የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሰኔ 17 - 23

1ኛ ትምህርት

Jun 24 - 30




ጳውሎስ እና የኤፌሶን ሰዎች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ሐዋ. 18:18-21፣ ሐዋ. 19:13-20:1፣ ሐዋ. 20:17-38፣ ኤፌ. 1:1-2፣ ኤፌ. 6:21-24፣ ኤፌ. 3:13፣ ኤፌ. 1:9-10።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “በክርስቶስ ያቀደውንም የፈቃዱን ምስጢር እንደ በጎ ሐሳቡ እንድናውቅ አደረገ። በዘመን ፍጻሜ ይሆን ዘንድ ያለው ሐሳቡ በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል ነው።” (ኤፌ1፡9-10)።

ስለ አንድ ነገር ስንጽፍ የምንጽፍበት ዓላማ አለን። አንዳንዴ መጻፍ በራሱ ከባድ ሊሆን ይችላል። ለምሳሌ የአሜሪካው ፕሬዚደንት አብርሃም ሊንከን ጌቲስቡርግ አድሬስ በመባል የሚታወቀውን ዝነኛ ሥራቸውን የጻፉት በ1863 ዓ.ም. ላይ ሲሆን፣ ይኸውም 7,000 ወታደሮች በአንድ የውጊያ ዐውድ በተቀጠፉበት፣ አስከፊው የአሜሪካ እርስ በርስ ጦርነት ወቅት ነበር። ሊንከን በዚያ ጽሑፋቸው በ1776 ላይ የተመሠረተው አገረ መንግሥት የገጠመውን የመጨረሻውን ፈተና ተቋቁሞ ያልፋል ወይም “ከምድር ገጽ ይጠፋል” የሚል ጥሪ ለአሜሪካ መሥራች አባቶች አቅርበው ነበር።

ጳውሎስ ደብዳቤውን እንዲጽፍ ያነሣሣው ጥልቅ ዓላማ አለው። ለዚህ አንዱ ምክንያት መታሰሩ ሲሆን (ኤፌ. 3፡13፣ 6፡20) ሌላው ደግሞ በወቅቱ የተንሰራፋው ስደትና ፈተና የኤፌሶን ሰዎች ተስፋ እንዲቆርጡ መፈተኑ ነበር። እነርሱ ክርስቶስን እንደ ግል አዳኛቸው ተቀብለው የቤተ ክርስቲያን አባል በሆኑበት ወቅት ምን እንደተከሰተ ጳውሎስ አስታውሷቸዋል። የክርስቶስ አካል ሆኑ (ኤፌ. 1፡19-23፣ ኤፌ. 4፡1-16)፣ በእግዚአብሔር ማደሪያነት ተገነቡ (ኤፌ. 2፡19-22)፣ የክርስቶስ ሙሽራ (ኤፌ. 5፡21-33) እና በሚገባ የታጠቀ ሰራዊት (ኤፌ. 6፡10-20) ሆነው ተደራጁ።

ማንኛውንም ነገር በክርስቶስ አንድ እያረጉ ታላቁን አምላካዊ እቅድ ወደ ፍጻሜ በማምጣት ረገድ ስልታዊ ሚና ይጫወታሉ (ኤፌ. 1፡9-10)። ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩ ክርስቲያኖች እንደ ክርስቶስ ተከታይነታቸው የተሟላ ማንነታቸውን ብሎም መብቶቻቸውንና ጥቅሞቻቸውን በጉልህ እንዲመለከቱ እነርሱን ለመቀስቀስ ጽፏል።

ሰኔ 18
Jun 25

ጳውሎስ፡ የኤፌሶን ሰዎች ወንጌላዊ


ጳውሎስ ኤፌሶንን ለመጀመሪያ ጊዜ በጎበኘበት የሁለተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ማብቂያ ላይ ምን አደረገ? (ሐዋ. 18፡18-21)።



ከሮም ግዛት ትላልቅ ከተሞች አንዷ የነበረችው ኤፌሶን ወደ 250,000 የሚጠጉ ነዋሪዎች የነበሯት። ኤፌሶን ከእስያ ባለጸጋ አውራጃዎች መካከል የአንዱ ርዕሰ መዲና የነበረች ሲሆን፣ የእስያ አውራጃ ዛሬ--እስያ ትንሹ በሚል ከምናውቃቸው (ጣሊያን፣ ግሪክ፣ አልባኒያ፣ ሜቆዶንያ፣ ቡልጋርያ፣ ቱርክ፣ ግብጽ፣ ሊቢያ፣ እስራኤል እና ሊባኖስ) መካከል አብዛኛውን ክፍል ይሸፍናል። በጳውሎስ ዘመን አውራጃው በዕድገትና ብልጽግና ግስጋሴ ላይ ነበር። የወደብ ከተማ የነበረችው ኤፌሶን ቁልፍ የየብስ መንገዶች ማሳለጫ ጭምር ነበረች። ሕዝቡ በከተማ ውስጥ የነበሩትን በርካታ አማልክት ያመልክ የነበረ ሲሆን፣ እንደ መዲናው ጠባቂ አማልክት ትቆጠር የነበረችው አርጤምስ የሁሉም የበላይ ነበረች። አማልክቷ እንደ ሠርግ ባለ ማኅበራዊ ሥነ ስርዓት፣ የአትሌቲክስ ጨዋታዎች እና ዓመታዊ ክብረ በዓላት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቷት ትመለክ ነበር። (አርጤምስ በሮማውያን ዲያና ተብላ ትጠራ ነበር፤ ሐዋ. 19፡24፣ 35)።

ቆየት ብሎ፣ ጳውሎስ በሦስተኛው የሚሲዮናዊ ጉዞው ወደ ኤፌሶን ከተመለሰ በኋላ “ለሦስት ዓመታት” (ሐዋ. 20፡31) በዚያ ቆይቷል።

ሐዋርያው በኤፌሶን ጥብቅ መሠረት ያለውን ክርስትና ለመመሥረት በማሰብ በቂ አጽንኦት የተቸረው አገልግሎት ሰጥቷል።

በኤፌሶን “ለጌታ የሱስ” ከፍተኛ አክብሮት እንዲቸር መንስኤ የሆነው እንግዳ ክስተት ምንድን ነው? (ሐዋ. 19፡13-20)



ሉቃስ በከተማዋ እየዞሩ አጋንንትን ያስወጡ የነበሩ ሰባት አይሁዳውያንን አስመልክቶ አንድ እንግዳ ታሪክ ያጋራናል። እነዚህ መናፍስት አውጪዎች የየሱስንና የጳውሎስን ስም በአንድ እየቀላቀሉ ማነብነባቸው፣ ጥምረታቸው የተሳሳተ መስመር ውስጥ የመውደቁ ማስረጃ ነበር። ወሬው በከተማዋ በናኘ ጊዜ “ሁሉም ፍርሀት ያዛቸው፤ በዚህም የጌታ የኢየሱስ ስም ተከበረ” (ሐዋ. 19፡17)። ክስተቱ በአንዳንድ ያመኑ ወገኖች ላይ ሳይቀር ብርቱ ተጽእኖ ማሳደሩን ተከትሎ “አምሳ ሺህ (የብር ሣንቲሞች)” ዋጋ ያላቸውን ውድ የአስማት መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው በአደባባይ አቃጠሉ። አብዛኞቹ የከተማው ነዋሪ አማኞች፣ የሱስ የሚመለክበት መንገድ በሌላ በማንም ሆነ በምንም ዓይነት አምልኮ መበከል እንደሌለበት ተማሩ።

ከፍተኛ ገንዘብ የሚያወጡ የገዛ መጽሐፎቻቸውን ማቃጠላቸው ምን ያሳያል? ይህ ለጌታ ስላላቸው ቁርጠኝነት ምን ይናገራል?

ሰኔ 19
Jun 26

በጨዋታ ማሳያው ስፍራ የተነሳው ሁከት


ጥቅሶቹን ያንብቡ፡ ሐዋ. 19፡21-20፡1። ከዚህ ታሪክ ምን መማር እንችላለን?



ጳውሎስ ሰፊና እጅግ ዘመናዊ ከተማ በሆነችው በኤፌሶን ያደረገው ምሥክርነት በጣም ውጤታማ ከመሆኑ የተነሣ፣ የከተማዋ ጠቃሚ የኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት በሆነው ቱሪዝምን ያማከለ የአርጤምስ ቤተ አምልኮ ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ችሎ ነበር። የቤተ አምልኮው ሕንፃ ንድፍ ምንኛ ውብ ነበር! የዚህ አስደናቂ ንድፍ ከፊል ገጽታ 127 ምስሶዎች የነበሩት ሲሆን፣ እነዚህ እያንዳንዳቸው 18 ሜትር ከፍታ የነበራቸው ምሰሶዎች ከንጹህ የፔሪያን እብነበረድ የተሠሩ ነበሩ። እብነበረዱ ለቅርጻ ቅርጾች ከፍተኛ ዋጋ የሚሰጠው ነጭና እንከን የለሽ ነበር። ከእነዚህ የምሰሶ ዓምዶች መካከል ሠላሳ ስድስቱ በወርቅ የተለበጡ ሲሆን፣ ይህም ቤተ አምልኮው ከጥንቱ ዓለም ሰባት ድንቃ ድንቅ ሥራዎች አንዱ እንዲሆን አስችሎታል።

የጳውሎስ ጸረ ጣዖት አምልኮ መልእክት ከቤተ አምልኮው ይገኝ የነበረውን የገንዘብ ድጋፍ እያሳጣ (ሐዋ. 19:27) መሆኑ ያሳሰበው የብር አንጥረኛው ድሜጥሮስ አብረውት የነበሩትን የእጅ ጥበብ ባለሙያዎች በንዴት ገረፋቸው። ሕዝቡ ከገበያው ስፍራ ጥርግርግ ብሎ በመውጣት በፍጥነት እየበዛና እየተተራመሰ 25ሺህ ሰዎችን ወደሚይዘው የጨዋታ ማሳያ ስፍራ ይተም ጀመር።

በዚያም ሁከቱ የቀጠለ ሲሆን “የኤፌሶኗ አርጤምስ ታላቅ ናት!” እያሉ ሁለት ሰዓት ያህል ጮኹ (ሐዋ. 19፡34)። ሕዝቡ በከተማው ዋና ጸሐፊ እንዲበተን ከተደረገ በኋላ ጳውሎስ ከአማኞች ጋር ተገናኝቶ ከተማዋን ለቆ ወጣ።

ጳውሎስ በሦስተኛው ሚስዮናዊ ጉዞው ማብቂያ ላይ ከኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ጋር ተገናኘ። ጳውሎስ ያሳሰበውን ነገር እንዴት በአጭሩ ይገልጹታል? (ሐዋ. 20፡17-38)።



ጳውሎስ ከኤፌሶን ጋር የነበረው ግንኙነት የዘመን ቅደም ተከተል፡-
♦ 52 ዓ.ም፡ የጳውሎስ የመጀመሪያ፣ አጭር ጉብኝት ወደ ኤፌሶን (ሐዋ. 18፡18-21)።
♦ 53-56 ዓ.ም፡ የጳውሎስ የሦስት ዓመት አገልግሎት በኤፌሶን (ሐዋ. 19፡1-20፡1)። በዚያ ቆይታው መጨረሻ አካባቢ 1ኛ ቆሮንቶስን አቀናበረ (1ቆሮ. 16፡5-9)።
♦ 57 ዓ.ም: ጳውሎስ በሚሊጢን በነበረበት ወቅት ከኤፌሶን ሽማግሌዎች ጋር ተገናኘ (ሐዋ. 20፡17-38)።
♦ 62 ዓ.ም: ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች የጻፈውን ደብዳቤ ያቀናበረው ምናልባትም በሮም ታስሮ በነበረበት ወቅት ሊሆን ይችላል።

“ስለዚህ ተጠንቀቁ፤ ሦስት ዓመት ሙሉ ሌሊትና ቀን ምንም ሳላቋርጥ በእንባ እያንዳንዳችሁን እንደ መከርኋችሁ አስታውሱ” በማለት ጳውሎስ ተናግሯል (ሐዋ. 20፡31)። ጳውሎስ በዚህ ዘመን ቤተ ክርስቲያናችንን ስለ ምን ያስጠነቅቃታል ብለው ያስባሉ? ለምን?

ሰኔ 20
Jun 27

ለኤፌሶን ሰዎች የተጻፈውን ደብዳቤ ማድመጥ


ጳውሎስ ወደ ኤፌሶን ሰዎች የጻፈው ደብዳቤ አማኞች በሚሰባሰቡባቸው በየቤቱ የሚደረጉ ጉባዔዎች ላይ እንዲነበብ ጽፎላቸዋል። ጳውሎስ ከተሰናበተ በኋላ በነበሩት ዓመታት በኤፌሶን የነበረው የክርስትና እንቅስቃሴ እያደገ በመሄዱ የቤት ለቤት ጉባዔ ቁጥርም በእጅጉ ጨምሮ ነበር። የመሥራቹ ሐዋርያው ጳውሎስ የግል ተወካይ የሆነው ቲኪቆስ፣ በእነዚያ የጥንት አማኞች መካከል ቆሞ ከእርሱ የተላከውን ደብዳቤ ሲያካፍላቸው መስማታቸው ለእነርሱ በእጅጉ የላቀ ትርጉም ነበረው። ራሱ በመልእክቱ እንደጠቆመው፣ የተሰበሰበው ጉባዔ የአስተናጋጁን ቤተሰብ አባላት ማለትም አባት፣ እናት፣ ልጆች እና ባሪያዎችን ያካተተ ነበር (ኤፌ. 5፡21-6፡9)። በዚያን ዘመን አንድ የቤተሰብ አባል ሌሎችንም (በቤቱ ባለቤት ላይ ጥገኛ የሆኑ ነፃ ሰዎችን) እንዲሁም ሌሎች የቤተሰብ አባላትን ይጨምር ነበር።

ከዚህ በታች ከተዘረዘሩት የደብዳቤው አስተዋጽኦዎች ጋር በተያያዘ ሙሉውን ደብዳቤ ያንብቡ፣ በተለይ ድምጽዎን ጮክ አድርገው ቢያነቡ ይመረጣል (ይህን ለማድረግ 15 ደቂቃ ያህል ይፈጃል)። በጥቅሉ ሲታይ በደብዳቤው ውስጥ የሚስተጋባው ጭብጥ ምንድን ነው?



የመክፈቻ ሰላምታ (ኤፌ. 1:1, 2) የመግቢያ ቡራኬ (ኤፌ. 1፡3-14) አማኞች በክርስቶስ ላይ ያተኮረ ጥበብን እንዲቀበሉ መጸለይ (ኤፌ. 1፡15-23) በአንድ ወቅት በመንፈስ ሙታን የነበርን፣ አሁን ግን ከክርስቶስ ጋር ከፍ ከፍ ያልን (ኤፌ. 2፡1-10) ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያንን ከአይሁድ እና አሕዛብ መፍጠሩ (ኤፌ. 2፡11-22) ጳውሎስ፡ ለአሕዛብ የተላከ የክርስቶስ ሰባኪ (ኤፌ. 3፡1-13) አማኞች የክርስቶስን ፍቅር እንዲለማመዱ መጸለይ (ኤፌ. 3፡14-21) በመንፈስ አነሳሽነት የተቋቋመውን የቤተ ክርስቲያን አንድነት አጥብቃችሁ ያዙ (ኤፌ. 4፡1-16) አንድነት የሚያጎለብተውን አዲሱን ሕይወት ኑሩ (ኤፌ. 4፡17-32) በፍቅር፣ በብርሃን እና በጥበብ ተመላለሱ (ኤፌ. 5፡1-20) በክርስቲያናዊ ቤተሰብ ውስጥ የክርስቶስን ቅርጽ ያለው ሕይወት ተለማመዱ (ኤፌ. 5:21-6:9) እንደ እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያን ሰራዊት በአንድነት ቁሙ (ኤፌ. 6፡10-20) የመዝጊያ ሰላምታ (ኤፌ. 6፡21-24) በዚህ ደብዳቤ ውስጥ ምን ቁልፍ ጭብጥ ያለ ይመስላል? ለእርስዎ ምን መልእክት አለው? የትኛውን ነጥብ ወይም ነጥቦች ይዳስሳል?

ሰኔ 21
Jun 28



የኤፌሶን ሰዎች መልእክት የተጻፈበት ጊዜና ሁኔታ


ጳውሎስ ለኤፌሶን አማኞች የጻፈውን ደብዳቤ የጀመረበትና ያበቃበት መንገድ ምን ይመስላል? ለእነሱ ካለው ጥልቅ ምኞት ምን እንማራለን? ኤፌ. 1 1፣ 2፣ ኤፌ. 6፡ 21-24።



ጳውሎስ በደብዳቤው መግቢያ ላይ ራሱን እንደ መልእክቱ ደራሲ አድርጎ ሲገልጽ እንመለከታለን (ኤፌ. 1፡1)። በደብዳቤው መሀል ገደማ ደግሞ ጳውሎስ በድጋሚ ራሱን በስም ይገልጽና “በዚህም ምክንያት እኔ ጳውሎስ ለእናንተ ለአሕዛብ የክርስቶስ ኢየሱስ እስረኛ ሆኛለሁ” (ኤፌ. 3፡1) ይላል። በዚህም ሐዋርያ በመሆን ባከናወናቸው ሥራዎች ላይ የግል ማሰላሰሉን ያስተዋውቃል (ኤፌ. 3፡1-13)። በደብዳቤው መጨረሻ አካባቢ እንደገና ስለ ታሰረበት ሁኔታ (ኤፌ. 6፡20) ይጠቅስና ጽሑፉን በራሱ አባባል ይደመድማል (ኤፌ. 6፡ 21, 22)። አንዳንድ ምሑራን ደብዳቤው በጳውሎስ መጻፉን ቢክዱም፣ ነገር ግን መልእክቱ የጳውሎስ ጽሑፍ ውጤት ሆኖ መናገሩን መገንዘብ በእጅጉ አስፈላጊ ነው። በርካታ ሕዝበ ክርስቲያን ጳውሎስን የመልእክቱ ደራሲ አድርገው መቀበላቸው ተገቢና ትክክል ነው።

ጳውሎስ መታሰሩ በኤፌሶን በሚገኙ አማኞች ላይ ሊያስከትል የሚችለው ተጽእኖ ምን ያህል አሳስቦት ነበር? (ኤፌ. 3፡13)።



የኤፌሶን ሰዎች መልእክት ጳውሎስ ከእስር ቤት ከጻፋቸው ሌሎች ደብዳቤዎች ማለትም ከቆላስይስ ሰዎች (ቆላ. 4፡7፣ 8) እና ፊልሞና ጋር ተመሳሳይ የሆነ አጠቃላይ ጊዜ እና ሁኔታዎችን የሚጋሩ ይመስላል። በተጨማሪ ጳውሎስ በኤፌሶን ካገለገለ በኋላ ብዙ ጊዜ ያለፈ ይመስላል (ኤፌ. 1፡15፣ ኤፌ. 3፡1-2)። ጳውሎስ የኤፌሶን ሰዎችን መልእክት የጻፈው በ62 ዓ.ም. አካባቢ፣ በሮም በሚገኝ እስር ቤት ውስጥ በነበረበት ወቅት ሳይሆን እንደማይቀር ይታመናል።

ጳውሎስ በኤፌሶን መልእክቱ፣ በዚያ የነበሩ አድማጮቹን ሁኔታ አስመልክቶ ሰፋ ያለ ዝርዝር ሐሳብ አልዘገበም። የእርሱ ትኩረተ ሀሳብ እጅግ ሰፊ ነው። እግዚአብሔር ከወሰነበት ማለትም “ዓለም ከመፈጠሩ አስቀድሞ” (ኤፌ. 1፡4) ካለው ግዙፍ የጊዜ ርዝመት ጭብጥ--በክርስቶስ እስከ ቀረቡት የእግዚአብሔር ማዳን መሪ ሃሳቦች ያሉትን ጥልቅ ማሰላሰሎች ያቀርባል። በዚህም ደብዳቤው ረጅም ዓረፍተ ነገሮችን፣ ተደጋጋሚ መግለጫዎችንና ዘይቤያዊ አነጋገሮችን ያካተተ ከፍ ያለ የሥነ ጽሑፍ ስልት ይዟል። ጳውሎስ እንዲህ ያለውን የአጻጻፍ ስልት በሌላም ቦታ ሊጠቀም ቢችልም (ለምሳሌ በሮሜ 8፡31- 39)፣ ነገር ግን በኤፌሶን ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ይህም በርካታ የውዳሴ፣ የጸሎትና የአምልኮ ቋንቋ (ኤፌ. 1፡3-14፣ ኤፌ. 1፡15-23፣ ኤፌ. 3፡14-21) እንዲሁም በጥንቃቄ የተቀመሩና ከፍ ያለ ተምሳሌታዊ ሀሳብ የያዙ መልእክቶችን ያቀርባል (ለምሳሌ፣ ኤፌ. 4 1-16፣ ኤፌ. 5 21--33፣ ኤፌ. 6 10-20)።

ሰኔ 22
Jun 29

ወደ ኤፌሶን ሰዎች፡ Ephesians: A Christ-saturated Letter


ጳውሎስ የደብዳቤውን ጭብጥ የሚያስታውቅበት መንገድ ምን ይመስላል? ኤፌ. 1፡9-10።





የኤፌሶንን መልእክት ጠቅለል አድርጎ ማቅረብ የሚቻለው እንዴት ነው? ጳውሎስ በእስር ቤት ሆኖ ክርስቶስን ያማከለውን አምላካዊ ራእይ ያቀርባል። ዕቅዱ ውሎ አድሮ ገቢራዊ የሚሆነውንና በዚያ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን የሚኖራትን ሚና ይገልጻል። እግዚአብሔር እቅዱን ለመጀመርና “በሰማይም በምድርም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ራስ በሆነው በክርስቶስ ሥር ለመጠቅለል” (ኤፌ. 1፡10) እነሆ በእርሱ አስፈላጊውን ሁሉ አደረገ። ይህን ያደረገው በአይሁድና አሕዛብ አዲስ ስብዕና የተዋቀረችውን አንድ የቤተ ክርስቲያን አካል በመፍጠር ነው (ኤፌ. 2፥14)። አማኞች የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዓላማ ወደ ፍጻሜ እየተቃረበ መሆኑን በመገንዘብ፣ ለክፉ ኃይላት የማስጠንቀቂያ ምልክት እየሆኑ ከዚህ መለኮታዊ ዕቅድ ጋር በጥምረት ይሠሩ ዘንድ ተጠርተዋል (ኤፌ. 3፡10)።

ኤፌሶን 1፡9-10 እንደሚናገረው እግዚአብሔር አንድነት ብሎ የሚጠራው ክርስቶስን ያማከለውን ሕብረት ነው። ስለዚህ የኤፌሶን መልእክት እግዚአብሔር በክርስቶስ ውስጥ ያደረጋቸውን ነገሮች ሁሉ የሚያወድስና፣ አማኞች በክርስቶስ ለተሰጣቸው መንፈሳዊ ሀብቶች ሐሴት የሚያደርጉበት በክርስቶስ የተጻፈ ደብዳቤ መሆኑን መገንዘብ ብዙም አያስገርምም።

ጳውሎስ "በክርስቶስ" የሚለውን ቃልና ሌሎች ተመሳሳይ ሐረጎችን ከሠላሳ ጊዜ በላይ የተጠቀመ ሲሆን፣ የሱስን በየትኛውም ቦታ ከፍ ከፍ አድርጎታል።

ደብዳቤውን ሲያነቡ እነዚህን ቃላቶችና ሐረጎች ልብ ብለው ይመልከቱ። በተጨማሪ ጳውሎስ በየሱስ ላይ የሚያተኩርባቸውን በርካታ መንገዶች በንቃት ይከታተሉ።

ጳውሎስ የኤፌሶን አማኞች ሁሉንም ነገር በክርስቶስ አንድ የማድረግ አምላካዊ እቅድ የሆነው የቤተ ክርስቲያን አካል መሆናቸውን በማስታወስ፣ በአማኞች ልብ ውስጥ መንፈሳዊ ቁርጠኝነት ለመጫር ያላሰለሰ ጥረት ያደርጋል።

በደብዳቤው “ቤተ ክርስቲያን” (በግሪክ፡ ekklēsia) የሚለውን ቃል ሲጠቀም፣ “ዓለማቀፋዊ” ቤተ ክርስቲያን ለማለት ነው። ከዚያ ውጪ አባባሉ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያን የሚል አንደምታ የለውም።

እርሱ የተጠቀመው ቀዳሚ ስልት ስለ ቤተ ክርስቲያን መናገር ሲሆን፣ ይህንንም የሚያደርገው ግልጽ ዘይቤዎችን በመጠቀም ነው። ከእነዚህም ውስጥ አራቱን በተወሰነ መልኩ አዳብሯል፡-
1. ቤተ ክርስቲያንን እንደ አካል (ኤፌ. 1:22፣ 23፤ ኤፌ. 2:16፣ ኤፌ. 3:6፣ ኤፌ. 4:1-16፣ 25፤ ኤፌ. 5:23፣ 29-30)።
2. ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሕንፃ/ ቤተ መቅደስ (ኤፌ. 2፡19-22)።
3. ቤተ ክርስቲያንን እንደ ሙሽራ (ኤፌ. 5፡22-27)።
4. ቤተ ክርስቲያንን እንደ ተዋጊ ሰራዊት (ኤፌ. 6፡10-20)። እነዚህ እያንዳንዳቸው ገጽታዎች እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ያለው ዓላማና ሃሳብ ምን እንደሆነ በየራሳቸው መንገድ ይገልጻሉ።

እርስዎ አካል በሆኑባት ሰባተኛ ቀን ዳግም ምጽአቱ ተጠባባቂ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት እግዚአብሔር ዓለማቀፋዊ ወደ ሆነው፣ ዘርፈ ብዙውን ቋንቋ፣ ባህልና ሁሉንም ማኅበረሰብ ወደሚያስተናግደው (ራእ. 14፡6-7) ብሎም ሁሉንም ነገር በኢየሱስ ሥር ወደሚጠቀልለው (ኤፌ. 1፡9-10) ሕብረት እየሳበን ነው። ከታላቁ አምላካዊ እቅድ ጋር ተባባሪ ሆነን መሥራት የምንችለው እንዴት ነው?

ሰኔ 23
Jun 30


ተጨማሪ ሀሳብ


የየሱስን እና የጳውሎስን ስም (ሐዋ. 19፡13-20፣ የእሁድ ጥናት) በተሳሳተ መንገድ ጥቅም ላይ ያዋሉት ሰዎች ታሪክ፣ ጳውሎስ ሥልጣንን አስመልክቶ በኤፌሶን ሰዎች መሃል በርካታ የአነጋገር ስልቶችን የተጠቀመበትን ምክንያት ለመረዳት ያስችለናል። በየሱስ ሉዓላዊ አምላክነት ያመኑ አንዳንድ አዳዲስ አማኞች ውድ ዋጋ የነበራቸውን የድግምት መሥሪያ መጽሐፎቻቸውን ሰብስበው እሳት ውስጥ ጣሉ። ለአርኪዮሎጂ ግኝት ምስጋና ይግባውና ከእነዚህ የአስማት መምሪያ መጽሐፎች ጋር የሚመሳሰሉ--የአምልኮ ሥርዓቶችን፣ ድግምቶችን፣ ልዩ ልዩ ቀመሮችን፣ ርግማኖችን ወዘተ አካትተው የያዙ ከ250 በላይ ጥራዞች በቁፋሮ ተገኝተዋል። ጥራዞቹ እነዚህን የወንድ እና የሴት አማልክት ብሎም መናፍስት ለመለማመጥ የሚያስችሉ አምልኮአዊ ሥርዓቶች እንዴት እንደሚከወኑ ምክረ ሀሳብ የሚሰጡ ነበሩ።

እነዚህ ጥራዞች 50ሺ የብር ሣንቲሞች ወይም የ50ሺ ቀናት ደሞዝ የሚያህል ዋጋ እንደነበራቸው ሉቃስ ይነግረናል። (ይህ መጠን በዛሬው ዋጋ ቢሰላ፣ አንድ በሰሜን አሜሪካ የሚገኝ ሠራተኛ የቀን ደሞዝ 80 የአሜሪካ ዶላር ቢሆን፣ ይህ መጠን 4ሚልዮን ዶላር ይደርሳል እንደ ማለት ነው።) ይህ ዝርዝር ጥራዞቹ ለዕለት ከዕለት ሕይወታቸው ምን ያህል አስፈላጊ እንደነበሩ ጥሩ አድርጎ ያመለክታል። “እነዚህ ሰዎች ክታቦቻቸውን፣ ምትሃታቸውን፣ አማልክት መለማመጫቸውን እና መንፈሳዊ ኃይል የሚያገኙበትን ባህላዊ መንገድ ርግፍ አድርገው ትተው ንስሐ መግባት እንዳለባቸው ያምኑ ዘንድ፣ መለኮታዊውን ጣልቃ ገብነት ጠይቋል።”-Clinton E. Arnold, Ephesians (Grand Rapids, MI: Zondervan, 2010), p. 34.

የኤፌሶን መጽሐፍ “የማያባራውን የርኩሳን 'ኃይላት' ተጽእኖ እና ጥቃቶች እንዴት መቋቋም እንደሚቻል” ተገቢው መመሪያ ለሚያስፈልጋቸው አማኞች እንደ ተጻፈ እናስተውላለን።”-Clinton E. Arnold, Pow- er and Magic: The Concept of Power in Ephesians (Grand Rapids, MI: Baker Books, 1992), p. 165.

ጳውሎስ በኤፌሶን ሰዎች መልእክቱ ለኤፌሶናውያን በሰጠው ምላሽ ክርስቶስን ከማንኛውም ኃይላት በላይ የከበረ አድርጎ የሚያቀርብ ሲሆን (ኤፌ. 1፡20-23)፣ እግዚአብሔር ለአማኞች የሚሰጠው ብርታት የላቀ መሆኑንም አጉልቶ ያሳያል (ኤፌ. 2:15-19፣ ኤፌ. 3:14-21፣ ኤፌ. 6:10-20)።


የመወያያ ጥያቄዎች




1. ዛሬ በዓለማችን እና በእርስዎ ሕይወት ንቁ ተጽእኖ ያላቸው የትኞቹ ኃይላት ወይም ሥልጣናት ናቸው? እነዚህ ኃይላት አማኞች ለከበረውና ከፍ ከፍ ላለው ክርስቶስ ንጹህና ያልተበከለ ታማኝነት በመሰጠት ፋንታ እንዲያከብሯቸውና እንዲንበረከኩላቸው በመፈተን ራሳቸውን የሚገልጡት እንዴት ነው?

2. ሁሉንም ነገሮች በክርስቶስ አንድ የማድረግ አምላካዊ ዕቅድ ዐውድ መሠረት “የተወሰነው ዘመን” ሲደርስ የሚሆነውን የወደፊቱን ተስፋ ጳውሎስ ይገልጻል። ጳውሎስ “ተስፋ” የተሰኘውን ቃል የተጠቀመባቸውን የሚከተሉትን ጥቅሶች ይከልሱ፡ ኤፌ. 1፡18፣ 2፡12፣ 4፡4። ለወደፊቱ የሚበጅ ተስፋ አለ ብሎ ለምን አመነ?

3. ጳውሎስ ታላቁን የክርስቶስን መምጣት ተስፋ በሚቀጥሉት የኤፌሶን ምንባቦች የገለጸው እንዴት ነው? ኤፌ. 1:13-14፣ ኤፌ. 1:21፣ ኤፌ. 2:7፣ ኤፌ. 4:30፣ ኤፌ. 5፡5። ይህ ተስፋ አሁን ለእኛ ያለው ትርጉም ምንድን ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL