የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 2
11-22፤ ሮሜ. 3 31፤ ሮሜ. 7 12፤ ኢሳ. 52 7፤ ኢሳ. 57 19፤ ፦
ዮሐ. 14፡27፤ 1ቆሮ. 3 9-17።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “አሁን ግን እናንተ ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል። ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን እርሱ ራሱ ነውና” (ኤፌ. 2፡13-14)።
አንተ የአይሁድን አምላክ ከፍ ከፍ አድርገህ መመልከትን የተማርክ
አሕዛብ፣ የግሪክ ሰው ነህ። እንደ እውነቱ ከሆነ ለበርካታ አማልክት
ታቀርብ የነበረውን አምልኮ ትተህ እውነተኛውን አምላክ ተቀብለሃል።
በየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ውብ አደባባዮችና በእነዚያ የተንቆጠቆጡ ዓምዶች
ውስጥ ስታልፍ የአምልኮ ድምጾች ምስጋናህን አስተጋብተዋል። ሆኖም በዚያን
ጊዜ፣ አራት ጫማ ከፍታ ካለው የድንጋይ ግድግዳ ጋር ፊት ለፊት ተጋፍጠህ ራስህን
ታገኘዋለህ። በጥቂት ጫማዎች ርቀት በላቲን እና በግሪክ ፊደላት በግድግዳው ላይ
የተቀረጸውን ይህን መልእክት ታገኛለህ፡ “ማንኛውም የባዕድ አገር ተወላጅ በቤተ
መቅደሱ ዙሪያ ያለውን አጥር አልፎ መግባት አይችልም። ይህን ሲያደርግ የተያዘ
ማንኛውም ሰው ለተከተለው ሞት ተጠያቂው እርሱ ራሱ ነው።” በዚያው
ቅጽበት መግባት የተከለከልህ፣ የተለየህ እና የተነጠልክ ሆኖ ይሰማሃል።
ጳውሎስ በኤፌ. 2፡11-22 መልእክቱ የክርስቶስ መስቀል አስገራሚ
ለውጥ እንደሚያመጣና እንደነዚህ ያሉ መሰናክሎችንና ግድግዳዎችን እንደሚያፈርስ
ተመልክቷል። ከላይ ወደ ታች ቀጥ ብሎ የተሰመረው የመስቀሉ ክፍል ጠላትነትን
በመሻር ሰዎችን ከእግዚአብሔር ጋር ሲያስታርቅ፤ አግድም የተሰመረው የመስቀሉ
ክፍል ደግሞ ሰዎችን እርስ በርስ ያስታርቃል። መስቀል ጠላትነትን አስወግዶ
በአይሁዶች እና በአሕዛብ መካከል ሰላምን በማምጣት “አንድ አዲስ ሰው”
(ኤፌ. 2፡15) አደረጋቸው። ይህ እውነት ዛሬ ለኛ ምን ትርጉም አለው?
ጳውሎስ ቀደም ባለው መልእክቱ አሕዛብን አስመልክቶ በኤፌ.
2፡1-3 የሰጠውን መግለጫ ከኤፌ. 2፡11-12 ጋር ያስተያዩ።
የቀድሞውን ያወሳበት የአዲሱ አገላለጹ ድምጸት ምን ይመስላል?
አሁን በክርስቶስ ያመኑትና የእርሱ “አካል” የሆነችው ቤተ ክርስቲያን
አባላት የሆኑት አሕዛብ፣ በአንድ ወቅት ከእስራኤል እና እግዚአብሔር ካቀረበው
ማዳን ፈጽሞ ተለይተው ነበር። ጳውሎስ ያለፈውን ጊዜ “አስታውሱ” በማለት
ያን ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጿል (ኤፌ. 2፡11)። በዚያን ጊዜ የእስራኤል
መሲሕ ከሆነውና ከተቀባው “ከክርስቶስ ተለይተው” ነበር። “ከእስራኤል
ወገን” [መንግሥት ወይም ሕዝብ] የራቁ መጻተኞች ነበሩ። እግዚአብሔር
በመዳን ታሪክ ስላቀረባቸው የደኅንነት ተስፋዎች ግንዛቤው አልነበራቸውም፣
“ለኪዳኑም ተስፋ ባዕዳን” ነበሩ። ከእስራኤልና በዚያ ከተሰጠው መዳን ተገልለው
ነበር ማለት፣ በአንድ ወቅት “በዓለም ላይ ያለ ተስፋና ያለ እግዚአብሔር” እንደ
ነበሩ ያመለክታል (ኤፌ. 2፡12)።
እንዲሁም ቀደም ባለው ተሞክሮአቸው፣ አሕዛብ በራሳቸው እና በአይሁዶች
መካከል ከፍ ያለ ጠብ ውስጥ ገብተው ነበር። ጳውሎስ ይህን ሥር የሰደደ ጥላቻ
የጠቀሰበት አንዱ ምልክት እርስ በርስ የሚጠራሩበት ስያሜ ነበር። አይሁዶች
አሕዛብን “ያልተገረዙ” ብለው ሲያፌዙባቸው፣ አሕዛብ በበኩላቸው “እነሆ
የተገረዙት” በሚል እኩል የሹፈት ድምጸት ይጠሯቸው ነበር (ኤፌ. 2፡11)።
የሆነው ሆኖ፣ ጳውሎስ በኤፌ. 2፡13 መልእክቱ አሁን የሚገኙበትን
ፍጹም የተለየ ሁናቴ እንዲህ ሲል ያመለክታል፡ “አሁን ግን እናንተ ቀድሞ
ርቃችሁ የነበራችሁ፣ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም አማካይነት ቀርባችኋል።”
ጳውሎስ አሕዛብ አማኞችን “ቀድሞ ርቃችሁ የነበራችሁ” ብሎ
የሚገልጽበትን ሃረግ የተዋሰው ከኢሳ. 57፡19 ነው፡ “ ‘በቅርብና በሩቅ
ላሉት ሰላም፣ ሰላም ይሁን፤ እኔ እፈውሳቸዋለሁ’ ይላል እግዚአብሔር።”
ከእግዚአብሔር፣ ከተስፋው እና ከአይሁድ ወንድምና እህቶቻቸው ተለይተው
የነበሩ አሕዛብ አማኞች፣ በክርስቶስ እና በመስቀሉ አማካይነት አሁን ወደ ሁሉም
ቀርበዋል። የክርስቶስ መስቀል በአይሁዶችና በአሕዛብ መካከል ያለውን ሰፊ
አለመግባባት መፈወስ ይችላል የሚለውን ጠንከር ያለ የምሥራች የያዘው
የጳውሎስ መግለጫ፡ ሁሉም አለመግባባቶቻችንና መከፋፈሎቻችን በዚያ ሊፈቱ
ይችላል የሚል አንደምታ አለው። ይህ የምሥራች በሕይወታችን እና በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያለውን መለያየት እንድንመረምርና የመስቀሉ ኃይል ይተካው
ዘንድ እንድናገናዝብ ይጋብዘናል።
የሱስ ከዚያ ሁናቴ ዋጅቶዎታልን? ቀድሞ ከነበሩበት ስፍራ እንዴት
እንዳገኘዎ እና እርሱ ባያገኝዎ ኖሮ አሁን ሊገኙ ይችሉ የነበረበትን
ሁኔታ ሲያስቡ… ታዲያ አልፎ አልፎ ያን ማስታወስዎ አስፈላጊ
ሊሆን የሚችለው ለምን ይመስሎታል?
“ሁለቱን አንድ ያደረገ፣ የሚለያየውንም የጥል ግድግዳ ያፈረሰ ሰላማችን
እርሱ ራሱ ነውና… በመስቀሉም ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር
አስታረቀ።” (ኤፌ. 2፡14-16)።
ጳውሎስ መስቀሉንና የክርስቶስን ሥራ ተጽእኖ በእያንዳንዱ
የኤፌሶን መጽሐፍ ምንባብ እንዴት ይገልጸዋል? ጳውሎስ
ስለ መስቀሉና መስቀሉ ግንኙነታችንን እንዴት እንደሚለውጥ
የሚናገረውን ሀሳብ ጠቅለል አድርገው ያቅርቡ። ( ኤፌ. 1:7-8፣
ኤፌ. 4:32፣ ኤፌ. 2:13-14፤ ኤፌ. 2:16፣ ኤፌ. 5:2፣ 25)።
በዚህ ሳምንት የኤፌ. 2፡11-22 መጽሐፍ ምንባባችን ዐውድ መሠረት፣
መስቀሉ ሦስት የከበረ ዋጋ ያላቸውን ትሩፋቶች ለአማኙ ያስገኛል፡ (1)
ከእግዚአብሔር እና ከሕዝቡ “ርቀው” የነበሩ አሕዛብ ለእግዚአብሔር ወንዶችና
ሴቶች ልጆች፣ ለአይሁድ አማኞች ደግሞ ወንድም እና እህት በመሆን ለሁለቱም
“ቀረቡ” (ኤፌ. 2፡13)። (2) እንዲሁም በአይሁድ እና አሕዛብ መካከል
የነበረውን “ጥል ገደለ” (ኤፌ. 2፡16)። የክርስቶስ መስቀል አይሁድና አሕዛብ
የተማማሉ ጠላታሞች የነበሩበትን ቋሚ የጠላትነት እና የጦርነት ሁኔታ አስወገደ
(ኤፌ. 2፡17)። (3) እርቅ የጠላትነትን ስፍራ ይወስዳል። “በመስቀሉም
ሁለቱን በዚህ በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር” ማስታረቅ የክርስቶስ ዓላማና
ግብ ነበር (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ኤፌ. 2፡16፣ ቆላ. 1፡19-22)።
ለመሆኑ እርቅ ምን ዓይነት ገጽታ አለው? እርቅ የመፍጠር ስሜትስ
ምን ይመስላል? በአንዲት እናት እና ሴት ልጇ መካከል ስለተከሰተና ለበርካታ
ዓመታት ስለ ዘለቀ ጽኑ መለያየት አሰብ ያድርጉ። ይህ መራርነት የጸጋና የይቅርታ
ሞገድ ሲፈታው፣ ይህንንም ተከትሎ የሁለቱ አብሮነት ዳግም ሲያንሰራራና ነፍስ
ሲዘራ በዓይነ ሕሊናዎ ይሳሉ። ይህን ሁኔታ እርቅ ብለን እንጠራዋለን። አንድ
የቤተ ክርስቲያን አባል ከሌላው ጋር የሚለያየውን ማንኛውንም ጉዳይ ወደ ጎን
በመተው ይህን አባል እንደ ተወዳጅ ወንድም ወይም እህት ሲቀበልና፣ ግለሰቡም
ለቀረበለት አዎንታዊ ምላሽ ሲሰጥ፣ በዚያው ቅጽበት እርቅ ይወርዳል። እርቅ፡
ስሜት የለሽ ወይም የሕግ አንቀጾችን ብቻ የተሸከመ ቃል ሳይሆን፣ የተበላሹን
ግንኙነቶች መስተካከል የሚያከብር የትስስር መስመር ነው። ክርስቶስ በመስቀል
ላይ የሠራው ብርቱ ሥራ በግለሰቦች ብቻ ሳይሆን በሕዝቦች መካከል ባለ
ግንኙነትም እንዲሁ ዓይነተኛ ተጽእኖ እንዳሳደረ ጳውሎስ ይናገራል። የእርቅ
በሕይወታችን መንሰራፋት--መከፋፈላችንን እያፈረሰ፣ ጠባችንን እየፈታ የእርስ
በርስ ወዳጅነታችንን እና መግባባታችንን እያደሰ እንደሚሄድ ጳውሎስ ተገንዝቧል።
ከሆነ ሰው ጋር እርቅ ለመፍጠር በዚህ ትምህርት የቀረቡትን
መርኅዎች በምን መልኩ ጥቅም ላይ ያውላሉ? እንዴት
ይተገብሯቸዋል?
ክርስቶስ ከሕግ፣ ከትእዛዛቱና ከሥርዐቱ ጋር በተያያዘ ምን ዓይነት እርምጃ ወሰደ ሲል ጳውሎስ ይነግረናል? ይህን ርምጃ ለምን ወሰደ? (ኤፌ. 2፡14-15)።
ጳውሎስ እዚህ ላይ የጠቀሰው በሄሮድስ ቤተ መቅደስ የሚገኘውንና
የእስራኤል አደባባይ የከበበውን የግድያ ዛቻ የተጻፈበትን ግድግዳ ወይም
አጥር ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል። ጳውሎስ ይህ ግንብ ተገርስሶ አሕዛብ
እግዚአብሔርን እንዲያመልኩ ሙሉ በሙሉ ይፈቀድላቸው ዘንድ አስቧል
(ኤፌ. 2፡18)። እንዲህ ያለው ግድግዳ በመስቀሉ ተወግዷል በማለት ጳውሎስ
ይናገራል። እነዚህ ሁለት ሕዝቦች ማለትም አይሁድና አሕዛብ በእርግጥ አንድ
እንደሆኑ እንገነዘባለን።
አንዳንዶች የሰንበትን ትእዛዝ የሚያካትቱት አሥርቱ ትእዛዛት በመስቀሉ
“ተሽረዋል” ወይም “ተወግደዋል” ሲል ኤፌ. 2:14-15 ያስተምራል ብለው
ያምናሉ። ነገር ግን ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ፣ ክርስቲያን ደቀ መዝሙርን
ለመቅረጽ አሥርቱ ትእዛዛትን እንደ ምንጭ በመጠቀም፣ ለትእዛዛቱ ያለውን
ጥልቅ አክብሮት አሳይቷል። አምስተኛውን ትእዛዝ ከመጥቀሱ በተጨማሪ (ኤፌ.
6፡2-3) ለሌሎቹም ትኩረት ሰጥቶአል (ለምሳሌ፡ ሰባተኛውን፣ ኤፌ. 5፡3-14፣
21-33፤ ስምንተኛውን፣ ኤፌ. 4፡28፤ ዘጠነኛውን፣ ኤፌ. 4:25፤ አሥረኛው፣
ኤፌ. 5:5)። ይህ ደግሞ ጳውሎስ ቀደም ሲል ስለ ሕጉ ከተናገረው ጋር
ይስማማል (ሮሜ 3፡31፣ ሮሜ 7፡21)። ሕጉ ያለ አግባብ ጥቅም ላይ ስለዋለበት
መንገድ የሚናገር ሲሆን፣ ነገር ግን ራሱን ሕጉን ያከብራል፣ ስለ ቀጣይነቱም
ግምቱን ያሰፍራል። በተለይ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለ ሕጉ ዘላለማዊነት ከሚናገሩ
ሌሎች ጥቅሶች ብርሃን አኳያ ከመመልከት ይልቅ እነዚህን ጥቅሶች ተጠቅሞ
አስርቱን ትእዛዛት መሻር፣ ጳውሎስ በዚህ ቦታ ላቀረበው ሀሳብ የተሳሳተ ትርጓሜ
መስጠት ነው።
ይልቁንም በአይሁድና በአሕዛብ መካከል ልዩነት ለመፍጠር፣ በተለይም
አሕዛብን ከእግዚአብሔር ሕዝቦች ጋር ሙሉ አጋርነትና የአምልኮ አገልግሎት
እንዳይሰጡ የሚደረግ የትኛውም የሕግ አካሄድ ለጳውሎስ ርኩስ ነው፤ መለኮት
ለሕጉ ያለውን ትርጓሜ በተሳሳተ መንገድ መጠቀም ነው። በኤፌ. 2፡14-
15 “ሕግንም፣ ከትእዛዛቱና ከሥርዐቱ ጋር” በሚል በጳውሎስ የተጠቀሰው
ውስብስብ ሃረግ ላይ የቀረበው “ሕግ”--አይሁዳውያንን ከአሕዛብ የለየው
የሜዳዊ ሥርዓተ ሕግ ገጽታ ነው ወይም ይህ “ሕግ” አይሁዳውያንን ከአሕዛብ
ለማራቅ ሲባል ሲተረጎም፣ ሲስፋፋና እንደ ሽብልቅ አላግባብ እየተሰነጠረ ጥቅም
ላይ ሲውል የነበረ መላው የብሉይ ኪዳን ሥርዓት ነው።
በሰባተኛው ቀን የዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂዎች ወይም በሰፊው
የክርስቲያን ማኅበረሰብ አባላት መካከል የትኞቹን ውጥረቶች
መጋፈጥና ማሸነፍ ያስፈልጋል? ለክርስቶስ ያለን የጋራ ፍቅር
እነዚህን ውጥረቶች ለማሸነፍ በቂ የሆነው ለምንድነው?
ጳውሎስ በኤፌ. 2፡17-18 መልእክቱ የክርስቶስን አገልግሎት ጠቅለል አድርጎ የገለጸው እንዴት ነው?
ለኤፌሶን ሰዎች የተላከው ደብዳቤ የሚጀምረው እና የሚያበቃው በሰላም
ቡራኬ ቃል እንደመሆኑ፣ በዚህ መልእክት የሰላም ጽንሰ ሀሳብ ወሳኝ ነው፡
“ከእግዚአብሔር ከአባታችን፣ ከጌታም ከኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋና ሰላም ለእናንተ ይሁን”
(ኤፌ. 1፡2፣ ኤፌ. 6፡23)። ጳውሎስ ቀደም ባለው ኤፌ. 2፡11-22 መልእክቱ
“ሰላማችን እርሱ ነውና” በማለት ክርስቶስ ሰላምን ይወክላል ሲል የሞገተ ሲሆን፣
መስቀሉ ደግሞ ይህን እንደፈጠረ ይናገራል (ኤፌ. 2፡14-16)። ክርስቶስ በአይሁድ
እና በአሕዛብ መካከል የነበረውን ጠላትነት ማጥፋት ብቻ ሳይሆን (ኤፌ. 2፡14-
15)፣ እነሆ በእርቅና ሰላም ተለይቶ የሚታወቅ አዲስ ሰው በራሱ ፈጠረ (ኤፌ. 2፡
15-17)። ይህ ዓይነቱ ሰላም በግጭት አለመኖር ብቻ የሚገለጽ ሳይሆን ነገር ግን
በዕብራውያኑ ሻሎም ጽንሰ ሀሳብ መሠረት ከእግዚአብሔር ጋርም ሆነ ከሌሎች ጋር
የተሟላና ስምሙ ሁናቴ እና ደኀንነት ከመፍጠር ጋር የሚጣጣም ነው (ሮሜ 5፡1)።
ጳውሎስ የአማኞችን በየሱስ የሰላም መልእክት ተካፋይነት እንዴት
ይመለከተዋል? (ኤፌ. 4:3፤ ኤፌ. 6:14፣ 15፤ የሚከተሉትን
ጥቅሶች ከሮሜ 10፡14-15 ጋር ያወዳድሩ ኤፌ. 2፡17-19፣ ኢሳ.
52፡7፣ ኢሳ. 57፡19)።
የወንጌል መልእክቶች የሱስ የሰላም ሰባኪ መሆኑን የሚያሳዩ
ምሳሌዎች ይዘዋል። ለደቀ መዛሙርቱ ባደረገው የስንብት መልእክት “ ‘ሰላምን
እተውላችኋለሁ፤ ሰላሜን እሰጣችኋለሁ’ ” (ዮሐ. 14፡27) በማለት ቃል
ገብቶላቸው የነበረ ሲሆን፣ መልእክቱን እንዲህ ሲል ደምድሟል “በእኔ ሰላም
እንዲኖራችሁ፣ ይህን ነግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር
ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ. 16፡33)። ከትንሣኤው
በኋላ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ሲገለጥ በተደጋጋሚ እንዲህ ብሏቸው ነበር፡ “ ‘ሰላም
ለእናንተ ይሁን’ ” (ዮሐ. 20፡19፣ 21፣ 26)።
ጳውሎስ በኤፌ. 2፡17-18 መልእክቱ የክርስቶስ የሰላም ስብከት
ከምድራዊ አገልግሎቱ ባሻገር መስፋፋቱን ለመጠቆም እንደጓጓ እናያለን። እርሱ
በወቅቱ “ሩቅ” (አሕዛብ አማኞች ከመለወጣቸው በፊት) እና “ቅርብ”
(አይሁድ አማኞች ኤፌ. 2፡11-13) ለነበሩት ለሁለቱም “ሰላምን ሰበከ”።
ይህን ድንጋጌ የተቀበሉ ሁሉም አማኞች ጥልቅ የሆነ በረከት ተለማምደዋል።
ከግጭት መንስኤዎች በተቃራኒ የሰላም ሰባኪ ስለ መሆን እንዴት
መማር እንችላለን? በአሁኑ ወቅት፣ ለየትኞቹ ሁናቴዎች ፈውስ
እገዛ ማድረግ ይችላሉ?
ጳውሎስ በኤፌ. 2፡11በቤተ ክርስቲያን ባሉ አይሁዶች እና አሕዛብ መካከል ያለውን አንድነት ለማሳየት የተጠቀመው የመጨረሻው ምስል ምንድን ነው?
ኤፌሶን ምዕራፍ ሁለትን ስንገመግም ከቁ. 1-10 እንዴት ከየሱስ
ጋር ኅብረት ፈጥረን እንደምንኖር፣ ከቁጥር 11-22 ደግሞ እንደ ቤተ ክርስቲያን
አካል ከሌሎች ጋር ኅብረት ፈጥረን መኖር እንዳለብን ያስተምራል። የየሱስ ሞት
ከእግዚአብሔር ጋር ግንኙነት ለመመስረት የሚያስችል ከላይ ወደ ታች የተሰመረ
ጥቅም ያለው ሲሆን (ኤፌ. 2፡1-10)፣ አግድሙ ደግሞ ከሌሎች ጋር ያለንን
ግንኙነት ያጠናክራል (ኤፌ. 2፡11-12)። የሱስ የሕጉን አላግባብ ጥቅም ላይ
መዋል ጨምሮ፣ አሕዛብ አማኞችን ከአይሁድ አማኞች የሚለያዩትን ነገሮች ሁሉ
በመስቀሉ አማካይነት አፍርሶአል (ኤፌ. 2፡11-18)። በተጨማሪ የሱስ አማኞችን
ያቀፈ በዓይነቱ አስደናቂና አዲስ ቤተ መቅደስ ገነባ። በአንድ ወቅት አሕዛብ ከቤተ
መቅደሱ ቅዱሳን ስፍራዎች ተገልለው የነበረ ቢሆንም፣ አሁን ግን አዲስ መቅደስ
በመሆን ከአይሁድ አማኞች ጋር ሕብረት ፈጠሩ። እኛ ሁላችን “የጌታ ቅዱስ ማደሪያ”
(ኤፌ. 2፡19-22) የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አካል በመሆን፣ ከየሱስ እና
በክርስቶስ ወንድምና እህቶቻችን ጋር ተባብሮ የመኖር መብትና ጥቅም አገኘን።
ጳውሎስ በኤፌ. 2፡19-22 ቤተ ክርስቲያንን እንደ መቅደስ የጠራበትን
ዘይቤያዊ አነጋገር፣ የሚከተሉትን ጥቅሶች ከጻፈበት አኳያ ያስተያዩ-
-1ቆሮ. 3:9-17፤ 2ቆሮ. 6:14-7:1፤ 1ጴጥ. 2፡4-8።
ጳውሎስ ቤተ ክርስቲያንን በመቅደስ ዘይቤአዊ አገላለጽ በማቅረብ
አሕዛብ ሙሉ በሙሉ ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚካተቱበትን የመጨረሻ ምስል
ያሳያል። በአንድ ወቅት በቤተ መቅደሱ “የእስራኤል ቅጥር” አምልኮ ከማድረግ
ታግደው የነበሩ ወገኖች፣ አሁን አምልኮ ማድረግ ብቻ ሳይሆን (ኤፌ. 2፡18)፣
ነገር ግን እነርሱ ራሳቸው “እግዚአብሔር በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ” ይሆኑ
ዘንድ አብረው የሚገነቡ ሆኑ (ኤፌ. 2፡22)።
የአዲስ ኪዳን ጸሐፊዎች የቤተ ክርስቲያንን ቅድስና፣ ቤተ ክርስቲያንን
በመቆርቆርና በማሳደግ ረገድ የሚኖረውን አምላካዊ ሚና፣ እና በቤተ ክርስቲያን
ውስጥ ያሉ አማኞችን አንድነት ለመሳል ቤተ መቅደስ የተሰኘውን ዘይቤያዊ ቃል
ሲጠቀሙ ይስተዋላሉ። ዘይቤያዊው አገላለጽ ከሥነ ሕይወታዊ ቋንቋ ጥምረት አኳያ
(ኤፌ. 2፡21፣ ቤተ መቅደሱ “ዕድገት” በሚያሳይበት) ጥቅም ላይ የዋለ ሲሆን፣
የግንባታው ሂደት ተደጋጋሚ አጽንዖት ተሰጥቶታል (ኤፌ. 2፡22፣ “እግዚአብሔር
በመንፈሱ የሚኖርበት ማደሪያ ትሆኑ ዘንድ አብራችሁ እየተገነባችሁ ነው”)። ቤተ ክርስቲያን የተሰጣት ግኡዝ ምስል ሳይሆን ነገር ግን “የሕያው እግዚአብሔር ቤተ
መቅደስ” (2ቆሮ. 6፡16) በሚል ማንነቷ ተወስቷል።
ከታች ለተዘረዘሩት የውይይት ጥያቄዎች የሚከተሉትን
የመግቢያ ቃላት በጥሞና ያጥኑ፡
ጳውሎስ በኤፌ. 2፡11-መስቀል በሰዎች ግንኙነት ላይ
የሚያመጣውን መጠነ ሰፊ አዎንታዊ ተጽእኖ በመግለጽ የጻፈበት የመልእክቱ
አውድ ምንድን ነው? ጳውሎስ የቤተ ክርስቲያን አባላት በሆኑት አይሁድ
እና አሕዛብ አማኞች መካከል ስላለው ግንኙነት ሲናገር ይደመጣል። እንደ
እግዚአብሔር ቤተሰብ አባልነታቸው እርቅ በወረደበት የጋራ ማንነት አረዳድ ላይ
የነበረውን ግልጽ ስጋት አስቀምጧል (ኤፌ. 2፡19)። ይሁን እንጂ ከአጠቃላይ
የደብዳቤው አውድ አኳያ ሲታይ፣ ጳውሎስ ሰፊ እና ሩቅ መዳረሻ ያለው ዓላማ
ባለቤት እንደሆነ አሳይቷል። የመልእክቱ ጭብጥ በመጨረሻ ሁሉንም በክርስቶስ
አንድ ስለሚያደርገው (ኤፌ. 1፡9-10) ታላቁ አምላካዊ እቅድ ሲሆን፣
መዳረሻው “በሰማይና በምድር ያለ ቤተሰብን ሁሉ” (ኤፌ. 3፡15) ያካትታል።
በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ምእመናን አንድነት--በዚህ ርዕሰ ጉዳይ ዙሪያ
በተለይ ኤፌ. 2፡11-22 የሚናገር ሲሆን፤ መልእክቱ ጳውሎስ በኤፌ. 3፡10
ለሚገልጸው ሀሳብ ጥልቅ የመፍትሔ ሃሰብ ይዟል፡ “አሳቡም በአሁኑ ዘመን በቤተ ክርስቲያን አማካይነት ብዙ ገጽታ ያለው የእግዚአብሔር ጥበብ በሰማያዊ ስፍራ
ላሉት አለቆችና ባለ ሥልጣናት ይታወቅ ዘንድ ነው።” ክርስቶስ በመስቀል ላይ
ያሸነፈውን አንድነት በተግባር በማዋል፣ አማኞች ሁሉንም ነገር በክርስቶስ አንድ
የማድረጉ አምላካዊ የመጨረሻ እቅድ እየተካሄደ ለመሆኑ፣ እንደ ማስጠንቀቂያ
ምልክት ማሳወቅ አለባቸው። እርቅ የወረደበት ግንኙነታቸው፣ አጥናፈ ሰማይ
በክርስቶስ አንድ ይሆን ዘንድ የቀደመው አምላካዊ እቅድ ምልክት ነው። ስለዚህ
ከሰዎች፣ ከቡድኖች ወይም ከነገዶች ጋር የግንኙነት መስመር ለመፍጠር ያግዝ
ዘንድ ኤፌ. 2፡11-22 ከመጽሐፍ ቅዱስ መርኅ አኳያና በአጠቃላይ ከኤፌሶን
ሰዎች ዐውድ መመልከቱ፣ ገጣሚና ለዚህ ዘመን በእጅጉ አስፈላጊ ነው።
1. የብሔረሰብ ግንኙነቶችን አስመልክቶ በኤፌ. 2፡11-22
ምን ዓይነት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርኅዎች ተሰጥተዋል?
የአንዱ ብሔረሰብ አባል ከሌላው ጋር እንዴት ግንኙነት
ሊፈጥር ይገባል በሚለው ጭብጥ ዙሪያ ከመልእክቱ
የምናገኘው በዓይነቱ የተለየና ክርስቶስን ያማከለ አቀራረብ
ምን ይመስላል?
2. እግዚአብሔር ወደ ፊት ለሰብዓዊው ፍጡር ያለውን
እቅድ (ኤፌ. 1:9, 10፤ ኤፌ. 2:11-22) ስንመለከት
ቤተ ክርስቲያን የራሷን ውስጣዊ ጉዳዮችና በዘር መካከል
ያሉ ግጭቶችን ማስተናገድ መቻሏ ምን ያህል አስፈላጊ
ነው?
3. በማኅበረሰባችሁ ውስጥ ብዙውን ጊዜ የተደበቁና ችላ
የተባሉ የሚመስሉ፣ ነገር ግን በጎሳዎች መካከል አወዛጋቢ
የሆኑ ምን ጉዳዮች አሉ? ቤተ ክርስቲያናችሁ ክርስቶስ
በመስቀል ላይ ያከናወነውን አንድ የማድረግ ሥራ እውን
በማድረግ ረገድ ጠቃሚ ሚና ልትጫወት የምትችለው
እንዴት ነው? እርስዎ እንዴት የዚህ ሥራ ተካፋይ መሆን
ይችላሉ?