የጎልማሶች ሰንበት ትምህርት

የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ

ስለ ሞት፣ ስለ መሞትና ስለ ወደፊቱ ተስፋ


የመጸሐፍ ቅዱስ ጥናት መምሪያ - 3ኛ ሩብ ዓመት 2022

ጥቅምት 12-18

5ኛ ትምህርት

Oct 22–28




ከመስቀሉ በፊት የተከሰቱ ትንሳኤዎች



ሰንበት ከሰዓት

ለዚህ ሣምንት የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት የሚከተሉትን ጥቅሶች ያንብቡ፡ ይሁዳ ቁ. 9፣ ሉቃስ 9፡28-36፣ 1 ነገስት 17፡8-24፣ ሉቃስ 7፡11-17፣ ማርቆስ 5፡3543፣ ዮሐንስ 11፡1-44።


የሣምንቱ ጥናት መሪ ጥቅስ “ኢየሱስም፦ ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ፤ የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ ሕያው የሆነም የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም፤ ይህን ታምኚያለሽን? አላት።” ዮሐንስ 11፡25-26

ት ንሳኤን በተመለከተ ከብሉይ ኪዳን እስካሁን የተመለከትናቸው ኃሳቦች በአብዛኛው በግል ወደፊት ይሆናሉ ተብለው የሚጠበቁ እምነቶች ወይም በተስፋዎች ላይ የተመሰረቱ ናቸው (ኢዮብ 19፡ 25-27፣ ዕብ. 11፡17-19፣ መዝ. 49፡15፣ መዝ. 71፡20፣ ዳን. 12:1፣2፣13)። ይሁን እንጂ ሰዎች ከሞት የተነሱባቸውን ታሪኮች የሚተርኩ በመንፈስ አነሳሽነት የተጻፉ መዛግብት አለን።

የመጀመሪያው ትንሣኤ የሙሴ ነበር (ይሁዳ 9፣ ሉቃስ 9፡28-36)። በእስራኤል ንጉሣዊ አገዛዝ ጊዜ ደግሞ የሰራፕታዋ የመበለት ልጅ (1ኛ ነገሥት 17፡8-24) እና የሱነማዊቷ ልጅ (2ኛ ነገሥት 4፡18-37) ከሞት ተነስተዋል። ክርስቶስ፣ እዚህ በአካል ሳለ የናይኗን መበለት ልጅ (ሉቃስ 7፡11-17)፣ የኢያኢሮስን ሴት ልጅ (ሉቃስ 8፡40-56) እና አልዓዛርን (ዮሐንስ 11) አስነስቷል። ከሙሴ በቀር እነዚህ ሁሉ ሰዎች እንደ ሟች ሆነው የተነሱ ሲሆን በመጨረሻም እንደገና ሞተዋል። እነዚህ ታሪኮች ሙታን ምንም እንደማያውቁ የሚናገረውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ያረጋግጣሉ (ኢዮብ 3፡11-13፣ መዝ. 115፡17፣ መዝ. 146፡4፣ መክ. 9፡5፣10)። ከእነዚህ ዘገባዎች በአንዱም ሆነ በሌላ በማንኛውም መጽሐፍ ቅዱሳዊ የትንሳኤ ትረካዎች ውስጥ፣ ከሞት በኋላ ስላለው ተሞክሮ የተጠቀሰ ነገር የለም። በዚህ ሳምንት ከክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ በፊት ስለተከናወኑት ትንሣኤዎች በጥልቀት እናሰላስላለን። * ለጥቅምት 19 ሰንበት ለመዘጋጀት የዚህን ሳምንት ትምህርት ያጥኑ።

ጥቅምት 13
Oct 23

የሙሴ ትንሳኤ


ይሁዳ ቁ. 9ን እና ሉቃስ 9፡28-36ን ያንብቡ። በእነዚህ ጥቅሶች ውስጥ ሙሴ በአካል ስለመነሳቱ የሚያስረዱ ምን ማስረጃዎችን እናገኛለን?



አንዳንድ በአሌክሳንድርያ ያሉ የግሪክ ቤተክርስቲያን አባቶች ሙሴ ሲሞት ሁለት ሙሴዎች ታይተዋል፤ አንዱ በመንፈስ ሕያው ነው፤ አንዱም በሥጋ ሞተ፤ አንዱ ሙሴ ከመላእክቱ ጋር ወደ ሰማይ ዐረገ፤ ሌላውም በምድር ተቀበረ(Origen, Homilies on Joshua 2.1; Clement of Alexandria, Stromata 6.15.) ብለው ያስተምራሉ። ይህ በነፍስ መውጣት እና በሥጋ መቀብር መካከል ያለው ልዩነት ነፍስ አትሞትም በሚለው የግሪክ ጽንሰ ሐሳብ ለሚያምኑ ሰዎች ትርጉም ሊሰጥ ይችላል፤ ነገር ግን ኃሳቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም። ይሁዳ 9 ስለ ሙሴ ሥጋ ትንሣኤ የሚሰጠውን መጽሐፍ ቅዱሳዊ ትምህርት ያረጋግጣል፤ ምክንያቱም ክርክሩ “ስለ ሙሴ ሥጋ” እንጂ በሕይወት ይኖራል ተብሎ ስለሚገመት ስለሌላ ነፍስ አልነበረም።

ዘዳግም 34፡5-7 ሙሴ በ120 አመቱ እንደሞተ እና እግዚአብሔርም በሞዓብ ምድር በሸለቆ ውስጥ በተሰወረ ስፍራ እንደቀበረው ይነግረናል። ሙሴ ግን በመቃብር ውስጥ ብዙም አልቆየም። “ክርስቶስ ራሱ ሙሴን ከቀበሩት መላእክት ጋር የተኛውን ቅዱስ ለመጥራት ከሰማይ ወረደ። . . . ክርስቶስ ለመጀመሪያ ጊዜ ለሙታን ሕይወት ሊሰጥ ነበር። ልዑሉና የሚያበሩት መላዕክት ወደ መቃብር ሲቃረቡ ሰይጣን ስለ ልዕልናው ደነገጠ። . . . ክርስቶስ ከሰይጣን ጋር ለመጨቃጨቅ ጎንበስ አላለም። . . . ነገር ግን ሁሉንም ወደ አባቱ በማመላከት ‘ጌታ ይገስጽህ’ አለው (ይሁዳ 9). . .። ትንሣኤው ለዘላለም የተረጋገጠ ሆነ። ሰይጣን ግዛቱን ተነጠቀ፤ ጻድቃን ሙታን እንደገና ሕያው ይሆናሉ።”—ኤለን ጂ ኋይት፣ የኃይማኖት አባቶች እና ነቢያት፣ ገጽ 478-479 የሙሴን ትንሣኤ የሚያሳይ ግልጽ ማስረጃ በመለወጥ ተራራ ላይ ይገኛል።

በዚያም ሙሴ ሞትን ሳያይ ከተነጠቀው ከነቢዩ ኤልያስ ጋር ተገለጠ (2ኛ ነገ 2፡1-11)። ሙሴ እና ኤልያስ ከኢየሱስም ጋር ተነጋግረዋል (ሉቃስ 9፡28-36)። “እነሆም፥ ሁለት ሰዎች እነርሱም ሙሴና ኤልያስ ከእርሱ ጋር ይነጋገሩ ነበር፤ በክብርም ታይተው በኢየሩሳሌም ሊፈጽም ስላለው ስለ መውጣቱ ይናገሩ ነበር።” (ሉቃስ 9:30-31)። የሙሴ መገለጥ ክርስቶስ በኃጢአትና በሞት ላይ እንደሚያሸንፍ ማረጋገጫ ሆኖ በዚህ ቦታ በማያሻማ መልኩ ተገልጧል። በዚያ ለኢየሱስ የተገለጡት ሙሴና ኤልያስ እንጂ “መንፈሳቸው” (ደግሞም ኤልያስ አልሞተም) አልነበረም።

ሙሴ ወደ ምድራዊ ከነዓን እንዲገባ አልተፈቀደለትም (ዘዳ. 34፡ 1-4) ነገር ግን ወደ ሰማያዊት ከነዓን ተወሰደ። ይህ እግዚአብሔር “በእኛም እንደሚሠራው ኃይል ከምንጠይቀው ወይም ከምናስበው ሁሉ በላይ አብልጦ ሊያደርግ እንዲችል” (ኤፌ. 3:20) የሚያስተምረው እንዴት ነው?

ጥቅምት 14
Oct 24

ሁለት የብሉይ ኪዳን ትንሳኤዎች


1 ነገሥት 17፡8-24 እና 2 ነገሥት 4፡18-37 ያንብቡ። በእነዚህ ሁለት ትንሳኤዎች ውስጥ ምን ተመሳሳይነት እና ልዩነት እንመለከታለን?



በዕብራውያን 11 ላይ፣ በእምነት “ሴቶች ሙታናቸውን በትንሣኤ ተቀበሉ” (ዕብ. 11፡35) ተብሎ ተፅፏል። ከላይ በተዘረዘሩት ጥቅሶች ላይ በተገለጹት ሁለት ትንሣኤዎች ውስጥ ያለው ሁኔታ ይህ ነው። የመጀመሪያው (1ኛ ነገሥት 17፡8-24) በእስራኤል በታላቅ ክህደት በተከሰተበት ወቅት የተከሰተ ሲሆን ይህም የሆነው በንጉሥ አክዓብና በአረማዊት ሚስቱ በኤልዛቤል ተጽዕኖ ነበር። በምድሪቱ ላይ ከባድ ድርቅ በነበረበት ወቅት ፣ ከእስራኤል ውጭ ወደምትገኘው ወደ ሰራፕታ ከተማ እንዲሄድ እግዚአብሔር ኤልያስን አዘዘው። እዚያም ለራሷና ለልጇ የመጨረሻውን ምግብ አዘጋጅታ ልትሞት የተዘጋጀችን አንዲት ምስኪን መበለት አገኘ። ነገር ግን በዱቄቱ እና በዘይቱ ተአምር ሕይወታቸው ተረፈ፤ ይህም ድርቁ እስኪያልቅ ድረስ አላለቀም። ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ልጇ ታሞ ሞተ። እናቱ ተስፋ በመቁረጥ ኤልያስን ተማጸነች፤ እርሱም ወደ ጌታ ጮኸ። “እግዚአብሔርም የኤልያስን ጩኸት ሰማ፤ የልጁም ነፍስ ተመለሰችለት፤ እርሱም ዳነ።” (1ኛ ነገ. 17:22)።

ሁለተኛው ትንሣኤ (2ኛ ነገሥት 4፡18-37) የተከናወነው በሱነም፣ ከጊልቦአ ተራራ በስተደቡብ በምትገኝ ትንሽ መንደር ነበር። ኤልሳዕ አንዲት ምስኪን መበለት ብዙ እንስራዎችን በተአምር በዘይት በመሙላት ዕዳዋን እንድትከፍል ረድቷታል (2 ነገሥት 4፡1-7)። ቆየት ብሎም በሱነም ልጅ የሌላት አንዲት ባለትዳር ሴት አገኘ። ነቢዩም ወንድ ልጅ እንደምትወልድ ነገራት፤ እናም እንደተተነበየው ሆነ። ልጁ አደገ እና ጤናማ ነበር፤ ነገር ግን አንድ ቀን ታሞ ሞተ። ሱነማዊቷ ሴት ወደ ቀርሜሎስ ተራራ ሄዳ ልጇን ለማየት ከእሷ ጋር እንዲመጣ ኤልሳዕን ጠየቀችው። ኤልሳዕ ያለማቋረጥ ወደ ጌታ ጸለየ፣ እና በመጨረሻም ሕፃኑ እንደገና ሕያው ሆነ።

እነዚህ ሴቶች የተለያየ አስተዳደግ የነበራቸው ቢሆንም አንድ የሚያድን እምነት ነበራቸው። የሠራፕታዋ መበለት ነቢዩ ኤልያስን በእስራኤል ውስጥ አስተማማኝ ቦታ በሌለበት እጅግ አስቸጋሪ ጊዜ ውስጥ አስተናግዳለች። ሱነማዊቷ ሴትና ባለቤቷ ነቢዩ ኤልሳዕ በአካባቢያቸው ሲያልፍ የሚቆይበት ልዩ ክፍል ሠርተውለታል። ሁለቱ ልጆች ሲሞቱ ታማኝ እናቶቻቸው ለእነዚያ የእግዚአብሔር ነቢያት ይማፀኑ ነበር፤ እናም ልጆቻቸው እንደገና ወደ ህይወት ሲመጡ በማየታቸው ተደሰቱ።

እነዚህ እጅግ ጥሩ ታሪኮች ናቸው፤ ነገር ግን ያልተነገሩ እንደዚህ ያለ ተአምራዊ የሆነ ነገር ያላጋጠማቸው ምን ያህል ኖረው ይሆኑ? በዘመን መጨረሻ ላይ ቃል የተገባው የትንሳኤ ተስፋ በእምነታችን ውስጥ ምን ያህል አስፈላጊ እንደሆነ ይህ አሳዛኝ እውነታ ምን ያስተምረናል?

ጥቅምት 15
Oct 25

የናይን መበለቷ ልጅ


መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ “መልካም እያደረገ ለዲያብሎስም የተገዙትን ሁሉ እየፈወሰ ዞረ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ነበረና፤” (ሐዋርያት 10፥38) ይላል። በእርግጥም፣ ሁሉም ወንጌሎች ኢየሱስ ብዙ ችግረኞችን እንዳገለገለ በሚገልጹ ዘገባዎች የተሞሉ ናቸው፣ ለዚህም ነው በኋላ ላይ ብዙ አይሁዶች ኢየሱስ ተስፋ የተደረገበት መሲሕ መሆኑን ያመኑት። “እርሱ በእነርሱ አልፎ ድውያንን ሁሉ ስለፈወሰ በየትኛውም ቤት የሕመም ልቅሶ የሌለባቸው መንደሮች ነበሩ። ሥራዎቹ በመለኮት ለመቀባቱ ማረጋገጫ በመሆን ፍቅር፣ ምህረትና ርኅራኄ በእያንዳንዱ የህይወቱ እንቅስቃሴ ተገልጾ ይታይ ነበር። ልቡ ለሰው ልጆች በፍቅርና በርህራሄ ይፈስ ነበር።

እርሱ የሰዎችን ፍላጎት ለመድረስ ይችል ዘንድ ሰብዓዊውን ተፈጥሮ ወሰደ። እጅግ ድኾችና እራሳቸውን ዝቅ ያደረጉ እርሱን ቀርቦ ለማናገር ፍርሃት አልነበራቸውም። እንዲያዉም ትናንሽ ብላቴናዎች ሳይቀሩ በእርሱ ተስበው ነበር። —ኤለን ጂ. ኋይት፣ ወደ ክርስቶስ የሚመራ መንገድ፣ ገጽ 11-12 ሉቃስ 7፡11-17 ያንብቡ። በዚህ ትንሳኤ በተከናወኑት ነገሮች እና ትናንት በተመለከትናቸው መካከል ምን ዋና ልዩነት አለ?



ኢየሱስ በገሊላ ባገለገለበት ወቅት በሽተኞችን ፈውሷል፤ አጋንንትንም አስወጥቷል። አንድ ጊዜ እሱና ተከታዮቹ ወደ ናይን በር ሲቃረቡ አስከሬን የያዙ ሰዎች በእነዚያ በሮች እያለፉ ነበር። በተከፈተው የሬሳ ሣጥን ውስጥ የአንድ ልጅ አስከሬን የነበረ ሲሆን አምርራ እያለቀሰች ለነበረችዋ መበለት ብቸኛ ልጇ ነበር። ኢየሱስም ለእናቲቱ አዝኖላት “አታልቅሺ” አላት። ከዚያም ኢየሱስ በሬሳ ሣጥን ውስጥ ወዳለው ወደ ሙት ልጅ ዘወር ብሎ “አንተ ጐበዝ፥ እልሃለሁ፥ ተነሣ።” ብሎ አዘዘው (ሉቃስ 7:13-15)። ልጁም ህያው ሆነ፤ ኢየሱስም ለእናቱ ሰጣት። የኢየሱስ መገኘት ሁኔታውን ሙሉ በሙሉ ለወጠው፤ እናም ተአምሩን የተመለከቱ ብዙ ሰዎች አስገራሚ ነገር መከሰቱን ብቻ ሳይሆን ልዩ የሆነ ሰው (“ታላቅ ነቢይ” ብለው ይጠሩታል) በመካከላቸው እንዳለ አወቁ።

የሠረፕታዋ መበለት (1ኛ ነገሥት 17፡8-24) እና ሱነማዊቷ ሴት (2ኛ ነገሥት 4፡18-37) ከኤልያስ እና ከኤልሳዕ እርዳታ ጠይቀዋል። የናይኗ መበለት ግን ምንም ሳትለምን ተረዳች። ይህ ማለት እርሱን ለእርዳታ ለመጠየቅ የማንችል ወይም ብቁ እንዳልሆንን በሚሰማን ጊዜ እንኳን እግዚአብሔር ያስብልናል ማለት ነው። ኢየሱስ ችግሩን አይቶ ቀረፈው—በአጠቃላይ የኢየሱስ አገልግሎት ውስጥ ይህ መመሳሰል አለ።

እውነተኛው ሃይማኖት በዙሪያችን ወላጅ የሌላቸውን ልጆችና መበለቶችን መንከባከብን ይጨምራል (ያዕቆብ 1፡27)። ምንም እንኳን ግልጽ በሆነ መልኩ እንደ ኢየሱስ ተዓምር ማድረግ ባንችልም በዙሪያችን ያሉ የተቸገሩ ወገኖችን ማገልገል የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 16
Oct 26

የኢያኢሮስ ሴት ልጅ


ከኢየሱስ ሞትና ትንሣኤ በፊት የነበሩት ትንሣኤዎች በየትኛውም ጎሣ ወይም ማኅበረሰብ ብቻ የተገደቡ አልነበሩም። ሙሴ ምናልባት የእግዚአብሔር ሕዝብ ታላቁ መሪ ሊሆን ይችላል (ዘዳ. 34፡10-12)። በአንጻሩ፣ ምስኪኗ የሰራፕታ መበለት እስራኤላዊት አልነበረችም (1 ነገ. 17፡9)። ሱነማዊቷ ሴት በአካባቢዋ ታዋቂ ነበረች (2 ነገሥት 4፡8) ነገር ግን ዕብራዊት አልነበረችም። የናይኗ መበለት አንድ ወንድ ልጅ ብቻ ነበራት፤ ምናልባትም በእርሱ ላይ ጥገኛ ነበረች(ሉቃስ 7፡12)። በአንጻሩ፣ ኢያኢሮስ የምኩራብ አለቃ ነበር፣ ምናልባትም በቅፍርናሆም (ማርቆስ 5፡22)። የነበሩበት ባሕላዊ ዳራ ወይም ማኅበራዊ ደረጃ ምንም ይሁን ምን፣ ሁሉም በእግዚአብሔር ሕይወት ሰጪ ኃይል ተባርከዋል።

ማርቆስ 5:21-24፣ 35-43ን ያንብቡ። ክርስቶስ “ሕፃኑ ተኝቷል እንጂ አልሞተም’ ብሎ ከተናገረው ሐሳብ ስለ ሞት ምን እንማራለን? (ማር. 5:39)።



የኢያኢሮስ የ12 ዓመት ሴት ልጅ ቤት ውስጥ ለሞት በሚያደርስ ህመም ታማ ነበር። ስለዚህ ወደ ኢየሱስ ሄዶ ወደ ቤቱ እንዲመጣና የፈውስ እጁን በእሷ ላይ እንዲጭን ለመነው። ነገር ግን እዚያ ከመድረሳቸው በፊት አንድ ሰው አሳዛኝ ዜና አመጣ። “ልጅህ ሞታለች። ስለ ምን መምህሩን አሁን ታደክመዋለህ?” (ማርቆስ 5:35) አለው። ከዚያም ኢየሱስ ለሐዘንተኛው አባት፣ “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ” አለው(ማርቆስ 5፡36)። በእርግጥም አባትየው ማድረግ የሚችለው በእግዚአብሔር ጣልቃ ገብነት ሙሉ በሙሉ መተማመን ነበር።

ኢየሱስ ወደ ቤቱ በደረሰ ጊዜ በዚያ ለተሰበሰቡት ሰዎች እንዲህ አላቸው:ስለ ምን ትንጫጫላችሁ ታለቅሳላችሁም? ብላቴናይቱ ተኝታለች እንጂ አልሞተችም አላቸው።” (ማርቆስ 5:39)። (1)መሞቷን ስለሚያውቁ እና (2) የቃሉን ትርጉም ስላልተገነዘቡ ሳቁበት። ‘ሞት” በሚለው ፈንታ ክርስቶስ “እንቅልፍ” የሚለውን አጽናኝ ዘይቤ መጠቀሙ ይህን ተሞክሮ የሚያመለክትበት መልካም አገላለጽ ነው(ማቴ. 9፡24፣ ሉቃ. 8፡52 ዮሐንስ 11፡11-15)። ሞት እንቅልፍ ነው፣ ነገር ግን እርሱ ብቻውን የመቃብር መክፈቻ ስላለው ሕይወት ሰጪው እርሱ ብቻ ሊቀሰቅሰው የሚችልበት ጥልቅ እንቅልፍ ነው (ራዕ. 1:18፣ ዮሐንስ 3:16፣ ሮሜ. 6፡23)”— The SDA Bible Commentary, vol. 5, p. 609.

ይህች ልጅ ከሞት ከተነሳች በኋላ፣ ተዓምሩን ያዩት “በጣም ተገረሙ” (ማርቆስ 5፡42)። አሁን ሞት የመጨረሻ፣ ፍፁም እና የማይቀለበስ የሚመስል ነው። በገዛ ዓይናቸው ይህን የመሰለ ነገር ማየታቸው በእርግጥም አስደናቂና ሕይወትን የሚለውጥ ተሞክሮ መሆን አለበት። “እመን ብቻ እንጂ አትፍራ’” (ማርቆስ 5:36) የሚሉት የኢየሱስ ቃላት ዛሬም ለእኛ ትርጉም ያላቸው ናቸው። ማመናችንን መቀጠል አስፈላጊ በሆነባቸው አስፈሪ ሁኔታዎች ውስጥ እንኳን ይህን ማድረግ የምንችለው እንዴት ነው?

ጥቅምት 17
Oct 27

አልአዛር


ዮሐንስ 11፡1-44ን ያንብቡ። በአልአዛር መታመምና ሞት(ዮሐ. 11፡4) ኢየሱስ የከበረው ከምን አንፃር ነው?



እዚህ ላይም ኢየሱስ ስለ ሞት ሲናገር እንቅልፍ የሚለውን ቃል ይጠቀማል። “ወዳጃችን አልዓዛር ተኝቶአል፤ ነገር ግን ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” (ዮሐንስ 11፡11)። አንዳንዶች ስለ ቀጥተኛ እንቅልፍ የተናገረ ሲመስላቸው (ዮሐንስ 11፡11-13)፣ ኢየሱስ “አልዓዛር ሞቷል” (ዮሐንስ 11፡12-14) በማለት በግልፅ ተናግሯል። ኢየሱስ ቢታንያ በደረሰ ጊዜ አልዓዛር ከሞተ አራት ቀን ሆኖት ነበር። አስከሬኑ በስብሶ ነበር (ዮሐ. 11:17፣ 39)። አንድ አካል መበስበስ ጀምሮ በከፋ ሁኔታ ሲሸት ምንም ጥያቄ የለም:- ሰውየው ሞቷል። በዚህ ዐውደ-ጽሑፍ፣ ኢየሱስ ለማርታ “‘ወንድምሽ ከሞት ይነሣል’” (ዮሐንስ 11፡23) ብሎ በነገራት ጊዜ በመጨረሻው ትንሣኤ ላይ ያላትን እምነት አረጋግጣለች። ኢየሱስ ግን “ትንሣኤና ሕይወት እኔ ነኝ። የሚያምንብኝ ቢሞት እንኳ ሕያው ይሆናል፤ የሚያምንብኝም ሁሉ ለዘላለም አይሞትም። ይህን ታምኚያለሽን?” (ዮሐንስ 11፡23-26) ብሎ አወጀ። ኢየሱስም አክሎ፡ “ብታምኚስ የእግዚአብሔርን ክብር ታያለሽ’ (ዮሐንስ 11፡40)። ማርታም አመነች የእግዚአብሔርንም ክብር በወንድሟ ትንሣኤ አየች።

መጽሐፍ ቅዱስ በእግዚአብሔር ቃል ሕይወት እንደ ተፈጠረ ይናገራል (መዝ. 33: 6) እናም ልክ እንደ አልዓዛር በቃሉ ሕይወት እንደገና ሊፈጠር ይችላል።. ከትንሽ ጸሎት በኋላ ኢየሱስ እንዲህ ሲል አዘዘ፡- “አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና” (ዮሐ 11፡43)። በዚያን ጊዜ እነዚህ ሰዎች የእግዚአብሔርን ሕይወት ሰጪ ኃይል፣ በቃሉ ዓለማችንን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣውን ያ ኃይል፣ እና በዘመኑ መጨረሻ ሙታንን በትንሣኤ የሚጠራውን ኃይል አዩ። አልዓዛርን በማስነሳት፣ ኢየሱስ ሞትን ድል የማድረግ ኃይል እንዳለው አረጋግጧል። እንደ እኛ ላሉ ሟች ፍጥረታት ከዚህ በላይ ምን የእግዚአብሔር ክብር መገለጫ ሊኖር ይችላል?

ዮሐንስ 11:25-26ን ያንብቡ። ኢየሱስ በአንድ መስመር አማኞች እንደሚሞቱ በሚቀጥለው ደግሞ አማኞች ፈጽሞ እንደማይሞቱ ተናግሯል። ኢየሱስ እዚህ ላይ የሚያስተምረን ምንድን ነው? የክርስቶስን ቃላት ለመረዳት ሞት ምንም የማናውቅበት እንቅልፍ መሆኑን መረዳት በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው? ሟች እንደመሆናችን ቃሉ ብዙ ተስፋን የሚሰጠን ለምንድነው?

ጥቅምት 18
Oct 28


ተጨማሪ ሀሳብ


የኃይማኖት አባቶችና ነብያት ከሚለው መጽሐፍ “የሙሴ ትንሳኤ” የሚል ርዕስ ያለውን ምዕራፍ፣ እንዲሁም ነብያትና ነገስታት ከሚለው መጽሐፍ “የተግሳፅ ድምፅ” እና “የሠላም ነቢይ” የሚል ርዕስ ያላቸውን ምዕራፎች እንዲሁም የዘመናት ምኞት ከሚለው መጽሐፍ “የመቶ አለቃው”፣ “በእምነት መንካት” እና አልአዛር ና ውጣ የሚል ርዕስ ያላቸውን ምዕራፎች ያንብቡ። “የክርስቶስ ህይወትነት ከጥንት ከመሠረቱ ከራሱ የመነጨ እንጂ በብድር ወይም በውሰት ከሌላ የተገኘ አይደለም። ‘ልጁ ያለው ሕይወት አለው።’ 1ኛ ዮሐንስ 5፡12 የክርስቶስ አምላክነት ለምዕመናን የዘላለም ሕይወት ማግኛ ዋስትና ነው። “በእኔ የሚያምን ቢሞት እንኳ በሕይወት ይኖራል፤ በሕይወት የሚኖርና በእኔም የሚያምን ሁሉ ከቶ አይሞትም ይህን ታምኛለሽን?’ አለ ኢየሱስ። ከዚህ ላይ ኢየሱስ ዳግመኛ የሚመጣበትን ጊዜ ያስታውሳል(ዮሐ. 11፡ 25-26)።

ያን ጊዜ ጻድቃን ሙታን የማይበሰብሱ ሆነው ይነሣሉ፤ በሕይወት ያሉ ጻድቃንም ሞትን ሳያዩ ወደ ሰማይ ይነጠቃሉ። አልዓዛርን ከሙታን በማስነሳት ክርስቶስ ሊያደርገው ያለው ተአምር የጻድቃን ሙታን ሁሉ ትንሣኤን ያመለክታል። ኢየሱስ በቃሉም ሆነ በተግባሩ የትንሣኤው ስልጣን ያለው መሆኑን አወጀ። ብዙም ሳይቆይ ራሱ በመስቀል ላይ ሊሞት የነበረው፣ የመቃብርን ድልነሺነትና የሞትን ቁልፎች ይዞ፣ የዘላለም ሕይወት የመስጠት መብቱንና ኃይሉን አረጋገጠ።” ኤለን ጂ. ኋይት፣ የዘመናት ምኞት፣ ገጽ. 549


የመወያያ ጥያቄዎች



1.በኤልያስና በኤልሳዕ ትንቢታዊ አገልግሎት እንዲሁም በክርስቶስ ምድራዊ አገልግሎት ወቅት ብዙ ሰዎች ሞተዋል። ከሞት የተነሱት ጥቂቶች ብቻ ናቸው(ሉቃስ 4: 24–27):: መሞት ምን ማለት እንደሆነ ካለን መረዳት በመነሳት ቀደም ብለው ቢነሱ ወይም በዳግም ምጽዓት ትንሣኤ ተካፋይ ቢሆኑ ምን ያህል ለውጥ እንደሚያመጣ በመግለጽ ስለ ሙታን ተሞክሮ ያሰላስሉ።

2.ለዘመናት የኖሩ ብዙ ጸሐፍት ሁልጊዜም በሞት ስለሚያበቃው ስለ ሕይወት ከንቱነት ጽፈዋል። ከሌሎች ሕያዋን ፍጥረታት ጋር - ከዶሮዎች፣ ከእርግቦች፣ ከሰጎኖች ወዘተ ጋር ሁላችንም እንሞታለን። ነገር ግን የእኛ የሰዎች ችግር ከእንስሳት ይልቅ የከፋ ነው፤ ምክንያቱም እንደምንሞት ስለምናውቅ ነው (መክ. 9:5ን ይመልከቱ)። ዶሮዎች፣ እርግቦች እና ሰጎኖች ይህን አያውቁም። ታዲያ የትንሣኤ ተስፋ ለእኛ በጣም አስፈላጊ የሆነው ለምንድን ነው?

3.ነፍስ አትሞትም እና ሙታን በተለይም ጻድቃን ሙታን ከሞቱ በኋላ በሰማይ እንደሚኖሩ የምታስብ ከሆነ በዘመኑ መጨረሻ ትንሣኤ ለምን አስፈለገ? 4.አንድ ሰው ደውሎ “ሳሊ አለች?” ብሎ ከጠየቀ “አዎ፣ ግን ተኝታለች።” ብለው ይመልሱ ይሆናል። ሆኖም አንድ ሰው ደውሎ “ሳሊ አለች” ብሎ ከጠየቀ “አዎ፣ ግን ሞታለች” ብለን አንመልስም። ለምን? ይህ ስለ ሞት ተፈጥሮ ምን ያስተምረናል?




Shalom Teleconference Ministries Inc -- Translated by Ethiopian SDA union SSL