤፌ. 5፡27)። ክርስቶስ ሙሽራይቱን የሚያጥባት ብቻ ሳይሆን ያዘጋጃታል፣ ያስውባታልም።

ክርስቶስ ስለ እኛ ምን እንደሚሰማው እንድናስተውል እነዚህ ጥቅሶች የሚረዱን እንዴት ነው? ይህን ነገር እጅግ አጽናኝ ሆኖ የምናገኘው ለምንድር ነው?

ነሐሴ 23
Aug 29

ቤተ ክርስቲያን እንደ ክርስቶስ ሙሽራ፡- ክፍል 2


ጳውሎስ በጥንቱ ጋብቻ ውስጥ ያሉ ነገሮችን በቆሮንቶስ ለነበሩ ክርስቲያኖች ተማጽኖ ለማቅረብ የተጠቀመው እንዴት ነው? መልእክቱ የቀረበው መቼ ነበር? (2ኛ ቆሮ. 11:1-4)።



ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡25-27 ላይ ከጥንቱ ጋብቻ አንድ የመጨረሻ ነገር በመጠቀም ክርስቶስን እንደሚከተለው ያሳያል፡- (6) ሙሽራይቱን ለራሱ ያቀርባል። በጥንት ባህል ሙሽሪት ለሙሽራው የምትሰጠው በወንዱ ሚዜ ወይም ሚዜዎች ወይም በአባቷ ነበር። በፍጹም በሙሽራው አትሰጥም! ነገር ግን ጳውሎስ በዚህ ቦታ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሙሽሪት ለራሱ እንደሚሰጥ አድርጎ ያስባል።

ጳውሎስ የጋብቻ ወጎችንና ሚናዎችን ቅደም ተከተሉን ጠብቆ በሚገለጥ መልኩ ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያን ጋር ያለውን ግንኙነት ለማጉላት ይጠቀማል፡- 1. ማጨት።

ክርስቶስ ራሱን ለቤተ ክርስቲያን አሳልፎ ሰጠ (እንደ ጥሎሽ ወይም የሙሽራ ዋጋ)፤ ከዚህ የተነሣ ለእርሷ ታጨ (ኤፌ. 5፡25)። 2. ለጋብቻ ሥነ-ሥርዓቱ መዘጋጀት። ሙሽራው አሁን በሚያደርጋቸው ጥረቶቹ ትኩረት የሚያደርገው ሙሽራይቱን በመቀደስና በማንጻት ላይ ነው (ኤፌ. 5:26)። 3. ራሱ የጋብቻው ሥነ-ሥርዓት። የክርስቶስ የአሁኑ ትኩረት በሰርጉ ላይ ሙሽራይቱን “ማቅረብ” ነው (ኤፌ. 5:27)። ይህ የመጨረሻው ጉዳይ ሙሽራው ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሙሽሪት በመቁጠር ለራሱ ሊያቀርብ ወደሚመለስበት ታላቅ የሰርግ ሥነ-ሥርዓት ይመለከታል። (ኤፌ. 5:27ን ከ2ኛ ቆሮ. 11:1፣ 2፤ ቆላ. 1:21-23 28 ጋር ያነጻጽሩ)።

የጥንት ጋብቻዎች ብዙ ጊዜ የሚጀምሩት በሌሊት በሚደረግ ጉዞ ነው (ማቴ 25፡1-13ን ይመልከቱ)። ሙሽራውና አጃቢዎቹ በሙሽራው ቤት--ለጥንዶቹ በተዘጋጀው አዲስ ቤት--ይሰበሰቡና ደማቅ በሆነ ሥነ-ሥርዓት ጉዞአቸውን ይጀምራሉ። ሕዝቡ የተለኮሱ ችቦዎችን ይዘውና ከፍና ዝቅ በሚል ጣዕመ ዜማና ታላቅ ደስታ ታጅበው ወደ ሙሽራይቱ አባት ቤት ይሄዳሉ። ከዚያ ሙሽራይቱን ከተቀበሉ በኋላ ወይም ሙሽራይቱን አጅቦ ይጓዝ ከነበረው ሕዝብ ጋር በመንገድ ላይ በመገናኘት ተጓዦቹ ጥንዶቹን ወደ አዲሱ ቤታቸው ያደርሱአቸዋል። በዚህ ቦታ ለሰርጉ የታደሙ እንግዶች ለአንድ ሳምንት በሙሉ በግብዣ ላይ ይቆዩና ሙሽራይቱ ለሙሽራው ስትሰጥ የጋብቻው ሥነ-ሥርዓት ፍጻሜ ያገኛል።

ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ለራሱ እንደሚያቀርብ አድርጎ ጳውሎስ ሲያሳይ ስለዚህ ታላቅ ጉዞና ስለሚያቀርብበት ሰዓት ፍንጭ ይሰጣል። ይህን በማድረጉ የክርስቶስን መመለስ እንደ የወደፊት የሰርግ ሥነ ሥርዓት የሚገልጽ ተንቀሳቃሽ ምስል ይሰጣል። በዚህን ጊዜ በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያኑ መካከል ለረዥም ጊዜ የቆየው መተጫጨት ያበቃና ሰርጉ ይከበራል።

ከዚህ አዎንታዊ ከሆነ፣ ደስታ ካለበትና ተስፋ ከተሞላበት ምሳሌ ለራሳችን መውሰድ ያለብን መልእክት ምንድር ነው?

ነሐሴ 24
Aug 30

ሚስትህን እንደ ራስህ ውደድ


ባሎች ለሚስቶቻቸው ደግነት ያለበትን ፍቅር ማሳየትን እንዲለማመዱ ለማደፋፈር ጳውሎስ የሚያቀርበው አዲስ መከራከሪያ ምንድር ነው? ኤፌ. 5:28-30።



ጳውሎስ ለክርስቲያን ቤተሰብ የሰጣቸው ደንቦች (ኤፌ. 5:21- 6:9) አስቸጋሪ የሆነ ማህበራዊ አውድን ይገልጣሉ። በኤፌሶን 5:28-30 ላይ ከሚጠበቀው በላይ እየተደጋገመ የሚሄደውን ዘዴ በመከተል “የገዛ ሥጋቸውን ለመጥላት” ስለሚመርጡ፣ ሚስቶቻቸውን ስለሚደበድቡና ስለሚሳደቡ ባሎች ይናገራል (ኤፌ. 5፡ 28፣ 29ን ይመልከቱ)። በጳውሎስ ዘመን በነበረው የግሪክና የሮም ዓለም “የቤተሰቡ አባት” (በላቲን ቋንቋ ፓቴር ፋሚሊያስ የሚባለው) ሕጋዊ ሥልጣን እጅግ ሰፊ ነበር። ሚስቱን፣ ልጆቹንና ባሪያዎቹን ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ ሊቀጣ ወይም ሊገድልም ይችላል። ነገር ግን በዚህ ሁኔታ ከልክ ያለፈ ኃይል መጠቀም በሕዝብ አመለካከት ከጊዜ ወደ ጊዜ እቀባ እየተደረገበት ቢሆንም የተሰጠው ሕጋዊ መብት ይህንን እንዲያደርግ ይፈቅድለታል።

በኤፌሶን 5:25-27 ላይ ጳውሎስ የፍቅር የመጨረሻ ምሳሌ የሆነውንና ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ፍቅር በመዘርዘር ለባሎች ከተለመደው የተለየ ሞዴል ይሰጣል። አሁን፣ ሌላ አዲስ መከራከሪያ ከማስቀመጡ በፊት ሙሽራው ለሆነችው ቤተ ክርስቲያን “ራሱን አሳልፎ የሰጠው” እና እያንዳንዱን ፍላጎቷን ተከታትሎ የሚያሟላው ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ (ኤፌ. 5:25- 27) ክርስቲያን ባሎችም “በተመሳሳይ መንገድ” (ኤፌ. 5:28) ምላሽ እንዲሰጡ በመጠየቅ በድጋሚ ወደዚህ ታላቅ ምሳሌ ይጠቁማል። ጳውሎስ ክርስቲያን ባሎችን በዘመናቸው ከተለመዱ ልምምዶች ተመልሰው ከክርስቶስ ደግ ፍቅር ጋር ጥምረት ለመፍጠር እንዲሹ ይገዳደራቸዋል።

በኤፌሶን 5:28-30 ላይ ክርስቲያን ባሎች ለሚስቶቻቸው ፍቅር ሊኖራቸው እንደሚገባ ለመደገፍ አዲስ ምክንያት፣ ያውም ግለሰቡ ለራሱ የሚኖረውን ፍቅር ይጨምራል። “የገዛ ሥጋውን የሚጠላ ማንም የለም” (ቢያንስ በትክክል ማሰብ የሚችል ማንም ሰው) በማለት እውነቱን ይነግራል።

ባሎች ራሳቸውን አይጎዱም ወይም የራሳቸውን አካል አይደበድቡም። ከዚህ ይልቅ “ይመግበዋል ይከባከበውማል”(ኤፌ. 5:29)። ጳውሎስ በክርስቲያን ሚስቶች ላይ የሚደረገውን ጭካኔና ጥቃት ለማስወገድ በመጠየቅ ክርስቲያን ባል ራሱን ከሚስቱ ጋር እንዲያመሳስል ይጋብዛል። ከሚስትህ ጋር አንድ ስለሆንክ፣ እሷን መጉዳት ራስህን ከመጉዳት የማይተናነስ ስለሆነ፣ ጤናማ አእምሮ ያላቸው ብዙ ሰዎች ይህንን አያደርጉም በማለት መከራከሪያውን ያቀርባል።

ጳውሎስ ወደ ኢየሱስ ምሳሌ በመመለስ ክርስቶስ “አካሉ” (ኤፌ. 5:29፣ 30) ለሆኑ ክርስቲያኖች የፍቅር እንክብካቤ በማድረግ ለራሱ የደግነት ክብካቤ ማድረግን እየተለማመደ ነው በማለት ይከራከራል። ሚስትህን በተመለከተ ያለህን ባሕርይ ራስህን በምትይዝበት ምሳሌ ቅረጽና በመጨረሻም ክርስቶስ አንተን በሚይዝበት መንገድ ቅረጽ ይላል።

ጳውሎስ ለባሎችና ለሚስቶች የኢየሱስን ምሳሌ ይጠቅስላቸዋል። በቤተሰብዎ ክበብ ውስጥ ያሉትን ስለመውደድ ከኢየሱስ ምን መማር ይችላሉ?

ነሐሴ 25
Aug 31

ጋብቻ “አንድ ሥጋ” የመሆን ምሳሌ


በዘፍጥረት 2:15-25 ላይ ያለውን የፍጥረት ታሪክ ያጥኑ። ባልና ሚስት “አንድ ሥጋ” መሆናቸውን ከሚገልጸው አረፍተ ነገር በፊት በታሪኩ ውስጥ ምን ሆነ (ዘፍ. 2:24)?



ጳውሎስ ለሚስቶችና ለባሎች የሰጠውን ምክር ለመተግበር ቁልፉ በኤፌሶን 5፡31 ላይ ከዘፍጥረት 2፡24 የጠቀሰውን ጥቅስ የእርሱ መደምደሚያ እንደሆነ አድርጎ መመልከት ነው። በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ በተገለጸው የፍጥረት ታሪክ ላይ እያሰላሰለ ሳለ የክርስቲያን ጉባኤዎችን ችግሮችና በመካከላቸው ያለውን የቤተሰብ ግንኙነት ጤንነት ከግምት ውስጥ ያስገባል። በዘፍጥረት 2፡24 ላይ ዘመናትን እየተሻገረ ሲያስተጋባ የነበረውን መልእክት ይሰማል። በመለኮት ዕቅድ ትዳር “የአንድ ሥጋ” ግንኙነት እንዲሆን የታቀደ ሲሆን በግብረ ሥጋ ግንኙነት አንድ መሆን በስሜታዊና በመንፈሳዊ አንድነት ተንጸባርቋል፤ ስሜታዊና መንፈሳዊ አንድነትም ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ትርጉም ይሰጣሉ።

ጳውሎስ ዘፍጥረት 2፡24ን በመምረጡ ከውድቀት በፊት ለተፈጠረው ጋብቻ አረፍተ ነገር በመምረጥ በክርስቲያን ሚስቶችና ባሎች መካከል ስለሚኖሩ ግንኙነቶች እንደሚያውለው ልብ በሉ። በተለየ ሁኔታ ከውድቀት በኋላ ባለው ዓለማችን በወንድና በሴት መካከል ያለውን የግብረ ሥጋ ግንኙነት ከአግባብ ውጭ በሆነ ሁኔታ መጠቀም (መበዝበዝ) የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሴትን በቁጥጥር ሥር ማዋልን ይወክላል የሚለው ሀሳብ በዘመናዊው ባህሎች ውስጥ ምን ያህል ሥር የሰደደ እንደሆነ ይገልጣል። የግብረ ሥጋ ግንኙነት በዘፍጥረት መጽሐፍ ውስጥ እንደተንጸባረቀው በቁጥጥር ሥር የማዋል ሳይሆን አንድ የመሆን ጉዳይ ነው በማለት ጳውሎስ ይከራከራል። የወንድን የበላይነት አይወክልም ወይም እውነት አያደርገውም፣ ነገር ግን ሁለቱም “አንድ ሥጋ” እስኪሆኑ ድረስ ያለውን የባልና የሚስት አንድነት ይወክላል። ስለዚህ ትዳርንና ወሲብን በተመለከተ ወሳኝ የሆነ፣ ባህልን የሚቃወምና እርምት የሚሰጥ የሥነ-መለኮት ትምህርትን ለማግኘት ኤፌሶን 5፡21-33ን እና ዘፍጥረት 2፡24ን መመልከት እንችላለን።

በዚህ ተመሳሳይ አውድ ጳውሎስ በሚቀጥለው ቁጥር ላይ ስለ “ታላቅ ምስጢር ” ይናገራል (ኤፌ. 5:32ን ይመልከቱ)። ይህ ጳውሎስ እየተናገረ ያለው መንታ ዘይቤአዊ አነጋገር ሁለቱንም ወገን ያካትታል። እርሱም ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ባለው ግንኙነት ብርሐን የሚስተዋለው የክርስቲያን ትዳር (ኤፌ. 5፡32) እና በክርስቲያን ትዳር ብርሐን የሚስተዋለው ክርስቶስ ከቤተ ክርስቲያኑ ጋር ያለው ግንኙነት ነው (ኤፌ. 5፡32)።

የክርስቲያን ትዳር በክርስቶስና በቤተ ክርስቲያን መካከል ባለው ግንኙነት በመነጻጸር ከፍ ከፍ ብሏል። በተጨማሪም ለሌላው በሚጠነቀቅ የክርስቲያን ትዳር መነጽር አማካይነት ቤተ ክርስቲያን ከክርስቶስ ጋር ስላላት ግንኙነት በማሰብ አማኞች ከክርስቶስ ጋር ስለሚጋሩት ግንኙነት አዲስ መረዳት ያገኛሉ።

ኤፌሶን 5፡33 ጳውሎስ በኤፌሶን 5፡21-32 ላይ ለሰጠው ምክር እጥር ምጥን ያለ ማጠቃለያ ሆኖ የሚያገለግለው በምን መንገዶች ነው? ባለትዳር ከሆኑ እነዚህን መርሆዎች በትዳር ሕይወትዎ በሙላት ለመተግበር መሻት የሚችሉት እንዴት ነው?

ነሐሴ 26
Sep 01


ተጨማሪ ሀሳብ


ከኤለን ጂ ኋይት ጽሁፎች ቴስቲሞኒስ ፎር ዘ ቸርች በሚለው መጽሐፍ ቅጽ 7፣ ገጽ 45-50 ላይ “የትዳር ሕይወት ኃላፊነቶች” የሚለውን እና የዳግም ምጻቱ ተጠባባቂዎች ቤትና ቤተሰብ ከሚለው መጽሐፍ “የጋራ ግዴታዎች” የሚለውን ክፍል ገጽ 114-120 ያንብቡ።

ኤለን ጂ ኋይት የትዳር አጋሮች አንዱ ሌላውን ለመቆጣጠር ከሚደረጉ ጥረቶች እንዲቆጠቡ እንዲህ በማለት በቀጣይነት ታደፋፍራለች፡- “አንዱ ለሌላኛው ግለሰብ ፍላጎት እንዲሸነፍ ለማስገደድ አትሞክሩ። ይህንን እያደረጋችሁ ለእርስ በርሳችሁ ያላችሁን ፍቅር መጠበቅ አትችሉም። ደግ፣ ትዕግሥተኛ፣ ራሳችሁን የምትገዙ፣ አሳቢና ትሁት ሁኑ።”-The Adventist Home, p. 118.

በቆላስይስ 3፡18 እና ኤፌሶን 5፡22-24 ትርጉምና አተገባበር ላይ በቀጥታ ሀሳብ ትሰጣለች:- “ብዙ ጊዜ እንዲህ የሚል ጥያቄ ይጠየቃል፣ ‘ሚስት የራሷ ፈቃድ የላትምን?’ ባል የቤተሰብ ራስ እንደሆነ መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ይናገራል።

‘ሚስቶች ሆይ፣ ለባሎቻችሁ ተገዙ።’ ይህ ትዕዛዝ እዚሁ ቢያበቃ ኖሮ ሚስት ያላት ቦታ የሚያስመኝ አይሆንም ነበር።…ብዙ ባሎች ‘ሚስቶች ሆይ፣ ተገዙ’ የሚሉትን ቃላት ብቻ ወስደው እዚያው ያቆማሉ፣ ነገር ግን የዚህ ትዕዛዝ መደምደሚያ የሆነውን ‘በጌታ እንደሚገባ’ የሚለውን እናነባለን [ቆላ. 3:18]። ሚስት እግዚአብሔርን እንድትፈራ እና የእርሱን ክብር ሁልጊዜ በፊቷ እንድታስቀምጥ እግዚአብሔር ይጠይቃታል። ራሷን ሙሉ በሙሉ ማስገዛት ያለባት በራሱ ሕይወት ገደብ የለሽ ዋጋ በመክፈል እንደ ልጁ አድርጎ ለገዛት ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው። …ለሚስት ከባል በላይ የሆነ አለ፤ እርሱ አዳኟ ስለሆነ ለባሏ የሚኖራት መገዛት እግዚአብሔር ባዘዛት መሰረት-‘በጌታ እንደሚገባ’መሆን አለበት።”- The Adventist Home, pp. 115, 116.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ኤፌሶን 5፡21-33 ላይ ያለው ንባብ በባል ሥልጣንና ገዥነት ላይ ትኩረት የሚያደርግ የጋብቻ ምሳሌ እንዲተገበር ስለሚያስገድድ ክርስቲያናዊ ግንኙነትን የማይገልጽ ጊዜው ያለፈበት ንባብ ነው በማለት አንድ ሰው እንደሚከራከር አድርገው ያስቡ። ለዚህ ክርክር እርስዎ መልስ የሚሰጡት እንዴት ነው? ከንባቡ ከራሱ ምን መመለስ እንዳለብዎ የሚገልጹት ምን ነጥቦች ናቸው?

2. ራሳቸውን ግድድሮሽ ባለበትና አስቸጋሪ የትዳር ግንኙነት ውስጥ ለሚያገኙ ሰዎች ጳውሎስ በኤፌሶን 5:21-33 ላይ የሚሰጠው ምክር ምን ይሰጣቸው ይሆን?

3. በዘፍጥረት ምዕራፍ 1 እና 2 ላይ ያለው የፍጥረት ታሪክ ዝም ብሎ ምሳሌ እንጂ በቢሊዮኞች በሚቆጠሩ ዓመታት ውስጥ የሆነውን የዝግመት ለውጥ ወደማሳየት እንኳን አይቀርብም ብለው አንዳንድ ክርስቲያኖች ይከራከራሉ። ጳውሎስ ታሪኩን መጠቀሙ እነዚህን ቃላት እንዴት ቃል በቃል እንደተቀበላቸው ምን ያስተምረናል?

4. “አንድ ሥጋ” በሚለው ርዕሰ ጉዳይ ላይ የበለጠ ትኩረት አድርጉ። ይህ የጋብቻን ቅድስና እንድናስተውልና የተጋቡ ጥንዶች ያንን ቅድስና ለመጠበቅ ማድረግ የሚችሉትን ሁሉ ለምን ማድረግ እንዳለባቸው እንድንረዳ የሚረዳን እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL