የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሐምሌ 29 - ነሐሴ 5

7ኛ ትምህርት

Aug 5 - 11




የተዋሃደው የክርስቶስ አካል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 4፡1-16፤ ፊል. 2፡3፤ መዝ. 68፡ 18፤ ሐዋ. 2፤ 1ቆሮ. 12፡4-11፣ 27-30፤ ኢሳ. 5፡4


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “አንዳንዶቹ ሐዋርያት፣ አንዳንዶቹ ነቢያት፣ አንዳንዶቹም ወንጌል ሰባኪዎች፣ ሌሎቹ ደግሞ እረኞችና አስተማሪ ዎች ይሆኑ ዘንድ የሰጠ እርሱ ነው፤ ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት” ነው (ኤፌ. 4፡11-12)።

ከኤሶፕ ተረቶች አንዱ “ሆድ እና እግሮች” በሚል ርዕስ ይታወቃል። ታሪኩ ይህን ይመስላል፡ “ሆድ እና እግሮች፣ እኔ ይበልጥ አስፈላጊ ነኝ እያሉ እርስ በርስ ይሟገቱ ነበር። እግሮች--እኛ በጣም ጠንካሮች ከመሆናችን የተነሣ ሆድን እንኳ የሚያህል ነገር ተሸክመን እንዞራለን እያሉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ የሰማው ሆድ ፡“እናንት መልካም ወዳጆቼ፣ እኔ ምግብ ባልወስድ ኖሮ ምንም ነገር መሸከም ባልቻላችሁ ነበር’ አለ ይባላል። ”-Lloyd W. Daly, Aesop Without Morals (New York: Thomas Yoseloff, 1961), p. 148.

ጳውሎስ ስለ መንፈሳዊው ነገር ሊያጋራ ለፈለገው ነጥብ፣ የሰውን አካል በምሳሌነት ሲጠቀም ይታያል። ለጳውሎስ--ሰብዓዊው አካል እንዲሁም የክርስቶስ አካል የሆነችው ቤተ ክርስቲያን--በልዩ ልዩ ዓይነት ብልቶች እና ችሎታዎች የተዋቀሩ ቢሆኑም፣ አካል ጤናማ ይሆን ዘንድ ሁሉም ተቀናጅተው በአንድነት መሥራት ይኖርባቸዋል። ጳውሎስ ቀደም ሲል በኤፌ. 4፡1-16 የሰውነት አካልን በጥሩ ሁኔታ በምሳሌ የተጠቀመበትን ሁናቴ፣ እንደገና በጽሑፉ አስፍሯል (ሮሜ. 12፡3-8፣ 1ቆሮ. 12፡12-31)። ክርስቶስ አሁን የአካሉ ራስ እንደመሆኑ፣ የዚህ አካል አንድነት እንዲጠበቅ የሚያግዙ “ስጦታ” ያላቸውን ሰዎች የሚያቀርብ ሲሆን፣ በዚህም እያንዳንዱ የቤተ ክርስቲያን አባል የየግል ችሎታ አስተዋጽዖውን ለአጠቃላዩ አካል ይለግሳል።

ጳውሎስ ያቀረበው ጤናማና የተዋሃደ አካል ምስል፣ እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ዓላማ ማስተዋል እንድንችል የሚረዳን ሲሆን፡ ይኸውም በክርስቶስ የተዋሃደ ፍሬያማ ቤተ ክርስቲያን አካል እንሆን ዘንድ ነው።

ሐምሌ 30
Aug 06

የመንፈስ አንድነት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 4፡1-16። ጳውሎስ አማኞች የቤተ ክርስቲያንን አንድነት እንዲያሳድጉ ያበረታታቸው እንዴት ነው?



ጳውሎስ የኤፌሶንን መጽሐፍ ሁለተኛ አጋማሽ (ምዕ. 4-6) የሚጀምረው አማኞች በሁለት ዋና ዋና ክፍሎች ሕብረት እንዲኖራቸው በሚቀሰቅስ ጥሪ ነው። በመጀመሪያ በኤፌ. 4፡1-6 አማኞች ሕብረትን የሚገነቡ በጎ ምግባሮች በማሳየት “የመንፈስን አንድነት” እንዲያሳድጉ የሚጠይቃቸው ሲሆን (ኤፌ. 4፡1-3)፣ ጥሪውን ያቀረበው ለሰባት ጊዜ ያህል “አንድ” የሚለውን ቃል በተደጋጋሚ ባሰፈረበት (ኤፌ. 4፡4-6) የግጥም ለዛ ባለው የአጻጻፍ ስልት ነው። ሁለተኛ፡ በኤፌ. 4፡7-16 ጳውሎስ ድል አድራጊውንና የከበረውን የኢየሱስን ወንጌል ለማካፈል (ኤፌ. 4፡7-10) ወደፊት ለሚገሰግሱ የጸጋ ምንጭ አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን፤ እነዚህ በአንድነት ከመላው የቤተ ክርስቲያን አባላት ጋር ለቤተ ክርስቲያን ጤንነት፣ ዕድገት እና ለክርስቶስ አካል ሕብረት (ኤፌ. 4፡11-16) ስለሚያደርጉት አስተዋጽዖ ይገልጻል።

ጳውሎስ ለክርስቲያኖች በሚያቀርበው ጥሪ ምዕራፉ ይጀምራል፡ “ለተቀበላችሁት ጥሪ የሚገባ ኑሮ ትኖሩ ዘንድ እለምናችኋለሁ” (ኤፌ. 4፡ 1)። “ትኖሩ ዘንድ” ወይም “ትመላለሱ ዘንድ” (1962 ትርጉም) የሚሉት ቃላት መልካም ምግባር ይኑራችሁ የሚል አንደምታ አለው (ኤፌ. 2:2፣ 10፤ ኤፌ. 4:17፤ ኤፌ. 5:2፣ 8፣ 15)። ጳውሎስ ስለ ተቀበሉት ጥሪ መናገሩ፣ የክርስትና እምነት ጥሪን ያመለክታል (ኤፌ. 1:18፤ ኤፌ. 2:4-6፣ 13)።

ጳውሎስ አማኞች የእግዚአብሔርን የመጨረሻ እቅድ የሚያንጸባርቀውን፣ አንድ የሚያደርጋቸውን ባህሪ ይለማመዱ ዘንድ ያሳስባል (ኤፌ. 4፡9፣ 10)። ለዚያ አጽንኦት መስጠት የሚጀምረው እንደ ትህትና፣ ገርነት እና ትዕግሥት ዓይነት ወደ አንድነት የሚመሩ በጎ ምግባሮችን እንዲለማመዱ ባቀረበው ጥሪ ነው (ኤፌ. 4፡1-3)።

እስቲ እያንዳንዱን ቃል እንመልከት፡-

ጳውሎስ በኤፌ. 4፡2 የተጠቀሰውን ትሑታን የሚለውን ቃል በሌላ ቦታ “ከራስ ይልቅ ሌሎችን የተሻለ አድርጎ መቁጠር” (ፊልጵ. 2፡3) ሲል ያብራራዋል። ስለዚህ ትሕትና ስለ ራስ አሉታዊ አመለካከት መያዝ ሳይሆን (ቆላ. 2፡18፣23)፣ ሌሎችን የማድነቅና የማገልገል አዎንታዊ ተግባር ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል። ገርነት፡ (ኤፌ. 4:2) ደግሞ--“ደግነት፣ ጨዋነት፣ አሳቢነት፣ የዋህነት ተብሎ ሊገለጽ ይችላል።”-Frederick Danker, ed., Greek-English Lexicon of the New Testa- ment and Other Early Christian Litera- ture, 3rd ed. (Chicago: University of Chicago Press, 2000), p. 861. ትዕግሥት፡ ሊያስቆጣ በሚችል ሁናቴ ወይም በመከራ ውስጥ ታግሶ ማለፍ ማለት ነው። እነዚህ ባሕርያት፡ ከራስ ወዳድነት ርቆ በምትኩ ለሌሎች በጎ በሆኑ ነገሮች ላይ ማተኮር የሚል ጭብጥ ይዘዋል።

ትሑትነት፣ ገርነት፣ ትዕግሥት። እነዚህ ባህሪያት እንደ ሕዝብ እንዴት አንድ እንድንሆን እንደሚረዱን ያስቡ። እነዚህን መልካም ምግባሮች ማዳበር የምንማረው እንዴት ነው?

ነሐሴ 1
Aug 07

አንድ በሆነው በእርሱ እንደ አንድ መሆን


ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያንን አንድነት አስመልክቶ የሰጠውን ጭብጥ ለመደገፍ የተጠቀሱት ሰባቱ “አንድ” ምንድን ናቸው? በዚህ ዝርዝር ለማሳየት የፈለገው ነጥብ ምንድን ነው? ( ኤፌ. 4:4-6)



ጳውሎስ “አንድ” የተሰኘውን ቃል ሰባት ጊዜ የዘረዘረበት የግጥም ይዘት ያለው አቀራረብ፣ በኤፌሶን ጥቅም ላይ የዋለውን አዎንታዊ የመዝሙር ስልት ሊያስተጋባ ይችላል። ዝርዝሩ የሚጀምረው ሁለቱን “አንድ” በአንድ ላይ በመጥቀስ ነው፡--“አንድ አካል” (ቤተ ክርስቲያንን እንደ ክርስቶስ አካል በመጥቀስ፡ ኤፌ. 4:12፣ 16፤ ኤፌ. 1:23፤ ኤፌ. 5:23፣ 29-30) እና “አንድ መንፈስ” (ኤፌ. 4፡4)። ሦስተኛው፡ “ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ” (ጥቅሶቹን ያስተያዩ--ፌ. 4፡4፤ ኤፌ. 4፡1)።

ከዚያም ዝርዝሩ ሦስት ተጨማሪ አካላትን ያቀርባል፡ “አንድ ጌታ” (የክርስቶስ ማጣቀሻ)፣ “አንድ እምነት” (ማለትም የክርስቲያኖች እምነት ይዘት፣ ኤፌ. 4:13፤ ቆላ. 1:23፤ ቆላ. 2:7፤ ገላ. 1:23፤ 1ጢሞቴ. 4:1፣ 6) እና “አንድ ጥምቀት” (ከኤፌ. 5:26 ጋር ያወዳድሩ)፣ ይህን የሚያደርጉት “ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ” (ኤፌ. 4፡6) በሚል ሰፊ መግለጫ ከመደምደሙ በፊት ነው።

ጳውሎስ እግዚአብሔር አብን በግጥም ስልት በገለጸበት በዚህ ጽሑፉ ምን እያለ ነው? እግዚአብሔር “የሁሉም አባት” የመሆን ባህሪ ስለተላበሰ ፈጣሪ አምላክ ነው። የተቀረው ዓረፍተ ነገር ዓለም አንዴ ከተፈጠረ በኋላ፣ እግዚአብሔር ከፈጠረው “ሁሉም” ነገር ጋር እንዴት እንደሚዛመድ ይገልጻል። እዚህ ላይ ጳውሎስ ፓንቴይዝም (ተፈጥሮን ከእግዚአብሔር ጋር በአንድ የሚመለከት) የስህተት አስተምህሮ ውስጥ እጁን እያስገባ አይደለም። ይልቁንም ሉዓላዊ (“ከሁሉም በላይ”) ባህሪ ያለውን፣ ንቁ ሚና (“በሁሉም የሚሠራውን”) የሚጫወተውን ግዙፍ አምላክ (“በሁሉ የሚኖር”) እያወጀ ነው።

የቤተ ክርስቲያን ኅብረትን አስመልክቶ ሁለት ጽንሰ ሀሳቦችን በጥንቃቄ ይመልከቱ (ኤፌ. 4፡1-6)። በመጀመሪያ፣ አንድነት በእነዚህ ሰባት “አንድ” ላይ የተመሠረተና ከፍ ተደርጎ ሊታይ የሚገባ መንፈሳዊ እውነታ ነው (ኤፌ. 4፡ 4-6)። ሁለተኛ፡ አንድነቱ ይህን እውነታ ለመንከባከብ እና ለማሳደግ ያለንን ቅንዓት ይጠይቃል (ኤፌ. 4፡3)። ይህንን አንድነት እውን ለማድረግ፣ በድክመቶቻችን ልናነባ የምንችልባቸው ምክንያቶች ይኖራሉ። የሆነው ሆኖ፣ የቱንም ዓይነት ወድቀት ቢደርስብን እንኳ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ በሚሠራው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ኅብረት የመፍጠር ሥራ እና “የመንፈስ አንድነት” (ኤፌ. 4፡3) ሥነ መለኮታዊ እውነታ ሐሴት ማድረግ ይኖርብናል። ይህን ማድረጋችን ኅብረቱ ወደሚገሰግስበት ከባድ ሥራ መለስ የምንልበትን ጉልበት የሚሰጠን ሲሆን፣ በዚህም በታደሰ እምነት የእግዚአብሔርን ሥራ ከታቀደለት ግብ እናደርሳለን።

ጥቅሶቹን በድጋሚ ያንብቡ፡ ኤፌ. 4፡4-6። ምን ዓይነት ስሜት ፈጠረብዎ? በክርስቶስ በኩል ከእግዚአብሔር ጋር የሚኖረን አንድነት ምን እንደሚል ማወቅዎ ምን ዓይነት ስሜት ሊፈጥርብዎ ይገባል?

ነሐሴ 2
Aug 08

የከበረው ክርስቶስ፣ የስጦታዎች ሰጪ


“በተጠራችሁ ጊዜ ወደ አንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ ሁሉ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ፣ አንድ እምነትና አንድ ጥምቀት አለ፤ ከሁሉም በላይ የሆነ፣ በሁሉም የሚሠራ፣ በሁሉ የሚኖር የሁሉም አባት የሆነ አንድ አምላክ አለ።

ነገር ግን ክርስቶስ በወሰነው መጠን ለእያንዳንዳችን ጸጋ ተሰጥቶናል። ስለዚህም እንዲህ ይላል፤ ‘ወደ ላይ በወጣ ጊዜ፣ ምርኮ ማረከ፤ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ።’ ታዲያ፣ ‘ወደ ላይ ወጣ’ ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው? ወደ ታች የወረደውም፣ መላውን ፍጥረተ ዓለም ይሞላ ዘንድ ከሰማያት ሁሉ በላይ የወጣው እርሱ ራሱ ነው።” (ኤፌ. 4፡7-10)። በዚህ ስፍራ እየሆነ ያለው ምንድን ነው? ጳውሎስ ጥቅሶቹን ተጠቅሞ ሊያመላክት የፈለገው ነገር ምንድን ነው?



እዚህ ላይ ጳውሎስ ከመዝ. 68:18 እንደጠቀሰ እንመለከታለን፡ “ወደ ላይ ዐረግህ፤ ምርኮ አጋበስህ፤ እግዚአብሔር አምላክ ሆይ፤ አንተ በዚያ ትኖር ዘንድ፣ ከዐመጸኞችም ሳይቀር፣ ከሰዎች ስጦታን ተቀበልህ።” መዝሙረ ዳዊት 68፡18 ጌታ ማለትም ያሕዌ እንደ ድል አድራጊ የጦር አዛዥ ጠላቶቹን ድል አድርጎና ምርኮውን አስከትሎ ዋና ከተማው ወደ ተመሠረተችበት ከፍታ እንደወጣ ይስላል (መዝ. 68:1-2 )። ከዚያም ድል ከተነሱ ጠላቶቹ ግብር (“ስጦታን ተቀበልህ”) ይሰበስባል።

የመዝሙር 68፡18 ቅደም ተከተል ይዘን የምንሄድ ከሆነ ማረጉ-- የክርስቶስ ወደ ሰማይ መውጣት (ኤፌ. 1፡21-23) በመጀመሪያ የሚከሠት ሲሆን፣ ከዚያም ወደ ታች በመውረድ፣ የተነሣውና የከበረው የሱስ ስጦታ መስጠቱና መላውን ፍጥረተ ዓለም መሙላቱ ተወስቷል። ይህ መንፈስ ቅዱስ በጴንጤቆስጤ የፈሰሰበትን ጳውሎስ የገለጸበት መንገድ ነው (ሐዋ. ምዕ. 2)። ይህ አመለካከት በኤፌ. 4: 11-12 የጸና ሲሆን፣ ይኸውም ከፍ ከፍ ብሎ በከበረው የሱስ የተሰጡትን ስጦታዎች እንደ መንፈስ ስጦታዎች የሚገልጽበት ነው።

“ክርስቶስ ወደ ላይ ባረገ ጊዜ፣ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታዎችን ሰጠ። ከክርስቶስ ዕርገት በኋላ፣ መንፈስ በተገባው ቃል መሠረት ሲወርድ፣ እንደ ድንገተኛ፣ ኃይለኛ ነፋስ፣ ደቀ መዛሙርቱ የተሰበሰቡበትን ቦታ ሁሉ ሲሞላው፣ ውጤቱ ምን ነበር? በአንድ ቀን ብቻ በሺዎች የሚቆጠሩ ተለወጡ።”-Ellen G. White, Ye Shall Receive Power, p. 158. እነዚህ በኤፌሶን መልእክት ውስጥ የሚገኙ ጥቅሶች የቱንም ያህል ጥልቅ ቢሆኑም፣ ክርስቶስ ለእኛ ካደረገልን እና እንደሚያደርግልን ከሚያሳዩት ነገሮች መጽናናት ማግኘትን መማር የምንችለው እንዴት ነው--በተለይ “ሁሉን ነገር በሁሉም ረገድ የሚሞላ” (ኤፌ. 1:23) ከመሆኑ አኳያ?

ነሐሴ 3
Aug 09



በሰማያዊው ስፍራ የከበረው የየሱስ ስጦታዎች


ጳውሎስ ከመዝ. 68፡18 በመውሰድ--የተነሣው፣ የከበረውና ድል ያደረገው የሱስ በላይ በከፍታ ሆኖ ለሕዝቡ ስጦታ መስጠቱን ይገልጻል። በከበረው የሱስ የተሰጡት “ስጦታዎች” ምን ነበሩ? ለምን ዓላማ ተሰጡ? ኤፌ. 4፡11-13።



ጳውሎስ የከበረው የሱስ ለቤተ ክርስቲያኑ የሰጠው ውድ ሀብት አካል የሆኑትን “ሰጦታ” የተቀበሉ አራት ቡድኖች ያስቀምጣል፡ (1) ሐዋርያት (2) ነቢያት (3) ወንጌላውያን (4) እረኞችና መምህራን። (የግሪኩ ሃረግ አወቃቀር እነዚህ አንድ ቡድን መሆናቸውን ይጠቁማል።) ክርስቶስ እነዚህን ስጦታዎች የሰጠው አስፈላጊ የሆነ ሥራ ለማከናወን ሲሆን፡ “ይኸውም የክርስቶስ አካል ይገነባ ዘንድ፣ ቅዱሳንን ለአገልግሎት ሥራ ለማዘጋጀት” እና “ሁላችንም የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኘው አንድነት በመምጣትና ሙሉ ሰው በመሆን፣ በክርስቶስ ወዳለው ፍጹምነት ደረጃ እስከምንደርስ ነው” (ኤፌ. 4፡12-13)።

ይህ የመጨረሻው ነጥብ የኤለን ጂ ዋይትን መንፈሳዊ ስጦታዎች እያሰላሰሉ ለነበሩት የመጀመሪያዎቹ የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ልዩ ጠቀሜታ ነበረው።

መጽሐፍ ቅዱስ የትንቢት ስጦታ በቤተ ክርስቲያን ለመሥራቱ ሕጋዊ እውቅና የሚሰጠው ለሐዋርያት ዘመን ብቻ ነው? ወይስ ስጦታው እስከ ክርስቶስ ምጽአት ድረስ ይቀጥላል? የጥንቶቹ የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች መልሱን በኤፌ. 4፡ 13 ላይ አግኝተው፣ ለጉዞ የተሰጠውን መመሪያ ይከተል ስለነበረው የመርከብ መሪ የሚተርከውን ታሪክ አካፍለዋል። መርከቧ ወደ ወደብ ስትቃረብ፣ መርከቧን ለመምራት የሚረዳ አንድ አብራሪ የሚመጣ መሆኑን ካፕቴኑ በአንዳንድ መመሪያዎች አማካይነት ተረዳ። ከመጀመሪያዎቹ መመሪያዎች ጋር በታማኝነት መጽናት ይችል ዘንድ፣ አብራሪውን ማሳፈርና የሚሰጠውን ተጨማሪ መመሪያ ለመታዘዝ ፈቃደኛ መሆን ነበረበት። አሁን ለዚያ የቀደመ እውነተኛ አቅጣጫ ጠቋሚ መጽሐፍ ትኩረት የሚሰጥ ማን ነው? ፓይለቱን የሚቃወሙ ወይስ መጽሐፉ በሚያዘው መሠረት እርሱን የሚቀበሉ? ፍርድዎን ይስጡ።”-Uriah Smith, “Do We Discard the Bible by Endorsing the Visions?” Review and Herald, January 13, 1863, p. 52.

እነዚህን ኃላፊነቶች የምናገናዝበው ከራሳችን አውድ እና ጊዜ አኳያ እንደመሆኑ “እረኞችን” (ወይም “ፓስተሮችን”)፣ “መምህራንን” እና “ወንጌላውያንን” ስንለይ ጥንቃቄ ማድረግ ይኖርብናል። መወሰን የምንችለውን ያህል መሄድ ቢኖርብንም፣ በጳውሎስ ዘመን እነዚህ ሁሉ የኤፌሶንን ቤተ ክርስቲያን የሚያገለግሉ የፈቃደኛ ወንጌላውያን መሪዎች በሆኑ ነበር (1ጴጥ. 2፡9፣ ሐዋ. 2፡46፣ ሐዋ. 12፡12)።

ጥቅሱን ያንብቡ፡ ኢሳ. 5፡4 “ከዚህ ካደረግሁለት በላይ ለወይኔ ቦታ ምን ሊደረግለት ይገባ ነበር? እግዚአብሔር በኤለን ጂ. ኋይት አገልግሎት ከሰጠን አውድ አኳያ ስለዚህ ጥቅስ ያስቡ። እንዴት ጥቅም ላይ ይውላል?

ነሐሴ 4
Aug 10

በክርስቶስ ማደግ


የክርስቶስን የሚመስለውን የቤተ ክርስቲያን ብስለት አደጋ ላይ የሚጥለው ምንድን ነው? ኤፌ. 4፡14?



ጳውሎስ ከእኛ በተለየ መንገድ በአማኞች ላይ ሊበረታ የሚችለውን እንደ “ልዩ ልዩ ዓይነት የትምህርት ነፋስ” እና “ረቂቅ ተንኮል” ተገንዝቧል። የአፈንጋጭ ሥነ መለኮታዊ አስተምህሮ አደጋዎችን ለመግለጽ የሦስት ገጽታዎችን ስብስብ ይጠቀማል፡ (1) አለመብሰል፡ “ወዲያና ወዲህ እየተንገዋለልን ሕፃናት አንሆንም።” (2) ባሕር ላይ ሊደርስ የሚችል አደጋ፡ “በማዕበል ወደ ፊትና ወደ ኋላ እየተነዳን” (3) እንደ ቁማርተኞች ባሉ አፈ ጮሌዎች እንዳይጭበረበሩ። “መታለል” እንዳይደርስባቸው።

ጳውሎስ መከፋፈል የስሕተት ዋነኛ ምልክት እንደሆነ ያምናል። አካልን የሚመግብና የሚያሳድግ እንዲሁም በአንድ እንዲተሳሰሩ የሚረዳ መልካም ነው፤ የሚያጠፋውና የሚከፋፍለው ግን ክፉ ነው። ፊታቸውን ከከፋፋይ ትምህርት ወደ ተፈተኑና የታመኑ መምህራን የሚመልሱ፣ (ኤፌ. 4:11) ወደ እውነተኛ ክርስቲያናዊ ጉልምስና ያድጋሉ፣ እንዲሁም በክርስቶስ አካል ውስጥ ውጤታማ ሚና ይጫወታሉ (ኤፌ. 4:12-13፤ ኤፌ. 4:15-16)።

ጤናማዋ ቤተ ክርስቲያን እንደ ጤናማ አካል የምትሠራው በምን መንገዶች ነው? ኤፌ. 4:15-16





በኤፌ. 4፡1-16፣ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት ጥብቅና በመቆም የመልእክቱ አንባቢ ተግባሩን በንቃት ወደፊት ያራምድ ዘንድ ያሰማራል። ኀብረት በመለኮት የተሰጠ የተረጋገጠ ተስፋ ቢሆንም (ኤፌ. 4፡4-6) የእኛን ጠንካራ ሠራተኝነት ይጠይቃል (ኤፌ. 4፡3)። ኅብረትን የምናጎለብትበት አንዱ መንገድ ንቁ የክርስቶስ አካል “ክፍሎች” በመሆን ነው (ኤፌ. 4፡7-16)። እያንዳንዳችን የአካሉ ክፍሎች እንደመሆናችን ለዚህ አካል ጤናማነትና እድገት አስተዋጽኦ ማድረግ አለብን (ኤፌ. 4:7፣16)። እንዲሁም ሁላችንም ከሐዋርያት፣ ከነቢያት፣ ከወንጌላውያን እና ከመጋቢ መምህራን አልግሎት ተጠቃሚዎች መሆን ይኖርብናል (ኤፌ. 4፡11)። እያንዳንዱ አገናኝ ጅማት እና ሥር “እየተያያዘና እየተጋጠመ” (ኤፌ. 4፡16) አንድ የሚያደርገው ተግባር ያለ ሲሆን፣ ይህም የአካል ራስ ወደሆነው ወደ ክርስቶስ በአንድነት እንድናድግ ይረዳናል (ኤፌ. 4:13፣ 15)።

ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን እየነፈሱ ካሉ “የትምህርት ነፋሳት” መካከል አንዳንዶቹ ምንድን ናቸው? እንዴት በጽናት መቆም እንችላለን? መልስዎን ለሰንበት ትምህርት የጥናት አባላት ያካፍሉ።

ነሐሴ 5
Aug 11


ተጨማሪ ሀሳብ


ሁለት ማስታወሻዎች የኤፌ. 4፡7-10 ጥናታችንን በስፋት ለመመልከት ይረዱናል።
1. የኤፌ. 4፡9 ፍቺ ማስቀመጥ። አንዳንድ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉሞች ወረደ የሚለውን ቃል ወጣ ከሚለው በፊት ያስቀምጣሉ። ሌሎች ትርጉሞች ግን (የአማርኛውን ጨምሮ) የግሪኩን ጽሑፍ ይበልጥ በቅርበት ስለሚከተሉ፣ የመውጣትን እና የመውረድን የጊዜ ጉዳይ ክፍት አድርገው ይተዋሉ (ለምሳሌ “ታዲያ፣ “ወደ ላይ ወጣ” ማለት ደግሞ ወደ ምድር ታችኛው ክፍል ወረደ ማለት ካልሆነ በቀር ምን ማለት ነው?”) ይህ ደግሞ በማክሰኞ ትምህርት ላይ የተገለጸውን አመለካከት በመፍቀድ፣ በመዝ. 68:18 የሚገኘውን የትረካ ሥርዓት መከተል ያለበት ሲሆን፣ የክርስቶስ በሰማይ መክበር (“መውጣቱ”) መጀመሪያ ገቢራዊ ይሆንና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት “መውረዱ” ይከተላል።
2. ምርኮ ማረከ። በግሪክኛ ከተጻፈውና ሴፕቱጀንት (ጥንታዊው የብሉይ ኪዳን ግሪክኛ ትርጓሜ) በመባል ከሚታወቀው የብሉይ ኪዳን መጽሐፍ፣ መዝ. 68፡18--ጳውሎስ በኤፌ. 4፡8 የተጠቀመውን “ምርኮ ማረከ” የተሰኘ ሃረግ ቃል በቃል የወሰደ ሲሆን፣ ነገር ግን ቃሉ በስፋት ጥቅም ላይ የዋለው “የምርኮኞችን ስብስብ እንደ እስረኛ ወሰደ” የሚል ፍቺ ለማግኘት ነው። ሰባተኛ ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ይህን ሃረግ በተደጋጋሚ የተረዱት ሲሆን፣ ይኸውም ክርስቶስ ባረገ ጊዜ፣ በእርሱ ትንሣኤ ወቅት በልዩ ትንሳዔ አብረውት ከመቃብር የተነሡትን ከእርሱ ጋር ወደ ሰማይ መውሰዱን በመግለጽ ነው (ማቴ. 27፡51-53)። እነዚህ “እንደሚወዘወዝ ቁርባን”፣ የተዋጁ በኩራት እርሱ ወደ ሰማያዊው ቅጥር ሲመለስ ለአብ ያቀረባቸው ናቸው። (ለማመሳከሪያ እነዚህን ይመልከቱ፡ The SDA Bible Commentary, vol. 6, p. 1022; The De- sire of Ages, p. 834, compare The Desire of Ages, pp. 785, 786). እንደ አማራጭ፣ በቆላ. 2፡15 መሠረት ምንባቡ ክርስቶስ በጠላቶቹ ማለትም እንደ ተሸነፉ ምርኮኞች በተሳሉት በሰይጣንና መላእክቱ ላይ ድል የተቀዳጀበትን ምስል ይሰጣል።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. በኤፌ. 4፡11 ያለውን “የመንፈሳዊ ስጦታዎች” ዝርዝር በ1ቆሮ. 12፡4-11፣ 27-30 ካለው ዝርዝር ጋር ያስተያዩ። ሮሜ 12:4-8፤ እና 1ጴጥ. 4:10-11። ምን ዓይነት ልዩነቶችና መመሳሰሎች አስተውለዋል?

2. በክፍል ውስጥ፣ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ስለሚነፍሱ አንዳንድ “የትምህርት ነፋሳት” ተነጋገሩ። ጳውሎስ በእነዚህ ነፋሳት መወሰድ እንደሌለብን አስመልክቶ የተናገረውን ልብ ይበሉ። እነዚህ ነፋሳት ሊያደርሱ ከሚችሉት ጉዳቶች መጠበቅ እንችል ዘንድ፣ ራሳችንን እና ሌሎችን በቤተ ክርስቲያን የምንረዳባቸው ልዩ መንገዶች የትኞቹ ናቸው?

3. ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው መልእክቱ ለ“አንድነት” ጭብጥ አጽንኦት ሰጥቶአል። ነገር ግን ማንኛውንም መከፈል ያለበት ዋጋ ከፍለን አንድነትን የማምጣት ጽኑ ፍላጎት አለን? በሌላ አነጋገር የአንድነት ፍላጎት ተቃራኒ ውጤት ይዞ ሊመጣ የሚችለው መቼ ነው? ተወያዩበት።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL