የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ሶስት ዓለም አቀፋዊ መልእክቶች



2ኛ ሩብ ዓመት 2023



ሚያዝያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ 2015 ዓ.ም.

መደበኛ እትም

Mar 25 - Jun 23




አዘጋጅ : መልእክቶች

ትርጉም : በማርክ ፊንሊ



ትርጉም፡ ታምሬ ሻዕማሎ ይህ የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ የሚዘጋጀው በሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ዋና መስሪያ ቤት በሆነው በጀነራል ኮንፍረንስ ውስጥ ሆኖ፤ የጎልማሶች የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያን በሚያዘጋጀው ቢሮ ነው። መምሪያዎቹ የሚዘጋጁት የጀነራል ኮንፈረንስ አስተዳደር ኮሚቴ ንዑስ ኮሚቴ በሆነውና የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያዎችን በሚያሳትመው የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድ ነው። የታተመው መምሪያ በውስጡ ዓለም አቀፋዊ የሆነ የምዘና ኮሚቴ ሀሳቦችንና የሰንበት ትምህርት ሕትመት ቦርድን ማረጋገጫ ስለሚያንጸባርቅ የአዘጋጁን (የአዘጋጆችን) ሀሳብ ብቻ የሚወክል አይደለም።

በኢትዮጵያ አድቬንቲስት ማተሚያ ቤት ታተመ
2ኛ ሩብ ዓመት
ሚያዝያ፣ ግንቦት፣ ሰኔ 2015 ዓ.ም.
የሶስቱ መላእክት መልእክት እ.አ.አ ጥቅምት 15 ቀን 1844 ዓ.ም፣ ከታላቁ ተስፋ መቁረጥ አንድ ሳምንት በፊት፣ በጀርመን አገር መንፈሳዊ በሆነ የሉተራውያን ቤተሰብ ውስጥ አንድ ወንድ ልጅ ተወለደ። ስሙ ፍሬድሪክ ኒዤ ሲሆን ይህ ልጅ በዘመኑ እጅግ ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ ከሃዲዎች መካከል አንዱ ሆነ። የክርስቲያኖች እግዚአብሔር በምዕራቡ ዓለም እየሞተ እንደሆነ በማመን ኒዤ የክርስቲያኖች ኃይማኖት በቀጣይነት እያሳደረ ባለው የሞራል ተጽእኖ ላይ በመማረር “የባሪያዎች ግብረገብ፣” ብርቱ ከሆኑ ሰዎች ራሳቸውን ለመከላከል በሚያደርጉት ጥረት “ጠላቶቻችሁን ውደዱ” የሚል የጅል ሀሳብ የፈጠሩ የደካሞች ግብረገብ ነው በማለት አሾፈ። ለኒዤ ዘመናዊነት ጊዜ ካለፈበት የ“መልካምና ክፉ” አስተሳሰብ ባሻገር ማለፍ ነበረበት፤ ከመጻሕፍቱ አንዱ በሆነው ‹‹ዛራቱስትራ እንዲህ ተናገረ›› በሚለው መጽሐፍ ውስጥ ካሉ ገጸ ባህርያት መካከል አንዱ “የአሮጌውን ህግ ጽላቶች ስበራቸው!” በማለት ይናገራል። እያወራ ያለው ስለ አሥርቱ ትዕዛዛት እንደሆነ ግልጽ ነው።

የኮሙኒዝም መስራች ለነበረው ካርል ማርክስም 1844 ዓ.ም ወሳኝ ዓመት ነበር። ይህ ዓመት “የ1844 ዓ.ም ኢኮኖሚያዊና ፍልስፍናዊ ጽሁፎች” የተባለ ሥራው የተጻፈበት ዓመት ነበር። ነገር ግን ጽሁፉ በማተሚያ ቤት የታተመው በ1932 ዓ.ም በሶቪየት ሕብረት ነበር። ጽሁፎቹ የዓለም ሰራተኞች ተባብረው የካፒታሊስት ጨቋኞቻቸውን በመጣል በምድር ላይ ሁሉም ፍላጎቱ ተሟልቶለት የሚኖርበት ሁኔታ እስኪፈጠር ድረስ ሙሉ በሙሉ ለቁሰ-አካላዊ እውነታ የተከራከረበትን የማርክስን ቀደምት ርዕዮተ ዓለም የሚያሳይ ነበር።

እ.አ.አ 1844 ዓ.ም ለቻርልስ ዳርዊንም ወሳኝ አመት ነበር። ያኔ ለሕዝብ እንዲታወቅ ባይደረግም “የ1844 ዓ.ም መጣጥፍ” ተብሎ በሚታወቀው ሥራው ላይ በዝግመተ ለውጥ ጽንሰ ሀሳብ ላይ ቀደምት ከሆኑ መግለጫዎቹ መካከል አንዱን ያዘጋጀበት አመት ነበር። ዳርዊን የዝሪያዎች መነሻ በሚለው የሕትመት ውጤቱ ላይ በምድር ላይ ያለው ሕይወት በሙሉ በተፈጥሮአዊና በአጋጣሚ ሂደቶች ብቻ ከአንድ የዘር ሀረግ/ግንድ መነሳቱን የሚገልጸውን አመለካካቱን ለሕዝብ ይፋ ያደረገው እ.አ.አ በ1859 ዓ.ም ነበር። ነገር ግን እ.አ.አ 1844 ዓ.ም በዳንኤል 8፡ 14 ላይ የተገለጸው የ2600 ቀናት ትንቢት የተፈጸመበት ዓመት ሲሆን ከታላቁ ተስፋ መቁረጥ የተረፉት ያስተላለፉት ወሳኝ/ ቁልፍ መልእክት የማርክሲስቶችን፣ የኔዤያውያንን እና የዳርዊናውያንን ርዕዮተ ዓለም ከንቱ በማድረግ ወደ ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ በፍጥነት የሚያድግ ዘር የተዘራበት ዓመት ነበር። ከማርክስ በተቃራኒ፣ የዓለም ፍጻሜ የሚሆነው ሰው ሰራሽ በሆነ የኮሚኒስቶች ፍጹም ማህበረሰብ ምስረታ ሳይሆን መለኮት በሚመሰርተው ዘላለማዊው የእግዚአብሔር መንግስት እንደሆነ የሚገልጸው በክፉና በመልካም መካከል የሚደረገው ጦርነት የዓለምን ታሪክ እንደሚያብራራ እንጂ የቁሰ- አካላውያን የታሪክ ፍሰት እንደማያብራራ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት እንቅስቃሴ አወጀ። ከዳርዊን በተቃራኒ፣ የሕይወት መነሻው በዘፈቀደ በሚከሰት የዘረመል ቅይርታና ተፈጥሮ የተሻለውን መርጦ በማስቀረት የማይጠቅመውን በሚያስወግድበት ተፈጥሮአዊና አጋጣሚ ሂደት ሳይሆን በስድስት ቀን በምድር ላይ ሕይወት ያላቸውን ነገሮች ከፈጠረ በኋላ በሰባተኛው ቀን ባረፈው ፈጣሪ በሆነ አምላክ ኃይል መሆኑን የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች እንቅስቃሴ አስተማረ። ከኔዤ በተቃራኒ፣ እግዚአብሔር ብቻ ሳይሆን የእርሱ ዓለም አቀፋዊ የግብረገብ መመሪያ የሆኑት (“አሮጌዎቹ የህግ ጽላቶች”)፣ አስርቱ ትዕዛዛት፣ የመጨረሻዎቹ የፍርድ መስፈርቶችና ሰብአዊ ዘርን በሙሉ የሚገዙ እንደሆኑ የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስቶች እንቅስቃሴ አወጀ።

እነዚህ ክስተቶች በሙሉ በ1844 ዓ.ም መሆናቸው ዝም ብሎ የአጋጣሚ ጉዳይ ነው? ማንም ሰው እንደዚህ ማሰብ የለበትም።

የሶስቱ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች፡-ማርክስ፣ ኔዤ እና ዳርዊን ሥራዎች በሰብአዊ ዘር ላይ እንደገና ሊታረም የማይችል ጉዳት አስከትለዋል። ነገር ግን በእነዚህ ስህተቶች ሁሉ መካከል እግዚአብሔር ዓለምን ያለ ምስክር አልተወም፤ ለዓለም እውነቱን የሚያስተላልፉ ምስክሮች ነበሩት። እግዚአብሔር በእነዚህ አውዳሚ በሆኑ ርዕዮተ-ዓለሞች መካከል በሂደት ወደ ሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት እንቅስቃሴ የሚለወጠውንና ለዓለም የመጨረሻ ዘመን መልእክት፣ የሶስቱን መላእክት መልእክቶች የሚያውጀውን እንቅስቃሴ ያስነሳው ለዚህ ነበር። እነዚህ መልእክቶች የእነዚያን በአሰቃቂ ሁኔታ የተታለሉትን ሶስት ሰዎች ስህተቶች የሚቃወሙ ናቸው። የሶስቱ መላእክት መልእክት የሰባተኛ ቀን አድቬንቲስት ቤተ ክርስቲያን ወደ ጦርነት ለመዝመት የምትሰጣቸው ትዕዛዞች ናቸው። መልእክቶቹ በውስጣቸው ንጹህና ቀላል ወንጌል ናቸው፣ ነገር ግን “በወቅቱ እውነት” አውድ የቀረበ ወንጌል ናቸው (2ኛ ጴጥሮስ 1፡12)። የዚህ ሩብ ዓመት ጥናታችን የሚሆነው ስለ ሶስቱ መላእክት መልእክቶች ነው።




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL