የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሶስት ዓለም አቀፋዊ መልእክቶች



2ኛ ሩብ ዓመት 2023


መጋቢት 16 - 22

1ኛ ትምህርት

Mar 25 - 31




ኢየሱስ ያሸንፋል-ሰይጣን ይሸነፋል



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሳምንት ትምህርት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡- ራዕይ 12፤ ኤፌ. 5:25–27፣ 32፤ ፊልጵስዩስ 3:9፤ ዳን. 7:25፤ ኢሳ. 14:12–14፤ ራዕይ 13:14–17።


የሳምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ዘንዶውም በሴቲቱ ላይ ተቈጥቶ የእግዚአብሔርን ትእዛዛት የሚጠብቁትን የኢየሱስም ምስክር ያላቸውን ከዘርዋ የቀሩትን ሊዋጋ ሄደ” (ራዕይ 12:17)።

ኮርማክ ኦብሪየን የተባለ ሰው በቁጥር የተበለጡ፡-በታሪክ የሚታወቁ እጅግ አስደናቂ የጦር ሜዳ ጭንቀቶችን የሚገልጹ፣ ለማመን የሚከብዱ ታሪኮች በሚለው መጽሐፉ ላይ ምንም እንኳን በቁጥር እጅግ ቢበለጡም ጦርነቱን ስላሸነፉ የጦር ሰራዊቶች ያወራል። ታሪኩ 55,000 ወታደሮች የነበሩት ካርቴጅ ከተባለ ቦታ የተነሳው የሃኒባል ጦር 80,000 ወታደሮች የነበሩትን የሮምን ‹‹የማይደፈር›› ብርቱ ጦር ማሸነፉን ይነግረናል። በታላቁ እስክንድር የሚመራው የግሪክ ጦር የፋርስን ጦር ማሸነፉንም ይነግረናል። እኛም ከአታላይ ጠላት ጋር የሞት የሽረት ጦርነት ላይ ነን። ለማመን የሚያስቸግሩ ኃይሎችን እየተዋገን ሳለን በቁጥር እጅግ ተበልጠናል። የክፉ ኃይሎች የማይደፈሩ ይመስላሉ። መሸነፋችን እርግጠኛ ይመስላል። ሽንፈት የማይቀር ይመስላል። ድል ከእይታ የራቀ ይመስላል። ከሰብአዊ ዕይታ ስንመለከት የሰይጣን ኃይሎች የሚያሸንፉን ይመስላል።

ነገር ግን ምንም እንኳን በቁጥር ብንበለጥም፣ በሰውኛ አነጋገር የማንጠብቃቸው ነገሮች አደጋ ሊያደርሱብን ቢጋፈጡንም፣ ምንም እንኳን የሰይጣን ጥቃቶች በጭካኔ የተሞሉ ቢሆኑም በኢየሱስ አማካይነት በመጨረሻ እናሸንፋለን። የመጽሐፍ ቅዱስ የመጨረሻው መጽሐፍ የሆነው የራዕይ መጽሐፍ ዋና ሀሳብ ኢየሱስ ያሸንፋል፣ ሰይጣን ይሸነፋል የሚል ነው። የዚህ ጦርነት ዋና ሀሳብ የተዘረዘረው በራዕይ ምዕራፍ 12 ሲሆን የሳምንቱ ጥናታችን ትኩረትም ይኸው ነው። ይህ ጥናት ራዕይ 14ን እና የሶስቱን መላእክት መልእክት እንድናስተውል በደንብ ያዘጋጀናል። *የዚህን ሳምንት ትምህርት ለመጋቢት 23 ሰንበት ለመዘጋጀት አጥኑ።

መጋቢት 17
Mar 26

ጦርነት በሰማይ


ራዕይ ምዕራፍ 12 በሰማይ ተጀምሮ እዚህ በምድር ላይ ስለሚጠናቀቀውና በክፉና በመልካም መካከል ስለሚካሄደው ዘመናትን ስላስቆጠረው ጦርነት ተከታታይነት ያላቸውን ትዕይንታዊ ክስተቶች ስዕል ያቀርብልናል። እነዚህ ክስተቶች ሰይጣን በሰማይ ካመጸበት ጊዜ አንስቶ በመጨረሻ ዘመን በእግዚአብሔር ህዝብ ላይ የጭካኔ ጥቃት እስከሚያደርስበት ድረስ ይወስደናል። ይህን በክፉና በመልካም መካከል የሚደረገውን ዓለም አቀፋዊ ጦርነት የሚገልጸውን ራዕይ 12፡7-9ን ያንብቡ። ይህንን የሚመስል ነገር እንዴት በሰማይ ሊከሰት ቻለ? እነዚህ ጥቅሶች ስለ ነጻ ፈቃድና ስለ ምርጫ ነጻነት ምን ፍንጭ ይሰጣሉ?



የምርጫ ነጻነት በምድርም ሆነ በሰማይ የእግዚአብሔር መንግስት መሰረታዊ መርህ ነው። እግዚአብሔር በምድርም ሆነ በሰማይ ሮቦቶችን አልፈጠረም። እኛ፣ ሰብአዊ ፍጡራን በእግዚአብሔር አምሳል ስለተፈጠርን የሞራል ምርጫዎችን ማድረግ እንችላለን ።

የመምረጥ ኃይል ከመውደድ ችሎታ ጋር በቅርበት የተገናኘ ነው። ፍቅርን በፍጹም ማስገደድ ስለማይቻል የምርጫን ኃይል ካስወገዳችሁ የመውደድ ችሎታንም ታጠፋላችሁ። ፍቅር የነጻ ፈቃድ መገለጫ ነው። በሰማይ ያለው እያንዳንዱ መልአክ ለእግዚአብሔር ፍቅር ምላሽ ለመስጠት ወይም በራስ ወዳድነት፣ በእብሪትና በኩራት ከእግዚአብሔር ለመለየት ምርጫ ቀርቦለት ነበር። ሰማያዊ መላእክት በፍቅር ከዘላለማዊ ምርጫ ጋር እንደተጋፈጡ ሁሉ በዚህ ምድር ላይ በሚሆነው የመጨረሻው ጦርነት ላይም እያንዳንዳችን ዘላለማዊ ምርጫዎችን እንደምናደርግ የራዕይ መጽሐፍ ይናገራል።

በታላቁ ተጋድሎ ውስጥ መሃል-ሰፋሪነት በፍጹም ተከስቶ አያውቅም (ሉቃስ 11፡23ን ይመልከቱ)፣ በምድር የመጨረሻው ጦርነትም መሃል-ሰፋሪነት አይኖርም። እያንዳንዱ መልአክ በኢየሱስ ወገን ወይም በሉሲፌር ወገን ለመቆም እንደመረጠ ሁሉ ሰብአዊ ዘር በሙሉ በመጨረሻው ዘመን የመጨረሻውን የማይለወጥ ምርጫ ወደማድረግ ይመራል። ታማኝነታችንን፣ አምልኮአችንን እና ታዛዥነታችንን የሚቀበል ማን ነው? ይህ ጉዳይ ሰብአዊ ዘር ሁልጊዜም የሚጋፈጠው ጉዳይ ሲሆን በምድር ታሪክ የመጨረሻው አስጨናቂ ሁኔታ ውስጥ ከድሮ ይበልጥ ትዕይንታዊ በሆነ ሁኔታ ይፈጸማል። ነገር ግን አስገራሚ የሆነ የምስራች አለ። ራዕይ ምዕራፍ 12 በጦርነቱ ክርስቶስ አሸናፊ መሆኑን ስለሚገለጽ ሁላችንም ነጻ ፈቃዳችንን በመጠቀም ከእርሱ ወገን ለመሆን፣ ከአሸናፊነት ወገን ለመቆም መምረጥ አለብን። በጦርነቱ አሸናፊ የሚሆነው ማን እንደሆነ አስቀድማችሁ በምታውቁት ሁኔታ ከማን ጎን እንደምትቆሙ መምረጥ እንዴት ያለ ታላቅ ነገር ነው። የእኛ ምርጫ እርሱን ወደ መስቀል እንደሚወስደው ቢያውቅም (2ኛ ጢሞ. 1፡9) ለእኛ ነጻ ፈቃድ መስጠቱ ለኢየሱስ ነጻ ፈቃድና የምርጫ ነጻነት ምን ያህል የተቀደሱ ነገሮች እንደሆነ አስቡ። ይህን የተቀደሰ ግን እጅግ ውድ የሆነ ስጦታ እንዴት በጥንቃቄ መጠቀም እንዳለብን ይህ ምን ይነግረናል?

መጋቢት 18
Mar 27

የሰይጣን ጥቃት


ሰይጣን ከመጀመሪያው ጀምሮ ክርስቶስን ለማጥፋት ፈለገ (ራዕይ 12፡ 4፣ 5ን ይመልከቱ)። ነገር ግን የሰይጣን እያንዳንዱ ጥረት ሳይሳካ ቀራ። ለምሳሌ፣ በክርስቶስ ልደት ጊዜ ስለ ሄሮድስ የክፋት እቅዶች መልአክ ማርያምንና ዮሴፍን ስላስጠነቀቃቸው ወደ ግብጽ ሸሹ። ኢየሱስ በምድረ በዳ ‹‹ተጽፏል›› የሚል ጥቅስ ያለባቸውን እጅግ አታላይ የሆኑ የሰይጣን ፈተናዎችን የተጋፈጠ ሲሆን በእግዚአብሔር ቃል ውስጥ መከላከያን አገኘ። በመስቀል ሞቱ የፍቅሩን ግዝፈት የገለጸ ሲሆን ከኃጢአት ኩነኔ ቅጣት ነጻ አወጣን። በትንሣኤው፣ እንደ ህያው ሊቀ ካህናችን፣ በሕይወታችን ከኃጢአት ኃይል ነጻ ያወጣናል። ራዕይ 12:4–6፣ 9፤ ኤፌሶን 5:25–27፣ 32፤ እና መዝሙር 2:7–9ን ያንብቡና ለሚከተሉት ምልክቶች ትርጉም ይስጡ:- ዘንዶ



ሴት



ወንድ ልጅ



የብረት በትር



በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በትር የገዥነት ምልክት ነው። የብረት በትር ደግሞ የማይሰበር፣ ኃያል፣ የማይበገር አገዛዝ ምልክት ነው። ኢየሱስ እኛ የሚገጥመንን እያንዳንዱን ፈተና የተጋፈጠ ሲሆን በሁሉም አሸናፊ ሆኖ ወጥቷል። ሰይጣን የተሸነፈ ጠላት ነው። ኢየሱስ በሕይወቱ፣ በሞቱና በትንሣኤው አሸንፎታል። ኢየሱስ ሰይጣንን በቀራኒዮ መስቀል ስላሸነፈው እኛም አሸናፊዎች መሆን እንችላለን። ክርስቶስ በሰይጣን ላይ የተቀዳጀው ድል የተሟላ ቢሆንም በክርስቶስና በሰይጣን መካከል የሚደረገው ታላቁ ተጋድሎ አሁንም አላበቃም። ሆኖም ክርስቶስ ለእኛ ያደረገልንን ነገር በእምነት ስንቀበል የኃጢአት ዕዳችን ተሰርዞልን ለኃጢአታችን ይቅርታ ይደረግልናል። በክርስቶስ ጽድቅ ተሸፍነን በእግዚአብሔር ፊት ፍጹማን ሆነን እንቆማለን። ጳውሎስ እንዲህ በማለት ጽፏል፡- “ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት “ክርስቶስንም አገኝ ዘንድ፥ በክርስቶስም በማመን ያለው ጽድቅ ማለት በእምነት ከእግዚአብሔር ዘንድ ያለው ጽድቅ እንጂ ከሕግ ለእኔ ያለው ጽድቅ ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ” ሳይሆንልኝ፥ በእርሱ እገኝ ዘንድ ሁሉን እንደ ጕድፍ እቈጥራለሁ” (ፊልጵስዩስ 3:9)። ይቅር ከተባልን የምንከሰስበት አንዳች ነገር አይኖርም። ኢየሱስ ኃጢአትና ክፋት ሊያደርሱበት የሚችሉትን እጅግ አስከፊ ነገሮች ለዘላለም ድል አድርጓል። በክፉው ላይ ሙሉ ጥቃት በመሰንዘር አሸንፎታል። ኢየሱስን በእምነት ስንቀበል የእርሱ ድል የእኛ ይሆናል። ክርስቶስ ሰይጣንን ከማሸነፉ የተነሣ የተሰጠን የድነት ማረጋገጫ ለእኛ እጅግ ወሳኝ የሚሆነው ለምንድር ነው? ጳውሎስ በፍልጵስዩስ 3፡9 ላይ የጻፈው ነገር የእኛ ልምምድ መሆን የሚችለው እንዴት ነው?

መጋቢት 19
Mar 28

የኢየሱስን ድል መቀበል


በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ እንደተገለጸው ኢየሱስ ከሰይጣን ጋር ባደረጋቸው ጦርነቶች በፍጹም ተሸንፎ አያውቅም። እርሱ ኃያል አሸናፊ ነው። እርሱ በክፉ ኃይሎች ላይ ድል አድራጊ ነው። ኢየሱስ የሰይጣንን ፈተናዎች ማሸነፉን ማመን አንድ ነገር ነው፤ የክርስቶስ ድል የእኛ ድል ነው ብሎ ማመን ሌላ ነገር ነው። ራዕይ 12:10ን ያንብቡ። ከሳሽዎ ወደ ምድር ከመጣሉ እውነታ ምን ማበረታቻ ማግኘት ይችላሉ?



አሁንም ጦርነቱ በምድር ላይ ተጠናክሮ ቢቀጥልም ሰይጣን ተሸንፏል። አራት ነጥብ። ይህ እውነት የሆነው በሰብአዊ ዘር ታሪክ መጨረሻ ላይ ክርስቶስ ስለሚቀዳጀው የመጨረሻው ድል ብቻ ሳይሆን እኛ በግል ሕይወታችን ከክፉ ኃይላትና ሥልጣናት ጋር ስለምናደርገው ጦርነትም እውነት ነው። አንዳንድ ክርስቲያኖች ተስፋ በመቁረጥ ሽንፈት ውስጥ ናቸው። በሆነ አመለካከት ወይም ልማድ ላይ ድል ለመቀዳጀት ተስፋ ያደርጋሉ፣ ነገር ግን በራሳቸው ሕይወት የክርስቶስን ድል እውነታ በፍጹም አይገነዘቡም። ራዕይ 12:11ን ያንብቡ። በዚህ ንባብ ውስጥ ክርስቶስ የሰጠን ምን የድል መተማመኛ ነው?



ለሰባቱ ቤተ ክርስቲያናት በተላኩት የራዕይ መልእክቶች ውስጥ ‹‹ድል ለነሣው›› የሚለውን መግለጫ ሰባት ጊዜ እናገኛለን። በራዕይ 12፡11 ላይ እንደ ገና ድል የማድረግን ጽንሰ ሀሳብ እናገኛለን። ‹‹ድል መንሳት›› ለሚለው ቃል በመጀመሪያ ቋንቋ ጥቅም ላይ የዋለው ቃል ኒካኦ የሚል ነው። ቃል በቃል ሲተረጎም ‹‹በቁጥጥር ሥር ማድረግ፣ ማሸነፍ፣ ድል መንሳት ወይም አሸናፊ ሆኖ መውጣት›› የሚል ትርጉም አለው። ለእኛ አሸናፊ ሆኖ መውጣት እንዴት የሚቻል ነገር እንደሆነ ልብ በሉ። ራዕይ 12፡11 ላይ ይህ ሊሆን የሚችለው ‹‹በበጉ ደም›› ብቻ እንደሆነ ያረጋግጣል። በራዕይ 5፡6 ላይ በተገለጸው ትንቢታዊ ራዕይ ኢየሱስ ወደ ሰማይ በመመልከት ‹‹በጉን እንደ ታረደ ሆኖ›› ያየዋል። የክርስቶስ መስዋዕትነት የመላው ሰማይ የትኩረት ነጥብ ነው። የእግዚአብሔርን ዘላለማዊና ሊለካ የማይችል ፍቅር ለመግለጽ ከመስቀል የበለጠ ማራኪ የሆነ ነገር የለም። ክርስቶስ ያደረገልንን ነገር በእምነት ስንቀበል ዕዳችን ይሰረዝልንና በእግዚአብሔር እይታ ፍጹማን ሆነን እንቆማለን። ኃጢአቶቻችን ይቅር ተብለውልናል (ቆላ. 1፡14፣ ኤፌ. 1፡7፣ ቆላ. 2፡14)። ‹‹የወንድሞቻችን ከሳሽ ተጥሏል›› (ራዕይ 12፡10)። የተዋጀነው፣ ድል የነሣነውና የዳንነው በእኛ መልካም ሥራ ሳይሆን ክርስቶስ ስለ እኛ ድል ስለነሣ ነው።

መጋቢት 20
Mar 29

በበረሃ ያለችው ሴት


ራዕይ 12:6ን ያንብቡና ከራዕይ 12፡14-16 ጋር ያነጻጽሩ። ጊዜውን፣ ሰይጣን በ‹‹ሴቲቱ›› (በእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን) ላይ ጥቃት መሰንዘሩንና እግዚአብሔር ለሕዝቡ ያዘጋጀውን ነገር በጥንቃቄ ልብ ይበሉ። እነዚህ ጥቅሶች እየተናገሩ ያሉት ስለ ምንድር ነው?



በራዕይ 12፡6 ላይ የተገለጹ 1260 ቀናት በራዕይ 12፡4 ላይ ከተገለጹት ዘመን፣ ዘመናትና የዘመን እኩሌታ ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ተመሳሳይ ወቅትን የሚገልጽ ተመሳሳይ የጊዜ ትንቢት በዳንኤል 7፡25፣ ራዕይ 11፡2፣3 እና ራዕይ 13፡ 5 ላይ ይገኛል። እነዚህ ትንቢታዊ ምልክቶች ስለሆኑ ለእነዚህ ትንቢቶች (ቃሉ እንደሚገልጸው ክንፍ ያላት ሴት ወደ በረሃ አልሄደችም)፣ ትንቢታዊ ጊዜን፣ ቀን ለዓመት መርህን እንጠቀማለን (ለምሳሌ ዘሁልቁ 14፡34 እና ሕዝቅኤል 4፡4-6ን ይመልከቱ)። ይህ ማለት፣ በቀላሉ፣ አንድ ትንቢታዊ ቀን አንድ ዓመትን ይወክላል ማለት ነው። አንድሪውስ ዩኒቨርሲቲ ሰቴዲ ባይብል በራዕይ 11፡2 ላይ በተገለጸው ትንቢታዊ ወቅት ላይ አስተያየቱን ሲሰጥ ‹‹ታሪካዊ የአተረጓጎም ዘዴን የሚከተሉ ሰዎች 1260 ትንቢታዊ ቀናት 1260 ዓመታትን የሚወክሉ ሲሆኑ ከ538 ዓ.ም እስከ 1798 ዓ.ም ያለውን ጊዜ የሚሸፍኑ መሆናቸውን ተረድተው ነበር›› (ገጽ 1673፣ አስተያየት በራዕይ 11፡2 ላይ)። የረከሰችው ቤተ ክርስቲያን ከረከሰው ምድራዊ መንግስት ጋር በመሆን የእግዚአብሔርን ታማኝ ሕዝብ ጨቁናለች፣ አሳድዳለች፣ አንዳንድ ጊዜም ገድላለች።

መጽሐፍ ቅዱስን በሚያምኑ ክርስቲያኖች ላይ የደረሰው ይህ ጭካኔ የተሞላበት ሰይጣናዊ ስደት በመልካምና በክፉ መካከል ሲካሄድ ከነበረው ታላቁ ተጋድሎ የቀጠለ ነበር። በተሃድሶው ጊዜ ወንዶችና ሴቶች ከመካከለኛው ዘመን ጨለማ ስለወጡ ከፊታቸው ምርጫ የማድረግ አማራጭ ቀርቦላቸው ነበር። ለእግዚአብሔር ቃል ታማኝ ለመሆን ወይም የካህናትንና የቤተ ክርስቲያን መሪዎችን (ጳጳሳትን) ትምህርቶች ለመቀበል ምርጫ ማድረግ ነበረባቸው። እንደገና እውነት ስላሸነፈ ብርቱ በሆነ ተቃውሞ ውስጥ እግዚአብሔር ታማኝ የሆነ ሕዝብ ነበረው።

በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ስለ እግዚአብሔር ጥበቃ የሚያስደስቱና እጅግ የሚያበረታቱ አንዳንድ አገላለጾች አሉ። ራዕይ 12፡6 “በእግዚአብሔር “በእግዚአብሔር ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ” ተዘጋጅቶላት ወደ ነበረው ስፍራ” የሚል አገላለጽ ይጠቀማል። ራዕይ 12፡14 ሴቲቱ በምድረ በዳ “እንደተመገበች” ሲገልጽ ራዕይ 12፡ 16 ደግሞ “ምድሪቱም ሴቲቱን “ምድሪቱም ሴቲቱን ረዳቻት” ረዳቻት” ይላል። እጅግ ኃይለኛ ስደት በነበረባቸው ጊዜያቶች እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያኑ የሚያስፈልጋትን ነገር አዘጋጀላት። ያኔ እንዳደረገው ሁሉ ለመጨረሻው ዘመን ቅሬታዎችም ተመሳሳይ ነገር ያደርግላቸዋል። በራስዎ ሕይወት በቀላሉ ተስፋ መቁረጥ ይችሉ የነበሩበትን፣ ነገር ግን እግዚአብሔር የመሸሸግያ ቦታ አዘጋጅቶሎት በገጠመዎ ተግዳሮቶች ውስጥ የመገበዎትን የፈተና ወይም የችግር ጊዜን ይግለጹ። እጅግ ባስፈለገዎ ጊዜ እግዚአብሔር ድጋፍ የሰጠዎ እንዴት ነበር?

መጋቢት 21
Mar 30

የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ቅሬታ ሕዝብ


ሰይጣን በሰማይ አመጽ ካስነሳበት ጊዜ አንስቶ ከክርስቶስ ጋር በጦርነት ላይ ነው (ራዕይ 12፡17)። የሰይጣን ዓላማ ያኔም አሁንም ዩኒቨርስን መቆጣጠር ነው (ኢሳ. 14፡12-14ን ይመልከቱ)። በምድር ታሪክ የመጨረሻዎቹ ቀናት እርሱ ትኩረት የሚያደርገው በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ ነው። ዘንዶው (ሰይጣን) በሴቲቱ (ቤተ ክርስቲያን) ላይ መቆጣቱንና ከቀሩት ዘርዋ ጋር ይዋጋ ዘንድ መሄዱን ራዕይ 12፡17 በአጽንዖት ይገልጻል። ከቀሩት ዘርዋ የሚለው አባባል ቅሬታ ተብሎም ተተርጉሟል። የእግዚአብሔር ቅሬታ ሕዝብ ለክርስቶስ ተገዥ፣ ለእውነቱ ታዛዥና ለተልዕኮው ታማኝ ይሆናሉ። ራዕይ 12:17ን ያንብቡ። በዚህ ጥቅስ ውስጥ የእግዚአብሔር የመጨረሻው ዘመን ቤተ ክርስቲያን የሆነችውን ቅሬታዋን ቤተክርስቲያን የሚገልጹ ምን ባህርያት አሉ?



በራዕይ 12፡17 ላይ ሰይጣን (ዘንዶው) በሴቲቱ (የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን) ላይ ተቆጥቷል። ሰይጣን የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በሚጠብቁ ላይ ስለተቆጣ እነርሱን ለማጥፋት ማድረግ የሚችለውን ሁሉ ያደርጋል።

በመጨረሻም መግዛትና መሸጥ እንዳይችሉ የሚከለክልና እንዲታሰሩና እንዲገደሉ የሚፈቅድ አዋጅ እንዲወጣ ያነሳሳል (ራዕይ 13፡14-17ን ያንብቡ)። ሰይጣን ክርስቶስን ማጥፋት እስካልቻለ ድረስ የእርሱ ጥልቅ የፍቅር ርዕስ የሆነችውን ቤተ ክርስቲያኑን ሊያጠፋ ይሞክራል። የምድር የመጨረሻው ጦርነት ማዕከል ያደረገው በመካከለኛ ምሥራቅና በዚያ በሚደረጉ የተለያዩ ግጭቶች ላይ አይደለም። ነገር ግን ትኩረት ያደረገው በመላው ዓለም ላይ ተበታትነው ባሉ በእግዚአብሔር ሕዝብ አእምሮዎች ላይ ነው። ጦርነቱ በሁለት ታቃራኒ ኃይሎች፣ በክርስቶስና በሰይጣን መካከል የሚደረግ ጦርነት ነው። በዚህ ጦርነት መሃል ሰፋሪ የለም።

በዚህ የመጨረሻ ጦርነት ላይ ዋናው ጥያቄ ‹‹ታማኝነታችንን የምናሳየው ለማን ነው? ለማን ነው የምንገዛው?” የሚለው ነው። ሰማይ በክርስቶስ ፍቅር የተማረኩ፣ በጸጋው የዳኑ፣ ለዓላማዎቹ ራሳቸውን አሳልፈው የሰጡ፣ በመንፈሱ ኃይል የተሞሉና ለሥራው ሞትን ለመጋፈጥ ፈቃደኛ በመሆን ትዕዛዛቱን የሚታዘዙ አማኞችን እየጠራ ነው።

ዓለማችን አብይ ወደሆነ ችግር እያመራች ነው። ነገር ግን በኢየሱስ ውስጥ በመሆን፣ በእርሱ አማካይነትና በእርሱ ምክንያት ወደ መታዘዝ በሚመራ እምነት ከእርሱ ጋር እስከተገናኘን ድረስ ድል መንሳታችን እርግጠኛ ነው። ይህ ሁሉ የሚሆነው በምርጫችን ነው። ራዕይ 12፡17 ላይ የተጠቀሰው እውነታ በራስዎ ሕይወት፣ በራስዎ የክርስትና ልምምድ ሲተገበር የሚያዩት እንዴት ነው? ይህ ማለት ታላቁ ተጋድሎ በራስዎ ሕይወት እየተፈጸመ ያለው በምን መንገዶች ነው? ማለት ነው።

መጋቢት 22
Mar 31


ተጨማሪ ሀሳብ


እግዚአብሔር ምርጫ አልነበረውም ብለን ልንከራከር እንችላለን፡-እርሱንና ሌሎችን የሚወዱ ፍጡሮችን ከፈለገ ነጻ አድርጎ ሊፈጥራቸው ይገባል። ነጻ ካልሆኑ መውደድ ስለማይችሉ ዩኒቨርሳችን ያለ ፍቅር ምን ሊሆን ይችላል? አንዳንድ ሰዎች እንደሚሉት እኛ ጥብቅ በሆነ የመንስኤና ውጤት ሕግ እንደሚሰራ አእምሮ የለሽ ማሽን ነጻ የፈቃድ ኃይልና የምርጫ ነጻነት የሌለን፣ ግን ደምና ሥጋ ከመሆን ውጭ ምንም ያልሆንን--የፊዝክስ ሕጎችን ብቻ የሚከተሉ የአቶም ቅንጣቶች ስብስብ ከመሆን በስተቀር ምንም አይደለንም ማለት ነው። ይህ ጥሩ ስዕል አይደለም፣ ስለ ራሳችን እውነት እንደሆነ የምናውቀውን ነገርም በትክክል አይወክልም። ለምሳሌ፣ ለወላጆቻችን፣ ለልጆቻችንና ለትዳር ጓደኞቻችን ያለን ፍቅር ከአቶሞች ድርዳሮ በስተቀር ምንም አይደለም ብሎ የሚያስብ ማን ነው?

“የፍቅር ሕግ የእግዚአብሔር መንግስት መሰረት ስለሆነ አስተዋይ የሆኑ/ እውቀት ያላቸው ፍጡራን ሁሉ ደስታ የሚደገፈው እነርሱ ከታላቁ የጽድቅ መርሆዎች ጋር የተስማሙ ሲሆን ብቻ ነው። እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጡራን ሁሉ የፍቅር አገልግሎትን ይሻል--የእርሱን ባህርይ ከማድነቅ የሚመነጭ አገልግሎት። በግዴታ በሚሆን መታዘዝ አይደሰትም። በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ አገልግሎት እንዲያቀርቡለት ለሁሉም የፈቃድ ነጻነት ይሰጣል።

“ፍጡራን ሁሉ የፍቅር መታዘዝን ተቀብለው እስከኖሩ ድረስ በመላው የእግዚአብሔር ዩኒቨርስ ውስጥ ፍጹም መጣጣም ነበር። ለሰማያዊ ሰራዊት የፈጣሪያቸውን ዓላማ መፈጸም ደስታ ይሰጣቸው ነበር። ክብሩን በማንጸባረቅና ምሥጋናውን በማሳየት ይደሰቱ ነበር። ለእግዚአብሔር የነበራቸው ፍቅር ከሁሉም በላይ ሲሆን ለእርስ በርሳቸው የነበራቸው ፍቅርም መተማመን የነበረበትና ራስ ወዳድነት የሌለው ነበር። በሰማያዊ አካላት መካከል የነበረውን መጣጣም የሚያበላሽ የአለመስማማት ዜማ አልነበረም።”—Ellen G. White, Patriarchs and Prophets, pp. 34, 35.


የመወያያ ጥያቄዎች



1. ራዕይ 12 ለሶስቱ መላእክት መልእክት፣ በተለይም በመጨረሻ ዘመን በሚመጣው ጦርነት እይታ፣ ገጣሚ መግቢያ የሆነው ለምንድር ነው?

2. እርስዎ በየቀኑ በሚጋፈጡአቸው ፈተናዎችና መከራዎች ውስጥ ራዕይ 12 መተማመኛ የሚሆንዎት እንዴት ነው?

3. ድርጊቶቻችን በአብዛኛው በውርስና በአካባቢ እንደሆነ የሚያምኑ አንዳንድ ሰዎች አሉ። በዚህ ይስማማሉ ወይስ አይስማሙም? ባህርያችንን በመወሰን ረገድ ምርጫችን ምን ሚና አለው? በምርጫችንና በሕይወታችን በሚሰራው በእግዚአብሔር ኃይል መካከል ያለውን ግንኙነት ተወያዩበት።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL