የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ራዕይ 17:1፣ 2፣ 15፤ ራዕይ 18:1–4፤ ራዕይ 17:4–6፤ ማቴ. 16:18፤ ኤር. 50:33–38፤ መዝ. 115:4–8።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ:- “እነዚህ በጉን ይወጋሉ፤ በጉም የጌቶች ጌታና የነገሥታት ንጉሥ ስለ ሆነ እነርሱን ድል ይነሣል፥ ከእርሱም ጋር ያሉ የተጠሩና የተመረጡ የታመኑም ደግሞ ድል ይነሣሉ” (ራዕይ 17:14)።
የታላቁ ተጋድሎ ዋና ሀሳብ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ በምሳሌነት በቀረቡ
ሁለት ሴቶች ቀርቧል። በራዕይ ምዕራፍ 12 ላይ የተጠቀሰችው ሴት ፀሐይን
የተጎናጸፈች ስትሆን በራዕይ ምዕራፍ 17 ላይ የተገለጸችው ሴት ደግሞ ቀይ
ልብስ ለብሳለች።
የክርስቶስን አንጸባራቂ ክብር፣ ፀሐይን የተጎናጸፈችው ሴት አስደናቂ
ምልክት በራዕይ 12 ላይ አለ። እውነተኛ አፍቃሪዋ ለሆነው ኢየሱስ ታማኝ ነች።
በሀሰት አስተምህሮዎች ክፋት አልረከሰችም። በመላው መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ
ንጹህ የሆነች ሴት የኢየሱስን ሙሽራ፣ ወይም እውነተኛዋን ቤተ ክርስቲያን
ትወክላለች። በኤርምያስ 6፡2 ላይ ነቢዩ እንዲህ ይላል፡- “የጽዮንን ልጅ በተዋበችና
በተሰባቀለች ሴት እመስላታላሁ።” ነቢዩ የእግዚአብሔርን ሕዝብ ለመግለጽ
“የጽዮን ልጅ” ወይም ታማኝ ሴት የሚለውን መግለጫ ይጠቀማል። (ኤፌ. 5፡
25-32 እና ሆሴዕ 2፡20ን ይመልከቱ)።
በተቃራኒው መጽሐፍ ቅዱስ ክህደትን በምንዝር ወይም በግልሙትና
ይመስለዋል (ያዕቆብ 4፡4)። ሕዝቅኤል ስለ እሥራኤል አመጽና አለመታመን
ሲናገር እንዲህ በማለት አልቅሷል፡- “በባልዋ ፋንታ ሌሎችን ተቀብላ የምታመነዝር
ሴትን ትመስያለሽ” (ሕዝ. 16:32)።
በዚህ ሳምንት ትምህርት በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ የተገለጹትን እነዚህን
ሁለት ሴቶች በማጥናት በእውነትና በውሸት መካከል ያለውን ተጋድሎ በጥልቀት
እንመረምራለን።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለግንቦት 19 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
ሁለት የማይመሳሰሉ ሥርዓቶች ራዕይ 12:17 እና ራዕይ 17:14ን ያንብቡ። የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን የተገለጸችው እንዴት ነው? ለዚህ የሰይጣን ምላሽስ ምንድር ነው?
እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ታማኝ የሆኑ ሕዝቦች አሉት። ራዕይ 14፡12 ታማኝነታቸውን “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁ” በማለት የገለጸ ሲሆን በሌላ ቦታ “የተጠሩ፣ የተመረጡና ታማኝ” (ራዕይ 17:14) በማለት ይገልጻቸዋል። ራዕይ 14:8 እና 17:1፣ 2 ያንብቡ። መልአኩ እንዴት ያለ አስፈሪ መግለጫ (ማስታወቂያ) ነው የሰጠው? ለመግለጫው ዋስትና ለመስጠት ባቢሎን ምን አደረገች?
ዮሐንስ የራዕይን መጽሐፍ የጻፈው በመጀመሪያው መቶ ክፍለ ዘመን
ማብቂያ ላይ ነበር። በዚህ ጊዜ ጥንታዊቷ የባቢሎን ከተማ ፈራርሳ የአቧራ
ክምር ሆናለች። ዮሐንስ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ መልእክቶቹን በሚጽፍበት ጊዜ
የባቢሎን ከተማ ከፈራረሰች በርካታ ምዕተ ዓመታት አልፏታል።
በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰችው የጥንቷ ባቢሎን የመጨረሻው
ዘመን ባቢሎን ምሳሌ ተደርጋ ተወስዳለች። በራዕይ ትንቢቶች ውስጥ ባቢሎን
የምትወክለው ከብሉይ ኪዳን ባቢሎን ጋር ተመሳሳይ ባህርይ የሚኖረውን
ሀሰተኛውን ኃይማኖታዊ ሥርዓት ነው። የጥንቷን ባቢሎን የመሯት መርሆዎች
ዘመናዊቷን መንፈሳዊ ባቢሎንንም የሚያጠናክሩ መዋቅሮች ይሆናሉ።
በራዕይ 17፡1-6 ላይ በቀይና ሀምራዊ ልብስ የተጎናጸፈችው ሴት ዘመናትን
ተሻግራ የምትሄድ ነች። ይህቺ ሴት በቀይ አውሬ ላይ ተቀምጣለች። መጽሐፍ
ቅዱስ ጋለሞታ ብሎ ይጠራታል። እውነተኛ ፍቅረኛዋን፣ ኢየሱስ ክርስቶስን
ትታለች። በዚህ ቦታ ሐዋርያው ዮሐንስ እያሳየን ያለው በዓለም ኃይለኛ የሆነ
ተጽእኖ ያለውን ከሃዲ ኃይማኖታዊ ሥርዓት ስዕላዊ መግለጫ ነው። ቃላቱን
ተመልከቱአቸው፡- ይህ ኃይል “የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም
“የምድርም ነገሥታት ከእርስዋ ጋር ሴሰኑ በምድርም
የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ”
የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ” (ራዕይ 17:2)ከተባለው ኃይል ጋር አንድ
ነው። ሰከሩ? ስካር በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ሁልጊዜ አሉታዊ ትርጉም አለው።
አመነዘሩ? ይህ ደግሞ የሀሰት ትምህርቶች፣ አስተምህሮዎችና ልምምድ ምልክት
ነው።
መሪዎችና ተራው ሕዝብ በተመሳሳይ ሁኔታ በዚህ ኃይል አሉታዊ ተጽእኖ ሥር
ወድቀዋል። የእኛ ብቸኛው መከላከያችን ምንድር ነው? (ኤፌ. 6:10–18ን ያንብ)።
ራዕይ 17:1፣ 2፣ 15 እና 18:1–4ን ያንብቡ። የባቢሎን ተጽእኖ ምን ያህል ሰፊ ነው?
የወደቀችው ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት ዓለም አቀፋዊ ባህርይ ስላለው
በማታለያዎቿ አማካይነት በመላው ዓለም ባሉ ሰዎች ላይ ተጽእኖ ትፈጥራለች።
ወንጌል “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ፣ ለወገን” ሁሉ ስለሚሰበክ እና “በዓለም ሁሉ
የመንግሥት ወንጌል ስለሚሰበክ” ሰይጣን ተናዷል። ከዚህ የተነሣ ‘የምድር
ኗሪዎችን’ አእምሮ ለመያዝ የሚቻለውን ማታለያ ሁሉ ሥራ ላይ ያውላል (ራዕይ
14:6፣ ማቴ. 24:14፣ ራዕይ 17:2)።
ራዕይ 17፡2 የታላቂቱ ባቢሎንን ምስጢር ማብራራቱን ሲቀጥል
“ከምድር ነገሥታት ጋር ሴስናለች” በማለት ያውጃል። መሴሰን ምንድር ነው?
መሴሰን ሕገወጥ ሕብረት መፍጠር ነው። በወደቀችው ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት
ውስጥ ከምድራዊ መንግስት ጋር ሕብረት መፍጠር ነው። በእውነተኛዋ የቤተ
ክርስቲያን ሥርዓት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን አንድነት የፈጠረችው ከኢየሱስ
ክርስቶስ ጋር ነው። የወደቀችው ቤተ ክርስቲያን ኃይልና ሥልጣን እንዲሰጡአት
የምትመለከተው ወደ ምድራዊ የፖለቲካ መሪዎች ነው። መንግስት አዋጆቿን
እንዲያስፈጽምላት ትሻለች። እንደ እውነተኛ ራስ ብርታቷን ከኢየሱስ ከማግኘት
ይልቅ መንግስታት እንዲደግፏት ትፈልጋለች።
ራዕይ 17፡2 ነገሮችን በድራማ መልክ ማሳየቱን ይቀጥላል፡- “በምድርም
የሚኖሩ ከዝሙትዋ ወይን ጠጅ ሰከሩ።” በመላው አዲስ ኪዳን ውስጥ ንጹህ
የሆነ የወይን ጭማቂ ለድነታችን በመስቀል ላይ የፈሰሰውን ያልተበከለና ንጹህ
የሆነውን የኢየሱስ ክርስቶስን ደም ለመወከል ጥቅም ላይ ውሏል (ማቴ. 26፡
27-29)። በሉቃስ 22፡20 ላይ ኢየሱስ እንዲህ ብሏል፡- “ ይህ ጽዋ ስለ እናንተ
በሚፈሰው በደሜ የሚሆን አዲስ ኪዳን ነው።” ንጹህ የሆነው አዲሱ የወንጌል
ወይን ሲዛባና የእግዚአብሔር ቃል ትምህርት ሰብዓዊ በሆኑ የኃይማኖት መሪዎች
ትምህርት ሲተካ “የባቢሎን ወይን” ይሆናል። (ማቴ. 15፡9ን ይመልከቱ)።
እግዚአብሔር ሕዝቡን ከባቢሎን እንዲወጡ እንደሚጠራም ልብ
በሉ። በሌላ አገላለጽ ሥርዓቱ የቱንም ያህል የተበላሸና ክፉ ቢሆን የሚሸፍነው
እጅግ ሰፊ ቦታን ከመሆኑ የተነሣ በውስጡ፣ ቢያንስ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን፣
እግዚአብሔር “ሕዝቤ” ብሎ የሚጠራቸውን ታማኞቹን ሰዎች ያካትታል (ራዕይ
18፡4)። ሆኖም ከመበላሸቱና ከክፋቱ የተነሣ ሊወድቅ ከተቃረበውና “የአጋንንት
ማደሪያ” እና “የእርኩሳንና የተጠሉ ወፎች” (ራዕይ 18፡2) ሁሉ መጠጊያ ከሆነው
ከዚህ የተበላሸና ክፉ ሥርዓት ውስጥ እግዚአብሔር ሕዝቡን የሚጠራበት ጊዜ
እየመጣ ነው።
የሶስቱን መላእክት መልእክት የሚያውጁ ሰዎች እግዚአብሔር
“ሕዝቤ” ብሎ የሚጠራቸውን ሕዝብ ከባቢሎን እንዲወጡ ለመጥራት
እግዚአብሔር ሲጠቀምባቸው እነርሱ ምን ሚና ይኖራቸዋል?
ራዕይ 17:4–6ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለዚህ ክፉ ሥርዓት ምን ያስተምሩናል?
አስቀድመን እንደተመለከትነው ራዕይ 17 በብሉይ ኪዳን ዘመን
የነበረችውን የባቢሎንን ትምህርቶች በክርስትና ውስጥ ያስገባውን ከሃዲ
ኃይማኖታዊ ሥርዓትን ይገልጻል።
“የባቢሎንን ጠባይ ለመረዳት መመርመር ከፈለግን በመጽሐፍ ቅዱስ
ውስጥ አስቀድሞ ወደተጠቀሰበት ወደ ዘፍጥረት መጽሐፍ መሄድ ያስፈልጋል።
ነገሩ የተጀመረው በሜሶፖታሚያ ደቡባዊ ክፍል፣ ዛሬ ደቡብ ኢራቅ፣ ባቢሎንያ
ተብሎ በሚጠራው ቦታ በሚገኘው የሰነዖር ሜዳ ነበር። የሰብአዊ ዘር በራስ
ብቃት የመተማመን፣ ራስን ከጥፋት የመጠበቅና ከእግዚአብሔር ጥገኝነት ነጻ
የመሆን ምልክት የሆነው የባቢሎን ግንብ የተገነባው በዚህ ቦታ ነበር (ዘፍ. 11፡
1-4)።”—Ángel Manuel Rodríguez, paper entitled “The Closing of the
Cosmic Conflict: Role of the Three Angels’ Messages,” p. 43.
የባቤል ግንብ፣ የጥንቷ ባቢሎን የተመሰረተችበት ቦታ፣ የተገነባው
የእግዚአብሔርን ቃል በቀጥታ በመቃወም ነበር። የባቤል ግንብ ገንቢዎች
ይህን መታሰቢያ የሰሩት ለክብራቸው ስለሆነ እግዚአብሔር ቋንቋቸውን
አመሰቃቀለባቸው። የዘፍጥረት ዘገባ እንዲህ በማለት ያስቀምጠዋል፡- “ስለዚህም
ስምዋ ባቢሎን ተባለ፥ እግዚአብሔር በዚያ የምድርን ቋንቋ ሁሉ ደባልቋልና”
(ዘፍ. 11:9)።
ይህ ሥርዓት እጅግ ክፉ ከመሆኑ የተነሣ “በቅዱሳን ደምና በኢየሱስ
ምስክሮች ደም ሰክራ አየኋት” (ራዕይ 17:6) ተብሎ ተገልጾአል። ይህ አስደንጋጭ
የሆነ ስዕል ባቢሎን ምን ያህል የተበላሸች እንደሆነች የሚያሳይ ስዕል ነው (ኢሳ.
49:26ን ደግሞ ይመልከቱ)።
በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ሲታይ መንፈሳዊ ባቢሎን የምትወክለው
በሰብአዊ ትምህርቶችና ሀሳቦች ላይ የተመሰረተ እና በሰብአዊ ወጎች ላይ የተደገፈ
ኃይማኖትን ነው። ብሩህ አእምሮ ባላቸው ሰብአዊ መሪዎች የተገነባ ሰው ሰራሽ
ኃይማኖት ነው፣ ነገር ግን የወንጌልን ኃይልና ኢየሱስ የገነባትን ቤተ ክርስቲያን፣
በአመጽ ሳይሆን በፍቅር ላይ የተመሰረተችውን ቤተ ክርስቲያን የሚቃወም ነው።
የራዕይ መጽሐፍ እነዚህን ሁለት ኃይማኖታዊ ሥርዓቶች ይገልጻል።
የመጀመሪያው በኢየሱስ ሙሉ በሙሉ መታመንን እና በቃሉ መደገፍን ያሳያል።
ሁለተኛው ደግሞ በሰብአዊ ሥልጣን ላይ መታመንን እና በሰብአዊ ኃይማኖታዊ
ትምህርቶች ላይ መደገፍን ያሳያል። አንዱ ክርስቶስን ማዕከል ያደረገ እምነት
ሲሆን በክርስቶስ ጸጋ፣ መስዋዕትነትና ለድነታችን በተፈጸመው ሥርየት ሙሉ
በሙሉ የሚደገፍ ነው። ሌላኛው ለድነት ሙሉ በሙሉ በክርስቶስ በመደገፍ
ፋንታ በቤተ ክርስቲያን ወጎች በመደገፍ የሚተካ እምነትን በሰብአዊ መንገድ
ማቅረብ ነው።
አሳሳች ከሆነው የባቢሎን ተጽእኖ እና ሙሉ በሙሉ በእግዚአብሔር
ከመደገፍ ይልቅ በራሳችን እንድንደገፍ ከሚያደርገን ዝንባሌ ራሳችንን
መጠበቅ የምንችለው እንዴት ነው?
የራዕይ መጽሐፍ ተማጽኖ በሁለቱ ሴቶች ምሳሌነት ተጠቃልሎ ለመሰጠት የቀረበ አስቸኳይ ጥሪ ነው። በዚህ በእውነትና በሀሰት መካከል በሚደረግ ዓለም አቀፋዊ ተጋድሎ ውስጥ አንዳንድ ጊዜ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚሸነፍ ቢመስልም የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን በመጨረሻ አሸናፊ እንደምትሆን እርሱ ቃል ገብቶአል። ማቴ. 16:18 እና ራዕይ 17:14ን አነጻጽሩ። ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያኑን በተመለከተ ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ተስፋ ምን ነበር?
ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያኑ የተገነባችበት ጽኑ መሰረት ነው። ቤተ
ክርስቲያኑ በቃሉ ትምህርቶች የተመሰረተችና በመንፈሱ የምትመራ ነች። ከዚህ
በተቃራኒ፣ አስቀድመን እንደተመለከትነው፣ ባቢሎን የተመሰረተችው በሰው
ሰራሽ ትምህርቶችና ወጎች ላይ ነው። በቅዱሳት መጻሕፍት ውስጥ በተገለጠው
የእግዚአብሔር ፈቃድ ቦታ ሰብአዊ አስተያየቶችን ወይም ወጎችን የሚተካ ወይም
ከእነርሱ በላይ አድርጎ የሚያስቀምጥ ማንኛውም ኃይማኖታዊ መሪ ዝም ብሎ
የባቢሎንን ምስቅልቅል እያስፋፋ (እያበረታታ) ነው።
በጥንቷ ባቢሎን ዘመን ቤተ ክርስቲያንና መንግስት አንድና የማይነጣጠሉ
ነበሩ። ንጉሡ ናቡከደነፆር በቤተ መቅደሱ ውስጥ በነበረው በንጉሱ ዙፋን
በተቀመጠ ጊዜ ከአማልክቱ ጋር እንደተነጋገረ ተደርጎ ይወሰዳል። በአንድ
አጋጣሚ፣ የባቢሎን ንጉሥ በእውነተኛው አምላክ ላይ የማመጽ ተግባር ተደርጎ
በሚታይ መልኩ አምልኮን የሚያስገድድ ዓለም አቀፋዊ አዋጅ ያወጣ ሲሆን
በመንግስቱ ሥር ያሉ ሁሉ ለአዋጁ እንዲገዙና ለምስሉ እንዲሰግዱ ትዕዛዝ
አስተላልፎ ነበር። ይህም በመጨረሻ ዘመን ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነ ሕዝብ፣
ለሀሰተኛ ምሰል መስገድ እምቢ የሚሉ፣ የሚጋፈጡትን ነገር የሚያሳይ ኃይለኛ
ምልክት ነው። (ዳንኤል 3 ይመልከቱ)።
በምድር ታሪክ የመጨረሻዎቹ ቀናት የቤተ ክርስቲያንና የመንግስት ጥምረት
ያለበት ሥርዓት፣ መንፈሳዊቷ ባቢሎን፣ እንደ እግዚአብሔር እናገራለሁ ከሚል
መንፈሳዊ መሪ ጋር ትነሳለች። የዚህ መሪ ቃል የእግዚአብሔር ቃል እንደሆነ፣
ትዕዛዞቹም የእግዚአብሔር ትዕዛዞች እንደሆኑ ይታወጃል። በዘመናት ሁሉ የሮም
ጳጳሳት በምድር ላይ በእግዚአብሔር ቦታ እንደቆሙ ሲያውጁ ኖረዋል። ጳጳስ ሊዎ
13ኛው ሰኔ 20፣ 1894 ዓ.ም ለሮም ጳጳሳት በላከው ደብዳቤው እንዲህ ብሎ ነበር፡
- “በዚህች ምድር ላይ ሁሉን የሚችል አምላክን ቦታ እንይዛለን።” የፌራሪ የቤተ
ክህነት መዝገበ ቃላት እንዲህ የሚል ሀሳብ ይጨምራል፡- “ጳጳሱ እጅግ የተከበረና
ከፍ ያለ ከመሆኑ የተነሣ ተራ ሰው አይደለም፣ ነገር ግን እንደ እግዚአብሔርና
እንደ እግዚአብሔር ወኪል ነው።” ሐዋርያው ጳውሎስ ይህንን ኃይል በማጋለጥ
የሚከተሉትን ቃላት ይጨምራል፡- “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ብሎ አዋጅ እየነገረ
በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ እስኪቀመጥ ድረስ፥ አምላክ ከተባለው ሁሉ፥
ሰዎችም ከሚያመልኩት ሁሉ በላይ ራሱን ከፍ ከፍ የሚያደርገው ተቃዋሚ እርሱ
ነው” (2ኛ ተሰ. 2:4)።
እግዚአብሔር በባቢሎን ውስጥ ታማኝ ሰዎች እንዳሉት አስቀድመን
ስለተመለከትን ስለዚህ ሕዝብ እንዴት እንደምንናገር መጠንቀቅ
ያለብን ለምንድን ነው? ከሥርዓቱ በተቃራኒ ሰዎችን እንደ ግለሰቦች
እንዳንፈርድባቸው መጠንቀቅ ያለብን ለምንድን ነው?
“የታላቂቷ ባቢሎንን ምስጢር ጥርት ባለ ሁኔታ በመለየት ረገድ ሌላ ፍንጭ እዚህ ቀርቧል። ጣዖት አምልኮ የባቢሎናውያን አምልኮ እምብርት ነበር። ኤር. 50:33–38 እና 51:17፣ 47ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ስለ ጥንቷ ባቢሎን የምስሎች አምልኮ እና እግዚአብሔር ለዚህ ስለሰጠው ምላሽ ምን አገኙ?
ኤርምያስ 50 እና 51 ባቢሎን በሜዶንና ፋርስ ስለመጥፋቷ ተንብዮአል።
ለባቢሎን ስርዓተ ቀብር ምክንያት ከሆኑ ነገሮች አንዱ የጣዖት አምልኮ ነበር።
ባቢሎናውያን እነዚህ ምስሎች አምላኮቻቸውን እንደሚወክሉ ያምኑ ነበር።
በባቢሎናውያን ኃይማኖት ለአምላኮቻቸው ሀውልቶች የሚደረግ መንፈሳዊ
ሥርዓትና አምልኮ ቅዱስ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰድ ነበር፤ አማልክቱ በቤተ
መቅደሶቻቸው ውስጥ ባሉ ሀውልቶችና እነርሱ በሚገኙባቸው የተፈጥሮ ደኖች
ውስጥ በተመሳሳይ ጊዜ ይኖሩ ነበር። ጣዖቶቻቸውን መዝረፍ ወይም ማጥፋት
መለኮታዊ ድጋፍ እንደማጣት ይቆጠር ነበር። ከባቢሎናውያን ቀጥሎ በነበረው
ዘመን የከለዳውያን ልዑል የነበረው ማርዱክ-አፕላ-ኢዲና 2ኛው የባቢሎናውን
አማልክትን ሀውልቶች ከአሦራዊው ሰናክሬብ እጅ ለማዳን በሜሶፖታሚያ ደቡብ
ወደነበሩ ረግረጋማ ቦታዎች ይዞአቸው ሸሽቶ ነበር። (Jane R. McIntosh, An-
cient Mesopotamia: New Perspectives, ABC-CLIO, Inc., [Santa Barba-
ra, CA, 2005] pp. 35–43).
የመጽሐፍ ቅዱስ ነቢያት እነዚህን ሕይወት የለሽ ምስሎችን ማምለክን
ሕይወት ካለውና ሕይወት ሰጭ ከሆነው ፈጣሪ አምላክ አምልኮ ጋር አነጻጽረው
ነበር (ኤር. 51፡ 15፣ 16፣ 19)።
ዘጸ. 20:4–6 እና መዝ. 115:4–8ን ያንብቡ። ስለ ጣዖት አምልኮ ምን
ያስተምራሉ?
የመንፈሳዊቷ ባቢሎን የጣዖት አምልኮ ጉዳዮች ለእንጨትና ለድንጋይ
ምስሎች ከመስገድ ያለፈ ነገር ቢሆንም መንፈሳዊቷ ባቢሎን በአምልኮ
አገልግሎቶቿ ጋር ከተዋወቁት ምስሎች አንጻር ከጥንቷ ባቢሎን ጋር
ትመሳሰላለች። ምስሎችን እንደ አምልኮ ዕቃዎች መጠቀም ወይም “አክብሮት”
ተብሎ የሚጠራው ተግባር መንፈስ ቅዱስ በአእምሮዋችን ዘላለማዊውን ነገር
እንዳያሰርጽ ስለሚገድብና የእግዚአብሔርን ግርማ ሕይወት ወደሌለው ሀውልት
ዝቅ ስለሚያደርግ ሁለተኛውን ትዕዛዝ መጣስ ነው። ምስሎች ወደ ክርስትና
የገቡት በ4ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሲሆን እነዚህ ምስሎች ወደ ክርስትና እንዲገቡ
የተደረጉበት ምክንያት ክርስትና በአህዛብ ዘንድ የበለጠ ተቀባይነት እንዲያገኝ
ታስቦ ነው። እንደ አለመታደል ሆኖ ለእነዚህ ምስሎች ለእግዚአብሔር ብቻ
የሚገባው ቅድስናና አክብሮት የተሰጣቸው ሲሆን ይህ ድርጊት ሁሉም ነገር
በመንፈሳዊነት ረገድ ዝቅ እንዲል (እንዲዋረድ) ያደርጋል።
“የባቢሎንን ውድቀት የሚያውጀው የራዕይ ምዕራፍ
14 መልእክት በአንድ ወቅት ንጹህ ለነበሩ ግን አሁን ለረከሱ የኃይማኖት አካላት
የሚሰራ መሆን አለበት። ይህ መልእክት የፍርድ ማስጠንቀቂያን ስለሚከተል
በመጨረሻው ዘመን መሰጠት አለበት፤ ስለዚህ የሮም ቤተ ክርስቲያን ለብዙ መቶ
ምዕተ ዓመተት ወድቃ ሰስለምትገኝ ይህ መልእክት የሚያመለክተው የሮም ቤተ
ክርስቲያንን ብቻ አይደለም።”—Ellen G. White, The Great Controversy,
p. 383.
በዳንኤል 3 ላይ በጥንቷ ባቢሎን ዘመን “ንጉሡ ናቡከደነፆር ላቆመው
የወርቁ ምስል እንዲሰግዱ” ትዕዛዝ የተሰጣቸው የሶስቱ ዕብራውያን ታሪክ
መንፈሳዊቷ ባቢሎን በመጨረሻው ዘመን የሀሰት “ምስል” እንዲያመልኩ
ስታስገድድ ስለሚሆነው ነገር ምልክት ወይም ምሳሌ ሆኖ ይቆማል። (ራዕይ 13:15፤
14:9፣ 11፤ 16:2፤ 19:20፤ 20:4ን ይመልከቱ)። ሶስቱ ዕብራውያን እንዲጥሱት
ተጠይቀው የነበረው፣ ሁለተኛው ትዕዛዝ (ዘጸ. 20፡4፣ 5)፣ ይህ ኃይል በሌላ ቦታ
በተገለጸበት ሁኔታ “ዘመንንና ሕግን” (ዳን. 7፡25) ሊለውጥ እንደሚሻ ከተገለጸው
ከሁለቱ ትዕዛዛት አንዱ መሆኑ ምንኛ የሚገርም ነገር ነው።
ይህ ኃይል ለመሻር ጥረት ያደረገው ሌላኛው ትዕዛዝ የትኛው ነው??
አስቀድመን እንደተመለከትነውና አሁን በድጋሚ እንደምንመለከተው፣ አራተኛው
ትዕዛዝ በመላው የአምልኮ ጥያቄ ማዕከል ላይ ስለተቀመጠ፣ “ሰማይንና ምድርን፣
ባህርንም በውስጡም ያሉትን ነገሮች ሁሉ ፈጥሮ በሰባተኛው ቀን ላረፈው”
አምላክ ለመስገድ(ዘጸ. 20:11፤ ደግሞ ራዕይ 14:7ን ይመልከቱ) ወይም ለአውሬውና
ለምስሉ ለመስገድ ጥያቄ በሚቀርብልን በመጨረሻው ቀውስ ወቅትም የጥያቄው
ማዕከል ይሆናል።
1.የባቢሎን ግንብ ከዘመናዊቷ መንፈሳዊ ባቢሎን ጋር ምን ግንኙነት
አለው? በሁለቱ መካከል ያለው ተመሳሳይነት ምንድር ነው?
2. ሁለት የሚቃረኑ ሀሳቦችን የሚያጣጥሙት እንዴት ነው?
ኢየሱስ ለቤተ ክርስቲያኑ ሥልጣን ሰጥቷል፣ ነገር ግን መንፈሳዊ
ልምምዳችንን በማንኛውም መንፈሳዊ መሪ እጅ ማስቀመጥ አደገኛው
ነው። የቤተ ክርስቲያን ሥልጣን ገደብ ምንድር ነው?
3. ከባቢሎን ኃጢአቶች መካከል አንዱ የሆነው ጣዖት አምልኮ
ዝም ብሎ ለሐውልት (ለምስል) መስገድ ብቻ እንዳልሆነ ማወቅ
የምንችለው እንዴት ነው? ፕሮቴስታንቶች እንኳን በጣዖት አምልኮ
ውስጥ ሊወድቁ የሚችሉት በምን መንገዶች ነው?
4. በዳንኤል ምዕራፍ ሶስት እና በዚያ ከተጠቀሰው የግዳጅ አምልኮ
መካከል የምናገኛቸውና በመጨረሻ ዘመን ማስጠንቀቂያ የተሰጡን
አንዳንድ መመሳሰሎች ምንድር ናቸው?