የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሐምሌ 8 - 14

4ኛ ትምህርት

Jul 15 - 21




እግዚአብሔር እንዴት እንደተቤዠን



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 2፡ 1-10፤ ኤፌ. 5፡14፤ ሮሜ. 5፡17፤ ኤፌ. 5፡6፤ 2ጢሞቴ. 1፡7


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ፣ በበደላችን ሙታን ሆነን ሳለ፣ በክርስቶስ ሕያዋን አደረገን፤ የዳናችሁት በጸጋ ነው።” (ኤፌ. 2፡4-5)።

በጎርጎሮሳውያኑ ጥቅምት ወር 1987 ላይ ጀሲካ ማክሉር የምትባል የአንድ ዓመት ከስድስት ወር ብላቴና አክስቷ ጓሮ እየተጫወተች እያለ፣ ሳይታሰብ ክፍቱን የተተወ ሰባት ሜትር ጥልቀት በነበረው ጠባብ የውሃ ጉድጓድ ውስጥ ወደቀች። የደረሰባት አስጨናቂ ዱብዳ ከነበረችበት የቴክሳስ ግዛት እስከ ዓለም ዙሪያ የመገናኛ ብዙሃንን ቀልብ ሳበ። ብላቴናዋ ጀሲካ ጉድጓዱ ውስጥ ሆና አንዴ ስታለቅስ፣ ሌላ ጊዜ እንቅልፍ ሸለብ ሲያደርጋት፣ ስትዘምር፣ እናቷን ስትጣራ-- ዓለም በቴሌቪዥን መስኮት ተመለከታት። የድንገተኛ አደጋ ሠራተኞች ልዩ መሣሪያ በመጠቀም ንጹህ አየር ወደ ጉድጓዱ እንዲገባ ሲያደርጉም እንዲሁ ይታዩ ነበር።

በመጨረሻ ጀሲካ ጉድጓዱ ውስጥ ከወደቀች ከሃምሳ ስምንት ሰዓታት በኋላ 20.3 ሴንቲ ሜትር ወይም ስምንት ኢንች ስፋት ከነበረውና አላፈናፍን ካላት ጉድጓድ ውስጥ ከሁለት ቀናት በኋላ ወጣች። ጀሲካ ከጉድጓዱ እንደወጣች በፋሻ ተጠቅልላ የነበረችውን ይህችን ብላቴና አቀርቅረው ይመለከቱ የነበሩትን የተሸበሩ የነፍስ አድን ሠራተኞች ጭንቀት በአስገራሚ ሁናቴ በካሜራው ያስቀረው ፎቶግራፍ አንሺው ስኮት ሻው፣ በፎቶግራፍ ዘርፍ የ-ፑላይዘር የዓመቱ አሸናፊ ሆኖ ነበር።

እንደ ጥሩ የማዳን ታሪክ ያህል አጓጊ ነገር የለም። ጳውሎስ በኤፌ. 2፡ 1-10 መልእክቱ እግዚአብሔር ሰብዓዊውን ፍጡር ለመቤዠት እያደረገ ያለውን ሁሉን አካታች ግዙፍ ጥረት በቅርብ እና በግል እንድንመለከት ያደርገናል። እኛ የሌላውን መዳን ተመልካቾች ብቻ ሳንሆን ነገር ግን የገዛ ራሳችን ምስክሮች መሆናችንን ማወቃችን የታሪኩን ሁነት የላቀ ያደርገዋል።

ሐምሌ 9
Jul 16



በአንድ ወቅት ሙት እና በሰይጣን የተታለልን


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 2፡1-10። ጳውሎስ የሱስ ያደረገልንን ነገር አስመልክቶ በመልእክቱ የሰጠን ዋነኛ ሐሳብ ምንድን ነው?



ጳውሎስ ለክርስቲያኖች የተሰጠውን መዳን ቀደም ሲል የገለጸ ሲሆን (ኤፌ. 1፡3-14፣ 15-23)፣ በኤፌሶን የነበሩ አማኞችን ታሪክም በአጭሩ አስቀምጧል (ኤፌ. 1፡13)። በኤፌ. 2፡1-10 ላይ ጳውሎስ ወደ ክርስትና ስለ ተለወጡበት ታሪክ ላቅ ያለ ግላዊ ትኩረት በመስጠት በዝርዝር ይነግራቸዋል። ያለፈውን ኃጢአት መር ሕይወታቸውን (ኤፌ. 2፡1-3) ከእግዚአብሔር ማዳን በረከቶች ጋር በማነጻጸር የሚያቀርበው ሲሆን፣ ይህን የሚያደርገው ከክርስቶስ ትንሣኤ፣ ዕርገትና መክበር አኳያ በመሳል እና (ኤፌ. 2፡4-7) ያን የመዳን መሠረት በእግዚአብሔር ጸጋና የፍጥረት ሥራ በማክበር ነው። (ኤፌ. 2፡8-10)።

እነዚህ ሦስት የጥቅሱ ክፍሎች በኤፌ. 2:5 ባሉት ሃረጎች ጥሩ ሆነው ተጠቃለዋል:- (1) “በበደላችን ሙታን ነበርን”፤ (2) [እግዚአብሔር] ከክርስቶስ ጋር ሕያዋን አደረገን፤ (3) “በጸጋ ድናችኋል”።

በኤፌ. 2፡1-2 ጳውሎስ ታዳሚዎቹ በደልንና ኃጢአትን መደበኛ የሕይወታቸው ዘይቤ አድርገው የሚመላለሱ፣ (ኤፌ. 2፡1) በመንፈስ ሙታንና በሰይጣን አገዛዝ ስር (ኤፌ. 2፡2) እንደነበሩ በማውሳት፣ ከመለወጣቸው በፊት የነበራቸውን አሳዛኝ እውነታ ያሰምርበታል። ጳውሎስ መልእክቱን የጻፈው ለሕያዋን እንደመሆኑ፣ እነርሱን በአንድ ወቅት “ሙታን” ነበራችሁ በሚል ዘይቤያዊ አገላለጽ ይጠቅሳቸዋል (ኤፌ. 5፡14 ያስተያዩ)። ነገር ግን በአንድ ወቅት የሕይወት ምንጭ ከሆነው ከእግዚአብሔር አምላክ ተለይተው ስለ ነበር ችግራቸው እጅግ ተጨባጭና አስከፊ ነበር (ቆላ. 2፡13፣ ሮሜ 5፡ 17፣ ሮሜ 6፡23)። ጳውሎስ በአድማጮቹ የቀድሞ ሕይወት ዙሪያ በማሰላሰል በእነርሱ ላይ ይሠለጥኑ የነበሩትን ሁለት ውጫዊ ኃይሎች ገልጿል። ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው “የዓለምን ክፉ መንገድ” መከተላቸው ነው (ኤፌ. 2:2)-በኤፌሶን ማኅበረሰብ ውስጥ በስፋት ተንሰራፍተው የነበሩት ልማዶችና ባሕሪያት የሰው ልጅ ሕይወት በአምላክ ላይ እንዲያምጽ አድርገው ነበር።

ሰይጣን እንደ ቀደመው ሕይወታቸው ሁለተኛ ውጪያዊ ኃይል የበላይ ገዥነቱ፣ በሁለት መንገዶች ተጠቅሶአል። እርሱ “በአየር ላይ ላሉት መንፈሳዊ ኃይላት ገዥ” (ኤፌ. 2፡2) ነው። “አየር” (ወይም “ሰማያዊ ስፍራዎች”) ክፉውን ጨምሮ እንደ ልዕለ ተፈጥሮ ኃይላት መገኛ መታወቁ እሙን ነው (ኤፌ. 1፡ 3፣ ኤፌ. 3፡10፣ ኤፌ. 6፡12)። እርሱ “አሁንም ለእግዚአብሔር በማይታዘዙት ሰዎች” (ኤፌ. 2፡2) እየሠራ እንደ መሆኑ በዚህ ምድር ንቁ ነው።

እነዚህ ጥቅሶች ስለ ታላቁ ተጋድሎ እውነታ ምን ያስተምራሉ? በተመሳሳይ--የሱስ ድል ማድረጉና እኛም የእርሱ ድል ተቋዳሾች መሆን እንደምንችል ማወቃችን እንዴት መጽናናትና ተስፋ ሊሰጠን ይችላል?

ሐምሌ 10
Jul 17

በአንድ ወቅት በገዛ የሥጋ ምኞቶቻችን የተታለልን፤


“በእነዚህም ልጆች መካከል እኛ ሁላችን ደግሞ፥ የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበርን እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን።” (ኤፌ. 2፡3)።

ከእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ውጪ ያለው ሰብዓዊ ህልውና በኤፌ. 2፡ 2 በተጠቀሱት ውጫዊ ኃይላት ብቻ ሳይሆን በውስጣዊ ኃይሎችም እንዲሁ የበላይ ተጽእኖ ስር ወድቆ ነበር፡ “የሥጋችንንና የልቡናችንን ፈቃድ እያደረግን፥ በሥጋችን ምኞት በፊት እንኖር ነበር” (ኤፌ. 2፡3፣ ያዕ. 1፡14-15፣ 1ጴጥ. 1፡14)።

ጳውሎስ “እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን” (ኤፌ. 2፡3) በማለት ለአድማጮቹ ለማስተላለፍ የፈለገው መልእክት ምንድን ነው? (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ኤፌ. 2፡3 እና ኤፌ. 5፡6)።



አሁን እየተስተዋለ ያለው የነፍሳት መጥፋት እውነታ በበቂ ሁኔታ አስጨናቂ ቢሆንም፣ የመጨረሻው ቀን አንደምታዎች ግን ይበልጥ አስፈሪ ናቸው። “እንደ ሌሎቹም ደግሞ ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች” የነበርን (ኤፌ. 2፡3) ሰብዓዊ ፍጡራን፣ በመጨረሻው ጊዜ በአስፈሪው አምላካዊ ፍርድ ፊት እንቆማለን።

“ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች” ነበርን የሚለው ሃረግ ሌላ አስፈሪ እውነታንም ያመለክታል። የከበረው አምላካዊ አምሳል ተሸካሚዎች ሆነንም እንኳ፣ ውስጣችን በእጅጉ ግራ የሚያጋባ ነገር እንዳለ ተረድተናል። የክርስትናን ሕይወት መኖር ማለት--አንድ ወይም ሁለት መጥፎ ልማዶችን ማሸነፍ ወይም በዚህ ወቅት አስጊ የሆነውን ማንኛውንም “በደልና ኃጢአት” ማሸነፍ ብቻ አይደለም (ኤፌ. 2፡1)። የምንታገለው ከኃጢአቶች ጋር ብቻ ሳይሆን ከኃጢአት ጋር ነው። በእግዚአብሔር ላይ ለማመጽና ራሳችንን ለማጥፋት ቆርጠን ተነስተናል። የሰዎች ነባራዊ ርምጃ ራስን በሚያጠፋ፣ የሰይጣንን ትእዛዝ በሚከተል (ኤፌ. 2፡2) ኃጢአተኛ ባህሪና ሞኞት ተጠምዷል። አማኞች በአንድ ወቅት “ከፍጠረታቸው የቁጣ ልጆች” ነበሩ”።

ጳውሎስ የአሁን ሳይሆን የሃላፊ ጊዜ በመጠቀም፡ “ከፍጥረታችን የቁጣ ልጆች ነበርን” (ኤፌ. 2፡3) ሲል መጻፉን ልብ ማለት ተገቢ ነው። ሆኖም ይህ--ለክፉ ያዘነበለ ተፈጥሮአዊ ባህሪ በአማኞች ውስጥ መኖሩ አክትሟል ማለት አይደለም።

ጳውሎስ ከኤፌ. 4:17 እስከ 5:21 የመልእክቱን ክፍል እንደጻፈው-- በኃጢአተኛው ተፈጥሮ ላይ የተመሠረቱ ኃጢአተኛ ድርጊቶች ለክርስቲያኖች ስጋት ሆነው እንደሚቀጥሉ በቂ ምልከታ ሰጥቶ አስጠንቅቋል። ይህ ማለት ከዚህ በኋላ “አሮጌው ሰውነት” በአማኙ ላይ ሊሰለጥን ስለማይገባ በክርስቶስ ኃይል “አሮጌ ሰውነታችሁን አውልቃችሁ እንድትጥሉ… ደግሞም በአእምሮአችሁ መንፈስ እንድትታደሱ፣ እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው” (ኤፌ. 4፡22-24)።

ራሳችንን ለየሱስ ከሰጠን በኋላም እንኳ ተፈጥሮአችን ምን ያህል ብልሹ እንደሆነ ያላስተዋለ ማን ነው? በሕይወታችን እያንዳንዱ ቅጽበት ከእርሱ ጋር መጣበቅ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ አስመልክቶ ይህ ምን ሊያስተምረን ይገባል?

ሐምሌ 11
Jul 18

እነሆ አሁን ከክርስቶስ ጋር ተነሥተናል፣ ዐርገናል፣ ከብረንማል፤


“ነገር ግን በምሕረቱ ባለጠጋ የሆነ እግዚአብሔር ለእኛ ካለው ከታላቅ ፍቅሩ የተነሣ” (ኤፌ. 2፡4)። እዚህ ላይ ጳውሎስ “እግዚአብሔር… ግን” በሚሉት ሁለት ኃይለ ቃላት የአንባቢዎቹን ያለፈ አሳዛኝ ሕይወት ታሪክ (ኤፌ. 2፡ 1-3) ከገለጸ በኋላ፣ የአማኞችን ሕይወት ወደሚያሳዩት አዲስና በተስፋ የተሞሉ እውነታዎች ያልፋል (ኤፌ. 2፡4-10)።

አማኞች በክርስቶስ ትንሣኤ፣ ዕርገት እና መክበር በምን መልኩ ተሳታፊዎች ይሆናሉ? ይህ ተሳትፎ ገቢራዊ የሚሆነው መቼ ነው? ኤፌ. 2፡6-7።



ለኤፌሶን ሰዎች የተላከው መልእክት፣ የአማኞችን ከክርስቶስ ጋር ያለ አንድነት የሚያጎላ በክርስቶስ የተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን አስተውለናል። በኤፌ. 2፡ 5 እና 6 መልእክቱ፣ ጳውሎስ ሦስት ግሦችን በማካተት ይህን ጭብጥ የሚያስፋፋው ሲሆን፣ ይኸውም አማኞች ራሳቸው በእግዚአብሔር ተነሳሽነት በመሲሁ በየሱስ ዙሪያ በሚያተኩሩ አስፈላጊ የመዳን ታሪክ ክስተቶች ተሳትፎ የሚያደርጉበትን አስደናቂ እውነት ለመግለጽ ነው።

አማኞች፡ (1) ከክርስቶስ ጋር አብረው ተነሥተዋል፤ (2) ከክርስቶስ ጋር አብሮ መነሣት (ምናልባት ጳውሎስ በክርስቶስ ዕርገት የአማኞችን ተሳትፎ ለማመልከት ሳይጠቀምበት እንዳልቀረ ይታመናል) (3) ከክርስቶስ ጋር “በሰማያዊ ስፍራ” ተቀምጠዋል፣ ማለት--አማኞች በክርስቶስ ሰማያዊ ዙፋን “መቀመጥ” ተሳትፎ ያደርጋሉ የሚል አንደምታ አለው።

የጳውሎስን ሞጋች ሀሳብ ግዝፈት ለማስተዋል እንደገና ወደ ኤፌ. 1፡ 19-23 መለስ ብለን የክርስቶስን ሞት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገትና መክበር በመቃኘት-- በአንድ ወቅት የአማኞችን ሕይወት ይገዙ በነበሩት፣ በሁሉም ክፉ እና መናፍስታዊ ኃይላት ላይ የተቀዳጀውን ድል ማስታወስ ይኖርብናል። እነዚህ ኃይላት አሁንም በሰብዓዊው ሕልውና ላይ በንቃት እየሰለጠኑ ያሉና አስጊ ቢሆኑም እንኳ--በየሱስ ትንሣኤ፣ ዕርገትና መክበር ሙሉ በሙሉ ተተክተዋል። የዩኒቨርስ ነባራዊ ሁኔታ ተቀይሮአል። እውነታው ተለውጦአል። አማኞች የእነዚህን ክስተቶች ተመልካቾች ብቻ ሳይሆኑ ነገር ግን በግለሰብ ደረጃ፣ በቅርበት ተሳትፈዋል። ከየሱስ ጋር መነሣታችን፣ ማረጋችን እና መክበራችን በርካታ አዳዲስ መልካም ዕድሎች ይከፍትልናል። በአጋንንት ከሚገዛው ማንነት ወደ ተትረፈረፈ መንፈሳዊ ሕይወት፣ በክርስቶስ የመለወጥ መብት አለን (2ጢሞቴ. 1፡7)።

“እግዚአብሔር የኃይልና የፍቅር፣ ራስንም የመግዛት መንፈስ እንጂ የፍርሀት መንፈስ አልሰጠንምና።” (2ጢሞቴ. 1፡7)።

በዛሬው ጥናታችን የተመለከትናቸው ጥቅሶች፣ ጳውሎስ በዚህ ስፍራ የጻፈውን እንዴት ለመረዳት ያስችሉናል?

ሐምሌ 12
Jul 19

አሁን በጸጋው ለዘላለም ተባርካችኋል፤


በኤፌ. 1፡3-4 የቀረበውን የእግዚአብሔር የድነት እቅድ በኤፌ. 2፡ 7 ከተገለጸው ዘላለማዊ ውጤት ጋር ያስተያዩ። የእግዚአብሔር “የማዳን ዕቅድ” አስፈላጊ ባህሪያት እና ግቦች ምንድን ናቸው?



የመዋዕለ ሕፃናትም ሆነ የዶክትሬት ዲግሪ ምርቃቶች፣ ድንቅ የደስታ መግለጫ ሥነ ስርዓቶች ናቸው። የምረቃ ሥነ ሥርዓት ወደ ሌላኛው የሕይወት ወይም የሙያ ልቀት መሻገርን የሚያሳይ ትልቅ የስኬት ማሳያ ነው። እንደ አማኞች የወንጌልን ጥልቅ እውነት መረዳታችን አስፈላጊ ነው--ከጸጋ ባንመረቅም!

ጳውሎስ ይህን እውነት ባልተገደበ የሚመስል የዘመን ቅደም ተከተል ድምጸታዊ ቃና በኤፌ. 2፡7 ያረጋግጥልናል። እግዚአብሔር እኛን ለመቤዠት ቀደም ሲል በክርስቶስ በመሥራቱና እኛን በልጁ በየሱስ ክርስቶስ በማየቱ፣ እነሆ ዛሬ የትንሣኤው፣ የዕርገቱ እና የመክበሩ ተባባሪዎች ሆነናል (ኤፌ. 2፡4-6)። ሆኖም የእግዚአብሔር እቅድ ጸጋ በሞላው--ያለፈ ጊዜ እና ምኅረት በተነከረ የአሁን-- ጊዜ አያበቃም። ከጥንቱ መለኮታዊው የመማክርት ጉባዔ አንስቶ የተመሠረተው አምላካዊ እቅድ (ኤፌ. 1፡14) ወደፊትም እስከ ዘላለም ይዘልቃል። ይኸውም “በሚመጣው ዘመን” (ኤፌ. 2፡7) የሚሆነውን ሁሉ ያጠቃልላል። ዘላለማዊ የወደፊት እቅዱ የተመሠረተው እንዳለፈው እና እንደ አሁኑ ጊዜ ሁሉ፣ በተመሳሳይ መርኅ ላይ ነው። እግዚአብሔር አምላክ “በሚመጣው ዘመን በክርስቶስ ኢየሱስ በቸርነቱ የገለጠልንን ወደር የሌለውን የጸጋውን ባለጠግነት ያሳይ ዘንድ” እነሆ ወደፊት አሻግሮ ይመለከታል (ኤፌ. 2፡7)።

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ጸጋ--አማኞች የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ እንደሚያገኙበት የከበረ ሐብት ወይም ሊለካ የማይችል ዋጋ እንዳለው ንብረት አድርጎ ያስባል (ኤፌ. 1፡7፣ ኤፌ. 3፡8)። ይህ በእግዚአብሔር ለእኛ የተበረከተ ታላቅ ልግስና--የከበረው፣ ዘላለማዊውና በመላው ዩኒቨርስ ፊት ይፋ የሆነ ጸጋው ነው።

“ኢየሱስ ከእኛ ጋር ለመኖር የመጣው እግዚአብሔርን ለሰዎችና ለመላእክት ለመግለጽ ሲል ነው።… ይህ ራእይ የተሰጠው ለምድራዊ ልጆቹ ብቻ አልነበረም። ይህች ትንሽ ዓለማችን ለዩኒቨርስ የማስተማሪያ መጽሐፍ ነች። የእግዚአብሔር አስገራሚ ጸጋ፤ የማዳን ፍቅሩ ምስጢር መላእክት ለማወቅ የሚሹት አርዕስት ሲሆን ለዘለዓለም የሚያጠኑት ትምህርት ይሆናል። ከኃጢአት የተዋጁትና በኃጢአት ያልወደቁት ሁሉ የክርስቶስ መስቀል ሳይንሳቸውና መዝሙራቸው ይሆናል። በየሱስ ፊት ላይ የሚያበራው ክብር የመሥዋእትነት ፍቅር ሆኖ ይታያል።” (የዘመናት ምኞት፡ ገጽ 9)።

ሐምሌ 13
Jul 20

አሁን በእግዚአብሔር ድናችኋል


ወደ ኋላ መለስ ብለው ኤፌ. 2፡1-10 በማንበብ፣ ጳውሎስ ከቁ. 8-10 በጻፈው መደምደሚያ ላይ ትኩረት ያድርጉ። በጽሑፉ መደምደሚያ ጳውሎስ አጽንኦት የሚሰጣቸው ነጥቦች ምንድን ናቸው?



ጳውሎስ በኤፌ. 2፡1-3 መልእክቱ የኤፌሶን አማኞች መዳን ያገኙት በመልካም ባህሪያቸው ወይም ማራኪ ማንነታቸው እንዳልሆነ ዘግቦ እናገኛለን።

ታሪኩ ሲጀምር በመንፈስ ሙት ሆነው እናገኛቸዋለን። በእነርሱ ውስጥ አንዳችም የሕይወት እንጥፍጣፊ አልነበረም (ኤፌ. 2፡1)። ሙሉ ለሙሉ በኃጢአት ቁጥጥር ስር ውለዋል (ኤፌ. 2፡1)። ምንም ዓይነት የግል እቅድና ተነሳሽነት ያልነበራቸው እነዚህ ሰዎች፣ በራሱ በሰይጣን እና በገዛ ራሳቸው የውስጥ ምኞቶችና የአእምሮ መደለያዎች ይመሩ ነበር (ኤፌ. 22-3)።

እነዚህ ሰዎች ለእነርሱ ባልተገለጠ፣ መንፈሳዊ ሕይወትም ሆነ በጎነት በሌለበት የከፋ ሁኔታ ውስጥ ይገኛሉ። እነዚህ ሰዎች ከመላው ሰብዓዊ ዘር ጋር በአንድነት የእውነተኛው አምላክ ጠላቶች ከመሆናቸውም በላይ፣ ወደ መጨረሻው መለኮታዊ የፍርድ ቀን እየተጓዙ ነው። “እንደ ሌሎቹም የቁጣ ልጆች” ናቸው (ኤፌ. 2፡3)።

መዳናቸው በገዛ ራሳቸው መልካም ነገሮች ላይ ሳይሆን፣ ሊገለጽ በማይችል ምስጢራዊ የእግዚአብሔር ፍቅር ላይ የተመሠረተ ነው። እግዚአብሔር በምኅረትና በፍቅር በክርስቶስ የሱስ አማካይነት (ኤፌ. 2፡4) ከመንፈሳዊ ሞት አስነሣቸው። እግዚአብሔር ጣልቃ በመግባቱ የተነሣ አስደናቂ በሆነው በራሱ በየሱስ የታቀደ የጉዞ መስመር ውስጥ አለፉ። ከፍጹም መንፈሳዊ ሞትና ከጨቋኝ ባርነት አዘቅት ወጥተው ወደ “ሰማያዊ ስፍራዎች” በመተላለፍ ከክርስቶስ ጋር በሰማያዊው ዙፋን እንዲቀመጡ ሆኑ (ኤፌ. 2፡5-6)። ይሁን እንጂ ይህ መብረቅ መሰል መለኮታዊ ጣልቃ ገብነት ጊዜያዊ ክስተት አይደለም። እግዚአብሔር ለዘላለም በክርስቶስ የሱስ ለእነርሱ ጸጋውን ያሳያቸው ዘንድ እቅዱ በመሆኑ፣ እውነተኛ አብሮ የሚጸና ኃይልና ዘላለማዊ ጥንካሬ አለው (ኤፌ. 2፡7)።

ጳውሎስ በኤፌ. 2፡1-10 ያቀረበውን መልእክት ከቁ. 8-10 ሲደመድም፡--የአማኞች መዳን የሰው ሳይሆን የመለኮት ሥራ ነው። ከእኛ ውስጥ የመነጨ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ስጦታ ውስጥ የተገኘ ነው። ማንም ሰብዓዊ ፍጡር ራሱን የጉዳዩ መንስኤ አድርጎ ሊመካ አይችልም (ኤፌ. 2፡8-9)።

እኛ አማኞች በእግዚአብሔር ጸጋ እንደ መቆማችን፣ የጸጋው እና የጸጋው ብቻ መገለጫዎች ነን። እኛ በክርስቶስ የተፈጠርን ድንቅ የእግዚአብሔር እጅ ሥራዎች ነን (ኤፌ. 2፡10)። መዳናችን ከእግዚአብሔር እንደሆነ እና በራሳችን ዋጋ ወይም ጥረት ላይ ያልተመሠረተ መሆኑን መረዳታችን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 14
Jul 21


ተጨማሪ ሀሳብ


ብዙውን ጊዜ ሲጠቀስ የሚደመጠው ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈው መልእክት መሠረታዊ ሀሳብ ዋና ዋና ክስተቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
1. እግዚአብሔር ሕዝቦቹን የመረጠው “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ ነው” (ኤፌ. 1፡4-5፣ 11)
2. ያለፈ ማንነታቸው ሕይወት ዐልባ ነበር (ኤፌ. 2፡1-3፣ 11፣ 12፤ ኤፌ. 4፡17-19፣ 22፤ ኤፌ. 5፡8)።
3. እነርሱን ለማዳን እግዚአብሔር በክርስቶስ አማካይነት ጣልቃ ገባ ((ኤፌ. 1፡7፣ 8፣ ኤፌ. 2፡4-6፣ 13-19፤ ኤፌ. 4፡1፣ 20፣ 21፤ ኤፌ. 5፡2፣ 8)። 23፣ 25፣ 26)።
4. ወንጌልን መቀበላቸው (ኤፌ. 1፡12፣ 13) በአንድ ወቅት “ያለ ተስፋ” ነበሩ (ኤፌ. 2፡12) አሁን አማኞች “አንድ ተስፋ” ይዘው ይንቀሳቀሳሉ (ኤፌ. 4፡4፤ ከኤፌ. 1፡18 ጋር ያወዳድሩ)።
5. ደብዳቤው የተጻፈው አሁን በደቀ መዝሙርነት ሕይወት ለሚገኙ ነው። ምንም እንኳ አደጋዎች እና የክፉ ኃይሎች ተቃውሞ በሞላበት ጊዜ ውስጥ ቢኖሩም፣ የከበረው ጌታቸው የሚያስፈልጋቸውን ያሟላላቸው ነበር (ኤፌ. 1፡15-23፣ ኤፌ. 2፡6፣ ኤፌ. 3፡14-21 ኤፌ. 4፡7-16፣ ኤፌ. 6፡10-20)። 6 ወደፊት የምድር ታሪክ ሲደመደም፣ መንፈስ እንደ “ዋስትና” (ኤፌ. 1፡ 13-14) ወይም “ማኅተም” (ኤፌ. 4፡30) የተጫወተው ሚና-- ፍሬያማ ይሆናል። በዚህ የድል ብስራት ወቅት መልእክቱ የተጻፈላቸው፣ ስለ ታማኝነታቸው አስቀድሞ በክርስቶስ የተሰጣቸውን “ርስት” ይወርሳሉ (ኤፌ. 2:7፤ ኤፌ. 6:8, 9)። እንዲሁም በክርስቶስ ላይ ባላቸው እምነት፣ ክርስቶስን ባማከለው መጪው ዘመን ስፍራ ይሰጣቸዋል (ኤፌ. 1:21፤ ኤፌ. 2:7, 19-22፤ ኤፌ. 4:13, 15፤ ኤፌ. 5) : 27)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ከላይ የቀረበው ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈ ታሪክ፣ በመጀመሪያው ክፍለ ዘመን የነበሩ አማኞች ታሪክ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የገዛ ራሳችን ታሪክ ነው። በዚህ ወቅት የላቀ ተስፋ የሚሰጥዎት ከታሪኩ የትኛው ክፍል ነው?

2. ጳውሎስ የአድማጮቹን የኃጢአት ታሪክ በተደጋጋሚ እያስታወሰ ወደ ክርስትና ከመለወጣቸው በፊት ስለ ነበሩበት ሕይወት እንዲያሰላስሉ የሚጋብዛቸው ለምንድን ነው?

3. በኤፌሶን 2፡8-10 የሚገኘውን የጳውሎስን መልእክት ማጠቃለያ ከቀደመው ሮሜ 1፡16፣ 17 ማጠቃለያ ጋር ያስተያዩ። ምን ተመሳሳይ ጭብጦች ቀርበዋል? ሁለቱ እንዴት ይለያያሉ?

4. የአማኞች መልካም ሥራ ለመዳናቸው አንዳችም ዓይነት ሚና የለውም፤ ወይም ሰዎች በእግዚአብሔር ፊት ጻድቅ ስብዕና እንዲላበሱ ማድረግ አይችልም፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለአማኞች በዘረጋው እቅድ ውስጥ ምን ጠቃሚ ሚና ይጫወታል? ኤፌ. 2፡10።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL