የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

የኤፌሶን መጽሐፍ



3ኛ ሩብ ዓመት 2023



ሰኔ፣ ሐምሌ፣ ነሐሴ፣ ጳጉሜ፣ መስከረም 2015/16 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Jun 24 - Sep 29




አዘጋጅ : በጆን ኬ ማክቪ

ትርጉም : ዘላለም አስረስ እና ታምሬ ሻዕማሎ



ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
3ኛ ሩብ ዓመት
ከሰኔ 17/ 2015-መስከረም 18/ 2016 ዓ.ም
ኤፌሶን በአስቸጋሪ ጊዜ የሱስን መከተል የሚቻልበት መንገድ

ሐዋርያው ጳውሎስ ለኤፌሶን ሰዎች በጻፈው ደብዳቤው ስለ ራሳቸው ስለ ኤፌሶን ሰዎች ይነግረናል። በኤፌሶን የመጀመሪያዎቹ አስደሳች የክርስትና ተልእኮ ክንውኖች ገቢራዊ ከሆኑ ከዓመታት በኋላ፣ እነዚህ ሕዝቦች ከክርስትና እምነታቸው አንደምታዎች ጋር ታግለዋል።

በአንድ ወቅት ከሮም ግዛቶች መካከል በአራተኛ ደረጃ ትገኝ በነበረችው በዚህች ከተማ ምጣኔ ሐብት ላይ ችግር እስከ መፍጠር ደርሶ የነበረው ጳውሎስ፣ አሁን ገሸሽ ተደርጎ ታስሮአል። እስር ቤት ሆኖ በጻፈው ደብዳቤ፣ በዚያ በዘመኑ የተራቀቀ ከተማና የተጠናከረ የኤፌሶን የአረማዊ ባህል መሃል ይኖሩ የነበሩ የኤፌሶን አማኞች፣ የየሱስ ደቀ መዝሙር መሆን ምን ማለት እንደሆነ የነበራቸውን ማንኛውንም ዓይነት ግንዛቤ በመዘንጋት “ልባቸው እንዳይዝል” ይጨነቅ ነበር። ምንም እንኳ የመልእክቱ አድማጮች ክርስቲያኖች ቢሆኑም፣ የጳውሎስ ደብዳቤ ለአገልግሎት እጩዎችን በንቃት የመፈለግ፣ የማግኘት እና የመመደብ ሂደት ዓይነት ድምጸት አለው። እነርሱን እንደገና ወደ ክርስትና እምነት ለመጥራት፣ ለክርስቶስ ያላቸውን የተዳፈነ ቅንአት መልሶ ለማቀጣጠልና በዓለም የእግዚአብሔር ታላቅ ተቋም የሆነችው፣ የቤተ ክርስቲያን አካል የመሆንን ደስታ ከተቀበረበት ለማስነሳት ይፈልጋል።

የክርስትና እምነት ሙሉ ለሙሉ ክርስቶስን ያማከለ እንደመሆኑ፣ ጳውሎስ ለእርሱ ያለውን አድናቆት እና አምልኮ ያንጸባርቃል። በእምነት የደከሙ ክርስቲያኖች ዳግመኛ በሁለት እግሮቻቸው መቆም ካለባቸው፣ ለየሱስ የነበራቸውን የመጀመሪያ ፍቅር መልሰው ማጽናት፣ በጸጋው እና በኃይሉ ላይ አዲስ መተማመን መመሥረት ይጠበቅባቸዋል። ይህን ተከትሎ ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩትን አማኞች አምልኮ የመሳብ ምኞት ስላደረበት፣ ከኃይላትና አማልክት ሁሉ በላይ የሆነውን የክርስቶስን በሰማይ መክበር አጉልቶ ገልጿል። የሱስ የዘመናት መለኮታዊ እቅድ ግብ እንደመሆኑ፣ በዚህ እቅድ አማኞች እንደ ቤተ ክርስትያን ሁሉን ነገር በክርስቶስ አንድ የሚያደርገው አምላካዊ እቅድ ውስጥ ትልቅ ሚና ይኖራቸዋል።

ጳውሎስ በኤፌሶን የነበሩ አማኞች ለጌታቸው እንደ አዲስ እንዲሰለፉ ለመሳብ ጥረት ያደርግ በነበረበት ወቅት፣ የክርስቲያን ደቀ መዝሙርነት ጥያቄዎችን ሳይመልስ አላለፈም። ክርስቲያናዊ ባህሪ እና ማህበረሰብ ምን እንደሚመስሉ በዝርዝር አስቀምጧል። ክርስቲያኖች በመንፈስ አነሳሽነት፣ ክርስቶስን ወደሚያከብር፣ በእግዚአብሔር ወደሚመራ አምልኮ የተጠሩ ሲሆን፣ ይህንንም ጳውሎስ ደጋግሞ ገልጿል። የክርስቶስ አምልኮ በአንድ ሰው ሥራ እና ንግግር ላይ ተጽእኖ ይኖረዋል። ክርስቶስን መውደድ ማለት የእምነት ባልንጀሮችን ማክበር እና ተገቢውን ዋጋ ለአነርሱ መስጠት ነው። በባህላቸው ውስጥ አብዝቶ የተንሰራፋውን መጥፎ መንፈስ እና የወረደ የዝሙት ባህሪ መቃወም ማለት ነው።

በቤተ ክርስቲያን እና በቤተሰብ ውስጥ ባለን ግንኙነት ክርስቶስ ካሳየው የራስን ጥቅም መሥዋዕት የማድረግ ምሳሌ መዋስ ነው። ይህ ማለት አዲስ ስለሆነው ሰው ሕልውና በኤፌሶን ለሚኖሩ አማኞች ግልጽ ምሳሌዎችን መስጠት ነው።

ጳውሎስ በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አባል የሆነው አዲሱ ሰው በሚኖረው ገጽታ ዙሪያ የተሰማውን ደስታ ለመግለጽ በደብዳቤው ሰፋ ያለ ሽፋን ሰጥቶአል። በተለይ ደግሞ እግዚአብሔር ተራርቀው የነበሩትን የሰው ልጆች ማለትም አይሁድንና አሕዛብን በቤተ ክርስቲያን አንድ አድርጎ በመቀላቀሉ ይበልጥ ተበረታቷል። ጠላትነት ሊጠበቅ በሚችልበት አንድነት ውስጥ ሲኖሩ፣ የእግዚአብሔርን አዲስ ማኅበረሰብ እና የሚመጣውን መንግሥት ባህሪያት የማሳየት እድል ይኖራቸዋል።

የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን አካል በመሆን አስፈላጊነት ዙሪያ ጳውሎስ ለቤተ ክርስቲያን አራት ዘይቤያዊ ባህሪዎችን አዘጋጅቷል። አማኞች የክርስቶስ አካል እንደመሆናቸው፣ ለክርስቶስ ያላቸውን ታማኝነትና እርስ በርስ ያላቸውን አንድነት ያሳያሉ። በቀራንዮ ላይ በክርስቶስ መሥዋዕትነት የታነጹ እግዚአብሔር የሚመለክበት ሕያው መቅደስ ናቸው። ሙሽራው የራሱ አድርጎ ሊወስዳቸው ዳግም የሚገለጥበትን ታላቁን የጋብቻ ሥነ ሥርዓት በጉጉት የሚጠባበቁ የክርስቶስ ሙሽራ ናቸው። የመጨረሻው ዘይቤያዊ ባህሪ፣ ጳውሎስ ዳግመኛ ወደ ክርስትና እምነት እንዲመጡ ባደረገው ጥሪ፣ እነርሱ በስሙ ሰላምን የሚያውጁ፣ በእግዚአብሔር ኃይል ከጨለማው ኃይሎች ጋር የሚዋጉ፣ የክርስቶስ ሠራዊት እንደሆኑ ይገልጻል።

የኤፌሶን ሰዎች መልእክት በተለይ እንደ እኛው ዓይነት ስለሆነ ዘመን የሚናገር ሲሆን፣ በዓለም መማረካቸው፣ ብሎም እየነጎደ ያለው ጊዜ ክርስቲያናዊ ደቀ መዝሙርነትን አሰልቺ የሚመስል አደጋ ላይ ጥሎታል። መጽሐፉ ክርስቶስን ከፍ ከፍ የሚያደርግ እና በእርሱ ዳግም ምጽአት ተስፋ ስንኖር ሳለ፣ እንደ ታታሪ እና ንቁ የቤተ ክርስቲያኑ አባላት እርሱን መከተላችን አስፈላጊ ሰለመሆኑ አጽንኦት ይሰጣል። ይህ ሩብ ዓመት የኤፌሶን ሰዎችን በጸሎት መንፈስ የማዳመጥ ብሎም የሱስን በአስቸጋሪ ጊዜያት የመከተል ደስታን የምናጣጥምበትን ጸጋ ይሰጠናል።

ጆን ኬ ማክቪ፣ ፒኤች.ዲ.፣ ከጎርጎሮሳውያኑ 2006 ጀምሮ ባገለገሉበት በዋላ ዋላ ዩኒቨርሲቲ፣ በኮሌጅ ፕሌስ፣ ዋሺንግቶን፣ ዩኤስኤ የነገረ-ኃይማኖት ፕሮፌሰር ናቸው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL