የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ኤፌ. 4:17-32፤ ቆላ.
3:1-17፤ ዘካ. 3:3-5፤ ዘካ. 8:16፤ ኢሳ. 63:10፤ ሮሜ. 8:16፣ 26፣ 27።
የመታሰቢያ ጥቅስ:- “ፊተኛውን ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ፣ በአእምሮአችሁም መንፈስ ታደሱ፣ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተ ፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ።” (ኤፌሶን 4:22–24)።
ጆሴ አንቶኒዮ ለብዙ ዓመታት ቤት ያልነበረውና በእስፔን ፓልማ በተባለ
ቦታ በጎዳና ላይ የሚኖር ሰው ነበር። የሸበተና ስድ የተለቀቀ ፀጉርና
ጺም ስለነበረው ዕድሜው 57 ቢሆንም ከዚያ የበለጠ ያረጀ ይመስል
ነበር። አንድ ቀን የጸጉር ሳሎን ባለቤት የሆነች ሳልቫ ጋርሺያ ወደ ጆሲ ቀርባ
ጸጉሩን ማስተካከል እንደምትፈልግ ነገረችው።
ጆሲ በጸጉር ቤቱ ወንበር ላይ ተቀምጦ ብርቱ የሰራተኞች ቡድን ያንን
ስድ የተለቀቀውን ጸጉሩንና ጺሙን ቆርጦ፣ ቀለም ቀብቶ ቅርጽ አወጣለት። ከዚህ
በመቀጠል ጆሲ ጥሩ የሆነ ዘመናዊ አዲስ ልብስ አገኘ። ከዚያ በኋላ ትክክለኛው ነገር
ተገለጠ። ጆሲ በመስታወት ፊት ተቀምጦ ሳለ እንባ ከዓይኑ መውረድ ጀመረ። “ይህ
እኔ ነኝ? በጣም የተለየሁ ሰው ነኝ፤ አሁን ማንም ሰው አያውቀኝም!” አለ። ቀጥሎም
እንዲህ አለ፡- “የመልክ ለውጥ ብቻ አይደለም። ሕይወቴንም ለውጦታል።”
ጳውሎስ በኤፌሶን 4:17-32 ላይ አማኞቹ ፍጹም (የተሟላ) ለውጥ
ተለማምደዋል በማለት ይከራከራል። አሮጌ ማንነታቸውን አውልቀው አዲስ
ማንነት ተቀብለዋል። ምንም እንኳን ይህ ተራ ውጫዊ ለውጥ ባይሆንም የጆሲን
የመሰለ ለውጥ አድርገዋል። በሕይወት ውስጥ “እውነተኛ ጽድቅንና ቅድስናን”
ማምጣት (ኤፌሶን 4:24) “በአእምሮአችሁ መንፈስ መታደስን” ያካትታል
(ኤፌሶን 4:23)። የመጨረሻው መስተካከል ይህ ነው።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለነሃሴ 13 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
ኤፌሶን 4:17-32ን ከቆላስይስ 3:1-17 ጋር ያነጻጽሩ። አማኞች የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በሚያደፋፍር መንገድ እንዲኖሩ የሚከራከርላቸው እንዴት ነው?
አስቀድሞ በቀረበው ክፍል፣ በኤፌሶን 4:1-16 ላይ፣ የጳውሎስ ዋና ሀሳብ
የቤተ ክርስቲያን አንድነት ነበር። ኤፌሶን 4፡1ን ከኤፌሶን 4፡ 17 ጋር ስናነጻጽር
እንዴት መሄድ ወይም መኖር እንዳለብን በተመለከተ እነዚህ ሁለቱ ማሳሰቢያዎች
ተመሳሳይ መሆናቸውን እንመለከታለን። እነዚህ መመሳሰሎች ጳውሎስ እየተናገረ
ያለው ተመሳሳይ በሆነ ዋና ሀሳብ ላይ፣ ያውም በአንድነትና አንድነትን በሚደግፍ ሀሳብ
ላይ ሆኖ ግን አዲስና ከመነሻው አሉታዊ ከሆነ ነጥብ በመነሳት እንደሆነ ይጠቁማል።
በኤፌሶን 4:17-24 ላይ ጳውሎስ ለአንድነት ቦታ እንደማይሰጥ አድርጎ
የሚመለከተውን የአህዛብን የአኗኗር ዘይቤ (ኤፌሶን 4፡17-19) አንድነትን
ከሚያሳድግ ከእውነተኛው የክርስቲያን የአኗኗር ዘይቤ ጋር ያነጻጽራል (ኤፌሶን
4፡20-24)። ጳውሎስ በተበላሸው የአህዛብ የአኗኗር ዘይቤ ላይ የሚያቀርበውን
ትችት ስናነብ እግዚአብሔር አህዛቦችን በክርስቶስ አማካይነት እንዳዳናቸውና
ከእግዚአብሔር ሕዝብ ጋር ሙሉ ሕብረት እንዲኖራቸው ዕድል እንደሰጣቸው
ያለውን እምነት ማስታወስ አለብን።(ኤፌሶን 2:11-22 ኤፌሶን 3:1-13)።
ስለዚህ በኤፌሶን 4፡17-19 ላይ “ሥጋውያን ስለሆኑ አህዛብ” ውስንና አሉታዊ
መግለጫ እየሰጠ ነው(ኤፌ. 2:11)።
ጳውሎስ የተጨነቀው ዝም ብሎ አህዛብ ስለሚያሳዩአቸው የተወሰኑ
ኃጢአቶች ወይም ባህርያት ብቻ አልነበረም። እርሱ ይጨነቅ የነበረው ስለሚያሳዩት
የባህርይ ዓይነትና በኃጢአት መዳፍ ውስጥ እየኖሩ ስላሉበት የቁልቁለት ጉዞ
ነበር። በኤፌሶን 4፡17-19 ልብ ላይ ያለው ደደብ የሆነ መንፈሳዊነት ስዕል ነው።
“እንግዲህ አህዛብ ደግሞ በአእምሮአቸው ከንቱነት እንደሚመላለሱ ከእንግዲህ
ወዲህ እንዳትመላለሱ እላለሁ።…በልባቸውም ደንዳንነት ጠንቅ ልቦናቸው
ጨለመ፤ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ።” (ኤፌሶን 4:17፣ 18). ይህ
ከንቱ መንፈሳዊነት በንባቡ ጅምር ላይ የተብራራው የልብ መጨለም (መረዳት
አለመቻል) ምንጭ ነው። (“እነርሱም ባለማወቃቸው ጠንቅ በልባቸውም
ደንዳንነት ጠንቅ ልቦናቸው ጨለመ፣ ከእግዚአብሔርም ሕይወት ራቁ።” ኤፌ.
4:18፣ 19)። እንዲሁም ብልሹ የሆነ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ልምምዳቸውም
በመጨረሻ ላይ እንደሚከተለው ተሰምሮበታል፡- “ደንዝዘውም በመመኘት
ርኩሰትን ሁሉ ለማድረግ ራሳቸውን ወደ ሴሰኝነት አሳልፈው ሰጡ” (ኤፌ.
4:19)። ከእግዚአብሔር ስለተለዩ እንዴት መኖር እንዳለባቸው አያውቁም፤
ከእርሱ የሚያድን ጸጋ ስለተለዩ በኃጢአትና በብልሽት ቁልቁለት ጉዞ ዙሪያ
ጥምጥም መጓዛቸውን ይቀጥላሉ።
አንድን ግለሰብ ወደከፋ ኃጢአት ወደ ታች መጎተቱን የሚቀጥለውን
የኃጢአት ኃይል በተመለከተ የእርስዎ ልምምድ ምን ነበር?
ጳውሎስ የአድማጮቹን የመለወጥ ታሪክ እንደገና ሲነግራቸው ወደ እነርሱ እያደረሰ ያለው ወሳኝ የሆነ ዋና ነጥብ ምንድር ነው? (ኤፌ. 4:20-24)።
ጳውሎስ የቀድሞውን የአህዛብ ኑሮአቸውን ከገለጸ በኋላ (ኤፌ. 4፡
17-19) “ስለ ክርስቶስ የተማራችሁት እንደዚህ አልነበረም” አይላቸውም።
ከዚህ ይልቅ “እናንተ ግን ክርስቶስን እንደዚህ አልተማራችሁም!” ይላቸዋል
(ኤፌ. 4:20)። ጳውሎስ ንግግር የሚያደርግላቸው ሰዎች “እንደሰሙት”
[ክርስቶስን] “ከእርሱ እንደተማሩ“ ወይም “በእርሱ እንደተማሩ“ በማስተዋል
“እውነት በኢየሱስ እንዳለ” (ኤፌ. 4:21) ከሚለው ሀረግ ጋር በክርስቶስ
የተቀረጸ ሕይወትን መቀበል እንደሚያስፈልግ ይናገራል። ለጳውሎስ ከክርስቶስ
ጋር የግል ግንኙነት በመፍጠር ወደ እምነት ማዕከሎች መምጣት “ክርስቶስን
መማር” ተብሎ እስከሚገለጽ ድረስ ግልጽና የሚታይ ነገር ነው። የተነሣውና
ከፍ ከፍ ያለው ኢየሱስ ሕያውና ከእኛ ጋር ያለ መሆኑን እናምናለን። በእርሱ
ትምህርቶችና ምሳሌ ስለተቀረጽን እንደ ሕያው አምላካችን ለእርሱ ታማኝነታችንን
እናሳያለን። በመንፈስና በቃል አማካኝነት ለእርሱ ምሪትና መመሪያ ሕይወታችንን
ክፍት እናደርጋለን።
ጳውሎስ በልብስ ምሳሌ ክርስቶስን የመሰለ ሕይወትን መቀበል ሶስት
ሂደቶችን እንደሚሻ ይነግረናል፡- (1) አሮጌውን የአኗኗር መንገድ “ማስወገድ”
ወይም ከአሮጌው የአኗኗር መንገድ መመለስ (ኤፌ. 4:22)፤ (2) ውስጣዊ
መታደስን መለማመድ (ኤፌ. 4:23)፤ እና (3) እግዚአብሔርን የሚመስለውን
አዲሱን የኑሮ ምሳሌ “መልበስ” (ኤፌ. 4:24) ናቸው። የጳውሎስ ዘይቤአዊ
አነጋገር በብሉይ ኪዳን ዘመን ልብስ የኃጢአተኝነት ምልክትና (ለምሳሌ፡- መዝ.
73:6፤ ዘካ. 3:3፣ 4፤ ሚል. 2:16) የድነት ምልክት ሆኖ እንደሚያገለግል
ያሳያል (ለምሳሌ፡- ኢሳ. 61:10፤ ሕዝ. 16:8፤ ዘካ. 3:4፣ 5)።
በጥንት ዘመን ወንዶች እንደ ውስጥ ልብስ እስከ ጉልበት የሚደርስ ሸማ
ይለብሱና ከጸሐይ እንዲከላከልላቸው መጎናጸፊያን ይደርቡ ነበር። በተመሳሳይ ሁኔታ
ሴቶች የውስጥ ልብስና ቀሚስ ይለብሱ ነበር። በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የተንጸባረቁ
ባህሎች በዚያ ዘመን የኖሩ ሰዎች መሰረታዊ ፍላጎት መገለጫ ናቸው። ልብሶች የከበሩና
ውድ ስለነበሩ ለረዥም ጊዜ እንዲያገለግሉ ተደርገው ይጠበቁ ነበር። ከአንድ ልብስ
በላይ ባለቤት መሆን ያልተለመደ ነበር። የእነዚያ ልብሶች ጥራትና ዓይነት የለባሹን
ማንነትና የኑሮ ደረጃ ያመለክቱ ነበር። የአንድን ሰው ልብስ መቀየር፣ አንዱን ዓይነት
ልብስ በሌላ ዓይነት መቀየር ያልተለመደና ወሳኝ ክስተት ነበር (ዛሬ በብዙ ባህሎች
ከሚሆነው አላስፈላጊ ክስተት በስተቀር)። ጳውሎስ በሕይወት የሚከሰት ለውጥ
በዚህ የመጀመሪያው ምዕተ ዓመት አውድ አንድን ዓይነት ልብስ ከሌላ ዓይነት ልብስ
ጋር የመቀየርን ያህል የሚታይ እንደሆነ ያስባል።
ስለ ክርስቶስ በመማርና ክርስቶስን ለማወቅ በመማር መካከል
ያለው ወሳኝ ልዩነት ምንድር ነው?
አማኞች ባልሆኑ ሰዎች መካከል የምንጠቀመውን ንግግር በተመለከተ ከጳውሎስ የምክር ቃላት መካከል አሁን ለእርስዎ እጅግ ወሳኝ (ጠቃሚ) የሆነው የትኛው ነው? ለምን? (ኤፌ. 4:25-29)።
ጳውሎስ በኤፌሶን 4፡25-32 ላይ በኤፌሶን 4፡25 ላይ የተብራራውን
ደስ የሚል የቃላት አጠቃቀም፣ (“ውሸትን አስወግዳችሁ”) የሚለውን አሉታዊ
ትዕዛዝ፣ ቀጥሎ ደግሞ (“እርስ በርሳችሁ ከጎረቤቶቻችሁ ጋር እውነትን
ተነጋገሩ”) የሚለውን አዎንታዊ ትዕዛዝ፤ ከዚያም ምክንያቱን (”እርስ በርሳችን
ብልቶች ሆነናልና”); የሚለውን በተደጋጋሚ ይጠቀማል። ይህ አባባል የአንድ
አካል ብልቶች ስለሆንን እንደ አካል ክፍሎች ከእርስ በርሳችን ጋር የተገናኘን
ነን የሚል ይመስላል። ጳውሎስ እውነትን እንድንናገር ያቀረበው ልባዊ ምክር
ብልሃት በሌለው መልክ እውነታዎችን በመድገም ሌሎች የቤተ ክርስቲያን
አባላትን እንድንጋፈጥ የቀረበ ግብዣ አይደለም። እውነትን ሰላምን ሊያሳድግ
በሚችል መልኩ ስለመናገር ዘካርያስ 8፡16 የሚመክረውን ጳውሎስ ይጠቅሳል።
በኤፌሶን 4:31 ላይ ጳውሎስ ቁጣንና የቁጣ ንግግርን እንድናስወግድ
የነገረን ሲሆን በኤፌሶን 4፡26 ላይ የተናገራቸው ቃላት በጉባኤ ውስጥ ቁጣን
እንድንለማመድ ፈቃድ አይሰጡም። ከዚህ ይልቅ ጳውሎስ ቁጣችንን መግለጽን
እንድንወስን ቢነግረንም ቁጣ የሚኖርበት እድል መኖሩን ያምናል። “ከተቆጣችሁ
ወደ ኃጢአትነት በማደግ ፍሬ እንዲያፈራ አትፍቀዱለት።“
ጳውሎስ “የሚሰርቅ (ሌባው) ከአሁን ወዲህ አይስረቅ”(ኤፌ.
4:28) ብሎ ስለ ሌቦች አሉታዊ ትዕዛዝ በመስጠት የንግግሩን ዋና ሀሳብ
የሚያቋርጥ ይመስላል። በአዎንታዊ መልክ ሲታይ ሌባው “ለተቸገረ ሰው
የሚያካፍለው ነገር እንዲኖረው” (ኤፌ. 4:28) በሚለው ምክንያት ላይ
ተመስርቶ “በገዛ እጆቹ መልካምን እየሰራ ይድከም” ይላል (ኤፌ. 4:28፤
1ኛ ቆሮ. 4:12፣ 1ኛ ተሰ. 4:11ን ይመልከቱ)። ጳውሎስ እነዚህን ስለ ሌባ
የተነገሩ ቃላትን የጨመረው ምናልባት በሐዋርያት ሥራ 5፡1-11 ላይ በተጻፈው
የሐናንያና ሰጲራ ታሪክ ላይ እንደተገለጸው በሌብነትና በአታላይ ንግግር መካከል
ካለው ግንኙነት የተነሣ ሊሆን ይችላል። ጳውሎስ በክርስቶስ በሚለውጥ ኃይል ላይ
ያለው እምነት እጅግ ጠንካራ ስለሆነ ሌቦች በጎ አድራጊዎች ሲሆኑ ይመለከታል።
ከዚያ በኋላ ጳውሎስ “ክፉ ቃል ከአፋችሁ ከቶ አይውጣ” (ኤፌ.
4:29) በማለት ያዛል። ይህ አባባል አጥፊ ቃላት፣ ለማቆም የማይቻል
በሚመስል መልኩ፣ ጎጂ ሥራቸውን ለመስራት ወደ ከናፍር የሚያደርጉትን ጉዞ
የሚያሳይ ነው። በአዎንታዊ መልኩ ጳውሎስ የሚያስበው ማንኛውንም አሉታዊ
ንግግር ዝም ብሎ ማቆም ሳይሆን የሚከተሉትን ሶስት መስፈርቶች በሚያሟላ
አረፍተ ነገር መተካትን ነው፡- (1) “ለማነጽ የሚጠቅም” (2) “ለአጋጣሚው
ገጣሚ የሆነ” እና (3) “ለሚሰሙት ጸጋን የሚሰጥ” (ኤፌ. 4:29)።.
ቃላቶቻችን በሙሉ የዚህ ዓይነት ቢሆኑ ምንኛ መልካም ነበር!
በክርስቲያን ማህበረሰብ ውስጥ ስለ ንግግር ኃጢአቶች ስንነጋገር መንፈስ ቅዱስ ከአማኞች ጋር ስለመኖሩ ጳውሎስ ምን ልባዊ ምክር ያጋራል? ኤፌ. 4:30።
ጳውሎስ አስፈሪ ማስጠንቀቂያንና ልብን የሚያሞቅ ተስፋን በተመሳሳይ
ጊዜ ይሰጣል። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ በእርስ በርሳችን ላይ የምንፈጽማቸው
ኃጢአቶች ከዚህ ግባ የማይባሉና ጉዳት የማያስከትሉ የስህተት ተግባራት
አይደሉም። መንፈስ ቅዱስን የሚያሳዝነው እግዚአብሔር የሰጠንን የንግግር ስጦታ
ሌሎችን ለማፍረስ መጠቀማችን ነው (ኤፌ. 4:25-27፣ 29፣ 3፣ 32)።
ጳውሎስ ኢሳይያስ 63፡10ን ማስተጋባቱ ከባድ ማስጠንቀቂያ መሆኑን እንዲህ
በማለት ያሰምርበታል፡- “እነርሱ ግን [እሥራኤል] ዐመፁ፣ ቅዱስ መንፈሱንም
አስመረሩ፤ ስለዚህ ተመልሶ ጠላት ሆናቸው፣ እርሱም ተዋጋቸው።”
እንደገና ማረጋገጫ በሰጠበት ተስፋው መንፈስ ቅዱስ አማኞችን ክርስቶስን
እንደ ግል አዳኛቸው አድርገው ከተቀበሉበት ቀን ጀምሮ እስከ “መዳን ቀን” (ኤፌ.
4:30) እንደሚያትማቸው ያረጋግጣል (ኤፌ. 1:13፣ 14)። መንፈስ ከአማኙ
ጋር ያለው ግንኙነት የሚቋረጥ ሳይሆን ዘላቂ ነው። አማኞች እግዚአብሔር የሰጣቸውን
የንግግር ስጦታ የጦር መሣሪያ በማድረግ የመንፈስ ቅዱስን በውስጣቸው ማደር
አልቀበል ሲሉ መንፈስ ትቶአቸው እንደሚሄድ ሳይሆን እንደሚያዝን ተገልጾአል።
መንፈስ ቅዱስ አማኞች እስከ ክርስቶስ መመለስ ድረስ የእግዚአብሔር ንብረት
እንደሆኑና ከእርሱ ጥበቃ እንደሚያገኙ በማድረግ ከእነርሱ ጋር ለመቆየት ይፈልጋል።
ጳውሎስ “የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ ” በማለት የመንፈስ ቅዱስን
ሙሉ መለኮታዊነት ያሰምርበታል፤ መንፈስ ቅዱስ እንደሚያዝን በማሳየትም
የመንፈስ ቅዱስን ግለሰብነት ያሰምርበታል። (ሮሜ. 8:16፣ 26፣ 27፤ 1ኛ ቆሮ.
2:10፣ 13፤ 1ኛ ቆሮ. 12:11፤ ገላ. 5:17፣ 18ን ደግሞ ይመልከቱ)።
የመለኮትን ምስጢር ስንነጋገር በጥንቃቄ መጓዝ ያስፈልጋል። መንፈስ
ከአብና ከወልድ ጋር አንድና የራሱ ልዩ ማንነት ያለው ነው። “መንፈስ የራሱ ፈቃድ
ያለውና በዚህ መሰረት ምርጫ የሚያደርግ ነው። መንፈስ ቅዱስ ሊያዝንና ሊሰደብ
ይችላል። እነዚህ መግለጫዎች ዝም ብሎ ለኃይል ተጽእኖ ገጣሚ መግለጫዎች
አይደሉም፣ ነገር ግን የሰው (ግለሰብ) ባህርያት ናቸው። ስለዚህ መንፈስ ቅዱስ
እንደ እኔና እንደ እናንተ ሰው ነው ማለት ነው? አይደለም፣ መለኮትን ለመግለጽ
ውስን የሆኑ ሰብአዊ ቃላቶችን የምንጠቀም ሲሆን መንፈስ ቅዱስ ሰብአዊ ፍጡራን
በፍጹም መሆን የማይችሉት ነገር ነው።”-Paul Petersen, God in
3 Persons-In the New Testament (Silver Spring,
MD: Biblical Research Institute, 2015), p. 20.
“የእግዚአብሔር ቅዱስ መንፈስ” ድርጊቶቻችን እስኪጎዱት ድረስ ከእኛ
ጋር የቅርብ ግንኙነት በመፍጠር እንደሚኖር ተነግሮአል። እስከ ፍጻሜ ዘመን
ድረስ ከሚያትመን ጋር ዘላቂ ግንኙነት እንዲኖረን ከተሰጠን የመለኮት አባል ጋር
ሕይወትን እንጋራለን። ለዚህ አስደናቂ እውነት የእኛ የእምነት ምላሽ ምን ይሆን?
ጳውሎስ “የመዳን ቀን” (ኤፌ. 4:30) የሚለውን በመጥቀስ
አንባቢዎቹ ከክርስቶስ ዳግም ምጻት አውድ ስለ ንግግራቸው እንዲያስቡበት
ጋብዞአቸዋል። ስለዚህ ኤፌሶን 4፡31፣ 32 ሊስተዋል የሚችለው ወደዚያ ታላቅ
ክስተት ስንቃረብ ስለምንጠቀመው ንግግር እንደሚናገር ተደርጎ ነው።
በክርስቶስ መመለስ ብርሃን ከንግግር ጋር የተገናኙ መወገድ ያለባቸው
አመለካከቶችና ባህርያት ምንድር ናቸው? መታቀፍ ያለባቸው
አመለካከቶችና ባህርያትስ ምንድር ናቸው? ኤፌ. 4:31፣ 32።
ጳውሎስ በኤፌሶን 4፡17-32 ላይ ባቀረበው የመጨረሻው ልባዊ ምክር
ውስጥ በድጋሚ አሉታዊ ትዕዛዝ ያቀረበ ሲሆን “ከእናንተ መወገድ አለባቸው”
ያላቸውን ስድስት መጥፎ ምግባሮች ለይቶ ይጠቅሳል (ኤፌ. 4:31)፤
አዎንታዊ ትዕዛዝ ደግሞ ቸሮች፣ ርኅሩኆችና ይቅር ባዮች እንዲሆኑ የሚገልጽ
ሲሆን (ኤፌ. 4:32) ለዚህም ምክንያቱን ይሰጣል። አማኞች “እግዚአብሔር
በክርስቶስ ይቅር እንዳላችሁ” እርስ በርሳችሁ ይቅር መባባል አለባችሁ(ኤፌ.
4:32)። የስድስቱ መጥፎ ምግባሮች ዝርዝር የሚጀምረውና የሚያበቃው
አጠቃላይ በሆነ ሀሳብ ሲሆን ሁሉንም የሚያካትቱ ቃላት ናቸው። እነርሱም
“መራርነትን ሁሉ” እና “ክፋትን ሁሉ” የሚሉ ናቸው። በመካከል አራት
ተጨማሪ ቃላቶች ገብተዋል። እነርሱም “ንዴት፣” “ቁጣ፣” “ጩኸት፣” እና
“መሳደብ” ናቸው(ኤፌ. 4:31)።
ከእነዚህ መካከል የመጨረሻው በግሪክ ብላስፌሚያ ከሚል ቃል
የተተረጎመ ሲሆን እንግሊዝኛው በእግዚአብሔር ላይ በንዴት መናገርን የሚገልጽ
ቴክኒካዊ ቃል አድርጎ ተውሶታል። ነገር ግን የግሪኩ ቃል የእግዚአብሔርን ወይም
የሰውን ስም የሚያጎድፈውን ንግግር “መሳደብ” ወይም “ክፉ መናገር”
በማለት ይለየዋል። በዝርዝሩ ውስጥ አመለካከቶች (መራርነት፣ ንዴትና ቁጣ)
ወደ ቁጡ ንግግር (ጩኸትና ስድብ) የሚገነፍሉ ይመስላሉ። በመሠረታዊነት
ጳውሎስ የክርስቲያን ንግግርን ከጦረኝነት እንዲላቀቅ ያደርጋል። የቁጣ ንግግርንና
በአሽሙር የመናገር ስልቶችን የሚቀሰቅሱ አመለካከቶች ከክርስቲያን የጦር
መሣሪያ ውስጥ መወገድ አለባቸው። የክርስቲያን ማህበረሰብ የሚያድገውና
የቤተ ክርስቲያን አንድነት የሚጠነክረው እነዚህ ነገሮች በተተውበት ቦታ ብቻ
ነው (ኤፌ. 4፡1-16 ጋር ያነጻጽሩ)።
ክፉ ንግግር የመተካትን ያህል ብዙ አይታፈንም። በክርስቶስ ቤተሰብ
መካከል እና ከዚያም ባሻገር ንግግሮቻችንና ተግባሮቻችን ከቁጣ የመነጩ መሆን
የለባቸውም፤ ነገር ግን በደግነት፣ በገርነትና እጅግ ከፍ ባለ መስፈርት መሰረት
በይቅርታ የተነሳሱ መሆን አለባቸው። ይህም ይቅርታ እግዚአብሔር በክርስቶስ
አማካይነት ለእኛ የሰጠን ይቅርታ ነው (ኤፌ. 4:32)። ጳውሎስ “አምዳዊ
(ወደላይ የሚያመለክት) ይቅርታን” (እግዚአብሔር ለእኛ የሰጠውን)
“ለአግድማዊ ይቅርታ” (እኛ ለእርስ በርሳችን ለምንሰጠው ይቅርታ) እንደ
ምሳሌ ይጠቀማል። (ከቆላ. 3:13፤ ማቴ. 6:12፣ 14፣ 15 ጋር ያነጻጽሩ)።
ስለ ቃሎቻችሁ ኃይል አስቡ። ሌሎችን ከፍ ከፍ ለማድረግ፣
ለማበረታታትና እምነትን ለማነጽ መጠቀም የምትችሉአቸው
እንዴት ነው?
“የንግግራችሁ ጠባይ ንስሃ መግባት የማያስፈልጋችሁ
ዓይነት ይሁን። ‘ለቤዛ ቀን የታተማችሁበትን የእግዚአብሔርን ቅዱስ መንፈስ
አታሳዝኑ።’ . . . በልባችሁ ፍቅር ካለ ወንድማችሁን እጅግ ቅዱስ በሆነ እምነት
ለመመስረትና ለመገንባት ትሻላችሁ። ለወንድማችሁ ወይም ለጓደኛችሁ ጎጂ የሆነ
ቃል ከአፋችሁ ወጥቶ ከሆነ ይህን ክፉ ንግግር አታደፋፍሩ። ይህ የጠላት ሥራ
ነው። የእግዚአብሔር ቃል እንደዚህ ዓይነቱን ንግግር እንደሚከለክል ለተናጋሪው
በትህትና አስታውሱት። ”-Ellen G. White, Advent Review
and Sabbath Herald, June 5, 1888.
እርስዎና እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል ከዚህ ቀጥለው የተዘረዘሩት
ዓይነት ዓረፍተ ነገሮች ያሉበትን መሃላ ብትፈጽሙና ብትኖሩበት ኖሮ ጉባኤዎ
እንዴት ይለወጥ ነበር?
1. ተጽእኖዬ በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥና ባሻገር
አዎንታዊ፣ ከፍ የሚያደርግ፣ እምነትን የሚያንጽና ሞራልን የሚያነሳሳ
እንዲሆን እመኛለሁ። (ኤፌ. 4:29)።
2. ክርስቶስ ለአንድነትና ለፍቅር ያቀረበውን ጥሪ በማስታወስ
ስህተተኞች እንደሆኑ በማምናቸው ሰዎች ውድቀቶች ላይ ጣቴን
ከመቀሰር ይልቅ ጥሩ እንደሆኑ የማምንባቸውን ነገሮች እያደረጉና
እየተናገሩ ያሉ ሰዎችን ትክክለኛነት ለማጽናት ብዙ ጉልበት
አወጣለሁ። (ዮሐ. 13:34፣ 35፤ ዮሐ. 17:20-23፤ ኤፌ.
4:1-6፤ 1 ተሰ. 5:9-11)።
3. ከሆነ ሰው ጋር በማልስማማበት ጊዜ እንደ እኔው አማኝ ለሆነው ሰው
ያለኝን አክብሮት ግልጽ አደርጋለሁ። ለክርስቶስ ያለውን/ያላትን
ታማኝነትና መሰጠት እቀበላለሁ። የልዩነት ሀሳቤን በጩኸትና በጠንካራ
ቃላት ሳይሆን በጨዋነት አቀርባለሁ። (ኤፌ. 4:31፣ 32)።
4. የክርስቶስን መመለስ እየጠበቅኩ ሳለሁ የቤተ ክርስቲያን አባላትን
ለማነጽና ለማጽናት የሚያስችለውን እያንዳንዱን መልካም አጋጣሚ
በመፈለግ በደስታ እኖራለሁ። (ኤፌ. 4:29፣ 30፤ ገላ. 6:2፤
ዕብ. 10:24፣ 25)።
1. የሥላሤ ሶስቱ አካላት ለሰብአዊ ዘር ድነት በቅርበት
አብረው እንደሚሰሩ ጳውሎስ የገለጸባቸውን 11 ጊዜያት
ይከልሱ። ይህ ተደጋግሞ አጽንዖት መሰጠቱ ስለ ሥላሤ
ስላለን መረዳት መረጃ የሚሰጠው እንዴት ነው? ኤፌ.
1:3-14፣ ኤፌ. 1:15-23፣ ኤፌ. 2:11-18፣ ኤፌ.
2:19-22፣ ኤፌ. 3:1-13፣ ኤፌ. 3:14-19፣ ኤፌ.
4:4-6፣ ኤፌ. 4:17-24፣ ኤፌ. 4:25-32፣ ኤፌ.
5:15-20፣ ኤፌ. 6:10-20 (ኤፌ. 6:10፣ “ጌታ” ወደ
ክርስቶስ የሚያመለክትበት ቦታ)።
2. ጳውሎስ ስለ ክርስቲያን ንግግር የሰጠው ምክር (ኤፌ.
4፡25-32) ብዙ ጊዜ ለሳይበር ማስፈራራትና ማንነቱ
ለማይታወቅ ለበየነ-መረብ ገጸ-ባህርይ ግድያ እጅግ ጥቅም
ላይ በሚውልበት “በኮምፒዩተር በተደገፈ የተግባቦት
ዘመን” የሚሰራው እንዴት ነው?