የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሶስት ዓለም አቀፋዊ መልእክቶች



2ኛ ሩብ ዓመት 2023


መጋቢት 23 - 29

2ኛ ትምህርት

Apr 1 - 7




መዳረሻን የሚወስን ቅጽበት



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ማቴ. 24:14፣ ራዕይ 14:14-20፣ ማቴ. 16:27፣ የሐዋ. ሥራ 1:9—11፣ ማር. 4:26—29፣ ራዕይ 16:1።


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ፦ “አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል፥ በራሱም ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው። ሌላ መልአክም ከመቅደሱ ወጥቶ በደመናው ላይ ለተቀመጠው፦ የማጨድ ሰዓት ስለ ደረሰ ማጭድህን ስደድና እጨድ፥ የምድሪቱ መከር ጠውልጓልና ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ” (ራዕይ 14:14፣ 15)።

እግዚአብሔር ሕዝቡ በጊዜው መስማት ያለባቸውን እውነቶች ሁልጊዜ ሲናገራቸው ነበር፤ ስለ ውኃ ጥፋት ከተሰጠው ማስጠንቀቅ ጀምሮ (ዘፍጥረት 6፡7) ስለ ክርስቶስ የመጀመሪያው ምጻት (ዳንኤል 9፡ 24- 27)፣ ስለ ቅድመ-ዳግም ምጻት ፍርድ (ዳንኤል 7፡9፣ 10፤ 8፡14) እና ከክርስቶስ ዳግም ምጻት በፊት ስለሚፈጸሙ የመጨረሻዎቹ ክስተቶች (ራዕይ 12-14) እግዚአብሔር ተናግሮናል። በዚህ የሰው ዘር ታሪክ በመጨረሻዎቹ ቀናት የወቅቱን ጥያቄ እንዲመልስ የታቀደን ልዩ መልእክት ለዓለምና ለሕዝቡ ልኳል። ይህ መልእክት ለዓለም መተላለፍ ያለበትን አንገብጋቢ የመጨረሻው ዘመን መልእክት ይዘው በሰማይ መካከል በሚበሩ በሶስት መላእክት በሚነገር ምሳሌያዊ መልክ ገልጾታል።

የሶስቱ መላእክት መልእክት በራሳችን ጽድቅ ከመታመን ይልቅ ሊያጸድቀን፣ ሊቀድሰንና በመጨረሻም ሊያከብረን በሚችል በኢየሱስ ጽድቅ እንድንታመን የቀረበ ጥሪ፣ የኢየሱስ የመጨረሻው የምህረት መልእክት ነው።

ሁልጊዜ ማድረግ እንዳለብን ሁሉ ለእርሱ ራሳችንን አሳልፈን ለመስጠትና ለመታዘዝ ክርስቶስን መምረጥ ያለብን ሲሆን አሁን የምንመርጣቸው ምርጫዎች ከፊታችን ባላው የመጨረሻው ችግር ወቅት በምናደርጋቸው ምርጫዎች ላይ ተጽእኖ ይኖራቸዋል። ስለዚህ አሁን የመዘጋጀት ጊዜ ነው። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመጋቢት 30 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።

መጋቢት 24
Apr 02

ዘላለማዊ ምርጫዎች


ራዕይ 14 ወደ ስድስት ሺህ ዓመታት ለሚያህል ጊዜ በኃጢአትና በክፋት ተሞልቶ ለወደቀውና አመጸኛው ዓለም የኢየሱስ የመጨረሻው መልእክት ነው። በዚህች ምድር ላይ ያለው እያንዳንዱ ሰው ኢየሱስን በመደገፍ ወይም በመቃወም የመጨረሻውን ሊቀለበስ የማይችል ውሳኔ የሚያደርግበት ቀን ይመጣል። ከኃጢአት ኩነኔና ኃጢአት በሕይወታችን ላይ ካለው ቁጥጥር ነጻ ስለሚያደርገን ስለ ክርስቶስ ጽድቅ የሚገልጸው የራዕይ መልእክት በምድር ሁሉ በተደጋጋሚ ያስተጋባል። ማቴ. 24:14ን ያንቡበና ከራዕይ 14፡6 ጋር ያነጻጽሩ። ኢየሱስ ዳግም ከመምጣቱ በፊት ስለሚከናወነው ዓለም አቀፍ የወንጌል ሥርጭት ለደቀ መዛሙርቱ የሰጠው ተስፋ ምን ነበር?



በማቴዎስ 24፡14 ላይ “ይህ የመንግስት ወንጌል በዓለም ሁሉ ይሰበካል” ያለው የኢየሱስ ተስፋ ፍጻሜ የሚያገኘው በራዕይ 14፡6 ላይ በተሰጠውና ወንጌል “ለሕዝብ፣ ለነገድ፣ ለቋንቋ፣ ለወገን ሁሉ” ይታወጃል በሚለው የኢየሱስ የመጨረሻው መልእክት ነው። በራዕይ ምዕራፍ 22 ላይ ኢየሱስ ሶስት ጊዜ እነሆ በቶሎ እመጣለሁ ብሏል(ራዕይ 22:7፣ 12፣ 20)። ጌታችን በቶሎ ስለ መምጣቱ በተናገረው አውድ የሚከተለውን ሀሳብ ጨምሮበታል፡- “ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ዓመፀኛው ወደ ፊት ያምፅ፥ ርኵሱም ወደ ፊት ይርከስ፥ ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ” ጻድቁም ወደ ፊት ጽድቅ ያድርግ፥ ቅዱሱም ወደፊት ይቀደስ አለ” (ራዕይ 22:11)። የራዕይ መጽሐፍ እያንዳንዱ ሰው ክርስቶስን በመደገፍ ወይም በመቃወም ውሳኔ ለማድረግ ወደሚመራበት ወደ አንድ አስደናቂ ፍጻሜ ይመራናል።

በየቀኑ “ጥቃቅን ነገሮች” ተብለው በሚጠሩ ነገሮች መካከል በምናደርገው ምርጫችን እንኳን ኢየሱስን በመደገፍ ወይም በመቃወም ውሳኔ እያደረግን ነን። አሁን በሕይወታቸው ሁልጊዜ የተሳሳተ ምርጫ የሚያደርጉ ሰዎች በመጨረሻው አስጨናቂ ጊዜ፣ በተለይም የክፉው ኃይል በሙሉ ሊቃወማቸው ተሰልፎ ሳለ፣ በድንገት ከኢየሱስ ወገን ይቆማሉ የሚለው ሀሳብ እውነት ሊሆን የሚችል አይደለም። አሁን፣ ዛሬ፣ በየቀኑ ለክርስቶስና ለትዕዛዛቱ ታማኝ ለመሆን መምረጥ አለብን። “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሔር ፍቅር ይህ ነውና” (1ኛ ዮሐ 5:3)። ኤለን ጂ ኋይት እንዳለችው “ኢየሱስ ባህርይን የሚለውጠው ሲመጣ አይደለም። የለውጥ ሥራ መሰራት ያለበት አሁን ነው። በየዕለቱ የምንኖረው ኑሮአችንመዳረሻችንን እየወሰነ ነው።”—Last Day Events, p. 295. እግዚአብሔር ባህርያችንን የሚቀርጸው እንዴት ነው? እኛ በጸጋ ማደግ እንድንችል ለማድረግ ምን ዘዴዎችን ይጠቀማል? መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስን እንድንመስል እንዲለውጠን ሙሉ በሙሉ ለመፍቀድ ምን ማድረግ እንችላለን?

መጋቢት 25
Apr 03

የሰው ልጅ ይመለሳል


እግዚአብሔር ለሕዝቡና ለዓለም ያለውን መልእክት በተመለከተ ራዕይ 14 ቁልፍ ጥቅሶችን ይዟል። የዚህ ሁሉ ማዕከላዊው ነገር የኢየሱስ መመለስ፣ “የሰው ልጅም በኃይል ቀኝ ሲቀመጥ በሰማይም ደመና ሲመጣ ታያላችሁ” (ማርቆስ14:62)የሚለው ተስፋ ፍጻሜ ማግኘት ነው። ራዕይ 14:14ን ያንብቡ። ኢየሱስ ወደ ምድር ሲመለስ እርሱ ያለበትን ሁኔታ ለመግለጽ ጥቅም ላይ የዋለው ማዕረግ ምንድር ነው? ዮሐንስ ይህን ማዕረግ የተጠቀመው ለምን ይመስሎታል?



ኢየሱስ ራሱን ለመግለጽ “የሰው ልጅ” የሚለውን ቃል በወንጌላት ውስጥ 82 ጊዜ ተጠቅሟል። እጅግ ከሚወዳቸው ማዕረጎቹ አንዱ ነበር። ራሱን ከእኛ እንደ አንዱ አድርጎ ለማሳየት የተጠቀመበት የፍቅር መግለጫ ቃል ነው። እኛን የሚያስተውለን፣፣ ፈተናዎቻችንን የተለማመደ እና በምናልፋቸው ፈተናዎች ውስጥ ያለፈ አዳኝ ነው። ወደ ቤታችን ሊወሰደን የሚመለስ “የሰው ልጅ” ነው። የሚመጣልን ኢየሱስ ያው በመካከላችን የኖረው ኢየሱስ ነው። እኛን ለማዳን ብቁ የሚያደርገው ነገር ቢኖር ከእኛ እንደ አንዱ ሆኖ የሰይጣንን የፈተና ወላፈን (ቁጣ) ሙሉ በሙሉ መጋፈጡና በፈተናዎቹ አሸናፊ ሆኖ መገኘቱ ነው። በማቴዎስ ውስጥ ስለ ኢየሱስ፣ ስለ ሰው ልጅ፣ ከተነገሩ ከሚከተሉት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ምን እንማራለን? ማቴ. 16:27



ማቴ. 24:27፣ 30



ማቴ. 25:31፣ 32



በእነዚህ ንባቦች ውስጥ አንዳንድ ነገሮችን ልብ በሉ:- (1) ኢየሱስ፣ የሰው ልጅ ከመላእክቱ ጋር በክብር ይመጣል። (2) በጎችን ከፍየሎች ይለያል (በመሰረታዊነት የፍርድ ሥራ ነው)። (3) የሕዝቦችና የሁሉም ሰብአዊ ዘር መዳረሻ ይወሰናል። “የሰው ልጅ” ስለሚለው አባባልና ስለ ክርስቶስ ሰብአዊነት ምን እንደሚል አስቡ። አምላክ ቢሆንም ከእኛ እንደ አንዱ፣ ልክ እንደ እኛ ሆነ፤ ነገር ግን ከእኛ ልዩ የሚያደርገው ነገር በፍጹም ኃጢአት አለመስራቱ ነበር። ይህ ሁኔታ (1) እግዚአብሔር ለእኛ ያለውን ፍቅር በማወቃችን (2) መከራዎቻችንን በመጋራት ድል እንደሚሰጠን በመረዳታችን እንዴት ያለ አስደናቂ ተስፋ ይሰጠናል?

መጋቢት 26
Apr 04

ሰማያዊው ፍርድ


ራዕይ 14:14 እና የሐዋ 1:9—11ን ያንብቡ። ምን ተመሳሳይ ነገሮችን አገኙ?



ዮሐንስ “አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ “አየሁም፥ እነሆም ነጭ ደመና፥ በደመናውም ላይ የሰውን ልጅ የሚመስል ተቀምጦአል” የሚመስል ተቀምጦአል” (ራዕይ 14:14) ይላል። ኢየሱስ ወደ ሰማይ ባረገ ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ወደ ላይ አሻቅበው እየተመለከቱ ሳለ የነበረውን ሁኔታ በሐዋ. 1፡9 ላይ ሉቃስ እንዲህ በማለት ጽፎታል፡- “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ “እነርሱ እያዩት ከፍ ከፍ አለ፤ ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” ደመናም ከዓይናቸው ሰውራ ተቀበለችው።” ኢየሱስ በመላእክት ደመና ታጅቦ ወደ ሰማይ እንዳረገ ሁሉ በመላእክት ደመና ታጅቦ ይመለሳል። መላእክቱ በመደነቅ ተሞልተው ለነበሩት ደቀ መዛሙርት በሐዋርያት ሥራ 1፡11 ላይ እንዲህ ብለው ነበር፡- “ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ “ይህ ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ ወደ ሰማይ ሲሄድ እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” እንዳያችሁት፥ እንዲሁ ይመጣል አሉአቸው።” በዚህ ንባብ ውስጥ ግልጽ ያልሆነ መለኮታዊ እውነት አለ። ይህ “ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ፣” “ከእናንተ ወደ ሰማይ የወጣው ኢየሱስ፣” “የሰው ልጅ፣” በናዝሬት አቧራማ መንገዶች ላይ የተጓዘው፣ በተጨናነቁ የኢየሩሳሌም መንገዶች ላይ ያገለገለው፣ በኢየሩሳሌም መንደሮች ህመምተኞችን የፈወሰው እና በሳር በተሸፈኑ የገሊላ ኮረብታዎች ላይ የሰበከው ኢየሱስ ዳግም ይመጣል። የሰው ልጅ በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይም ከፍርድ ጋር በተገናኘ ሁኔታ ተጠቅሷል። ዳንኤል 7:9፣ 10፣ 13፣ 14ን ያንብቡ።- ዳንኤል እንደ ፍርድ ባለ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ኢየሱስን “የሰው ልጅ” ብሎ የጠራው ለምንድር ነው። እስካሁን በተመለከትነው መሰረት “የሰው ልጅ” ፍርድን በተመለከተ ይህን ያህል ማዕከላዊ ቦታ መያዙን በማወቃችን ሊያጽናናን የሚገባ ምን አለ?



በዳንኤል 7:9፣10 ላይ ዳንኤል እልፍ አእላፋት መላእክት በዙፋኑ ዙሪያ ተሰብስበው ሰማያዊው ጉባኤ ተሰይሞ ተመለከተ። ፍርድ ተጀመረ፣ የሕይወታችን ታሪክ የተመዘገበባቸው ሰማያዊ መጻሕፍት በዩኒቨርስ ፊት ተከፈቱ። በዳንኤል 7፡ 13፣ 14 ላይ የሰው ልጅ ወደ ጥንታዌ ጥንቱ (በእድሜ ወደ ሸመገለው)፣ ወደ አብ በመቅረብ ዘላለማዊውን መንግስት ወሰደ። ፍርዱ አብ፣ ወልድና መንፈስ ቅዱስ ሰብአዊ ዘርን ለማዳን የሚቻለውን ነገር ሁሉ ማድረጋቸውን ያሳያል። ይህ ፍርድ ቅዱሳንን ነጻ የሚያወጣ ብቻ ሳይሆን ከሰይጣን ክስ በተቃራኒ የእግዚአብሔርን ባህርይም ይገልጣል (ኢዮብ 1-2፤ መዝሙር 51፡1-4)። ሕይወትዎ በሙሉ በእግዚአብሔር በጥንቃቄ እንደሚመረመር ስለማወቅዎ እውነታ ያስቡ። ይህ በሚሆንበት ጊዜ ያለዎት ብቸኛው ተስፋ ምንድር ነው? (ሮሜ. 8:1ን ይመልከቱ)።

መጋቢት 27
Apr 05

የአሸናፊው (የድል አድራጊው) ዘውድ


ዮሐንስ ኢየሱስን “የሰው ልጅ ፣በራሱ ላይ የወርቅ አክሊል በእጁም ስለታም ማጭድ ነበረው” በማለት ይገልጸዋል (ራዕይ 14:14)። “ዘውድ” ተብሎ የተተረጎመው የመጀመሪያው ቃል እስቴፋኖስ ይባላል። የአሸናፊ ዘውድ ማለት ነው። አንድ አትሌት ወሳኝ በሆነ ውድድር ላይ አሸናፊ ሲሆን እስቴፋኖስ፣ የክብር፣ የግርማ ወይም የድል አክሊል ይሰጠዋል።

ኢየሱስ በአንድ ወቅት የውርደትና የፌዝ ምልክት የሆነውን የእሾክ አክሊል ጭኗል። በአንድ ወቅት በሰዎች ዘንድ ተንቋል ተጠልቷልም። ተነቅፏል፣ ተቀልዶበታል፣ ምራቅ ተተፍቶበታል፣ በበትር ተመትቷል፣ በጅራፍ ተገርፏል። ነገር ግን አሁን የክብር አክሊል በመጫን የነገሥታት ንጉሥና የጌቶች ጌታ ሆኖ ዳግም ይመጣል። ራዕይ 14:15 እና ማርቆስ 4:26—29ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች መካከል ያለው መመሳሰል ምንድር ነው? ሁለቱም እየተናገሩ ያሉት ስለምንድር ነው?



መልአኩ በቤተ መቅደስ ክብር ከእግዚአብሔር ፊት መጣ። እግዚአብሔር መልአኩን በመመልከት እንዲህ አለው፡- “ጊዜው ደርሷል። መከሩ በስሏል።” መልአኩ ከቤተ መቅደስ ወደ ኢየሱስ በመብረር በትልቅ ድምጽ:- “አሁን ጊዜው ደርሷል። መከሩ ለመታጨድ ተዘጋጅቷል” በማለት ተናገረ። ሂድና ልጆችህን ፈልገህ ወደ ቤት አምጣቸው።

ኢየሱስ በአዲስ ኪዳን ውስጥ በተደጋጋሚ የግብርና መግለጫዎችን ይጠቀም ነበር። ከአንድ አጋጣሚ በላይ የወንጌል ዘር በሕዝቡ ሕይወት ማደጉን ለመግለጽ የመከርን መድረስ ምልክት ተጠቅሟል።

“የዘር መብቀል የመንፈሳዊ ሕይወት ጅምርን የሚወክል ሲሆን የተክሉ እድገት ደግሞ የክርስትና እድገት ውብ ስዕል ነው። በተፈጥሮ ውስጥ እንደሆነ ሁሉ በጸጋ ውስጥም የሚሆነው ተመሳሳይ ነገር ነው። ሕይወት ያለ እድገት ሊኖር አይችልም። ተክሉ ማደግ ወይም መሞት አለበት። እድገቱ ሳይታይ በጸጥታ እንደሚሆን ሁሉ የክርስትና ሕይወትም እንዲሁ ነው። በእያንዳንዱ የእድገት ደረጃ ሕይወታችን ፍጹም ሊሆን ይችላል፤ ሆኖም እግዚአብሔር ለእኛ ያለው እቅድ ከተፈጸመ የማያቋርጥ እድገት (ለውጥ) ይኖራል። ቅድስና የእድሜ ልክ ሥራ ነው። መልካም አጋጣሚዎቻችን በበዙ ቁጥር ልምምዳችን ይሰፋና እውቀታችን ይጨምራል።”—Ellen G. White, Christ’s Object Lessons, pp. 65, 66.

የወርቃማው ዘር መብሰል የሚወክለው በጸጋ የተለወጡትን፣ በፍቅር የተነሳሱትንና ለክርስቶስ ስም ክብር የመታዘዝ ሕይወት የሚኖሩትን ሁሉ ነው። ልቦቻቸው ከኢየሱስ ልብ ጋር አንድ ስለሆኑ እነርሱ የሚፈልጉት ነገር ቢኖር እርሱ የሚፈልገውን ነገር ብቻ ነው። “በእያንዳንዱ የእድገት ደረጃ ሕይወታችን ፍጹም ሊሆን ይችላል” የሚሉትን የኤለን ጂ ኋይት ቃላት እንዴት እንረዳቸዋለን? ይህ በተለይ አሁን ስህተቶቻችንን እና የባህርይ ጉድለቶቻችንን ማየት ስንችል ምን ማለት ነው?

መጋቢት 28
Apr 06

እያንዳንዱ ዘር መከር ይሆናል


በራዕይ 14 ላይ ሁለት መከሮች አሉ። የወርቃማው ዘር መከር የሚወክለው ቅዱሳንን ሲሆን በደም የተነከረው የወይን መከር የሚወክለው ኃጢአተኞችን ወይም የጠፉትን ነው። ሁለቱም መከሮች ለአጨዳ ደርሰዋል። የተዘራው እያንዳንዱ ዘር በደንብ በስሏል። ራዕይ 14:17—20ን ያንብቡ። “ታላቁ የእግዚአብሔር ቁጣ ወይን መጭመቂያ” የሚለው አባባል ምን ማለት ነው? ደግሞ ራዕይ 14፡ 10፤ 15፡ 1 እና 16፡1ን ያንብቡ።



“በእሳትም ላይ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከመሠዊያው ወጣ” (ራዕይ 14:18)። በዚህ ቦታ የተጠቀሰው መልአክ የእግዚአብሔርን የመጨረሻ ፍርድ እሳት የሚያዝ መልአክ ነው። መከሩ ደርሷል። ኃጢአት ወደ ገደቡ ደርሷል። አመጽ የእግዚአብሔርን የምህረት መስመር ጥሶ አልፏል። ነገሮች ክፉና መጥፎ የነበሩ ቢሆንም ሁሉም ነገር ከመፈጸሙ በፊት እየከፉ ይሄዳሉ። አፍቃሪው አምላክ ለእኛ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ አድርጓል፤ ይህ ለኃጢአታችን ራሱን በመስቀል ላይ መስዋዕት አድርጎ ማቅረብን ያካትታል። “እኛ በእርሱ ሆነን የእግዚአብሔር ጽድቅ እንሆን ዘንድ ኃጢአት ያላወቀውን እርሱን ስለ እኛ ኃጢአት አደረገው” (2ኛ ቆሮ. 5:21፤ ገላ. 3:13ን ደግሞ ይመልከቱ)።

ከዚያ መስቀል ባሻገር እግዚአብሔር ሌላ ምን ማድረግ ይችል ነበር?? በተደጋጋሚ የመንፈስ ቅዱስን ተማጽኖ አልቀበል ያሉትን ሰዎች ለማዳን ጸጋ ሊያደርገው የሚችል ከዚህ ሌላ ምንም ነገር የለም።

የራዕይ 14 አንገብጋቢው ትንቢታዊ መልእክት ይህ ነው። እያንዳንዱ ዘር ለመከር ተዘጋጅቷል። መከሩ ደርሷል፣ የወይን ዘለላዎቹም በስለዋል። የእግዚአብሔር ሕዝብ በዩኒቨርስ ፊት የእርሱን ምስል፣ ርኅራኄ፣ ምህረትና ፍቅር አሳይተዋል። የክፉው ልጆች ስስትን፣ ፍትወትን፣ ቅንዓትንና ጥላቻን አሳይተዋል። በአንዱ ቡድን ላይ የክርስቶስ ባህርይ የታየ ሲሆን በሌላኛው ቡድን ላይ ደግሞ የሰይጣን ባህርይ ተገልጧል።

ዩኒቨርስ ከዚህ በፊት የነበረው ማንኛውም ትውልድ አይቶት የማያውቀውን የጽድቅ መገለጥ በእግዚአብሔር ህዝብ ያያል። በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ከታየው የክርስቶስ ጽድቅ በተቃራኒ በእግዚአብሔር ላይ የማመጽን ሙሉ ውጤት ዩኒቨርስ ይመለከታል። ሀኬት፣ ክፋት፣ ኃጢአትና ህገ-ወጥነት በሰዎችና በመላእክት ፊት በግልጽ ይታያሉ። በክፉና በመልካም፣ ትክክል በሆነውና ስህተት በሆነው፣ በመታዘዝና ባለመታዘዝ መካከል ያለው ልዩነት ለመላው ዓለም፣ ለሰዎችና ለመላእክት ግልጽ ይሆናል። በክፉና በመልካም መካከል ያለውን ልዩነት ምን ያህል ለይተው ያውቃሉ? ይህን ማድረግ የሚያስፈልገው ለምንድር ነው? (ዕብ. 5:14ን ይመልከቱ)።

መጋቢት 29
Apr 07


ተጨማሪ ሀሳብ


“በማየት እንለወጣለን የሚለው ሀሳብ የእውቀት ዘርፍም ሆነ የመንፈሳዊው ተፈጥሮ ሕግ ነው። አእምሮ እንዲያስብ ከተፈቀደለት ነገር ጋር በሂደት ይለማመዳል። ለመውደድና ለማምለክ ከተለማመደው ነገር ጋር ይዋሃዳል። ሰው ለንጽህና ወይም ለመልካምነት ወይም ለእውነት ካስቀመጠው ከራሱ መስፈርት በላይ በፍጹም ከፍ ማለት አይችልም። ከሁሉ የሚበልጠው ሀሳቡ ራስ ወዳድነት ከሆነ ከዚህ ከፍ ወዳለ ምንም ነገር መድረስ አይችልም። ይልቁንም ከጊዜ ወደ ጊዜ ወደ ታች እየሰመጠ ይሄዳል። ሰውን ከፍ ማድረግ የሚችል የእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ነው፡፤ ሰው ለራሱ ከተተወ መንገዱ የሚያመራው ያለማቋረጥ ወደ ቁልቁል ነው።”—Ellen G. White, The Great Controversy, p. 555.

ባህሪያችንና ማንነታችን አሳሳች በሆነ ሁኔታ፣ ሳይታይ፣ በመጀመሪያ ሳይታወቅ በአእምሮአችን ውስጥ እየዘራናቸው ባሉት ዘሮች ላይ ተመስርተው ይለወጣሉ። መልካም ዘር ከዘራችሁ መልካም ፍሬ ታፈራላችሁ። የዚህን ዓለም ክፉ ዘር ከዘራችሁ በባህርያችሁ የዚህን ዓለም ክፉ ፍሬ ታፈራላችሁ። ለእግዚአብሔርና ለመንፈሳዊ እሴቶች ግድ የለሽ የመሆን ዘር ከዘራን የግድ የለሽነት ፍሬ የሆኑትን ደንታ ቢስነትን፣ ባለበት መንፈሳዊ ሁኔታ ረክቶ መቀመጥን እና በመንፈሳዊ ሕይወታችን ተስፋ መቁረጥን እናጭዳለን። አንድ ቀን የመጨረሻው ስደት፣ ‹‹የአውሬው ምልክት›› እና የመሳሰሉ ነገሮች እንደሚመጡ አውቃለሁ፣ ነገር ግን እነዚህ ነገሮች ሲደርሱ ነገሮችን አስተካክላለሁ ብለው የሚያስቡ ሰዎች እጅግ አደገኛ የሆነ መንገድ እየመረጡ ናቸው። እግዚአብሔር አሁን፣ በዚህች ቅጽበት፣ ሕይወታችንን ለእርሱ አሳልፈን እንድንሰጥ ይጠራናል። ሰው ለመንፈስ ቅዱስ ምላሽ ለመስጠት በዘገየ ቁጥር ነፍሱ ለእግዚአብሔር ጥሪ ምላሽ ለመስጠት እየጠነከረ ይሄድና በክፉው ውሸቶች ለመሸነፍና እነርሱን ለማመን የበለጠ ተጋላጭ ይሆናል።


የመወያያ ጥያቄዎች



1.በራዕይ 14፡14-20 እና የመከር መርህ አውድ፣ በጸጋ በመዳንና በጸጋ በማደግ መካከል ያለው ግንኙነት ምንድር ነው?

2. ለተክሎች እድገት አስፈላጊ ስለሆኑ ንጥረነገሮች ተወያዩና ያንን ከእኛ መንፈሳዊ እድገት ጋር አነጻጽሩ። የሚያመሳስሉአቸው ነገሮች ምንድር ናቸው? ከተክሎች አስተዳደግ ለራሳችን ሕይወት የሚሆን ምን ትምህርት እናገኛለን?

3. እግዚአብሔር እንድንመርጥ በሰጠን ችሎታና በፈቃድ ኃይል መካከል ልዩነት አለ? ለሚያድግ ክርስቲያን ይህንን ልዩነት መረዳት አስፈላጊ የሚሆነው ለምንድር ነው?

4. የክርስቶስን ዳግም ምጻት እየጠበቅን ሳለ “የሰው ልጅ” የሚለው ርዕስ በፍርዱ ሰዓት ላይ ማደፋፈሪያ የሚሆነን ለምንድር ነው? ሰው፣ ሰብአዊ ፍጡር፣ በፍርድ ፊት እኛን ወክሎ በሰማይ መገኘቱ ለእኛ ማጽናኛ የሚሆነው ለምንድር ነው?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL