የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 3፤
ኢዮ. 11፡ 5-9፤ ሕዝ. 43፡13-16፤ አሞጽ 7 7-8፤ ራዕ. 11 1-2።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “እንግዲህ በእኛ ውስጥ እንደሚ ሠራው እንደ ኃይሉ መጠን፣ ከምንለምነው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ እጅግ አብልጦ ማድረግ ለሚቻለው፣ በቤተ ክርስቲያን እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ፣ በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም ለእርሱ ክብር ይሁን፤ አሜን” (ኤፌ. 3፡20-21)።
ጳውሎስ የኤፌ. 3 መልእክቱን የሚከፍተው ቀደም ሲል በዳሰሰው ጭብጥ
ነው፡ “ይህም ምስጢር አሕዛብ በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው ነው”። ምንም እንኳ ይህ
በአብዛኛው አሕዛብን ላቀፈችው ለዛሬዋ ቤተ ክርስቲያን ባያስገርምም፣ በዚያን
ወቅት ግን ለብዙዎቹ አንባቢዎቹ አዲስ ነገር ይመስል ነበር።
ሐዋርያው የየሱስን ወንጌል ለአሕዛብ ለመስበክ ያለውን ፍቅር
እያሰላሰለ በመንፈስ ምሪት መጻፉን ቀጠለ። ጳውሎስ አገልግሎቱን በማራዘም
በወቅቱ ስላጋጠመው ችግር፣ በሮም እስር ቤት የቆየባቸውን ጊዜያቶች ጨምሮ
ስለተጋፈጣቸው ፈታኝ ሁናቴዎች እንማራለን።
እንዲሁም የወንጌል አስኳል ለሆነው ምስጢር ያለውን ቁርጠኝነት፣
ይኸውም አሕዛብ ከአይሁድ ወንድሞቻቸውና እህቶቻቸው ጋር በቤተ ክርስቲያን
ውስጥ በእኩል የመታየታቸውን ምስጢር እንሰማለን። በቤተ ክርስቲያን ብሎም
በዩኒቨርስ አቀፍ ተልዕኮው ምን ያህል ሐሴት እንዳደረገ በመመልከት ይህን
ደስታውን እናጣጥማለን።
በአጭሩ፣ ጳውሎስ ምን ያህል ለወንጌል የጋለ ፍቅር እንዳለው በመመልከት
እርሱን ለመቀላቀል እንነሳሳለን።
ኤፌሶን ምዕራፍ 3 ያንብቡ። ከምዕራፉ አንድ ወይም ሁለት ጭብጦችን ለማውጣት ይሞክሩ። ጳውሎስ የተናገራቸው ዋና ዋና ነጥቦች ምንድን ናቸው?
የኤፌሶን 3 አወቃቀር ማራኪ ገጽታ የተላበሰ ነው። ጳውሎስ ምዕራፉን
በሚከተሉት ቃላት ይጀምራል፡ “በዚህም ምክንያት እኔ ጳውሎስ ለእናንተ ለአሕዛብ
የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ” (ኤፌ. 3፡1)። ከዚያም ለአሕዛብ ሐዋርያ
ሆኖ ያከናወነውን ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ሥራ ለጊዜው ያቋርጣል (ኤፌ. 3፡
2-13)። ከአገልግሎት ገለል ካለ በኋላ፣ “በዚህም ምክንያት” (ኤፌ. 3፡
14) የሚለውን ሃረግ በመደጋገም፣ ወደ ቀደመው ዋና ርዕሰ ጉዳይ የመመለሱን
ምልክት የሚሰጥ ሲሆን፣ ከቁ. 14 እስከ 21 ባለው መልእክቱ ደግሞ ተቋርጦ
የነበረውን የጸሎት ዘገባ ያቀርባል።
ምንም እንኳ እርሱ በሮማውያን ግዞት ስር የሚኖርና በሮም ግዛት ሥልጣን
ስር ያለ መስሎ ቢታይም፣ በሕይወቱ ውስጥ ጥልቅ የሆነ መለኮታዊ ዓላማ እተከናወነ
እንደ ነበር ጳውሎስ በሚሞግተው የኤፌ. 3፡1 መልእክቱ፣ ራሱን “የክርስቶስ
ኢየሱስ እስረኛ” አድርጎ ገልጿል። እርሱ “የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ” እንጂ
የሮም መንግሥት እስረኛ አልነበረም! (ከኤፌ. 4፡1 ጋር ያስተያዩ)።
ጳውሎስ ስለ ደረሰበት “መከራ” (ኤፌ. 3:13) መጥቀሱና ቆየት
ብሎ ደግሞ በሰንሰለት ታስሮ ስለ ነበረበት ሁኔታ መናገሩ (ኤፌ. 6:20)፣
በአንጻራዊ ሻል ሊል በሚችል የቤት እስር ሳይሆን ወኅኒ መውረዱን ይጠቁማል
(ከሐዋ. 28፡16 ጋር ያስተያዩ)። በተለይ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን ላይ
በሮም እስር ቤት መጣል በእጅጉ ፈታኝ ነበር። በዘመኑ ዓለምን በቅኝ ግዛቱ
ስር አውሎ በነበረው የሮም ግዛት፣ ወኅኒ ቤቶች በንጽህና መጠበቂያና መደበኛ
የምግብ አገልግሎት ረገድ የተሟሉ አልነበሩም። ለነገሩ እስር እንደ ቅጣት ይቆጠር
ስላልነበር፣ የሮም ግዛት እስር ቤቶች እነዚህ ነገሮች እምብዛም አያስፈልጓቸውም
ነበር። ሰዎች እስር ቤት የሚገቡት ፍርድ ቤት እስኪቀርቡ ወይም እስኪገደሉ
ለመጠበቅ ብቻ ነበር። ስለዚህ እስረኞች የሚያስፈልጋቸውን ራሳቸው
እንዲያሟሉ የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ ምግብና ሌሎች መሠረታዊ ነገሮች ለማግኘት
በዘመዶቻቸው ወይም በጓደኞቻቸው ላይ ጥገኞች መሆን ነበረባቸው።
የጳውሎስ ጭንቀት ምናልባት መታሰሩ ከሚያስከትለው ማኅበራዊ
ውርደት አውድ አኳያ፣ የአማኞች ስሜት እንዳይጎዳ ያተኮረ ሊሆን ይችላል።
አንዳንዶች “ጳውሎስ በአንድ ፊት የተዋረደ እስረኛ በሌላ በኩል ደግሞ እንዴት
የከበረው ክርስቶስ ሐዋርያና መልእክተኛ ሊሆን ይችላል?” ብለው እንዳይጠይቁ
ሊሰጋ ይችላል። ስለዚህ አማኞች እስሩን የእግዚአብሔር እቅድ አካል አድርገው
ይመለከቱ ዘንድ እንደገና ይገልጸዋል። እርሱ መከራ የደረሰበት ስለ እነርሱ ነበር
(“ስለ እናንተ በደረሰብኝ መከራ”) ይህን ተከትሎ አሳፋሪ ይመስል የነበረው
ነገር ስለ እነርሱ “ክብር” (ኤፌ. 3፡13) ወደ መሆን ይለወጣል።
በጣም ፈታኝ በሚመስሉ ሁናቴዎች ውስጥ በእግዚአብሔር እና
በእርሱ መንገዶች እምነት መጣል የምንችለው እንዴት ነው?
ለጳውሎስ የተሰጠው ምሥጢር ምንድን ነው? ኤፌ. 3፡1-6
ኤፌ. 3፡1-6 ሲያጠኑ የሚከተሉትን ልብ ይበሉ፡በመጀመሪያ፣ ጳውሎስ
ይህንን የመልእክቱን ክፍል የጻፈው በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ላሉ አሕዛብ
አማኞች መሆኑን (ኤፌ. 3፡1)።
ሁለተኛ፡ ጳውሎስ ለአሕዛብ አማኞች “ለእናንተ” የተሰጠውን
“የእግዚአብሔር ጸጋ መጋቢነት” የሚል ስያሜ የሰጠው አንድ ነገር ተቀባይ
እንደሆነ ይናገራል (ኤፌ. 3፡2)። ይህ መጋቢነት ወይም ይህ የጸጋ አገልግሎት
ጳውሎስ ለአሕዛብ ወንጌልን (“የእግዚአብሔርን ጸጋ”) እንዲሰብክ የተሰጠውን
ተልዕኮ የሚገልጽበት መንገድ ነው (ኤፌ. 3፡7-8)።
ሦስተኛ፡ ጳውሎስ ምሥጢር እንደ ተገለጠለት ተናግሯል፣ ይህ ደግሞ
እርሱ አስቀድሞ በደብዳቤው የጻፈው (ኤፌ. 1፡9-10፤ ኤፌ. 2፡11-22)፣
“የክርስቶስ ምሥጢር” ርዕስ ነው። ጳውሎስ እንደ ወንጌል ጠንሳሽ አድርጎ ሰው
እንዲረዳው አይፈልግም፤ ይልቁንም ወንጌልን ማወጅ ከእግዚአብሔር የተሰጠው
አልግሎት እንደሆነ ይናገራል።
አራተኛ፡ መንፈስ ቅዱስ ለክርስቶስ “ቅዱሳን ሐዋርያትና ነቢያት” ለቀደሙት
ትውልዶች የእግዚአብሔር እቅድ በላቀ መንገድ እንዲተላለፍ አድርጎ የገለጠ ከመሆኑ
አኳያ፣ ስለዚህ ምሥጢር የላቀ መገለጥ የተሰጠው ጳውሎስ ብቻ አይደለም (ኤፌ.
3፡5)። እዚህ ላይ ነቢያት የሚለው ቃል ምናልባት ከብሉይ ኪዳን ነቢያት ይልቅ፣
በጥንቶቹ የክርስቲያን ቤት ለቤት አገልግሎት መካከል የትንቢት ስጦታ የነበራቸውንና
ጥቅም ላይ ያዋሉ የነበሩትን ያመለክታል። በአንድ ወቅት ተሸሽጎ የነበረው ነገር አሁን
ግን “የአደባባይ ምስጢር” ብለን የምንጠራው ሆኗል።
በመጨረሻ እንዲህ ሲል በይፋ ይናገራል፡ “ይህም ምስጢር አሕዛብ
በወንጌል አማካይነት ከእስራኤል ጋር አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ በሆነው ተስፋ አብረው ተካፋይ መሆናቸው
ነው።” (ኤፌ. 3፡6)።
ጳውሎስ ለወንጌል፣ በተለይም በአይሁድ እና በአሕዛብ በተዋቀረችው
ቤተ ክርስቲያን ወንጌል ስለተገለጸበት መንገድ ጠንካራ ስሜት ነበረው። እነዚህ
ሁለት ቡድኖች የአዲሱ አምላካዊ ማኅበረሰብ ሕንጻ፣ የእርሱ አዲስ ሰው ይኸውም
ቤተ ክርስቲያን ሆነው ተገነቡ (ኤፌ. 2፡14-16)። አሁን ጠላት ከመሆን
“አብረው ወራሾች፣ አብረው የአንዱ አካል ብልቶች” ወደመሆን ተለውጠዋል
ማለት እንችላለን (ኤፌ. 3፡6)።
ምናልባት እርስዎ ከወንጌል አስተምህሮ ጋር ሊቃረን የሚችል
አመለካከት ይዘው ቢሆንስ? ያን እንዴት ማስወገድ ይችላሉ?
ጳውሎስ በኤፌ. 3፡7-13 ስለ እግዚአብሔርና እርሱ ስላከናወናቸው ነገሮች ምን ይላል?
ጳውሎስ “በእግዚአብሔር የጸጋ ስጦታ የዚህ ወንጌል አገልጋይ ሆኛለሁ”
(ኤፌ. 3፡7 ያስተያዩ፡ ኤፌ. 3፡1-2) ሲል በድጋሚ ተናግሯል። ይህ ስጦታ፣ ልክ እንደ
ወንጌል፣ የተሰጠው በተቀባዩ ዋጋ ሳይሆን በእግዚአብሔር ጸጋ ነው። ጳውሎስ “ከቅዱሳን
ሁሉ ያነስሁ” (ኤፌ. 3፡8) ብሎ ራሱን በመግለጽ ለዚህ ነጥብ አጽንኦት ይሰጣል።
ጳውሎስ የጻፋቸውን ደብዳቤዎች በቅደም ተከተላቸው መሠረት
ስንመለከት፣ ስለ ራሱ ባለው ግንዛቤ ዙሪያ አስደናቂ የለውጥ ሂደት መኖሩን
እንረዳለን። ጳውሎስ ገና ከመጀመሪያው፣ በመለኮት የተሾመ ሐዋርያ መሆኑን
ይገልጣል (ገላ. 1፡1)። ኋላ ላይ ደግሞ፣ “ከሐዋርያት ሁሉ የማንስ… ሐዋርያ
ተብዬ ልጠራ የማይገባኝ” (1ቆሮ. 15፡9) በማለት ራሱን ሲገልጽ ይስተዋላል።
ጳውሎስ በዚህ በኤፌሶን መልእክቱ “ከቅዱሳን ሁሉ ያነስሁ” (ኤፌ.
3፡8) በሚል አገላለጽ ራሱን ይመለከታል። በመጨረሻም፣ ከኃጢአተኞች ሁሉ
“ዋና” አድርጎ ራሱን ይገልጻል (1ጢሞቴ. 1፡15)።
ምናልባት እዚህ ላይ የቀረበው የጳውሎስ አስተሳሰባዊ መስመር የኤለን
ጂ ኋይትን ዝነኛ ጽሑፍ ለማብራራት ሊረዳ ይችላል፡-“አንድ ሰው ይበልጥ ወደ
የሱስ በቀረበ መጠን፣ በራሱ ላይ በርካታ ጉድለቶች መኖራቸውን ይመለከታል።
ዐይን አጥርቶ ሲያይና ራሱን ከእርሱ ፍጹም ተፈጥሮ አኳያ መታዘብ ሲጀምር፣
ፍጽምና የጎደለው ማንነቱ ወለል ብሎ ይታየዋል። በዚህም መጠነ ሰፊ ልዩነት
መኖሩን ይታዘባል።”-Steps to Christ, p. 64.
ጳውሎስ መልእክቱን በመቀጠል በኤፌ. 3፡10 እንዲህ ይላል፡ “አሳቡም
በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው።” ለመሆኑ እዚህ
ላይ የተመለከቱት “በሰማያዊ ስፍራ” ያሉት “አለቆችና ባለ ሥልጣናት” እነማን
ናቸው? ቤተ ክርስቲያን “ብዙ ገጽታ ያለውን” ጥበብ ለእነርሱ የምትገልጠው
እንዴት ነው? ምንም እንኳ ኤፌ. 3:10 የኃይላቱን ተፈጥሮአዊ ባህሪ ባይገልጽም፣
በኤፌ. 6፡11-12 በተሻለ ዝርዝር የተገለጹትን፣ እንደ ክፉ መናፍስት መውሰዱ
የተሻለ ይመስላል። እንዲህ ከሆነ፣ የቤተ ክርስቲያን አሰበጣጠር፣ በአንድ ወቅት እጅግ
ተከፋፍለው የነበሩት አይሁድ እና አሕዛብ ሰብዓዊ ፍጡሮች መዋሃዳቸው፣ ለእነዚህ
“በሰማያዊ ስፍራ ላሉ” አጋንንታዊ “አለቆችና ባለ ሥልጣናት” የደወል ደምጽ
ይሆናል። የእግዚአብሔር የወደፊት እቅድ “በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ
ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል” (ኤፌ. 1፡10) ነውና። የእግዚአብሔር
እቅድ በግስጋሴ ላይ እንደሆነና የመጨረሻው ፍርዳቸውም እንደተረጋገጠ ያስተውላሉ።
በኅብረቷ የጸናች ቤተ ክርስቲያን ዓይነተኛ ባህሪ፣ የመጨረሻ ሽንፈታቸው ማሳያ ነው።
የእርስዎ ጉባዔ ጳውሎስ በኤፌ. 3፡10 ያቀረበውን “የሥራ መግለጫ”
በቁም ነገር የሚመለከተው ከሆነ፣ የእርስዎንና የቤተ ክርስቲያን
አባላትን እርስበርስ ግንኙነት እንዴት ሊለውጥ ይችላል?
በኤፌ. 1፡16-19 የቀረበውን የጳውሎስን የቀደመ የጸሎት ልመና፣
በኤፌ. 3፡14-19 ለአማኞች ካቀረበው ልመና ጋር ያስተያዩ።
ሁለቱን የጸሎት ጥያቄዎች ምን ያመሳስላቸዋል?
ከኤፌ. 3፡14-15 ትርጉም ጀርባ ቃላቶች ጉልህ ሚና ይጫወታሉ።
ጳውሎስ “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብ ሁሉ ስያሜ” በሚያገኝበት “በአብ ፊት
እንበረከካለሁ” ብሎ ሲናገር፣ አባት patēr በሚለው የግሪክኛው ቃል እና ቤተሰብ
በሚለው የግሪክኛ ቃል patria መካከል ያለውን የቃላት ድምጸት ግንኙነት
እየመረመረ ነው። ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ ሁሉን አካታች በሆነው (ኤፌ.
1:9-10) እና ለሁሉም ዘመን (ኤፌ. 1:21) በሆነው የእግዚአብሔር
የማዳን እቅድ አጠቃላይ ባህሪ ሐሴት ያደርጋል። እዚህ ላይ “በሰማይና በምድር
ያለ ቤተሰብ ሁሉ” የ “አብ” ንብረት እንደሆነ ተናግሯል። እያንዳንዱ ቤተሰብ
(patria) ስያሜውን የወሰደው ከአብ (patēr) ነው። ይህ በእጅጉ ግሩም
የሆነ ዜና ነው!
ይህን ሀሳብ ያሰላስሉ፡ ቤተሰብዎ ፍጽምና የጎደለው ቢሆንም እንኳ
የእግዚአብሔር ንብረት ነው። ቤተሰብዎ በጨካኙ ዕጣ ፈንታ ቁጥጥር ስር ሳይሆን፣
በእግዚአብሔር አሳቢ እጆች ውስጥ ነው። እግዚአብሔር ፍጽምና የጎደላቸውን
ቤተሰቦች ይወዳል። እነርሱ መለኮታዊውን ስም፣ የባለቤትነቱንም ምልክት ይሸከማሉ።
ጳውሎስ በኤፌ. 3፡16-19 መልአክቱ አማኞች የመንፈስ መገኘትን
የሚያሳይ ውስጣዊ ጥንካሬ (ኤፌ. 3፡16)፣ የተትረፈረፈ መንፈሳዊ ተሞክሮ፣
ከክርስቶስ ጋር የጠበቀ ግንኙነት--ይኸውም እርሱ በልባቸው እንዲያድር (ኤፌ.
3፡17)፣ የተደላደለና አስተማማኝ መንፈሳዊ ማንነት (“ሥር ሰዳችሁ በፍቅር
ታንጻችሁ” ኤፌ. 3፡17) እግዚአብሔር ይሰጣቸው ዘንድ ይጠይቃል።
ጳውሎስ እግዚአብሔር ለአማኞች ስለሚሰጠው ተቆጥረው የማያልቁ በረከቶች
የሚያመስግንበት መንገድ ሦስት ሳይሆን አራት የልኬት ገጽታዎችን ያካትታል፡ “ስፋት፣
ርዝመት፣ ከፍታ ጥልቀት” (ኤፌ. 3፡18)። እነዚህ የልኬት ገጽታዎች አስፈላጊ የሆነው
ነገር ስላለው ግዝፈት ቢናገሩም፣ እንዴት እንደሚተገበሩ ግን በግልጽ አያስቀምጥም።
ይህ ደግሞ የመጽሐፍ ቅዱስ ተማሪዎችን ትኩረት የሚስብ እንቆቅልሽ ይሆናል። እነዚህ
የልኬት ገጽታዎች ምንን ይገልጻሉ--የእግዚአብሔርን ጥበብ (ኢዮ. 11፡5-9)፣
የእግዚአብሔርን ኃይል (ኤፌ. 3፡16-17) ወይስ በኤፌሶን የቀረበው መንፈሳዊ
መቅደስ 2፡19-22 (ሕዝ. 43፡13-16፣ አሞጽ 7፡7-8፣ ራእ. 11፡1-2)? እነዚህ
ባለ አራት ገጽታዎች “የክርስቶስን ፍቅር” (ኤፌ. 3፡19) ግዝፈት ሲገልጹ መመልከቱ
የተሻለ ሊሆን ይችላል። “የክርስቶስ ፍቅር ስፋቱ፣ ርዝመቱ፣ ከፍታውና ጥልቀቱ”
(ኤፌ. 3፡18) የሚለው ሃረግ “ምን ያህል እንደሆነ… የመገንዘብ ኃይል እንድታገኙ”
ከሚለው ጋር የተጣጣመ ነው (ኤፌ. 3፡19፣ ሮሜ 8፡35-39)። የሆነው ሆኖ፣
የጳውሎስ ቃላት መልካም የምሥራች መሆናቸውን እንመለከታለን።
ክብር ይሁን ጳውሎስ አጠር ባለ፣ የሥነ ግጥም ለዛ ባለው የምስጋና ማጠቃለያ ቃል የጸሎት ዘገባውን ይደመድማል። እግዚአብሔርን የሚያመሰግንበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ኤፌ. 3፡20-21
ጳውሎስ ለአማኞች ጥቅም ጸሎቱን በጽሑፍ ሲያሰፍር ቆይቶአል (ኤፌ.
3፡14-19)። አሁን ደግሞ በቀጥታ እና በኃይል ይጸልያል። የጳውሎስ አጠር ያለ
የምስጋና ማጠቃለያ ሁለት ጥያቄዎች ያስነሳል፡
1. ምንባቡ ተገቢ ባልሆነ መንገድ ቤተ ክርስቲያንን ከፍ ከፍ በማድረግ
ከክርስቶስ ጋር በእኩል ደረጃ ያስቀምጣታል--“በቤተ ክርስቲያን
እንዲሁም በክርስቶስ ኢየሱስ… ለእርሱ ክብር ይሁን” (ኤፌ. 3፡21)?
ምንም እንኳ ጳውሎስ ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ከፍተኛ ትኩረት የሚሰጥ
ቢሆንም፣ በምእመናን ልብ ውስጥ የሚኖረው ክርስቶስ እንደመሆኑ፣
የእርሱ የቤተ ክርስቲያን አዳኝነት ግልጽ ነው (ኤፌ. 3፥17)። አጠር
ባለው የምስጋና ማጠቃለያው፣ ጳውሎስ በክርስቶስ የሱስ በኩል ለቤተ ክርስቲያን ስለተሰጠው መዳን ለእግዚአብሔር ምስጋና ያቀርባል።
2. “በዘመናት ሁሉ ከዘላለም እስከ ዘላለም” (ኤፌ. 3፡21) የሚለው ሃረግ፡
ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጊዜ ያበቃል ለማይባል ዘመን በምድር የምትወሰን፣
የክርስቶስም ዳግም ምጽአት በእንጥልጥል እንደሚቆይ አድርጎ ይስላል?
የኤፌሶን ሰዎች መልእክት በወደፊቱ ዙሪያ ጠንካራና ሕያው ተስፋ ያሳያል።
ለምሳሌ ኤፌ. 4፡30 አሻግሮ ወደ “ቤዛ ቀን” ይመለከታል። እንዲሁም፣
አማኞች የክርስቶስን ገደብ የሌለው ሉዓላዊ ሥልጣን “በሚመጣውም
ዘመን” (ኤፌ. 1፡21) ይለማመዳሉ። የጳውሎስ አጠር ያለ የምስጋና
ማጠቃለያ፣ ክርስቶስ ስለ አማኞች ለተጠቀመው ማለቂያ የሌለው ኃይል
ሐሴት ማድረግ ተብሎ ሊነበብ ይችላል።
ወደ ኋላ መለስ ብለን ሁለተኛውን የጳውሎስ ጸሎት ዘገባ ስንመለከት (ኤፌ. 3፡14-
21፤ ኤፌ. 1፡15-23)፣ ሐዋርያው ከአብ ጥበቃና እንክብካቤ የተነሣ ብርታትና
ጥንካሬ (ኤፌ. 3፡14-15)፣ የመንፈስ ቅዱስ አብሮነት (ኤፌ. 3፡16)፣ የራሱ
የክርስቶስ አጋርነት (ኤፌ. 3፡17) እና የማይለካውን የተትረፈረፈ የክርስቶስ ፍቅር
(ኤፌ. 3፡18-19) እንዳገኘ እንመለከታለን። ይህ ፍጹም እውነት ከመሆኑ የተነሣ
አማኞች “እስከ እግዚአብሔር ሙላት” (ኤፌ. 3፡19) ደርሰው ይሞሉ ዘንድ ተስፋ
እያደረገ፣ ስለ እነዚህ መንፈሳዊ እውነታዎች በምስጋና ሐሴት ያደርጋል፤ እግዚአብሔር
ለቅዱሳን በሰጠው የተትረፈረፈ ኃይልም አብልጦ ይደነቃል (ኤፌ. 3፡20-21)።
ችግሮች፣ ፈተናዎች ወይም ጥርጣሬዎች ሲከቡን፣ ፊታችንን ወደዚህ አበረታች
የጳውሎስ ጸሎት መመለስ እንችላለን። በወህኒ የነበረው ሐዋርያ ራዕያችንን ወደ ግዙፉ
አምላካዊ ዓላማና ጸጋ አድማስ ያሳድጋል፤ አሁን ያለንበት ሁኔታ ምንም ይሁን ምን፣
እኛ በእግዚአብሔር የመጨረሻ እቅድ ውስጥ ተካፋዮች መሆናችንን ያስታውሰናል
(ኤፌ. 1፡9-10)፣ እናም የእርሱ ኃይል በእኛ ውስጥ እየሠራ ይገኛል።
ለእርስዎ የተለየ ዋጋ ያላቸው የትኞቹ የእግዚአብሔር በረከቶች ናቸው?
እግዚአብሔርን ለእነዚህ ነገሮች ያመሰግኑት ዘንድ በምስጋና የተሞሉ ጸሎቶችን
ይለማመዱ።
“ዘመናዊ መነቃቃቶች” ታላቁ ተጋድሎ [በመታገስ
አጋዤ ከተተረጎመው] ገጽ፡ 526-543
“ደካማ የሆነውን መንፈሳዊ ሁኔታችንን--የእውቀት ሙላት ባለቤት
እንድንሆን የተሰጠን ልዩ መብት መሆኑን ከሚገልጸው፣ ከተሰጠን ጥቅስ (ኤፌ.
3፡14-19) ጋር እንዴት ማስማማት እንችላለን? በጸጋ እናድግ ዘንድ እያንዳንዱ
መንፈሳዊና ለየወቅቱ ገጣሚ ልዩ መብትና ጥቅም ተሰጥቶን ሳለ፣ እኛ ግን ይህን
ሳንጠቀምበት መቅረታችንን ሰማይ እንዴት ይመለከተው ይሆን? ሐዋርያው እነዚህን
ቃላት የጻፈው በእኛ ለማሾፍ፣ እኛን ለማታለል፣ ወይም የማይሆን ነገር በውስጣችን
አጭሮ ተስፋ እንድንቆርጥ ለማድረግ አይደለም። ነገር ግን እነዚህን ቃላት የጻፈው፣
የእግዚአብሔር መንግሥት ወራሾች እስከሆንን ድረስ እነዚህን ነገሮች ማድረግ
እንዳለብን ለማሳየት ነው። ጎዶሎ ተሞክሮ ይዘን ከእግዚአብሔር ጋር እንዴት
አብረን ሠራተኞች እንሆናለን? እኛ ለክርስቲያኖች ልዩ መብትና ጥቅም የተሰጠው
የክርስቶስ ዕውቀት ያለን ሕዝቦች እንደመሆናችን፣ ጌታ እንዲኖረን ለተመኘው ለዚያ
ጥልቅ አምላካዊ ነገሮች መንፈሳዊ ማስተዋል እንዲሰጠን ልንጠይቀው ይገባል።
“መጽሐፍ ቅዱስን በእርግጥ እናምናለን? በዚህ ጽሑፍ በፊታችን
የቀረበውን የእግዚአብሔርን እውቀት ማግኘት እንደምንችል በእርግጥ እናምናለን?
ከእግዚአብሔር አፍ የሚወጣውን እያንዳንዱን ቃል እናምናለን? የብርሃንና በረከት፣
የመለኮት ሙላትና ባለጸግነት ሁሉ ባለቤት በሆነው በየሱስ ክርስቶስ፣ በነቢያትና
በሐዋርያት የተነገሩትን ቃላት እናምናለን? በእግዚአብሔር አብ እና በልጁ ወልድ
በእርግጥ እናምናለን?-Ellen G. White, The Advent Review
and Sabbath Herald, October 1, 1889.
1. በኤፌ. 3፡20-21 የቀረበውን የጳውሎስን አጠር ያለ የምስጋና
ማጠቃለያ ጸሎት ቃል ከሌሎች ጋር ያስተያዩ--ሮሜ. 11፡33-36፤
ሮሜ 16:25-27፤ ፊልጵ. 4:20፤ 2ጴጥ. 3:18 ፤ ይሁዳ 24-25።
በእነዚህ ምንባቦች ምን ጭብጦች ወይም ሐሳቦች ይንሸረሸራሉ?
2. ጳውሎስ አራት ቦታዎች ላይ የተጠቀመውን plēroma “ሙላት”
የተሰኘ የግሪክ ቃል ያስተያዩ፡ (ኤፌ. 1፡10፣ 23፣ 3፡19፣ 4፡
13)። ይህ ሃሳብ ለጳውሎስ ጠቃሚ የሆነው ለምን ይመስሎታል?
3. ጳውሎስ በኤፌሶን ምዕራፍ 3 ላይ ምስጋና ካቀረበባቸው አምላካዊ
ተግባራት ሁሉ ለእርስዎ ይበልጥ አነሳሽ ሆኖ ያገኙት የትኛውን
ነው? ለምን?
4. ጳውሎስ የኤፌሶንን መጽሐፍ የመጀመሪያ አጋማሽ የሚያጠቃልለው
መልእክቱን በጀመረበት (ኤፌ. 1፡3-21) የጸሎትና የምስጋና ቃላት
ነው። በክርስቶስና በመንፈስ ቅዱስ አማካይነት (ኤፌ. 3፡16-
21) በአማኞች ሕይወት በሆነው ነገር በእግዚአብሔር ይመካል።
ኤለን ጂ ኋይት ከላይ እንደጻፈችው፣ ይህን ኃይል በተሻለ ሁኔታ
በሕይወታችን መለማመድ የምንችለው እንዴት ነው?