የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሶስት ዓለም አቀፋዊ መልእክቶች



2ኛ ሩብ ዓመት 2023


ሚያዝያ 14 - 20

5ኛ ትምህርት

Apr 22 - 28




የፍርዱ መልካም ዜና



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ራዕይ 14:7፤ መዝ. 51:1–4 ራዕይ 20:12፤ ዳን. 7:9፣ 14፣ 26፤ ራዕይ 4:2–4፤ ራዕይ 5:1–12።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ:- “በታላቅ ድምፅም፦ የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት አለ” (ራዕይ 14:7)።

መጽሐፍ ቅዱስ እጅግ ግልጽ የሆነባቸው ነገሮች ካሉ እግዚአብሔር የፍርድ አምላክ መሆኑና ይፍጠንም ይዘግይም፣ በዚህም ሆነ በዚያ፣ ፍርድ-አሁን እጅግ ጠፍቶ ያስቸገረው ፍርድ- “የምድር ሁሉ ፈራጅ” በሆነው እግዚአብሔር በራሱ ሊተላለፍ ነው (ዘፍ. 18፡25፤ ደግሞ መዝሙር 58፡11፤ 94፡2፤ 98፡9)። ጳውሎስ እንደጻፈው “እንግዲያስ እያንዳንዳችን “እንግዲያስ እያንዳንዳችን ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” ስለ ራሳችን ለእግዚአብሔር መልስ እንሰጣለን” (ሮሜ 14:12)። አስፈሪ ሀሳብ ነው፣ አይደለም እንዴ? በእግዚአብሔር ፊት፣ እጅግ ጥልቅ የሆኑ ነገሮችን በሚያውቅ አምላክ ፊት፣ “ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ “ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ በሚያመጣው” መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ በሚያመጣው” (መክብብ 12:14) አምላክ ፊት መልስ ለመስጠት መቆም አስፈሪ አይደለም? ሆኖም፣ ፍርድ በመጨረሻ የእግዚአብሔርን በጎነትና ጸጋ፣ ከዳኑት ጋርም ሆነ ከጠፉት ጋር ፍትህ የሚያሰፍን እና መሃሪ መሆኑን የሚገልጥ ነው።

በዚህ ሳምንት በዓለም ላይ እየተካሄደ ካለው ታላቁ ተጋድሎ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ጥልቅ የሆኑ የፍርድ ሀሳቦችን እንመረምራለን። በተለይም ታማኝ የሆኑ የእግዚአብሔር ሕዝብ “ሊመጣ ያለውን” አይቀሬ ፍርድ ሲጋፈጡ ምን እንደሚሆን እንመለከታለን(የሐዋ. 24:25)። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሚያዝያ 21 ሰንበት ለመዘጋጀት ጥኑ።

ሚያዝያ 15
Apr 23

የፍርዱ ሰዓት አስፈላጊነት (ቁም ነገር)


የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ፣ ራዕይ፣ በክፉና በመልካም መካከል ለዘመናት በዘለቀው ታላቁ ተጋድሎ ድምዳሜ (ፍጻሜ) ላይ ትኩረት ያደርጋል። አማጺው መልአክ፣ ሉሲፌር፣ የእግዚአብሔርን ፍርድ፣ ፍትሃዊነትና ጥበብ ተገዳድሮ ነበር። እግዚአብሔር ዓለማትን በሚያስተዳድርበት መንገድ ኢ-ፍትሃዊና ፍርደ ገምድል ነው በማለት ከሷል። የራዕይ የመጨረሻው ፍርድ በእግዚአብሔር ባህርይ ላይ የሚደረገውን ይህን ጦርነት ማዕከል ያደረገ ነው። ራዕይ 14:7 እንዲህ ይነበባል፡- “የፍርዱ ሰዓት ደርሶአልና እግዚአብሔርን ፍሩ ክብርንም ስጡት፤ ሰማይንና ምድርንም ባሕርንም የውኃንም ምንጮች ለሠራው ስገዱለት።” ስለ “ዘላለማዊው ወንጌል” ከተነገረን በኋላ የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ስለ ፍርድ መናገሩ ወሳኝ የሚሆነው ለምንድር ነው? “ዘላለማዊው ወንጌል” ከእግዚአብሔር ፍርድ ጋር ምን ግንኙነት አለው?



የመጀመሪያው መልአክ መልእክት አካል የሆኑት ወንጌልና ፍርድ ሊነጣጠሉ በማይችሉበት ሁኔታ የተቆራኙ ናቸው። “ዘላለማዊው ወንጌል” ባይኖር ኖሮ በፍርድ ጊዜ ተስፋ አይኖረንም ነበር። አሁን እንደምንመለከተው “ዘላለማዊው ወንጌል” በፍርድ ጊዜ ብቸኛው ተስፋችን ነው። ወንጌል በውስጡ ከሚይዛቸው ነገሮች ከፊሉ የፍርድ እወጃ እንደሆነ ምንም ጥያቄ የለውም።

በዚህ የፍርድ ጊዜ እያንዳንዱን ሰብአዊ ፍጡር ለማዳን እግዚአብሔር ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን ያልወደቁ አለማት ይመለከታሉ። ይህ ፍርድ የእግዚአብሔርን ፍትሃዊነትና ምህረት ይገልጣል። ስለ ፍቅሩና ሕጉ የሆነ ነገር ይነግረናል። ስለሚያድነው ጸጋውና ነጻ ስለሚያወጣው ኃይሉ ይናገራል።

ፍርድ ለኃጢአት ችግር የእግዚአብሔር የመጨረሻው መፍትሄ አካል ነው። በዩኒቨርስ ውስጥ በክፉና በመልካም መካከል ባለው ተጋድሎ ውስጥ እግዚአብሔር ለሰይጣን ክሶች በመስቀል ላይ መልስ ሰጠ፣ ነገር ግን በፍርድ ጊዜ እግዚአብሔር ሊያድነንና ወደ መስቀል ሊመራን ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ማድረጉን ይገልጣል።

ወሰን የለሽ የሆኑ፣ ዝርዝርና ትክክለኛ ሰማያዊ መዝገቦች ይከፈታሉ (ዳን. 7፡10)። ለእግዚአብሔር እጅግ ውድ ከመሆናችን የተነሣ በመንፈስ ቅዱስ ተማጽኖና በመስቀል ላይ በቀራኒዮ መስቀል ላይ በክርስቶስ በነጻ በተሰጠን ድነት ብርሃን የመረጥነውን ምርጫ ለማየት መላው ዩኒቨርስ ጸጥ ይላል። መዝሙር 51:1–4ን፣ በተለይም ቁጥር 4ን በጥንቃቄ ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች በፍርዱ ትርጉምና ዓላማ ላይ ብርሃን ለማብራት የሚረዱት እንዴት ነው?

ሚያዝያ 16
Apr 24

የእግዚአብሔር ምህረትና ፍርድ


መስቀልና ፍርድ እግዚአብሔር ፍትሃዊና መሃሪ እንደሆነ ይገልጣሉ። የተጣሰው ሕግ የኃጢአተኛውን ሞት ይጠይቃል። ፍርድ “የኃጢአት ደሞዝ ሞት” መሆኑን ያውጃል። ምህረት ደግሞ “የእግዚአብሔር ስጦታ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የዘላለም ሕይወት ነው›› (ሮሜ 6፡23) በማለት ይመልሳል። የእግዚአብሔር ሕግ ሊለወጥ ወይም ሊጣስ የሚችል ከሆነ የኢየሱስ መሞት በፍጹም አስፈላጊ አልነበረም። የኢየሱስ ሞት የሕግን ዘላለማዊ ባህርይ ስለሚያጸና ሕግ የፍርድ መሰረት ነው። ራዕይ 20:12ን ያንብቡ። የምንፈረደው እንዴት ነው? መልካም ሥራዎቻችን ከድነታችን ጋር ምን ግንኙነት አላቸው?



ሥራዎቻችን ምርጫዎቻችንን እና ለእግዚአብሔር ያለንን ታማኝነት ይገልጣሉ። በኤፌሶን 2፡8 እና 9 ላይ እንደተገለጸው “ጸጋው በእምነት አድኖአችኋልና፤ . . . ማንም እንዳይመካ ከሥራ አይደለም።” ነገር ግን ክርስቶስ ሲያድነን ይለውጠናል። “እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጀውን መልካሙን ሥራ ለማድረግ በክርስቶስ ኢየሱስ ተፈጠርን” (ኤፌ. 2:10)።

በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የተሞሉ መልካም ሥራዎቻችን አያድኑንም፣ ነገር ግን እምነታችን እውነተኛ መሆኑን ይመሰክራሉ። የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍርድ ማስመሰልን ሁሉ፣ ግብዝነትን ሁሉ፣ ውሸትን ሁሉ በማስወገድ ወደ ጥልቅ ማንነታችን ሰንጥቆ ይገባል። ኤለን ጂ ኋይት በፍርድ ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት የሚኖረንን ቦታ በማሳየት ወንጌልና ፍርድ እንዴት እጅ ለእጅ ተያይዘው እንደሚሄዱ በመግለጽ የሚከተለውን ኃይለኛ የሆነ ግንዛቤ ሰጥታናለች።

“በእግዚአብሔር እውቅና የተሰጠው ሕዝብ ያደፈ ልብስ ለብሶ በእግዚአብሔር ፊት እንደቆመ ተደርጎ የመወከሉ እውነታ በእርሱ ስም እናምናለን በሚሉ ሁሉ ዘንድ ራስን ዝቅ ወደማድረግና በጥልቀት ልብን ወደ መመርመር መምራት አለበት። እውነትን በመታዘዝ ነፍሳቸውን እያነጹ ያሉ ስለ ራሳቸው እጅግ ትሁት አመለካከት ይኖራቸዋል። የክርስቶስን እንከን የለሽ ባህርይ በተመለከቱ ቁጥር ከእርሱ ምስል ጋር ለመስማማት ያላቸው ፍላጎት ጠንካራ ይሆንና የራሳቸው ንጽህና ወይም ቅድስና አነስተኛ እንደሆነ ይመለከታሉ። ነገር ግን ኃጢአተኛ ሁኔታችንን እየተገነዘብን ሳለን ክርስቶስ ጽድቃችን፣ ቅድስናችንና ድነታችን በመሆኑ ላይ መደገፍ ያስፈልገናል። ሰይጣን እኛን ለከሰሰበት ክስ መልስ መስጠት አንችልም። ስለ እኛ ውጤታማ ተማጽኖ ሊያቀርብልን የሚችል ክርስቶስ ብቻ ነው። በእኛ መልካም ሥራ ሳይሆን በክርስቶስ መልካም ሥራ የከሳሹን መከራከሪያ ጸጥ ማድረግ ይችላል።”—Testimonies for the Church, vol. 5, pp. 471, 472። በእርሷ ቃላት ውስጥ ወንጌልና ፍርድ የማይነጣጠሉ መሆናቸውን እንዴት ተመለከቱ? በወንጌልና በፍርድ መካከል ካለው ከዚህ ግንኙነት ለራስዎ ምን ተስፋ ማግኘት ይችላሉ?

ሚያዝያ 17
Apr 25

አስደናቂ (እፁብ ድንቅ) ትዕይንት


የዳንኤልና ራዕይ ትንቢታዊ መጻሕፍት በምድር ታሪክ የመጨረሻዎቹ ቀናት እየተገለጡ ስላሉ ክስተቶች የሚጠቁሙ መንታ መጻሕፍት ናቸው። የራዕይ መጽሐፍ የእግዚአብሔር የፍርዱ ሰዓት መድረሱን ያውጃል። የዳንኤል መጽሐፍ ፍርድ መቼ እንደተጀመረ ይገልጣል።

በዳንኤል 7 ላይ እግዚአብሔር የዓለምን ታሪክ ለነብዩ ገለጠለት። መንግስታት ይነሳሉ ይወድቃሉም። አሳዳጅ ኃይሎች የእግዚአብሔርን ሕዝብ ይጨቁናሉ። በጥቅሱ ውስጥ እግዚአብሔር ለዳንኤል ባቢሎንን፣ ሜዶንና ፋርስን፣ ግሪክን፣ ሮምን፣ የሮምን መከፋፈልና በቤተ ክርስቲያን ላይ ለ1260 ዓመታት የደረሰውን ስደት (ዳን. 7፡25፤ ራዕይ 12፡14ንም ደግሞ ይመልከቱ) ከገለጸለት በኋላ የዳንኤል አእምሮ ሁሉንም ነገር በሚያስተካክለው በግርማ በተሞላ ሰማያዊ ክስተት ላይ እንዲያተኩር አደረገው። የነቢዩ ትኩረት ከመንግሥታት መነሳትና መውደቅ እና ከምድር ጨቋኝ ኃይሎች ተነስቶ የዩኒቨርስ ዙፋን ወዳለበት ክፍልና ስህተትን ሁሉ ወደሚያስተካክልበትና ዘላለማዊ የሆነውን የጽድቅ መንግሥቱን ወደሚያቋቁምበት የእግዚአብሔር የመጨረሻው ፍርድ ተመራ።

እግዚአብሔር ዳንኤልን ትንቢታዊ በሆነ ራዕይ ከምድር ህውከትና ግጭት ወደ ዘላለማዊው ሰማያዊ ቤተ መቅደስና የዚህ ዓለም ሕጋዊ ገዥ የሆነው ክርስቶስ ህጋዊ የሆነውን መንግሥቱን ከአባቱ ወደሚቀበልበት የዩኒቨርስ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወሰደው። ዳን. 7:9፣ 10፣ 13ን ያንብቡና በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ዳንኤል የተመለከተውን ነገር ይግለጹ። የፍርዱ የመጨረሻው ውጤትስ ምንድር ነው? ዳን. 7:14፣ 26፣ 27ን ይመልከቱ።



የሰብአዊ ዘር የመጨረሻው መዳረሻ በሰማያዊው ፍርድ ቤት ይወሰናል። እውነት ያሸንፋል። ፍትህ ይሰፍናል። በቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ ውስጥ ይህ እጅግ አስገራሚና አስደናቂ ከሆኑ ትዕይንቶች አንዱ ነው። መልካሙ ዜና በክርስቶስ ጽድቅ ለተሸፈኑ ታማኝ የእግዚአብሔር ሕዝብ ነገሮች በጥሩ ሁኔታ ይጠናቀቃሉ።

በመላው ዩኒቨርስ ፊት ኢየሱስ ወደ አባቱ ይቀርባል። ሰማያዊ ፍጡራን በዙፋኑ ዙሪያ ይሰበሰባሉ። በመላው ዩኒቨርስ ያሉ ያልወደቁ ፍጡራን ይህን የፍርድ ትዕይንት አክብሮት በተሞላበት ፍርሃት ይከታተላሉ። ለብዙ ሺህ ዓመታት ሲከናወን የነበረው ረዥም ጦርነት በቅርቡ ሊያበቃ ነው። የዩኒቨርስ ዙፋንን ለመቆጣጠር ሲካሄድ የነበረው ጦርነት ሙሉ በሙሉ ተወስኗል። በትንቢት እንደተገለጸው የመንግስታትን መነሳትና መውደቅን በተመለከተ ዳንኤል ትክክል ነበር። ስለዚህ የእግዚአብሔር ቃል በፍጹም ስለማይለወጠው ስለ መጨረሻው “ዘላለማዊ መንግሥት” የተናገረውን ማመን ትርጉም የሚኖረው ለምንድር ነው?

ሚያዝያ 18
Apr 26

ሰማይ በጨረፍታ/በውልብታ ሲታይ


በራዕይ ምዕራፍ 4 ላይ ዮሐንስ በሰማይ የተከፈተ በር ይመለከትና “ወደዚህ ውጣና ከዚህ በኋላ ሊሆን የሚያስፈልገውን ነገር አሳይሃለሁ” የሚል ግብዣ ቀረበለት (ራዕይ 4:1)። ኢየሱስ በሰማያዊው ቤተ መቅደስ በተከፈተው በር በክፉና በመልካም መካከል ሲካሄድ የነበረውን የታላቁን ተጋድሎ ዘላለማዊ ትዕይንት እንዲመለከት ሐዋርያውን ጋበዘው። እኛም ከዮሐንስ ጋር በተከፈተው በር አማካይነት ዘላለማዊውን የድነት ዕቅድ በጨረፍታ/በውልብታ ማየት እንችላለን። በሰማያዊው ጉባኤ እየተወሰኑ ስላሉ ጉዳዮች እኛ ምስክሮች ነን። በመልካምና በክፉ መካከል በሚካሄደው ታላቁ ተጋድሎ ውስጥ ያሉ መሰረታዊ ጉዳዮች በዓይኖቻችን ፊት እያደጉ ይሄዳሉ። ራዕይ 4:2–4ን ያንብቡ። በዚህ ቦታ በዳንኤል 7 ላይ ካለው የፍርድ ትዕይንት ጋር ምን የሚመሳሰል ነገር ማየት ቻሉ?



ይህ የዙፋን ክፍል ትዕይንት መሆኑ ግልጽ ነው። እግዚአብሔር አብ በሰማያዊ መላእክት ታጅቦ በዙፋኑ ላይ ተቀምጧል። የእግዚአብሔርን ፍርድ የሚያሳይ መብረቅና ነጎድጓድ አለ። በራዕይ 4፡4 ላይ በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ 24 ሽማግሌዎች እንዳሉ እንመለከታለን። 24ቱ ሽማግሌዎች እነማን ናቸው? በጥንቷ እሥራኤል በሌዋውያን ክህነት ውስጥ 24 ክፍሎች ነበሩ። እነዚህ ካህናት በእግዚአብሔር ፊት ሕዝቡን የሚወክሉ ነበሩ። ሐዋርያው በ1ኛ ጴጥሮስ 2፡9 ላይ የአዲስ ኪዳን አማኞች “የተመረጠ ትውልድ፣” “የንጉሥ ካህናት” እንደሆኑ ያውጃል። እነዚህ 24ቱ ሽማግሌዎች ምናልባት አንድ ቀን በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ ደስታቸውን የሚገልጹትን የዳኑትን ሁሉ ሊወክሉ ይችላሉ፤ ወይም ምናልባት ክርስቶስ ከሙታን ተነስቶ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ከሙታን ተነስተው ከእርሱ ጋር ወደ ሰማይ ያረጉ ሰዎችን ሊወክሉ ይችላሉ (ማቴ. 27፡ 52፤ ኤፌ. 4፡7፣8)።

በየትኛውም መንገድ ቢሆን መልካም ዜና አለ። ከምድር ከዳኑት መካከል በእግዚአብሔር ዙፋን ዙሪያ ጥቂቶች አሉ። እኛ የምንጋፈጣቸውን ዓይነት ፈተናዎች ተጋፍጠዋል። በክርስቶስ ጸጋና በመንፈስ ቅዱስ ኃይል አሸናፊዎች ሆነዋል። ኃጢአታቸውን የሚሸፍነውንና የሚያነጻውን የክርስቶስን ጽድቅ የሚወክለውን “ነጭ ልብስ” ለብሰዋል። ከክፉ ጋር በሚደረገው ጦርነት አሸናፊዎች ከመሆናቸው የተነሣ በእምነት የተሞሉ አማኞች የሰማያዊው ልዑላን ዘር መሆናቸውን የሚያመለክተውን የወርቅ አክሊል በራሳቸው ላይ ጭነዋል።

በሰማይ ዙፋን ተዘርግቶ እግዚአብሔር በዙፋኑ ላይ ተቀምጦ እንመለከታለን። በዙፋኑ ዙሪያ ሰማያዊ ፍጡራን ያሉ ሲሆን ወዲያውኑ ሰማይ በሙሉ መዝሙር መዘመር ይጀምርና የምሥጋናው ድምጽ ቀስ በቀስ እየጨመረ ይሄዳል። ዝማሬውም:- “ጌታችንና አምላካችን ሆይ፥ አንተ ሁሉን ፈጥረሃልና ስለ ፈቃድህም ሆነዋልና ተፈጥረውማልና ክብር ውዳሴ ኃይልም ልትቀበል ይገባሃል” ይላል (ራዕይ 4:11)።

ሚያዝያ 19
Apr 27

ኢየሱስ የተገባው ነው


በራዕይ 5:1–3 ላይ በድጋሚ ዙፋን እንመለከታለን። መጽሐፉ ከፊትና ከጀርባ እንደተጻፈበት ሆኖ ተገልጾአል። በመለኮታዊ ማህተም የታተመ (የተዘጋ) ስለሆነ በሰማይም ሆነ በምድር መጽሐፉን ሊከፍት የሚችል ማንም አልተገኘም ነበር። ሰማያዊ ፍጡራን ተብረከረኩ። ጉዳዩ አሳሳቢ ነው። በምድር የመጨረሻው ፍርድ ሰዓት አንድም መልአክ ሰብአዊ ዘርን መወከል አይችልም። ማንም መጽሐፉን መክፈት ስላልቻለ ዮሐንስ አለቀሰ። በዚያን ሰዓት ከምድር ከዳኑት መካከል አንዱ የሆነው፣ ከሽማግሌዎቹ አንዱ፣ ለዮሐንስ የማበረታቻ ቃላት ተናገረ። የእግዚአብሔር በግ የሆነው ኢየሱስ መጽሐፉን ለመክፈት የተገባው ሆኖ ተገኝቷል።

ዮሐንስ በራዕይ 5፡ 5 ላይ ለኃጢአት ችግር የመጨረሻውን መልስ ተመለከተ። በዚህ ቦታ ማንም ቢሆን ከእግዚአብሔር ዙፋን በሚተላለፈው የመጨረሻው ፍርድ መቆም የሚችልበትን ብቸኛ መንገድ ሽማግሌው ነቢይ ተመለከተ።

“ከሽማግሌዎቹም አንዱ፦ አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው ከሽማግሌዎቹም አንዱ፦ አታልቅስ፤ እነሆ፥ ከይሁዳ ነገድ የሆነው አንበሳ እርሱም የዳዊት ሥር መጽሐፉን ይዘረጋ ዘንድ… ድል ነሥቶአል አለኝ። በዙፋኑና በአራቱ እንስሶች መካከልም በሽማግሌዎችም መካከል እንደ ታረደ በግ ቆሞ አየሁ።” ቆሞ አየሁ።” (ራዕይ 5:5፣ 6)። ራዕይ 5:8–12ን ያንብቡ። ኢየሱስ የፍርድ መጽሐፉን ሊከፍትና እኛን ሊያድን የተገባ መሆኑን ለሚገልጸው መግለጫ ሰማይ በሞላ ምላሽ የሚሰጠው እንዴት ነው?



ሰብአዊ ዘርን በሙሉ ለማዳን ሕይወቱን መስዋዕት ያደረገው የእግዚአብሔር በግ፣ ኢየሱስ፣ የፍርዱን መጽሐፍ ወስዶ ይከፍታል። ሰማይ በሙሉ በምሥጋና ይሞላል። በሰይጣን ፈተናዎች ላይ የተቀዳጀው ድል፣ በቀራኒዮ መስቀል ላይ መሞቱ፣ ትንሣኤው፣ የሊቀ ክህነት አገልግሎቱ፣ በእምነት ለጸጋው ምላሽ ለመስጠት ለሚመርጡ ሁሉ ድነትን ይሰጣል። ለእግዚአብሔር ሕዝብ በሚያስደንቅ መልኩ የምሥራች ነው። ስለ ኃጢአት ግዛት መጨረሻ እና ስለ እግዚአብሔር ሕዝብ ነጻ መውጣት ይናገራል። ከዚህ የበለጠ ሊያደፋፍር የሚችል ነገር ይኖራል? በፍርድ ኢየሱስ ይቆምልናል። የእርሱ ፍጹም የሆነ የጽድቅ ሕይወት ይሸፍነናል። የእርሱ ጽድቅ አዲስ ሊያደርገን በውስጣችን ይሰራል። ጸጋው ይምረናል፣ ይለውጠናል፣ እግዚአብሔርን የሚመስል ሕይወት መኖር እንድንችል ኃይል ይሰጠናል።

መፍራት የለብንም። ኢየሱስ በፍርድ ለእኛ ይቆምልናል፣ የክፉ ኃይሎች ተሸንፈዋል። ለእግዚአብሔር ሕዝብ ይፈረድላቸዋል (ዳንኤል 7፡22)። የፍርዱ ዓላማ ምን ያህል ክፉ እንደሆንን ለማወቅ ሳይሆን እግዚአብሔር ምን ያህል መልካም እንደሆነ ለመግለጥ ነው። በድጋሚ በፍርድ ባለን ታላቅ ተስፋና ምትካችን በሆነው ኢየሱስ ላይ ትኩረት አድርጉ። ይህ ብቸኛው ተስፋችን የሆነው ለምንድር ነው?

ሚያዝያ 20
Apr 28

ተጨማሪ ሀሳብ


በመጨረሻዎቹ ቀናት፣ በፍርድ ጊዜና በዓለም ፍጻሜ የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚገኙበትን ሁኔታ በተመለከተ የትንቢት መንፈስ የሚሰጣቸውን ኃይለኛ ግንዛቤዎች ይመልከቱ።

”ብቸኛው ተስፋቸው የእግዚአብሔር ምህረት ነው፤ ብቸኛው መከላከያቸው ጸሎት ይሆናል። ኢያሱ በመልአኩ ፊት ይማጸን እንደነበረ ሁሉ ቅሬታዎቹም በተሰበረ ልብና ጽኑ እምነት ጠበቃቸው በሆነው በኢየሱስ አማካይነት ለምህረትና ነጻ መውጣት ይማጸናሉ። ሕይወታቸው በኃጢአት የተሞላ መሆኑን ሙሉ በሙሉ ስለሚያውቁ፣ ደካማነታቸውንና የተገቡ አለመሆናቸውን ስለሚመለከቱ፣ ራሳቸውን ሲመለከቱ ተስፋ ለመቁረጥ ዝግጁ ናቸው። ፈታኙ ኢያሱን ለመቋቋም ከጎኑ እንደቆመ ሁሉ እነርሱንም ለመክሰስ ከጎናቸው ይቆማል። በቆሸሹ ልብሶቻቸውና የባህርይ ጉድለታቸው ላይ ጣቱን ይቀስራል። አዳኛቸውን ያዋረዱትን ድክመታቸውንና የሞኝነት ተግባሮቻቸውን፣ አመስጋኝ ያለመሆን ኃጢአቶቻቸውን፣ ክርስቶስን አለመምሰላቸውን ያቀርባል።….የእግዚአብሔር ሕዝብ በብዙ መንገዶች እጅግ ስህተተኞች ናቸው። ሰይጣን እንዲፈጽሙአቸው ስለፈተናቸው ኃጢአቶች ትክክለኛ የሆነ እውቀት ስላለው እነዚህን ነገሮች እጅግ በተጋነነ መልኩ እንዲህ በማለት ያቀርባል፡- “እግዚአብሔር እኔንና መላእክቴን ከፊቱ በማባረር እኔ የፈጸምኳቸውን ኃጢአቶች የፈጸሙትን ይሸልማልን? ጌታ ሆይ፣ ፍትህ የምታሰፍን ከሆንክ ይህን ማድረግ አትችልም። ዙፋንህ በጽድቅና በፍርድ አይቆምም። ፍትህ እንዲፈረድባቸው ጥያቄ ታቀርባለች።’ ነገር ግን የክርስቶስ ተከታዮች ኃጢአት ቢሰሩም ክፉው እንዲቆጣጠራቸው ራሳቸውን አሳልፈው አልሰጡም። ኃጢአቶቻቸውን አስወግደው ራሳቸውን ዝቅ በማድረግና በመጸጸት ጌታን ፈልገዋል፤ ከዚህ የተነሣ መለኮታዊው ጠበቃ ስለ እነርሱ ይለምናል። በእነርሱ ምሥጋና-ቢስነት እጅግ የተበደለው፣ ኃጢአታቸውን የሚያውቀውና መናዘዛቸውንም የሚረዳው አምላክ እንዲህ በማለት ያውጃል፡- ‘ ሰይጣን ሆይ፣ እግዚአብሔር ይገስጽህ። ”ለእነዚህ ነፍሳት ሕይወቴን ሰጥቻለሁ። በእጆቼ መዳፍ ተቀርጸዋል።’ ”—Ellen G. White, Testimonies for the Church, vol. 5, pp. 473, 474.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.“የፍርዱ ሰዓት መድረሱን” ማወቅ የየዕለት ሕይወታችን ላይ ተጽእኖ የሚያሳድረው እንዴት ነው? አብዛኞቻችን ታማኝ ብንሆን ኖሮ ተጽእኖ አይፈጥርም ብለን ልንመልስ እንችላለን፣ አይደለም? እንዴት መለወጥ እንችላለን?

2. ፍርድ መጥፎ ዜና ሳይሆን መልካም ዜና የሚሆነው ለምንድር ነው? በክፍላችሁ በፍርድ ሰዓት ኢየሱስ ለእኛ ስለሚጫወተው ሚና ተወያዩ። የመዳን ተስፋ ልናገኝ የቻልነው እርሱ ለእኛ ባደረገልን ነገር ብቻ መሆኑን ማወቃችን ለእርሱ ታማኝ እንድንሆን ሊያነሳሳን የሚችለው እንዴት ነው?

3. ለዩኒቨርስ የእግዚአብሔርን ባህርይ በሚገልጠው የፍርድ ሀሳብ ላይ ትኩረት አድርጉ። ይህ ሀሳብ ከመላው የታላቁ ተጋድሎ ክስተት (ትዕይንት) ጋር በደንብ የሚገጥመው እንዴት ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL