የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሶስት ዓለም አቀፋዊ መልእክቶች



2ኛ ሩብ ዓመት 2023


መጋቢት 30 - ሚያዝያ 6

3ኛ ትምህርት

Apr 8 - 14




ዘላለማዊው ወንጌል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ራዕይ 14:6–12፤ 1ኛ ቆሮ. 15:1–4፤ ሮሜ 3:24–26፤ 1ኛ ጴጥ. 1:18–20፤ ማቴ. 28:19፣ 20፤ የሐዋ. 1:8።


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፡ “በምድርም ለሚኖሩ ለሕዝብም ለነገድም ለቋንቋም ለወገንም ሁሉ ይሰብክ ዘንድ የዘላለም ወንጌል ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ መካከል ሲበር አየሁ”። (ራዕይ 14:6)

በጥንታዊቷ እሥራኤል ዘመን፣ በዙሪያቸው የነበሩ አህዛብ ከእንጨትና ከድንጋይ የተሰሩ በርካታ ‹‹አማልክትን›› ሲያመልኩ በነበሩበት ወቅት፣ የእሥራኤላውያን ግልጽ፣ ተለይቶ የሚታወቅና ኃይለኛ የእምነት ቃላቸው የሚገኘው በዘዳግም 6፡ 4 ላይ ሲሆን “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን “እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው” የሚለው ነበር።

በዘመናት ሁሉ “ስማ” በሚለው የዕብራይስጥ ቃል ላይ የተመሰረተውን ሼማ መደጋገም (በመዝሙር መልክ ማዜም) ለአይሁዶች እንደ ሕዝብ አንድ ያደረጋቸውን እና እውነተኛ የሆነ አንድ አምላክን አምላኪዎች የመሆናቸውን ልዩ ማንነት የመጠበቅ ውሳኔያቸውን ያጠናከረላቸውን መንፈሳዊ ራዕይ ያስታውሳቸው ነበር።

ለሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች በራዕይ ምዕራፍ 14 ላይ ያሉ የሶስቱ መላእክት መልእክቶች ሼማ ናቸው። የእምነታችን መለያ አንቀጽ ወይም አረፍተ ነገሮች ናቸው። እኛ እንደ ሕዝብ ማን እንደሆንን ይገልጹና ለዓለም ያለንን ተልዕኮም ይገልጻሉ። በአጭሩ፣ ልዩ የሆነ ትንቢታዊ መለያችን በራዕይ 14፡ 6-12 ላይ የተዘረዘረ ሲሆን ለዓለም ወንጌልን የማወጅ ኃይለኛ ተነሳሽነት የምናገኘውም እዚህ ላይ ነው።

በዚህ ሳምንት ትምህርት ራዕይ 14፡6-12ን በጥልቀት ማጥናት እንጀምራለን፣ ነገር ግን ይህን የምናደርገው እግዚአብሔር ለልቦቻችን ሲናገር እየሰማን በጸጋ መነጽር ነው። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሚያዝያ 7 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

ሚያዝያ 1
Apr 09

ጸጋን የተሞላ የተስፋ መጽሐፍ


ብዙዎች የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ ስለሆነው የራዕይ መጽሐፍ ሲያስቡ ስለ እግዚአብሔር ጸጋ አያስቡም። የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ዘመን መልእክት ሲመለከቱ ብዙ ጊዜ ወደ ሀሳቦቻቸው የሚመጡት አስፈሪ የሆኑ አራዊት፣ ምስጢራዊ የሆኑ ምልክቶች እና ያልተለመዱ ምስሎች ናቸው። የራዕይ መጽሐፍ እንደ አለመታደል ሆኖ ብዙ ሰዎችን ቢያስፈራራም በጸጋና በተስፋ የተሞላ ስለሆነ ለብዙ ሰዎች ደግሞ መተማመኛ ይሰጣል። አስፈሪ በሆኑ አራዊትና ከፊት ለፊታቸው በሚጠብቃቸው ስደትና አስቸጋሪ ጊዜያቶች ማስጠንቀቂያዎች መካከል በእርሱ ማዳን ሀሴት የምናደርግበትን ምክንያቶች ይሰጠናል። ራዕይ 1:1–3 እና ራዕይ 14:6ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች አንድ ላይ ስለ ራዕይ መጽሐፍ ብቻ ሳይሆን ስለ “ዘላለማዊው ወንጌል” የሚነግሩን እንዴት ነው?



የራዕይ መጽሐፍ ሙሉ በሙሉ የሚናገረው ስለ ኢየሱስ ነው። እርሱ ለሕዝቡ የላከው መልእክት ሲሆን በተለየ ሁኔታ በመጨረሻ ዘመን ላለችው ቤተ ክርስቲያኑ ገጣሚ መልእክት ነው። በፍጻሜ ዘመን ተስፋ ስለምናደርገው ነገር የሚናገር በጸጋ የተሞላ መልእክት ነው። በመጽሐፉ ውስጥ ክርስቶስ እንደ ታረደ በግ የተገለጸ ሲሆን መጽሐፉን የሚያነቡ፣ የሚያስተውሉና በውስጡ የተገለጹ እውነቶችን በሥራ ላይ የሚያውሉ እንደሚባረኩ ቃል ተገብቶላቸዋል።

በራዕይ 1፡5፣ 6 ላይ በተገለጸው መሰረት ኢየሱስ “የወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ያጠበን፥ መንግሥትም ለአምላኩና ለአባቱም ካህናት እንድንሆን ያደረገን” ነው። በክርስቶስ ይቅርታ አግኝተናል። ጸጋ ያለፈውን ይቅር በማለት፣ ለአሁኑ ብቃት በመስጠት፣ ለወደፊቱ ተስፋ ይሰጣል። ይህ ማለት በክርስቶስ ከኃጢአት ቅጣትና ኃይል ነጻ የወጣን ሲሆን በቅርቡ ደግሞ ከኃጢአት መገኘት ነጻ እንወጣለን። ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ የሆነው የራዕይ መጽሐፍ መልእክት ነው። በመጀመሪያ “የዘላለም ወንጌል” ይዞ በሰማይ መካከል በፍጥነት በሚበር መልአክ የተወከለ አስቸኳይ (አንገብጋቢ) መልእክት ነው። ወንጌል? ድነት በክርስቶስ በማመን በጸጋ? የክርስቶስ የስርየት ሞት? እኛ ማድረግ ስለምንችለው ሳይሆን ክርስቶስ በእኛ ፋንታ ስላደረገልን የተሰጠን የዘላለም ሕይወት ተስፋ? ይህ ሁሉ በሶስቱ መላእክት መልእክት ጅምር ላይ ያለ ነገር ነው? በትክክል!

እንግዲያውስ ለተሰበርንና ስቃይ ውስጥ ላለን ለእኛ ተስፋና ቃል ኪዳን የሞለባቸው በጸጋ የተሞሉ መልእክቶች መሆናቸው የሚያስገርም ነገር አይደለም። በአውሬዎቹ ላይ እና ስለ መጨረሻው ቀናት በተሰጡ ማስጠንቀቂያዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ቀላል ቢሆንም፣ በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ በተገለጸው መሰረት፣ መካድ በማይቻል ደረጃ እጅግ ወሳኝ የሆነውን የራዕይን መልእክትና ክርስቶስ በእኛ ፋንታ ስለፈጸመው ራስን መስዋዕት የማድረግ ሞት ከእነዚህ ነገሮች ጋር ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ለማየት መማር የምንችለው እንዴት ነው?

ሚያዝያ 2
Apr 10


“ዘላለማዊው” ወንጌል

የሶስቱ መላእክት መልእክት ጅምር የሆነው ራዕይ 14፡6 በ“ዘላለማዊው” ወንጌል መጀመሩን ልብ ይበሉ። የወንጌልን ጥልቀት መረዳት ካቃተን የሶስቱን መላእክት መልእክት አጠቃላይ ሀሳብ እናጣለን። ወንጌሉን መረዳት ካቃተን በእግዚአብሔር የፍርዱ ሰዓት መልእክት ውስጥ ያሉ ነገሮችን ወይም የባቢሎንን ውድቀት ወይም የአውሬውን ምልክት በሙላት መረዳት በፍጹም አንችልም። 1ኛ ቆሮ. 15:1–4፣ ሮሜ3:24–26፣ እና ሮሜ 5:6–8ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ “የዘላለም ወንጌል” የቀረበው እንዴት ነው? በዚህ ቦታ የቀረበልን ትልቅ ተስፋ ምንድር ነው?



ወንጌል ክርስቶስ ስለእኛ ኃጢአት ስለመሞቱ፣ በግርማ ስለተሞላው ትንሳኤው፣ ሁልጊዜ ለእኛ ስላለው ፍቅርና ጭንቀት አስደናቂ የሆነ የምስራች ነው። በፈሰሰው ደሙና በትንሣኤው ኃይል በማመን ከኃጢአት ቅጣትና ኃይል ነጻ ወጥተናል። ክርስቶስ የሐዋርያው ጳውሎስን ሀሳቦች በሙሉ ከመያዙ የተነሣ የትምህርቶቹና የስብከቶቹ ሁሉ ማዕከል ነበር። የተሰቀለው ክርስቶስ ካለፈው ኃጢአቱ ኩነኔና የበደለኝነት ስሜት ነጻ አድርጎታል። ከሙታን የተነሣው ክርስቶስ ለአሁን የሚሆን ኃይል የሰጠው ሲሆን ተመልሶ የሚመጣው ክርስቶስ ደግሞ ለወደፊቱ ተስፋ ሰጥቶታል። በሮሜ መጽሐፍ ውስጥ በተገለጹ በእነዚህ መልእክቶች ውስጥ ያሉትን አራት ነጥቦች ልብ በሉ፡- 1. በጸጋ (በክርስቶስ ጸጋ) በነጻ ጸድቀናል። 2. ጸጋ የእግዚአብሔር ጽድቅ ማረጋገጫ ነው። 3. ጸጋ ኢየሱስን በእምነት የሚቀበሉትን ያጸድቃል። 4.እኛ ገና ኃጢአተኞች ሳለን እግዚአብሔር ፍቅሩን ገልጾልናል። የክርስቶስ ጸጋ የማይገባን ስጦታ ነው፤ በመልካም ሥራችን ጥረን ግረን ያገኘነው ነገር አይደለም። የጠፉ ኃጢአተኞች መሞት የነበረባቸውን አስጨናቂና የስቃይ ሞት ኢየሱስ ሞተ። አብ በኃጢአት ላይ የነበረውን ቁጣ ወይም ፍርድ ሙሉ በሙሉ ተቀበለ። እኛ ተቀባይነት እንድናገኝ እርሱ ተቀባይነት አጠ። የእርሱ የሆነውን ሕይወት እኛ እንድንኖር እርሱ የእኛን ሞት ሞተ። እንግዲያውስ ድነት በሕግ ሥራ ሳይሆን በእምነት መሆኑ ምን ያስደንቃል? ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባደረገልን ነገር ላይ ምን መጨመር እንችላለን? በደንብ ታስቦባቸው የተከናወኑና በመንፈስ ቅዱስ የተሞሉ ሥራዎቻችን እንኳን ክርስቶስ በመስቀል ላይ ባደረገልን ነገር ላይ ምን ሊጨምሩ ይችላሉ? ለምን “ዘላለማዊ” ወንጌል እንደተባለ ለማብራራት የሚረዳው ይህ እቅድ፣ የድነት እቅድ፣ የተዘጋጀው ከጊዜው ጅምር በፊት ነበር(2ኛ ጢሞ. 1:9፣ ቲቶ 1:2፣ ኤፌ. 1:4)። ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ምን ሊሆን እንደሚችል እግዚአብሔር ስላወቀ ችግሩ ሲከሰት መፍትሄ ለመስጠት የድነትን እቅድ አዘጋጀ።

ሚያዝያ 3
Apr 11


የጸጋ ታሪክ የሶስቱ መላእክት መልእክቶች የጸጋ ታሪክ ናቸው። ሊለካ የማይችለው የአዳኙ ፍቅር ታሪክ፣ ከእኛ አንዳችን ከምንጠፋ ገሃነምን መለማመድን እስከመምረጥ ድረስ እጅግ የሚወደን የኢየሱስ ታሪክ ነው። ገደብና ወሰን የሌለው፣ ሙሉ በሙሉ ማስተዋል የማይቻልና ከማስተዋል በላይ የሆነ፣ የማይሞትና ፍጻሜ የሌለው ዘላለማዊ የፍቅር ታሪክ ነው።

እግዚአብሔርን በድንገት የሚያገኘው ነገር በፍጹም የለም። ተለዋዋጭ ለሆኑ የሰብአዊ ዘር የምርጫዎች ነፋሳት ተገዥ አይደለም። አስቀድመን እንደተመለከትነው እኛን ከኃጢአት ግዛት ነጻ የማውጣት ዕቅድ ኃጢአት አስቀያሚ ራሱን ብቅ ካደረገ በኋላ የታሰበ ነገር አይደለም። አስፈሪ የሆነው የኃጢአት ቲያትር (ድራማ) እግዚአብሔርን ሳይዘጋጅ በድንገት አላገኘውም። ራዕይ 13:8 እና 1ኛ ጴጥ. 1:18–20ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ስለ ድነት ዕቅድ ምን ያስተምሩናል?



በራዕይ 14፡ 6 ላይ ያለው “ዘላለማዊ ወንጌል” የሚለው ሀረግ ስላለፈው፣ ስለ አሁኑና ስለመጪው ጊዜ የሚናገር ነው። እግዚአብሔር ሰብአዊ ዘርን ከግብረገብ የመምረጥ ችሎታ ጋር ሲፈጥረው የተሳሳተ ምርጫ ሊያደርጉ እንደሚችሉ ጠብቆ ነበር። ፍጥረቶቹ የመምረጥ ችሎታ እስካላቸው ድረስ በፍቅር ተፈጥሮው ላይ የማመጽ ችሎታም ነበራቸው። ይህ እንዳይሆን መከላከል ይቻል የነበረው ብቸኛው መንገድ በአንድ ዓለም አቀፋዊ መለኮታዊ ዕቅድ ቁጥጥር ሥር ያሉ ሮቦት የሆኑ ፍጡራንን በመፍጠር ነበር። በግድ እንዲታዘዙ (እንዲገዙ) ማድረግ የእግዚአብሔር ባህርይ ተቃራኒ ነው። ፍቅር ምርጫ የሚሻ ሲሆን ፍጡራን የምርጫ ኃይል እስከተሰጣቸው ድረስ የተሳሳተ ምርጫ የማድረግ ዕድል አለ። ስለዚህ የድነት ዕቅድ በእግዚአብሔር አእምሮ ውስጥ የተፀነሰው የመጀመሪያዎቹ ወላጆቻችን በኤደን ገነት ከማመጻቸው በፊት ነበር። “የድነታችን ዕቅድ ከአዳም ውድቀት በኋላ ታስቦ የተነደፈ ዕቅድ አይደለም። ‘ከዘላለም ዘመንም ጀምሮ ተሰውሮ የነበረው ምስጢር’ መገለጥ ነው (ሮሜ 16:25)። ከዘላለም ጀምሮ የእግዚአብሔር ዙፋን መሰረት የነበሩ መርሆዎች መገለጥ ነበር።”—Ellen G. White, The Desire of Ages, p. 22. “ዘላለማዊው ወንጌል” ስለ አላፊ ጊዜና ስለ አሁን ብቻ የሚናገር ሳይሆን በተስፋ የተሞላ የወደፊት ተስፋ መሰረትም ነው። ከእኛ ጋር ለዘላለም ለመሆን ልቡ ከፍተኛ ምኞት ካለው ጋር ስለሚኖረን ሕያው ዘላለማዊነት ይናገራል። ኤፌሶን 1:4ን ያንብቡ። ድነት ለማግኘት “ከዓለም መሰረት” በፊት በክርስቶስ “ተመርጣችኋል” ማለት ምን ማለት እንደሆነ ያስቡ። ይህ እውነት እጅግ አበራታች የሚሆንልዎ ለምንድር ነው?

ሚያዝያ 4
Apr 12

በዓለም ሁሉ


ራዕይ 14:6ን በድጋሚ ያንብቡ። የዘላለም ወንጌል መታወጅ ያለበት እስከ ምን ድረስ ነው? የዚህ ጥያቄ መልስ ለእኛ፣ ለተልዕኮአችንና እንደ ቤተ ክርስቲያን ለጥሪያችን አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?



`ከሶስቱ መላእክት መልእክት መካከል አንገብጋቢና የመጨረሻው ዘመን መልእክት የሆነው የመጀመሪያው መልአክ መልእክት እንደሚገልጸው “ዘላለማዊው ወንጌል” ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋና ለወገን ሁሉ መታወጅ አለበት። እዚህ ላይ የተሰጠው ተልዕኮ እጅግ ደማቅ፣ እጅግ ትልቅ፣ እጅግ ግዙፍና ሁሉን አቀፍ ስለሆነ የሰዎችን ጊዜና ትኩረት የሚይዝ ነው። በተሻለ ሁኔታ ጥረት ማድረግንና ሙሉ በሙሉ መሰጠትን ይሻል። በራሳችን ፍላጎት ከመጠመድ ይልቅ ለክርስቶስ አገልግሎት ውስጣዊ ፍላጎት እንዲኖረን ያደርጋል። ከራሳችን የሚበልጥ ነገር፣ መገለጥን በመስጠት ከራሳችን አእምሮዎች ጠባብ አጥር በማውጣት ወደ ትልቅ ራዕይ ይመራናል። ማቴ. 28:19፣ 20ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች ከመጀመሪያው መልአክ መልእክት ጋር የሚገናኙት እንዴት ነው?



ፖል ዴቪድ ትርፕ የተባለ ሰው ኤ ኩዌስት ፎር ሞር በሚለው መጽሐፉ ውስጥ ከራስህ ለሚበልጥ ነገር መኖር በሚለው ርዕስ ሥር እያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ከራሱ የሚበልጥ ነገር አካል ለመሆን ያለውን ሥነ-ልቦናዊ ፍላጎት እንዲህ በማለት ይገልጻል፡- “ሰብአዊ ፍጡራን ከራሳቸው ሕይወት የሚበልጥ ነገር አካል ለመሆን ተፈጥረዋል። ኃጢአት ሕይወታችን ወደ ራሳችን ሕይወት መጠን እንዲቀንስ አድርጎአል። የክርስቶስ ጸጋ የተሰጠው በራስ ላይ ከሚያተኩር የራሳችን ትንሽ መንግስት አጥፊ ገደብ ያድነንና ለዘላለማዊ ዓላማዎችና የእግዚአብሔር መንግስት አርኪ የሆኑ ደስታዎች እንድንኖር ነጻ ያወጣናል።”

ማንኛውም ሰብአዊ ፍጡር በራሱ ሊፈጽም ከሚችለው እጅግ ትልቅና ግዙፍ የሆነ ሥራ ለመስራት በእግዚአብሔር በራሱ ፈቃድ የተነሳ መለኮታዊ እንቅስቃሴ አካል የመሆንን ያህል የሚያነሳሳ፣ የሚያረካና ዋጋ ያለው ምንም ነገር የለም። በራዕይ 14 ላይ የተገለጸውና በእግዚአብሔር የተሰጠው ተልዕኮ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ ከሰጣቸው ተልዕኮዎች ሁሉ ትልቁ ተልዕኮ ነው። ኢየሱስ ከመመለሱ በፊት ከማስተዋል በላይ የሆነውን የእግዚአብሔርን ፍቅር መግለጥ እንድንችል ራሳችንን ለሰማያዊው ግዙፍ ሥራ እንድንሰጥ የቀረበ ልባዊ ተማጽኖ ነው። ከራስዎ በላይ በሆነ ነገር ላይ ስለመሳተፍ የራስዎ ልምምድ ምንድር ነው? ያ ልምምድዎ የዛሬው ሰንበት ትምህርት የሚያነሳውን ነጥብ እንዲረዱ እንዴት ረዳዎት? በዩኒቨርስ ውስጥ ዘላለማዊ ለውጥ ማምጣት እንዲችሉ የዓለማት ፈጣሪ እርስዎን ከመጠቀም የሚበልጥ ምን ነገር ይኖራል?

ሚያዝያ 5
Apr 13

የተልዕኮ እንቅስቃሴ


ቀደምት አድቬንቲስቶች ጥሩ እይታ ባለው ጥልቅ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት አማካይነት ስለ እነዚህ መልእክቶች ወሳኝነት እያደገ የሚሄድ መረዳት ነበራቸው። እግዚአብሔር ዓለምን ለክርስቶስ ዳግም ምጻት ለማዘጋጀት ለዚህ ትውልድ የተዘጋጀ፣ ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ፣ ለወገን ሁሉ መታወጅ ያለበት አንገብጋቢና የፍጻሜ ዘመን መልእክት እንዳለው ተሰምቶአቸው ነበር። የሶስቱ መላእክት መልእክቶች የአድቬንቲስት ሚስዮኖች ከጅምር ጀምሮ ለተልዕኮአቸው እንዲነቃቁ ምክንያቶች ነበሩ።

እ.አ.አ 1874 ዓ.ም ጄኔራል ኮንፍራስ የመጀመሪያዎቹን ሚስዮናውያን ወደ እውሮፓ ላከ። ኤለን ጂ ኋይት ጆን አንድሪውስ የተባለውን ሚስዮናዊ “በመካከላችን ካሉ ሰዎች ሁሉ የተሻለ አቅም ያለው ሰው” በማለት ጠቅሳለች። አንድሪውስ ቢያንስ ሰባት ቋንቋዎችን የሚናገር፣ አዲስ ኪዳንን በአእምሮው የሚደግምና ብሉይ ኪዳንንም በአብዛኛው የሚያውቅ ሰው ነበር። ብሩህ አእምሮ የነበረው ምሁር፣ የበርካታ መጻሕፍት ጸሐፊ፣ ኃይለኛ ሰባኪና ብቃት ያለው የስነ- መለኮት ምሁር ነበር።

እንደዚህ ዓይነቱን ሰው እጅግ ጥቂት አማኞች ወዳሉበት ቦታ መላክ ለምን አስፈለገ? አለኝ የምትለውን፣ “ከሁሉ የተሻለ ችሎታ ያለውን” ሰው ወደማይታወቅ የሚስዮን ፊልድ መላክ ለምን አስፈለገ? እርሱስ ለመሄድ ለምን ፈቃደኛ ሆነ? ባለቤቱ ከጥቂት ዓመታት በፊት ሞተበታለች። ቤተሰቡንና ጓደኞቹን አሜሪካ ትቶ ለክርስቶስ ሥራ አደጋን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ በመሆን ከሁለት ልጆቹ ጋር ወደማይታወቅ አገር በመርከብ ለመሄድ ለምን ፈቃደኛ ይሆናል?

ለዚህ የሚሆን አንድ ምክንያት ብቻ አለ። ኢየሱስ በቅርብ እንደሚመጣ ስላመነ የመጨረሻው ዘመን የእውነት መልእክት ወደ ዓለም ሁሉ መድረስ እንዳለበት አመነ።

ታሪካችንን ስንመለከት የእግዚአብሔርን የመጨረሻው ዘመን መልእክት ለማወጅ ብሩህ አእምሮ ያላቸውና ከሁሉ የተሻሉ ሰዎቻችን ወደ ምድር ዳርቻዎች ተጉዘዋል። እነዚህ ሰዎች መምህራን፣ የሕክምና ባለሙያዎች፣ ቀሳውስት፣ ገበሬዎች፣ መካኒኮች፣ አናፂዎችና ሁሉንም ዓይነት የእጅ ሙያ የሚያውቁ ሰዎች ነበሩ። ጥቂቶቹ የድርጅቱ ተቀጣሪዎች የነበሩ ሲሆን ብዙዎቹ ተቀጣሪዎች አልነበሩም። ኢየሱስ በቶሎ እንደሚመጣ ያመኑ ፈቃደኛ አገልጋዮች ነበሩ። ራዕይ 14:6፣ የሐዋ. 1:8 እና ማቴ 24:14ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ምን ተመሳሳይነት ማየት ቻሉ?



የዘላለምን ወንጌል መስበክ መልክዓ-ምድራዊ ወሰኖችን የሚሻገር ነው። የምድርን ጥግ ዘልቆ የሚሄድ ነው። ልዩ ልዩ ቋንቋና ባህል ወዳላቸው ሰዎች ይደርሳል። በመጨረሻም በመላው ዓለም ላይ ተጽእኖ ይፈጥራል። እስካሁን ድረስ በተባበሩት መንግስታት እውቅና ከተሰጣቸው ከ235 አገሮች ውስጥ መልእክታችን ወደ 210 አገሮች መድረሱን ማወቅ ምንኛ ይመስጣል። የሶስቱን መላእክት መልእክት “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ፣ ለወገን” ሁሉ ለማሰራጨት በመርዳት ረገድ እርስዎ ምን ሚና መጫዎት ይችላሉ? እንዴትስ በተሻለ ሁኔታ ሚናዎን መወጣት ይችላሉ?

ሚያዝያ 6
Apr 14

ተጨማሪ ሀሳብ


ከራሳችን እና ዝቅተኛ ከሆነው፣ አጭር ዕድሜ ካለውና ብዙ ጊዜ ከተበላሸ፣ ከተጎዳና ተስፋ ከሚያስቆርጥ ሕይወት የሚበልጥ ነገር አካል ለመሆን ስላለን ፍላጎት በሚገልጸው የረቡዕ ትምህርት ላይ የበለጠ ትኩረት ያድርጉ። (በሕይወት ዘመኑ ከእነዚህ ነገሮች አንዳንዶቹ የሌለበት ሰው ማን ነው?)። ይህ ፍላጎት ትልቅ ትርጉም አለው። አካላችንን ስንመለከት በአእምሮአችን ዙሪያ ጥቂት የስጋ ጥርቅም ያለን ከመሆን ያለፈ እኛ ምንድር ነን? አካላዊ አወቃቀራችንን ስንመለከት አንድ ባልዲ ከሚያክል ጥብስ ዶሮ ጋር የሚጠጋጋ፣ ካርቦንን መሰረት ያደረጉ የተወሰኑ ፓውንዶች ተፈጥሮአዊ ነገር ከመሆን ያለፍን አይደለንም።

እነዚህ ትናንሽ ራስ-አገዝ የሥጋ ጥርቅሞች ዙሪያቸውን ከበው ካሉ ገደብ የለሽ ነገሮች ጋር ሲነጻጸሩ ምን ማለት ነው? በዙሪያችንና ከእኛ ባሻገር እጅግ ብዙ ነገሮች እያሉ ለራስዎ ብቻ እና ከራስዎ ለማይበልጥ ነገር መኖር ማለት የቤትዎን ግድግዳ ዘልቆ እንቅስቃሴው በሚሰማዎ ታላቅ ከተማ መካከል ብቸኛ በሆነ ቦታ ዕድሜ ልክ ተዘግተው እንደመኖር ነው። በኢየሱስ የተሰጠንን የዘላለም ሕይወት ተስፋ እያወጅን ከመኖር ያለፈ ለየትኛው የሚበልጥ፣ ቀልብ የሚስብ፣ እጅግ የከበረ እና ውጤት የሚያስከትል ነገር ልንኖርለት እንችላለን?

“የእግዚአብሔር ባሪያዎች በቅዱስ መቀደስ ፊታቸው በርቶ ከሰማይ የተላከውን መልእክት ለማወጅ ከቦታ ወደ ቦታ በፍጥነት ይንቀሳቀሳሉ። በሺሆች በሚቆጠሩ ድምፆች በምድር ሁሉ ማስጠንቀቂያው ይሰጣል። ተዓምራቶች ይፈጸማሉ፣ የታመሙት ይፈወሳሉ፣ አማኞችን ድንቆችና ተዓምራቶች ይከተሉአቸዋል። ሰይጣንም ከሰማይ ወደ ምድር እሳትን እንኳን በማውረድ በውሸት ድንቆችን ይሰራል (ራዕይ 13፡13)። ስለሆነም የምድር ኗሪዎች አቋማቸውን እንዲለዩ ይገደዳሉ።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 612.


የመወያያ ጥያቄዎች



1.“ብዙዎች የጽድቅ በእምነት መልእክት የሶስተኛው መልአክ መልእክት ነው ወይ? በማለት በደብዳቤ ጠይቀውኛል፤ እኔም በእርግጠኝነት የሶስተኛው መልአክ መልእክት ነው በማለት መልሼላቸዋለሁ።”—Ellen G. White, The Advent Review and Sabbath Herald, April 1, 1890. ጽድቅ በእምነት ከሶስቱ መላእክት መልእክት ጋር ምን ዝምድና (ግንኙነት) አለው?

2. “ዘላለማዊ ወንጌል” በሚለው ሀረግ ላይ የበለጠ ትኩረት ያድርጉ። ወንጌልን በተመለከተ ዘላለማዊው ነገር ምንድር ነው?

3. የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች በዓለም ውስጥ ባሉ ብዙ አገሮች ውስጥ መገኘታቸው ምን ማለት ነው? እስካሁን ድረስ እግዚአብሔር ጥረቶቻችንን ስለመባረኩ ምን ይነግረናል? በዚህ ሁኔታ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያንዎ፣ የአጥቢያ ሰንበት ትምህርት ክፍልዎም ቢሆን፣ “ሥራውን በመጨረስ” ሂደት ውስጥ እንዴት ትልቅ ሚና መጫወት ይችላል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL