የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሰኔ 24 - 30

2ኛ ትምህርት

Jul 1 - 7




ክርስቶስን ያማከለው ታላቁ አምላካዊ እቅድ



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ኤፌ.1:3-14፣ ኤፌ. 2:6፣ ኤፌ. 3:10፣ ቆላ. 1:13-14፣ ዘዳ. 9:29።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት ይባረክ” (ኤፌ. 1፡3)።

ኒል አርምስትሮንግ በጨረቃ ላይ የተራመደ የመጀመሪያው ሰው ከሆነ ከሃያ አምስት ዓመታት በኋላ ለብሶት የነበረውን የጠፈር ልብስ ዲዛይን ላደረገው ተቋም አንድ የምስጋና ማስታወሻ ጽፎ ነበር። “በታሪክ በጣም ብዙ ፎቶ የተነሣ መንኮራኩር” ብሎ የጠራውንና በውስጡ የያዘውን “አስቀያሚ መንኮራኩረኛ” በመሸሸግ የተዋጣለት ሲል በተሳለቀበት ደብዳቤው፣ ጆንሰን የሕዋ ማዕከልን አመስግኗል። ሕይወቱን የተጠበቀ ላደረገው “ጠንካራ፣ አስተማማኝና እቅፍ አድርጎ የሚይዝ” የጠፈር ልብስ “የሩብ ምዕተ ዓመት ምስጋናና ማበረታቻ” ልኮላቸዋል።

ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈው መልእክት የሚጀምረው እግዚአብሔር ላፈሰሰው በረከት ንጉሣዊ የምስጋና ማስታወሻ በመተው ነው። በጨረቃ ላይ ለተራመደው ሰው የጠፈር ልብስ አስፈላጊ እንደሆነ ሁሉ፣ ለአማኞች ሕይወትም ባርኮቶች በእጅጉ ወሳኝ ናቸው። እግዚአብሔር “ዓለም ከመፈጠሩ በፊት” በእነዚህ መሠረታዊ በረከቶች ላይ ሲሠራ ኖሯል ሲል የሚሞግተው ጳውሎስ (ኤፌ. 1፡4) ለዘመናት ለሠራው ሥራ በአማኞች ስም እግዚአብሔርን ያመሰግናል።

ጳውሎስ በመክፈቻ ንግግሩ የኤፌሶን ክርስቲያኖች እግዚአብሔርን በማምለክ ምሳሌ ስለ መሆናቸውና እርሱ ለሰጠው ቁጥር ስፍር የሌለው በረከት አመስጋኝነታቸው ላቅ ያለ ዋጋ ይሰጣል።

ሰኔ 25
Jul 02

በክርስቶስ የተመረጡና ተቀባይነት ያገኙ


የምስጋና ማስታወሻ ብዙውን ጊዜ ስለ ስጦታው ወይም ስለ ተቀበሉት ስጦታ አጠር ያለ መግለጫ ይይዛል። ጳውሎስ ስለ ወንጌል በረከቶች እግዚአብሔርን በሚያመሰግንበት የኤፌ. 1፡3-14 መልእክቱ፣ ረዘም ያለ የስጦታ ዝርዝር አካቷል።

“በመንፈሳዊ በረከት ሁሉ በክርስቶስ የባረከን” (ኤፌ. 1፡3) እግዚአብሔር አምላክን ጳውሎስ ያመሰግናል። በረከቶቹ መንፈሳዊ (በግሪክ፡pneu- matikos) በመሆናቸው በመንፈስ ቅዱስ (pneuma) በኩል እንደሚመጡ የሚጠቁመው ጳውሎስ፣ መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሕይወት በሚሠራው ሥራ ሐሴት በማድረግ ወደ መደምደሚያው ቡራኬ ያመራል (ኤፌ. 1፡13-14)።

እግዚአብሔር እኛን እንዴት በክርስቶስ እንደሚመለከተን የሚያሳይ አበረታች አገላለጽ በኤፌ. 1፡3-6 ቀርቧል። እኛ “ቅዱስና ነውር አልባ” (ጥቅሶቹን ያስተያዩ፡ ኤፌ. 1፡4 እና ኤፌ. 5፡27) ሆነን በፊቱ እንቆም ዘንድ፣ የከበረ ዋጋ እንዳላቸው ወንዶችና ሴቶች ልጆቹ አድርጎ በመፍጠር እና በመዋጀት (ኤፌ. 1፡5) እነሆ እግዚአብሔር ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ በክርስቶስ መረጠን። ፀሐይ መፈንጠቅ ከመጀመሯ አስቀድሞ “በሚወደው በእርሱ በኩል” (ኤፌ. 1፡6) ተቀባይነት እናገኝ ዘንድ የእርሱ እቅድ ነበር። በአጭር አነጋገር፣ መዳናችን የእርሱ እቅድ ነው። ደህንነትን የምናጣው በገዛ ራሳችን የኃጢአት ምርጫዎች ነው። በኤፌሶን መልእክት “በሰማያዊ ስፍራ” በሚል የቀረበው ሀረግ ፍቺ ምንድን ነው (በአዲስ ኪዳን በብቸኝነት ጥቅም ላይ የዋለ) ሃረጉ ጥቅም ላይ የዋለበትን አግባብ ያጥኑ። (ኤፌ. 1:3፣ 20፣ ኤፌ. 2:6፣ ኤፌ. 3:10፣ ኤፌ. 6:12፣ ሃረጉ ጥቅም ላይ የዋለበትን መንገድ ከሚከተሉት ጥቅሶች ጋር ያስተያዩ፡ ኤፌ. 3:15፣ ኤፌ. 4:10፣ ኤፌ. 6:9)።



በኤፌሶን መልእክት “በሰማያዊ ስፍራ” እና “በሰማያት” ወይም “በሰማይ” በሚል የምናገኛቸው ሃረጎች፣ ሰማይ የእግዚአብሔር መኖሪያ (ኤፌ. 1፡3፣ ኤፌ. 6፡9)፣ የመንፈሳዊ ኃይላት መገኛ (ኤፌ. 1:10፣ 20-21፣ ኤፌ. 3:10፣ 15፣ ኤፌ. 6:12) እና ክርስቶስ በአብ ቀኝ የሚከብርበት ስፍራ መሆኑን ያመለክታሉ። አማኞች በአሁኑ ወቅት በክርስቶስ በኩል መንፈሳዊ በረከቶች (ኤፌ. 1፡3፣ ኤፌ. 2፡6) ወደሚቀርቡባቸው ወደ እነዚህ “ሰማያዊ ስፍራዎች” መድረስ የሚያስችል ፈቃድ አላቸው። ምንም እንኳ “ሰማያዊ ስፍራዎች” ለአማኞች የበረከት ቦታ ቢሆኑም፣ አሁንም የክርስቶስን ጌትነት ከሚቃወሙ ከክፉ ኃይሎች የሚነሱ ግጭቶች መናኸሪያ ስፍራ ናቸው (ኤፌ. 3፡10፣ ኤፌ. 6፡12)።

“ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” በክርስቶስ ስለ መመረጣችን በሚናገረው ኤፌ. 1፡4 ላይ ትኩረት ያድርጉ። ይህ ምን ማለት ነው? እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር እና እንድንድን መፈለጉን እንዴት ይገልጽልናል?

ሰኔ 26
Jul 03



ዋጋ ያስከፈለ ቤዛነት፤ የተትረፈረፈ ይቅርታ


ኃጢአት በጳውሎስ አድማጮች ሕይወት ውስጥ ጥቁር ጥላ ያጠላ የበላይ ኃይል ነበር። ጳውሎስ የቀድሞ ሕይወታቸውን በድኑ እንደሚራመድ ፍጡር አድርጎ በመግለጽ “በበደላችሁና በኃጢአታችሁ ምክንያት ሙታን ነበራችሁ” (ኤፌ. 2፡ 1) በዚህም ሰይጣንን “እየታዘዛችሁ ትኖሩ” (ኤፌ. 2፡1-3) ወይም ትራመዱ ነበር ይላል። የኃጢአትና የሰይጣን ባሪያዎች በመሆናቸው ራሳቸውን ነፃ የማድረግ ችሎታ አልነበራቸውም። አዳኝ ያስፈልጋቸው ነበር። እግዚአብሔር በጸጋ ከተሞላ በጎነቱ የተነሣ እነሆ በክርስቶስ ያን ያደረገ ሲሆን፣ ጳውሎስ በአማኞች ሕይወት ገቢራዊ በሆኑት ሁለት አዳዲስ ጸጋዎች ማለትም ቤዛነት እና ይቅርታ ሐሴት ያደርጋል።

ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ኤፌ. 1፡7-8። “ቤዛነት” በአዲስ ኪዳን በተደጋጋሚ ጥቅም ላይ የዋለ ጽንሰ ሀሳብ ነው። የዚህን ጽንሰ ሀሳብ አጠቃቀም ከጥቅሶቹ ጋር ያስተያዩ፡ ቆላ. 1፡13-14፣ ቲቶ 2፡13-14፣ ዕብ. 9፡15። እነዚህን ጥቅሶች ከኤፌ. 1፡7-8 ጋር የሚያመሳስሏቸው ጭብጦች ምንድን ናቸው?



በኤፌ. 1፡7 ላይ “ቤዛነት” የሚል ፍቺ የተሰጠው የግሪክ ቃል apo- lutrōsis ሲሆን ይህ ቃል መጀመሪያ ላይ ባሪያን ነፃነት በማቀዳጀት ወይም ምርኮኛን ነፃ በማውጣት ዐውድ ጥቅም ላይ ይውል ነበር። ምናልባት እንደ ገደል ማሚቶ እያስተጋባ የሚደመጠውን የባሪያ ንግድ አጫራች ድምጽ እና እጆቻቸው የተከረቸሙባቸውን “ሸቀጦች” የሚፋጭ የሰንሰለት ቅጭልታ በዐይነ ህሊናችን እንስል ይሆናል። አዲስ ኪዳን ስለ ቤዛነት ሲያብራራ ባሪያዎችን ነፃ ማውጣት ምን ያህል ዋጋ እንደሚያስከፍል አጽንኦት ሰጥቶ ይገልጻል።

ነጻነታችን የተገኘው ከፍተኛ ዋጋ ተከፍሎበት ነው፡ “በእርሱም[በየሱስ]… በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን” (ኤፌ. 1፡7)። በተጨማሪ የቤዛነት ጽንሰ ሀሳብ ለነጻነታችን ከፍተኛ ዋጋ በመክፈል ረገድ፣ የእግዚአብሔርን በጸጋ የተሞላ በጎነት ያሳያል። እግዚአብሔር አምላክ ነጻነታችንን እና ክብራችንን ሰጠን። ስለዚህ በባርነት ቀንበር ስር መውደቃችን አክትሟል!

“መቤዠት ማለት እንደ ሸቀጥ ሳይሆን እንደ ሰው መታየት ነው። የምድር ባሪያ ከመሆን ይልቅ የሰማይ ዜጋ መሆን ነው።”-Alister E. McGrath, What Was God Doing on the Cross? (Grand Rapids, MI: Zondervan, 1992), p. 78.

እግዚአብሔር የመቤዠትን ዋጋ ለሰይጣን ይከፍላል የሚለው ጽንሰ ሀሳብ የመካከለኛው ዘመን እንጂ መጽሐፍ ቅዱሳዊ አለመሆኑን ልብ ይሏል።

እግዚአብሔር ከሰይጣን የተበደረውም ሆነ የሚከፍለው ምንም ዕዳ የለበትም።

የቀራኒዮ ትሩፋቶች “የኃጢአት ይቅርታ” (ኤፌ. 1፡7) ማግኘታችንን ያካትታል። የኃጢአታችንን ዋጋ ራሱ የወሰደው ክርስቶስ “ሲቃወመንና ሲጻረረን የነበረውን የዕዳ ጽሕፈት ከነሕግጋቱ በመደምሰስ፣ በመስቀል ላይ ቸንክሮ ከመንገድ አስወገደው” (ቆላ. 2፡14)። እግዚአብሔር ይህን የመቤዠት እና የይቅርታ ሥራ በክርስቶስ በመሥራት “እንደ ባለጠግነቱ መጠን” ጸጋውንም በጥበብና በማስተዋል ሁሉ አበዛልን (ኤፌ. 1፡7-8)።

በከርስቶስ ሥርየት ይቅር ተብለዋል አርነትም ወጥተዋል ማለት ለእርስዎ ምን ትርጉም አለው? ይህ እንደማይገባዎ ሆኖ ቢሰማዎትስ? (ሁላችንም ይህ እንደማይገባን ከአጠቃላዩ የመስቀሉ ርዕሰ ነጥብ አኳያ ያስታውሱ)።

ሰኔ 27
Jul 04

ክርስቶስን ያማከለው ታላቁ አምላካዊ እቅድ


“በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው” እቅድ ምንድን ነው? ስፋትና ጥልቀቱስ ምን ያህል ነው? (ኤፌ. 1፡9-10)።



ጳውሎስ ለእግዚአብሔር ዕቅድ ሦስት ስያሜዎችን ተጠቅሟል፡ (1) “የፈቃዱ ምስጢር” (2) “በጎ ሐሳቡ” (3) “በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ”። የእግዚአብሔር የመጨረሻው እቅድ ምንድን ነው? ሁሉንም ነገር በየሱስ አንድ ማድረግ! ጳውሎስ እቅዱን ለመግለጽ የተጠቀመው--ሁሉንም ነገር በክርስቶስ “ሥር ለመጠቅለል” የሚለው ቃል (ግሪክኛው፡ anakephalaiōsasthai) ውበት አለው። በጥንታዊው የሒሳብ ስሌት አሠራር በዝርዝር የቀረቡ አኻዞች ከተሰሉ በኋላ “ጥቅል” ድምሩ ከላይ ይቀመጥ ነበር። የሱስ ከሞት፣ ከፍርድ እና ከዚያ በኋላ ያለውን የመጨረሻውን አምላካዊ እቅድ ሁሉ ይመራል። ይህ ክርስቶስን ያማከለ ዕቅድ የተነደፈው “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” ነው (ኤፌ. 1፡4)። ዕቅዱ በጣም ግዙፍ ከመሆኑ የተነሣ ጊዜን (“በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው” ) እና ቦታን (“በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ”) ያካትታል። ጳውሎስ በክርስቶስ ያለውን አንድነት ለመላው ዩኒቨርስ እንደ ታላቅ መለኮታዊ ግብ አድርጎ ያቀርበዋል።

ጳውሎስ “በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ” (ኤፌ. 1፡10) ያለውን አምላካዊ እቅድ በደብዳቤው ጭብጥ አስፍሯል። እግዚአብሔር ሁሉንም ነገር አንድ የማድረግ ዕቅዱን በየሱስ ሞት፣ ትንሣኤ፣ ዕርገት እና መክበር (ኤፌ. 1፡15-2፡10)፣ ይኸውም ቤተ ክርስቲያንን በመመስረት እና ፍጹም ተዛምዶ ያልነበራቸውን አይሁድ እና አሕዛብ (ኤፌ. 2፡11-3፡13) አንድ አድርጎ በውስጧ በማኖር ጀመረ።

በዚህ መልኩ ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር እቅድ እየተተገበረ መሆኑንና ከፋፋይ የክፉ ኃይሎች አገዛዝ እንደሚያከትም ለእነዚህ ኃይሎች ትጠቁማለች (ኤፌ. 3፡ 10)። መጽሐፍ ቅዱስ በሌላ ስፍራ እንዲህ ይላል፡ “ዲያብሎስ ጥቂት ዘመን ብቻ እንደ ቀረው ስላወቀ፣ በታላቅ ቍጣ ተሞልቶ ወደ እናንተ ወርዶአል” (ራእ. 12፡12)።

የጳውሎስ ደብዳቤ የመጨረሻው አጋማሽ ስለ አንድነት (ኤፌ. 4፡ 1-16) ጥልቅ ጥሪ በማድረግ ይጀምርና አንድነትን የሚጎዱ ባህሪያትን አስወግደን በምትኩ ከእምነት ባልንጀሮቻችን ጋር አንድነትን እንገነባ ዘንድ ረዘም ያለ ማሳሰቢያ በመስጠት ይቀጥላል (ኤፌ. 4፡17-6፡9)። ጳውሎስ በክርስቶስ ስም ሰላምን ለማስፈን በትጋት በመሳተፍ እንደ ተዋሃደ ሰራዊት በሚያቀርበው አነቃቂ የቤተ ክርስቲያን ምስል ጽሑፉን ይደመድማል (ኤፌ. 6፡10-20)።

በክርስቶስ የሱስ የተለማመዱት ቤዛነት ሁሉንም በአንድ የሚጠቀልል እና የግዙፉ ነገር አካል ማለትም፣ ሁሉንም ነገር በክርስቶስ አንድ ለማድረግ የእግዚአብሔር የተጠና እና የመጨረሻ እቅድ አካል መሆኑን እንዴት መቀበል እና ማክበር ይችላሉ?

ሰኔ 28
Jul 05

ክብሩን በምስጋና እያወደሱ መኖር


“ሁሉን በፈቃዱ ምክር መሠረት እንደሚሠራው እንደ እርሱ ዕቅድ አስቀድሞ የተወሰንን እኛ ደግሞ በእርሱ ተመርጠናል፤ ይኸውም በክርስቶስ ተስፋ በማድረግ የመጀመሪያ የሆንነው እኛ ለክብሩ ምስጋና እንሆን ዘንድ ነው።” (ኤፌ. 1፡ 11-12)።

በኤፌሶን ያሉ አማኞች እንደ ክርስቲያን ትክክለኛውን ማንነታቸውን አጥተውና ልባቸው ዝሎ ነበር (ኤፌ. 3፡13)። ጳውሎስ ቀደም ሲል ከገለጸው (ኤፌ. 1:3-5) ጋር በሚስማማ መልኩ፣ ክርስቲያን ማንነታቸውን ማየት እንዲችሉ ሊረዳቸው ሲፈልግ በድጋሚ ይስተዋላል። አማኞች የተለያዩ አማልክቶች ወይም የጠፈር ኃይሎች የተዛባ፣ የዘፈቀደ ውሳኔ ሰለባ አይደሉም። የእግዚአብሔር ልጆች ናቸው (ኤፌ. 1፡5)፣ እናም በእግዚአብሔር ጥልቅ ምክሮች እና ዘላለማዊ ውሳኔዎች ላይ ተመሥርተው በክርስቶስ በኩል በርካታ በረከቶችን ማግኘት ይችላሉ። በክርስቶስ ያለውን ሁሉ አንድ ለማድረግ ከእግዚአብሔር ሰፊ እቅድ ጋር በሚስማማ መልኩ በሕይወታቸው እየሠራ ያለው የእግዚአብሔር ዓላማ፣ ምክርና ፈቃድ ነው (ኤፌ. 1፡10)። በእግዚአብሔር ፊት ባላቸው አቋም እና እርሱ በሚሰጣቸው በረከቶች ውጤታማነት ላይ የማይናወጥ እምነት ሊኖራቸው ይችላል። ሕይወታቸው በኤፌ. 1፡3-14 የቀረበውን የጌታችን የየሱስ ክርስቶስ አምላክና አባት የተባረከ ይሁን! የሚለውን መልእክት ማስተጋባት አለበት።

በኤፌ. 1:11፣ 14፣ 18 የቀረበውን “ርስት” (ቅርስ) የሚለውን ሐሳብ ያስተያዩ። ይህ ጽንሰ ሐሳብ ለጳውሎስ አስፈላጊ የሆነው ለምን ይመስሎታል?



በአንድ ሰው ሞት ምክንያት ርስት ደርሶት ወይም ቅርስ ተቀብለው ያውቃሉ? ምናልባት ዘመድዎ የከበረ ዋጋ ያለው ሐብት ወይም ዳጎስ ያለ ገንዘብ ትተውሎት አልፈው ሊሆን ይችላል። በጳውሎስ አመለካከት መሠረት ክርስቲያኖች በየሱስ ሞት ምክንያት ከእግዚአብሔር ርስት በመቀበላቸው (ኤፌ. 1፡14) እነሆ ለእግዚአብሔር “ርስት” ሆነዋል (ኤፌ. 1፡18)።

በብሉይ ኪዳን የእግዚአብሔር ሕዝቦች አንዳንዴ እንደ እርሱ “ርስት” ወይም ቅርስ ተደርገው ይታሰባሉ፡ (ዘዳ. 9፡29፣ ዘዳ. 32፡9፣ ዘካ. 2፡12)። ይህ ሁኔታ ወይም የእግዚአብሔር ርስት የመሆን ስሜት በኤፌሶን 1፡18 ግልጽ ሆኖ የቀረበ ሲሆን፣ ምናልባትም በኤፌ. 1፡11 ላይ ያለው ቃል ፍቺ ሊሆን ይችላል (ይኸውም “በእርሱ ርስት ሆንን” ተብሎ ይተረጎማል)። አማኞች እንደ ክርስቲያን ማንነታቸው በእግዚአብሔር ፊት ያላቸውን ዋጋ ያውቁ ዘንድ ጳውሎስ አጥብቆ ይመኛል። ከእግዚአብሔር ርስት የሚቀበሉ ብቻ ሳይሆን (ኤፌ. 1፡14፣ ኤፌ. 3፡6) ነገር ግን የእግዚአብሔር ርስት ናቸው።

አንድን ነገር ለማግኘት በመሥራትና በምትኩ በመውረስ መካከል ያለው ልዩነት ምንድን ነው? ይህ ጽንሰ ሃሳብ በየሱስ የተሰጠንን ነገር ለመረዳት የሚያስችለን እንዴት ነው?

ሰኔ 29
Jul 06

መንፈስ ቅዱስ፡ ማኅተም እና ቀብድ


ጳውሎስ በኤፌ. 1፡13-14 የአንባቢዎቹን መለወጥ ታሪክ በአጭሩ ያቀርባል። በዚያ ታሪክ ውስጥ የቀረቡት ቅደም ተከተሎች ምንድን ናቸው?



ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ በምእመናን ሕይወት ውስጥ ባለው ጠቀሜታ ዙሪያ በሚያደርገው ቅኝት፣ ለመንፈስ ሁለት ገጽታዎችን ወይም ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ይጠቀማል። መንፈስ ቅዱስን የሚያስቀምጥበት የመጀመሪያው ምስል “ማኅተም” ሲሆን፣ ይህም አንድ ግለሰብ ከተለወጠበት ጊዜ አንስቶ የሚከናወን የመንፈስ መታተም መኖሩን ያመለክታል። በጥንት ዘመን ማኅተሞች ለተለያዩ ተግባሮች ጥቅም ላይ ይውሉ የነበረ ሲሆን፣ ከእነዚህም ውስጥ--የሕጎችንና ስምምነቶችን ቅጂዎች ትክክለኛነት ለማረጋገጥ፣ በአንድ ዕቃ መያዣ ውስጥ ላለ የቁስ ዓይነት ወይም ብዛት ማረጋገጫ ለመስጠት ወይም የንግድ ልውውጦችን (ኤር. 32፡10-14፣ 44)፣ የኮንትራት ስምምነቶችን፣ ደብዳቤዎችን (1ነገሥ. 21፡8)፣ ኑዛዜዎችን እና ልጅን በጉዲፈቻ ተቀብሎ ለማሳደግ ማኅተም ጥቅም ላይ ይውል ነበር። በአንድ ቁስ ላይ የታተመ ማኅተም የባለቤትነት መብትንና ተገቢው ጥበቃ እንደሚያስፈልግ ያመለክት ነበር። አማኞች መንፈስ ቅዱስ በሕይወታቸው ውስጥ መኖሩ የእግዚአብሔር ንብረት መሆናቸውን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፣ እግዚአብሔር ጥበቃ ሊያደርግላቸው የገባውን ቃልም እንዲሁ ይዟል (ኤፌ. 4፡30)። “ተስፋ ሆኖ በተሰጠው በመንፈስ ቅዱስ ማኅተም ታትማችኋል” (ኤፌ. 1፡13)።

“አንድ ሰው ሕይወቱን ለየሱስ ሲሰጥ እና በእርሱ ሲያምን፣ መንፈስ ቅዱስ ወዲያውኑ ለቤዛ ቀን የሚሆነውን ማኅተም እንደሚያትምበት (ግሪክኛው፡ sphragizō) ጳውሎስ በግልጽ ይናገራል። እንዴት ያለ--ነጻ የሚያወጣ፣ ፍርሐትና ጥርጣሬን የሚያስወግድ አስደናቂ እውነት ነው! የክርስቶስ ተከታዮች በመጀመሪያ እንዳመኑ፣ የእግዚአብሔር መንፈስ የድነትን ማኅተም ያትምባቸዋል።””-Jiří Moskala, “Misinterpreted End-Time Issues: Five Myths in Adventism,” Journal of the Adventist Theological Society 28, no. 1 (2017), p. 95.

ጳውሎስ ለመንፈስ ቅዱስ የተጠቀመው ሁለተኛው ምስል “ዋስትና” የሚለውን ቃል ነው። መንፈስ ቅዱስ የርስታችን ዋስትና ነው፣ ይህም ርስቱ ሙሉ ለሙሉ የሚሰጥበትን ጊዜ ተስፋ በማድረግ ይጠባበቃል (ያስተያዩ፡ 2ቆሮ. 1፡ 22፣ 2ቆሮ. 5፡5)።

“ዋስትና” ወይም አረቦን (arrabōn) ተብሎ የተተረጎመው ቃል የዕብራይስጥ የውሰት ቃል ሲሆን፣ ከፋዩ ተጨማሪ ክፍያዎችን እንዲፈጽም የሚጠየቅበትን “ቀብድ”፣ “ተቀማጭ ገንዘብ” ወይም “ቅድሚያ ክፍያ” ለማመልከት አዲስ ኪዳን በተጻፈበት ግሪክኛው በስፋት ጥቅም ላይ ውሎአል።

እዚህ ላይ አማኞች ይህን ቀብድ እንደማይከፍሉ፣ ይልቁንም ከእግዚአብሔር እንደሚቀበሉ ልብ ይሏል። ጳውሎስ እንደሚለው ከሆነ፣ የከበረ ዋጋ ያለው መንፈስ ቅዱስ በአማኞች ሕይወት ውስጥ መገኘቱ፣ ከክርስቶስ ዳግም ምጽአት ጋር የሚመጣው እና የምንወርሰው ሙሉ የደኅንነት ርስት እና ቤዛነት ቀብድ ነው። የእኛ ሥራ በየሱስ የቀረበልንን በአመስጋኝና በታዛዥ ልብ መቀበል ነው።

ሰኔ 30
Jul 07


ተጨማሪ ሀሳብ


እግዚአብሔር የሰው ልጆችን የወደፊት ዕጣ አስቀድሞ በመወሰን አንዳንዶችን ለዘላለም ሕይወት ሌሎችን ደግሞ ለዘላለም ሞት አስቀድሞ ወስኗል ሲል ኤፌ. 1፡3-14 ያስተምራል ወይ? ብዙ ሰዎች፣ በሚያሳዝን ሁኔታ ይህንን ያምናሉ። ሆኖም እነዚህን ሃሳቦች ልብ ብለው ይመልከቱ፡-

በጥቅሱ የክርስቶስ ሚና ወሳኝ ነው። ምክንያቱም በመለኮት ምርጫ እኛን “በየሱስ ክርስቶስ” (ኤፌ. 1፡5) ወይም “በእርሱ” (ኤፌ. 1፡4፣11) አማካይነት ልጆቹ አድርጎናልና። ይህ የሚያመለክተው ሰዎች ከመወለዳቸው አስቀድሞም እንኳ ቢሆን በእያንዳንዱ ጉዳይ የሚድኑትን ወይም የሚጠፉትን ከመምረጥ ይልቅ፣ እግዚአብሔር የመረጠውና አስቀድሞ የወሰነው በክርስቶስ ላይ እምነት እንዲኖራቸው ለመረጡት ሁሉ ነው። የእግዚአብሔር ውሳኔ-- በክርስቶስ ለሚያምኑ የተጠና፣ አስቀድሞ የተወሰነ፣ መለኮታዊ ምላሽ ነው።

ኤፌ. 1፡3-14 የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ አስመልክቶ ሕያው ዝምድና ያለው አገላለጽ ይዟል። እግዚአብሔር “አባት” እኛ ደግሞ በረከቶቹን በተትረፈረፈ መጠን (ኤፌ. 1፡8) የምንቀበል ልጆቹ ነን (ኤፌ. 1፡3-5)።

የእግዚአብሔርን ምርጫ እና አስቀድሞ የመወሰን ጽንሰ ሀሳብ፣ ከዚህ የበለጸገና ተዛምዶ ያለው ቋንቋ ብርሃን አኳያ ማስተዋል ይኖርብናል። እግዚአብሔር እጅግ ርቆ የሚገኝና፣ ከሩቅ ስፍራ ፍርድ የሚሰጥ ስሜት አልባ ፈራጅ ሳይሆን ለልጆቹ ሁሉ የሚጠነቀቅ አምላክ ነው (ኤፌ. 3፡15)።

እግዚአብሔር የሰውን ምርጫ እንደሚያከብር በኤፌ. 1፡3-14 ተንጸባርቋል (በተለይ በኤፌ. 1፡13 “መስማት” እና “ማመን” በአስፈላጊነት ተፈርጀዋል)። በሌሎች ስፍራዎች (ኤፌ. 2፡8፣ ኤፌ. 3፡17፣ ኤፌ. 4፡1-6፡ 20 ሁሉም አጽንኦት የሚሰጡት ወይም ግምታቸውን የሚያስቀምጡት በመምረጥ ልምምድ እና በእምነት ምላሽ ዙሪያ ነው።) በሌሎች የአዲስ ኪዳን ጥቅሶች (ለምሳሌ፡ 1ጢሞቴ. 2:4፣ ሐዋ. 17:22-31)። ወይም ኤለን ኋይት እንደገለጸችው፡ “ከባቢ አየር ምድርንና ዙሪያዋን እንደሚሸፍን ሁሉ፣ እግዚአብሔር አምላክም አቻ በሌለው በልጁ ስጦታ ዓለምንና ሙላቷን በጸጋው ሸፍኗታል። ይህን ሕይወት ሰጭ ከባቢ አየር ለመተንፈስ የሚመርጡ ሁሉ፣ በክርስቶስ የሱስ ወንዶችና ሴቶች ከፍታ ይኖራሉ፣ ያድጋሉም።”-Steps to Christ, p. 68.


የመወያያ ጥያቄዎች




1. እግዚአብሔር ከመፈጠራችን አስቀድሞ አንዱ እንዲድን ሌላው ደግሞ እንዲጠፋ አልወሰነም የሚለውን ከላይ የቀረበ ጽንሰ ሀሳብ የሚደግፍ ምን መከራከሪያ ይጨምራሉ?

2. የአንድ ሰው በየሱስ ደኅንነት አለማግኘት ውሎ አድሮ በማን ምርጫ ይወሰናል?

3. “በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ጸጋ ባለጠግነት መጠን፣ በደሙ በተደረገ ቤዛነት፣ የኀጢአትን ይቅርታ አገኘን” (ኤፌ. 1፡7)። ጽድቅ የሚገኘው ሕጉን በመፈጸም ሳይሆን በእምነት ብቻ የመሆኑን እውነታ ጥቅሱ እንዴት ይገልጻል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL