የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ለዚህ ሳምንት ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ:- ራዕይ 14:12፣ ኤፌ. 2:8-10፣ ማቴ. 27:45–50፣ ራዕይ 13:15–17፣ ራዕይ 14:4፣ ሉቃስ 5:18–26።
የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ:- “የሕያው አምላክ ማኅተም ያለውም ሌላ መልአክ ከፀሐይ መውጫ ሲወጣ አየሁ፥ ምድርንና ባሕርንም ሊጐዱ ለተሰጣቸው ለአራቱ መላእክት በታላቅ ድምፅ እየጮኸ፦ የአምላካችንን ባሪያዎች ግምባራቸውን እስክናትማቸው ድረስ ምድርን ቢሆን ወይም ባሕርን ወይም ዛፎችን አትጕዱ አላቸው” (ራዕይ 7:2፣ 3)።
የአውሬውን ምልክት በተመለከተ የመጨረሻ ዘመን ክስተቶችን ስናጠና ሳለ
ከውስጡ ብቅ የሚለው አንድ ወሳኝ ነጥብ እግዚአብሔር በሚሰራበት
መንገድና የነፍሳት ጠላት በሚሰራበት መንገድ ላይ ያለው ልዩነት ነው።
እስካሁን ስናጠና እንደነበርነው በክርስቶስና በሰይጣን መካከል ባለው
ታላቁ ተጋድሎ ውስጥ ያሉት ማዕከላዊ ጉዳዮች የሚያተኩሩት በታዛዥነት፣
በሥልጣንና በአምልኮ ላይ ነው። በዳንኤል ምዕራፍ 13 ላይ ያለውን አውሬ፣
በዳንኤል ምዕራፍ 7 ላይ ያለውን ትንሹን ቀንድና በ2ኛ ተሰሎንቄ 2 ላይ ያለውን
“የጥፋት ልጅ” የሚገልጹ ትንቢቶች በሙሉ የሚናገሩት የእግዚአብሔርን
ሥልጣን ስለሚቀማ፣ እንዲታዘዙት ስለሚያስገድድና አስመሳይ የአምልኮ
ሥርዓትን ስለሚያስተዋውቅ ኃይል ነው። ይህን የሚያደርጉት በማስገደድ፣
በኃይልና አንዳንድ ጊዜም በጉቦና በሽልማቶች አማካይነት ሲሆን ዓላማቸው
እንዲሰግዱላቸው ለማስገደድ ነው።
ከዚህ በተቃራኒ፣ ፍቅር የእግዚአብሔር መንግስት ታላቁ የማነሳሻ ኃይል
ነው። የእግዚአብሔር ሕዝብ ለአውሬው በመስገድ ፋንታ እግዚአብሔርን
በማምለክ ታላቅ ደስታ ያገኛሉ። እርሱ ለእነርሱ ምን ያህል ራሱን እንደሰጠ
ስለሚያውቁ እነርሱም ለእርሱ ራሳቸውን የሰጡ ናቸው። በመጨረሻ ዘመን
የአውሬውን ምልክት እንዳንቀበል የሚከለክለን አንድ ነገር ብቻ አለ። ያውም
ምንም ነገር ከእርሱ ሊለየን እስከማይችል ድረስ ለእርሱ ያለን እጅግ ጥልቅ የሆነ
ፍቅር ነው።
በዚህ ትምህርት ውስጥ እነዚህን ጭብጦች የበለጠ እንመረምራለን።
*የዚህን ሳምንት ትምህርት ለሰኔ 3 ሰንበት ለመዘጋጀት ያጥኑ።
በራዕይ ምዕራፍ 14፡7 ላይ እንደተመለከትነው ሰዎች ሁሉ ፈጣሪን
እንዲያመልኩ (ለፈጣሪ እንዲሰግዱ) እግዚአብሔር ይጠራቸዋል። ይህ
የመጀመሪያው መልአክ መልእክት ነው። በራዕይ 14፡8 ላይ እግዚአብሔር ስለ
“ባቢሎን፣” መነሻው ከጥንት ባቢሎን ስለሆነው የውሸት ኃይማኖታዊ ሥርዓት
ያስጠነቅቃል። ይህ የሁለተኛው መልአክ መልእክት ነው።
በራዕይ ምዕራፍ 14፡ 9 እና 10 ላይ ሶስተኛው መልአክ ለአውሬው
እንዳንሰግድ ያስጠነቅቃል። መልአኩ በታላቅ ድምጽ “ለአውሬውና ለምስሉ
የሚሰግድ በግምባሩም ወይም በእጁ ምልክቱን የሚቀበል ማንም ቢኖር፥እርሱ
ደግሞ በቍጣው ጽዋ ሳይቀላቅል ከተዘጋጀው ከእግዚአብሔር ቍጣ ወይን ጠጅ
ይጠጣል፥ በቅዱሳንም መላእክትና በበጉ ፊት በእሳትና በዲን ይሳቀያል” በማለት
ያውጃል።
ራዕይ 14:12ን ያንብቡ። በዚህ ንባብ ውስጥ ስለ መጨረሻው ዘመን
የእግዚአብሔር ሕዝብ ምን ሁለት ባሕርያት ማግኘት እንችላለን? ሁለቱም
አስፈላጊ የሚሆኑት ለምንድር ነው?
“ትዕግስት” ተብሎ የተተረጎመው የግሪኩ ቃል ሁፖሞን ሲሆን “ጽኑ
ትዕግስት” ተብሎ በተሻለ ሁኔታ ሊተረጎም ይችላል። በኃይለኛ ስደትና ተቃውሞ
ውስጥ ለእግዚአብሔር ታማኝ የሆነ የመጨረሻ ዘመን ሕዝብ ይኖራል። በእርሱ
ፀጋ እግዚአብሔርን ማዕከል ያደረገ፣ በፀጋ የተሞላ፣ የመታዘዝ ሕይወት እየኖሩ
በጽኑ ትዕግስት ይቆማሉ።
ፈጣሪን ማምለክ (ራዕይ 14፡7) አውሬውን የማምለክ ታቃራኒ ስለሆነ
(ራዕይ 14፡9) ራሱን የሚገልጠው የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት በሚጠብቁና
የኢየሱስ እምነት ባላቸው ሰዎች ሕይወት ነው (ራዕይ 14፡12)። ለኢየሱስ
ወይም ለአውሬው ኃይል መታዘዝን የሚጠይቀው ይህ የመጨረሻው ጦርነት
የሚያጠነጥነው በአምልኮ ዙሪያ ሲሆን የዚህ በክፉና በመልካም መካከል
የሚደረገው ታላቁ ተጋድሎ እምብርት የሚሆነው ሰንበት ነው።
ሮሜ 8:1–4፣ ኤፌ. 2:8–10 እና ቆላ. 1:29ን ያንብቡ። እነዚህ ንባቦች
በእምነት ስለመኖር ውጤት ምን ያስተምሩናል?
በእምነት በመኖር ፀጋውን እንቀበላለን፣ ሕይወታችንም ይለወጣል።
ራሳቸውን የሰጡ የአዳኙ ተከታዮች በኢየሱስ ላይ እምነት የሚኖራቸው ብቻ
ሳይሆኑ የኢየሱስ እምነትም ይኖራቸዋል። የኢየሱስ ጥራት ያለው የመጨረሻ
ዘመን እምነት የእነርሱ ይሆንና ኢየሱስ እንዳደረገው ሁሉ እነርሱም እስከ ሞት
ድረስ ታማኝ ሆነው ይቆማሉ።
እርስዎ በትናንሽ ነገሮች ምን ያህል ታማኝ ነዎት? ይህ እውነተኛው ፈተና
ሲመጣ እንዴት ሊሆኑ እንደሚችሉ ምን ሊነግርዎት ይችላል? (ሉቃስ 16:10ን
ይመልከቱ)።
ማቴ. 27:45–50ን ያንብቡ። ይህ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ስለተለማመደው ነገር ምን ያስተምረናል? ኢየሱስ እግዚአብሔር ለምን እንደተወው ሲጠይቅ ምን ማለቱ ነበር? ይህ ትዕይንት “የኢየሱስ ኃይማኖት” ያላቸው ማለት ምን ማለት እንደሆነ እንድናስተውል ሊረዳን የሚችለው እንዴት ነው?
ኢየሱስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ፣ በጨለማ ተሸፍኖ፣ በዓለም ውስጥ
ያለውን የኃጢአት በደል፣ ውርደትና ኩነኔ ተሸክሞ እና ከአባቱ የፍቅር ስሜት
ሙሉ በሙሉ ተለይቶ ሳለ በሕይወት ዘመኑ ሁሉ ከአባቱ ጋር በነበረው ግንኙነት
ላይ ተደገፈ። ይህ ማለት በአባቱ ላይ ሙሉ በሙሉ በሚደገፍ ሕይወት፣
በመልካሙ ጊዜ ሳይቀር ለመጥፎ ጊዜ፣ ለመስቀል ሞትም ቢሆን ተዘጋጅቶ ነበር።
በዙሪያው ያሉ ነገሮች ሁሉ እንዲጠራጠር ጮኸው ቢናገሩም በአባቱ ተማመነ።
እግዚአብሔር የተወው በመሰለ ጊዜም ቢሆን ኢየሱስ ተስፋ አልቆረጠም።
“አስፈሪ በሆነው ጨለማ መካከል፣ እግዚአብሔር የተወው በመሰለ ሰዓት፣
ክርስቶስ በሰብአዊ ዘር የመከራ (ዋይታ) ጽዋ ውስጥ ያለውን የመጨረሻውን
አተላ ጨለጠ። በእነዚህ አሰቃቂ ሰዓታት ከዚህ በፊት በአባቱ ዘንድ በነበረው
ተቀባይነት ማረጋገጫ ላይ ተደገፈ።…ክርስቶስ በእምነት አሸነፈ።”—Ellen G.
White, Christ Triumphant, p. 277.
የኢየሱስ እምነት እጅግ ጥልቅ፣ እጅግ የሚተማመን፣ እጅግ የተሰጠ
ከመሆኑ የተነሣ በመላው ዩኒቨርስ የነበሩ አጋንንቶችና በምድር ላይ የነበሩ ፈተናዎች
ሁሉ ሊያናውጡት አልቻሉም። የእርሱ እምነት ማየት ሳይችል የሚታመን፣
መረዳት በማይችልበት ጊዜ የሚያምን ፣ በትዕግስት ለመቆየት የሚያስችል ነገር
በሌለበት በትዕግስት የሚቆይ እምነት ነው። ይህ “የኢየሱስ እምነት” በእምነት
የምንቀበለው ስጦታ ሲሆን ከፊታችን ባለው ችግር መካከል እንድናልፍ
የሚያስችለን ነው። ክርስቶስን ከሁሉ የበላይ አድርገን እንድናመልከውና በራዕይ
መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው የአውሬው ምልክት አስገዳጅ ሲሆን በጽናት ታግሰን
እንድናልፍ የሚያደርገን በልባችን ያደረው “የኢየሱስ እምነት” ነው።
ሆኖም ከሆነ ቦታ በድንገት የሚመጣ ነገር አይደለም። የእግዚአብሔር
ሕዝብ በየዕለቱ በእምነት ለመኖር እየተማሩ ነበር። በጥሩ ጊዜያትም ሆነ በመጥፎ፣
እግዚአብሔር የቀረበም ሆነ የራቀ ሲመሰል በእነርሱ ሕይወት ልዩነት አያመጣም።
“ጻድቅ በእምነት ይኖራል” (ገላ. 3:11፤ ዕንባቆም 2:4ን ደግሞ ይመልከቱ)።
የዝግጅት ጊዜ አሁን ነው። አሁን የሚመጣውን እያንዳንዱን ፈተና በትዕግስት
ማለፍ ከተቻለ በሕይወታችን ክቡር ፍሬዎችን ማፍራት ይችላል።
በዙሪያዎ ሕይወት እየተፈረካከሰ ያለ የመሰለዎትን ጊዜና የነበረዎ
ነገር እምነትዎ ብቻ የነበረበትን ጊዜ ያስቡ። ይህን ጊዜ እንዴት
ማለፍ ቻሉ? ምን ትምህርቶችን ተማሩ? ተመሳሳይ በሆነ ሁኔታ
ውስጥ እያለፉ ያሉ ሰዎችን ሊረዳ የሚችል ምን ልምምድ አገኙ?
የአውሬውን ምልክት በተመለከተ የተነገረው ትንቢት የሚናገረው ስለ
ኃይማኖታዊ አለመቻቻል፣ ኢኮኖሚያዊ ማዕቀብ፣ ስደትና በመጨረሻም ስለ ሞት
አዋጅ ነው። በሚያስገርም ሁኔታ የማደፋፈሪያ መልእክትም ነው። እጅግ አስከፊ
በሆኑ ጊዜያቶችም ቢሆን “የእግዚአብሔርን ትዕዛዛት የሚጠብቁትንና የኢየሱስ
እምነት ያላቸውን” (ራዕይ 14:12) እግዚአብሔር ደግፎ ያኖራቸዋል።
በራዕይ ምዕራፍ 13 ላይ የተነገረው የአውሬው ምልክት ትንቢት ሰይጣን
እግዚአብሔርን በመቃወም ስለሚከፍተው አስከፊ ጦርነት ትኩሳት የሚያሳይ
ፍጹም ድምጽ ነው። በዚህ ዘመቻ ውስጥ የመጀመሪያ ስልቱ ማታለል ነው። ራዕይ
13 ሰይጣን ወደ ፊት አውሬ ተብሎ በሚጠራው በምድራዊ የኃይማኖትና ፖለቲካ
ጥምረት ኃይል አማካይነት ስለሚሰራበትና ኃይል በመጠቀም ስለሚያስገድድበት
ጊዜ ይነግረናል።
በእርግጥ የኃይማኖት ስደት አዲስ ነገር አይደለም። አቤል እግዚአብሔር
በሚፈልግበት መንገድ አምላኩን ከማምለኩ የተነሣ ቃየል ከገደለው ጊዜ አንስቶ
የነበረ ነገር ነው (ዘፍ. 4፡1-8ን ይመልከቱ)። ኢየሱስ ከመጀመሪያው መቶ
ክፍለ ዘመን አንስቶ በዘመናት ሁሉ በአማኞች ላይ ስደት እንደሚመጣ ተናግሮ
ነበር። ማስጠንቀቂያው እንዲህ ይላል፡- “ከዚህ በላይ ደግሞ የሚገድላችሁ ሁሉ
እግዚአብሔርን እንደሚያገለግል የሚመስልበት ጊዜ ይመጣል” (ዮሐ. 16:2፤
ማቴ. 10:22፣ 1ኛ ጴጥ. 4:12ን ደግሞ ይመልከቱ)።
ስለ አውሬው ምልክት የሚናገረው ትንቢት የሚገልጸው በዚህ
እግዚአብሔርን በማይመስል ሰንሰለት ውስጥ ያለውን የመጨረሻ ማገናኛ ቀለበት
ነው። ከዚህ በፊት እንደነበሩት ስደቶች ሁሉ ሰዎች ከሆኑ እምነቶችና ተቀባይነት
ካገኘው የአምልኮ ሥርዓት ጋር እንዲስማሙ ለማስገደድ የታደቀ ነው።
ራዕይ 13:15–17ን ያንብቡ። በመጨረሻው አስጨናቂ ጊዜ
የእግዚአብሔር ሕዝብ የሚጋፈጡት ነገር ምንድር ነው?
ስደት የሚጀመረው በኢኮኖሚ ማዕቀብ እንደሚሆን ትንቢቱ ይናገራል፡
- “ምልክቱ የሌለው ማንም ቢሆን መግዛትም ሆነ መሸጥ አይችልም።” ይህ ሲሆን
አብዛኛው ሕዝብ እጅ ይሰጣል። እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ የማይሆን በሙሉ
በመጨረሻ የሞት አዋጅ ይተላለፍበታል።
ወደ ፊት የመጨረሻው ፈተና ሲመጣ ክርስቲያን ነን ባዮች በሕይወታቸው
በመደራደር የአውሬውን ምልክት እንዲቀበሉ እያዘጋጃቸው ነው። ከፊታችን
ባሉ አስቸጋሪ ጊዜያቶች እግዚአብሔር ለእያንዳንዳችን ያለው ፍቅር ያበረታናል፣
ይጠብቀናልም።
ገላ. 6:7–9ን ያንብቡ። ምንም እንኳን ይህ ሀሳብ በመጨረሻው
ዘመን ክስተቶች አውድ የተጻፈ ባይሆንም በዚያ ቦታ ያለው መርህ
በአውሬው ምልክት ላይ በሚነሱ ጉዳዮችና እንዴት ታማኝ ሆነን
መቆም እንደምንችል በተመለከተ ተያያዥነት የሚኖረው ለምንድር
ነው?
ራዕይ 13:1፣ 2ን ያንብቡ። አውሬው ከየት ነው የወጣው? ለአውሬው ሥልጣን የሰጠው ማን ነው?
በራዕይ ምዕራፍ 13 ላይ የተገለጸው የመጀመሪያው አውሬ ሥልጣኑን፣
ዙፋኑንና ትልቅ ሥልጣን የሚቀበለው ከዘንዶው ነው። ራዕይ 12፡ 9 እና 20፡
22 ዘንዶውን ሰይጣን እንደሆነ ይገልጻሉ። ሰይጣን ብልህ ጠላት ስለሆነ
የሚሰራው በምድራዊ ኃይሎች አማካይነት ነው። ይህ “ዘንዶ”-ሰይጣን- “ወንድ
ልጅ” ወዲያውኑ እንደተወለደ ሊያጠፋው ጥረት ማድረጉን ራዕይ 12፡ 3-5
ይገልጻል። ኋላ ይህ “ወንድ ልጅ” “ወደ እግዚአብሔርና ወደ ዙፋኑ ተነጠቀ።”
ይህ የሚያመለክተው ክርስቶስን ነው። ሰይጣን ልጁን ክርስቶስን ለማጥፋት
በመፈለግ በሄሮድስና በንጉሥ በምትመራው ሮም አማካይነት ሰራ። በኢየሱስ
የሕይወት ፍጻሜ ላይ የሮም ገዥ የነበረው ጲላጦስ እንዲሞት የፈረደበት ሲሆን
ሮማዊ ገዳይ ጨካኝ በሆነው መስቀል ላይ በምስማር ቸንክሮታል፤ ሮማዊ ወታደር
በጦር የወጋው ሲሆን የሮም ወታደሮች መቃብሩን ጠብቀዋል። እንደ ራዕይ 13፡
2 ከሆነ ዘንዶው፣ ሰይጣን፣ በአረመኔዋ ሮም አማካይነት በመስራት የመንግስቱን
መቀመጫ ለዚህ ብቅ እያለ ላለው የአውሬ ኃይል ይሰጣል።
“ዘንዶው በመጀመሪያ ሰይጣንን ቢወክልም በሁለተኛ ደረጃ የሮምን
መንግስት ይወክላል። …የሮምን መንግሥት ተከትሎ የመጣውና ‘ኃይሉን፣
ዙፋኑንና ታላቅ ሥልጣን’ ከዘንዶው የተቀበለው ኃይል በግልጽ ጳጳሳዊው ሮም
ነው ።”—The SDA Bible Commentary, vol. 7, p. 817። ኤ. ሲ. ፍሊክ የተባለ
የታሪክ ምሁር “ከፖለቲካዊው ሮም ፍርስራሽ ውስጥ ግዙፍ በሆነችው የሮም ቤተ
ክርስቲያን መልክ ግዙፍ የሆነ የሞራል ግዛት ተነሳ” በማለት ገልጾአል።—A. C.
Flick, The Rise of the Medieval Church (1900) p. 150 as quoted in The
SDA Bible Commentary, vol. 7, page 817.
ራዕይ 13:3 እና 14:4ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች መካከል ምን
ልዩነት ተመለከቱ?
አውሬውን በሚከተለው “ዓለም በሙሉ” በተቃራኒ “በጉን የሚከተል”
ሕዝብ እግዚአብሔር ይኖረዋል። ሁልጊዜ እንደነበረው ሁሉ ከሁለቱ በአንዱ
ወገን መቆም፣ ከኢየሱስ ጋር ወይም ከእርሱ በተቃራኒ መቆም ግድ ነው። አሁን
እንደሚሆነው ያኔ መሃል ሰፋሪነት፣ በአማካይ ቦታ መቆም አይኖርም። በማወቅም
ሆነ ባለማወቅ ራስን ለኢየሱስ አሳልፎ አለመስጠት ለሌላኛው ወገን ራስን አሳልፎ
መስጠት ነው።
“በሁሉም ስለ ስሜ የተጠላችሁ ትሆናላችሁ፤ እስከ መጨረሻ
የሚጸና ግን እርሱ ይድናል።” (ማቴ. 10:22)። እስከ መጨረሻው
ለመታገስ ምን ያህል ዝግጁ ነዎት?
ራዕይ 13:4፣ 5ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ የአውሬውን ኃይል የሚገልጹ ምን ምልክቶች እናገኛለን?
በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ የተጠቀሰው አውሬ ከአረመኔዋ ሮም በመነሳት ዓለም አቀፋዊ የአምልኮ ሥርዓት እስኪሆን ድረስ የሚያድግ ከሃዲ ኃይማኖታዊ ኃይል ነው። እንደ ራዕይ 13፡ 5 አገላለጽ ተሳዳቢ የሆነ ኃይል ነው። በአዲስ ኪዳን ውስጥ ስድብ አንድ ግለሰብ ለእግዚአብሔር ብቻ የሚገቡ መብቶችና ሥልጣኖች እንዳሉት አድርጎ መናገር ነው። ሉቃስ 5:18–26 እና ዮሐ. 10:33ን ያንብቡ። እነዚህ ጥቅሶች የሚያመለክቱት የትኞቹን ሁለት የስድብ ገጽታዎች ነው?
መሪዎች ኢየሱስን ይሳደባል ብለው ከሰውት ነበር። ኢየሱስ ኃጢአታችንን
ይቅር የማለትን መብት ጨምሮ እግዚአብሔር ያለው ኃይልና ሥልጣን
በሙሉ ስላለው ክሳቸው መሰረተ ቢስ ነበር። ይህ የሆነበት ምክንያት ኢየሱስ
እግዚአብሔር ስለሆነ ነው። ወይም እርሱ ራሱ “አንተ ፊልጶስ፥ ይህን ያህል ዘመን
ከእናንተ ጋር ስኖር አታውቀኝምን? እኔን ያየ አብን አይቶአል፤ እንዴትስ አንተ፦
አብን አሳየን ትላለህ?” (ዮሐ. 14:9) ብሎ ኃይለኛ በሆነ ሁኔታ እንደገለጸው ነው።
1ኛ ጢሞቴዎስ 2፡5 በእግዚአብሔርና በሰው መካከል አንድ አማላጅ፣
እርሱም ሰው የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳለ ያስተምረናል። ከዚህ በተቃራኒ
የሮም ቤተ ክርስቲያን በእግዚአብሔርና ኃጢአተኛ በሆነው ሰብአዊ ዘር መካከል
አማላጅ ካህኑ እንደሆነ ታስተምራለች። ነገር ግን ካህኑ ራሱ ኃጢአተኛ የሆነ
ሰብዓዊ ፍጡር ስለሆነ እና ለራሱም አማላጅ ስለሚያስፈልገው አማላጃችን
መሆን አይችልም። ስድብ ማለት ማንኛውም ሰው እግዚአብሔር እንደሆነ ወይም
በእግዚአብሔር ቦታ እንደሚቆም መናገር ነው። ከሮም ቤተ ክርስቲያን ሥልጣን
ካላቸው ምንጮች የተወሰዱ ሁለት አንቀጾች ከዚህ በታች ቀርበዋል:-
“ጳጳሱ ትልቅ ስብዕና ስላለውና እጅግ ከፍ ያለ ስለሆነ ዝም ብሎ ተራ
ሰው አይደለም።…እርሱ በምድር ላይ እንዳለ እግዚአብሔር ነው።”—Lucius
Ferraris, “Papa,” article 2 in his Prompta Bibliotheca (1763), vol. 6,
pp. 25–29.
ሊዎ 13ኛው የተባለ ጳጳስ እንዲህ በማለት በኩራት ተናግሯል፡- “እኛ
[ጳጳሳት] በዚህ ምድር ላይ የሁሉን ቻይ አምላክን ቦታ እንይዛለን።”—The Great
Encyclical Letters of Pope Leo XIII (New York: Benziger, 1903), p. 193.
እነዚህ አባባሎች የበለጠ ግልጽ የሚሆኑልን የክርስቶስ ተቃዋሚ በሚለው
ሀረግ ውስጥ ተቃዋሚ የሚለው ቃል የሚያመለክተው ዝም ብሎ ተቃዋሚ
መሆንን ሳይሆን “በእግዚአብሔር ቦታ” መሆን የሚል ትርጉም እንዳላቸው
እንረዳለን። ስለዚህ የክርስቶስ ተቃዋሚ ማለት “በክርስቶስ ቦታ የሆነ” ማለት
ነው።
“ታላቁ ተጋድሎ በሰማይ ከጀመረበት ጊዜ አንስቶ
የሰይጣን ዓላማ የእግዚአብሔርን ሕግ መገርሰስ ነበር። በፈጣሪ ላይ ወደማመጽ
የገባው ይህንን ዓላማ ለመፈጸም ሲሆን ከሰማይ ቢጣልም ያንኑ ጦርነት በምድር
ላይ ቀጥሏል። ሰዎችን ለማታለልና የእግዚአብሔርን ሕግ ወደመተላለፍ መምራት
በጽናት የሚከተለው ዓላማ ነው። ይህ ዓላማ ሕግጋትን በሙሉ ባለመቀበልም
ሆነ ከሕግጋቱ አንዱን በመጣስ ተፈጻሚ ቢሆን ውጤቱ በመጨረሻ ተመሳሳይ
ይሆናል።…መለኮታዊ ሕግጋት እንዲናቁ ለማድረግ በመፈለግ ሰይጣን የመጽሐፍ
ቅዱስን አስተምህሮዎች ያዛባ ሲሆን ቅዱሳት መጻሕፍትን እናምናለን በሚሉ
በሺሆች በሚቆጠሩ ሰዎች እምነት ውስጥ ስህተቶች ተካትተዋል። በእውነትና
በሀሰት መካከል የሚደረገው የመጨረሻው ታላቁ ተጋድሎ የእግዚአብሔርን ሕግ
በተመለከተ ለረዥም ጊዜ ሲካሄድ የቆየው የመጨረሻው ትግል ነው። አሁን በሰው
ሕጎችና በያህዌ ሕግጋት መካከል፣ በመጽሐፍ ቅዱስ ኃይማኖት እና በአፈ ታሪክና
በትውፊት (ሲወርድ ሲዋረድ የመጣ ልማድ) ኃይማኖት መካከል ወደሚደረገው
ወደዚህ ጦርነት እየገባን ነን።”—Ellen G. White, The Great Controversy,
p. 582.
በራዕይ መጽሐፍ ውስጥ አምልኮና ፍጥረት ሊነጣጠሉ በማይችሉበት
ሁኔታ የተገናኙ ናቸው። በክፉና በመልካም መካከል የሚደረገው ተጋድሎ
ዓላማና በአውሬው ምልክት ዙሪያ ያሉ ጉዳዮች የሚሽከረከሩት እግዚአብሔር
አምልኮ ይገባዋል ወይም አይገባውም በሚለው ሀሳብ ዙሪያ ነው።
አስቀድመን እንደተመለከትነው ክርስቶስን እንደ ፈጣሪ የማየት ሀሳብ
ሰንበትን በቅድስና በመጠበቅ ልብ ውስጥ ያለ ነገር ነው። ኢየሱስ ራሱን “ጌታ”
ብሎ የሚጠራበትን ቀን ወሳኝነት ያለማቋረጥ አስምሮበታል (ማቴ. 12፡8፣ ማር.
2፡28፣ ሉቃስ 6፡5)። ሰንበት የእኛ ማንነት ዘላለማዊ ማስታወሻ ነው። እንደ
ሰብአዊ ፍጡራን የማን እንደሆንን ያስታውሰናል። እያንዳንዱ ሰብአዊ ፍጡር ዋጋ
እንዳለው ያሳያል። እኛ ፍጡራን እንደሆንን እና ፈጣሪያችን መገዛትና አምልኮ
የሚገባው የመሆኑን ሀሳብ ያለማቋረጥ ያጠናክራል። ሰይጣን ሰንበትን አምርሮ
የሚጠላው ከዚህ የተነሣ ነው። ከፈጣሪያችን ጋር አንድ የሚያደርገን ወርቃማ
ማገናኛ ነው። በመጨረሻው አስጨናቂ ጊዜ ወሳኝ ሚና የሚጫወተውም ከዚህ
የተነሣ ነው።
1.አውሬው ስልጣን እንዳለው በሚናገረው ባህር በስተጀርባ ያሉ
መሰረታዊ መርሆዎች ምንድር ናቸው? እኛ ሳናውቃቸው እነዚህ
አመለካከቶች በልባችን ውስጥ ሊያድሩ የሚችሉት በምን መንገዶች
ነው?
2. ሰይጣን በትክክል የመኖሩ ሀሳብ የተማሩ ወይም ቢያንስ አዋቂ
የሆኑ ሰዎች ሊቀበሉት የማይችሉት ኋላ ቀር አስተሳሰብ ነው ብለው
ለሚከራከሩ ሰዎች እርስዎ እንዴት መልስ ይሰጣሉ? በምላሽዎ ምን
መከራከሪያዎችን መጠቀም ይችላሉ?