የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሐምሌ 1 - 7

3ኛ ትምህርት

Jul 8 - 14




የከበረው የሱስ ኃይል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ. 1:15-23፤ ኤፌ. 3:14-21፤ 1 ተሰ. 5:16-18፤ ዘዳ. 9:29፤ 1 ቆሮ. 15:20-22፤ መዝ. 110፡1።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኃይሉን እንድታውቁ እጸልያለሁ። ይህም ኃይል እንደ እርሱ ታላቅ ብርታት አሠራር፣ ክርስቶስን ከሙታን ሲያስነሣውና በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው የታየው ነው።” (ኤፌ. 1፡19-20)።

የሰው ልጆች ሁሌም ቢሆን የተጨማሪ ጉልበት ባለቤት ለመሆን የሚጥሩ ይመስላሉ። ለምሳሌ ዴቨል ሞተርስ የተባለው የመኪና አምራች ኩባንያ ከ5ሺ በላይ የፈረስ ጉልበት ያለውን ባለ 16 ሲሊንደር እና 12.3 ሊትር ሞተር ስሪቱን፣ ዴቨል አሥራ ስድስት ሞዴል መኪና አቅርቧል። ወይም ደግሞ ይህ በቂ ካልሆነ የጀት ሞተር የተገጠመለትን የፔተርቢልትን Pratt & Whitney J34-48 ከፊል የጭነት መኪና ይመልከቱ። ይህ 36ሺ የፈረስ ጉልበት ያለው ከፊል የጭነት መኪና በ6.5 ሴኮንድ ውስጥ ግማሽ ኪሎ ሜትር፣ ሁለቱን ፓራሹቶች ከመዘርጋቱ በፊት ደግሞ 376 ኪሎ ሜትር በሰዓት ይከንፋል!

በአንጻሩ፣ ጳውሎስ በኤፌሶን ያሉ አማኞች የባህላቸው አካል የሆኑ ልዩ ልዩ ኃይላትንና አማልክትን በማድነቅ በሚፈተኑ ጊዜ፣ እግዚአብሔር በክርስቶስ ለእነርሱ የሚያቀርበውን ታላቅ ኃይል በመንፈስ ቅዱስ ይለማመዱ ዘንድ ይጸልያል። ይህ መለኮታዊ ኃይል የሚለካው በፈረስ ጉልበት ወይም በአስማት አይደለም፤ ነገር ግን በደኅንነት ታሪክ ክስተቶች አራቱ ምስጢራዊ ኃይላት ታይቷል፡ (1) የየሱስ ትንሣኤ (2) በእግዚአብሔር ዙፋን መክበሩ (3) ሁሉም ነገር ለክርስቶስ መገዛቱ (4) ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ ሆኖ መሰጠቱ (ኤፌ. 1፡19-23)።

ስለ እነዚህ አራት ክንውኖች ሲያስቡ፣ አማኞች እግዚአብሔር ለእነርሱ ሲል የገለጠውን መጠነ ሰፊ አምላካዊ ኃይል መረዳትና መለማመድ ሊጀምሩ ይችላሉ።

ሐምሌ 2
Jul 09

መጸለይና ማመስገን


በኤፌሶን ያሉ አማኞች በየሱስ ላይ ያላቸው ፍቅር ብሎም የእርስ በርስ መዋደዳቸው እየጎለበተ የመሄዱን ወሬ በመስማቱ የተበረታታው ጳውሎስ (ምናልባትም በቲኪቆስ የተነገረው ዜና፣ ኤፌ. 6:21-22) ምን ያህል እየጸለየላቸው እንደሆነ ይነግራቸዋል።

ሁለቱን የጳውሎስ የጸሎት ዘገባዎች ያወዳድሩ--ኤፌ. 1፡15-23 እና ኤፌ. 3፡14-21። ሁለቱ ዘገባዎች የሚያካፍሉት ጭብጥ ምን ይመስላል?



እንደ ልማድ ሆኖ የጸሎት ድምጸታችን ሐዘን ያጨፈገገው ወይም ደስታ የራቀው ሆኖ ይታያል። ምናልባት በየቀኑ የምንጋፈጠው ፈተና ወይም ችግር ለዚህ እንደ ምክንያት ሊወሳ ይችላል። ነገር ግን በኤፌሶን መጽሐፍ የቀረበው የጳውሎስ ጸሎት ዘገባ እንደሚጠቁመው፣ ምስጋና የጸሎት አፍ መፍቻ ቋንቋ ነው።

የእግዚአብሔርን በረከቶች እየጠራን ስለ እነርሱ ምስጋና እንሰዋለታለን። አስቸጋሪ ሁኔታዎች ሲገጥሙን እግዚአብሔር በሥራ ላይ መሆኑን ለማየት እንደምንመኝ ሁሉ፣ በዚህ ነገሮችን የሚለውጥ ማንነት በመገኘቱ ምስጋና እናቀርብለታለን።

በየሱስ ጸጋ እና አምላካዊ ኃይል ሐሴት እያደረግን (ኤፌ. 1፡20-23) በእኛ ተጽእኖ ዙሪያ ያሉትን ስለባረከልን እናመሰግነዋለን። የጳውሎስ የጸሎት ምስጢር ይህ ነው፡--ጸሎት ምስጋና እና ውዳሴ የሚቀርብበት ቁልፍ መሣሪያ ነው።

በተጨማሪ ጳውሎስ እንዲህ ብሏል፡ “በጸሎቴ እያስታወስኋችሁ ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረብን አላቋረጥሁም።” (ኤፌ. 1:16፣ ፊልጵ. 1:3-4፣ 1ተሰ. 1:2፣ 1ተሰ. 5:16-18)። “ሳታቋርጡ ጸልዩ” (1ተሰ. 5፡17) ማለት ትክክለኛ ፍቺው ምንድን ነው?



ሁሌ በጸሎት በእግዚአብሔር ፊት እንንበረከካለን ማለት ሊሆን አይችልም።

በእግዚአብሔር መንፈስ ባገኘነው መባረክ፣ ለአምላክ መገኘት እና ኃይል ክፍት በሆኑ ልቦች ምስጋና የምናቀርብባቸውን ምክንያቶች እየፈለግን በሕይወት ጎዳና መራመዳችንን እንቀጥላለን ማለት ነው። ሕይወት የሚያመጣቸው ጠመዝማዛና ወጣገባ ተግዳሮቶች ሲገጥሙን፣ የሕይወትን ጉዳዮች በእግዚአብሔር ፊት ለመምራት ዝግጁ ሆኖ መለኮታዊውን ምሪት አጥብቆ መሻት ነው። ከእግዚአብሔር ርቀን ሳይሆን ከእርሱ ጋር ተባብረን ራሳችንን ለመለኮታዊው አመራር ክፍት ማድረግ ነው።

ብዙውን ጊዜ ጸሎትን ነገሮች አመቺ ሲሆኑ ልናከናውነው እንደሚገባ የደቀ መዝሙርነት ተጨማሪ ክፍል አድርገን እንመለከተዋለን። ጳውሎስ ከዚህ የተለየ አመለካከት ነበረው። ጳውሎስ በኤፌሶን ለነበሩ ምእመናን በቁም ነገር ይጸልይ ነበር። በጸሎቱ ስለ እነርሱ እግዚአብሔርን ያመሰግንና (ኤፌ. 1:16፤ ኤፌ. 1:3-14) ይማልድ ነበር (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ኤፌ. 1:17-23፣ ኤፌ. 3:14-21)። ለእርሱ፣ ጸሎት የክርስትና እምነት አስኳል ነው። እነዚህ ጥቅሶች ጳውሎስ ራሱን ለዚህ አገልግሎት ከሰጠበት ብርሃን አንጻር እያንዳንዳችን የየራሳችንን “የጸሎት አገልግሎት” እንድንመረምር የሚያበረታታ ጥሪ ያቀርባሉ። ማመስገን ስላለብዎ ነገር ሁልጊዜ እግዚአብሔርን በጸሎት ማመስገን አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

ሐምሌ 3
Jul 10

ጥበብና መገለጥን ከመንፈስ ቅዱስ መለማመድ


“በጸሎቴ እያስታወስኋችሁ ስለ እናንተ ምስጋና ማቅረብን አላቋረጥሁም።

የክብር አባት የሆነውን የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን አምላክ ይበልጥ እንድታውቁት፣ የጥበብና የመገለጥን መንፈስ እንዲሰጣችሁ ያለ ማቋረጥ እለምናለሁ።” (ኤፌ. 1፡16-17)።

ጳውሎስ ስለ ጸሎቱ በጻፈው ዘገባ፣ በእግዚአብሔር ዙፋን ፊት ያቀረበውን አንድ ዋና ልመና አስፍሯል። አንድ አማኝ በተለወጠበት ወቅት መንፈስ ቅዱስ ወደ ሕይወቱ እንደሚመጣ ቀደም ሲል ጠቅሷል (ኤፌ. 1፡13-14)። አሁን ጳውሎስ ስለ የሱስ ጥልቅ ግንዛቤ ማግኘት ላይ ያነጣጠረ አዲስ የመንፈስ ጥበብና መገለጥ በረከት እንቀበል ዘንድ ይጸልያል።” (ኤፌ. 1፡17)።

መንፈስ ቅዱስ ለአማኞች ልዩ ጥበብና መገለጥ ያመጣ ዘንድ ጳውሎስ የጸለየባቸው ሦስት ርዕሰ ጉዳዮች የትኞቹ ናቸው? ኤፌ. 1፡17-19።



ጳውሎስ--በእርሱ ስለ ተጠሩበት ተስፋ (ኤፌ. 1፡18) ጥበብና መገለጥ እንዲያገኙ ይጸልያል። እግዚአብሔር ለእነርሱ መዳን አስቀድሞ ለወሰዳቸው ተግባራት እና (ኤፌ. 1:3-9፣ 11-13) ወደፊት ስላቀደላቸው በክብር የተሞሉ ጊዜያቶች (ኤፌ. 1፡10፣14) ንቁ እንዲሆኑ ልመናውን ያቀርባል።

“በቅዱሳኑ ዘንድ ያለውን ክቡር የሆነውን የርስቱን ባለጠግነት ምን እንደሆነ” ያውቁ ዘንድ (ኤፌ. 1፡18) ጳውሎስ ጥበብና መገለጥ እንዲያገኙ የሚጸልይላቸው፣ አማኞችን እንደ እግዚአብሔር ርስት የሚጠቅሰውን የብሉይ ኪዳን ጽንሰ ሀሳብ በማስታወስ ነው (ዘዳ. 9፡29፣ ዘዳ. 32፡9፣ ዘካ. 2፡12፣-- ከኤፌ. 1፡11 ጋር ያስተያዩ)። እነርሱ በእግዚአብሔር ዘንድ ርስት እንዳላቸው ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ርስት መሆናቸውን እንዲያውቁ ይፈልጋል፣ እናም ጳውሎስ በእግዚአብሔር ዘንድ ምን ያህል ዋጋ እንዳላቸው ይገነዘቡ ዘንድ ይፈልጋል።

ጳውሎስ “ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኃይሉን እንድናውቅ” (ኤፌ. 1፡19) መንፈሳዊ ጥበብና መገለጥ እንዲሰጠን ሲጸልይ፣ መንፈስ ቅዱስ ስለ እግዚአብሔር ኃይል ታላቅነት አዲስ ግንዛቤ ሰያስጨብጥና ልምድ ሲሰጥ የሚሆነውን በዐይነ ሕሊናው ይመለከታል።

በእነዚህ ሁሉ ጸሎቶች፣ ጳውሎስ እነዚህ ሰዎች በየሱስ የተሰጣቸውን ለራሳቸው እንዲለማመዱ ይፈልጋል። “ለእኛ ለምናምነውም ከሁሉ በላይ ታላቅ የሆነውን ኃይሉን” በተሻለ መለማመድ የምንችለው እንዴት ነው? በዕለት ከዕለት ሕይወታችን ይህ ምን ማለት ነው?

ሐምሌ 4
Jul 11

የትንሣኤው ኃይል ተሳታፊ መሆን


በቀሩት የጳውሎስ የጸሎት ዘገባዎች፣ ኤፌ. 1፡20-23፣ ሐዋርያው መንፈስ ቅዱስ ለአማኞች እንደሚያመጣ ተስፋ ባደረገው ጥበብና መገለጥ፣ ሦስተኛው ርዕሰ ነጥብ ወደ ሆነው፡ የእግዚአብሔር ኃይል ግዙፍነት--ያመራል።

ጳውሎስ የእግዚአብሔርን ኃይል በቀዳሚነት የሚገልጽባቸውን ሁለት የመዳን ታሪክ ክስተቶች በመጠቆም ይጀምራል፡ (1) የየሱስ ከሞት መነሣት (2) የየሱስ በሰማያዊው ዙፋን መክበር (ኤፌ. 1፡20)።

የእግዚአብሔር ኃይል እንዴት በየሱስ ትንሣኤ ተገለጠ? ኤፌ. 1፡ 20፤ 1ቆሮ. 15፡20-22፤ ፊል. 3፡8-11፤ ዕብ. 13፡20-21፤ 1ጴጥ. 1፡3።





የየሱስ ትንሣኤ ለድርድር የማይቀርብ የክርስትና እምነት አስተምህሮ ነው (1ቆሮ. 15፡14፣17)። ታማኝ አማኞች የሱስ ዳግም ሲገለጥ ገቢራዊ የሚሆነውን ታላቁን የዘላለም ሕይወት ትንሣኤ የሚጠባበቁት ክርስቶስ ከመቃብር በመነሣቱ ነው (1ቆሮ. 15፡20-23)። የመንፈስ ቅዱስ በሕይወታችን መኖርን ጨምሮ ሁሉንም የወንጌል በረከቶች ለማግኘት ዛሬ ወደ እርሱ መመልከት የቻልነው ክርስቶስ በመነሳቱ ነው።

እግዚአብሔር “በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው” (ኤፌ. 1፡ 20) የሚለው ጥቅስ የተወሰደው ከመዝ. 110፡1 ሲሆን፣ ጥቅሱ በአዲስ ኪዳን አዘውትረው ከሚጠቀሱ መሃል ነው። የክርስቶስ መክበር በኤፌሶን መጽሐፍ ከፍ ያለ አጽንኦት ተሰጥቶታል። ያመንነውን “በሰማያዊ ስፍራ ከእርሱ [ከክርስቶስ ኢየሱስ] ጋር አስቀመጠን” (ኤፌ. 2፡6)። በተጨማሪ ጳውሎስ የክርስቶስን ዕርገት--ለቤተ ክርስቲያን የሚያስፈልገውን ስጦታ ለመስጠት ሁሉንም ነገር ካሟላበት ፈር ቀዳጅ ክንውኑ አኳያ በንጽጽር ያቀርበዋል (ኤፌ. 4፡8-11)።

ጳውሎስ በኤፌ. 4፡8-11 መልእክቱ በአብ ዙፋን ላይ የተቀመጠውን ክርስቶስ በምንም ዓይነት ምናባዊ ሥዕል እንዳንመስለው አስጠንቅቆናል። “በመንፈሱ ወደ ዓለም ሁሉ እየወጣ ድል እያደረገና ድል እየተቀዳጀ ያለው፣ የአዲስ ኪዳኑ የከበረው ክርስቶስ አስገራሚ ገጽታ ነው።”-F. F. Bruce, The Epis- tles to the Colossians, to Philemon, and to the Ephesians (Grand Rapids, MI: Eerdmans, 1984), p. 133። ስለዚህ ጳውሎስ የክርስቶስን መክበር ወይም ንግሥና ለአማኖች የተሰጠ መለኮታዊ ኃይል ምሳሌ ብቻ ሳይሆን፣ ነገር ግን የዚህ ኃይል ምንጭ አድርጎ ይገልጻል።

በሕይወትዎ ውስጥ የክርስቶስን ኃይል የሚሹባቸው መንገዶች ምንድናቸው? ራሳችንን በተሻለ የዚህ ኃይል ተጠቃሚ ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው? ወደ እርሱ ኃይል እንዳንደርስ እንቅፋት የሚሆኑ ተግባራት የትኞቹ ናቸው?

ሐምሌ 5
Jul 12

ክርስቶስ፡ ከኃይል ሁሉ በላይ


ጳውሎስ አሁን ከአብ ጋር በሰማያዊው ዙፋን የተቀመጠውን የየሱስ መክበር አሞግሷል። ክርስቶስ ከአብ ጋር ባለው ግንኙነት ሥልጣኑን ከገለጸ በኋላ (“…በሰማያዊ ስፍራ በቀኙ ሲያስቀምጠው” ኤፌ. 1፡20)፣ የሱስ “ከኃይል” ጋር ያለውን ዝምድና ያወሳል። የሱስ ከአብ ጋር የጋራ ገዢ እንደመሆኑ፣ ከ “ሁሉ በላይ ነው” (ኤፌ. 1፡21)። ጳውሎስ ስለ ክፉው፣ መንፈሳዊ ኃይላት የጠቀሳቸውን ያስተያዩ፡ ኤፌ. 1፡21፣ 2፡2፣ ኤፌ. 6፡12። ጳውሎስ የእነዚህ ኃይላት ጉዳይ ያን ያህል ትኩረቱን ለምን የሳበው ይመስሎታል?



በሐዋ. 19፡11-20 ስለ አስቄዋ ሰባት ወንዶች ልጆች የተነገረው ታሪክ፣ በጳውሎስ ጊዜ ኤፌሶን የአስማት ጥበብ ማዕከል እንደነበረች ያሳያል።

“በቀደመው የግሪክ ሄለናዊ ዘመን ይካሄድ የነበረውና ገንኖ ይታወቅ የነበረው አስማት፣ በሁሉም የሕይወት ዘርፍ ለማለት በሚያስችል መልኩ ተጽእኖ የሚያሳድር፣ መንፈሳዊው ዓለም የሚታወቅበት ተግባር ነበር። የአስማተኛው ግብ ጠቃሚ መናፍስትን ከጎጂዎቹ መለየት፣ የመናፍስቱን ልዩ አሠራር፣ አንጻራዊ ጉልበት እና ሥልጣን መማርና መገንዘብ ነበር። ይህን ዕውቀት መሠረት በማድረግ የግንኙነቱን መሥመር (በንግግር ወይም በጽሑፍ በሰፈሩ ቀመሮች፣ ክታቦች ወዘተ) እንደ ግለሰቡ ጥቅም መናፍስትን ለማባባል የሚያስችል ዘዴ ለመዘርጋት ይቻላል። አግባብ ያለውን ቀመር በመጠቀም፣ ከመንፈስ ጋር ተያያዥነት ያለው በሽታ ሊፈወስ ይችላል ወይም በሠረገላ እሽቅድድም አሸናፊ ሆኖ መውጣት ይቻላል።”-Clinton E. Arnold, Power and Magic: The Concept of Power in Ephesians, p. 18.

አማልክትንና ኃይላትን በድግምት የመጥራት ፍላጎት የኤፌሶን ኃይማኖታዊ ሕይወት ገጽታ (ሐዋ. 19፡13) የነበረ ሲሆን፣ ዛሬም በአንዳንዶች ሲተገበር ይታያል። ጳውሎስ በክርስቶስ እና “በኃይሎች” መካከል ያለውን ዝምድና በግልጽ ለማሳየት የፈለገ ሲሆን፣ የከበረው የሱስ “የተቀመጠውም ከግዛትና ከሥልጣን፣ ከኃይልና ከጌትነት… ሁሉ በላይ ነው” (ኤፌ. 1፡21)። አድማጮቹ ከየሱስ ሉዓላዊነት ውጪ ምንም ዓይነት ኃይል እንደሌለ እንዲገነዘቡ የፈለገው ጳውሎስ፣ በድግምት የሚሠሩትን አማልክት ስም ከዘረዘረ በኋላ፡ “ሊሰየም ከሚቻለው ስም ሁሉ በላይ ነው” (ኤፌ. 1፡21) ይላል። ጳውሎስ ፊቱን ከሰማይ ኃይላት ወደ ጊዜ መለስ ያደርግና፣ ለኢየሱስ ወሰን የሌለው ዘመን የከበረ ገዢነት አጽንኦት ይሰጣል። በሁሉም ኃይላት ላይ ያለው ገዢነት “በአሁኑ ዘመን ብቻ ሳይሆን፣ በሚመጣውም ዘመን” ጭምር ነው (ኤፌ. 1፡21)።

የእነዚህ እኩይ ኃይሎች አንዳንድ የዘመናችን መገለጫዎች ምንድን ናቸው? ከእነዚህ በአንዳቸውም ላለመጠመዳችን እንዴት እርግጠኞች መሆን እንችላለን?

ሐምሌ 6
Jul 13

የሱስ፣ ሁሉም ነገሮች እና ቤተ ክርስቲያኑ


ቀደምት ክርስቲያኖች በመዝ. 110፡1 ስለ የሱስ መክበር አስቀድሞ የተነገረውን ትንቢት ተመልክተው ነበር፡ “እግዚአብሔር ጌታዬን፣ ‘ጠላቶችህን ለእግርህ መርገጫ፣ እስከማደርግልህ ድረስ፣ በቀኜ ተቀመጥ’ አለው።” መዝሙረ ዳዊት ምዕራፍ ስምንትን በተመሳሳይ በማንበብ፡ “ሁሉንም ከእግሩ በታች አስገዛህለት” (መዝ. 8፡4) በሚለው ጥቅስ የቀረበው “የሰው ልጅ” እግር (መዝ. 8፡4) ለመሆኑ እንደ ማረጋገጫ ወስደውታል። በሰማያዊ ስፍራ ያሉ የጨለማ ኃይላት ከእነርሱ በላይ እንዳሉና በቁጥጥራቸው ስር ለማዋል እንደሚዝቱ ቢያስቡም፣ እነዚያ ኃይላት ከክርስቶስ እግር በታች የመሆናቸውን እውነታ አጽንተው ያዙ።

አብ “ሁሉንም ነገር ከእግሩ በታች አስገዛለት” እናም “በቤተ ክርስቲያንም፣ በማንኛውም ነገር ላይ ራስ አድርጎ ሾመው” (ኤፌ. 1፡22)።

“በማንኛውም ነገር ላይ” የሚለው ሃረግ ሁሉንም አካታች ቢሆንም፣ በኤፌ. 1፡ 21 የተጠቀሰው “ከኃይልና” የሚለው ቃል አሁንም በጳውሎስ አእምሮ ውስጥ ነበር። ሁሉም ነገሮች በሚለው ሃረግ ውስጥ የተካተቱት--ጠፈር፣ ልዕለ ተፈጥሮ ባሕሪያት፣ መናፍስታዊ ኃይሎች--እነሆ በክርስቶስ እግር ስር፣ ለእርሱ ተገዝተዋል።

የክርስቶስ መክበር እና በሰማይና በምድር ባሉት ነገሮች ሁሉ ላይ ገዢ መሆን ለሰማያዊው ዙፋን እንዲሁም ለቤተ ክርስቲያኑ ምን ጥቅም ያስገኛል? ኤፌ. 1፡22-23።



እግዚአብሔር ክርስቶስን በክፉ ኃይሎች ሁሉ ላይ አሸናፊ አድርጎታል።

ከክርስቶስ ጋር በቅርብ የተቆራኘችውና እርሱ የሚያስፈልጋትን ሁሉ የሚያሟላላት ቤተ ክርስቲያን ራሷ፣ በእነዚያ ጠላቶች ላይ ድል የመቀዳጀት ዋስትና ተሰጥቷታል።

በክርስቶስ ትንሣኤና በማንኛውም ሥልጣንና ኃይል ላይ ከፍ ከፍ ማለቱ የታየው የእግዚአብሔር ኃይል፣ ለቤተ ክርስቲያን ጥቅም ውሏል። እግዚአብሔር ድል አድራጊውን ክርስቶስ ለቤተ ክርስቲያን ሰጥቶአታል። ቤተ ክርስቲያን የእርሱ አካል ተብላ ትጠራ ዘንድ ከእርሱ ጋር ሕብረት ፈጥራለች።

እኛ አማኞች ከፍ ከፍ ያለውን ክርስቶስን ማወቅና በሕይወታችን ውስጥ የእግዚአብሔርን ኃይል መለማመድ የምንችለው እንዴት ነው? ጳውሎስ ይህ ክንውን የሚያገኝበትን ማንኛውንም ዘዴ ወይም ስልት በቀጥታ አልተናገረም። ይሁን እንጂ ጥቅሱ “የጸሎት ዘገባ” አካል እንደሆነ ይስተዋላል። ጳውሎስ እግዚአብሔር ጸሎቱን እንደሚመልስለት ያምናል። በክርስቶስ የተገለጠውን የእግዚአብሔር ኃይል በራሱ በእግዚአብሔር ፊት ማክበር እና በአማኞች ሕይወት ውስጥ ንቁ እንዲሆን መጠየቅ ጉልህ ጥቅም እንዳለው አጽንኦት ይሰጣል።

የእርስዎ የጸሎት ኃይል ተሞክሮ ምን ይመስላል? ይኸውም ስለ ጸሎት መልስ ሳይሆን በአጠቃላይ ጸሎት እንዴት ወደ እግዚአብሔር እንደሚያቀርበን እና በየሱስ ስለተሰጠን ኃይል።

ሐምሌ 7
Jul 14


ተጨማሪ ሀሳብ


ስለ ክርስቶስ መክበር የተጻፉትን የሚከተሉትን የኤለን ኋይት ሁለት መግለጫዎች ያጥኑ።

“ክርስቶስ በሰማያዊ ደጆች በማለፍ በመላእክት ከፍተኛ ፍቅርና አክብሮት በዙፋኑ ላይ ተቀመጠ። ይህ ሥነ ሥርዓት እንደተጠናቀቀ መንፈስ ቅዱስ በደቀ መዛሙርቱ ላይ በሙላት ወረደ። ክርስቶስም ከዘላለም አንስቶ በአባቱ በነበረው ክብር ከበረ። የጴንጤቆስጤው ዕለት ክስተት አዳኙ የከበረበት ሥነ ሥርዓት ክንውን ማግኘቱን በማብሰር ሰማይ ግንኙነት የፈጠረበት መንገድ ነበር።

እርሱ እንደ ካህን እና ንጉሥ ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር የተቀበለበትና በሕዝቡ ላይ የተቀባ ስለ መሆኑ--ምልክት ይሆናቸው ዘንድ አስቀድሞ ቃል በገባው መሰረት መንፈስ ቅዱስን ከሰማይ ወደ ተከታዮቹ ላከ።”-The Acts of the Apostles, pp. 38, 39.

“ደግሞም እግዚአብሔር በኵሩን ወደ ዓለም ሲያስገባ፣ ‘የእግዚአብሔር መላእክት ሁሉ ይስገዱለት’ ይላል።” ዕብ. 1፡6

“ስለዚህ ኀጢአት በአንድ ሰው በኩል ወደ ዓለም እንደ ገባ ሁሉ፣ ሞትም በኀጢአት በኩል ገብቶአል፤ በዚሁ መንገድ ሞት ወደ ሰዎች ሁሉ መጣ፤ ምክንያቱም ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋል፤

“ከዚያ የነበሩ ከፍተኛ ኃይልና ሥልጣን የነበራቸው ሁሉ የሕይወት መስፍን የሆነውን ክርስቶስን የበላይነት አወቁ። “የታረደው በግ ኃይልና ባለጠግነት፣ ጥበብና ብርታት፣ ክብርና ሞገስ፣ ምስጋናም፣ ሊቀበል ይገባዋል (ራእ. 5፡12)። የሚል ድምጽ የሰማይ አደባባዮች ባጥለቀለቃቸው ጊዜ የመላእክት ሰራዊት በመሬት ላይ ተደፍተው ለየሱስ ሰገዱለት።

“በመላእክት ሙዚቃ የታጀበ በድል አድራጊነት መዝሙር በተዘመረ ጊዜ ሰማይ በሙሉ የደስታና የውዳሴ ድምጽ አስተጋባ። የጠፋው ስለተገኘ በሰማይ በዙፋኑ ላይ ለተቀመጠውና ለበጉ፣ ምስጋናና ሞገስ፣ ክብርና ኃይል፣ ከዘላለም እስከ ዘላለም ይሁን” የዘመናት ምኞት ገጽ፡ 886።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. የኢየሱስን መክበር አስመልክቶ የተጠቀሱትን “አሁን” እና “ገና” የሚሉትን ቃላት ያሰላስሉ። የሱስ “የሁሉም ነገር” ጌታ የሆነው ከምን አንጻር ነው--አጋንንታዊ ኃይሎች “አሁን” ለእርሱ ስለተገዙለት? (1ቆሮ. 15፡ 24-28)። በሁሉም ነገሮች ላይ ሙሉ በሙሉ የሚገዛበትን የወደፊቱን ጊዜ “ገና” እየተጠባበቀ ያለው ከምን አንጻር ነው? ( 1 ቆሮ. 15:24-28 ተመልከት።)

2. ክርስቶስ ሁሉንም ነገር በሚገዛበት ብርሃን ምን ያህል እየተመላለሱ ነው? ወይስ ምን ያህል በእነዚህ ሥልጣናቸው እየደበዘዘ ባለ፣ በወደቁ ኃይላት ሥልጣን ስር እየኖሩ ነው? ማን ምን እንደሆነ እንዴት ያውቃሉ? ምንም እንኳ በእርግጠኝነት የተሸነፉ ቢሆንም፣ ነገር ግን ዛሬም በዓለማችን ተስፋፍተው ከሚገኙ ከእነዚህ ኃይላት እንዴት መጠበቅ ይችላሉ?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL